ቀጣይዋ ኢትዮጵያ በድምጻዊ አቡሽ ስንኞች

Wednesday, 25 July 2018 13:31

በይርጋ አበበ

በቦረና ኦሮሞ ባህላዊ ዘፈኖቹ ራሱን ከአድማጭ ጋር ያስተዋወቀው ወጣቱ ድምጻዊ ከዚህ በፊት በሚሰራቸው የኦሮምኛ ሙዚቃዎች ተወዳጅነትን ያተረፈ ነው። ድምፃዊ አቡሽ ዘለቀ፤ ቋንቋውን ከሚሰሙ ውጭ ባሉ የሙዚቃ አድማጮች ሳይቀር ዘፈኖቹ ከአገሪቱ አንደኛው ጫፍ እስከ ሌላኛው ጫፍ አድማጭን መማረክ ችለዋል። ይህ ወጣት ድምጻዊና የዘፈን ቪዲዮ (ክሊፕ) ዳይሬክተር ሰሞኑን ለአድማጮች የለቀቀው ሙዚቃ ደግሞ ይበልጥ ከሕዝብ ጋር አስተዋውቆታል።

“አነቃን” በሚል ርዕስ አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር የሚያሞግስበት ስራው ኢትዮጵያዊነትን ያነሳ፤ መለያየትን ደግሞ ያወገዘ ስራው ነው። ሙዚቃውን ያቀናበረው ካሙዙ ካሳ ሲሆን፤ ማስተሪንጉን ደግሞ ትልቁ የሙዚቃ ሰው አበጋዝ ክብረወርቅ ሺዎታ አከናውኖታል። ድምጽ ቀረጻውንና ሚክሲንጉን ደግሞ ይትባረክ ክፍሌ ነው ያዘጋጀው። የዚህን ሙዚቃ አብይ ሀሳብ ከዚህ በታች እየከፋፈልን እናየዋለን።

ኢትዮጵያ እና ልጆቿ

‹‹በአንቺ ሰማይ ጥላ ስር ክፉ ደጉን አይተናል

ሌላ እናት አገር የለንም ሲከፋሽም ይከፋናል።

በአንቺ ሰማይ ጥላ ስር የተስፋው ብርሃን ይታየናል

ሌላ እናት አገር የለንም ደስ ሲልሽ ደስ ይለናል›› ሲል ሙዚቃ ይጀምራል።

በዚህ ዘመን ፖለቲከኛው ብቻ ሳይሆን ስፖርተኛውና ዘፋኙ ሁሉ ስለ ወጣበት ብሔርና ስለሚናገረው ቋንቋ ብቻ በሚያስብበት ወቅት ይህ ወጣት ግን ‹‹አንቺን ሲከፋሽ ይከፋናል፤ ደስ ሲልሽ ደግሞ ደስ ይለናል›› ሲል ይናገራል። ኢትዮጵያ ደስ ሲላት ደስ የሚለንም ሆነ ሲከፋት የሚከፋን ደግሞ በምንም ሳይሆን ‹‹ሌላ እናት አገር ስለሌለን ብቻ ነው›› በማለት ሃሳቡን ያስረዳል።

ባለቅኔው ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ፡-

‹‹አገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፤

የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ›› ሲል እንደተቀኘው አቡሽ ዘለቀ በኦሮምኛ ቋንቋም ሆነ አሁን ባወጣው አማርኛ ዘፈኑ ‹‹ስለ አገር አንድነት እና የወገን ፍቅር›› ቢሰብክም የመንግስት እልፍኞች የሚከፈቱት ግን ለእሱ አይነት ሰው ሳይሆን ለጎጠኞች መሆኑ አስገራሚ ሆኗል። አቡሽ ይቀጥላል፤

‹‹አንዱ ከአንዱ ሳያንስ አንዱ ካንዱ ሳይበልጥ

ከኔ ወንዝ አይደለህ ከኔ ወንዝ አይደለሽ፤

ብለን ሳንጣላ ብለን ሳንለያይ

አገር ማለት እኛ እኛ ማለት አገር ብሎ አበሰረን

ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን›› ሲል የሚገልጸው ድምጻዊው የብሔርንና የጎጠኝነትን ካባ ማውለቅ እንዳለብን በዶክተር አብይ አህመድ የተነገረውን መሪ ቃል በማንሳት ነው። ዶክተር አብይ አህመድ የአራት ኪሎውን ወንበር በተረከቡበት ዕለት ‹‹እኛ ኢትዮጵያዊያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ እንሆናለን›› ያሉትን ጉልበታማ አገላለጽ በአድናቆት የሚናገረው አቡሽ ዘለቀ ‹‹ይህ ንግግር ከወንዜነትና ከብሔርተኝነት እንድንወጣ አደረገን›› በማለት ነው።

ጥበብ ማለት ደግሞ ገበያው ምን ይፈልጋል? ሳይሆን አድማጩ ምን ያስፈልገዋል? ብሎ ከዳቦ ከፍ ያለ ስራ መስራት ነው። አቡሽ በዚህ ዘፈኑ ያደረገውም ይህንኑ ነው።

ኢትዮጵያ እና ታሪኳ

የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ምሁራኖቿም ሆኑ ማንኛውም ዜጋ የተስማማበት አይመስልም። በተለይ በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ምስረታ ላይ ያለው አረዳድ ውዥንብር የሚታይበት ሲሆን ይህን ውዥንብር የፈጠሩት ደግሞ የ20ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ እና የ21ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ አገሪቱን የሚገዙ ፖለቲከኞች የፈጠሩት እንደሆነ ምሁራን ይናገራሉ። ድምጻዊ አቡሽ ዘለቀ በዚህ አነቃን ሲል በሰየመው ዘፈኑ ‹ታሪክን እንመርምር ክፉው ሳይሆን በጎውን በዝቶ እናገኘዋለን› ይለናል። ግጥሙ ይቀጥላል፤

‹‹አስተውለን ካየን ታሪክ ሳንረሳ

የአብሮነቱን ገመድ ቋጠሮውን ሳንፈታ

የሚያግባባን ብዙ የሚስማማን ብዙ

ሰፊውን በር ዘግተን ጠባቡን አናንኳኳ

ኢትዮጵያዊነቱ ነው ያስተሳሰረን ጎልቶ ይታይ በቃ›› ሲል ኢትዮጵያ የነበረችበትንና ያለፈችበትን መንገድ መርምሮ ይናገራል።

በመሆኑም አገራችን ያለፈችበት መንገድ ሁሉ እንከን አልባ እና ሁሉንም ያስደሰተ ሆኖ ሳይሆን የሚያግባባን እና የሚያስማማን ብዙ ስለሆነ ጠባቡን በር ከማንኳኳት ሰፊውን በር እንመልከት ይላል። ኢትዮጵዊነት ጎልቶ ከወጣ እኛ እንከበራለን ነገር ግን እርስ በእርስ በብሔርና በዘር በረት ውስጥ ሆነን የምንቀመጥ ከሆነ በዓለም አቀፍም ሆነ በጎረቤቶቻችን ከመናቅ የዘለለ የምናገኘው ነገር የለም። ይህን ደግሞ ቀደም ሲል ዶክተር አብይም ሀዋሳ ላይ ከከተማውና ከሲዳማ ብሔረሰብ ተወላጆች ጋር ባደረጉት ምክክር ተናግረዋል። ‹‹ቀይ ፓስፖርት ይዘን የምንኖር እኛ ኢትዮጵያዊን ፍቅር እንጂ ጥል የትም አያደርሰንም›› ነበር ያሉት።

አቡሽ አላቆመም፤

‹‹ላሚቷ ሳትነጥፍ ሳታጣ እምትግጠው

ሞፈሩም ሳይጠፋ በሬው እሚጎትተው፤

ይቅር እንባባል ተባባሉ እሚለን ሰው

አጥተን ነው እንጂ ቀድሞ ጥላቻው የነገሰው

ከታረሰው ይልቅ እልፍ ነው ያልታረሰው›› ይላል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የውሃ ማማ፣ የዳቦ ቅርጫት፣ የልምላሜ እና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት እንዲሁም የ13 ወር ጸጋ መሆኗን እኛ ብቻ ሳንሆን ጠላቶቻችንና ቅኝ ለመግዛት የቋመጡብን ሳይቀሩ ይናገሩታል። ነገር ግን እንዳለመታደል ሆኖ እኛ ከሀብታችን አልተጠቀምንም። ‹‹ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል›› እንዲሉ በእኛው ሃብት ጠላቶቻችን ከብረውበታል። ይህ የሆነው ደግሞ አቅም በማጣታችን ወይም ስንፍና ስለተጫነን ሳይሆን ‹‹ይቅር ባለመባባላችን ነው›› ይላል ወጣቱ ድምጻዊ አቡሽ ዘለቀ።

ዶክተር አብይ አህመድ ‹‹ኢትዮጵያ ማህጸነ ለምለም ናት›› እንዳሉት ድምጻዊውም ‹‹ላሚቱ ሳትነጥፍ የምትበላውም ሳይጠፋ፣ ሞፈሩም ሳይታጣ፣ የምናርሰው መሬትም ሆነ የምናርስበት በሬ ሳናጣ የምንጣላበት ምክንያት አንድ እና አንድ ነው እሱም ‹‹ይቅር ተባባሉ የሚለን ሰው ስለጠፋ ነው፤ ጥላቻ የነገሰብን›› በማለት የቁሳዊ ድህነታችን መጀመሪያው አእምሯዊ ድህነታችን እንደሆነ ያብራራል።

የመደመር አድማስ እና የወደፊቷ ኢትዮጵያ

አቡሽ ዘለቀ በዚህ ዘፈኑ ዶክተር አብይ ይዘውት የመጡት የመደመር ጥሪ እዚሁ አገር ቤት ተወስኖ የቀረ አይደለም ይላል። ቀይ ባህርን ተሻግሮ በአስመራው ቤተመንግስት ያሉትን ፈገግታ የራቃቸውን የ72 ዓመት ፖለቲከኛንም የደመረ ጥሪ ነው ሲል ይገልጸዋል።

ሃሳቡን በግጥም፤

‹‹በሰሜን ደቡቡ በምስራቅ ምዕራቡ በሁሉም ተሰማ

የመደመሩ ጥሪ ከእኛም ተሻገረ ተከዜንም አልፎ ሄደ ገሰገሰ

ቀይ ባህርን አቋርጦ ከአስመራ ደረሰ

ያ የጥላቻ ግንብ በፍቅር ፈረሰ›› በማለት ለ20 ዓመት የተለያዩ ቤተሰቦችን ስላገናኘው የሰላምና የእርቅ መንገድ ይናገራል።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በፈጠሩት ጦርነት ህያዋንን ወደ መቃብር ያወረደ ቢሆንም ያ ሁሉ አልፎ በፍቅር መደመሩ የተሻለ እና አማራጭ የሌለው መንገድ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተናግረው ነበር። ዘፋኙ መደመር እያለ ያዜመውም ይህን አንድነትን እና ወደፊት በአብሮነት እንኑር እያለ እንጂ ሰሞኑን እንደምናያቸው ዘውጌ ዘፋኞች ‹‹የእኔ ወንዝ ሞላ የአንተ ወንዝ ፈሰሰ›› እያሉ ለአገር አንድነት ሳይሆን መለያየትን ከሚሰብኩት ፈጽሞ የተለየ ነው።

ነገር ግን ይህ አሁን የተጀመረው የፍቅር ጉዞ ሊደናቀፍ እንደሚችል ብዙዎች ስጋት ቢያድርባቸውም አቡሽ ዘለቀ ግን ‹‹ማንም አይመልሰንም›› ሲል በእርግጠኝነት ተስፋውን ይናገራል። በመጨረሻው የዘፈኑ ግጥም እንሰናበታለን።

‹‹ማነው ማነው ማነው እሚመልሰን?

ከዚህ ቀና መንገድ ከዚህ የፍቅር ጉዞ

ወደፊት ነው እንጂ እጅ ለእጅ ተያይዞ።

እንደ ዐለት እንጠንክር ይብዛ አንድነታችን

ዛሬም ነገም ሁሌም ትኑር ኢትዮጵያችንን

ዛሬም ነገም ሁሌም ትኑር አገራችን››


ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
21 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 76 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us