ኢትዮጵያዊያን ሴቶች በሰዓሊ ታምራት ስልጣን

Wednesday, 23 May 2018 14:19

 

በይርጋ አበበ

ኢትዮጵያ ለሴት ልጆቿ የማትመች አገር ብትባል ማጋነን አይመስልም። በእርግጥ የሶስተኛው ዓለም አብዛኛው ዜጋ ኑሮውን በጉስቁልና የሚመራ መሆኑ የአደባባይ ሀቅ ቢሆንም በሴቶች ላይ የሚያሳርፈው የኑሮ በትር ግን ከተባዕቶቹ የጠነከረ ነው። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት ሴት ልጆቻቸውን ከማስተማርና ለአደባባይ ክብር ከማድረስ ይልቅ ‹‹የጓዳ ጌጥ›› ማድረጉ የተለመደ ነው። በዘፈን ሳቀር ‹‹የሳሎኔ ጌጥ፣ ውዬ ስገባ ከቤቴ፣ ወዘተ….›› እየተባለ የሚዘፈነው ለሴቶች ነው። ወንዶቹ ወደጓሮ ሴቶቹ ወደጓዳ እንዲል የጥንት ሰው ማለት ነው።

ከዚህ ሃሳብ በተቃራኒ የቆመው ሰዓሊ ታምራት ስልጣን ደግሞ የሴቶችን ድካም የሚገልጽ የስዕል አውደ ርዕይ አዘጋጅቶ ለእይታ አቅርቧል። ባሳለፍነው ሰኞ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ “ብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደስላሴ የጥበብ ማዕከል” ውስጥ የተከፈተው አውደ ርዕይ እስከቀጣዩ ሀምሌ ወር መጀመሪያዎቹ ሳምንታት በነጻ ለእይታ ክፍት ሆኖ ይቆያል።

የስዕል አውደርዕዩን ስያሜ ‹‹መክተፏ›› ሲል የሰየመው አርቲስቱ ከዚህ ቀደም ስድስት ጊዜ በግሉ፤ ከ20 ጊዜ በላይ በሆል ያቀረበ ሲሆን የአሁኑ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ትኩረቱን ለሴቶች ያደረገ ነው። ስለ ሃሳቡ ሲናገርም ‹‹ከዝብርቅርቅ ዕይታ እና ሃሳብ ወደጠራ መስመር ለማምጣት ብዙ ወራትን ቆየሁ›› ሲል ስለ ስዕሎቹ የሚናገረው ሰዓሊ ታምራት፤ ሃሳቡን ሲያብራራም ‹‹እነዚህን የዓመታት ትዝብቶቼንና ገጠመኞቼን ከንባብ፣ ከውይይት፣ የሕይወት ተሞክሮዬን እና ስሜቴን ለመግለጽ ይመጥናል በምላቸው ቀለሞች፣ ቅርጾች እና መስመሮች ባለፉት ወራት በስዕል መስሪያ ክፍሌ (ስቱዲዮ) ውስጥ በተለያዩ ቁሶች ማከናወን ጀመርኩ›› ሲል የስዕሎቹን ጅማሮና መዳረሻ ያስረዳል።

መክተፏ መክተፊያ ጣውላን ከሴት ልጅ አካል ጋር አቀናጅቶ የሳለው ሲሆን ‹‹ሴቶች ለአገራችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ያላቸውን መጠነ ሰፊ ሚና›› የሚያመላክት እንደሆነም ይናገራል። ሰዓሊው ስለ ስዕሎቹ ሲናገር ‹‹የመክተፊያ ቦርዱ በስዕሉ ቢላዋዎች በወጥ ቤት ምግብ በቀላሉ ተዘጋጅቶ በሳሎን ጠረጴዛ ከመቅረቡ በፊት እነዚህ የመክተፊያ ቦርዶች የሚታዩባቸው የተለያዩ ጠባሳዎች፣ አካላዊ ድካም እና የጥንካሬ እጦት ተገቢውን ትኩረት የሰጣቸው የለም። በተመሳሳይ መልኩ የእኛ የኢትዮጵያ ሴቶች ከመጋረጃው ጀርባ በተዘጉ በሮች ጀርባ በየቤቱ በየቀኑ የሚከፍሏቸው መስዋዕቶች ከእነዚህ የመክተፊያ ቦርዶች ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ናቸው›› ይላል።

ከ50 በላይ የስዕል ስራዎችን ከባህላዊ የሙዚቃ ጋር በማጀብ ያቀረበ ሲሆን፤ ይህም ታዳሚን ከማዝናናት ባለፈ ለሰዓሊው ስራዎች ጉልበት ለመስጠት የታሰብ ጭምር ነው።

መክተፊያን ከሴት ልጅ ጋር ብቻ ማገናኘት ተገቢ ነው ወይ? ወንዶችስ የጓዳውን ስራ ይሰሩት የለም ወይ? የሚል ጥያቄ የቀረበለት ሰዓሊ ታምራት ወንዶች ምግብ የሚመገቡት በቤታቸው እህቶቻቸው፣ እናቶቻቸው፣ የቤት ሰራተኞቻቸው ወይም ሚስቶቻቸው የሰሩላቸውን ነው። ከቤት ውጭ ቢበሉም እንኳን በሆቴል ወይም ሬስቶራንት ውስጥ ምግቡን የሚያበስሉት ሴቶች መሆናቸውን ያስታወሰ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የሴቶች ሚና ጎልቶ ይውጣ እንጂ ወንዶች መክተፊያን አይጠቀሙባትም ለማለት እንዳልሆነ ተናግሯል።

 

 

ነጻነት የሚናፍቀው የስዕል ሙያ

ሰዓሊው ስዕሎቹን ከሴት ልጅ የጉልበት ብዝበዛ ጋር አገናኝቶ እንዲህ ያቅርበው እንጂ በኢትዮጵያ የሰዓሊያ የጉልበት ብዝበዛም መንግስት ፊት የነሳው ዘርፍ መሆኑ በስፋት ይነገራል። በኢትዮጵያ የስዕል ኢንዱስትሪው እያደገ ለመሆኑ ጥያቄ የማይነሳበት ቢሆንም የሰዓሊያን ኑሮ ግን እያደገ አለመሆኑ ይነገራል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ብዙ ሊሆን ይችላል (የቀለምና ሌሎች የስዕል ግባቶች ዋጋ መወደድ፣ የስቱዲዮ ችግር፣ የገበያ እጥረት፣ የአውደርዕይ ማዘጋጃ ቦታ አለማግኘት ወዘተ)። በዚህ መሰናክል ውስጥ ታልፎ የሚሰራውን የስዕል ስራ በኢትዮጵያዊያን ዜጎች የመፈለግ እድል ቢኖረው እንኳን ኢትዮጵያዊያን ባላቸው የገንዘብ እጥረት አማካኝነት ከገበያው ያርቃቸዋል። ስለዚህ ለኢትዮጵያ ሰዓሊያን ዋና የገበያ ደንበኞች የውጭ ዜጎች ቢሆኑም ባለፉት ሶስት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት የቱሪስት ፍሰቱ ቀንሷል። ይህ መሆኑ ደግሞ በሰዓሊያን ገበያ ላይ የራሱን የሆነ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን የኢትዮጵያ ሰዓሊያን ማህበር የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሰዓሊ በቅርቡ በአንድ መድረክ ላይ ሲናገር ሰምተነዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶችና የኢትዮጵያ ሰዓሊያን ተመሳሳይ ጫና እና መገፋት የሚደርስባቸው ከመሆኑ የተነሳ ሁለቱም ነጻ እንዲወጡና እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ደግሞ አገሪቱ ልትከፍለው የሚገባት ዋጋ ይኖራል።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
4496 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 132 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us