የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አርት ስኩል ተማሪዎች ለዶክተር አብይ ያስገቡት ደብዳቤ

Wednesday, 16 May 2018 13:16

 

በይርጋ አበበ

 

የኢትዮጵያ መንግስት ለኪነ ጥበቡ ዘርፍ ትኩረት እንደሚሰጥና የልማቱ አካል አድርጎ እንደሚያየው ደጋግሞ ሲገልጽ ይሰማል። መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ከዚህ ተቃራኒ ነው ሲሉ በሙያው የተሰማሩ ዜጎችና ባለሙያዎች ይናገራሉ። እንደአብነት የሚያቀርቡት ምክንያትም በአገሪቱ የሲኒማ ቤቶችና ቴአትር ቤቶች ቁጥር አነስተኛ መሆን በተለይም መንግስት በክልሎች ቴአትር ቤቶችን አለማስፋፋቱን ነው።


የኪነ ጥበቡ ዘርፍ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ስር ሆኖ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ደግሞ የኪነ ጥበቡን ዘርፍ ‹‹እንደ ትርፍ ጊዜ ስራው አይቶታል›› ሲሉ ይሞግታሉ። ‹‹ይህ ባይሆን ኖሮ እስካሁን ድረስ በተለይ ቴአትር ተማሪዎች ከዩኒቨርስቲ ከወጡ በኋላ በስራ ቅጥር ሲቸገሩ አናይም ነበር›› የሚሉት የሀሳቡ ሞጋቾች ‹‹መንግስት በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የቴአትር ዲፓርትመንት ከፍቶ ተማሪዎች እየተማሩ ይገኛሉ። ሆኖም ከምረቃ በኋላ በተማሩት ሙያ ሰርተው ችሎታቸውን የሚያሳዩበትም ሆነ የገቢ ምንጫቸውን የሚያሳድጉበት ሜዳ የለም። ይህ የሆነው ደግሞ በክልሎች ቴአትር ቤት አለመኖሩ ነው›› ሲሉ ይገልጻሉ።


የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስነ ጥበባት ትምህርት ኮሌጅ (በተለምዶ ያሬድ ትምህርት ቤት) ተማሪዎች ይህን ችግራቸውን መንግስት ተመልክቶ ምላሽ እንዲሰጣቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በደብዳቤ አስታውቀዋል። የተማሪዎቹን ደብዳቤ እና ስለ ሀሳቡ ዝርዝር መረጃ ለሰንደቅ ጋዜጣ የሰጠው ተማሪ መሀመድ ጌታ ባልቻ ‹‹በኢትዮጵያ የስነ ጥበብ ተማሪዎች ቅጥር ላይ ችግር አለብን። በመሆኑን በሌሎች ዓለማት እንደሚደረገው በእኛ አገርም ‹‹ከፖለቲካ እና ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ነጻ እና ገለልተኛ የሆነ የስነ ጥበብ ምክር ቤት እንዲቋቋም ነው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ያቀረብነው›› ብሏል።


ተማሪ መሀመድ ጌታ ባልቻ አያይዞም ለአብነት የተለያዩ አገራትን ተሞክሮ ያቀረበ ሲሆን ‹‹ለምሳሌ የናይጄሪያ ስነ ጥበብ ምክር ቤት እ.ኤ.አ በ1975 የተመሰረተ ድርጅት ሲሆን ከመንግስት የተሰጠው ኃላፊነት ስነ ጥበብ እና ባህል በሀገሪቱ እንዲስፋፋ፣ እንዲያድግ እና ተደራሽነት እንዲኖረው ማድረግ ነው። ምክር ቤቱ ጋለሪ ቤት፣ ቴአትር ቤት፣ ሲኒማ ቤት እንዲሁም የዕደ ጥበባት ማዕከል የማቋቋም ስልጣን አለው። የምክር ቤቱ ሊቀመንበር በአገሪቱ ፕሬዝዳንት የሚመረጥ ሲሆን ስራውም የክልሎችን ምክር ቤት መምራት ነው›› ብሏል። ከናይጄሪያ በተጨማሪም የካናዳን፣ የህንድን እና የጀርመንን ተሞክሮ ያስታወሰው ተማሪ መሀመድ፤ በተለይ የጀርመን ስነ ጥበብ ማዕከል እ.ኤ.አ በ1696 የተቋቋመ አንጋፋ ምክር ቤት መሆኑን ገልጿል።


ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ድንጋጌ ‹‹ማንኛውም ሰው በስነ ጥበብ የመማር፣ የመዝናናት እንዲሁም ከስነ ጥበብ ጥቅም የማግኘት መብት አለው›› ሲል በአንቀጽ 27 ይደነግጋል። ዩኔስኮም ቢሆን እ.ኤ.አ በ2006 ሊዝበን ላይ ባደረገው የስነ ጥበባት ጉባዔ ‹‹ስነ ጥበብ በሁሉም አገሮች ላይ ተደራሽነት እንዲኖረው›› ሲል ውሳኔ ሃሳብ አሳልፏል፡


ከላይ የተቀመጡትን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች በዋቢነት የጠቀሰው ተማሪ መሀመድ፤ ‹‹የኢትዮጵያ መንግስትም ከፌዴራል እስከ ወረዳ ድረስ ቅርንጫፍ ያለው ጠንካራ የስነ ጥበብ ምክር ቤት ማቋቋም አለበት። ከዚህ በተጨማሪም የስነ ጥበብ ትምህርትን ከ1 እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ በትምህርት ካሪኩለም ሊያካትት ይገባዋል›› ሲል ተናግሯል።


እነዚህን ሃሳቦች በማካተትም ከ420 በላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስነ ጥበባት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጥያቄያቸውን በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት በኩል ገቢ ማድረጋቸውን ተማሪው ተናግሯል።

 

የደብዳቤው ይዘት በወፍ በረር

 

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር እኛ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስነ-ጥበባት ኮሌጅ ተማሪዎች በአሁኑ ጊዜ እያጨናነቀን እና ቤተሰቦቻችንንም እያሳሰባቸው ያለው ትልቁና አንገብጋቢው ጉዳይ ከተመረቅን በኋላ የራሳችንን የጥበብ ሥራዎችን ለህዝብ የት እናሳይ? የሚለው ጉዳይ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ያሉት የጥበብ ማሳያዎች የሚገኙት አዲስ አበባ ከተማ ላይ ብቻ በመሆናቸው ነው። ያሉትም የመንግስት የጥበብ ማሳያዎች ለምሳሌ ስዕል፣ የቴአትር እና የሙዚቃ ማሳያ ወይም ማቅረቢያ ቦታዎች በጣም ውስን ናቸው። እነኚህም ቦታዎች የቴዙት ቁጥራቸው ውስን በሆነ ግለሰቦች ነው። በተጨማሪም አብዛኛው የስነ ጥበባት ኮሌጅ ተማሪዎች የክፍለ ሀገር ልጆች እንደመሆናችን መጠን በአካባቢያችን ጋላሪ ቤቶች፣ ቴአትር ቤቶች፣ ሲኒማ ቤቶች እና ሙዚቃ ቤቶች (ኦፔራ) የለም።


የመጀመሪው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ (ከ2003-2007) አፈፃፀም ላይ፡- የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ምንም ዓይነት ጋለሪ ቤት፣ ቴአትር ቤት፣ ሲኒማ ቤት፣ ሙዚቃ ቤት /ኦፔራ/ እንዳላቋቋመና እንዳልሰራ ያሳያል። ባህልና ቱሪዝም ስነ ጥበብን ወደ ጎን በመተው በቅርስ ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ሁለት ቅርሶችን በዩኒስኮ አስመዝግቧል። በሀገር አቀፍ ደረጃ 323 ቋሚና 6863 ተንቀሳቃሽ ቅርሶች እንዲመዘገቡ ተደርጓል በማለት ይገልጻል።


በመሆኑም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት “ኢትዮጵያ ተስፋ የምትሰጥ እንጂ ተስፋ የምታስቆርጥ እንዳትሆን የምንችለውን ሁሉ እንደምናደርግ ቃል እገባለሁ” ባሉት መሠረት እና “ለተፈጠሩ ችግሮች እልባት በማበጀት ህዝባችንን እንደምንክስም ጭምር በዚሁ አጋጣሚ ቃል እገባለሁ” እንዳሉት የጨለመውን ህይወታችንና ተስፋችንን የስነ-ጥበብ ምክር ቤቱ እንዲቋቋምልን በመፍቀድ ተስፋችንና ህይወታችንን በገጠር በከተማ የምንኖረውን ኢትዮጵያዊያኖችን ብሩህ እንዲታደርጉት በአክብሮት እንጠይቃለን።

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
7322 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 973 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us