“የተቸገሩትን በመርዳት ብቻ እዝናናለሁ”

Wednesday, 02 May 2018 12:36

የታክሲ ሾፌር ማርቆስ ዘሪሁን

በይርጋ አበበ

ትውልድ እና እድገቱ አዲስ አበባ ልዩ ቦታው 22 ውሃ ልማት ወይም በተለምዶ ቺቺኒያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። ከልጅነት እስከ ወጣትነት ያለውን ዘመኑን በበርካታ ውጣ ውረድ ያሳለፈው ወጣት በአሁኑ ሰዓት የአንዲት ሴት ልጅ አባት ሲሆን በኑሮ ሸክም መክበድ የተነሳ ከባለቤቱ ጋር መለያየታቸውን ይገልጻል። ከግለሰብ ቤት እስከ ግል ድርጅት፣ ከጫማ መጥረግ አንስቶ ሁሉንም የስራ አይነቶች በመስራት ኑሮውን መግፋ ችሏል። የትምህርት ደረጃውን በተመለከተ ሲናገር ‹‹መንጃ ፈቃዴ ነው የኔ ዲግሪ›› የሚለው የዛሬ እንግዳችን ኑሮውን የሚገፋው በሹፍርና ሙያ ሲሆን የግሉን ታክሲ (በተለምዶ ላዳ የሚባሉት አይነት) እየነዳ በሚያገኘው ገቢ ነው።

ይህ ወጣት በራሱ ተነሳሽነት ነፍሰ ጡር ሴቶችን ወደ ህክምና ተቋማት ያለምንም ክፍያ (ድምቡሎ ሳይከፈለው) በማድረስ ህክምና እንዲያገኙ ያደርጋል። ከነፍሰ ጡሮች በተጨማሪም አቅመ ደካማ የሆኑትን ባልቴቶችና ሽማሌዎች ሳይቀር በነጻ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በዚህ ዘመን የመኪና ማሰሪያ እቃ (ስፔር ፓርት) ዋጋው ጣራ በነካበት፣ ነዳጅ እንደ ሜርኩሪ ቅንጦት በመሰለበት እና የትራንስፖርት አገልግሎት ክፍያውም ባደገበት ዘመን ይህ ወጣት ግን በግል ታክሲው ላይ ነጻ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። እንደዚህ አይነት መልካም አድራጊ ኢትዮጵያዊያንን መደገፍ ነገ ሌሎች የእሱን አርዓያ የሚከተሉ ዜጎችን መሳብ ይሆናል ብለን ስላሰብን በመዝናኛ አምዳችን የወጣቱን ልምድ እናካፍላችኋለን።

 

 

የሃሳቡ ጅማሮ

በመጽሃፍ ቅዱስም ሆነ በቅዱስ ቁርዓን ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው አስተምህሮቶች ውስጥ ቀዳሚው በጎነትን ማስፋት የሚለው ነው። እየሱስ ክርስቶስም ሆነ ነብዩ መሀመድ ተከታዮቻቸው ለሰው ዘር በሙሉ በጎ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ አስተላፈዋል። ነገር ግን በጎነትን ወይም መልካምነትን ሲያደርጉ በምትኩ ውለታ እንዳይጠብቁ ተጨማሪ መመሪያ ሰጥተዋል።

ይህ ከላይ የተቀመጠው መንፈሳዊ ይዘት ያለው የመልካምነት ስራ መመሪያ እንጂ የህሊና እዳ አይደለም። የታክሲ ሾፌሩ ማርቆስ ዘሪሁን ደግሞ ከመንፈሳዊም ሆነ ከመንግስታዊ ህግ ድጋፍ ሳይሻ በህሊናው ትዕዛዝ በጎነትን ያደርጋል። የመጀመሪያ የበጎነት ተግባሩን እንዴት እንደጀመረ ሲናገርም ‹‹ልጅ እያለን ሻላ መናፈሻ ሰርግ ሲኖር የእኛ ሰፈር ልጆች ተሰብስበን እየሄድን እንበላ ነበር። እንደተለመደው አንድ እሁድ ቀን ላይ ወደ ሰርጉ አዳራሽ ስንሄድ እንዲት ሴት እርዳታ ስትፈልግ አየኋት። ልጅ ስለነበርኩ ምጥ ይሁን ሌላ በሽታ አለወኩም ነበር። በዚህ ጊዜ መኪና ያላቸውን ሰዎች ስጠይቃቸው ሁሉም ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም። ታክሲ ደግሞ የለም ነበር ስለዚህ የነበረን ምርጫ ሴትዮዋን በቻልነው መንገድ ብቻ መርዳት ነበር። በዚህ ጊዜ ሴትዮዋ መንገድ ላይ ስትወልድ እረዳኋት›› ሲል ይናገራል።

ከዚያ ጊዜ በኋላም ቢሆን በቅጥር ስራው ውስጥ ሆኖም ሆነ የራሱን ታክሲ ከገዛ በኋላ ይህን ተግባሩን እንዳላቋረጠ እንዲያውም አጠናክሮ እንደገፋበት የሚናገረው ወጣቱ ማርቆስ፤ መኪናው ላይ ‹‹ለነፍሰ ጡር እና ለአቅመ ደካሞች ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት እንሰጣለን›› ብሎ ለጥፏል። ‹‹መኪናህ ነዳጅ ይፈልጋል፣ አንዲት ሴት ልጅም አለችህ፤ ስለዚህ በታክሲህ መስራት እና ገቢ ማምጣት ስላለብህ በክፍያ የሚሳፈርን ሰው ይዘህ ስትንቀሳቀስ የአንተን እርዳታ የሚፈልግ ሰው በተለይ ነፍሰ ጡር ብታገኝ ምን ታደርጋለህ?›› የሚል ጥያቄ አቅርበንለት ነበር። ‹‹ብዙ ጊዜ አይሁን እንጂ የተወሰኑ ጊዜያት እንደዚህ አይነት ነገር አጋጥሞኝ ያውቃል። እኔም ያደረኩት ሰውየውን አስፈቅጄ ነፍሰ ጡሯን ወደ ህክምና ተቋም አድርሼ ነው ሰውየውን ወደፈለገበት ቦታ ያደረስኩት። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ለሰው ተባባሪ ለተቸገረ አዛኝ ስለሆኑ ሳይከፋቸው ይተባበሩኛል›› ብሏል የእሱ መተባባር ሳይሆን የሰውየው ተባባሪነት እየታየው።

 

 

የመልካምነት ተግባር እና ማርቆስ

በዚህ ዘመን ነዳጅ እና የተሸከርካሪ ግብኣቶች ውድ መሆናቸውን ተከትሎ የትራንስፖርት ዋጋ እየናረ ሄዷል። በተለይ የኮንትራት ታክሲ ዋጋቸው ለታችኛው የህብረተሰብ ክፍል የማይቀመስ ሲሆን ሰውም ደፍሮ አገልግሎቱን ለማግኘት ጥያቄ አያቀርብም። ወጣቱ ማርቆስ ግን በዕድሜ የገፉ ሰዎችን እና ነፍሰ ጡር ሴቶችን በነጻ ትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጥ በኑሮው ላይ ያደረሰበት አሉታዊ ጎን እንዳለ ጠይቀነው ነበር። ‹‹እንደእውነቱ ከሆነ የእኔ ታክሲ ‹‹ኤ 2›› የምትባል ስትሆን የነዳጅ ፍጆታዋም ከፍተኛ ነው። ግን ደግሞ ይገርምሃል በነጻ አገልግሎት ስሰጥ በኑሮዬ ላይ ያደረሰብኝ መጥፎ ጎን የለም። ለምሳሌ ሰው እየጠበኩ ወረፋ ላይ ከምቆይ ሰዎቹን በነጻ አድርሼ ስመለስ በክፍያ የሚሳፈር ሰው አገኛለሁ። ስለዚህ ከልብ በመነጨ መልካምነት ስለምሰራው ኑሮዬ ላይ ችግር አልገጠመኝም›› ሲል ይናገራል።

ነፍሰ ጡሮችን በነጻ አገልግሎት ከሰጠህ በኋላ ሲወልዱ ቤተሰባዊ ወዳጅነት የመፍጠር ነገር ለምሳሌ በክርስትና፣ ልደት እና የተለያዩ ማህበራዊ ግንኙነቶች ላይ እንድትታደም ጥሪ ያቀረቡልህ አሉ? የሚል ጥያቄ አቅርበንለት ነበር። ብዙ ሰዎች ከታክሲው ላይ ከተለጠፈው ጽሁፍ ጋር ፎቶ እንደሚነሱ እና አድናቆታቸውን እንደሚገልጹለት የተናገረው የታክሲ ሾፌር ማርቆስ ዘሪሁን፤ ‹‹ያልከውን አይነት ቤተሰባዊ ቅርርብ እስካሁን አልገጠመኝም። እኔም ስራውን የምሰራው ለነገ ግንኙነት ይጠቅሙኛል ብዬ ሳይሆን ለህሊናዬ ብዬ ስለሆነ ሲቸግራቸው ሳይሆን በመልካም ቀን እንገናኛለን ብዬ አስቤ አላውቅም። ስልኬንም ስለማይጠይቁኝ ሰጥቻቸው አላውቅም›› ብሏል። ነገር ግን አንዲት ሴት ብቻ ለልጇ ክርስትና እንደጠራቸው የሚስታውሰው ማርቆስ፤ የሴቷን ማንነት ሲገልጽም ‹‹የወንድሜ ሚስት ናት›› ብሏል።

በቀን ቢያንስ ለአምስት ሰዎች ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጠው ወጣት ለመልካምነቱ ያገኘው ምላሽ አለመኖሩ አግራሞት ይፈጥርበት ይሆን? ማርቆስ ይመልሳል ‹‹በፍጹም አይገርመኝም። ትርፍና ኪሳራህን አስበህ ለሰው መልካም ነገር ማድረግ የለብህም›› ይላል።

መልካም ስራ መስራት እና በጎነት ማድረግን እንደጽድቅ፣ እንደስራ ወይስ እንደመዝናኛህ ነው የምታየው? ብለን ስንጠይቀው፤ ‹‹መልካም ማድረግ በራሱ መልካም ነው ብዬ ነው የማየው። እኔ ብቻ ሳልሆን ሁሉም ሰው መልካም ቢያደርግ ነው የምመኘው። ይህ ሃሳቤ ደግሞ አሁን አሁን ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል አንዳንድ ወዳጆቼ ሃሳብህን እንጋራለን እያሉኝ ነው›› ይላል። የታክሲ ሾፌሩ ማርቆስ ከትራስፖርት አገልግሎት በተጨማሪ በየሰፈሩ ያሉ ጫማ አሳማሪዎችን (ሊስት) ሲመክር እንደሚውል ገልጾ፤ በተለይ ለምሳ ሲሄዱ እቃቸውን ከመጠበቅ አልፎ ደንበኛ ሲመጣ ጫማ ጠርጎ ገንዘቡን ለሊስትሮዎቹ እንደሚሰጣቸው ተናግሯል።

 

 

በጎነት በአርቲስቶች እና በመንግስት ብቻ ለምን?

ብዙ ጊዜ ለተቸገሩ ሰዎች በችግራው ለመድረስ ሲታሰብ የታዋቂ ሰዎች እና የመንግስት ድጋፍ እንዲታከልበት ይፈለጋል። የታክሲ ሾፌሩ ማርቆስ ዘሪሁን ግን በዚህ አይስማማም። መልካምነት የሚጀምረው ከራስ ነው የሚል እምነት አለው። ለመሆኑ መንግስት በአገሪቱ መልካምነት እንዲሰፍን መልካም ለሚያደርጉ ሰዎች ምን ማድረግ አለበት? ተብሎ ሲጠየቅ ‹‹መጀመሪያ መንግስት ራሱ መልካም ይሁን›› የሚል አጭር መልስ ሰጥቷል።

‹‹መልካም ስራ የሚሰሩ ሰዎች እንዲበረቱና በመልካም ስራቸው ላቅ ያለ ስራ እንዲሰሩ ባለሃብቶች ምን ማድረግ አለባቸው?›› ብለን ጠይቀነው ነበር። ‹‹እኔ በዚህ ኑሮዬ የማደርገውን እነሱ ደግሞ በራሳቸው መንገድ በራሳቸው በኩል መልካም የሚሉትን ስራ ይስሩ። ይህን ካደረጉ በራሱ ይበቃል እንጂ መልካም ለሚያደርጉ ሰዎች ድጋፍ ያድርጉ ብዬ አልመክርም። ምክንያቱም መልካም አደርጋለሁ የሚል ሰው ከሰው ምንም ነገር መጠበቅ የለበትምና›› ብሏል።

‹‹አንተ ምንም ታዋቂ ሳትሆን እና ገንዘብም ሳይኖርህ በቻልከው ልክ ሰዎችን እየረዳህ ነው። ታዋቂ ሰዎች በተለይም በመዝናኛው ዘርፍ ላይ ያሉ ሰዎች ይህን ሲያዩ ምን ሊሉ ይገባል ትላለህ?›› የሚል ጥያቄ ስናቀርብለት የሰጠው ምላሽ ደግሞ የሚከተለው ነው። ‹‹እኔ የት ሄጄ ነው ብለው ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው›› ሲል በአጭሩ መልሷል።

በጎነትን ወይም መልካምነትን ለማድረግ የማንንም ድጋፍ እና የማንም ጉትጎታ ያላስፈለገው ወጣት ‹‹ብዙ ሰው የታክሲ ሾፌሮችን የሚያይበት እይታ እንዲስተካከል እፈልጋለሁ›› የሚል እምነት አለው። እኛም ለወጣቱ መልካሙን ሁሉ እየተመኘን በዚህ እንሰናበታለን።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
8155 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 882 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us