“ተመሳሳይ ገፀ-ባህሪያትን መደጋገም በተዋናዩ ላይ ተፅዕኖ አለው”

Wednesday, 21 May 2014 12:41

ሚኪ ተስፋዬ

 

“የምሁሩ ፍቅር” እና “ጓደኛሞቹ” በተሰኙት የቴአትር ስራዎች ብዙዎች ያውቁታል። አዲስ አበባ ተወልዶ ዲላ ያደገው ይህ ተዋናይ በዚህ ሳምንት ተመርቆ ለዕይታ በቃውን “ባጣ ቆዩኝ” ፊልምን ጨምሮ እሾሃማ ፍቅር፣ ካምፓስ፣ መስዋት፣ ገዳማዊቷ፣ የጥፋት ውሃ፣ የሞሪያም ምድር፤ የታሰረ ፍቅር፣ ያለሴት እና ኬኮሮን የተሰኙ ፊልሞች ላይ ተውኗል። በዲላ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ “ፅናት” በተሰኘ ቴአትር ክበብ ውስጥ መልካም የሚባል ተሳትፎ የነበረው ይህ የዛሬው የመዝናኛ አምድ እንግዳችን ፀሐፊና ተዋናይ ሚኪ ተስፋዬ ነው። ገና በአፍላ እድሜው “ሹመት” እና የተሰኘ የሬዲዮ ድራማ እና “የዶክተሩ ልጅ” የተሰኘ የቲቪ ድራማ ፅፎ ለህዝብ አቅርቧል። ወደትወናው አለም ለመግባት መሰረቱን የሰጡኝ መምህራኖቼ የሮኖቦት ፕሮዳክሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ኃይሉ ከበደ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቴአትር ጥበባት መምህሩ ተሻለ አሰፋ ናቸው ከሚለው የዛሬው እንግዳችን ጋር ይህን የመሰለ ቆይታ አድርገናል።

ሰንደቅ፡- ብዙዎች በትወናው ብቻ ነው የሚያውቁህ እስቲ የፃፍካቸውን ስራዎች በማስታወስ እንጀምር?

ሚኪ፡- መፃፍ የጀመርኩት ገና ዲላ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ነው። ትዝ ይለኛል የ9ኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ አሁን የሮኖቦት ፕሮዳክሽን ባለቤት የሆኑት አቶ ኃይሉ ከበደ በስራ አጋጣሚ ወደዲላ ከተማ መጥተው ወጣቶችን በቴአትር ሲያሰለጥኑ ከመጀመሪያዎቹ ሰልጣኞች አንዱ ነበርኩ። “ሹመት” የተሰኘ የሬዲዮ ደራማና “የዶክተሩ ልጅ” የተሰኘ የቲቪ ድራማ ፅፌ ነበር። ይህ ከሆነ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴአትር አርት መምህር የነበረው ተሻለ አሰፋ በድጋሚ ሌላ ስልጠና ሊሰጠን ወደዲላ ሲመጣ የመመረቂያ ቴአትራችን የፃፍኩት እኔ ነበርኩ፤ ርዕሱም “እሌኒና መንትዮቹ” ይሰኛል። ከዚያ ቀደም ብሎም የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት መነሻ በማድረግ በአለም ላይ ለጦርነት ማብቃት መፍትሄ ይዟል ብዬ ያሰብኩትን “አዲስ ሕግ” የተሰኘ ቴአትር ፅፌ ነበር ግን በወቅቱ ተገምግሞ ሳያልፍ ቀርቷል። በስራዎቹ ጥሩ ምላሽ በማግኘቴ የሞራል ስንቅ ሆኖኛል ማለት እችላለሁ።

ሰንደቅ፡- በመጀመሪያ ስራዎችህ ያገኘኸው ተቀባይነትና ወደፕሮፌሽናል መድረክ የመጣህበት ሂደት ምን ይመስላል?

ሚኪ፡- የሚገርምህ መፃፍ እንደምችል እርግጠኛ የሆንኩት ተሻለ አሰፋ አሰልጥኖን ለመመረቂያ የሰራነውን “እሌኒና መንትዮቹ” የተሰኘ ቴአትር የዲላ ህዝብ ተመልክቶት ጉድ ካለ በኋላ ነው። እሱን ቴአትር በድጋሚ ፅፌው ወደአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር አዳራሽ ለግምገማ አስገብቼው ነበር። ገምጋሚዎቹ ሃሳቡን ቢወዱትም ከኔ የመጣ ስለመሆኑ ሊያምኑኝ አልቻሉም። ይሄ ስራ የሶሲዮሎጂ ወይም የሳይኮሎጂ ዕውቀት ካላቸው ሰዎች የሚመነጭ ነው ብለው ነገሩኝ። ቴአትሩ ሃሳቡ ጥሩ ሆኖ ተመልካች ይከብደዋል፤ ፍልስፍና የሚበዛበት በመሆኑ አያዝናናም፤ ገበያም አያስገኝም በሚል አላሳለፉትም። እነሱ ባያሳልፉትም ለኔ ግን አቅሜን ስለጠቆመኝ በጣም ነበር ደስ ያለኝ። በመቀጠል ግን “ሙስና” ተሰኘችውን የ15 ደቂቃ የቲቪ ድራማ ጽፌ ራሴ ተውኜ ነበር። የሚገርመው በራሴ ልብስ ስለነበረ የምተውነው ድራማው ከታየ በኋላ ሰዎች መንገድ ላይ ሲያዩኝ በገፀ- ባህሪው ስም ይጠሩኛል።

ሰንደቅ፡- ከዚህ ሁሉ በኋላ የራስህ ድርሰትና ትወና በብሔራዊ ቴአትር መድረክ ያመጣኸው “የምሁሩ ፍቅር” ነበር ማለት ነው?

ሚኪ፡- “የምሁሩ ፍቅር” ዕድለኛ ስራ ነው። ድርሰቱ ከትንሽ ፅሁፍ ተነስቶ እያደገ የመጣ ቴአትር ነው። “የምሁሩ ፍቅር” የውስጥና የውጪ ግለሰባዊ ግጭትን በአስቂኝ መልኩ ያሳየሁበት ስራ ነው። በተመልካቹ በጣም አሪፍ ምላሽ ያገኘና እኔንም ከትላልቅ ሰዎች ጋር ያስተዋወቀኝ ስራዬ ነው ማለት እችላለሁ።

ሰንደቅ፡- “በምሁሩ ፍቅር” ቴአትር ላይ የምትተውነው ዋና ገፀ ባህሪይ በአንተ ላይ ተፅዕኖ አሳድሮ ነበር ማለት ይቻላል። የሚያውቁህ ሰዎች ቴአትሩ በሚታይበት ወቅት ሚኪና ገፀባህሪው እየተመሳሰሉ ነበር ሲሉ ሰምቻለሁ ምላሽህ ምንድነው?

ሚኪ፡- ገፀ-ባህሪው አቶ መኳንንት ይባላሉ። ሰውዬውን የሳልኳቸው በህይወት ከማውቃቸው ሁለት ሰዎች ተነስቼ ነው። ውስጣዊውን ባህሪ ከአንደኛው ሰው ውጪያዊውን እንቅስቃሴና አነጋገር ደግሞ ከሌላ ሰው ወስጄ የሰራዋቸው ገፀ ባህሪይ ናቸው። ነገር ግን በግል ህይወቴ ላይ ተፅዕኖ አልፈጠረብኝም። በርግጥ ከቴአትሩ በኋላ ብዙዎቹ የሚጠሩኝ አቶ መኳንንት እያሉ እንደነበረ አስታውሳለሁ። ይህ የተለመደ ነው ለምሳሌ “ጓደኛሞቹን” ያየ ሰው የሬሳ ሳጥን ሻጩን አስታውሶ “ካስሽ” ብሎ ቢጠራኝ አይገርምም አይደል? ተመልካች በገፀ-ባህሪው ልክ ሲያስብህ እንደዚያ ሊጠራህ ይችላል ብዬ አስባለሁ።

ሰንደቅ፡- ከሰራሃቸው የቴአትር ገፀ-ባሪያት ላንተ አይረሴዎቹ የትኞቹ ናቸው?

ሚኪ፡- በፕሮፌሽናል መድረክ ከስራሁዋቸው ቴአትሮች ሁለቱ አሁን ድረስ ደስ ይሉኛል። አንደኛው “የምሁሩ ፍቅር” ላይ ያሉት አቶ መኳንንት ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ ጓደኛሞቹ” ላይ ያለው ካሳ ናቸው። ለምን መሰለ ሁለቱ ገፀ-ባህሪያት በፍፁም የማይገናኝና የተራራቁ በመሆናቸው ነው።

ሰንደቅ፡- ከመድረክ ስራዎች ወደፊልም ስንመጣ ያንተ የመጀመሪያ ስራህ የቱ ነው?

ሚኪ፡- የመጀመሪው የፊልም ስራዬ “እሾሃማ ፍቅር” ይሰኛል። ከዚያ በኋላ ካምፓስ፣ መስዕዋት፣ ገዳማዊቷ፣ ኬብሮን፣ የሞሪያም ምድር፣ ያለሴት፣ የጥፋት ውሃ፣ የታሰረ ፍቅር እና አሁን ደግሞ “ባጣ ቆዩኝ” ላይ ተሳትፌያለሁ። ከዚህም በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘረሰናይ ብርሃነ የተሰራ “ድፍረት” የተሰኘ ፊልም ላይ ተውኛለሁ። በነገራች ላይ ይሄን ፊልም ታዋቂዋ ተዋናይት አንጄሊና ጁሊ ነች ፕሮዲዩስ ያደረገችው። አሁንም ያልወጡና እየሰራኋቸው ያሉ ፊልሞች አሉ።

ሰንደቅ፡- በርከት ያሉ ፊልሞች ላይ እንደመተወንህ ፊልም ለመፃፍ አላስብክም?

ሚኪ፡- ብዙ ጊዜ አስባለሁ። ነገር ግን ፊልም የገንዘብንም አቅም ጭምር የሚጠይቅ በመሆኑ ነው ትንሽ የዘገየሁት። ፊልም ሃሳብህን ለመግለፅ ትልቅ መሳሪያ ነው። በፅሁፍ እየሞከርኩ ነው ወደፊት የምናየው ይሆናል። ድርሰትን በተመለከተ ግን “ከምሁሩ ፍቅር” በኋላ የፃፍኳቸው ሁለት ቴአትሮች አሉኝ። አንዱ ቀደም ብዬ የነገርኩህ “ህሌኒ እና መንትዮቹ” የተሰኘ ነው አሁን “የምሁሯ ፍቅር” ብዬ ይዤው እመጣለሁ። ሌሎች ሁለት የአዋቂዎች ቴአትር እና ሁለት የህጻናት ቴአትሮችን ለመስራት በሂደት ላይ ነኝ።

ሰንደቅ፡- “የምሁሩ ፍቅር” ስለተወደደልህ ነው “የምሁሯ ፍቅር” ብለህ ርዕሱን ለመቀየር የፈለከው፤ ተመልካችስ አይምታታብህም?

ሚኪ፡- አይደለም! ሁለቱም ራሳቸውን የቻሉ ታሪኮች ናቸው። ተመልካቹ እንዳይምታታበት ማስታወቂያውን በአግባቡ እንሰራለን ብዬ አስባለሁ።

ሰንደቅ፡- በዚህ ሳምንት የተመረቀው አዲስ ስራ “ባጣ ቆዩኝ” ፊልም ነው። የትወና ዕድሉን እንዴት አገኘኸው?

ሚኪ፡- “ባጣ ቆዩኝ” የባለሙያ ፊልም ነው። ሰለሞን ጋሻው በጣም የማደንቀው ፀሐፊ እና ዳይሬክተር ነው። አብሯቸው የሰራቸውም ሰዎች ልምድና ዕውቀት ያላቸው ናቸው። ትወናው ላይ የተሳተፍኩት “ካስቲንግ ዳይሬክተሩ” ኤርሚያስ ይባላል፤ መርጦኝ ነው። በፊልም ፅሁፉ መሰረት ሰው ሲፈልግ ነው እኔን አግኝቶ የተመረጠው። ባይገርምህ የገፀ-ባህሪያቱ ስብዕና ብቻ ሳይሆን አካላዊ ገፅታም ቀድሞ በፅሁፍ ቀርቦለት ነበር፤ ከዚያ በመሳት ነው ለኔ የተሰጠኝ። በነገራችን ላይ ዳይሬክተሩ ሰለሞን ጋሻው አብሮን ብዙ ለፍቷል፤ ምናልባት በፊልሙ ውስጥ ጥሩ ነገር ከታየ የተዋናዮቹ ብቃት ብቻ ሳይሆን የእሱ ልፋትና ውጤትም ነው።

ሰንደቅ፡- ከዚህ በኋላ ምን አይነት ገፀ-ባህሪን መተወን ትመኛለህ?

ሚኪ፡- ሁሌ የሚገርመኝን ነገር ነው የጠየከኝ። ብዙዎቹ በአንድ ገፀባህሪይ ከወደዱህ በዛ ገፀ ባህሪ ብቻ እየፈለጉ ያሰሩሃል። አሁን ከሰራሁት “ባጣ ቆዩኝ” ውጪ ብዙዎቹ የሰራኋቸው ተመሳሳይ ገፀ ባህሪያት ናቸው። አብዛኞቹ በከፋ ሁኔታ ውስጥ አልፈው ክፉ የሆኑ ገፀ ባህሪያት ናቸው የሚመጡልኝ። እሱ ነገር በግል ህይወትህ ራሱ በጣም መጥፎ ነው። ተሳሳይ ገፀ-ባህሪያትን መደጋገም በተዋናይ ላይ ተጽዕኖ አለው። ሳታስበው የምትሰራቸው ተደጋጋሚ ገፀባህሪያት ተጽዕኖ ያሳድሩብሃል። የሰው ልጅ በተወሰነ ደረጃ ሜካኒካል ነው ብዬ አምናለሁ። አንድን ባህሪይ ስትደጋግመው ጥሩ አይደለም። አሁን ሳስበው የራሴን ድርሰት ካልሰራው በስተቀር እንደ “ባጣ ቆዩኝ” አይነት ፊልምና አዘጋጅን ለማግኘት የሚቆይ ይመስለኛል። ለምሳሌ አንድ ጥሩ ነገር ልንገርህ “የምሁሩ ፍቅር”ን ስሰራ ማንያዘዋ እንዳሻው አየኝ። ከዚያ ለጓደኛሞቹ” ቴአትር ጠቆመኝ። ሁለቱ ቴአትሮች ላይ ያሉት ገጸ ባህሪያት እኮ በጣም የሚለያዩ ናቸው። በዚህ አጋጣሚ ዳይሬክተሯ ገነት አጥላው ብዙ ደክማብኛለች ይሄን አስታውሳሁ። እናም እስካሁን ከሰራኋቸው የተለያየ ገፀ-ባህሪን መጫወት እፈልጋለሁ። በአካባቢዬ ብዙ ሰዎች አሉ እነሱን ወይም ሰው እንዲህ ቢሆን ብዬ የማልመው ህልም አይነት ሰው አለ መስራት የምፈልገው ያንን አይነት ገፀ ባህሪይ ነው።

ሰንደቅ፡- አብረሃቸው ልትሰራ የምትመኛቸው አንጋፋ ተዋንያን አሉ?

ሚኪ፡- በጣም ብዙ አሉ። በተለይ የቴአትር ባለሙያዎች አሉ። ሽመልስ አበራ አንዴ “የሚስት ያለህ” ላይ አጋጣሚውን አግኝቼ ነበር። በስራ መደራረብ ምክንያት ሳይሆንልኝ ቀረ። ከዚያ ውጪ ግን ከአለማየሁ ታደሰ፣ ከጌትነት እንየው፣ ከፍቃዱ ተ/ማሪያም፣ ከሃይማኖት አለሙ፣ ከሙለአለም ታደሰ ፣ ሀረገወይን አሰፋ፣ ከኤልሳቤጥ መላኩና ተፈሪ አለሙ፣ አበበ ባልቻ ግሩም ዘነበና ፈለቀ አበበ ጋር ብተውን በጣም ደስ ይለኛል።

ሰንደቅ፡- እስቲ በመጨረሻ ሚኪ ምን ያዝናናዋል?

ሚኪ፡- እግር ኳስ በጣም የምዝናናበት ጨዋታ ነው። ቀንደኛ የአርሰናል ደጋፊ ነኝ (ሳቅ)

ሰንደቅ፡- እንኳን ደስ ያለህ በዚህ ሳምንት የኤፍ. ኤ ዋንጫ በልታችኋል?

ሚኪ፡- አመሰግናለሁ፤ እንኳን አብሮደስአለን። (ሳቅ) በፊት እኮ እንዲህ መላጣ አልነበርኩም፤ በአርሴናል ምክንያት ነው ከቬንገር ቀድሜ መላጣ የሆንኩት።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
9555 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us