የወርቁ ሞላ “ሳንኪ” እና “እንጃልኝ” ሲዳሰሱ

Wednesday, 06 June 2018 13:53

 

 

በይርጋ አበበ

 

 

ቀጭን ሰውነትና ድምጸ መረዋ ወጣት በቅርቡ የዩቲዩብና ሎሚ ቲዩብ ገጾችን በሁለት ዜማዎቹ ተቆጣጥሯቸዋል ብሎ መናገር ይቻላል። ትውልዱ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን (በአሁኑ የዞን አወቃቀር ማዕከላዊ ጎንደር) አዳኝ አገር ጫቆ አካባቢ ነው። ዕድገቱ ደግሞ ጭልጋ አካባቢ ነው። ሙዚቃን የጀመረው በትምህርት ቤት ሲሆን እየቆየ ደግሞ በኪነት ቡድን ታቅፎ መዝፈንና እስክስታ መወዛወዝ መጀመሩን ይናገራል።

 

ወጣቱ ድምጻዊ ስድስት ሙዚቃዎችን ለአድማጭ ያቀረበ ቢሆንም ከአድማጭ ጋር በሚገባ ያስተዋወቀው ግን ‹‹ሳንኪ›› የሚለው ስራው ነው። በሳንኪ ከፍተኛ ተቀባይነትን ካገኘ በኋላም ለሁለት ዓመታት ከሙዚቃ ርቆ ከቆየ በኋላ በቅርቡ ‹‹እንጃልኝ›› የሚል የጎጃ ዜማ ይዞ ቀረበ። ለሁለት ዓመታት ከሙዚቃ የቆየበት ምክንያት ደግሞ በጎንደር አካባቢ በደረሰው ግጭትና በደረሰው ሰዋዊ እልቂት ምክንያት ሀዘን ላይ በተቀመጠ ህዝብ ፊት አልዘፍንም በማለቱ እንደሆነ ተናግሯል።

ድምጻዊው ከሚኖርበት ጎንደር ከተማ ሆኖ በሁለቱ ዜማዎችና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር በስልክ ቃለ ምልልስ ያደረገ ሲሆን፤ የቃለ ምልልሱን ይዘት ከዚህ በታች እናቀርበዋለን።

 

ሳንኪ እና እንጃልኝ አጀማመራቸው

ሳንኪ የሚለው ነጠላ ዜማ የተሰራው ጥናት ከተሰራለት በኋላ ሲሆን የአካባቢውን ነባር ባህል መሰረት ያደረገ እንደሆነ ይናገራል። ሳንኪ በጥናት የተሰራ በመሆኑም ከፍተኛ አድናቆትና የህዝብ ተቀባይነትን እንዲያገኝ አስችሎታል የሚለው ድምጻዊ ወርቁ ሞላ፤ በጎጃምኛ ዜማ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ስራ ለመስራት መነሳቱን ተናግሯል። በጎጃምኛ ዜማው ላይም ቢሆን ጥናት ማካሄዱን ገልጾ፤ ‹‹ሃሳቡም ሰፋ ብሎ አገር ሰላም ይሁን ብሎ ነው የሚጀምረው›› ሲል ስለ አዲሱ ነጠላ ዜማው ይናገራል።

‹‹ኢትዮጵያ ቅድስት አገር ናት ህዝቧ እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትኖ ያለፈ ኩሩ ህዝብ ነው›› የሚለው ድምጻዊ ወርቁ ሞላ፤ ‹‹ዘፈኑ ሰፋ ያለ ሃሳብ ይዞ የተነሳውም›› በዚህ የተነሳ መሆኑን ይናገራል። ዘፈኑ ላይም፡-

 

‹‹እየሙን እየሙን እየሙን

አገር ሰላም ይሁን›› በማለት ምኞቱን ይገልጻል። ‹‹አገር ቢሉ ከኢትዮጵያ ወዲያ፤ ህዝብ ቢሉ ከሀበሻ ወዲያ ኤዲያ›› በማለት ስለ አገሪቱና ህዝቧ ታላቅነት ይናገራል። በዚህ የተነሳም ዘፈኖቹ ሊወደዱ መቻላቸውን አስታውቋል። ‹‹የጃኖ ልብስን ከአስር ዓመት በፊት ለብሼው ብቅ ካልኩ በኋላ ጃኖ እንዲህ ፋሽን ሆኖ ሳየው ደስ ይለኛል›› የሚለው ወርቁ ሞላ፤ በዘፈኖቹ በርካታ ተወዛዋዦች የሚያሳትፍበት ምክንያትም ይህ እንደሆነ ተናግሯል።

 

ለምሳሌ በእንጃልኝ ዘፈኑ ውስጥ 32 ተወዛዋዦችን ያሳተፈ ሲሆን ‹‹ከእነዚህ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ለቀረጻ የበቁ እንዳሉት ሁሉ በማር እስከ ጧፍ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ልጆች አብረውን ሰርተዋል። ይህ መሆኑ ደግሞ የተለየ ድባብ እንዲኖረው አድርጎልናል›› ብሏል።

 

አርቲስት ወርቁ በዚህ ዘመን የሚሰሩ የባህል ሙዚቃች ላይ በውዝዋዜ በኩል የሚታዩ ክፍተቶች እንደሚያስከፉት ይናገራል። ‹‹በባህል ውዝዋዜ ላይ ጅንስን ሲጠቀሙ ማየት እየተለመደ መጥቷል›› ሲል መናገር የሚጀምረው ወርቁ፤ ‹‹እንጃልኝን ስንሰራ ቦታው ድረስ ሄደን በባህሉ ባለቤቶች ጥናት አስጠንተን ልንሰራ የቻልነው ከዚህ የተነሳ ነው›› ብሏል። ለዚህ ነጠላ ዜማ ቀረጻም ከ72 ሺህ ብር በላይ ወጭ እንዳደረገ ተናግሯል።

 

የአማርኛው ሃጫሉ?

አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ በሙዚቃ አድማጮች ዘንድ ይበልጥ ታዋቂ የሆነው ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆችን ለመደገፍ በተዘጋጀው የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ በዘፈነው ዘፈን ነው። በወቅቱ ሃጫሉ የኦሮሞ ህዝብ በዚህ ስርዓት እየደረሰበት ያለውን የመብት ጥሰት በባለስልጣኑ ፊት የዘፈነ ሲሆን ይህን ድርጊቱንም በቅርቡ ከስልጣን የተነሱት የብሮድካስት ባለስልጣን ዳይሬክተር ዘርአይ አስገዶም ‹‹ፈረስ ጭናችሁ አራት ኪሎ ግቡ እያለ የሚዘፍነውን የሀጫሉን ዘፈን በቴሌቪዥን ማስተላለፍ ምን ይሉታል?›› ሲሉ የኦሮሚያ ብሮድካስት ኔትዎርክን መተቸታቸው አይዘነጋም።

 

ልክ እንደሀጫሉ ሁሉ የጎንደሩ ልጅ ወርቁ ሞላም የአማራ ክልል ከፍተኛ ባስልጣናት በተገኙበት የፋሲል ደመወዝን ‹‹አለ ነገር›› የሚል ዘፈን በመዝፈን ታዳሚን ሲያስፈነድቅ ባለስልጣናቱን ደግሞ አስደምሟቸዋል። በዚህ ድርጊቱም ‹‹እንደ ሃጫሉ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

 

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየቱን እንዲሰጠን ላቀረብንለት ጥያቄ ሲመልስም ‹‹ቀደም ባሉት ጊዜያት የራሴን ስራ ከመስራት በፊት ነበር ይህን ዘፈኑን ስዘፍነው የነበረው። ይገርምሃል የመንግስት ካድሬዎች በራሳቸው የተሃድሶ ፕሮግራም ላይ ዘፈኑን እንድዘፍንላቸው ጠይቀውኛል›› ሲል ከአካባቢው ባስልጣናት የቀረበበት ትችት እንዳልነበረ ተናግሯል። ሆኖም ስጋት አድሮበት እንደነበረ ሳይሸሽግ አላለፈም። ዘፈኑ የመንግስት ባለስልጣናትን ስለማያስደስት (ቢያስደስታቸው እንኳን በፖለቲከኞች ስለማይደገፍ) ሆን ብለው ሊያጠምዱኝ አስበው ነው የሚል ስጋት አድሮበት ሁሉ እንደነበረ ተናግሯል።

 

የወርቁ ሞላ ዘፈኖችን በወፍ በረር

ድምጻዊ ሞላ ወርቁ ‹‹እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትኖ ያለፈ ህዝብ ነው›› በሚለው የኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ አንዱ ለሆነው ለጎጃም ህዝብ ሲቀኝ፤

‹‹እንደ ጣና አጥርቶት አሳምሮ ሰርቶት

ደግነት ጀግንነት አሳምሮ ችሮት›› ይላል።

ድምጻዊው የጎጃምን ህዝብ በጅግንነት እና ደግነት ብቻ በመወከል ሳያበቃ በፍቅር የተካኑ ናቸው ሲል በሚቀኝበት ስራው፡-

እነዚህ ጎጃሞች መወደድ ያውቃሉ

ከአንጀት እየመቱ አንጄት ይገባሉ›› ሲል ሞቴን ጎጃም ያድርገው የሚሉትን ሰዎች እንዳልተሳሳቱ ይደግፋቸዋል። ወርቅ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ከዜማም በላይ ነው የሚለው ይህ ወጣት ድምጻዊ፤ ‹‹ወደቀደመ እኛነታችን ስልንመለስ እና ራሳችንን ፈልገን ልናገኝ ይገባል›› የሚል እምነት አለው። ‹‹ኢትዮጵያ ስትነሳበት ደስ የማይለው አካል አለ›› የሚለው ይህ ወጣት ድምጻዊ፤ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቱሪዝም ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን መንግስት እየነገረን ነው። ቱሪስቶችን ወደ አገራችን እንዲመጡ ስናደርግ ደግሞ ልናሳያቸው የሚገባን የራሳችን ባህል እና ሙዚቃን እንጂ ካራቫት ያደረገን የባህል ዘፋኝ አይደለም ይላል።

ሌላው የወርቁ ሞላ ተወዳጅ ዘፈን ሳንኪ ነው። ሳንኪ ከሚለው ዘፈኑ ላይ ደግሞ የሚከተሉትን ስንኞች አንስተን እንመለከታለን።

‹‹ዝናው የታለ ያ ስመ ጥር

የአባ ታጠቅ ልጅ የኳሊ በር።

ስፍራው ቸር ውሎ ጫታ ይደር

ያ ያሳደገኝ በጌምድር›› ሲል የጎንደርን ትንሳዔ የሚመኝበትን ቅኔ በውብ ዜማ ያሰማናል።

‹‹የጉና ጠምበለል የበለሳ እንጉዳይ

ከአገሩ ካፈሩ ነው የኔማ ጉዳይ›› በሚለው ግጥሙ ደግሞ አገር ማለት ሰው ነው ከሚለውም በላይ አገር መሬትና አፈር እንደሆነ ይገልጻል።

የጎንደርን ታላቅነትና የህዝቡን ጀግንነት በተመለከተ ሲቀኝ ደግሞ፤-

     ‹‹ከነባር ቢነሱ ከላይ ከዘር ከዘር ግንዱ፤

ከጎንደር ወይዛዝርት ጀግና ከወለዱ።

ወንዶቹ እንደ አንበሳ ሴቱ እንደ ዱር አውሬ፤

ጥቃቱን አይወድም ሲፈጠር ጎንደሬ።

የኢትዮጵያ ቀኝ እጅ ሺ ጦር ያልበገረው፤

ገብርዬ ሲማርክ ይል ነበር እሰረው›› በማለት ስለ ጎንደርና ጎንደሬ ይናገራል።

 

ለመውጫ

 

 

‹‹ጎንደር ዙሪያ ገባው በእልፍ ጀግና ታጥሮ

በእስራኤሎች መንደር ወለዳ ተሸግሮ።

አገራችን ጎንደር ሰሜን አርማጭሆ ወልቃይት ጠገዴ ዳንሻና ሁመራ፤

አይ ደመንማናው አፈር፤ ጭልጋና መተማ ደንቢያና ፎገራ።

አገራችን ጎንደር መልሶ አገራችን

ጓያችን ይሰብራል እንኳን ጥይታችን›› በማለት ዘፈኑን ይቋጫል።

ዘፈኑን ትሰሙት ዘንድ እየጋበዝን በዚሁ እንሰናበታለን።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
2250 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 133 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us