አእምሮን አሳሹ ኢንጂነር

Wednesday, 30 April 2014 13:19

“አንድ መዘንጋት የሌለበት ነገር ስኬት፣ ጤና፣ ፍቅር፣ እርካታ፣ ሃሴት፣ ደስታ፣ ሰላምና ነፃነት አንጎላችን እንዴት እንደሚሰራ መሰረታዊ እውቀት ካለን ሁሌም ቢሆን ከኛ ሩቅ አይደለም። የአእምሮ አስተዳደር ሞዴል መፅሀፍ መግቢያ ላይ የተወሰደ።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ “አንቱ” የተባሉና በሀያላን አገራትም ዘንድ ልዩ ክብርን የተጎናፀፉ በርካታ ውድ ልጆች አሏት። በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ የዓለም መገናኛ ብዙሃን ትኩረትን በመሳብ የአንዳንዶቹን ስምና ዝና ማጉላት እየተለመደ መጥቷል። በስነ-ፅሁፍ፣ በአስተዳደር፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂያዊ ፈጠራዎች በኩል ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ስም ተደጋግሞ ሊጠራ መቻሉ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።

የዛሬው እንግዳችን ኢንጂነር ወንድሙ ነጋሽ ይባላሉ። ኢንጂነር ወንድሙ ላለፉት 24 ዓመታት በጀርመንና በእንግሊዝ ያሳለፉ ሰው ናቸው። በአሁኑ ወቅትም በእንግሊዝ የጦር መርከቦች ውስጥ የአደጋ መከላከያ ስርዓትን (Security system) በመሀንዲስነት በመምራት እያገለገሉ ሲሆን፤ ወደኢትዮጵያ ከተመለሱም ጥቂት ሳምንታት ሆኗቸዋል። ባሳለፍነው ቅዳሜ ሚያዚያ 18 ቀን 2006 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ በአእምሮ አስተዳደር ላይ የሚያተኩሩ ሁለት መፅሀፍቶቻቸውን በደማቅ ሥነ-ሥርዓት አስመርቀዋል።

በዚህ ደማቅ የመፅሃፍ ምረቃ ወቅትም ዶክተር ኢ/ር ሳሙኤል ዘሚካኤል ስለመፅሀፉ አጭር ዳሰሳ ሲያቀርቡ በክብር እንግድነት ከተገኙት መካከልም የስነ-አእምሮ ስርጀንና ተመራማሪው ዶ/ር ብርሃኑ ሃ/ሚካኤል፤ በደቡብ አፍሪካና በተለያዩ አገራችን ዩኒቨርስቲዎች በማስተማር የሚታወቁት ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ፤ የናኖ ቴክኖሎጂ ባለሙያው ዶ/ር ኃ/ሚካኤል ደምሴ፤ እንዲሁም የፒስ ኤንድ ግሪን ኢንቪቲሽ አፍሪካ መስራች ከሆኑት መካከል አቶ ታምራት ደገፉ የተገኙ ሲሆን፤ ከመፅሀፉ ሽያጭ ከተገኘው የተወሰነ ገቢ ድጋፍ የተደረገለት የመሰረት በጎ አድራጎት ተቋም መስራችና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ መሰረት አዛን በአደራሹ ተገኝተው ነበር።

“የአዕምሮ አስተዳደር ሞዴል” እና “ፍቅር ምንድነው?” የተሰኙ ሁለት መፅሀፍትን ያበረከቱልን ኢንጂነር ወንድሙ ነጋሽ፤ “አእምሯችንን በአግባቡ መያዝና ማስተዳደር የምንችልበት አስተሳሰብ ከገነባን ህይወት ቀላልና አስደሳች ትሆናለች” የሚል ፅኑ እምነት እንዳላቸው ይገልፃሉ። ኢንጂነር ወንድሙ በትምህርት አለም ካጠኑት ምህንድስና ውጪ በሆነው የሥነ-አእምሮ ጉዳይ ላይ በርካታ ንባቦችን በማድረግ እነዚህን ሁለት መፅሐፍት ለመፃፍ ያነሳሳቸውን ሃሳብ እንዲህ ይገልፃሉ፤ አንደኛውና የመጀመሪያው ስለራሴና ስለሰው ልጅ አእምሯዊ አሰራር ለማወቅ ያለኝ ጉጉት ሲሆን፤ ሁለተኛውና ይበልጥ ትኩረት እንዳደርግ ያስገድደኝ ደግሞ ታላቅ ወንድሜ በአእምሮ ህመም መጠቃቱን ተከትሎ ስለመሆኑ ያስረዳሉ።

ከንባታና ሃዲያ፤ ወላይታ ተወልደው ያደጉት ኢንጂነር ወንድሙ ነጋሽ፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቁት በአሁኑ አጠራሩ የካቲት 25 ትምህርት ቤት ሲሆን፤ እስከ 10ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በሆሳህና ከተማ ተከታትለው፤ የሁለተኛ ደረጃ የመጨረሻዎቹን ክፍሎች ደግሞ አዲስ አበባ በመምጣት በዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። ገና በለጋ የወጣትነት እድሜያቸው የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን በሚያማትሩበት ወቅት በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ግለት ሳቢያ “ኢሀፓ” ተብለው ለሶስት ዓመት ከስድስት ወራት ከበርካታ ወጣቶች ጋር ታስረው እንደነበር ያስታውሳሉ።

በ1975 ዓ.ም የሚወዱትን የፊዚክስ ትምህርት በዩኒቨርስቲ ደረጃ በማታው መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቴክኖሎጂ ክፍለ ትምህርት ውስጥ መማር የጀመሩት ኢንጂነር ወንድሙ፤ እድለኛ ነኝ በሚሉበት አጋጣሚ ከትምህርታቸው ጎን ለጎን በመብራት ኃይል በወቅቱ የንፋስ ስልክ እና የኮተቤ ኃይል ማመንጫ ውስጥ በቴክኒሽያንንት የመስራት ዕድልን አግኝተዋል። ከዓመታት በኋላ ማለትም በ1983 ዓ.ም ወደጀርመን የሚያስገባ የጉብኝት አጋጣሚ ያገኙት ኢንጂነር፤ የወቅቱን ሀገራዊ ሁኔታ አስፈሪነት በማሰብ ለጉብኝት በሄዱባት ጀርመን በዛው ኑሯቸውን አድርገዋል። ከምስራቅው በርሊን ወደምዕራብ በርሊን የተሸጋሩት ኢንጂነሩ፤ በምዕራብ ጀርመን ለሰባት ዓመታት ቆይተዋል።

በወቅቱ አዲስ አገር፤ አዲስ ባህልና አዲስ ማህበረሰብን በማይግባቡበት ቋንቋ መቀላቀል ከባድ እንደነበር የሚያስታውሱት ኢንጂነር ወንድሙ፤ ከሁሉም በላይ ግን ከቤተሰብ ርቀው መኖር ፈተና ሆኖባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ማህበራዊ ትስስሩ ጥብቅ ከሆነበት ኢትዮጵያ ወደጀርመን የሄደ ሰው ክፉኛ ሊፈተን እንደሚችልና በዚያ ማህበራዊ ትስስሩም እጅጉን የላላ እንደነበር የሚያስታውሱት ኢንጂነር ወንድሙ፤ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ዓመታት የቆዳ ቀለም ልዩነቱና የፖሊስ ተደጋጋሚ ጥያቄ አሰልቺ ሆኖባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ያም ሆኖ በትምህርታቸው በመግፋት በተለይም ወደ እንግሊዝ፤ ለንደን ከገቡ በኋላ ነገሮች ተለውጠውና ተሻሽለው እንደነበር ያትታሉ።

አሁን በደረሱበት የመርከብ ደህንነት ስርዓት ምህንድስና ውስጥ በርካታ ዓመታትን ከማሳለፋቸውም በላይ፤ በባህር ላይ ቆይታቸው የማንበብ አጋጣሚው ምቹ እና ሰፊ ሆኖላቸው እንደነበር ይናገራሉ። ራሳቸውን “የሥነ-ፅሁፍ ሰው አይደለሁም” ብለው የሚገልፁት ኢንጂነር ወንድሙ ነጋሽ፤ “ነገር ግን ያነበብኳቸውንና በሚገባ የተረዳኋቸውን በተለይም ከሥነ-አእምሮ ጋር የተያያዘ ነጥቦችን ለሀገሬ ሰዎች ማድረስ ፍላጎቴ ነው” ይላሉ።

“የአዕምሮ አስተዳደር ሞዴል” እና “ፍቅር ምንድነው” በተሰኙት ሁለት መፅሀፍት ለመፃፍ ዋና መነሻ የሆናቸው የታላቅ ወንድማቸው በአእምሮ ህመም መሰቃየት ስለመሆኑ የሚያስረዱት ኢንጂነር ወንድሙ፤ “ሰዎች ለአእምሮ ህመም የሚዳረጉት በአንጻራዊነት ትክክለኛ የሆነን አእምሯዊ አስተዳደርን ባለመከተላቸው ነው” ይላሉ። በቀዳሚው መፅሀፋቸው መግቢያ ላይም፤ “ዛሬ ለቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባውና የተለያዩ የአንጎል ምስል መቅረጫዎች፤ በአንጎል ውስጥ የደም ዝውውር፤ የነርቭ ሴሎችንም (ኒውሮችንም) ሆነ ሌሎች መረጃዎችን ለመቅረፅ አንጎላችን በባህሪያችን ላይ ያለውን ተፅዕኖ፤ እየንዳንዳችን ከቤታችን እስከ ስራችን ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት ለመረዳትና ልዩ ያደረገንን ጥያቄዎች ለመመለስ አስችሎናል” ባይ ናቸው።

በመፅሀፋቸው መግቢያ ላይ ማንበብ የሚችሉ አይኖችን ሁሉ ለንባብ የሚጋብዙ ሲሆን፤ ስለመፅሀፉ ፋይዳም ሲያትቱ፤ ጠቀሜታው ራስን ወደማወቅና ራስን ወደማግኘት የሚያደርስ ስለመሆኑ ይላሉ። ሰዎች ስለራሳቸውና ስለአካባቢያቸው እንዲሁም ስለአእምሯዊ አቅማቸው በአግባቡ መረዳት ከቻሉ አምራችና ጤናማ ህይወትን መምራት ይችላሉ የሚሉት ኢንጂነር ወንድሙ ነጋሽ፤ በመፅሀፎቻቸው ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ የዓላማ ጽናት፣ በራስ መተማመንና ስሜትን መቆጣጠር የሚያስገኙትን ውድ ዋጋ ያስቃኛሉ።

“በአደጉት አገራት በማህበራዊ ኑሮ ትስስር መላላት ምክንያት ሰዎች በአእምሮ ህመም የመጠቃታቸው መጠን ከፍተኛ ቢሆንም፤ ተመጣጣኝና አግባብነት ያላቸው የህክምና ማዕከላት በመኖራቸው የተሻለ ለውጥ ይመጣል” የሚሉት ኢንጂነር ወንድሙ ነጋሽ፤ የአእምሮ ህሙማንን ማቅረብና መንከባከብ ከፍተኛ ለውጥን ያመጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ቤተሰባዊ ተሞክሮአቸውን ተንተርሰው ይናገራሉ።

መዝናናትና ለራስ የሚሰጥ የተመስጥኦ ጊዜ ከአካላዊ እንቅስቃሴ ጋር ሲደመሩ ለሰው ልጆች ፍቱን የሆነ አካላዊና መንፈሳዊ ጤንነትን ለማጎናፀፍ እንደሚረዳ አትኩሮት ሰጥቶ ይናገራል።

በግላቸው መፅሃፍትን ከማንበብ እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር የጋራ ጊዜን ከማሳለፍ በተጨማሪም ስፖርት በመስራትና የተመስጦ (Meditation) ጊዜን እንደመዝናኛ ያገለግሉናል የሚሏቸው ህይወት አዳሽ የዘወትር ተግባሮቻቸው ናቸው።

     በመፅሀፍቱ አንጎላችንን ውስጣዊ ቅርፅ እና የየክፍሎቹን ትንታኔ ማንበብ በሚችለው ሁሉ በሚገባና ቀላል በሆነ መንገድ ስለመፃሀፉ የሚናገሩት ኢንጂር ወንድሙ ነጋሽ፤ በቀጣይነትም በሥነ-አእምሮ ላይ የሚያተኩሩ ተከታታይ መፅሀፍትን ለመፃፍ በዝግጅት ላይ ስለመሆናቸው ጭምር አስረድተዋል።

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
12727 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us