የመንግሥት ትኩረት ወረቀት ላይ ብቻ በሆነበት ዘርፍ በግላቸው ስኬታማ የሆኑ ታዳጊዎች

Wednesday, 09 May 2018 13:15

                                    

በይርጋ አበበ

የኢትዮጵያ መንግስት የሳይንሱን ዘርፍ በተለይም የቴክኖሎጂውን መስክ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው ከገለጸ አስርት (ከአስር ዓመት በላይ) አለፈው። ለዚህ እቅዱ ስኬታማ ሆኖ መገኘት ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ውጤት 70 በመቶ ለተፈጥሮ ሳይንስ 30 በመቶ በማህበራዊ ሳይንስ መስኮች እንዲማሩ የሚያስገድድ መመሪያ ካወጣ ቆይቷል። ከዚህ ባለፈም የቴክኖሎጂ ምርምር ኢንስቲትዩትም እስከመገንባት የደረሰ ሲሆን በአገሪቱ የጠፈር ሳይንስ (ሳተላይት) በመገንባትም አገሬውን ከቴክኖሎጂ ጋር ለማቀራረብ እየሰራ መሆኑን ከገለጸ ሰንበትበት ብሏል።

ዛሬ በዚህ የመዝናኛ አምድ ዝግጅታችን ልንመለከት የወደድነው መንግስት ለሳይንስና ቴክኖሎጂ የሰጠውን ትኩረት መዳሰስ ሳይሆን በቅርቡ በአሜሪካን አገር በተካሄደ የሮቦቲክ ኦሎምፒያድ ውድድር ላይ በራሳቸው ጥረት (በተለይ የገንዘብ ወጪውን በመሸፈን) አገራቸውን ወክለው ተወዳድረው በጥሩ ውጤት ስለተመለሱት ታዳጊዎች ይሆናል። የቡድናቸውን ስም ‹‹አድዋ›› ብለው የሰየሙት ታዳጊዎቹ ‹‹አይከን ኢትዮጵያ›› የተባለ የሮቦቲክ ቴክኖሎጂ ድርጅት ያዘጋጀውን ውድድር በራሳቸው ወጪ ተወዳድረው አገራቸውን ወክለው ወደ አሜሪካ በማቅናት ከ568 ተወዳዳሪዎች 23 ብቻ ቀድመዋቸው 24ኛ ደረጃን ይዘው የተመለሱ ሲሆን፤ ለጉዞው የሚያስፈልገውን ወጪ ሙሉ በሙሉ (እስከ 162 ሺህ ብር) የሸፈኑት ወላጆቻቸው ናቸው። በዚህ ጉዳይ ላይ ከተወዳዳሪዎች እና ከወላጆቻቸው ጋር አጠር ያለ ቆይታ ያደረግን ሲሆን የእነሱን አስተያየት ለአንባቢያን በሚመች መልኩ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

የአድዋ ድል በአሜሪካ

የ14 ዓመት ታዳጊው ኪሩቤል ጥበበ ደሊበራንስ በሚባል ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን ወደ አሜሪካ አቅንቶ ከተወዳደሩት ታዳጊዎች መካከል አንዱ ነው። ታዳጊው ልጅ ውድድሩን አስመልክቶ ከሰንደቅ ጋዜጣ ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ “ውድድሩ ፈታኝ እና አዝናኝ ነበር” ያለ ሲሆን አዝናኝና ፈታኝ የሆነበትን ምክንያት ሲያስቀምጥም ‹‹አዝናኝ የምለው የእኛ ቡድን የተወዳደረው በቡድን ስራ ሲሆን የቡድን ስራችንም ውጤት አምጥቶልናል። በቡድን መስራት ምን ያህል ውጤታማ እንደሚያደርግ ያየሁበት ነው›› በማለት ነበር የገለጸው።

ሆኖም በውድድሩ የነበረውን ፈተና በተመለከተ ሲናገር እንደ አገር እንጂ እንደ ልጆቹ አቅም አልነበረም ከባድነቱ። በታዳጊው ምልከታ የታዘበው ከእነሱ ጋር የተወዳደሩት እኩዮቻቸው በአስተሳሰብ ከእኛዎቹ ባይበልጡም በቁሳዊ ሀብት (ማቴሪያል) ግን ሊቀራረቡ አለመቻላቸው በኢትጵያዊያ ታዳጊዎች ላይ ውድድሩን ሊያከብድባቸው እንደቻለ ነበር የገለጸው። ኪሩቤል ሲናገር ‹‹እነሱ በማሽን ሲቆርጡ እኛ በመጋዝ እየቆረጥን ነው መወዳደሪያዎቻችንን እየሰራን ለዚህ የበቃነው። ነገር ግን በውድድሩ የታዘብኩት እኛ ኢትዮጵያዊያን ከማንም የማያንስ ብቃት እንዳለን ነው›› ብሏል።

የቡድናቸው ስም አድዋ የተባለበትን ምክንያት እንዲያብራራልን በጠየቅነው መሰረት ሲመልስም “የእኛ አባቶችና እናቶች ወራሪውን የጣሊያን ጦር ድል ያደረጉት በውስጣቸው ባለው ጀግንነት እና አልደፈር ባይነት እንጂ በታጠቁት የጦር መሳሪያ ብዛት እና ዘመናዊነት አልነበረም። እኛም ወደ አሜሪካ ሄደን ስንወዳደር ባለን ችሎታ እንጂ ከተፎካካሪዎቻችን ጋር ተቀራራቢ የመወዳደሪያ መሳሪያ ስላለን አይደለም። በዚህ የተነሳም የአድዋውን የጦር ሜዳ ድል በአሜሪካ የቴክኖሎጂ ውድድር እንደግመዋለን ብለን ነው የተጓዝነው። እንዳሰብነውም ተሳክቶልን ተመልሰናል” በማለት ተናግሯል። በወድድሩ 568 ቡድኖች የተሳተፉ ሲሆን ከአፍሪካ የተወከለው ብቸኛ ቡድን የኢትዮጵያው “አድዋ” ብቻ ነበር። ከሩቅ ምስራቅ፣ አውሮፓ እና አሜሪካ የተወከሉ ተወዳዳሪዎች የሰለጠኑት እጅግ ዘመናዊ በሆነ የቴክኖሎጂ ውጤት ሲሆን የእኛዎቹ ተወዳዳሪዎች ደግሞ ከተፎካካሪዎቻቸው ጋር ሲነጻጸር ኋላ ቀር የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ነው ማለት ይቻላል።

ከፕሮፓጋንዳ ያላለፈው የመንግስት ቃል

መንግስት የቴክኖሎጂውን ዘርፍ ለማሳደግ ጥረት አደርጋለሁ ብሎ ከተናገረ ዓመታት ቢያልፉም እስካሁን ግን እዚህ ግባ የሚባል ድጋፍ አለማድረጉን የሚናገሩ አልጠፉም። እንዲያውም ቴክኖሎጂው እንዲዳብር መንግስት ድጋፍ ማድረግ ሲገባው ምንም አይነት ድጋፍ አላደረገም ሲሉ በሙያው ያሉ ምሁራን፣ የተወዳዳሪዎቹ ወላጆች እና ታዳጊ ተወዳዳሪዎች ሳይቀሩ ይናገራሉ። ከመንግስት ምን አይነት ድጋፍ ጠብቃችሁ ስላጣችሁ ነው ድጋፍ አላደረገልንም የምትሉ? ስንል ጥያቄ ያቀረብንላቸው ወላጆች ነበሩ። ወይዘሮ ሰላማዊት ስሜ ‹‹ሁሉንም ልጆች ተጠቃሚ የሚያደርጉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በገበያ ላይ ለማግኘት ከባድ ነው። ለምሳሌ እኔ ኑሮዬ ትንሽ የተሻለ ስለሆነ የግል ፍላጎቴን ገትቼም ቢሆን ልጄ ይጠቅመኛል የሚለውን እቃ እንድገዛለት ሲጠይቀኝ ልገዛለት እችላለሁ። ነገር ግን በቴክኖሎጂ እውቀትና ፍላጎት ያላቸው የደህና ቤተሰብ ልጆች ብቻ አይደሉም። ስለዚህ ዝቅተኛ ኑሮ የሚኖሩ ወላጆች ሊገዟቸው የሚችሉ እና በገበያውም እንደልብ የሚገኙ መሳሪያዎች እንዲኖሩ መንግስት ምንም ድጋፍ አላደረገም። ከቀረጥ ነጻ ወይም በአነስተኛ ቀረጥ ወደ አገር ቤት መሳሪያዎቹ እንዲገቡ ቢፈቅድ የነገዋን ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ወደፊት የሚያራምዱ ልጆች ይበዙልን ነበር›› ብለዋል።

ወይዘሮ አትክልት የተባሉ ወላጅ በበኩላቸው “ልጆቻችን ወደ አሜሪካ የሄዱት አገራቸውን ወክለው ነው። አትሌቶቻችን አገራቸውን ወክለው ተወዳድረው ሲያሸንፉ በመንግስት ባለስልጣናት ደማቅ አቀባበል ይደረግላቸዋል። ሌላው ድጋፍ ይቅር፤ ነገር ግን የእኛ ልጆች ይህን ውጤት ይዘው ሲመጡ ‹እንኳን ደህና መጣችሁ” ብሎ ለመቀበል ከሚመለከተው የመንግስት ተቋም የመጣ ሰው የለም። 15 ቀናትን በፈጀው የአሜሪካ ቆይታቸው ልጆቻችን ያወጡት ወጪ ከፍተኛ ነው። ይህን ወጪ ለመሸፈን ሳይሆን ለመጋራት የኢትዮጵያን መንግስት ደጋግመን ጠይቀን ነበር። ቢያንስ የአውሮፕላን ቲኬት እንኳን እንዲቀንስልን ጠይቀነው የሰጠን ምላሽ ያሳዝናል። ‹ልጆቻችሁ በሚሄዱበት ሰዓት በረራ ስለሌለኝ ቻርተርድ ገዝታችሁ ሂዱ› የሚል ነበር። ይህ ራሱ የሚነግርህ እኛን ብቻ ሳይሆን ዘርፉን ለመደገፍ መንግስት ቆራጥ ውሳኔ ላይ አለመሆኑን የማያሳይ ነው›› ብለዋል።

በአሜሪካ በነበረው የሮቦቲክ ኦሎምፒያድ ውድድር ከ162 ሺህ ብር በላይ እያንዳንዱ ወላጅ ወጪ አድርገው ልጆቻቸውን እንደላኩ የነገሩን ወይዘሮ ሰላማዊት መንግስት ወጪውን ቢያግዛቸው ኖሮ እነሱም አቅም የሌላቸውን ልጆች ለማገዝ ይነሱ እንደነበረ ተናግረዋል።

ለድሆቹ ማን ይድረስላቸው?

ታዳጊ ኪሩቤል እና 13 ጓደኞቹ ወደ አሜሪካ ተጉዘው በሮቦቲክ ኦሎምፒያድ የተወዳደሩት ወላጆቻቸው ባላቸው ጠንካራ የገቢ ምንጭ ተደጉመው ነው። ወደ ውድድሩ ቦታ ከማቅናታቸው በፊትም ቢሆን ልጆቹ ፍላጎታቸውን ተመልክተው እቃዎቹን እና ማሽኖቹን እየገዙ ችሎታቸው እንዲጎለብት ያደረጉላቸው አሁንም ወላጆቻቸው ከካዝናቸው እያወጡ ነው። ነገር ግን ችሎታውና ፍላጎቱ ያላቸው የድሃ ልጆች በዚህ መስክ ወደፊት እንዳይገፉ የገንዘብ እጥረቱ እንቅፋት ደቅኖባቸዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየቱን የሰጠው ታዳጊ ኪሩቤል ጥበቡ፤ “እኛ ኢትዮጵያዊያን ጭንቅላታችን ከማንም የማያንስ ነው። ለምሳሌ ወደ ወረዳ እና ክፍለ ከተማ ብትሄድ ከእኛ የተሻለ (ወደ አሜሪካ ከሄዱት የቡድኑ አባላት ለማለት ነው) ብቃት ያላቸው ልጆችን ታገኛለህ። ነገር ግን እነዛን ልጆች ከቤታቸው ድረስ ሄዶ በማውጣት ድጋፍ ቢደረግላቸው ለአገራቸው ትልቅ ውለታ ማበርከት የሚችሉ ናቸው። ስለዚህ እነሱን መደገፍ የመንግስት ድርሻ ነው” ሲል በልጅ አንደበቱ ተናግሯል።

ይህን ሃሳብ የሚጋሩት ወይዘሮ ሰላማዊት ስሜ በበኩላቸው፤ ማሽኖቹ ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ቢደረግና በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ቢቀርቡ፤ እንዲሁም ለውድድሩ ጉዞና ለሆቴል ወላጆች ያወጡትን ወጪ መንግስት ቢጋራቸው እነሱም (በገቢ የተሻሉት ቤተሰቦች) የገቢ ምንጫቸው ዝቅተኛ የሆኑ ቤተሰቦችን ልጆች በመደገፍ ተያይዘው ማደግ እንደሚችሉ ብሎም ፍላጎት እንዳላቸው ነው ለሰንደቅ ጋዜጣ የተናገሩት።

ውስኪ ከቀረጥ ነጻ በሚገባበት አገር የቴክኖሎጂ ውጤቶችና ለታዳጊዎች ክህሎት ማጎልበቻ የሚሆኑ ማሽኖች ከፍተኛ የሆነ ቀረጥ እየተከፈለባቸው ሲገቡ አንድም የልጆችን የማደግ ፍላጎት ይገድባል ወዲህ ደግሞ የወላጆችን የወጪ ጣራ ያንረዋል። ይህ እንዳይሆን ደግሞ ቴክሎጂውን በአገር ቤት እንዲመረት ማድረግ ወይም ከቀረጥ ነጻ እና በስፋት ወደ አገር ቤት እንዲገባ በማድረግ በየዓመቱ ሚሊዮን ልጆችን ለምታመርተው ኢትዮጵያ የተሻለ አማራጭ መሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡ ምሁራን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ህጻን የሚወለድባት መሆኑን ተከትሎ የልጆች መሰረታዊ እቃዎች (አልባሳት፣ መጫወቻ እቃዎች እና የፈጠራ ማጎልበቻ ማሽኖች) በሙሉ የሚመጡት ከውጭ አገር ነው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረሰም የንጽህና መጠበቂያቸው ሳይቀር ከውጭ ይገባ እንደነበር የገለጹት ምሁራኑ “አገር የምታድገው አምራች ኢኮኖሚ ሲፈጠርና በፈጠራ ክህሎት የዳበሩ ህጻናት ሲኖሩ ነው። ለዚህ ደግሞ መንግስት በዚህ ዘርፍ ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ ቢሰራ የነገዋን ኢትዮጵያ በአስተማማኝ መሰረት ላይ ይገነባታል” ሲሉ ተናግረዋል።

በመጨረሻም ከአሜሪካው የሮቦት ኦሎምፒያድ ውድድር በድል የተመለሱትን ታዳጊዎች እንኳን ደስ አላችሁ እያልን በቀጣይም በዚህ መስክ ፍላጎትና ችሎታ ያላቸው ሁሉ እኩል የሚወዳደሩበት እድል ተፈጥሮ የተሻለ ውጤት እንድታመጡ መልካም ምኞታችንን እየገለጽን እንሰናበታችኋለን።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
7718 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 880 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us