በአንድ ድንጋይ ሁለት (መፅሐፍ) ወፍ ‘‘የስኬት መንገዶች’’ እና ‘‘ዴዚዴራታበአንድ ድንጋይ ሁለት (መፅሐፍ) ወፍ ‘‘የስኬት መንገዶች’’ እና ‘‘ዴዚዴራታ

Friday, 04 October 2013 18:09

በአሸናፊ ደምሴ

ባሳለፍነው አመት መጨረሻ አካባቢ ታትመው ለአንባቢያን ከደረሱ በርካታ ሥነ-ፅሁፋዊ፣ ታሪካዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሥነ-ልቦናዊ መፅሐፍት መካከል የደራሲ በተክሉ ጥላሁን ባለሁለት ገፁ መፅሐፍ አንዱ ነው። አንባቢያን ይረዱኛል ብዬ እንደማስበው ባለሁለት ገፅ መፅሐፍ ሲል የሁለት መፅሐፍቶችን ጥምረት ለማመልከት እንጂ የገፁን ቁጥር ለመናገር ፈልጌ አይደለም።

መፅሐፉ ‘‘የስኬት መንገዶች’’ እና ‘‘ዴዚዴራታ’’ የተሰኙ የሁለት መፅሐፍት ጥራዞችን በጥምረት የያዘ ሲሆን፤ በይዘቱ ግን ሥነ-ልቦናዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ስራ ነው። ደራሲው ተክሉ ጥላሁን የጭን ቁስል፣ ጃንሆይን ማን ገደላቸው?፣ የቀን ጨለማ፣ ከስኬት በስተጀርባ፣ ያልሰከነ ዜማ፣ የሎጥ መንገድ፣ ያልተዘመረላቸው ጀግኖችና ትላንትን ላስታውስ የተሰኙ መፅሐፍት ፀሐፊ መሆኑም ይታወቃል። ለምን እንደሆነ ደራሲው በግልፅ በመግቢያው ላይ ባይነግረንም ሁለቱም መፅሐፍት በተናጠል መነበብ የሚችሉ ሆነው ሳለ በጥምረት አምጥቷቸዋል። በዚህም መፅሐፉን (መፅሐፎቹን ማለት ይቻላል) በእጁ ያደረገ አንባቢ በሁለቱም የመፅሐፉ ገፆች ቁም ነገር መቅሰሙ አይቀሬ ነው። ‘‘በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ’’ እንዲሉ ማለት ነው።

በፊት ገፁ በኩል የተቀመጠው ‘‘የስኬት መንገዶች’’ ፅሁፍ እንደብዙዎቹ የሥነ-ልቦና መፅሐፍትና ፀሃፍት ሁሉ ‘‘የእኛን’’ ሕይወትና አኗኗር ለመቀየር ታልመው ስለመፃፋቸው ደራሲው ይተርክልናል፤ ከዚያም በተሻገረ መልኩ የቅርባችን የሆኑና የምናውቃቸውን የአገራችንን ዝነኞች የስኬት ምስጢር እንደምሳሌ አስቀምጦ ሊያሳየን ይሞክራል። ይህ መፅሐፉን እንደሩቅና የህልም አለም ሥነ-ልቦናዊ ትርክት ብቻ እንዳንመለከተው የሚያደርገን ይሆናል። ይህንንም የመፅሐፉ አርታኢ በማስታወሻው እንዲህ ሲል ከትቦታል፣ ‘‘የስኬት መንገዶች የሀገራችንን ታዋቂ ሰዎች ግላዊ አስተሳሰብ እና ተሞክሮ እንዳስፈላጊነቱ ማካተት መቻሉም ሌላው በጐ ጐኑ ነው። የቅርብ ምልከታ ለቅርብ ግንዛቤ ይረዳልና።’’ (ገፅ÷7)

ደራሲው በመፅሐፉ የመጀመሪያ ገፅ ላይ በጥቁምታ መልክ እንዳሰፈረው ሀሳብ ከሆነ ‘‘የስኬት መንገዶች’’ መፅሐፍ የተፃፈችው በአለማችን የቁጥር አንድ ሽያጭን ከተቀዳጁ በርካታ መፅሐፍቶችና ከሀገራችን ዕውቅ ሰዎች ማለትም፤ ክቡር ዶ/ር ኃይሌ ገ/ስላሴ፣ ከአምባሳደር አሀዱ ሳቡሬ፣ አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ (ሁለገብ የኪነ-ጥበብ ባለሙያ)፣ ሃያት አህመድ (ሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ እና ኩዊን ኦፍ አፍሪካ)፣ አርቲስት አለማየሁ ታደሰ፣ ዳንኤል መብራቱ (ዳን ቴክኖክራፍት)፣ ካፒቴን ሰለሞን ግዛው፣ አኒሜተር ግርማ ዘለቀ (የስንዝሮ አሻንጉሊት ፈጣሪና የአኒሜሽን ባለሙያ) እና የሌሎችም ህይወት ተሞክሮ ቀርቧል።

‘‘የስኬት መንገዶች’’ በተሰኘው የመፅሐፍ ገፅ በኩል ‘‘ሰው በልቡ እንደሚያስበው እንዲሁ ነው’’ የሚለውን የቅዱስ ቃል መልዕክት የሚያሰምርበት የመፅሐፉ ቃል አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ የተናገረውን ሀሳብ እንዲህ ያስነብበናል፣ ‘‘የሰው ልጅ የሚያስበውን መሆን እንደሚችል አምናለሁ። ማመንም ብቻ ሳይሆን በህይወቴ በተለያዩ ጊዜያት ላሳካቸው፣ ልከውናቸው የምፈልጋቸውን ነገሮች አሰቤ አድርጌያቸዋለሁ። ሁሌም አንድን ነገር ወጥኖ ከግብ ለማድረስ መጀመሪያ የመጨረሻ ውጤቱን ነው የማልመው።’’

በዚህች ጥራዝ በኩል በአስር አርዕስቶች የተከፋፈሉና ሰው-ሰው የሚሸቱ አጓጊ ሀሳቦች ከተጨባጭ ተሞክሮዎች ጋር ቀርበው እናገኛለን። በሌላም በኩል ‘‘ዴዚዴራታ’’ መሠረታዊ የኑሮ መመሪያ በሚለው የመፅሐፉ ገፅ በኩል፤ ደራሲው በመግቢያው እንደመፃፊያ ምክንያት የሚነግረን ተመሳሳይ የሥነ-ልቦናዊ ችግር ስነ-ልቦናዊ መፍትሄዎች መኖራቸውንና እነዛንም ችግሮች አሸንፈን የምንወጣበትን መላ እንደሆነ ይጠቁመናል። ‘‘ይህቺ ትንሽ (መፅሐፍ) ዴዚዴራታ /መሠረታዊ የህይወት መመሪያ ሳይኮሎጂ/ የተዘጋጀችው ቀብረው ሊያስቀሩን የመጡብን የሚመስሉንን ችግሮችና ሸክሞች ልክ እንደ እርግቦች በአየር ላይ ለመንሳፈፍ እንጠቀምባቸው ዘንድ ለማሳየት ነው’’ ይለናል። (ገፅ÷5) ይህንንም ለማሳየት በስድስት ክፍሎች የተቀነባበሩ የህይወት ተሞክሮዎችን በተዋዛ አቀራረብ ያስነብበናል።

የሰው ልጅ በተገነባበት መልካምና መጥፎ ሥነ-ልቦናዊ አጥር ልክ የሚቆም ስለመሆኑ በማተት የሚጀምረው ይህ የመፅሐፉ ክፍል፣ የሁለት የተለያዩ አፅናፎችን የህይወት ተሞክሮ መነሻ አድርጐ ይንደረደራል። የ‘‘ዴዚዴራታ’’ የመፅሐፍ ገፅ በአንድ በኩል፣ በእናቱ የተጠላን፣ በሚስቱ የተዋረደንና በማህበረሰቡ የተገፋን ሰው የስነ-ልቦና ቀውስ መዘዙ የት ድረስ እንደሆነ ምሳሌ ሲያደርግ ሊ ሀር ቬይ ኦስዋልድ ይህ የመገፋትና የመገለል ባህሪው ተገንብቶ - ተገንብቶ በስተመጨረሻም እ.ኤ.አ በህዳር 22 ቀን 1963 ዓ.ም የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲን በአደባባይ በጥይት ተኩስ ስለመግደሉ ይነገረናል። በአንፃሩ ደግሞ በቤተሰቡ ውስጥ በፍቅርና በለጋሽነት መንፈስ ያደገውን ሰው ሲጠቅስ፤ የፖሊዮ ህመምተኛ ቢሆንም እንኳን ተስፋ ሳየቆርጥ ገና በልጅነቱ ወደታሰበለት የፕሬዝዳንትነት መንበር ስለመጣው ፍራንክሊን ዲላኖ ሩዝቬልት ይተርክልናል። ይህ የሁለቱ ሰዎች ሥነ-ልቦናዊ ግንባታ ንፅፅር ሰዎች አስተዳደጋቸው፣ ቤተሰባቸውና አጠቃላይ ማህበረሰባቸው የሚቀርፃቸው ፍጡሮች መሆናቸውን በጉልህ ማሳየት የቻለ ነው።

ደራሲው በመግቢያው እንደሚጠቁመው ‘‘ዴዚዴራታ’’ ማለት የላቲን ቃል ሲሆን ትርጓሜውም መሠረታዊ የኑሮ መመሪያ ማለት ነው ይለናል። በ1962 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በቅዱስ ጳውሎስ ቤተ-ክርስቲያን ግድግዳ ላይ ተፅፎ የሚነበበው ይህ ፅሁፍ እንዲህ ይላል።

ዴዚዴራታ

በዚህ ምድር ብለን በምንጠራው ፕላኔት ውስጥ ካሉ ፍጥረቶች ሁሉ አንተ የላቅክና እጅግ የመጨረሻው ጠቃሚ ፍጥረት ነህ። ነገሩ ለጊዜው ግልፅ ሆኖ ባይታይህም የተፈጠርክበት አንዳች ምክንያት አለ። ባይሆንማ ኖሮ እንደ ብዙ ያልተወለዱ ፅንሶች ጭንጋፍ ሆነህ በቀረህ ነበር። የሰው ልጅ የከበረ ሀብቱ ትጋቱ ነውና የተፈጠርክበትን ምክንያት ፈልጎ በማግኘት ላይ ትጋ!

አንተ ልዩና ድንቅ ፍጡር በመሆንህ በራስህ ልትደሰት፣ ተገቢውን ክብርና ዋጋም ልትሰጥ ይገባሀል። ማፍቀርም ሆነ መፈቀር የምትችለው ለራስህ ተገቢ የሆነ ፍቅር ሲኖርህ ብቻ ስለሆነ ራስህን ከነድክመትህም ቢሆን ተቀበለው። ፍቅር ለጨለማ መንገድ ብርሃን፣ ለነፍስህም ምግብ ነው።

ኑሮህ የሰመረ ይሆን ዘንድ ከሰዎች ሁሉ ጋር ያለህ ግንኙነት ጥንቃቄ አይለየው። ለጥፋትህም ሆነ ለልማትህ ሰዎች እጅግ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉና በግንኙነትህ ሁሉ ብልህ ሁን። ብረት ብረትን እንደሚስለው ባልንጀራም ባልንጀራን ይስለዋልና ጓደኛን በጥንቃቄ በመምረጡ ላይ አትዘናጋ።

ህይወትህን ለዕምነት አስገዛ። በዚህ ትርምስና ሸፍጥ በበዛበት ዓለም ምርኩዝ የሚሆንህ እምነትህ ብቻ ነው። ለችግሮች ሁሉ አትረበሽ። የወርቅ ጥራቱ በእሳት እንደሚፈተን ሁሉ አንተም የምትፈተነው በችግር ነውና የሚደርሱብህን ፈተናዎች ሁሉ ታልፍ ዘንድ ፅኑ እምነት ይኑርህ።

በህይወትህ ውስጥ የሚሆኑት ነገሮች ሁሉ የሚጀምሩት፣ ፍፃሜህም የሚቀናው በምትወስነው ውሳኔ ስለሆነ ዳተኛ አትሁን። ዓለም በከፍተኛ ጀብዱ የተመላችው በታላላቅ ውሳኔዎች ነውና አትፍራ። ደግሞም በህይወት ወንዝ ውስጥ እስካለህ ድረስ ከጥቂት አለቶች ጋር መጋጨትህ ስለማይቀር ተስፋን የሙጥኝ በል። ራስህን ንዴት ለተባለው መርዛማ እባብ አሳልፈህ አትስጥ።

ሰላምህን ከሚያውኩ ነገሮች ሁሉ ዞር በል። ደስታ የሚገኘው ራስህን ለደስተኝነት ባዘጋጀኸው መጠን ነውና ብዙ ጊዜህን በደስታ ላይ አሳልፍ።

ዕለት በእለት አዕምሮህ ሰላም እየተመገበ መሆኑን አረጋግጥ። አንተ ያስተሳሰብህ ውጤት ስለሆንክ በተቻለህ ሁሉ በጎ አስብ። በዚህ የችግር አሜኬላ በመላበት ምድር በተረጋጋ ሁኔታ ለመኖር የሚረዳህ በጎ መሆን ብቻ ነው።

ክፉ ብታስብ በከፋ፣ በጎም ብታስብ በበጎ አስተሳሰብ አለምህን ስለምትሰራ አስተሳሰብህ ላይ ጥንቃቄ አይጉደል።

ወንዝ ሁሉ ከአንድ መነሻ ነጥብ ተነስቶ አያሌ መንገዶችን በማቆራረጥ በመጨረሻ የሚደርስበት አንድ የታወቀ መድረሻ ግብ እንዳለው ሁሉ አንተም ይኑርህ።

ወንዙ አንዳንዴ የፅናት ጉዞውን የሚያውኩ፣ የአወራረድ ስልቱን የሚያደፈርሱ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ይገጥሙታል። አንዳንዴ በማዕበልና በሀያል ሞገድ ተከብቦ እጅግ በሚደንቅ ፍጥነት አረፋ እየደፈቀ ሲጎርፍ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ እጅግ መንምኖና አቅሙ ተዳክሞ የወትሮው ባልሆነ ፍጥነት ሊያዘግም ይችላል። ይሁንና የሀይል የፍጥነትና የጊዜ ሚዛን መዋዠቅ ቢያናውጠው ወደ መድረሻ ግቡ የሚያደርገውን የፅናት ጉዞ ከመቀጠል ፈፅሞ አይታቀብም። ፈፅሞ!

ወንዙ ከአንድ ትንሽ ሀይቅ መንጭቶ በሂደት እየገዘፈ… አያሌ መሰናክሎችንና ውጣ ውረዶችን እያለፈ… ሳይበገር እስከመጨረሻው በፅናት እንደሚጓዘው ሁሉ… አንተም በረጅሙ የህይወት ጉዞ የሚገጥሙህ እንቅፋቶችና መሰናክሎች ወደ መጨረሻው ግብህ ከማምራት ሊገቱህ… በፅናት ከመግፋት ተስፋ ሊያስቆርጡህ አይገባም።

በዚህ ግዙፍ ዓለም ውስጥ በስጋና በደም… በነፍስና በእስትንፋስ የተገለጥክ ህያው ወንዝ ነህና ፍሰትህ የተረጋጋ፣ ጉዞህም ሰላማዊ ይሁን። ይህች ዓለም ያንተ ግዛት ናትና በአግባቡ አስተዳድራት። (ከገፅ 92÷95) የተወሰደ።

በዚህ ጥራዝ ውስጥ መልካም ናቸው ያላቸውን ሀሳች ከተለያዩ ግለሰቦችና መፅሐፍት እንዲሁም ከቅዱሳን መፅሐፍት ጭምር ወስዷል። አንድ ሰው በመጀመሪያ ራሱን መውደድና ማክበር ሲችል ብቻ ሌሎችን እንደሚወድና እንደሚያከብር ሲያስረዳ፣ ‘‘በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንኳን ራስህን መውደድ እንዳለብህ የሚያስገነዝብ ቃል አስራ ዘጠኝ ጊዜ ተጠቅሷል። ወዳጄ በቅዱስ ቁርአኑም ቢሆን ቁጥሩ ይለያይ እንጂ ራስህን እንድትወድ… ሰውነትህን እንድታከብር ትመከራለህ። ራስን መውደድ ማለት በቀላሉ በራስህ አውንታዊና ጤናማ ስሜቶችን በውስጥ መዝራትና ተንከባክበህ ማሳደግ ማለት ነው’’ ይለናል። ለዚህም እንደምሳሌ የታላቁን እንግሊዛዊ ገጣሚ ሉርድ ባይረን እልም ያለ ሸፋፋ መሆኑን በማታወስ ሸፋፋነቱ ግን ከባለቅኔነት እንዳላገደው ይጠቅሳል። ሲቀጥልም የህንዳዊው ባለቅኔ ማሎክ ሞሀመድ ጃያሲንን እጅግ ሲበዛ መልከ ጥፉ መሆን ቢነግርህም፤ ዳሩ ግን ዕውቅ ባለቅኔ ከመሆን እንዳላገደው ያስታውስሃል። ለጥቆ የሚያነሳው ሶቅራጠስን ነው። ግሪካዊው ፈላስፋ ሶቅራጠስ እልል የተባለለት መልከ ጥፉ ቢሆንም እንኳን አለም አሁንም ድረስ የማይረሳቸውን ምጡቅ አስተሳሰቦች ማፍለቁን ይነግረናል። ቀጥሎም የፈረንሳዩን ንጉስ ናፖሊያን ቦናፖርቴን እና የእንግሊዙን ጠቅላይ ሚኒስቴር ሎይጅ ጆርጅ ቁመት አጭርነት በማስታወስ ነገር ግን ከመሪነት እንዳላገዳቸው ይነግረናል። እናም የሰው ልጅ በሀሳቡ ጭምር እንጂ በተክለ ሰውነቱ ብቻ ሊከበር እንደማይችል ያሳስበናል። እነዚህ የአለም ታላላቅ ሰዎች በጐደላቸው ነገር ላይ ብቻ አተኩረው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ስማቸው ባልተነሳ፤ ስራቸውም ባልተወሳ ነበር።

በዚህ የመፅሐፍ ክፍል ውስጥ አንድ ሰው ህይወቱን መቀየር ከፈለገ የውሳኔ ሰው መሆን አለበት ይለናል። አክሎም፣ በህይወትህ ውስጥ የተከሰቱ ወይም የሚከሰቱ የትኞቹም ችግሮች ቢሆኑ ደግሞ ተገቢውን ውሳኔ ከማሳለፍ የሚያግዱህ ምክንያቶች መሆን የለባቸውም። ወሳኝ በሆኑ ጊዜያቶችም ላይ ውሳኔ ካለማስተላለፍ ችግሮችህን ወይም የምትገኝባቸውን አመቺ ያልሆኑ ሁኔታዎችን ምክንያቶች ለማድረግ በመሞከር ቁጥር አንተው ለራስህ ህይወት መሰናክል እየሆንክ፣ መንገድህንም በእሾህ እያጠርክ መሆኑን አስታውስ’’ ይለናል። (ገጽ÷51)

‘‘አካባቢያችን ከጠቢቡ ቤተ-ሙከራ በምንም የተለየ አይደለም’’ የሚለው እና ‘‘ውድቀት የስኬት መሰላል’’ መሆኑን በሚያመላክተን ክፍል ውስጥ ህፃናትን ምሳሌ አድርጐ ቃላትን በማማጥ፣ የስሜት ሁኔታዎችን በመረዳና እንቅስቃሴዎች በመመልከት ይማራሉ ይለናል። ከውድቀታቸው በመነሳት በዓለም ላይ ትልቅ ቦታ የደረሱትን የእነ ቶማስ ኤድሰን፣ አብርሃም ሊንከን፣ አኪዮ ሞሪታ፣ ሄነሪ ፎርድ፣ አልበርት አንስታይንን ጨምሮ የአስራ ሁለት ሰዎችን ታሪክ በቁንስል ያስነብበናል። እናም ውድቀትን ሳንፈራ የስኬት መሰላል እናደርገው ዘንድ ይመክረናል።

መፅሐፉ ለውጥን በመፈለጋችንን ለለውጡ ውጤት የውሳኔ ሰው መሆናችን አስፈላጊ መሆኑን ለሥነ-ልቦናዊ መንደርደሪያዎች ላይ ተንተርሶ ይተርክልናል። ደራሲው ተክሉ ጥላሁን የበርካታ መፅሐፍት ፀሐፊ ከመሆኑ አንፃር ጠንካራ ሊባሉ የሚችሉ ሥነ-ልቦናዊ አስተሳሰቦችን ሳይቀር በቀላል አቀራረብና በማራኪ አገላለፅ ለሁሉም አንባቢ በሚገባ መልኩ ፅፎልናል። የሁለቱን መፅሐፍት በጥምረት ማግኘታችን ‘‘በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ’’ እንድንል ያችለናል። በውስጡ አዳዲስ ሀሳቦች፣ አዳዲስ እርምጃዎች፣ አዳዲስ መንገዶች፣ አዳዲስ ታሪኮች የሚያስነብበን በመሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው።               


Last modified on Friday, 04 October 2013 18:14
ይምረጡ
(34 ሰዎች መርጠዋል)
14951 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us