የከረመ ፍቅር የሚጎነጉነው “የጉድ ቀን”

Wednesday, 28 May 2014 13:14

ትዳር በመላመድ ላይ በተመሰረተ ጥልቅ ፍቅርና ድንገት በሚከሰት ትክክለኛ ውሳኔ መካከል የሚመሰረት ቤተሰባዊ ትስስር እንደሆነ ያትታል። ይህን የሚያትተው በጉድ ቀን፤ ጉድ ይጸነሳል -ጉድ ይወለዳል ባዩ ቴአትር ነው። “የጉድ ቀን” ቴአትር በሀገር ፍቅር ቴአትር መታየት ከጀመረ የሶስት ወራትን ጊዜ አስቆጥሯል። በደራሲ ህይወት አበጀ የተፃፈው ይህ ስራ የተዘጋጀው በእስጢፋኖስ ከበደ ሲሆን በትወናው ላይም ተስፉ ብርሃኔ፣ አብዱልከሪም ጀማል፣ ባዩሽ አለማየሁና ሙሉነሽ ተሰማ ተጫውተውታል።

የሳምንቱን የመጨረሻ ቀናት ማለትም ቅዳሜና እሁድን በአንድ ቀን ሁለት ቴአትሮችን ማሳየት እየለመደለት የመጣው ሀገር ፍቅር ቴአትር ለተመልካች የተሻለ አማራጭ ማቅረብን ችሏል። በዛሬው የመዝናኛ አምድ የምንዳስሰውን “የጉድ ቀን” የተሰኘ ቴአትርንም በሀገር ፍቅር ቴአትር አመሻሽ 11፡30 ሰዓት ሄጄ የታደምኩት ነው።

“የጉድ ቀን” ኮሜዲ ቴአትር ይሁን እንጂ በርካታ ስነ-ልቦናዊ፣ ማህበራዊና ቤተሰባዊ ጉዳዮችን እየቆሰቆሰ ተመልካችን በሳቅ ወዝ እና በነገር የሚቦርሽ ቴአትር ነው።. . . በእናቱ እጅ ብቻ በእንክብካቤ ያደገውና የእርሳቸውን ቃል ከማጠፍ ሞትን የሚመርጠው ኢዮብ (ተስፉ ብርሃኔ) ከብዙ ማባበል በኋላ ከባህር ዳር አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት የፍቅር ጓደኛውን ለመተዋወቅ የሚመጡትን እናቱን ላለማሳፈር ሲል የውሸት ፍቅር ለመመስረት ሲሯሯጥ የገባበትን አጣብቂኝ መንደርደሪያ አድርጎ ይነሳል።

“የጉድ ቀን” ነውና ለስላሴ ብሎ በሚጠራው ደላላ (አብዱልከሪም ጀማል) አማካኝነት በተዋወቃት የቡና ቤት ሴት ጋር ድንገት ለማስመሰል የተመሰረተው ፍቅር አቅጣጫውን ስቶ፤ ውሉን አፍርሶ ወደ አላሳበበት አቅጣጫ ሲፈስና ተመልካችንም በሳቅ እንባ ሲያራጭ እንመለከታለን።

ተዋንያኑ ከተሰጣቸው ገፀ ባህሪይና ከመድረክ ተጋሪዎቻቸው ጋር እርስ በእርስ የነበራቸው ጥምረትና ውህደት ለቴአትሩ ሞገስ መሆን እንደቻለ መመስከር የማይካድ ሃቅ ነው። ዲግሪውን በምን ትምህርት እንዳገኘ ያልተነገረን ኢዮብ (ተስፉ ብርሃኔ) ሴቶችን የመፍራት ሥነ-ልቦናዊ ችግር ያለበትና የመጡት ሁሉ የሚሄዱበት እየሆነ የተቸገረ ሰው ተደርጎ ተስሏል። ይህንንም የሴቶችን ፀባይ አስቸጋሪነትና የእርሱንም ፍርሃት በሚያሳብቅ መልኩ፤ “እናንተ ሴቶች ዘለው ሲወጡባችሁ እንስሳ ትሉናላችሁ። ዝም ሲሏችሁ ደግሞ የሆነ ችግር አለበት ትላላችሁ” ሲል ወቀሳውን ለውሸት ለተመረጠችለት ፍቅረኛው ለምስር (ባዩሽ አለማየሁ) ሲያቀርብ ይሰማል።

በሌላ በኩል ደግሞ የበኩር ልጃቸው ለትዳር ወግ ማዕረግ በቅቶ የልጅ ልጃቸውን ለማየት የሚጓጉት የኢዮብ እናት ወ/ሮ ፀሐይነሽ (ሙሉነሽ ተሰማ) ከባህር ዳር ድረስ የልጃቸውን ፍቅረኛ ሊተዋወቁ በመምጣታቸውና ያገኟትንም “ፍቅረኛ” ተብዬ የልጃቸውን የውሸት አፍቃሪ በመውደዳቸው ድንገት ሽማግሌ ተልኮ የጋብቻው ዕለት እንዲቆረጥ ሲሯሯጡ ማየት ቴአትሩ ውስጥ ጉድ ሲፀነስና ጉድ ሲወለድ እንድናይ እንጋበዛለን።

እንደአብዛኞቹ ደላሎች እንቅስቃሴዎች ሁሉ ሳንቲም ይቆጥራሉ የሚል ለስላሴ (አብዱልከሪም ጀማል) የጉድ ቀን ምጥ የሆነበትን ኢዮብን (ተስፉ ብርሃኔ) “መላ ሞልቷል” በሚል ምላሱ ሊያዋልደው ሲሞክር የቴአትር የጨዋታ ግለት ከትዕይንት ትዕይንት እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል። ለዚህም እንደቀልድ ተብሎ የተጀመረው ግንኙነት ፈሩን ሲስት የተመለከተው ለስላሴ (አብዱልከሪም ጀማል)፣ “ውሸት ስትደጋግመው በልክህ እንደተሰፋ ኩታ ነው” ሲል ያሽሟጥጣል።

ለኢዮብ (ተስፉ ብርሃኔ) የውሸት ጓደኝነት ታጭታ ከጫት ቤት እንደመጣች የተነገረላት ምስር (ባዩሽ አለማየሁ) የእናቱንና የባሏን እግር እስከማጠብ በደረሰ እንክብካቤዋ በአንዳቸው ዘንድ ተወዳጅነትን ስታተርፍ በሌላኛቸው ዘንድ ደግሞ ግራ አጋቢነትን ስትፈጥር ያየ ተመልካች፤ በተለይም ኢዮብ የሚያሳየውን ባህሪ ታዝቦ ቀጣዩን ትዕይንት መጓጓቱ ሳይታለም የተፈታ ነው።

“ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል” እንዲሉ ለብዙ ጊዜያት በሆዷ ሸሽጋው የነበረው የፍቅር ጥንስስ ያሰከራት ምስር (ባዩሽ አለማየሁ) ለጉድ ቀን መወጣጫ ተብላ ከተጠራችበት ቤት ዘው ብላ ብትገባም ለመውጣት ጊዜ ግን፣ “በፌዴራልም ቢሆን አልወጣም” ስትል የቴአትሩን የሳቅ ከፍታ ጣሪያ ታደርሰዋለች።

በእናቱ የትዳር ጉጉትና በሀሰተኛ የፍቅር ጓደኛው ያልጠበቀው ሁኔታ ግራ የተጋባው ኢዮብ (ተስፋ ብርሃኔ)፣ “የስዕል እንጂ የሰው አብስትራክት እንዳለ አላውቅም” ሲል ነገሮች ምስጢር እንደሆኑበት ይናገራል። ከአንድም ሁለት ሴቶችን በመውደድ ትዳር ደጃፍ ደርሶ ያጣው ኢዮብ ድንገት ግን ምስር “እንጋባ” ስትለው መልሱ “ከጠለፋ አይተናነስም” ሲሆን የቤቱን ልዩነት በአግራሞት እንመለከታለን።

“የጉድ ቀን” ቴአትር እንቁላል ቀስ በቀስ በእግሯ ትሄዳለች ይሉትን ተረት በተግባር የሚያሳይ ነው። ይህም ብቻ አይደለም በ “የጉድ ቀን” ቴአትር ውስጥ ለእናት ያለ ክብርና ፍቅር የትድረስ እንደሆነ ከኢዮብ (ተስፉ ብርሃኔ) ጭንቀትና ጥበት እናያለን። እናትነት ከልጅ ብዙ የሚጠበቅበትና የሚጓጓበት እንደሆነ ከወ/ሮ ፀሐይነሽ (ሙሉነሽ ተሰማ) እንመለከታለን። በአንጻሩ ደግሞ ሴት ልጅ ከወደደች ልትከፍል የምትችለውን መስዕዋትነት ልትሄድ የምትችልበትን ርቀት ከምስር (ባዩሽ አለማየሁ) ተመልክተናል። “አፉ ጤፍ ይቆላል” የሚባልለትን አይነት፤ የለምና አይቻልምን የሚያውቀው ደላላን በለስላሴ (አብዱልከሪም ጀማል) በኩል አይተናል።

እንዲህ ቢስተካከል . .

“የጉድ ቀን” ቴአትር የእረፍት ቀንን የሚያዋዛ ስራ ነው። ነገር ግን በቴአትሩ ሂደት የታዘብኳቸውን ስህተቶች መጠቆሙ ለመጪው ጊዜ መድረክ ሊታሰብባቸው ይችላልና እነሆ። የመጀመሪያው የኢዮብ ገጸ-ባህሪይ (ተስፉ ብርሃኔ) ይህን ያህል የተጋነነ ቂልነት ማሳየቱ የኮሜዲውን ዘውግ ወደቧልት የሚያመራ ድልድይ መሸጋገሪያ ሊያደርገው ምንም አልቀረውም። ይህም ብቻ አይደለም፤ ገፀ-ባህሪው ከእንግሊዛዊው ተዋናይ ሚስተር ቤን ባህሪይ ጋር በእጅጉ የመመሳሰል ተፅዕኖ አለበት። (ብዙ ከመናገሩ በስተቀር) ይህ የሚለዝብበት ሁኔታ ቢመቻች።

ሁለተኛው ኢዮብ ቤተዘመድ በተጠራበት ድግስ ላይና ከዚያ በፊት በነበረው ጊዜ ሁሉ አንድ አይነት ልብስ መልበስ አብረውት ከነበሩት ገፀ-ባህሪያት ድምቀት አንጻር ለምን የሚያሰኝ ጥያቄን የሚፈጥር ነውና ድግሱን የሚያሳይ አልባስ ቢጠቀም።

     ሶስተኛው ነገር የእናትዬው በጠፋ ስልክ መነጋገር ድንገት በተፈጠረ ቴክኒካዊ ችግርም ቢሆን ያስገምታልና ቢታረም መልካም ነው።

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
12216 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us