የሞራል ከፍታ በ“ቅጥልጥል ኮከቦች”

Wednesday, 25 June 2014 13:18

እውነት የምታድንበትና እውነት የምትታደንበት፤ ፍቅር የሚፈተንበትና ተስፋ የሚረገዝበት፤ እምነት የሚረክስበትና የሙያ ሥነ-ምግባር የሚፈተንበት፤ በአጠቃላይ የህይወት ጉዳጉድ የሚታይበት የሙሉ ጊዜ ቴአትር ነው። ይህ በደራሲ ውድነህ ክፍሌ ተጽፎ፤ በተሻለ አሰፋ የተዘጋጀው “ቅጥልጥል ኮከቦች” የተሰኘው ቴአትር።

የምስኪን ዜጎችን ህይወት እየነጠቀና አደጋ ላይ እየጣለ ለውጪ ሀገር ዜጎች በዶላር የሚቸበቸብ ኩላሊትን የሚያቀርብ ድርጅትን ስውር ሴራ በማስረጃ አስደግፎ ለህዝብ አይንና ጆሮ ለማድረስ የሚታትረው ጋዜጠኛ አዲስ (ሽመልስ አበራ (ጆሮ)) ከአሳዳጆቹ ለመሸሽ ሲል በፍቅር ከሚያውቃት ወዳጁ ቤት ተደብቋል። የአዲስ የፍቅር አጋር ወይንሸት (መሰረተ ህይወት) ከጋዜጠኛው አሳዳጆች አንዷ ብትሆንም በወዳጇና በተሰጣት ተልዕኮ መካከል ሆና የምትወጠርበት የጭንቅ ስብጥር ከመጀመሪያው ትዕይንት ጀምሮ የሚንተከተክ የስሜት ጡዘትን ይዟል።

በሰው አካል ስርቆት ላይ በተሰማሩት አሳዳጆችና መረጃውን ለህዝብ አይንና ጆሮ ለማድረስ በሚታትረው ጋዜጠኛ መካከል በስውር የቆሙት አገር ወዳጆቹ የቅጥልጥል ኮከቦች አባላት የሚፋለሙበት ይህ ቴአትር፤ ለሁለት ሰዓት ከግማሽ በላይ የተመልካቹን ቀልብ እንደያዘ መቆየት የሚችል ነው።

የተዋንያኑ አቅምና የውህደት ደረጃ ስራው ተውኔት መሆኑን የማስረሳት አቅም የነበረው ነው ማለት ይቻላል። በተለይም የሽመልስ አበራ (ጆሮ) አተዋወን ችሎታ ብዙ ተመልካቾችን የመሰጠ ያስደሰተና በአድናቆት ጭብጨባን ያስደጋገመ ጭምር ሆኗል። ሽመልስ አበራ (ጆሮ) የተሰጠውን ገፀ-ባህሪይ “አዲስ”ን በብቃት ከመተወኑም ባሻገር በጭንቀቱና በደስታው መካከል በሚቀያየር ስሜቱ በላብ ወርዝቶ ለሚመለከተው ተመልካች የልፋቱን ጣሪያ በጉልህ የሚያሳይለት ሆኗል። ይህም ብቻ አይደለም ተዋንያኑ ከተዋንያኑ ጋር እርስ በእርስ የነበራቸውም ጥምረት መጠቀስ የሚያስችል አቅም አለው።

“በታዳጊ አገር ውስጥ የምርመራ ጋዜጠኝነትን መስራት ነፍስን የመስጠት ያህል ነው” የሚለው ጋዜጠኛ አዲስ፤ የሙያውን ስነ-ምግባርና የህዝብን አደራ ለመውጣት የቆረጠ ሆኖ ተስሏል። እርሱ ያገኘው መረጃና አሳዳጆቹ ያላቸው ጉልበት የቴአትሩን ውጥረትና ልብ አንጠልጣይነት ከፍ እንዲል አድርጎታል። ከሁሉም በላይ ደግሞ አሳዳጆቹ የሚሰበስቡበት የወይንሸት ቤት፤ የጋዜጠኛው መሸሸጊያ መሆኑን ለሚመለከተው ተመልካች “አይጥ የድመትን አፍንጫ የማሽተት” ያህል አድርጎ ሊቆጠር ይችላል።

በአንጻሩ ደግሞ የራሱን ኩላሊት በውጪ ሀገር ህክምና በብዙ ብር አስቀይሮ የመጣውና ይህ ነገር “ቢዝነስ” እንዲሆን ሴራ ጎንጉኖ፤ “ዋሲም” የተሰኘ የህክምና ተቋምን የከፈተው ደበበ (ሳሙኤል ተስፋዬ)፣ ምን ያህል ራስ ወዳድና ጨካኝ ሰው እንደሆነ ለተመለከተው ፍጥጫውን በንቃት እንዲጠባበቅ ያደርገዋል። እዚህ'ጋ “ሰውን ያህል ጥሬ ዕቃ ከነሙሉ አካሉ ወደአፈር መክተት በዚህች ሀገር ሃብት ላይ መቀለድ ነው” የሚለው ይህ ሰው፤ “የሚቆጨው ሰው ከነሙሉ አካሉ መቀበሩ እንደሆነ” ሲነግረን የአዘጋጁ ጥበብ በድርጊት ሲገለጥ ወደተመልካቹ ጣቱን እያሳየ “ገና እቸበችበዋለሁ!” ይለናል። ይህ ሰው ከኩላሊት ንግድ ባሻገር የሌሎች አካላት ሽያጭንም ለማጧጧፍ እቅድ ያለው “ሆድ አምላኩ” ነው። ለዚህ አላማውም ማስፈፀሚያ በዙሪያው ያሉትን ሰዎች ሁሉ በጥቅም በመደለል የሚያፍን ነው። በዝግጅት ሂደቱ ወደተመልካቹ ላይ እጁን ቀስሮ የሚሳለቅበትና የሚያሳስቅበት ትዕይንት ውስጥ “የአፋልጉኝ ማስታወቂያ የበዛው በኛ ስራ ምክንያት ይመስለኛል” ሲል የማሳቁን ያህል፤ የስላቁን ጣሪያ ለማሳየት፣ “እዚህች አገር ላይ ልማታዊ ባለሀብት መሆን መሳቀቅ ነው” ሲል የተመልካቹን ሳቅ ከፍታ ያንረዋል።

የእህቷን የእብደት መንስኤ እንኳን በቅጡ ያልተረዳችው ወይንሸት፤ ፍቅረኛዋ ጋዜጠኛ አዲስ የያዘው መረጃ እርሷን ጨምሮ በአባልነት በምትሰራበት ድርጅት ውስጥ ያሉትን አጋሮቿን በሙሉ ጠራርጎ ከአፈር የሚደባልቅ መሆኑን ብታውቅም እርሱን ላለማጣትና በሆዷ የያዘችውንም “ፅንስ” አባት ላለማሳጣት የገባችበት አጣብቂኝ፤ በጥቅሟና በፍቅሯ መካከል በባህር ላይ አውሎ ነፋስ እንደሚወዘውዛት ጀልባ አቅም ሲያሳጣት እንመለከታለን። “በዚህ ዕድሜዬ ከመወደድና ከመወለድ ምረጪ ብባል መውለድን እመርጣለሁ” የምትለው ወይንሸት፤ እድሜዋ፣ ሴትነቷና የእናትነት አምሮቷ ተዳምረው ፍቅረኛዋን ላለማጣት ያላትን ፍራቻ ስትገልፅ፣ “ሰላሳዬን ካንተ ጋር አጋምሼ ላጣህ አልፈልግም” ስትል ትሰማለች።

አፈቅረዋለሁ ባለችው ሰው ተመልምላ፤ የፀነሰችውን ነፍስ ያጣችውና ፍቅሯ የመረረባት የስነ-ልቦና ባለሙያዊ ቲቲ (ስናፍቅሽ ተስፋዬ) ከራሷ ጉዳት ተነስታ ሌሎችን ለመከላከል ስትል የጥፋት ቡድኑን ለመዋጋት ብላ “እብደትን” የተቀበለች የ“ቅጥልጥል ኮከቦች” ፈርጥ ሆና ትተውናለች። 

“ቅጥልጥል ኮከቦች” ይህቺ አገር በልማትና በባለሃብት ስም ዜጎችን እየሸጡና ህመምን እያበዙ የራሳቸውን የተመቻቸ ኑሮና የማህበረሰቡን ህመም ከዕለት ወደዕለት የከፋ የሚያደርጉ “አያ ጅቦ!” ተብዬዎች የመብዛታቸውን ያህል፤ ራሳቸውን ለሙያቸውና ለሙያዊ ሥነ-ምግባር አስገዝተው እናገለግለዋለን ባሉት ህዝብ ከመገልገል ይልቅ ማገልገልን የመረጡ ታጋዮች ለመስዋት ያላቸውን ቁርጠኝነት ጭምር ያሳየ ቴአትር ነው።

መገናኛ ብዙሃን (ጋዜጠኝነት) የብዙሃንን እንባና ጩኸት በአደባባይ እንካችሁ የፍትህና የፍርድ ያለህ! “ብለው የሚጮሁ ተቋማት ከመሆን በተቃራኒ፤ ክፉዎችን፣ ሞራለ ቢሶችንና አያ ጅቦዎችን በሌላቸው ስምና የዝና ካባ ሸፍነው ማኖር የሚችሉ “የአደባባይ ምሽጎች” የመሆን አቅም እንዳላቸው “ቅጥልጥል ኮከቦች” ቴአትር ይጠቁመናል።

ሁሉም ሰው  በየተሰማራበት ከራሱ በላይ አሻግሮና ቀጥሎ ማየት እስካልቻለ ድረስ የማህበረሰብን መፍረስ አይቀሬነት የሚያሳየው ቴአትሩ፤ ሁሉም ባይሆን እንኳን አንዳንዶች ለአገር፣ ለወገንና ለራሳቸው ሲሉ ለፍትህ፣ ለእኩልነት፣ ለሞራልና ለመልካምነት ቅጥልጥሎሽ ቢሰሩ አንድ ቀን እንደኮከብ አብርተው መውጣታቸው አይቀርም፤ እነዛም ሰዎች ናቸው በተከፈለው መሰዋትነት ሁሉ መካከል ተገኝተው “ቅጥልጥል ኮከቦች” የሚሆኑልን። ታዳጊ አገሮች ነፍስን የሚያስከፍሉ ከጋዜጠኝነትም በላይ ብዙ የሞራል ጥያቄዎችን የሚያጭሩ ክስተቶች በየቦታውና በየመስኩ የሚከናወንባቸው “አኬልዳማዎች” ናቸው። ለዚህም ነፃ እንወጣ ዘንድ ህይወታቸውን የማይሰስቱ “ቅጥልጥል ኮከቦች” ያስፈልጉናል።

      “ቅጥልጥል ኮከቦች” በአንድ ድንጋይ “ብዙ” ሊባልበት የሚያስችል ቴአትር ነው። የቋንቋ አጠቃቀሙ ደራሲውን፣ የመድረክ እንቅስቃሴዎቹ አዘጋጆቹን፤ የትወና ውህደቱ ተዋንያኑን የሚያስመርቀን ድንቅ ቴአትር ነው። ያም ሆኖ “ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት” እንዲሉ ሊነሱ የሚገባቸው የሚጎረብጡ የአመክንዮ መላላቶችም ተስተውለውበታል። አንደኛው በምርመራ ጋዜጠኝነት ቁም ስቅሉን የሚያየው አዲስ (ሽመልስ አበራ (ጆሮ)) የህገ-ወጥ ድርጅቱን በርካታ ሚስጥሮችና ጉዳጉዶች አነፍንፎ ሲደርስ የፍቅረኛውን አባል መሆን ሊያውቅ አለመቻሉ ጥያቄን ያጭራል። ሌላውና ሁለተኛው ደግሞ የእህትማማቾቹ የሀሳብ ልዩነትና አለመተዋወቅ የታሪኩን ጡዘት ከፍ ከማድረግ ባለፈ ይህን ያህል መቆየታቸው እምነት አጉዳይ ነው። በስተመጨረሻም እንደ ግርጌ- ማስታወሻ ብትያዝ የማልከፋበት አንድ ነገር በተለይም በመጀመሪያዎቹ የግጭት ትዕይንቶች ወቅት ወይንሸት (መሰረት ህይወት) እና ደበበ (ሳሙኤል ተስፋዬ) ደጋግመው ሲጋራቸውን በማጨሳቸው ያለ ፍላጎታቸው እንዲያጨሱ የተገደዱ ተመልካቾችን ቅር ሊያሰኝ ይችላልና ቀነስ ቢደረግ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
12004 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us