“አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል” የባለቤትነት ሸርተቴ ገጥሞታል

Wednesday, 04 June 2014 12:12

 

8ኛው አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ከግንቦት 30 እስከ ሰኔ 4 ቀን 2006 ዓ.ም (ለአምስት ተከታታይ ቀናት) “ዘጋቢ ፊልሞች ለማህበራዊ ጥናት እና ግንዛቤ” በሚል መሪ ቃል ይካሄዳል፤ ሲሉ አዘጋጆቹ ባሳለፍነው ሳምንት አርብ በሲዮናት ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ተናግረዋል። በመግለጫው ወቅት የተነሱትን አንኳር ጥያቄዎችና ሃሳቦች ከማቅረባችንም በተጨማሪ የአዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫልን ያለፉት ሰባት ዓመታት ሂደትን በተመለከተ መለስ ብለን በወፍ በረር ለዛሬው በመዝናኛ አምዳችን ስር እንመለከታለን።

የፊልም ፌስቲቫሉ ማህበረሰብን ከማስተማር፣ ከማዝናናትና ማህበራዊ ችግሮችን ነቅሶ ህብረተሰቡ እንዲወያ በማስቻልና የአገራችንን የፊልም ኢንዱስትሪ ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ አላማው አድርጎ አንድ ብሎ የጀመረው በ1999 ዓ.ም ነው። ከተለየዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን ስራውን የጀመረው ኢኒሼቲቭ አፍሪካ የ“አዲስ ፊልም ፌስቲቫልን” በአህጉሪቱ ብሎም በአለም አቀፍ ደረጃ በቅጡ የሚታወቅና ትኩረትንም መሳብ የሚችል እንዲሆን ታስቦ የተጀመረ እንደሆነ የኢኔሼቲቭ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ክቡር ገና አስታውሰዋል።

በ“አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል” የሰባት ዓመታት ጉዞ ውስጥ ከ410 በላይ በወቅታዊና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ከተለያዩ የዓለም አገራት የተውጣጡና የተጋበዙ ፊልሞች ለዕይታ በቅተዋል። በዝግጅቶቹም ላይ ከ45ሺህ በላይ ታዳሚዎች በተለያዩ ፊልሞችን የማሳያ ስፍራዎች ተገኝተው ፊልሞችን የማጣጣም ዕድሉን አግኝተዋል። እግረመንገድም በርካታ የፊልም ባለሙያዎች እየተጋበዙ እውቀታቸውን ለታዳሚው እንዳካፈሉ የፌስቲቫሉ ታሪክ ይመሰክራል።

በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት በመድረኩ ተገኝተው ስለቀጣዩ የአዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ሃሳባቸውን ካቀረቡት አጋር ተቋማት መካከል ከአምስተኛው የፌስቲቫሉ ፕሮግራም ጀምሮ በአብሮነት የዘለቀው የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ይገኝበታል። የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ መድሃኔ መለሰ ስለዝግጅታቸው ሲናገሩ፤ “ይህ የዘጋቢ ፊልም ፌስቲቫል ለበርካታ የከተማችን ወጣቶች ከመዝናኛነት ባለፈ ትምህርት የሚቀስሙት ይሆናል የሚል ተስፋ አለን” ብለዋል። አክለውም ፌስቲቫሉ በዋናነት በባህል፣ በትምህርት፣ በኪነጥበብ፣ በሥነ ፆታ፣ በድህነት፣ በስደትና በወጣቱ ማህበራዊ ችግሮች ላይ አተኩሮ የሚሰራ በመሆኑ ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ሃሳቦችን ከፌስቲቫሉ ማግኘት እንደሚቻል ተጠቁመዋል።

ከባለፉት ዝግጅቶቻችን ያገኘናቸውን የተመልካች አስተያየቶች እንደግብዓት እየተጠቀምንባቸው ነው የሚል ሃሳብ ያነሱት የኢኒሼቲቭ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር አቶ ክቡር ገና በበኩላቸው፤ “የዘንድሮውን የፊልም ፌስቲቫል ዝግጅት ልዩ ከሚያደርጉት ክንውኖች አንዱ የኢትዮጵያ ባለሙያዎችን ስራ ያካተተ መሆኑ ሲሆን ሌላኛው ግን እንደከዚህ ቀደሙ ስታንዳርዳቸውን የጠበቁና መታየት የሚገባቸውን አዳዲስ ፊልሞች ለተመልካች ማቅረባችን ነው” ሲሉ የታዋቂዋን የፊልም ተዋናይት አምለሰት ሙጬ ስራ “አረንጓዴ መሬት” በዘጋቢ ፊልሞቹ ስብስብ ውስጥ ማካተታቸውን ተናግረዋል። ተደጋግሞ እንደተነሳው በአዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ዝግጅቶች ውስጥ የኢትዮጵያውያን የፊልም ባለሙያዎች ተሳትፎ አናሳ እንደሆነ ቀጥሏል። በዘንድሮም ከሌጣነት ያዳነው የአምለሰት ሙጬ “አረንጓዴ መሬት” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ነው። ለበርካታ ጋዜጠኞች ወደመድረኩ ከተሰነዘሩት ጥያቄዎች መካከልም፤ በተለይም የዘንድሮው የፊልም ፌስቲቫል በወጣቶች ላይ ያተኮረና በዝግጅቱም ላይ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር በአጋርነት የመቀጠሉን ያህል ችሎታውና አቅሙ እያላቸው ስራዎቻቸውን ለአደባባይ ማብቃት ያልቻሉትን ወጣቶች ስለምን እድል በመስጠት አላገዛችሁም? የሚል ሆኗል። የአዲስ አበባ ወጣቶች ፕሬዝዳንት የሆነው አቶ መድሃኔ መለስ ሲመልስም፤ “በዚህ ደረጃ ማህበራችን ሊንቀሳቀስ አለመቻሉ ስህተት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ፕሮግራሙ ሲዘጋጅ ወጣቶች ማንኛውንም አይነት ሊታይ የሚችል ዘጋቢ ፊልም ካላቸው ወደአዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ለግምገማ እንዲያመጡ ጋብዘናል። ዕድሉንም ሰጥተን ነበር” ሲሉ መልስ ተሰጥቷል።

“አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል”

ማን ያስተዳድረዋል?

በኢኒሼቲቭ አፍሪካ ቆስቋሽነት በ1999 ዓ.ም አንድ ብሎ የጀመረው ይህ የአዲስ ኢንተርሽናል ፊልም ፌስቲቫል ዝግጅት አሁን አሁን የባለቤትነት ሚናው ከኢኒሼቲቭ አፍሪካ ወደ አዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር እየተንሸራተተ ነው። ለዚህም ይመስላል አርብ ዕለት በሲዮናት ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት በርካታ ጋዜጠኞች ይህን ጥያቄ አጠንክረው ሲያነሱት የነበረው። መድረኩን ሲመሩ ከነበሩት ሰዎች መካከል የኢኒሼቲቭ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር አቶ ክቡር ገና ስለጉዳዩ ምላሽ ሲሰጡ፤ “የኢንሼቲቩ ተደራሽነትና አቅም ውሱን በመሆኑ ምክንያት አብረውን እንዲሰሩ ከጋበዝናቸው አጋር ድርጅቶች ውስጥ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ከ5ኛው ዝግጅታችን ጀምሮ አብሮነቱን በማሳየቱ ቀጥሏል። እስካሁንም ያገኘናቸውን ልምዶች ለማህበሩ እያስተላለፍንና እያስተማርን ሲሆን በቀጣይነት ግን በኢኒሼቲቭ አፍሪካ ደጋፊነት ሙሉ በሙሉ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር የአዲስ ፊልም ፌስቲቫልን በማዘጋጀት ይቀጥላል” ብለዋል።

የፊልም ፌስቲቫሉን የባለቤትነት መብት የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር መውሰድ ብቻ ሳይሆን የወሰደበት ምክንያትም ለበርካቶች አጥጋቢ አልነበረም። ኢንሼቲቭ አፍሪካ ከበርካታ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆነ የሲቪክ ማህበራት ጋር አብሮ የመስራት አጋጣሚው እንዳለው እየታወቀ፤ ስፖንሰሮችንና ደጋፊዎችን የማግኘት አቅሙ እያለው፤ ሲጀምርም ከአገር አልፎ የአህጉራትንና የአለምን ትኩረት መሳብ የሚችል ፌስቲቫል ለማዘጋጀት ያሰበ ሆኖ ሳለ፤ የአቅም ውሱንነትና በርካታ ተመልካቶችን የማግኘት (የተደራሽነት) ችግሮችን በመጥቀስ ከመድረኩ ወደጀርባ ለመሄድ ያሰበበት አካሄድ ምክንያታዊነቱ “ውሃ የሚያነሳ” ሃሳብ ሆኗል።

በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ከተበተኑ ጽሑፎች ውስጥ የሚከተለው አንቀፅ የፌስቲቫሉን ቀጣይ ባለቤት በጉልህ የሚያሳይ ነው። “. . . ይህንን በማጠናከር ኢኒሼቲቭ አፍሪካ ማህበረሰብ አቀፍ የሆኑ የሲቪክ ማህበራትን ሚና ለማጎልበት ባለው ዕቅድ መሰረት የጋራ ትብብሩን በማጎልበትና የማህበሩን አቅም በማሳደግ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በጋራ፤ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በከፊል እንዲሁም ከ2008ዓ.ም ጀምሮ አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ሙሉ በሙሉ የወጣቶች ማህበር እንዲያዘጋጀው የአቅም ማሳደግ ስራ ለመስራት ስምምነት ላይ ተደርሶ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ሂደት ላይ እንገኛለን” የሚል ሐተታ ሰፍሮ ይገኛል።

በበርካቶች ዘንድ ጥያቄን ያጫረው ሌላው ጉዳይ የሚታይም ይሁን የማይታይ በርካታ ተግባሮችና ተግዳሮቶች ያሉበት የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ይህን የመሰለ ዓመታዊና (ምናልባትም ወደፊት) ተጠባቂ ሊሆን የሚችልን የፊልም ፌስቲቫል በኃላፊነት እንዲመራው ሲደረግ በምን መነሻነት ነው? የሚሉ አልታጡም። ከዚህም ባሻገር የፊልምን ፌስቲቫል ከፊልም ስራ ተቋማትና ባለሙያዎች ጋር እንዲከናወን ማመቻቸት ሲቻል፤ ለራሱ በርካታ የቤት ስራዎች ያሉትን የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ይህን የሚያክል ቀንበር እንዲሸከም ማመቻቸት ዕዳን የመግፋት ያህል ሊቆጠር የሚችል ነው።

ይህን መሰል የባለቤትነት ሸርተቴ ውስጥ የወደቀውና በበርካቶች ዘንድ ከዓመት ዓመት ሳይቋረጥ ቀጣይነቱን እያየንለት የመጣነው “አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል” እስካሁን እንጂ በቀጣይ እጣ ፈንታው ምን ሊሆን እንደሚችል ለማወቅ አዳጋች ሆኗል።

ይህም ሆኖ ሲጀመር በ1999 ዓ.ም የመጀመሪያ ፌስቲቫሉን ዘጠኝ ፊልሞችን በማሳየት እዚህ የደረሰው አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል እስካሁን በጥቅሉ 410 ፊልሞችን ለዕይታ ሲያቀርብ፤ ከነዚህም መካከል በርካታ የፊልም ባለሙያዎች ትምህርታዊ ስልጠናን የመስጠት አጋጣሚ ያገኘ ሲሆን፤ በዘንድሮውም የዘጋቢ ፊልሞችን በተመለከተ ስልጠና የሚሰጡ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚገኙም ተነግሯል።

ከግንቦት 30 እስከ ሰኔ 4 ቀን 2006 ዓ.ም የአዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል በጣሊያን ባህል ማዕከል እና በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ አዳራሾች በነፃ ለዕይታ ይቀርባል። በዚያም ላይ በርካታ ወጣቶችና የፊልም ጉዳይ ይመለከተኛል የሚሉ አካላት መታደም እንደሚችሉ አዘጋጆቹ ከወዲሁ አስታውቀዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
11732 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us