“ፖለቲካ አልወድም እና ሌሎችም” ምን ይዞ መጣ?

Wednesday, 04 July 2018 12:29

 

በይርጋ አበበ

 

ደራሲ በሐይሉ ገብረእግዚአብሔር ከዚህ በፊት ‹‹ኑሮ እና ፖለቲካ›› የሚሉ ባለ ሶስት ቅጽ መጽሃፍት ለአንባቢያን ያቀረበው ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ነው። ከኑሮና ፖለቲካ ቀደም ብሎ ደግሞ ‹‹እኔም ልረሳው ተቃርቤያለሁ›› የሚለውን ‹‹መንታ መልኮች›› የተሰኘ የአጭር ልቦለድ ስብስብ መጽሃፍ በ1997 ዓ.ም አሳትሟል።

በእነዚህ ስራዎቹና ከተለያዩ የህትመት ውጤቶች ላይ በአምደኝነት በሚጽፋቸው ‹‹የወግ›› ጽሁፎች የሚታወቅ ሲሆን፤ በተለያዩ መድረኮች ተጋብዞ የሚያቀርባቸው ወጎችም ታዳሚያንን እየቆነጠጡ አስተማሪዎች ናቸው። ይህ ወጣት ደራሲም በቅርቡ ‹‹ፖለቲካ አልወድም እና ሌሎችም›› የተሰኘ የወግ ሲዲ ለገበያ ለማቅረብ ዝግጅት ላይ ነው። በቅርቡ (ምናልባትም በቀጣዮቹ ሁለት ሶስት ቀናት) ለገበያ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ አዲስ የወግ ሲዲ ዙሪያ ጸሀፊው ለሰንደቅ ጋዜጣ አጠር ያለ ቃለ ምልልስ ሰጥቷል።

 

 

የሲዲው እሳቤ

‹‹ፖለቲካ አልወድም እና ሌሎችም›› በውስጡ ሰባት ወርደ ሰፊ የወግ ጽሁፎችን ያካተተ ሲሆን ሁሉንም ወጎች አድምጦ ለመጨረስ 1፡20 ይወስዳል። ሃሳቡ እንዴት ተጸነሰ ለሚለው ጥያቄ አጠር ያለ ምላሽ የሰጠው ደራሲ በሀይሉ ‹‹በተለያዩ መድረኮች ላይ ያቀረብኳቸው ወጎች ነበሩ። እነዛን ወጎች አድማጮች ስለወደዷቸውና ለሰፊው ህዝብም መድረስ ስላለባቸው ዋጋው አዋጭ ባይሆንም በህዝብ ጥያቄ እንዲታተሙ ሆነዋል›› ብሏል።

ከዚህ በፊት ግጥሞች እንጂ ወጎች በሲዲ ሲታተሙ አይታወቅም። በዚህ ጉዳይ ላይ ሲናገርም ‹‹ከእኔ በፊት በእውቄ (በእውቀቱ ስዩም) ስራዎቹን በሲዲ አቅርቧል ጊዜው ረዘም ስላለ ተዘንግቶ ይሆናል እንጂ። ከበእውቄ በተጨማሪም ደረጀ በላይነህ እንዲሁ ስራዎቹን በሲዲ አሳትሞ ለአድማጭ አቅርቧል። እኔ እስከማውቀው የእኔ ሲዲ ሶስተኛ መሆኑ ነው›› ሲል ተናግሯል። ሆኖም የሲዲ ስራ አድካሚ እንጂ አትራፊ አለመሆኑን ይናገራል።

ፖለቲካ እና በሀይሉ

በቅርቡ ስልሳ ደራሲያን በጋራ ባሳተሙት ‹‹ደቦ›› የተባለ የጋራ መጽሀፍ ላይም ‹‹ከምር ፖለቲካ አልወድም›› ሲል አንድ ጽሁፍ አሳትሟል። ደቦ ላይም ሆነ በግሉ ያሳተማቸው ሶስት መጽሃፍት እና አንዲሱ ሲዲ ላይ ፖለቲካን ያካተቱ ናቸው። ከፖለቲካ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ወጣት ነህ ወይ? ስንል ጠይቀነው ሲመልስም፤ ማንም ሰው ከፖለቲካ ውጭ እንደማይሆን ገልጾ፤ ‹‹ኑሮ በፖለቲካ፤ ፖለቲካም በኑሮ ይገለጻሉ። ከዚህ በተጨማሪም ቀደም ሲል እንደ አዲስ ጉዳይ የመሳሰሉና አሁን ደግሞ ግዮን የመሳሰሉ መጽሔቶች ጋር አብሬ መስራቴ ከፖለቲካው ጋር እንድቆራኝ ሊያደርገኝ ችሎ ይሆናል እንጂ ማንም ከፖለቲካ ውጭ አይደለም። የመጽሔቶቹና ጋዜጦቹ ተጽእኖ ታይቶብኝም ይሆናል›› ይላል።

ከዚህ ቀደም ኑሮና ፖለቲካ በሚለው መጽሀፉ ላይ ‹‹መዋጮ መዋጮ ›› ሲል አንድ መታጥፍ አቅርቦ ነበር። አሁንም በአዲሱ ሲዲው በመንግስት መዋጮ ከሚጠየቅባቸው መስኮች አንዱ የሆነውን ‹‹ኮብል ስቶንን›› የተጠቀመ ሲሆን የሲዲውን ስዕል ትርጉም እንዲነግረን ላቀረብንለት ጥያቄ መልሱን በቀጥታ ከማቅረብ ይልቅ ‹‹ጊዜ እና አድማጭ ይፍታው›› ሲል በአጭሩ መልሷል።

ልማት የተረጋጋ ፖለቲካ ለጸብራቅ ሲሆን በበሀይሉ ‹‹ፖለቲካ አልወድም›› ሲዲ ላይ የሰፈረው የኮብል ስቶን ምስልም ጥራቱን ለተመለከተ ‹‹የኮስሞቲክስ ፖለቲካ ውጤት›› የሆነውን የመንግስትን ‹‹ስንኩል›› የልማት ስራ ለማሳየት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። ሆኖም ደራሲው የስዕሉን ትርጓሜ ለመግለጽ ፍላጎት አላሳየምና ‹‹ትርጉሙ ይህ ሊሆን ይችላል›› የሚባለው ከደራሲው ፈቃድና እውቅና ውጭ ነው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1557 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 922 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us