ጋዜጠኛ ብሩክ እንዳለ የጤንነት ሁኔታው እና ለሙያው ያሳየው ተቆርቋሪነት

Wednesday, 20 June 2018 12:38

 

በይርጋ አበበ

 

ጋዜጠኛ ብሩክ እንዳለ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ባልደረባ በነበረበት ወቅት ለህዝብ ያቀርባቸው በነበሩ አነጋጋሪ ስራዎቹ ይታወቃል። በ2009 ዓ.ም ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) “ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ባወጣው አልበሙ ዙሪያ ቃለ ምልልስ ሊያደርግለት ከድምጻዊው መኖሪያ ቤት ተገኝቶ ያዘጋጃቸውን ጥያቄዎች ጠይቆ የተሰጠውን ምላሽ ይዞ ወደ እናት መስሪያ ቤቱ ተመለሰ። በጋዜጠኝነት ሙያ አሰልቺ ከሆኑት የዕለት ተዕለት ስራዎች መካከል አንዱ ቃለ መጠይቅ የተደረገለትን ግለሰብ ድምጽና ምስልን ለተመልካች፣ አድማጭና አንባቢያን በሚጥም መልኩ ማስተካከል (ኤዲት ማድረግ) ሲሆን ታታሪው ጋዜጠኛ ብሩክ እንዳለ ግን የድምጻዊ ቴዲ አፍሮን ቃለ ምልልስ በጥራትና በትጋት ኤዲት አድርጎ ጨርሶ ለበላይ አለቆቹ አስረከበ።

ቃለ ምልልሱም በኢቢሲ ዋናው የቴሌቪዥን ጣቢያ እሁድ መዝናኛ ላይ ለተመልካች እንደሚቀርብ ጣቢያው አስተዋወቀ። ሆኖም ትንሽ ቆይቶ የቴዲ አፍሮ ቃለ ምልልስ በኢቢሲ እንደማይተላለፍ ተገለጸ። ከዚህ ክስተት በኋላ ይበልጥ አነጋጋሪ የሆነው የጣቢያው ውሳኔ እና የጋዜጠኛ ብሩክ እንዳለ ድካም “በወንፊት የተያዘ ውሃ ሆኖ መቅረቱ” ነበር። “ለሙያው ክብር ስል በዚህ መልኩ ስራዬን እየሰራሁ መቆየት አልፈልግም” ሲል አቋሙን ግልጽ ያደረገው ጋዜጠኛ ብሩክ እንዳለም ከድርጅቱ ለመልቀቅ ደብዳቤ አስገብቶ ወደ ቤቱ ተመለሰ።

ጋዜጠኛው ስራውን ከለቀቀ ከሳምንታት በኋላ ግን ሌላ አስደንጋጭ ዜና ተሰማ። ጋዜጠኛ ብሩክ እንዳለ የጤና እክል ገጥሞት በተለያዩ ሆስፒታሎች የህክምና ካርድ ይዞ ታየ የሚሉ ወሬዎች ተበራከቱ። ለዓመታት የማስታወሻ ደብተርና መቅረጸ ድምጽ ይዞ ሲዋከብ የሚታየው ፈጣንና ባለ ብሩህ አዕምሮ ወጣት፤ በአንድ ጀምበር ወደ ህክምና መስጫ ተቋማት ሄዶ ህክምና ወረፋ ሲጠብቅ ተገኘ። በምን ምክንያት ለህመም ተዳረገ ለሚለው ጥያቄ እስካሁን ይህ ነው የተባለ ተጨባጭ ምላሽ የለም። በጉዳዩ ዙሪያ የተለያዩ መላ ምቶች ቢሰጡም ባለ ጉዳዩ ጋዜጠኛ ብሩክ እንዳለ ግን ‹‹ሆድ ይፍጀውን›› መርጦ በተረገመ ቀን የደረሰበት ዱብ እዳ እንደሆነ ከመናገር ውጭ እሱም የህመሙን መነሻ ግልጽ አላደረገም።

ስራ ከለቀቀ አንድ ዓመት በኋላ ወይም ህመሙ ከደረሰበት አንድ ዓመት ሲሞላው ለተሻለ ህክምና ወደ ቱርክ ሊያቀና መሆኑን ሰማንና “ጠያቂውን ልንጠይቅ” ቤቱ ድረስ ሄድን። ጋዜጠኛ ብሩክ ስለ ቱርክ ጉዞው፣ ስለ ህመሙ መጠን እና ስለ ጋዜጠኝነት ሙያ የሰጠንን ሃሳብ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

ህመሙ ሲጀምር የነበረው ሁኔታ እና ያደረገው ክትትል

ህመሙ ሲጀምረኝ እግሬን ነበር የያዘኝ። ህመሙ እንደተሰማኝ ወደተለያዩ ሆስፒታሎች ስሄድ አንዱ የሚቀባ መድሃኒት ሲሰጠኝ ሌላኛው መርፌ ይሰጠኛል። ነገር ግን ስቀባ የነበረውም ሆነ ስወጋ የነበረው መርፌ ዋጋ አልነበረውም። ወደ ባልቻ ሆስፒታል ሄጄም ራጅ ተነሳሁ፤ ሩሲያዊያን ሃኪሞች ነርቭህን ብርድ መቶት ነው ብለው ነገሩኝና በተለምዶ ደረቅ መርፌ የሚባለውን እና ኪኒን ሰጡኝ። ይህን ተከታትዬም ለውጥ የለውም። ከዚያም ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል ሄድኩ። መድሃኒት ሰጥተውኝ ሲከታተሉኝ ለውጥ ስላላዩብኝ MRI ምርመራ ሲደረግልኝ የዲስክ መንሸራተት እንደሆነ ተገለጸልኝ።

እኔን ያመመኝ ዲስክ መንሸራተት ደግሞ በፊዚዮቴራፒ ክትትል የሚድን ስላልሆነ ኦፕራሲዮን መደረግ እንዳለብኝ ነገሩኝ። በዚህ አገር በዚህ ህመም ዙሪያ ያለን የህክምና ልምድ ከስድስት ዓመት የማይበልጥ ከመሆኑም በላይ ህክምናውን ማካሄድ ከባድ ነው። እስካሁንም ውጤታማ የሆኑት ህክምናዎች በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። ስለዚህ ማድረግ የነበረብኝ የተሻለ ህክምና እስከማገኝ ድረስ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ፊዚዮቴራፒስት አቶ ይሳቅ ሽፈራው ዘንድ ሄጄ ፊዚዮቴራፒ ክትትል ማድረግ ነበር። በዚህም ለውጥ ላገኝ አልቻልኩም። ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተመልሼ ስሄድ ኦፕሬሽን መደረግ እንዳለብኝ በድጋሚ ገለጹልኝ።

የገቢ ማሰባሰቡ ሂደትና የተገኘ ውጤት

ህመሙ እንዳመመኝ አካባቢ ከ20 እና 30 ሜትር በላይ መንቀሳቀስም ይከብደኝ ነበር። የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሀኪሞች ቦርድ ወደ ውጭ ሄጄ እንድታከም ወሰነ። ህክምናውን ለማድረግ ጀርመን ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል የሮሆቦቲክስ ህክምና እንዳገኝ የተወሰነ ሲሆን በወቅቱ ለህክምናው የሚያስፈልገው 30 ሺህ ዶላር እንደሆነ ነገረን። ገንዘቡ ብዙ ስለነበረ ኮሚቴ ተዋቅሮ እንቅስቃሴ ተጀመረ። ህዝቡ ያደረገልኝ ድጋፍ ከፍተኛ ነው። ኮሚቴዎቹም በራሳቸው ተነሳሽነት ያደረጉልኝ ድጋፍ የሚደነቅ ነው። ወደ ገንዘቡ ስንመጣ በባንክ አካውንቴ የታሰበውን ያህል ገንዘብ አልገባም፤ ለዚህ ደግሞ ችግሩ የሚመስለኝ የባንክ ገንዘብ ዝውውር ስርዓታችን ኋላ ቀርና ምቹ ስላልሆነ ነው። የተሻለ ገንዘብ የተገኘው በ‹‹ጎፈንድሚ›› (GOFUNDME) በጋዜጠኛ ሊባኖስ ዮሀንስ አጋዥነት የተሻለ ገንዘብ መሰብሰብ ተችሏል። በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ግን የአፍሪሄልዝ ቴሌቪዥን ባለሙያዎች ይከታተሉኝ ነበር። ዶክተር ሜሎን ወርቁም ጉዳዩን ተከታትላ ወደ ውጭ አገር ሄጄ የምታከምበትን ሁኔታ እያመቻቸችልኝ እንደሆነና በቦርድ እየታየ መሆኑንም ነግራኝ ነበር።

አፍሪሄልዞች ባይመጡ ኖሮ ህክምና ለማድረግ የቤተሰቦቼ መኖሪያ ቤት ተሸጦ ለመታከም ነበር ያሰብነው። በዚህ መሃል የአፍሪ ሄልዝ ጥረት መሳካቱን ነገሩኝ። ነገር ግን እስካሁን የደረሱበትን ደረጃ አላውቅም። ከእግዚአብሔር ጋርም ይሳካል ብዬ አስባለሁ።

የጋዜጠኞች ጥረት

በሆነ አጋጣሚ የህክምና ስህተት ተሰራ ተብሎ ሲነገር የሀኪሞች ማህበር ቀድሞ በመውጣት ነው የሚከላከሉት። ይህን የሚያደርጉትም ለሙያው ክብር ሲሉ ነው። በጋዜጠኝኘቱም ስንመለከት ህመም ሲፈጠር ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ነገር ጠንካራ የሆነ የጋዜጠኞች ህብረት መንፈስ ሊያሳዩ ይገባል።

ጋዜጠኝነት እና ለኢትዮጵያ ያበረከተው ሚና

በአሁኑ ወቅት ጋዜጠኝነት ለአገር የሚገባውን ያህል እያበረከተ ነው ብዬ አላምንም። ለዚህ ደግሞ ከዚህ በፊት የነበረው የመንግስት አሰራርም ሊሆን ይችላል (ከዶክተር አብይ ወደ ስልጣን መምጣት በፊት ያለውን) ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ሙያው ተገቢውን ክብር እንዳያገኝ የተደረገው በጋዜጠኛው ድክመትም ነው ብዬ አስባለሁ።

በተለያዩ አጋጣሚዎች ሙያው ሲበደል እንሰማለን። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ብዬ የማስበው ጠንካራ ማህበር ስለሌለን ሊሆን ይችላል። በዚህ ዘመን አንድ ሰው ጋዜጠኛ ለመሆን ምንም የሚጠየቀው ነገር የለም። አንድ ሃኪም በሙያው ስህተት ቢሰራ አንድ ሰው ነው ሊጎዳ የሚችለው፤ ጋዜጠኛው ግን ኃላፊነት ሳይሰማው ቀርቶ ወይም በሙያ ብቃት ማነስ ስህተት ቢሰራ ሚሊዮኖችን ነው የሚጎዳው። ይህን ያህል ስስ (ሴንሲቲቭ) ጉዳይ ስለሆነ በኃላፊነት ሊሰራ የሚገባው ሙያ ቢሆንም እኛ አገር ውስጥ ግን ያለው እውነታ ከዚህ በተቃራኒው ነው።

ሌላው ቀርቶ የአገሪቱን የሚዲያ ዘርፍ እንዲመራ ስልጣን የተሰጠው የብሮድካስት ባለስልጣን ለግለሰቦች የሚዲያ ፈቃድ ሲሰጥ የግለሰቡን የሙያ ብቃት ታሪክ አያጠናም። 12ኛ ክፍልን ያላጠናቀቀ ሰው የቴሌቪዥን ባለቤት እንዲሆን ፈቃድ ሲሰጠው በተሰጠው ጣቢያ ምን ሊሰራበት እንደሚችል አስብ። በዚህ ሰው ስር የሚቀጠሩ ጋዜጠኞች ሙያቸው እንዴት ሊከበር እንደሚችልም ስናስብ ያጠያይቃል። በአገራችን እኮ አንቱታን ያተረፉ የሚዲያ ባለቤቶች አሉ። የተሰጣቸውን ሚዲያ ከአንባቢ እና አድማጭ ጋር አዋህደውና አስማምተው ከበሬታን ያተረፉ ሚዲያዎች።

ነገር ግን በርካታ የሚዲያ ባለቤቶች በተባባሪ አዘጋጅነት የሚሰሩ ድርጅቶችን የአየር ሰዓት ሲሰጡ የአዘጋጆቹን ሙያዊ እውቀት እና ሊያስተላልፉ የሚችሉትን ይዘት አይመዝኑም። ብዙዎቹ ተባባሪ አዘጋጆቹ ሊያስገቡላቸው ስለሚችሉት የስፖንሰር ገቢ ብቻ ነው የሚጨነቁት።

ሌላው ደግሞ ዩኒቨርስቲዎቻችንም ቢሆኑ ምን ያህል ተማሪን እንዳስመረቁ እንጂ በጥራት ስለማስተማራቸው የሚያስቡበት አይመስለኝም። ይህ በመሆኑም ብዙ ክብር የሚሰጣቸው ጋዜጠኞች ከሙያው ሲሸሹና በሌላ ስራ ሲሰማሩ ይታያል።

ስለዚህ ጋዜጠኝነት እንዲከበርና ለአገር ግንባታም አስተዋጽኦዋቸው የጎላ እንዲሆን መንግስት፣ ዩኒቨርስቲዎች እና ጋዜጠኞች ሊያስቡበት ይገባል። በተለይ እኛ ጋዜጠኞቹ ራሳችንን እና ሙያችንን ለማስከበር በስነ ምግባር እና በእውቀት ራሳችንን ማሳደግ ይኖርብናል። ህክምናዬን ተከታትዬ ስመጣ በዚህ ጉዳይ የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማድረግ ነው ያሰብኩት።

ሚዲያው የተዳከመበት ተጨማሪ ምክንያት

መንግስት ጠንካሮቹን የሀይማኖት ተቋማትን፣ ሲቪክ ማህበራትን እና ሚዲያውን በአንድም በሌላ መልኩም አጠፋቸው። ያሉትን ደግሞ የእሱ አጀንዳ ሰባኪ አደረጋቸው። በዚህ ምክንያት ህዝቡ የሚያከብረው ተቋም አጣ።

ለምሳሌ ባለፉት ሶስት ወራት በአገራችን በነበረው ግጭት ሚዲያዎች በተለይ የሬዲዮ ጣቢዎች ግጭቱ እንዲበርድ ያደረጉት አስተዋጽኦ ምንድን ነው? ብለን ስንመለከት ምንም ያደረጉት አስተዋጽኦ አልነበረም። ይህ የሆነው ደግሞ በደህና ቀን የሰሩት ረብ ያለው ስራ ስላልነበረ ነው። በችግር ቀን ተነስተው ግጭቱ እንዲቆም ቢናገሩስ ማን ሊሰማቸው ይችላል? ነገም የሆነ ችግር ቢፈጠር ለመፍትሔ የሚሆን መልእክት ሊያስተላልፍ የሚችል አይደለም።

ስለዚህ ይህ የተከበረ ሙያ ለአገር ግንባታ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲጫወት ጋዜጠኝነት በነጻነት የምትሰራው ስራ ስለሆነ መንግስት ለሙያው ነጻነት ሊሰጠው ይገባል።

Last modified on Wednesday, 20 June 2018 13:12
ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1653 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 883 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us