የታምሩ ፕሮዳክሽን እና የኢሬቴድ ውዝግብ

Wednesday, 14 May 2014 13:21
  • “አሸናፊው እኔ ነኝ።” (አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ)
  • “ሌሎች ተወዳዳሪዎች አሻሽለው ካቀረቡት የድራማ ታሪክ አኳያ

  • ዝቅ ያለ ሆኖ በመገኘቱ አልተመረጠም” (ኢሬቴድ)

 

ከ23 ዓመታት ላላነሰ ጊዜ በኢትዮጶያ የፊልምና የድራማ እንቅስቃሴ ውስጥ ስሙን ከምንጠራለት ሰው መካከል አንዱ የሆነውና በማስታወቂያ ስራዎቹም ተዘውትሮ የሚሰማው አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ፤ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት (ኢሬቴድ) አንዳንድ የመዝናኛ ክፍል ኃላፊዎች “አሸናፊ” የሆነ ስራዬን በመጣል ግልጽነት በጎደለው አሰራር በድለውኛል ሲል አቤቱታውን ለፌዴራል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን እንዲሁም ለተቋሙ የበላይ ኃላፊዎች ማቅረቡን ባሳለፍነው ሳምንት ገልጿል። ይህን የገለፀው ግንቦት 1 ቀን 2006 ዓ.ም በአምባሳደር ሆቴል በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነው።

“ጉዳዩ አሳሳቢና የስራ መንፈስንም የሚጎዳ ነው” ሲል የገለፀው አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ በመግለጫው ለተገኙት ጋዜጠኞች በሙሉ ከኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት የተፃፉለትን ደብዳቤዎችና በቃል የተለዋወጣቸውን ሃሳቦች ከነምሬቱ በዝርዝር አብራርቷል።

በአሁኑ ወቅት በመታየት ላይ በሚገኘው “ሰው ለሰው” ድራማ ውስጥ የነበረውን ሚና በተመለከተ ከደራሲነት ስሙ ወደመነሻ ሃሳብ የሄደበት አካሄድ ብዙ አወዛጋቢ ጉዳዮች የነበሩት ስለመሆኑ በመድረኩ ከጋዜጠኞች በቀረቡለት ጥያቄ ጋር ምላሽ የሰጠው አርቲስት ታምሩ፤ ለዓመታት የደከምኩበትን የራሴን የሴራ አተናተን ጭምር ይዤ በሚገባ ፕሮፖዛል አቅርቤ “አሸናፊ” የሆንኩበትን የቲቪ ድራማ ወደጎን በማድረጋቸው የቴሌቪዥን ጣቢያውን ሳይሆን በውስጥ የሚገኙትንና ስነ-ምግባር የጎደላቸውን አንዳንድ አካላት ማጋለጥ ይኖርብናል ብሏል።

በነሐሴ ወር 2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ለተቀዳሚ ጣቢያው (ቻናል አንድ) ለ52 ሳምንታት የሚቆይ ተከታታይ ድራማ በገቢ መጋራት (ኮሚሽኒንግ) አሰራር በትብብር ለመስራት ባወጣው የውድድር ጨረታ ማስታወቂያ መሰረት ታምሩ ፕሮዳክሽንን ጨምሮ 52 ፕሮዳክሽኖች ለውድድር ቀርበው ነበር። በአየር ላይ ያሉትን ተከታታይ ድራማዎች የመጠናቀቂያ ጊዜያቸው ሲያበቃ በቦታቸው ለመተካት ቀደሞውኑ የተሻለ ስራ ይዞ ለመቅረብ ሲጥር እንደነበረ የገለፀው “ታምሩ ፕሮዳክሽን” በወጣው ጨረታ መሰረት ፕሮፖዛል ማስገባቱን ያትታል።

ተወዳዳሪ ፕሮዳክሽኖቹ ያስገቡትን የጨረታ ውጤት ሲጠብቁ ይፋ ይሆናል ከተባለበት የአምስት ወራት ጊዜን ዘግይቶ በየካቲት ወር መጨረሻ አካባቢ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት አድራሻ እንዲገኙ ተደረገ። በዚህም መሰረት ሃምሳ ሁለቱም ተወዳዳሪ ድርጅቶች በተገኙበት አዳራሽ ከጣቢያው ኃላፊዎች በተሰጠው ማብራሪያ መነሻነት ዘጠኝ ፕሮዳክሽኖ የተሟላ ፕሮፖዛል አለማቅረባቸውን ተከትሎ ገና ከጅምሩ መሰናበታቸው ሲገለፅ፤ ከቀሪዎቹ 42 ፕሮዳክሽኖች ውስጥ ደግሞ 34ቱ የአፅመ-ታሪክ አቀራረብ (Synopsis presentation) እና የታሪክ አካሄዳቸውን በመገምገም ሳያልፉ መቅረታቸው ተገልጿል። የተቀሩት ስምንት ፕሮዳክሽኖች ግን የታሪክ ጭብጥ (20በመቶ)፤ የታሪክ ግጭት (20በመቶ)፣ የታሪኩ ገዢነት (15በመቶ)፣ የገፀ-ባህሪያት አሳሳል (15በመቶ)፣ መቼት (10በመቶ)፣ የድራማው ደራሲ ብቃትና ልምድ (10በመቶ) እናየድራማው ዳይሬክተር ብቃትና ልምድ (10በመቶ) በሚሉ መስፈርቶች መመዘኛነት ተወዳድረው እንደነበር ለጋዜጠኞች የሚገልፅው አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ፤ ከስምንቱ ፕሮዳክሽኖም አራቱ ማለትም ታምሩ ፕሮዳክሽን፣ ሮኆቦት ፕሮዳክሽን፣ ዳኒ ፕሮዳክሽን እና ሚልክዌይ ፕሮዳክሽን አሸናፊዎቹ መሆናቸው ለመድረኩ ተገለፆ ነበር ይላል።

“ለአንድ ውድድር አራት ተወዳዳሪዎች አንደኛ ሊወጡ የሚያስችል ስነ-አመክኗዊ አካሄድ ባለመኖሩና በደፈናው አራት አሸናፊዎች መባላችን ጥርጣሬ ውስጥ ስለከተተኝ ያገኘነው ነጥብና ደረጃችን በግልፅ እንዲነገረን ስል በመድረኩ ፊት ጥያቄን አቅርቤ ነበር” የሚለው አርቲስት ታምሩ፤ የጣቢያው ኃላፊዎችም ከአፍታ ምክክር በኋላ ታምሩ ፕሮዳክሽን በ79 ነጥብ አንደኛ ደረጃ፤ ሮኆቦት ፕሮዳክሽን በ78 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ፤ ዳኒ ፕሮዳክሽን በ77 ነጥብ ሶስተኛ እንዲሁም ሚልክዌይ ፕሮዳክሽን በ75 ነጥብ አራተኛ ደረጃን እንደያዘ በይፋ ተነግሮናል ይላል። ይህም ሆኖ ይህ ውጤት በወረቀት ያልተገለፀና አፋዊ መሆኑን ልብ በሉልኝ ያለው አርቲስቱ፤ ውጤቱ መደበኛ አካሄድን ተከትሎ በደብዳቤ እንዲገለፅ ቢጠይቁም በተለያዩ ምክንያቶች አንደኛ የወጣንበትን ማስረጃ በደብዳቤ ሳይሰጡን ቀርተዋል ባይ ነው።

የጣቢያው የመዝናኛ ክፍል ኃላፊዎች በአንደበታቸው አንደኛነቱን ያረጋገጡለት ፕሮፖዛል “የውድድር መንፈስን” ለመፍጠር ያህል ተብሎ ከተሰነዘሩ የማሻሻያ ሃሳቦች በኋላ በከፍተኛ ድካም ያቀረብነው ፕሮፖዛል ምስጢራዊነቱ ካበቃና ያሸነፍንበት ጠንካራ ጎኖች ተለይተው ከታወቁ በኋላ በድርጅቱ ታሪክ ታይቶና ተ ሰምቶ በማይታወቅ መልኩ ከውጤት በኋላ ውድድር በማድረግ ሚዛን በማይደፋ ምክንያት ከአሸናፊነታችን መሰረዛችንን የሚያበስር ደብዳቤ ሚያዚያ 24 ቀን 2006 ዓ.ም በኮሚሽኒንግ ዳይሬክቶሬት ቢሮ ኃላፊው በአቶ ገብረአምላክ ተካ በኩል ተፈርሞ እንዲደርሰን መደረጉ አግባብነት የሌለው ነው ሲል ይሞግታል።

አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ ይህን ይበል እንጂ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት በቁጥር ቴ14/14/27 በላከው ደብዳቤ ፕሮዳክሽኑ የወደቀበትን ምክንያት ሲያስረዳ፤ “ለአራቱ ተወዳዳሪዎች በተሰጠው እኩል እድል ከመጨረሻ ዙር ተወዳዳሪ ድራማዎች መካከል በታሪክ አካሄድ፤ ሴራና ግጭት አፈጣጠር፣ በገፀ-ባህሪያት አሻሻል እንዲሁም በያዘው ጭብጥና መቼት ድርጅታችሁ ያቀረበው ታሪክ ሌሎች ተወዳዳሪዎች አሻሽለው ካቀረቡት የድራማ ታሪክ አኳያ ዝቅ ያለ ሆኖ በመገኘቱ ያልተመረጠ መሆኑን እንገልጻለን” ሲል ይዘረዝራል።

ይህም በመሆኑ በመዝናኛ ፕሮግራሙ ጨረታ ውጤት መሰረት ከቀሩት አራት እጩዎች ውስጥ ሮኆቦት ፕሮዳክሽን እና ሚልክዌይ ፕሮዳክሽን ማለፋቸው ከአንዳንድ ምንጮች ተሰምቷል። ይህን የጣቢያውን ውጤት ተከትሎ ታምሩ ፕሮዳክሽን አለኝ የሚለውን ቅሬታ በግልፅ ለሚዲያ ባለሙያዎች አስታውቋል።

“ታምሩ ፕሮዳክሽን” ይሄን ቅሬታውን ተከትሎ ስላከናወናቸው ተግባራት በሰጠው ምላሽም፤ “በመጀመሪያ ጉዳዩን ለኢ.ሬ.ቴ.ድ. የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሬድዋን ሁሴን አቤቱታችንን አቅርበናል። እሳቸውም ጉዳዩ ተጣርቶ መፍትሄ እንደሚሰጡን ቃል ገብተውልናል” ብሏል። በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ለአቶ ብርሃነ ኪዳነማሪያም በዝርዝር ደብዳቤ አቤቱታችንን በማቅረባችን እርሳቸውም በቅንነት ጉዳያችንን ተመልክተው ሚዛናዊ ፍትህን እንደሚሰጡን ቃል ገብተውልናል” ይላል። ሶስተኛውና በሚዲያው አባላትም ዙሪያ መነጋገሪያ የሆነው ሃሳብ ደግሞ “ታምሩ ፕሮዳክሽን” የጣቢያው የመዝናኛ ክፍል ባልደረቦች (በተለይም አንዳንድ ኃላፊዎች) ሕግና ስርዓትን በተከተለ መንገድ ስራቸውን አልሰሩም ብሎ ስለሚያምን፤ የጨረታ ሂደቱ ሚዛናዊ እንዳልነበርና ግልፅነት የሚጎለው በመሆኑ ለስነ-ምግባር ግድፈቶች የተጋለጠ ነው ብለን በመጠራጠራችን ለፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ቅሬታችንን አሰምተናል። ተቋሙም ቅሬታችንን ተቀብሎ በምርመራ ሂደት ላይ ይገኛል” ሲል ገልጿል።

በአምባሳደር ሆቴል የተጠራውን ጋዜጣዊ መግለጫ ተከትሎ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የመጡ ባለሙያዎች ለአርቲስት ታምሩ ብርሃኑ የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበውለታል። ከነዚህም ውስጥ ቀዳሚው ተፈፅሞብኛል ላልከው በደል ወደክስ የምትሄድ ከሆነ በቂ ማስረጃዎች አሉኝ ብለህ ታምናለህ? የሚለው አንዱ ሲሆን አርቲስቱም ሲመልስ፤ “በሕግ ስነስርዓት አካሄድ ሰው አንዱና ትልቁ ምስክር ነው ብለን እናምናለን። ሁለተኛው ቃለ ጉባኤያቸው በራሱ የሚናገር ይሆናል። ይህ በምርመራ ክትትል ላይ ያለ ጉዳይ ነው” ያለ ሲሆን በቀጣይም ከኢቲቪ ሌላ አማራጭ ማፈላለጉ አስፈላጊ ነው በሚል በተነሳው ሀሳብ ላይ፤ “አማራጭ ማየት አስፈላጊ መሆኑን ቢታመንም ረጅም እድሜ ያስቆጠረና ብዙ ተመልካችን ያፈራ ጣቢያ በመሆኑ እንጂ በርካታ አማራጮችም ስለመኖራቸው እናውቃለን” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ሌላው ከጋዜጠኞች ተነስቶ የነበረው ጥያቄ ውጤታችሁ ይፋ ከሆነ በኋላ ካንተ ስራ ሃሳብ ተወስዶ ላለመሰራቱ ምን መተማመኛ አለህ? በሚል ለተነሳው ጥያቄ አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ ሲመልስ ደግሞ ደጋግሞ፤ “ምንም መተማመኛ የለኝም” ሲል መልሷል። ለዚህም በቀደመው በ“ሰው ለሰው” ድራማ ሂደት ምንያህል የስም ሽሚያ እንደገጠመው አስታውሷል።

ከሌሎቹ አራት ዕጩ አላፊዎች መካከል ቅሬታ አለኝ ብለህ ወደመድረክ የመጣኸው አንተ ብቻ ነህ፤ ይህ ለምን ሆነ? የሚል ጥያቄ የተቀበለው ታምሩ፤ “እኔ ራሴን አውቃለሁ፤ በስራዬም እርግጠኛና ልበ ሙሉ ነኝ” ሲል አስረግጦ ይናገራል።

ይህ የኢሬቴድ ውጤት ይፋ ከሆነ በኋላ ታምሩ ፕሮዳክሽን ወድቋል ከተባለ አንደኛ ወጥቶ ያለፈው ታዲያ ማን ነው? የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች የቀረበለት አርቲስቱ፤ “እውነት ነው አንደኛ የወጣው ታውቋል። እኔ ደብዳቤውን ስወስድ ሁለት አሸናፊዎች እንዳሉ ታውቀዋል። ነገር ግን ከሁለቱም ተወዳዳሪዎች እኔ አንደኛውን መናገር አይገባኝም። ምክንያቱም አሸናፊው እኔ ነኝ። አንደኛ የወጣሁት እኔ ነኝ። እያልኩ ስለሆነ እገሌና እገሌ አሸንፈዋል አልልም። ምክንያቱም ያሸነፍኩት እኔ ስለሆንኩ” ሲል በቁጭት የተሞላ ምላሹን ሰጥቷል።

     በስተመጨረሻ የተነሳው ጥያቄ ደግሞ የኢቲቪን የመዝናኛ (በተለይም የድራማ አገማገም ሂደት) የሚመለከት ነበር። በመጀመሪያ አንደኛ የተባለው ያንተ ድራማ ውድቅ ሆኖ ሌለው በሁለተኛ ዙር ውድድር እንዲያልፍ ከተደረገ፤ ኢቲቪ መሰል የዙር ውድድሮችን ከዚህ ቀደም ያከናውን ነበር ወይ ተብሎ የተጠየቀው አርቲስት ታምሩ “እኔም በሰራሁበት አጋጣሚም ሆነ ሌሎች ወዳጆቼ በሰሩበት አጋጣሚ እንደዚህ በሁለት ዙር የሄደበት አጋጣሚ የለም። ይህ አዲስ አሰራር ነው” ሲል መልስ ሰጥቷል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
11439 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us