ኢንቫይሮንመንት

ኢንቫይሮንመንት (45)

ሀገራችን በብዝሃ ህይወት ተለያይነትና እጅግ መበርከት የተነሳ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ካገኙት ሀገሮች መካከል አንደኛዋ መሆን ችላለች። ብዝሃነት መኖር ስነ-ምህዳር ሳይዛባ እንዲቆይ በማድረግ በሰው ልጅ እንቅስቃሴ የሚፈጠረውን የሙቀት መጨመርና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ያስችላል። ይህ ብቻ ሳይሆን ለምግብነት የሚውል ተክሎችን በማብዛት በምግብ ራስን ለመቻል እገዛ ያደርጋል።

የሀገራችን መልክዓ ምድር አቀማመጥ በጣም አስገራሚና የተለያዩ የአየር ፀባዮችን በውስጡ ለማቀፍ ያስቻለ ነው። ከባህር ወለል በታች እስከ 5 ሜትር ከሆነው ዳሎል አካባቢ እስከ በረዷማውና ከባህር ወለል ከፍታው 4,591 ሜትር ድረስ ያለውን ያጠቃልላል። ከቆላ ደጋ ወይናደጋና በርሃ ተብለው ከተለዩት የአየር ፀባያት በተጨማሪ እስከ 18 የሚደርሱ አግሮ ኢኮሎጂ ዞን እንደያዙ ሙያተኞች ይገልፁታል። ይህም በርካታ ተለያይነት ያላቸው ለዘርፉ ብዙ ጠቀሜታ ሊሰጡ የሚችሉ የጄኔቲክ ሀብቶች እንዲገኙ ምክንያት ሆኗል። በኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢኒስቲትዩት የጄኔቲክ ሀብት አርክቦትና ጥቅም ተጋሪነት ዳይሬክተር ዶክተር ዘለቀ ወልደሚካኤል እንደሚገልፁት፤ የብዝሃ ህይወት ዕፅዋት እንስሳትና የደቂቅ አካላት ዘረመሎች በስብጥርና በተደጋጋፊነት የሚኖሩበት ስርዓተ ምድር ሲሆን፤ የእነዚህ ሀብቶች ይዘትና መጠንም የበርካታ ዘመናት የተፈጥሮ ውጤት ሂደት ነው።

የብዝሃ ህይወት ሀብቶችን በመንከባከብ በማበልፀግና በዘላቂነት በመጠቀም ረገድ አርሶ አደሩ የላቀ ሚና ተጫውቷል። በሀገራችን ለረጅም ጊዜ በምግብነት ጥቅም ላይ የዋሉት ስንዴ፣ ምስር፣ ማሽላ ከቅጠላ ቅጠል ምግቦች ደግሞ እንደ ጐመን፣ ካሮት እና እንሰት የመሳሰሉት ሳይጠፉ የቆዩት አርሶ አደሩ ከምግብነት በተጨማሪ ለዘርነት በማከማቸት ስላቆያቸው ነው። በድርቅ ወቅት አካባቢውን በመልቀቅ በሚሰደዱበት ወቅት የአዝዕርት እህሎችን በማሰሮ በማድረግ ጉድጓድ ውስጥ በመቅበር ክፉ ቀን ካለፈ በኋላ ወደቀያቸው በመመለስ ዘሮችን በመዝራት ቀጣይነት እንዲኖራቸው አድርገዋል። አዝዕርቶች ለተለያዩ ምግብነት ማለትም ለዳቦ፣ ለእንጀራ፣ ለቂጣ፣ ለቅንጬ፣ ለገንፎ፣ ለንፍሮ፣ ለቆሎ ወዘተ በሚቀላቸው የምግብ አሰራር እውቀቱ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ በመዝለቁ ለአዘዕርቶችም ቀጣይነት የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል። አዝዕርቶችና ተክሎች በሚበቅሉበት አካባቢ ተጠብቀው መቆየታቸው የአፈር ኬሚካሎች መስተጋብር እንዲካሄድ የአየር መዛባት እንዳይፈጠር በአካባቢው ያሉ አራዊቶችዋ እንዳይጠፉና እንዲኖሩ አድርጓል። ብዝሃ ህይወት ከዚህ በተጨማሪ የዕፅዋት በሽታዎች ሲያጋጥሙ ከመካከላቸው በሽታውን መቋቋም የሚችሉትን ለይቶ በማውጣትና በማራባት በበሽታ የተጠቃው ተክል ከመጥፋት እንዲድን ማድረግ ያስችላል። ከዚህ አኳያ የጄኔቲክ ሀብታችን ለሌሎች ሀገሮች እንደተረፈ ጭምር መረዳት አያዳግትም።

ለአብነትም ከ10 ዓመታት በፊት በዶ/ር ሰለሞን ይርጋ የአራት ኪሎ ሳይንስ ፋኩልቲ ተመራማሪ “ህልውና” ብለው በፃፉት መጽሐፋቸው ላይ የጠቀሱትን ማንሳት ይቻላል። በደርግ አገዛዝ ዘመን በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት የሚገኝ አንድ የቢራ ገብስ አምራች ኩባንያ ገብሱ በበሽታ ይመታበታል። በዚህ ሳቢያም ለፋብሪካው የሚቀርብ የቢራ ገብስ እየተመናመነ መጥቶ ፋብሪካው ወደ መዘጋት ይቃረባል። ይሁን እንጂ የኩባንያው ባለቤቶች ፋብሪካውን ከመዝጋት ለማዳን ትኩረታቸውን በብዝሃነት ወደምትታወቀው ኢትዮጵያ ያደርጋሉ። ከዚያም ወደዚህ በመምጣት ከካሊፎርኒያ ጋር ተመሳሳይ የአየር ፀባይ ካለው ወደ ሰሜን ሸዋ በማምራት ምርምር አድርገው በሽታውን መቋቋም የሚችል የገብስ ዘር ማግኘት በመቻላቸው ዘሩን ከኢትዮጵያ ወስደው አሜሪካ በመትከልና በማራባት ስንዴውን ከመጥፋት ከማዳን በተጨማሪ የቢራ ፋብሪካውን ከመዘጋት አድነውታል።

ይሁን እንጂ ከዚህ የጄኔቲክ ሀብት ሀገራችንም ሆነች የአካባቢው አርሶ አደሮች አንዳችም ጥቅም አላገኙም። የገብሱ ዘር በዝርያ ተወልዷል ማለት ይቻል። በሌሎች በሰለጠኑት ሀገሮች ቢሆን ቀድሞውኑ ሲጀመር የሌሎች ሀገሮች ተመራማሪዎች የጄኔቲክ ሀብት ሲፈልጉ በአግባቡና በሕግ አስፈቅደውና አስፈላጊውን ክፍያ በመፈፀም ነው። በዚያን ዘመን በሀገራችን ይህን በሚመለከት ጠንካራ ተቋማትና ሕጐች ስላልነበሩ ችግሩ ሊከሰት ችሏል። ከዚህ አንፃር የሀገራችን የጄኔቲክ ሀብት እንዲጠበቅ በማድረግ በኩል የብዝሃ ህይወት ጽህፈት ቤት ከፍተኛ ኃላፊነት ይጠበቅበታል።

ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መልኩ በጤፍ ሀብታችን ላይ የተፈፀመው ደባ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ጤፍ በአሁኑ ወቅት በውስጡ የያዘው ንጥረ ነገር ከፍተኛ በመሆኑና ከኮሌስትሮል የነፃ በመሆኑ በአውሮፓ ገበያ ጭምር ፍላጐቱ እያደገ መጥቷል። በዚህ የተነሳ አንድ የሆላንድ ኩባንያ የፓተንት መብትን በሕግ ከኢትዮጵያ በመግዛት ምርቱን ለማስተዋወቅ የገባውን ውል በማፍረስ በራሱ ባለቤትነት ስም በማስተዋወቁ ጉዳዩ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን ዶ/ር ክበበው ሰለሞን የተባሉ የደብረዘይት እርሻ ምርምር ተቋም ተመራማሪ በቅርቡ መግለፃቸው አይዘነጋም።

ከዚህ አኳያ የጄኔቲክ ሀብት ከየት ሀገር ተገኘ የሚለው በራሱ በሕግ ዕውቅና የተሰጠው ሲሆን፤ ወስዶ ለመጠቀምም ሕግና ስርዓት ተበጅቶለታል። ይሁን እንጂ ለዘመናት የጄኔቲክ ሀብት በዘፈቀደ ሲዘረፍ እንደቆየ የሚታወቅ ነው። አሁን እየተደረገ ያለው የጥበቃ ጥረትም ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው ነው።

በአሁኑ ወቅት በዓለም በጣዕሙ ጥሩነት የሚታወቀው ቡና ከኢትዮጵያ የተገኘውና በተለያዩ የዓለም አህጉራት የተሰራጨው ኮፊ አረቢካ የተባለው ሲሆን፤ ኢትዮጵያንም በማስጠራት ላይ ይገኛል። አብዛኛው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኘው የቡና ተክል በተፈጥሮ የበቀለና በጥቅጥቅ ደን ውስጥ የሚገኝ ነው። ለቡናው እንክብካቤ መደረጉ ደኑ እንዲጠበቅ ማድረጉ የሚታወቅ ነው። ይህን በተመለከተ ዶ/ራ ዘለቀ ሲገልፁ፤ ቡና ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው የጄኔቲክ ሀብት በመሆኑ በዘላቂነት ጥቅም ላይ እንዲውልና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ የአካባቢውን ስነምህዳር እንዲጠበቅ ማድረግ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ቡና በተፈጥሮው ጥላ ስለሚፈልግ ደኑ ከተመነጠረ ቡናውም ወደ መመናመን ስለሚያመራ የአካባቢ ጥበቃ ስራ መስራቱን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ይታመናል። ዶ/ር ዘለቀ አክለው እንደሚያስረዱት፤ የጫካ ቡናና ሌሎች የብዝሃ ህይወት ሀብቶችን በተገቢው መንገድ መጠበቅ በተለይ በአካባቢው ያለው ማኅበረሰብ ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት። ከዚሁ ጐን ለጐንም የብዝሃ ህይወት የሚያስገኘው ሀብት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተገቢ በመሆኙ በዚህ ረገድ የወጡትን ሕጐችንና ደንቦች እንዲያውቁ በብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት አማካኝነት ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተሰራ ይገኛል።

ይሁን እንጂ በቡና አብቃይነት የሚታወቀው የሸካ አካባቢ ደን አደጋ እየተጋረጠበት መሆኑን አንዳንድ በአካባቢ ጥበቃ ስራ በቦታው የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይገልፃሉ። ይህን በተመለከተ የመልካ ኢትዮጵያ ማኅበር ስራ እስኪያጅ ዶ/ር ሚሊዮን በላይ ሲገልፁ አካባቢው በጥቅጥቅ ደን የተሸፈነ ከመሆኑም በላይ 10 ለሚሆኑ ወንዞች በምንጭነት ያገለግላል። በዓመት ለ10 ወራትም ዝናብ በማግኘት ይታወቃል። ነገር ግን በህዝብ ብዛት መጠናቀቅ የተነሳ ባለው የስራ መጣበብ ሰዎች በመሀል ደን ውስጥ በመግባት አካባቢውን በመመንጠር ቡና በመትከልና በማልማት የራሳቸውን ገቢ እየፈጠሩ ይገኛሉ። ይህም በደኑ ላይ አሉታዊ ጫና እያስከተለ ይገኛል። እንደሚታወቀው ቡና Cash Crop ነው። በቀላሉ ተመርቶ ብዙ ገንዘብ የሚያስገኝ ነው። ስለሆነም የአካባቢው ሰዎች በቡና ስራ በመጠመድ በደን ምንጠራ ስራ መሰማራታቸው ለወደፊቱ በብዝሃ ህይወት ላይ አሉታዊ ጫና መፍጠሩ ስለማይቀር ሁኔታው ከወዲሁ ቁጥጥር ሊደረግበት ግድ ይላል።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የባዮሎጂ ተመራማሪው ዶክተር ቄጡሱ ሁንዲራ ከላይ በዶ/ር ሚሊዮን የተገለፀውን አባባል ያጠናክራሉ። በሀገሪቱ ቡና በሚበቅልባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለተለያየ ጥቅም በደኑ ውስጥ ያሉ ትላልቅ ዛፎችን ይቆርጣሉ። የዛፉ መቆረጥ ቡናውን ፀሐይ እንዲያገኝ በማድረግ ምርት መጨመር ቢቻልም በተቃራኒው የአካባቢው አየር ንብረት እንዲለወጥ በማድረግ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ ይገኛል። የተፈጥሮ ቡና በዓለም ተወዳጅነት ያለው ነው። ጣዕሙም ተመራጭ ነው። በባህርይው ጥላ ይፈልጋል። ጥላው የሚገኘው ከደኖች ነው። ደኖች ከተቆረጡ የቡናው ህልውናውም ያከትማል። ስለዚህ ጥንቃቄ ማድረጉ ተገቢ ነው።

በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ወደ ውጭ የምትልከው ቡና መጠን በመጨመር ላይ ይገኛል። ለዚህ ሲባልም አዳዲስ የቡና እርሻ መሬቶች በመስፋፋት ላይ ይገኛሉ። የቡና ችግኞችም የሚራቡትና የሚሰራጩትም የአካባቢውን ስነምህዳርና የአየር ፀባይ ከግምት በማስገባት ነው። የቡና ፍሬ እንደማናቸውም አዝዕርት የተለያዩ የጄኔቲክ ክፍሎች አሉት። ችግኞቹም በደጋና በወይና ደጋ አየር ፀባይ ላይ መብቀል እንደሚችሉ ተረጋግጦ ለገበሬዎች ይታደላል። በዛም መሰረት የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው ውጤታማነታቸውን ከማስመስከራቸውም በተጨማሪ ራሳቸውን ውርጭ ከሚያስጥለው በሽታ ለመጠበቅ ችለዋል። እነኚህ ችግኞችም በተለያዩ አካባቢዎች እየተሰራጩ እንደሚገኙ ሙያተኛው ገልፀዋል።

የብዝሃነት ጠቀሜታ አካባቢን ከመጠበቅ በተጨማሪ የተለያየ የጄኔቲክ ማንነት ያላቸው አዝዕርቶች በተለያዩ አካባቢና እጅግ በጣም ተቃራኒ የአየር ፀባይ ባለበት አካባቢ ለመብቀል ጭምር አስችሏቸዋል። እንደ ደብረዘይት የእርሻ ምርምር ተቋም ተመራማሪው ዶ/ር ክበበው ገለፃ፤ ለምሳሌ ጤፍ ከበረሃማ ቦታዎች ጀምሮ እስከ ከባህር ወለል 2,000 ሜትር በላይ በሚገኙ ደጋማ ቦታዎች መብቀል የቻለው በውስጡ ብዙ ተለያይ የሆኑ አይነቴዎችን በመያዙ ነው። ስለሆነም የጄኔቲክ ሀብት ከተጠበቀ ድርቅም ሆነ የተፈጥሮ አደጋ ቢከሰት የጐርፍ መጥለቅለቅ ጭምር ቢመጣ የዘር አይነቶቹ ተለይተው በሚስማማቸው የመሬት አቀማመጥና የአየር ፀባይ እንዲበቅሉ በማድረግ ቀጣይነታቸውን ማረጋገጥ ይቻላል። ይህም በራሱ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል።

በስርዓት በተጠበቀ ስነ ምህዳር ውስጥ የሚገኙ ነባር ዝርያዎች ከበሽታና ከድርቅ የተነሳ የሚከሰቱ የአካባቢ ተፅዕኖዎችን በመቋቋም የተሻለ ምርት እንደሚሰጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያም ሆነ በሌላው ዓለም የሚገኝ በቆሎና ዳጉሳ ከደጋ ጀምሮ በርሃማና በርሃ ቀመስ በሆኑ ቦታዎች በመብቀል ምርትን መስጠት መቻሉ በውስጡ የተለያዩ ዘረ መሎችን በመያዙ ነው። ይህ ዘረመል በተክሉ ውስጥ ያለውን ባህርይና ማንነት ይወስናል። ዘሩ በቆሎ ወይም ስንዴ ቢሆን ሁሉም ተመሳሳይ ነው ማለት አይደለም። ፍሬው በቆሎ ሆኖ የሚበቅልበት ቦታ ይወስነዋል። በደጋማ ቦታ ላይ መተከል ያለበት በቆሎ ቆላማ ቦታ ላይ ቢተከል ፍሬ አይሰጥም። ይህንን ሁሉ ጉዳይ ሙያተኞችም ሆነ አርሶ አደሮች በተገቢው በማወቃቸውና ስራ ላይ በማዋላቸው የሀገራችን ብዝሃ ሀብት እንደተጠበቀ ሊቆይ ችሏል።

በአሁኑ ወቅት በሀገራችን አርሶ አደሮች በኅብረት ስራ ማኅበሮቻቸው አማካኝነት የተለያዩ ጄኔቲክ መሰረት ያላቸውን የዘር እህሎችን ማለትም ድርቅን መቋቋም፣ ለበሽታ የማይበገሩትንና ምርታማነታቸው ከፍተኛ የሆኑትንም በመለየት በመጋዘኖች አከማችተው እንደየፍላጐታቸው እየተጠቀሙባቸው ይገኛል። ይህም ለብዝሃነት መጠበቅ የራሱን እገዛ እያደረገ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በሀገራችን በሚገኙ 13 የአዝዕርት የምርምር ጣቢያዎች ውስጥ የተለያየ ዘረመል መሠረት ያላቸው እህሎች በስርዓት ተቀምጠው ምርምር የሚደረግባቸው ሲሆን፤ በምርምር የተሻሻሉ ዘሮችም ተመርጠው ለአርሶ አደሩ እንደሚደርሱ ዶ/ር ዘለቀ ይገልፃሉ። ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ የጄኔቲክ ኢንስቲትዩት ውስጥ የዚህ መሰሉ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

    በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ6 ሺህ በላይ የዕፅዋት ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥም ከ10 እስከ 12 በመቶ የሚሆኑት በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ እንደሚገኙ የጄኔቲክ ባለሙያዎች ይገልፃሉ። እኒህ ዝርያዎቹ እንዲበራከቱ ያደረገውም ሀገራቱ እጅግ በጣም የተበራከተ የመልክዓ ምድር ገጽታና የአየር ፀባይ በመያዝዋ ሲሆን፤ አብዛኛውም ዱር በቀል ነው። አብዛኛዎቹም በደን፣ በሣራማ፣ በቁጥቋጦ እንዲሁም በርጥበታማ መሬቶች ላይ ይገኛሉ። ስለሆነም ስነምህዳሩ ተጠብቆ እንዲቆይ ለብዝሃ ህይወት ክብካቤ ማድረጉ ጠቃሚ ነው።

በኢትዮጵያ የግብርና ሥራ ለጅም ጊዜ ያስቆጠረ ሲሆን፤ ከክርስቶስ ልደት በፊት በአክሱም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ሲተገበር ቆይቷል። እርሻ በዛን ዘመን ለነበሩ መንግሥታት እንደ አይነተኛ የገቢ ምንጭ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ለመንግሥት ሃያልነትም ስልተ ምርቱ ጠንካራ መሠረት ሆኖ ቆይቷል። ለበርካታ ምዕተ ዓመታት ለኢትዮጵያ መንግሥታት መቀመጫ የነበረው የሰሜኑ የሀገራችን አካባቢም በተለይ ደጋውና ተራራማው ክፍል ለዘመናት ያለዕረፍት ሲታረስ ከርሟል። ከዚሁ ሥራ ጎን ለጎን የሚካሄደው የከብት ርባታም የአካባቢው የግጦሽ መሬት በጣም እንዲጋጥና እንዲራቆት አድርጓል። ይህ በበቂ እውቀት ያልታገዘ የእርሻ ሥራ በብዙ ዘመን መቀበሉ አሁን ላለው የመሬት መበላትና መጎዳት የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል።

ከዚሁ ጎን ለጎን የህዝብ ብዛት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄድ የአርሶ አደሩ የመሬት ይዞታ መጠን ይበልጥ እየቀነሰ እንዲሄድ ያደረገ ሲሆን ይህም ለመሬት መሸርሸርና መጎዳት የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል። በመሬት ማነስ የተነሳም በተለይ በሰሜኑ የሀገራችን አካባቢ በጣም ገዳላማ የሆኑ መሬቶች ጭምር ለእርሻ ስራ እንዲውሉ ተገዷል። ይህም ለአፈር መታጠብና መከላት አስተዋጽኦ አድርጓል። በዚህ ሁኔታ በሚታረስ መሬት በባህላዊ ዘዴ የሚካሄደው የመሬት እንክብካቤ ማለትም አዝርእቶችን ማፈራረቅ መሬትን መከተርና የመሳሰሉት ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም። የአፈር መከላትን ለመግታትም አስቸጋሪ ነው።

ከዚህ ከሰው ልጅ የእርሻ እንቅስቃሴ በተጓዳኝ ተፈጥሮም ለመሬት መበላት የበኩሏን አስተዋፅኦ ታደርጋለች። ከፍተኛ የዝናብ መጠን በክረምት ወቅት መምጣቱ እንዲሁም አውሎ ንፋስ የአፈር መሸርሸር መባባስን አስከትሏል። ምንም እንኳን ያለፉት መንግሥታት በተለያዩ አቀራረቦች በተለይም በምግብ ለሥራ ፕሮግራም አማካኝነት ከዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመተባበር የተጎዱ መሬቶችን መልሰው እንዲያገግሙ ለማድረግ በተለይ ላለፉት 50 ዓመታት ጥረት ቢደረግም በህዝብ ቁጥር እድገት የተነሳ ደኖች እየተመነጠሩ ምንጮችና ሀይቆች እየደረቁ አካባቢ ሲጎዳ ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ ከልማት አጋር መንግሥታትና ድርጅቶች ጋር የተጎዳ መሬት መልሶ እንዲያገግም ለማድረግ ጥረት እያደረገ ይገኛል። ይህ ሁኔታ በተለይ በአርሶ አደሩ አማካኝነት በተፋሰስ ልማት የተሰራው ሥራ ተስፋ ሰጭ ምልክቶችን እያሳየ ይገኛል።

መንግሥት የተራቆቱ መሬቶችን እንዲያገግሙ ለማድረግ መርሃ ግብር ይዞ መተግበር የጀመረው ከ7 ዓመታት በፊት እንደነበር የሚጠቅሱት በግብርና ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ የሆኑትና የሚኒስትሩ አማካሪ ፕሮፌሰር ተካልኝ ማሞ በፌዴራል መንግሥትና በክልል መንግሥታት ትብብር፣ በገበሬ ማህበራትና በሲቪል ማህበራት በመታገዝ በመሠራቱ ተጨባጭ ውጤት መምጣቱን አመልክተዋል።

እንደ እርሳቸው ገለፃ መሬትን መልሶ እንዲያገግም በተደረገው ሥራ በአማራ፣ በትግራይና በኦሮሚያ፣ በደቡብ እና በቤንሻንጉል ክልሎች ውጤቶች ታይተዋል። የተራቆቱ መሬቶች እንደገና ደን ለብሰዋል። በዝናብ ጊዜ የሚመጣው ውሃ ወደ መሬት መስረግ በመቻሉና በጎርፍ መልክ አለመፍሰሱ ምንጮችን ሀይቆች ወደነበሩበት ለመመለስ ተችሏል። ገበሬዎች ለእርሻነት አይሆኑም ብለው የተዋቸውን መሬቶች እንደገና መጠቀም ችለዋል። በአካባቢው ጠፍተው የነበሩ አውሬዎችም ተመልሰው መጥተዋል። አፈርም ርጥበትን መልሶ ተላብሷል። ይህም በድርቅ የመጠቃትን አደጋ ከመቀነስ አልፎ ለገበሬው የተሻለ ተስፋን ለመፈንጠቅ ችሏል።

በቅርቡ በፌዴራል መንግሥትና በክልሎች ትብብር በትግራይ ክልል የተከናወነውን የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ የማገገም ሥራን በተመለከተ በስፍራው ከሄደው ጎብኚ የባለሥልጣናት ቡድን ጋር ወደዚያው የተጓዙት የአለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስተር ጉዋንግ ዚቼን እንዳመለከቱት ከሰባት ዓመታት በፊት በአለም ባንክ እገዛና በኢትዮጵያ መንግሥት ጥብቅ ክትትል የተከናወነው የመሬት ማገገም ስራ ውጤታማ እየሆነ ነው። ውጤቱ ሊገኝ የቻለውም ከፍተኛው የመንግስት አካል እስከ ታችኛው አርሶ አደር ጉዳዩን በባለቤትነት በመያዝና ተግተው በመስራታቸው እንደሆነ ገልፀው ተቋማቸው ለወደፊቱም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የባንኩ ዳይሬክተር በማከልም በተጠናከረና በቁርጠኝነት በሚሰራ ስራ የተራቆተ አካባቢን መሬት፣ ዛፎች፣ ውሃዎችንና ተዛማጅ ስነምህዳሮችን መልሶ እንዲያገግም ማድረግ ድህነትን በመቀነስም ሆነ በምግብ ራስን ለመቻል ለሚደረገው ጥረት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በድንገት ከሚከሰቱ የአየር ንብረት ለውጦችና ሙቀት መጨመር ሳቢያ ሊፈጠር የሚችለውን የግብርና ቀውስን ለመታደግ ከፍተኛ አማራጭ መሆኑን ጠቅሰዋል።

“እንደሚታወቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች ከፍተኛ የህዝብ ክምችት የሚገኝባቸው ናቸው። የወሊድ መጠኑም ከፍተኛ ነው። ስለሆነም የህዝብ ቁጥርን የሚመጥን የተፈጥሮ እንክብካቤ ማድረግ ካልተቻለ አሁን የተገኙት አውንታዊ ውጤቶች ተመልሰው የሚቀለበሱበት አጋጣሚ ሊመጣ ይችላል” ብለዋል የባንኩ ዳይሬክተር።

የህዝብ ቁጥር እድገት በተገቢው ካልተያዘ በተፈጥሮ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያስከትል ይህም እንደገና ድህነትን እንደሚያባብስ የተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በአብነት በመጥቀስ መከራከር ይቻላል። ለምሳሌ ከ20 ዓመታት በፊት ከሻሸመኔ እስከ ወንዶ ገነት እንዲሁም ከወንዶ ገነት ዙሪያ እስከ አዋሳ መዳረሻ ድረስ የነበረው አካባቢ 80 በመቶው ህዝብ ያልሰፈረበት ነበር። ደኖች ጥቅጥቅ ብለው ይታዩ ነበር። ከወንዶ ገነት ተራሮች የሚፈሱት ጅረቶችና ወንዞች ከላይ ተንደርድረው በመፍሰስ የሀዋሳ ሀይቅን ያጠግቡት ነበር። ዛሬ ከሁለት አስርታት በኋላ ሁኔታው ፍፁም ተለውጧል። ባዶ የነበረው ቦታ ህዝብ ሰፍሮበታል። ደኖች ተመንጥረው ወደ እርሻነት ተቀይረዋል። ደን ለአብዛኛው ገቢ ለሌለው የአካባቢው ነዋሪ ለማገዶነትና ለከሰልነት እየዋለ ለገበያ በመቅረብ መተዳደሪያ ሆኗል። ይህ ደግሞ ለደን መመንጠር ለአፈር መሸርሸርና መራቆት የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቶ ከተራሮች ወደ ሀዋሳ ሀይቅ የሚጎርፉት ጅረቶችም በክረምት ካልሆነ በበጋ የሚታዩ መሆናቸው አክትሟል። ይህ ሁኔታ ወደፊት ለሀይቁ ውሃ መቀነስና ለስነምህዳር መዛባት ምክንያት በመሆን ድህነትን ለመቀነስ የሚደረገውን ትግልንም ሆነ በምግብ ራስን በመቻል ረገድ እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚጎዳ ስለሆነ የክልሉ ባለሥልጣናት ይበልጥ ትኩረት ሊሰጡት የሚገባው ጉዳይ ነው። በርግጥ በደቡብ ክልል ሌሎች አካባቢዎች እጅግ ውጤታማ የሆነ የተፋሰስ ልማትና የመሬት ማገገም ስራ መሰራቱ የሚታሰብ አይሆንም። ነገር ግን ይህም ትኩረት ይሻል፡ በሌላም በኩል ከሞጆ እስከ አዋሳ በሚወስደው መንገድ ዳርና ዳር ያለው አካባቢ ከሶስት አስርታት በፊት ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈነ እንደነበር ማንም አካባቢውን የማያውቅ ሰው የሚያስታውሰው ነው። አሁን ያ ደን ተመንጥሮ አልቆ ገላጣ መሬት ሆኗል። በአካባቢው ያለው የህዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን መጨመሩንና ድህነት በመባባሱ ሳቢያ ወደ ከሰል አምራችነት መስክ የሚገባው ህዝብ የዚያኑ ያህል ጨምሯል ወደ ከተማችን ለሚገባው የከሰል መጠንም ከዚያ አካባቢ የሚመረተው ከሰል ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው።

በተመሳሳይ በዝዋይ በአብያታ ሀይቆች ዙሪያ የሚገኘው የህዝብ ቁጥር መጨመር እንዲሁም የከብት ቁጥር መጨመር በሀይቆች ዙሪያ የሚገኘው የተፈጥሮ ሳርና ደን ተመናምኖ እንዲያልቅና የሀይቁ መጠን እንዲቀንስ እያደረገ ይገኛል።

የግብርና ሚኒስቴር እንደሚገልጸው በሰሜን ኢትዮጵያ ከእርሻ ስራ ጎን ለጎን የከብት ርባታ ስራም ይካሄዳል። ቁጥራቸውም ከፍተኛ ነው። አርሶ አደሮቹ ሁለቱንም የግብርና ሥራ የሚያከናውኑት አንደኛው ለምሳሌ እርሻው በዝናብ መቅረት ሳቢያ አደጋ ውስጥ ቢወድቅ በከብቱ ርባታ የሚገኘው ጥቅም ድጎማን ያስገኛል ከሚል ሲሆን ከብቶቹም በበሽታ ወይም በሌላ ጉዳት ቢደርስባቸው እርሻው አይነተኛ አማራጭ ይሆናል በሚል ነው ነገር ግን ሁለቱም የግብርና አይነቶች አካባቢው ከተራቆተ ለአደጋ የሚጋለጡ እንደመሆናቸው የግብርና ሙያም ሆነ እንቅስቃሴው ከአካባቢ ጥበቃ ስራ ጋር እጅግ የተቆኘ መሆን ይጠበቅበታል። ምክንያቱም የአካባቢ መራቆት የገበሬውን ህይወት ስለሚነካ ነው። በአሁኑ ወቅት ባለሙያዎች እንደሚመክሩት በተለይ በደጋው አካባቢ የሚካሄደው የከብት ርባታ ስራ ቁጥር በጣም ውስን መሆን ያለበት ሲሆን የግማሽ መሬቶችም የታጠሩ መሆን ይኖርባቸዋል። ልቅ የግጦሽ መሬት ሳሩ ከነስሩ ተግጦ የአፈር መከላትን ጭምር የሚያስከትል ይሆናል። የከብቶች መጠን መብዛት ከግጦሽ መሬት እጥረት በተጨማሪ ለእነርሱ የሚሆን ውሃ ማቅረብም እጅግ አስቸጋሪ ነው። ከቦታ ወደ ቦታም ለውሃና ለግጦሽ ተብሎ ከብቶችን ማንቀሳቀስ ከባድ ከመሆኑ ባሻገር እንዳይደልቡ ያደርጋል። ምክንያቱም በመንገድ ብቻ በሰውነታቸው ያለው ስብ ስለሚቀልጥ ነው። እንደሚታወቀው ገበሬው በውስን እርሻ መሬት ላይ ስራውን ያከናውናል። በዚህ የተነሳም ለግጦሽ የምትኖረው መሬት ትንሽ ስለሆነች የከብቶች ቁጥር ውስን መሆን ይኖርበታል። የከብት ቁጥር መብዛት ተጨማሪ ውጭ ከማስከተሉ በተጨማሪ መሬትን በስርዓት ለመምራት የሚደረገውን ጥረት ያውካል።

የመሬት መራቆትን ለመግታትና አካባቢን ለመንከባከብ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ግብርናን ህይወቱ ያደረገው አርሶ አደሩ ነው። በዚህ ውስጥም የሴቶች ሚና ጉልህ ነው። ነገር ግን በሀገራችን ባለው ሁኔታ ለሴቶች የሚሰጠው ቦታ አናሳ በመሆኑ በአካባቢው ጥበቃ ስራ የበኩላቸውን ሚና እንዳይጫወቱ እንዳደረገ አንዳንድ ጥናቶች አመልክተዋል። በሰሜን ወሎ ዞን በተደረገ ጥናት መረዳት እንደተቻለው የኤክስቴንሽን ሰራተኞች ስለግብርናም ሆነ ስለአካባቢ ጥበቃ መረጃን የሚያስተላልፉት ለወንዶች እንጂ ለሴቶች አይደለም። ነገር ግን እርሻው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ የሴቶች የስራ አስተዋፅኦ 70 በመቶ ነው። ይህ ሆኖ እያለ ግን ሴቶች በሚሰጣቸው ዝቅተኛ ቦታ መረጃውን ስለማያገኙ አካባቢ ለጉዳት ይዳረጋሉ። ይህም ትኩረትን የሚያሻ ነው።

ተፈጥሮንና የእርሻ መሬትን የመንከባከብ ጉዳይ ከያዘ ባለቤትነትም ጋር በቀጥታ ይገናኛል። ሰው የኔ የሚለው ነገር ላይ ጉልበቱን እውቀቱንና ገንዘቡን በማፍሰስ እንክብካቤ ያደርጋል። ለዛሬ ሳይሆን ለነገና ለተነገወዲያ በሚልም የረጅም ጊዜ እቅድ ይይዛል። ይህም ይበልጥ ጥረቱን እንዲያጠናክር ያደርገዋል። በርግጥ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ያለው የመሬት ይዞታ በመንግስት ባለቤትነት ስር ነው። ለዚህም መንግስት የራሱ መከራከሪያ አለው። ይዞታው እንደዚህ በመሆኑ ምርታነትን ማሳደግ ተችሏል ይላል። ሌሎች ደግሞ በገበሬው ይዞታ ስር ቢሆን ከዚህ የበለጠ ሊንከባከበው ይችላል የሚል ክርክር ያቀርባሉ።  

    ይህን ከግምት በማስገባት መንግሥት ለገበሬዎች የመሬት የመጠቀም መብታቸውን የሚያረጋግጥ በብዙ ክልሎች ሰርተፊኬት ሰጥቷል። ይህም በአብዛኛዎቹ ገበሬዎች ተቀባይነት እንዳገኘ ለማረጋገጥ ተችሏል። የተሻለ ምርት በማሳ ማስገኘት እንደታቻለም ተገልጿል። አፍሪካ ግሪን ሪቮሉሽን ፎረም የተባለው ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በኢትዮጵያ መንግሥት ለገበሬዎች የመሬት የመጠቀም መብት የሚያረጋግጥ ሰርተፊኬት መስጠቱ የእርሻ ምርታማትን ለመጨመር እንዳስቻለ ገልጿል። በአጠቃላይ የእርሻ ምርታማትን በመጨመር በምግብ ራስን ለመቻልም ሆነ ድህነትን ለመቀነስ የአካባቢ ጥበቃ ስራና የተራቆቱ መሬቶችን እንዲያገግሙ ማድረግ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። አሁን ሀገራችን ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አካባቢ እንዲያገግም በየዓመቱ 100 ሚሊዮን ዶላር ቢያንስ እስከ 10 ዓመት ድረስ መመደብ እንዳለበት ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ በአንድ ወቅት መግለፃቸው አይዘነጋም።

     አዲስ አበባ ከተማ ከተቆረቆረች ከ120 ዓመታት በላይ አሳልፋለች። የስፍራው አቀማመጥም ከባህር ወለል በላይ ከ2780 ሜትር ከፍታ ባላቸው ተራሮች የተከበበ ሲሆን በተለይ በክረምት ወቅት ከፍተኛ የዝናብ መጠን ሲኖር ከተማዋን አቋርጠው የሚያልፉ በርካታ ጅረቶች በመሙላት አደጋን የማስከተል አቅማቸው ከፍተኛ ይሆናል። በዚህ ወቅት ግን የሚያስከትለው ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ተጠራርጎ ወደ ከተማዋ ዳርቻዎች መውሰዱ ለተወሰነ ጊዜ ፋታ ቢሰጥም ከቀናት በኋላ ግን ወደ ወትሮው ብክለት ስለሚመለስ ነዋሪዎችን ማስመረሩን ይቀጥላል።

የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ባለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመት በፈጣን የከተማ መስፋፋት በህዝብ ቁጥር ዕድገትና በኢንዱስትሪ መበራከት የተነሳ በከተማዋ የሚገኙ ወንዞች ለደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃነት በዋንኛነት ተመራጭ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

በከተማዋ አነስተኛ ወንዞችን ሳይጨምር ሰባት ታላላቅ ወንዞች በዙሪያዋ ከሚገኙ ተራሮች ተነስተው ከተማዋን በማቋረጥ ያልፋሉ። ከከተማዋ በስተሰሜንና ምዕራብ ተራሮች የሚነሱት ወንዞች ገባሮቻቸውን ይዘው ወደ ደቡባዊ ምስራቅ የሚያመሩ ሲሆን ዋንኛ የሚባሉትን ቡልቡላ፣ ቀበና ፣ አቃቂና ግንፍሌ ወንዞችን በማጠናከር ወደታችኛው ተፋሰስ ያመራሉ።

የከተማችን ወንዞች ከሰው ከሚወጣ እዳሪና ፍሳሽ በተጨማሪ በሌላ በአደገኛ የኬሚካል ንጥረ ነገሮች ማለትም ከጋራዥና ከኢንዱስትሪ በሚለቀቁ ክሮሚያም፣ አርሰኒክ፣ ኒኬል፣ መዳብ፣ ዚንክ፣ ማንጋንስ ካድሚያምና ኮብልት በተባሉ ኤለመንቶች ክፉኛ የተበከለ ነው። እነኚህ ኬሚካሎች በውሃ ውስጥ የሚገኙ ህያው ነገርን በሙሉ ያወድማሉ። ከዚህ በተጨማሪም በወንዞቹ ውስጥ በመሆናቸው በትነት መልክ ወደ ከባቢ አየር ሲመጡ የሰዎችን የመተንፈሻ አካላት በመጉዳት ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳርፋሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጥናት ይፋ እንዳደረገው በከተማችን የሚገኝ 35 ፋብሪካዎች የተበከለ ፍሳሽን ወደ ወንዞች ይበቃሉ። እነኚህ ብክለቶች ከሰሜን አዲስ አበባ ተነስተው 13 ወረዳዎችን በማቋረጥ ወደ አባሳሙኤል ሃይቅ ይገባሉ። ይህ ሃይቅም የሚገኘው ከከተማችን በስተደቡብ በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው። ጥናቱ እንዳረጋገጠው ከፋብሪካ የመነጨው በካይ ንጥረ ነገር በውሃና በወንዝ ዳርቻ በሚገኙ ፍጥረታት ላይ ጉዳት ያስከትላል። ከሆስፒታል የሚለቀቁ ፍሳሾችና ደረቅ ቆሻሻዎችም ብክለቱን በማጠናከር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። በአቃቂ ወንዝ የብክለቱ ዋንኛ ተሸካሚ ሲሆን ወደ አባ ሳሙኤል ሃይቅ ያመራል። መነሻውም ከሰሜን ምዕራብ ከተማዋ ዳርቻዎች ከሚገኙ ተራች ነው። ትንሿአቃቂ ወንዝ ከአቅራቢያው በመነሳት በወጣጫ ተራራን በማካለል ወደ አባሳሙኤል ያመራል። በዚህም ከመነሻ እስከ መዳረሻው 40 ኪሎ ሜትሮችን ያቆራርጣል።

የከተማዋ ታሪክ እንደሚያመለክተው ኢንዱስትሪዎች፣ ሆስፒታሎችና ህንጻዎች ከመስፋፋታቸው በፊት ወንዞች እጅግ በጣም ንጹህ ነበሩ። ነገር ግን ወንዞች በአሁኑ ወቅት ከህብረተሰቡ ግንዛቤ ማነስና በተገቢው የሚመለከተው አካል ቁጥጥር ባለማድረጉ የተነሳ የብክለት መንስኤ ሆነው በአካባቢ፣ በሰውና በእንስሳት ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማድረስ ላይ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀፅ 44 ህዝብ ለኑሮዎቹ በሆነና ከብክለት በፀዳ አካባቢ የመኖር መብቱ የተጠበቀ ይሆናል ይላል። ይህ ህግ ምን ያህል ተተግብሯል የሚለው ያው የሚታወቅ ነው። ሕግ በወረቀት ላይ መፃፍ አንድ ነገር ሆኖ እንዲተገበር ማድረግ ደግሞ የሁሉም ባለድርሻ አካላት መረባረብን ይጠይቃል። በተለይም ሕጉ የወጣለት ህብረተሰብ መብቱን የሚጠይቅና የሚያስከብር ካልሆነ ውጤታማ ይሆናል ማለት ዘበት ነው።

አቶ አዱኛ መኮንን የአዲስ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ ናቸው። እንደ እርሳቸው ገለፃ የከተማዋ ወንዞች መበከል ከከተማዋ መቆርቆር ጋር በቀጥታ ይዛመዳል። በዛን ወቅት የህብረተሰቡ ንቃተ ህሊና ገና እጅግና ያልዳበረ በመሆኑና የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይም ጭራሹን የማይታወቅ ስለነበር ወንዞች በቆሻሻ ማስወገጃነት የተፈጠሩ አድርጎ የመውሰዱ ጉዳይ በጣም የተለመደ ነበር። ይህን ሁኔታ ለመከታተል የህግም ሆነ የተቋም መሠረት አልነበረም። ከዚያ በኋላ በነበሩት አስርታት ፋብሪካዎች እየተገነቡ ሲመጡም ፋብሪካዎች መገንባታቸውና የስራ እድል መፍጠራቸውን እንጂ የሚለቋቸው ፍሳሾች በአካባቢና በህብረተሰብ ጤና ላይ ሊያደርሷቸው የሚችሉትን ተፅዕኖዎች የሚመለከት ሁኔታ በፍፁም አለመኖሩ ችግሩ እየተንከባለለ መጥቶ አሁን ላለንበት ዘመን እንዲደርስ አድርጓል። ፍሳሾች ታክመው እንዲለቀቁ የማድረጉ ጉዳይም የማንንም ትኩረት አላገኘም ነበር።

በአሁኑ ወቅት ሁሉም ኢንዱስትሪዎች ሆስፒታሎችና ሌሎች ተቋማት ጥልቅ ጥናት ከተደረገባቸው በኋላ በተቆረጠ የጊዜ ገደብ የብክለት ማከሚያ ማሽነሪዎችን በየተቋማቸው እንዲተክሉ ትዕዛዝ የተሰጣቸው ሲሆን ከዚህ ወቅት በኋላ ወደ ወንዝ የሚለቋቸው ፍሳሾች የታከሙ እንደሆነ ጥብቅ መመሪያ ተሰጥቷል። ይህን ካላደረጉ ግን የህግ ተጠያቂነት እንደሚያስከትልባቸው ተገልፆላቸዋል። የመጨረሻው ርምጃም ተቋማቱን እስከመዝጋት የሚደርስ ነው።

እንደ ምክትል ስራ አስኪያጁ ገለፃ አካባቢን በመበከልና ፍሳሽን ወደ ወንዞች በመልለቅ አንዳንድ ትላልቅ የመንግስት ተቋማት ጭምር ይታወቃሉ። ስለሆነም ከችግሩ ውስብስብነት የተነሳ መፍትሄ ለመስጠት ከሚመለከታቸው ተቋማት በተጨማሪ የሌሎች ባለድርሻ አካላት ትብብርን ይጠይቃል። “ወንዞች በየቀኑ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ እየተበከሉ ነው” የሚሉት አቶ አዱኛ ችግሩን ለመቅረፍ መስሪያቤታቸው በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ደፋ ቀና እያለ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ለዚህ እንዲያግዝም ከጤና ቢሮና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተጋገዝ ስራው እየተከናወነ መሆኑም ለዚህ አብይ ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል። በሆስፒታችና በተጠቀሱት ኢንዱስትሪዎችም ለሠራተኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ተከናውኗል። የቁጥጥር ስራም የተሰራ ሲሆን ከዚህ ባለፈም ፍሳሾቻቸውን በተገቢው በማከም ወደ ወንዞች በማይለቁ 10 ኢንዱስትሪዎች ማስጠንቀቂያ የተሰጠ ሲሆን በስድስት ኩባያዎች ላይ ደግሞ ክስ ተመስርቶባቸዋል። ወደፊትም ቢሮው ለሌሎች መቀጣጫና ትምህርት እንዲሆን በሚል ክስ የተመሰረተባቸውን ኩባንያዎች ለህዝብ ይፋ ያደርጋል።

በከተማ ግብርና የተሰማሩ ሙያተኞች በተለይ አትክልትን ከወንዞች በሚገኝ ውሃ በማምረት ለህብረተሰቡ ያቀርባሉ። በተበከለ ውሃ የሚመረት ዕፅዋት ከብክለት ነፃ ሊሆን አይችልም። ይህም በአካባቢና በሰው ጤና እንዲሁም በእንስሳት ላይ ጉዳት በማስከተል ላይ ይገኛል። በዚህ ረገድ በርካታ አካባቢዎችን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። እንደሚታወቀው በተለምዶ ቄራ ተብሎ የሚታወቀው አካባቢ ጋራዦች ማምረቻ ተቋማትና አገልግሎት አቅራቢዎች የሚገኙበት እንዲሁም ቁጥሩ ከፍተኛ ነዋሪ የሚገኝበት አካባቢ ነው። በዚያ አካባቢ ከተለያዩ ስፍራዎች በማምጣትና ቆሻሻን በማግበሰበስ በአካባቢው የሚያልፉ ጅረቶች ይገኛሉ። ከአካባቢ ጋራዦች የሚለቀቀው የተቃጠለ ጋዝና የመኪና እጣቢ ወደ ውሃው ይገባል ቀላል የማይባል መሬት ከቄራ ጀርባ ጀምሮ እስከ መካኒሳ ባለው የወንዝ ዳርቻ ላይ ሰላጣ፣ ጎመን፣ ቆስጣ ወዘተ በስፋት ይመረታል። ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በወንዝ ውስጥ እጅግ አደገኛ የሆኑ እንደ መዳብና ዚንክ የመሳሰሉ ንጥረ ነገሮች በአትክልቶች ስራ በመግባት ቅጠሎች ውስጥ ይደበቃሉ። በተለይ ተቀቅሎ የማይበላ ሰላጣ ሰዎች ሲመገቡት ካንሰርን ጨምሮ ለተለያዩ በሽታዎች እንደሚያጋልጥ ሙያተኞች ይገልጻሉ። በርግጥ በግብርና ስራ የተሰማሩት ሰዎች ለራሳቸው መተዳደሪያ የሚሆን ሥራ መፍጠር ቢችሉም በተጓዳኝ ለተመጋቢው ይዞ የሚመጣው ዳፋን በተገቢው የተረዱት አይመስልም። ይህን በተመለከተም ለአምራቾቹ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በተለያዩ ወቅት ስለጉዳዩ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ትምህርት ቢሰጥም ስራው ግን እንደቀጠለ ነው። የአትክልትና ቅጠላቅጠል ተመጋቢው ህብረተሰብ ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል። የህክምና ባለሙያዎች እንደሚገልጹት በተበከለ ውሃ የሚለማ አትክልት ውስጥ በካይ ንጥረ ነገሮች ተመችቷቸው ይቀመጣሉ። ሰው ከተመገባቸው በኋላም በሰውነት አካላት ውስጥ ክፍል ውስጥ ይቀመጣሉ። ጉዳታቸው ወይም ምልክታቸው ግን በፍጥነት አይከሰትም። ነገር ግን ከረጅም ዓመታት በኋላ ተፅዕኖአቸው መከሰት ይጀመራል። ከዚያ በኋላም በህክምና ለመዳን ከፍተኛ ወጭን ያስወጣሉ። በአዲስ አበባ ከተማ የወንዞች ብክለት ከዕፅዋትና ከሰው ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት አልፎ በአቃቂ አካባቢ በከብቶች ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ ከአመታት በፊት ተገልፆ እንደነበርና ይህን ጉዳዳይም ተበዳዮች ወደ ሕግ ወስደው ውሳኔ ለማግኘት በሂደት ላይ መሆኑ ከተሰማ በኋላ መጨረሻው ሳይታወቅ ለህዝብም ይፋ ሳይደረግ እንደቀረ አይዘነጋም።

ከዚህ አኳያ ችግሮቹን በሕግ አግባብ ለመፍታት የሚደረገው ጥረት እጅግ በጣም ደካማ መሆኑን መረዳት አያዳግትም። በተለምዶ ሰዎች በድብደብና በመሰል ሁኔታዎች በአካላቸው ላይ ጉዳት ሲደርስ ጉዳዩ ሕግ ፊት ቀርቦ በአፋጣኝ ውሳኔ እንደሚያገኝ ይታወቃል። ነገር ግን በብክለት አማካኝነት በተዘዋዋሪ ሁኔታ በሰው ጤና ላይ ለሚደርሰው ጉዳት የጠያቂም ተነሳሽነት አናሳ መሆንና የተጠያቂነት አለመኖር ችግሩን ለመፍታት ገና ረጀም ርቀት መጓዝ እንደሚጠይቅ አመልካች ነው።

በሌላም በኩል በከተማ የተበከሉ ወንዞችን እንደገና ለማንፃት በአንዳንድ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሙከራ እየተደረገ ሲሆን የተገኘውን ተሞክሮ ወደ ሌሎች አካባቢ ለማድረስ ጥረቱ መቀጠል ይኖርበታል። ለምሳሌ በቀልና አካባቢ በግንፍሌ ወንዝ ዳር ቬቲቫር የተባለውን እስከ ሁለት ሜትር የሚደርስ ስር ያለውን ሳር በመትከል ቆሻሻው በተክሉ ስሮች አማካኝነት እንዲመጠጥ የማድረጉ ጥረት ተስፋን የሚሰጥ ውጤት ስላስገኘ እንዲስፋፋ ማድረጉ ጠቀሜታው የጎላ ነው። የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣንም በበኩሉ የወንዝ ዳርቻዎችን በማጠርና በማጽዳት ወደ መናፈሻነት ለመቀየር ዕቅድ እንደነበረው አቶ አዱኛ የገለፀ ሲሆን ነገር ግን የከተማዋ የጂኦግራፊ አቀማመጥ ምቹ አለመሆን ወንዞች ከክረምት ወቅት አደጋ በሚያደርስ ደረጃ መሙላታቸው በለጋ ወቅት ደግሞ ጨራሹኑ መድረቃቸው ከዚህ በተጨማሪ በህዝብ ብዛትና ፍልሰት የተነሳ አብዛኛዎቹ የወንዝ ዳርቻዎች በህገ ወጥ ሰፋሪዎ በመወረራቸው የሁኔታው አዋጭነትና አጠያያቂ እንዳደረገው አመልክተዋል።

እንዲያም ሆኖ ግን ሁኔታው ከእነ ጭራሹ እንዲቀር አልተደረገም። በከተማዋ ማስተማር ፕላን መሰረት የወንዝ ዳርቻዎች ሊታጠሩ የሚችሉበት ዝግጅት ለማድረግ ጥረት ይደረጋል። ከዚያም አካባቢ ከሰውና ከእንስሳት ነፃ ሲሆን ባለሀብቶች መንግስትና ባለድርሻ አካላት በመተጋገዝ አካባቢው ሰዎች የገቢ ማስገኛ መናፈሻ የማድረግ ዕቅድ አለ። ውጤቱም ወደፊት የሚታይ ይሆናል።     

በአሁኑ ወቅት በሀገራችንም ሆነ በአዲስ አበባ ፈጣን ልማት እየተከናወነና ኢኮኖሚዋም እየገዘፈ በመሄድ ላይ ይገኛል። ይህም ለከተሞች መስፋፋት፣ ከገጠር ወደ ከተማ ለሚደረግ ፍልሰት ኢንዱስትሪዎችና የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት እንዲሁም የትራንስፖርቱ ዘርፍ እየጎለበተና አዲስ የአኗኗር ዘይቤ እንዲፈጠር አድርጓል። የስራ ዕድል መፈጠርም ለዜጎች ተጨማሪ ገቢ ሲያስገኝ መንግስት በታክስ የሚሰበስበው ገቢም የዚያኑ ያህል እንዲያድግ እያደረገ ነው። እነኚህ ሁኔታዎች በከተሞች መስፋፋት እየተመዘገበ ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን የሚያመለክቱ ናቸው። ይሁን እንጂ የዚያኑ ያህልም በከተሞች መስፋፋት ሳቢያ የሚከሰቱ የድምፅና የአየር ብክለቶች ለወደፊት ከተማ ለመኖሪያ ምን ያህል የተመቸ ነው? የሚለውን ጥያቄ እንድናጭር እያደረገ ነው።

ለምሳሌም አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች በጣም ያረጁና መቀየር የሚገባቸውን ማሽኖች እስካሁን በስራ ላይ ማዋላቸው ላልተፈለገ ድምፅ መፈጠር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው። ይህ ብክለትም በቀንም ሆነ በሌሊት የሚስተዋል ሲሆን የሌሊቱ ለሰዎች እንቅልፍ ሰዓት መዛባትና ዕረፍት በማሳጣት ረገድ አስከፊ ተፅዕኖ በማሳረፍ ላይ ነው። በሌላም በኩል በየቀበሌውና ከመኖሪያ አካባቢዎች ጋር ተጣምረው የተሰሩት ወፍጮ ቤቶች ያልተፈለገ ድምጽን በመፍጠርና ፀጥታን በማወክ ይታወቃሉ። የትራንስፖርት ዘርፉም ቢሆን በዚህ ጉዳይ ከመወቀስ የሚድን አይደለም። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በአዲስ አበባ ከተማ ጥቅም ላይ ከዋሉት ተሸከርካሪዎ 80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከ20 ዓመታት በላይ አገልግሎት የሰጡ ሲሆን የቴክኒክ ብቃታቸውም ከእርጅና ብዛት የተዳከመ በመሆኑ በሚሽከረከሩበት ወቅት ሞተሮቻቸው የሚለቁት ጭስና ድምጽ አካባቢን በመበከል ጥፋት በማስከተል ላይ ይገኛል። መኪኖች ከውጭ ሀገር አካባቢን በመበከል ጥፋት በማስከተል ላይ ይገኛል። መኪኖቹ ከውጭ ሀገር ሲገቡ ረጅም አገልግሎት ከሰጡ በኋላ ሲሆን ሀገር ውስጥ ካገለገሉ በኋላም እንደገና ለሶስተኛ ወገን በደላላ አማካኝነት እንደ አዲስ መሸጣቸው ለችግሩ መወሳሰብ የራሱን አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ነው።

አቶ ብርሃኑ አበራ በአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በድምፅ ብክለት ምርምር ክፍል ውስጥ በመስራት ላይ ይገኛሉ። በትምህርታቸው የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን በስራ ህይወታቸውም የረጅም ጊዜ ተሞክሮ አላቸው። እንደ እርሳቸው ገለፃ የድምፅ ብክለት ማለት ያልተፈለገ ድምፅ ሆኖ በሰዎች አካልና ስነልቦናዊ ሁኔታ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳርፍ እንዲሁም ለጤና መታወክ አሳልፎ የሚሰጥ ነው። ይህም ማለት ሰዎች ድምጽን ለተለያዩ ጉዳይ ሊጠቀሙበት ወይም በስራቸው አማካኝነት ድምጽን ሊለቁ ይችላሉ። ይህ ሁኔታ ግን መወጣት ካለበት የድምፅ መጠን ሲያልፍ ለሌላው ላይ ጉዳት ያስከትላል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስትም ሆነ የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አዋጅ ዜጎች ከብክለት ነፃ በሆነ ሁኔታ የመኖር መብት እንዳላቸው ደንግጓል። ከእነኚህ ድንጋጌዎች የወጣ መመሪያም ድምጽን ከተገቢው በላይ የለቀቀ ግለሰብም ሆነ አካል የተጠያቂነት ኃላፊነት እንዳለበት ደንግጓል። ድንጋጌው እንደሚያመለክተው ለመኖሪያ አካባቢዎች፣ ለንግድ አካባቢዎችና ለኢንዱስትሪ ዞኖች መውጣት የሚገባው የድምጽ መጠን በቀን ወቅት 55፣ 65 እና 75 ዲሺ ቤል ነው። እንዲሁም 45፣ 57 እና 75 ዲሺ ቤል በሌሊት እንዲሆን ይጠቅሳል። ነገር ግን ሕጉ ምን ያህል እየተከበረ ነው የሚለው ብዙ የሚያነጋግር ነው። በርግጥ በአዲስ አበባ ከተማ ለአብዛኛው ነዋሪ የድምፅ ብክለት ከግንዛቤ ማነስ ጋር ተያይዞ በቁጥር አንድ አጀንዳነት የሚታይ አይደለም። ነገር ግን ሳይታወቅ ስር እየሰደደና በሰዎች ላይ ችግር በማስከተል ላይ ይገኛል። በአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የተደረጉ ጥናቶች እንደሚመለክቱት የመንገድና የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ፣ የማምረቻ ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች፣ የሙዚቃ ሱቆች፣ ባለቤት ያላቸውና የሌላቸው ውሾች፣ የምሽት ክበቦች፣ የድምፅ ማስታወቂያዎችና የሃይማኖት ተቋማት ቁጥር አንድ የድምፅ ብክለት መንስኤ ናቸው። በተለይ ከእነኚህ ተቋማት የሚለቀቁ ድምፆች በሌሊት በነዋሪዎች ላይ የሚያሳርፉት ጫና ቀላል የሚባል አይደሉም።

ወ/ሮ መሰረት አበበ የመንግስት ሠራተኛ ሲሆኑ መኖሪያቸው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ሳሪስ ተብሎ የሚጣው አካባቢ ነው። እንደ እርሳቸው ገለፃ በመኖሪያቸው አካባቢ በተለይ በምሽት ላይ ያልተፈለገ ድምፅ ሰዎችን ከእንቅልፍ በመቀስቀስ እንዲሁም ጭራሹኑ በመከልከል ዕረፍት ይነሳል። በጠዋት ተነስቶ ወደ ስራ ለመሄድ ባለው ተነሳሽነት ላይ ጫና ያሳርፋል። ወደ ስራ ቢኬድም የሰውነት መዛልና የአእምሮ አለመረጋጋት የስራ ውጤታማነት እንዳይገኝ ምክንያት ሲሆን ይስተዋላል። ይህ ደግሞ ምርታማነት እንዲቀንስ በማድረግ ስራ እንዲቀዛቀዝ እስከማድረስ የሚሄድ ነው። በእርሳቸው ምልከታ በተለይ በሌሊት የኢትዮጵያ አየር መንገድና የውጭ ግዙፍና ዘመናዊ አውሮፕላኖች ከመኖሪያ ቤተችን አነስተኛ ርቀት ላይ ሆነው ከባድ ድምፅ በመልቀቅ መብረራቸው የሁኔታውን አሳሳቢነት እንደሚጠቁም አልሸሸጉም።

በርግጥ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት በፍጥነት እያደገ ለሚሄደው ኢኮኖሚያችን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከሚያደርጉት ተቋማት በዋንኛነት የሚጠቀስ ነው። ለሀገራችን የውጭ ምንዛሪ በከፍተኛ መጠን እያስገኙ ከመጡት ምርቶች መካከል ውስጥ እንደ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬን ለአውሮፓ ገበያ ለማቅረብ ድንቅ አገልግሎት እየሰጠ ያለው የአየር ትራንስፖርት በጣም የሚደነቅ ነው። ከዚሁ ጋር ግን እያመነጨ ያለው ብክለት በሂደት እልባት የሚሰጠው መሆን ይኖርበታል። ምክንያቱም የልማት ሁሉ ግን ለሰው ልጅ ብልጽግናና የተረጋጋ ህይወት ማስገኘት በመሆኑና ልማት በዚህ በኩል ካልተተረጎመ ዘላቂነቱ አጠያያቂ ስለሚሆን ነው።

በሌላም በኩል በሳሪስ አካባቢ ከኑሮ መሻሻልና ከሰዎቸ የመዝናናት ፍላጎት የተነሳ በርካታ የምሽት ክበቦች ተስፋፍተዋል። ክበቦቹ ቀን በስራ የዋለን አእምሮ ከማዝናናት ባለፈ እረፍት ለማድረግ በመኝታው ላይ የተኛን ነዋሪ እረፍት መንሳታቸው በአሉታዊ ጎኑ እንደሚታይ ወ/ሮ መሰረት አስረድተዋል። እዚህ ላይ መታወቅ የሚገባው የንግድ ተቋማትም ሆኑ የምሽት ክበባት በሕግ ተመዝግበው ተገቢውን ግብር ለመንግስት በመክፈል ሠራተኞች ቀጥረው ስራውን ስራ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ናቸው። በስራቸው አጋጣሚም ሰውን ለማዝናናት በሚል ድምጽ ይለቃሉ። ነገር ግን ድምጽ ከተፈቀደለት መጠን ሲያልፍ ማረፍ የሚፈልግን የህብረተሰብ ክፍል ሰላም መንሳቱ አግባብነት ካለመኖሩም በተጨማሪ በሕግ ተጠያቂነት ሊስከትል እንደሚገባ ባለቤቶቹ ሊገነዘቡት ይገባል። እያዝናኑ ገቢ ማግኘት እንደሚቻል ሁሉ እረፍት በመንሳትም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ኪሳራ እንደሚያስከትል ግንዛቤ ሊኖር ግድ ይላል።

አቶ ሙኒር አሊ የኢንቴግሬትድ የገጠር ልማት መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ሲሆኑ በድምጽ ብክለት ላይ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ ለሚመለከተው አካል በማቅረብ ይታወቃሉ። እንደ እርሳቸው ገለፃ የድምፅ ብክለት በሰውና በእንስሳት ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳርፋል። በተለይም በእድሜ የገፉ አዛውነቶችና ህጻናት ለማንኛውም ጉዳት ተጋላጭ በመሆናቸው የህብረተሰቡን እንክብካቤ ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ እነኚህ ወገኖች በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ የድምጽ ብክለት ሰለባ በመሆን ላይ ናቸው። ለምሳሌ በእድሜ የገፉ አዛውንቶች በድንገት ከባድ የመኪና ክላስክ ድምፅ ሲሰሙ ደንግጠው ለመሸሽ ሲሞክሩ በሌላ መኪና የመገጨት አደጋ እየገጠማቸው ለአካል መጉደል ከዚያም ሲከፋ ለህልፈተ ህይወት ይዳረጋሉ። ከዚህ አንጻር በእድሜ የገፉ ሰዎች እጣ ፈንታቸው አሳዛኝ ከመሆኑም በላይ ይበልጥ ወደ ተረጅነት ይገፋሉ። የህፃናቶች ጉዳይም ተመሳሳይ ነው። ገና ያልበሰሉ ህጻናት ወደትምህርት ቤት ሲሄዱና ሲመለሱ በሚያጋጥማቸው የመኪና ጥሩንባ ጩኸት በመደንገጥና በመረበሽ በሌሊት እንቅልፍ እጦትና ቅዠት የሚዳረጉ ሲሆን ትምህርታቸውንም በወጉ እንዳይከታተሉ ያደርጋል።

አቶ ሙኒር በተጨማሪ ሲገልፁ ያልተፈለገ ድምፅ በሰዎች ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከማሳረፉም በላይ ተጎጂዎችን ለከባድ የህክምና ወጭ ይዳርጋቸዋል። ይህም ተጨማሪ ለቤተሰብ ሸክም እንዲሆኑ ያደርጋል። ከባድና አስጨናቂ ድምፅ ሰዎችን ለአእምሮ መቃወስ በሽታ፣ ለልብ፣ ለልብ ድካም፣ ለጆሮ መደንቆር፣ ለኩላሊት ከስራ ውጭ መሆንና ለዕድሜ ማጠር ይዳርጋል።

በድምፅ ብክለት ሳቢያ እንቅልፍ ያጡ ሠራተኞች በስራ ገበታቸው ላይ ንቁ አይሆኑም። ይፈዛሉ፣ ተግተው ባለመስራታቸውም ተቋሙ ተወዳዳሪነቱን ይቀንሳል። በዚህ ሳቢያም ደንበኞችን እስከማጣት ይደርሳል። ይህም በድርጅቱ ላይ ኪሳራ በማስከተል የሰራተኞች ዕጣ ፈንታም በጥያቄ እንዲቀመጥ ያደርጋል። ችግሩ የሰው ልጆችን ህይወት ከማዛባት አልፎ የእንስሳትን ህልውናንም በመፈታተን ላይ ይገኛል። በከተማ ዳርቻዎች የሚገኙ አእዋፋትና አጥቢ እንስሳት በፋብሪካዎችና በሌሎች ረባሽ ድምፆች ድንጋጤ መኖሪያቸውን እየለቀቁ ወደማውቁት አካባቢ እንዲሰደዱ በማድረግ ላይ ሲሆን ይህም በአንጻሩ ኢኮ-ሲስተም እንዲዛነፍ አስገድዷል። ባዮዳይቨርስቲ እንዲመናመን ማድረጉን ሳይንቲስቶች እንዳረጋገጡ አቶ ሙኒር አሊ ገልጸዋል። በተመሳሳይም የቤት እንስሶችም የችግሩ ሰለባ ናቸው። ውስጣዊ ህዋሳቸው እየታወከ ለህመም ይጋለጣሉ።

አቶ ሰለሞን ተፈራ በተለምዶ ደጃች ውቤተብሎ በሚታወቀው ቦታ ነዋሪ ናቸው። እንደ እርሳቸው ገለፃ በአካባቢው መኖሪያ ቤቶችና የምሽት ክበቦች ተጠጋግጠው በመሰራታቸው በሌሊት ወቅት ከፍተኛ የድምጽ ብክለት ይስተዋላል። ከቡና ቤቶችና ከሬስቶራንቶች በምሽት የሚለቀቁ ያልተፈለጉ ድምጾች በእረፍት ላይ የሚገኘውን ነዋሪ ሰላም ይነሳሉሉ። በመኝታ ላይ ሆነው ራሳቸውን የሚያስታምሙ አዛውንቶች ከበሽታቸው በተጨማሪ በሌሊት ድምፅ ጩኸት ለበለጠ ስቃይ ይዳረጋሉ። ጥናት ለማጥናት የሚፈልጉ ተማሪዎችም በዚህ የተነሳ ከጥናታቸው ያስተጋገሉላሉ በአጠቃላይ በአካባቢው ያሉ አዛውንቶችና ባልቴቶች በድምፅ ሳቢያ ከእንቅልፍ በመንቃታቸው በማግስቱ ውጥረትን የተሞላበት ጊዜ ለማሳለፍ ይገደዳሉ።ከምሽት ክበቦች በተጨማሪ ንጋት ላይ ከቤት እምነት ተቋማት የሚለቀቁ ድምፆች ለተጨማሪ እንቅልፍ ዕጦትና ጭንቀት ይዳርጋሉ። በርግጥ የሃይማኖት ተቋማት መደበኛ መርሃ ግብራቸውን የሚጀምሩት በዚያው ሰዓት እንደመሆኑ የተለመደ ስራቸውን ያከናውናሉ በሌላ በኩል ሌሊት በሙዚቃ ድምፅ የተረበሸውና እንቅልፍ ያጣው ነዋሪ ትንሽ ሊያሸልብ ሲል ከእምነት ተቋማት ሌላ ድምፅ ሲለቀቅበት ምሬቱ ይበልጥ ይባባሳል።

እንደ አቶ ሰለሞን ገለፃ በርግጥ አንዳንደ የችግሩ ሰለባ የሆኑ ነዋሪዎች ችግሩን እልባት እንዲሰጠው ለቀበሌ መማክርቶች አቤቱታቸውን ያቀረቡ ቢሆንም ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ መፍትሄ አላገኙም። በድምፅ ብክለት ሳቢያ ሰዎች አቤቱታ ሲያቀርቡ የህግ አካሄዱና አፈፃፀሙን በተመለከተ አቶ ብርሃነቱ አበራ ሲገልፁ አንዳንድ ጉዳዮች በአስተዳደራዊ አግባብ መፍትሄ እንደሚሰጣቸው ከዚህ በተጨማሪ የእርምት እርምጃ እንደሚወስድ አመልክተዋል። በአሁኑ ወቅት መንግስት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ያለው በዚህ ረገድ የህብረተሰብ ንቃተ ህሊና ግንዛቤ እንዲዳብር ማድረግ መብቱን እንዲያውቅና እንዲጠይቅ ማድረግ ሲሆን ፈፃሚ አካላትም ተቋማዊ ጥንካሬ ተላብሰው እንዲንቀሳቀሱ ጥረት ተደርጓል። ከሃይማኖት ተቋማት የሚለቀቀውን የድምፅ ብክለት በተመለከተም በተለያዩ ወቅት ከተቋማቱ አመራር ጋር ውይይት ለማድረግ ችግሩ እንዳለ ከመግባባት ላይ መደረሱን አቶ ብርሃኑ ጠቅሰው በሂደት እንዲቀረፍ እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል። በሌሊት የሚደረገውን የአየር በረራና የድምፅ ብክለት በተመለከተም በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ ደረጃ አውሮፕላኖች በተመጠነ ድምፅ እንዲበሩ የሚያደርግ ኮንቬንሽን መኖሩን ጠቅሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድም የኮንቬንሽኑ አካል እንደሚሆን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ ደረጃ ለአየር ትራንስፖርት ቢዝነስ ተወዳዳሪ መሆን የሚቻለው የተመጠነ ድምጽን መልቀቅ በመሆኑ በሀገራችንም ይህ ሁኔታ ይፈጠራል የሚል ግምታቸውን ጠቅሰዋል። የድምጽ ብክለት በከተማችን መኖሩን ተቋማት ከተገነዘቡት መፍትሄውም ይገኛል።

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ግማሽ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ ለምግብ ማብሰያነትና ለገቢ ማስገኛነት በከሰል ይተማመናል። 81 በመቶ የሚሆነው ከሰሀራ በታች ያለው የአፍሪካ ህዝብ በሀገራችን ደግሞ 90 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ከደን ውጤት በሚያገኘው ከሰል ምርትን ለቤት ውስጥ ምግብ ማብሰያነት ይጠቀማል። ከሰሉ ከሚሰጠው ጠቀሜታ አንፃር ሲታይ ኅብረተሰቡ በከሰል የመጠቀሙን ባህል በቀላሉ የሚተው አይመስልም።

አቶ መላኩ በቀለ የኢነርጂ ሙያተኛ ሲሆኑ፤ ለረጅም ዓመታት በዚህ ሙያ በማገልገል ላይ የሚገኙ ናቸው። በከሰል አመራረትና አጠቃቀም እንዲሁም በየትኞቹ የሀገራችን አካባቢ ከሰል በይበልጥ እንደሚመረት፣ የንግድ ሰንሰለቱንና የተለያዩ ወገኖች እንደ ገቢ ማስገኛነት ስለሚጠቀሙበት ሁኔታ እንዲሁም በአካባቢ ላይ እያስከተለ ስላለው አሉታዊ ተፅዕኖ ጥናታዊ ጽሁፋቸውን በቅርቡ በማኅበራዊ ጥናት መድረክ በኩል አቅርበዋል።

እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ከሰል 99 በመቶ የመቀጣጠል ኃይል ያለው ሲሆን፤ ኅብረተሰቡም በቀላሉ ሊያገኘው የሚችለው ነው። ከአብዛኛዎቹ ዘመናዊ የኃይል ምንጮች ጋር ሲነፃፀርም ዋጋው ርካሽ ነው። በቀላሉ ከቦታ ወደ ቦታ በጭነት ተሽከርካሪዎች አማካኝነት የሚዘዋወር ሲሆን፤ በምግብ ማብሰል ረገድ ውጤታማነቱ የጐላ ነው። በጣም ዝቅተኛ ጭስ በተለይ ሲቀጣጠል መኖሩ ተመራጭ እንዲሆን አድርጐታል። ከሰል ለአብዛኛዎቹ ገጠሬ ደሀዎች የገንዘብ ማግኛ ቢዝነስ ነው። ይበልጥ ጥቅም ላይ የዋለውም ከገጠር ይልቅ በከተሞች ውስጥ ነው። ምክንያቱም ገጠሬው የእንጨት ማገዶ በቀላሉ ስለሚያገኝ ከሰልን የመጠቀም ዝንባሌው አነስተኛ ነው። ከሰል አክሲዮኖች ጭምር ገንዘብ ማግኛቸው በመሆኑ ከሰሉን ለማብሰያነት አይጠቀሙም።

የዓለም ባንክ የ2011 ጥናት እንደሚያመለክተው በዓለም 10 ሀገሮች በከሰለ ማምረት ቀዳሚውን ስፍራ ይዘው ይገኛሉ። እነርሱም ብራዚል፣ ናይጄሪያ፣ ኢትዮጵያ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጐ፣ ሞዛምቢክ፣ ህንድ፣ ቻይና፣ ታንዛኒያ፣ ጋና እና ግብፅ ናቸው።

እንደ አቶ መላኩ ጥናት የኢትዮጵያ ከተሞች በዓመት እስከ 3 ሚሊዮን ቶን የሚገመት ከሰል ጥቅም ላይ ይውላል። ነገር ግን አሁን ባለው አያያዘ ከቀጠለ በአካባቢው ላይ የሚያደርሰው ጥፋት ለመተንበይ አስቸጋሪ ነው። አብዛኛው ለከሰል ምርት ግብአት የሚሆነው ተረፈ ምርትን አክሳዮቹ ያለምንም ወጭ በነፃ ነው የሚያገኙት። አብዛኛው ከሰል የሚነደው በባህላዊ ማንደጀ በመሆኑ ለብክነት የተገለጠ ነው። የንግድና የገበያው ሁኔታ ተለዋዋጭ እንደመሆኑ ለቁጥጥር አስቸጋሪ ሲሆን በአካባቢና በሰው ልጅ ጤና ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ እጅግ ከባድ ነው።

እ.ኤ.አ በ1984 የዓለም ባንክ ባወጣው ጥናታዊ መረጃ፤ በከሰል ማክሰል የተነሳ አዳጊ ሀገሮች በዓመት 10 ሚሊዮን ሔክታር ደን ይወድምባቸዋል። በሌላም በኩል በየዓመቱ ደን ለከሰልና ለማገዶ እየተመናመነ በመሄድ ብዙ ሀገሮች እጥረት እያጋጠማቸው ይገኛል። በዚህ ሳቢያም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገሮች የእህል ገለባንና የከብት እዳሪን በኩበት መልክ እያዘጋጁ ለማገዶነት እየተጠቀሙ ሲሆን፤ ይህ በመሆኑም አፈርን ለማልማት ሊውል ይችል የነበረው ተረፈ ምርትና የከብት እዳሪ ከመሬት በመነሳቱ የአፈር ለምነትና ምርታማነት ይበልጥ እንዲያሽቆለቁል አድርጓል። የኩበት ጭስም የእናቶችንና የህፃናትን የመተንፈሻ አካላት እየጐደ ለህመምና ለህልፈት አያደረገ ይገኛል። በዘህ ረገድ በሰሜን ሸዋ ከሱሉልታ ጀምሮ እስከ አባይ ሸለቆ መዳረሸ ድረስ የሚገኙ አርሶ አደር ሚስቶች ለከፍተኛ የጤና ችግር በኩበት ጭስ አማካኝነት እየተዳረጉ መሆኑን ጤና ጥበቃ በቅርቡ አመልክቷል።

የማኅበራዊ ጥናት መድረክ የ2009 ሪፖርት እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ በኦሮምያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እንዲሁም በአማራ ክልሎች እንደየቅደም ተከተላዠው የእንጨት ማገዶና ከሰል በከፍተኛ መጠን በየዓመቱ የሚመረትና ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን፤ ትግራይ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላም በስፋት ከሰል እየተመረተ ጥቅም ላይ ይውላል። በአብዛኛው በሀገራችን በዝቅተኛ መሬት በሚገኙ ውድ ላንድ ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች ከሰል ይመረታል። በአፋር ከሰል በብዛት ቢመረትም ጥቅም ላይ የሚውለው ግን ሌላ ክልል ነው። እንደ አቶ መላኩ ገለፃ ምንም እንኳን የከሰል ኢንደስትሪ ለብዙዎች ማለትም ለ10 ሺህዎች ገቢ ማስገኛና መተዳደሪያ እንዲሁም ለበርካታ ከተማዎች የኃይል ምንጭነት ጥቅም ላይ ቢውልም፤ ፖሊሲ አውጭዎችም ሆኑ የልማት ኤጀንሲዎች ለጉዳዩ እዚህ ግባ የሚባል ትኩረት አልሰጡትም።

የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በአስተዳደራዊና መዋቅራዊ ችግሮች የተተበተቡ ከመሆኑ የተነሳ በቂና አካታች የሆኑ መረጃዎች ለኅብረተሰቡም ሆነ ለውሳኔ ሰጭዎች በተገቢው ሁኔታ አይቀርቡም። ይህ ለሚሊዮኖች የኃይል ምንጭ የሆነው ዘርፍ በተገቢው እንዲታወቅና በሂደት በታዳሽ ኃይል እንዲተካ ሰፊ ጥናትና ምርምር የሚያስፈልገው እንደሆነ አቶ መላኩ አመልክተዋል። የከሰል አመራረት ገበያውና ጥቅም ላይ አዋዋሉ በምን መልኩ እየተከናወነ እንደሆነ በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ግንዛቤያቸውን ሊያዳብሩ ይገባል። በኢትዮጵያ በበርካታ ከተሞች ውስጥ የከሰል አጠቃቀምና ንግድ በስፋት ይካሄዳል። ከእነርሱ መካከል በተገቢው የሚታወቁትና የተጠኑት መቀሌ፣ ባህርዳር፣ ገዋኔ፣ ድሬዳዋ፣ አዲስ አበባ፣ ናዝሬት፣ አዋሽ፣ ጅጅጋ፣ አዋሳና አርባ ምንጭ ይገኙባቸዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ የከሰለ አመራረትና ስርጭትን በኢንቫይሮሜንትና በጤና ላይ እያስከተለ ስለሚገኘው ጉዳት በተገቢው ተጠንተው የተቀመጡ ጽሁፎች በጣም ውስን ሲሆኑ፤ በፌዴራል ደረጃም ስለ ጉዳዩ በበቂ ሁኔታ መረጃ መስጠት የሚችል አካል እንደሌለ የጥናቱ አቅራቢ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ በአብዛኛው ግራራማ መሬቶች ውድላንድ ተብለው በሙያተኞች የሚጠሩትና ሰፋፊ ቅጠል ባላቸው ቁጥቋጦዎች አካባቢ ከሰል በስፋት ይመረታል። ከዚያም በከተሞች ለገበያ ይቀርባል። ዋንኛ ቦታዎችም በአፋር ክልል ገዋኔ ከተማ አካባቢ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ብላቴ በተባለው ስፍራ በኦሮምያ ክልል ላንጋኖ እና ቦረና ዞን፣ በሶማሌ ክልል ሀርሺን አካባቢ ደረቃማ ደኖች በሚገኙባቸው የትግራይ፣ የአማራና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ አካባቢዎች ከሰል በስፋት ይመረትባቸዋል። አብዛኛዎቹ የአካሲያ ዝርያ ያላቸው ዛፎች ማለትም፤ ፕሮሶፊና ጁሉፍሎራ የተባሉ እሾሃማ ዛፎች ከሰልን ለማምረት በስፋት ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን፤ ከእያንዳንዱ የዛፍ አይነት ምን ያህል ከሰል እንደሚመረት በተገቢው አይታወቅም። ከዚህ ሌላ በአሁኑ ወቅት አልፎ አልፎ በአንዳንድ አካባቢዎች ባህር ዛፍ ለከሰልነት ጥቅም ላይ መዋሉን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በኢትዮጵያ በአብዛኛዎቹ አካባቢ ከሰል የሚመረተው እጅግ ኋላ ቀር በሆነ ዘዴ መሬት ውስጥ በተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ እንጨትን በማንደድ ሲሆን አክሳዮችንም ሆነ አካባቢን ለጉዳት የሚዳርግ ከመሆኑም በጣም አባካኝና ለደንና ለአካባቢ መራቆት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ነው። በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች የእንጨት ከሰል በተሻለ ቴክኖሎጂ የሚመረት ሲሆን፤ በተለይ በኬንያ ያለው ብክለትን የሚቀንስና አባካኝ ያልሆነ ነው ቴክኖሎጂውም ቅዳጅ በርሜልን ወይም የበርሜልን ግማሽ አካል ከመሬት በላይ በማስቀመጥ እንጨት በውስጡ ገብቶ እንዲነድና እንዲከስል የሚደረግበት ሲሆን፤ የሚጠይቀው የካፒታል ኢንቨስትመንት አነስተኛ የሚያስፈልገው ሠራተኛም አነስተኛ ሲሆን፤ ምቹና የማክሰል ሂደቱን በቀላሉ መቆጣጠር የሚያስችል ነው። የምርታማነት ብቃቱም ከ25 እስከ 30 በመቶ ሲደርስ ከሰሉም ተመራጭነት ያለው ነው። በአንፃሩ በሀገራችን ያለው የከሰል አመራረት እንጨትን ከመሬት ስር ባለ ጉድጓድ በመቅበርና በማቃጠል ሲሆን፤ የሚጠይቀው ኢንቨስትመንት አነስተኛ የሚጠይቀው የስራ ኃይል እጅግ ከፍተኛ ሲሆን፤ የማክሰል ሂደቱን ለመቆጣጠርና ለመከታተልም እጅግ አስቸጋሪ ነው። የምርታማነት ውጤታማነት መጠኑ ከ15 እስከ 25 በመቶ ሲሆን፤ ጥራቱም ይህን ያህል ነው። በአሁኑ ወቅት በሀገራችንም ሆነ በሌሎች ታዳጊ ሀገሮች የደን ውድመትን ለመከላከል እንዲቻል ኅብረተሰቡ ከእንጨት ከሰል ይልቅ ከወዳደቁ ተረፈ ምርቶች የሚመረተውን የብሪኬትስ ከሰል እንዲጠቀም እየተበረታታ ይገኛል። የብርኬት ከሰል ከእንጨት ከሰል ጋር ሲነፃፀር ተመራጭነቱ እጅግ የላቀ ነው። የእንጨት ከሰል ጭሳማ፣ ውስን የሙቀት እምቅ ያለው፣ የደን ውድመትን የሚያባብስ ለአጭር ጊዜ ተቃጥሎ የሚያልቅ ነው። በተቃራኒው የብርኬትስ ከሰል ጭስ አልባ፣ የኃይል አቅሙ ከፍተኛ፣ የደን መመንጠርን ለመቀነስ የሚያስችልና ከሁለት እስከ ሦስት ሰዓት ያህል መንደድ የሚችል ነው።

እንደ አቶ መላኩ በቀለ ጥናት፤ በከሰል አመራረትና ንግድ ሰንሰለት የሰዎች ጾታና እድሜ እንደ አንድ ጠቋሚ ተወስዷል። በአዲስ አበባ እድሜያቸው ከ20 እስከ 30 የሚገመቱ ወጣቶች 58 በመቶ የሚሆነውን የጅምላ አከፋፋይነት ስራን እንዲሁም እድሜያቸው ከ30 እስከ 40 የሚደርሱት 30 በመቶ የሚሆነውን የጅምላ አከፋፋይነት ስራ ይሰራሉ። ከ40 በላይ የሆኑት 10 በመቶ የሚሆነውን የጅምላ አከፋፋይነት ስራን ይሰራሉ። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው አብዛኛው የከሰል ቢዝነስ ስራ የሚሰራው በወጣቶች ሲሆን፤ 70 በመቶው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕድሜው ከ30 ዓመት በታች መሆኑ ከግምት ሲገባ በገጠር ያለው ስራ አጥነት በተገቢው ካልተገረፈ በከሰል ቢዝነስ የተነሳ አካባቢው በከፍተኛ ሁኔታ ሊወድም እንደሚችል መገመት አያስቸግርም።

ጾታን በተመለከተ ጥናቱ እንዳመለከተው 33 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ከሰልን በጅምላ በማከፋፈል ስራ የተሰማሩ ሲሆን፤ በአንፃሩ 67 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች በጅምላ አከፋፋይነት ይሰራሉ። የትምህርት ደረጃቸውም 26 በመቶ የሚሆኑት ፊደል ያልቆጠሩ ሲሆኑ፤ 43 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ናቸው። 30 በመቶ የሚሆኑት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያላቸው ሲሆን፤ የከፍተኛ ትምህርት የቀሰሙ የ1 በመቶ ድርሻ አላቸው። ከዚህ አንፃር የከሰል ንግድ እንደ ሙያ ተይዞ መተዳደሪያ መሆኑ ግልፅ ሲሆን፤ ገጠር ደንን ጨፍጭፈው ከሚያከስሉት ጀምሮ ከተማ ውስጥ ከሰልን በችርቻሮ እስከሚሸጡት ያለው የሰው ኃይል ሲታይ ቁጥሩ ቀላል እንደልሆነ መገመት ይቻላል። ስለሆነም አረንጎዴ ኢኰኖሚ በሀገራችን ለመገንባት ከፊት ለፊታችን ከባድ ስራእንደተደቀነና ስራውም ጊዜ ሳይሰጠው መሠረት እንዳለበት የከሰል ቢዝነስ ቀጥተኛ አመላካች ነው።

በአሁኑ ወቅት የከሰል ዋጋ በከተሞች እያሻቀበ ቢሄድም ለአብዛኛው መካከለኛ ገቢ ባለው ከተሜ ሊሸመት የሚችል ነው። በቀላሉ የሚገኝና ጥቅም ላይ የሚውል ነው። በአዲስ አበባ ከተማም 73 በመቶ የሚሆን ቤተሰብ ከሰልን ለምግብ ማብሰያነት፣ ለቡና ማፍያነት፣ ቤትን ለማሞቂያ፣ በቆሎ ለመጥበሻ፣ ለብስን በካውያ አማካኝነት ለመተኮስ እና ለሌሎች አገልግሎት ይጠቀምበታል።

    የጥናቱ አቅራቢ እንደገለፁት አብዛኛዎቹ በከሰል ቢዝነስ ውስጥ የገቡት ሰዎች ባለፉት አምሰት ዓመታት ውስጥ ሲሆን፤ ጥቅሙ እየታወቀ በመሄዱም ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው። በገጠር ገበሬዎች በድርቅ ወቅት ምርታቸው በጣም ሲያሽቆለቁል በቀጥታ የሚታያቸው አካባቢን በሚያወድመው በከሰል ማክሰል ስራ መሰማራትን ነው። ይሁን እንጂ ከሰል ማክሰል በራሱ ለእርሻቸው ምርታማነት መቀነስ ቀጥተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት እጅግም የተረዱት አይመስልም። ስለሆነም የግንዛቤ ማስጨበጡ ስራ በይደር መቆየት የሌለበት ነው።

በአይቼው ደስአለኝ

 

የአየር ንብረት መዋዠቅ ጉዳይ ለሀገራት የራስ ምታት ሆኖ ማወያየት ከጀመረ በርካታ አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል። ከዚህ ቀደም የበለፀጉ ሀገሮች ኢኮኖሚያዊ እድገታቸውን ለማሳለጥ የተጠቀሙበት አካሄድ ወደ ከባቢ አየር በካይጋዞችን በስፋት በመልቀቅ ላይ ያተኮረ ስለነበር አሁን ላለው ችግር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል። በዚህ ሳቢያም አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ እንዲሉ በካዮቹ ሀገሮች ባላቸው የኢኮኖሚ የቴክኖሎጂና የእውቀት አቅም በመታገዝ ችግሩን ሲቋቋሙ ለዚህ መሰሉ ጥፋት አንዳችም አስተዋፅኦ ያላደረጉት ታዳጊ ሀገሮች ይበልጥ ገፈቱን ለመጨለጥ ተገደዋል። የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎቻቸው ለጉዳት ተጋላጭ ለመሆን በቅቷል። በዓለም ላይ የመቅሰፍትን ያህል በሰው ልጅ በእንስሳትና በተፈጥሮ ሀብት ላይ ጉዳት እየደረሰ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ ሀገሮች በጋራ ካልሆነ በተናጠል ለመቋቋም እንደማይችሉ ተገንዝበዋል። በተለያዩ አጋጣሚዎች እየተገናኙ በችግሩ ዙሪያ በመወያየት መፍትሄ ለማፈላለግ ጥረታቸውን ቀጥለዋል። ይሁን እንጂ በሀገሮቹ የተለያዩ ፍላጎቶችና የጥቅም ግጭቶች ሳቢያ ችግሮቹ መፍትሄ አላገኙም ጥረቱ ግን እንደቀጠለ ነው።

አቶ ገብሩ ጀንበር በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በአየር ንብረት ለውጥ ዘርፍ የቡድን አስተባባሪ ናቸው። የአየር ንብረት ለውጥና የሙቀት መጨመርን አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ሲገልፁ ተፅዕኖው በቀጥታና በተዘዋዋሪ እንደሚከሰት ያስረዳሉ። እንደ እርሳቸው በኢትዮጵያ ባለው ሁኔታ በእርሻ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ አለው የእህል ዘር መዝሪያ ወቅትን ያዛባል፣ ምርት ከመቀነስ አልፎ እንዲጠፋ ጭምር ሊያደርግ ይችላል። አንዳንዴ ዝናብ ዘግይቶ ሲጀምር ማሳ ላይ ተዘርቶ የነበረ እህል ሊጎዳ ይችላል። በሌላ በኩል ከባድ ዝናብ ሲመጣ እህሉን አውድሞና በጎርፍ ጠራርጎ ሊወስድ ይችላል። አክለውም ቀደም ባለው ዘመን ድርቅ የሚከሰተው በየ10 ዓመቱ የነበረ ሲሆን አሁን ችግሩ እየከፋ በመምጣቱ በየ5 እና 3 ዓመታት ውስጥ እየተከሰተ ከባድ አደጋን በመደቀን ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል። ስለዚህ የእርሻው ዘርፍ ዋንኛ የችግሩ ሰለባ ነው ብለዋል።

ሌላው ክፉኛ በአየር ንብረት ለውጥ የሚጎዳው የውሃው ዘርፍ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ድርቅ ሲከሰት የዝናብ መጠን ይቀንሳል። ይህም በገፅና በከርሰ ምድር የሚገኝ ውሃ መጠን እንዲያሽቆለቁል አድርጎ በይበልጥ የአርብቶ አደሩን የህይወት እንቅስቃሴ ለተጋላጭነት ይዳርጋል። ዝናብ ዘግይቶ ሲጀምርና መጠኑ ሲቀንስ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው ለመሰደድ ይገዳደሉ። በዚያ አካባቢ የሚገኙ አርብቶ አደሮችም ከሌላ አካባቢ በመጡ አርብቶ አደሮች የውሃና የግጦሽ ሀብታችን ተነካ በሚል ወደግጭት ማምራት ሊሄዱ ስለሚችሉ በሰውና በእንስሳት ላይ ከባድ አደጋ ያመጣል። በሌላም በኩል የውሃ እጥረት በሃይል አቅርቦት ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ያሳርፋል። ለምሳሌ የሀገራችን የሃይል አቅርቦት ምንጭ 90 በመቶው ከውሃ የሚገኝ ነው። ይህ ታዳሽ መሆኑ በጣም ጠቃሚና ከብክለት ነፃ የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያግዝ ቢሆንም የራሱ ሆነ ችግርም አለው። ይኸውም በድርቅ ወቅት ዝናብ ሲቀንስ ወደ ወንዞች ብሎም ወደ ግድቡ የሚገባ ውሃ ስለሚቀንስ ኃይል በማመንጨት አቅሙ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው። በዚህ ሳቢያም የኤሌትሪክ አቅርቦት በራሽን መልክ እንዲሰጥ ለማድረግ ያስገድዳል። ከዚህ አለፍ ሲልም የአቅርቦቱ ማነስ ፋብሪካዎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎታቸው ተስተጓጉሎ በምርታማነትና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። በሌላም በኩል በድርቅና በከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ በግድብ ውስጥ የሚገኝ ውሃ የትነት መጠኑ ስለሚጨምር ውሃው እንዲቀንስ አድርጎ ኃይል በማመንጨት ኃይሉ ላይ ጫና ሊያሳርፍ ይችላል።

እንደ አቶ ገብሩ ጀንበር አገላለፅ ችግሩ ከግብርናው አልፎ በሌሎች ሴክተሮች ላይ ጫና ሊያሳርፍ ይችላል። ከእነኚህ ዘርፎ አንዱና ዋንኛው የጤናው ዘርፍ ነው። በአየር መዋዠቅ የተነሳ ከፍተኛ የዝናብ መጠን ተከስቶ የጎርፍ መጥለቅለቅ ሊያጋጥም በአንዳንድ አከባቢዎች ላይ የውሃ መታቆር ሁኔታ ይከሰታል። ይኸም ውሃ ወለድ በሽታ እንዲከሰት ያደርጋል። በተለይ የወባ እና መሰል ትንኞች የመራባት አጋጣሚ ስለሚፈጥርላቸው በሰው ህይወትና ጤና ላይ በቀላሉ ጉዳት ያደርሳሉ። የተበከሉ ውሃዎች ወደ ወንዞችና ኩሬዎች ውስጥ ከገቡም በውሃው ተጠቃሚ ገጠሬ ላይ ተላላፊ በሽታዎችን በማስከተል ለከፍተኛ የህክምና ወጭ ይዳርጉታል። ይህም ያላቸውን ውስን ጥረት በዚህ ሳቢያ እንዲያወጡት ያስገድደዋል። የሙቀት መጨመር ከቦታ ወደ ቦታ መስፋፋቱ አዳዲስ ክስተቶችን እየፈጠረ ይገኛል። ቀደም ባለው ጊዜ የወባ ትንኝ በቆላ አካባቢ ነበር የሚራቡት። አሁን ግን ከወይናደጋ አልፈው እንደ አዲስ አበባ በመሰል ከፍተኛና ደጋ መሬት ላይ ሁሉ የወባ ትንኝ መራባት ስለቻሉ በሽታውን ለመግታት ከመንግስትና ከሌላው ባለድርሻ አካል የሚወጣው ገንዘብ እንዲጨምር አድርጓል።

አቶ ገብሩ አያይዘውም የጎርፍ መጥለቅለቅ በንፁህ ውሃ አቅርቦት ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳረፈ እንደሚገኝ ይገልፃሉ። በጎርፍ መጥለቅለቅ የንፁህ ውሃ ማቅረቢያ ግድቦች ሊበክሉ ወይም ተደርምሰው ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ሊፈሱ ይችላሉ። ይህም ሌላ ጥፋት ነው። መሰረተ ልማቶችም የዚህ አደጋ ሰለባዎች ናቸው። ጎርፍ መንገዶችንና ድልድዮችን ከጥቅም ውጭ አድርጎ የአንድ አካባቢ ህዝብ ከለላው አካባቢ ጋር እንዲቆራረጥ ያደርጋል። የሃይል አቅርቦት መስመሮችም ተበጣጥሰውና በጎርፍ ተወስደው ኃይል እንዲቋረጥ ያደርጋል። እንደ አቶ ገብሩ ገለፃ በኢትዮጵያ የተፅእኖው መጠን ከቦታ ቦታ ይለያይ እንጂ ሁሉንም ዘርፎች ይጎዳል።

የአየር ንብረት ለውጥ ቀጥተኛ ተፅዕኖው በከፊል ይህን ሲመስል ቀጥተኛ ባልሆነ መልኩ ደግሞ የራሱን ጫና እንደሚከተለው ያሳርፋል። በድርቅ ወቅት አርሶ አደሮችም ሆኑ አርብቶ አደሮች ለህይወታቸውም ሆነ ለከብቶቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ለመፈለግ ከቦታ ወደ ቦታ ተፈናቅለው ይፈልሳሉ። በዚህ ወቅት ልጆቻቸው ትምህርት ይማሩ እንደሆነ ከትምህርት ገበታቸው ይገለላሉ። ይህም በትምህርት ላይ ያለው የህብረተሰብ ተሳትፎ እንዲቀንስ ያደርጋል። በሌላም በኩል በቤተሰብ ውስጥ ወንዶች በብዛት በቀን ስራ ለመሰማራትና ገቢ ለማግኘት ወደ ሌላ አካባቢ ሲፈልጉ ቤት ውስጥ በሴቶች ላይ ከፍተኛ የስራ ጫና ይከሰታል። ውሃ መቅዳት፣ እንጨት ከመልቀም ምግብ ማብሰልና ልጆችን መንከባከብ በተጨማሪ ሌሎችን ኃላፊነቶች ይወጣሉ።

ችግሩ በዚህ ብቻ ተከስቶ የሚቀር አይደለም። ወንዶች ከመንደራቸው ርቀው በሌላ ስራ ተሰማርተው ሲከርሙ ከሌላ ሴቶች ጋር ለወሲብ የመተኛት ዕድላቸው ከፍተኛ ስለሚሆን ለኤች አይ ቪና ለመሰል በሽታዎች ተጋላጭነታቸው ይሰፋል። ተመልሰው ወደ መንደራቸው ሲገቡም ሚስቶቻቸውን በዚህ በሽታ ሊበክሉ ይችላሉም። ሴቶችም በቤታቸው ውስጥ ያለባል ሲቀመጡ በሌላ ወንድ የመደፈርና የተጋላጭነት መጠናቸው የዚያኑ ያህል ከፍ ይላል። ይህ እንግዲህ በጤናውና በትምህርቱ ዘርፍ ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ እንደሆነ መጥቀስ ይቻላል።

ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ የሚያገለግለው የእርሻው ዘርፍ እንደሆነ ይታወቃል። እንዲያም ሆኖ ቀላል ኢንዱስትሪዎችና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ እንደመጣ መረዳት አያዳግትም። ይህ ዘርፍም በስፋት በግብአትነት የሚጠቀመው የእርሻ ምርትን ነው። በመሆኑም እርሻው በድርቅ ሲመታና ምርቱ ሲቀንስ ለማኑፋክቸሪንግ የሚቀርበው ግብአትም ስለሚቀንስ ለዘርፉ ስራ መስተጓጎልና ለተጨማሪ ወጭ መዳረግን ያስከትላል። እነኚህ ዘርፎች በተለይ ኤክስፖርት የሚያደርጓቸው ምርቶች ካሉ ተፅዕኖው ሀገራችንን የውጭ ምንዛሪ እስከማሳጣት ያደርሳል።

ከሀገራችን ራቅ ባሉ አካባቢዎችም የአየር ንብረት ለውጥና የሙቀት መጨመር ሁኔታ ሌላም ተፅዕኖ እያስከተለ ይገኛል። በሰሜን ዋልታ አካባቢ የሚገኙ በረዶዎች በሙቀት ሳቢያ እየቀለጡ የባህር መጠን እንዲጨምር በማድረግ አንዳንድ አነስተኛ ደሴቶች በውሃ የመዋጥ ስጋታቸው ከፍ እንዲል አድርጓል። በሌላም በኩል አብዛኛዎቹ የአለም ከተሞች ለንግድና ለአመቺ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በሚል በባህርና በውቅያኖስ ዳርቻዎች ላይ የተቆረቆሩ በመሆናቸው የባህር መጠን መጨመር እነርሱም በውሃ የመጥለቅለቅ ስጋታቸው እየጨመረ አንዳንዴም እውን እየሆነ በንብረትና በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እያስከተለባቸው ይገኛል። ይህን በተመለከተ አቶ ገብሩ ጀንበር ሲናገሩ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ከቦታ ወደ ቦታ የተለያየ እንደሆነ ጠቅሰው ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ በተደጋጋሚ ሲከሰት ሌሎች ሀገሮችን ደግሞ ጎርፍ ያጠቃቸዋል። ለዝናብ መፈጠር ምክንያት የሆኑ ክስተቶች ከአንድ አካባቢ አልፈው በሌላው ላይ ተፅዕኖ ያሳርፋሉ። አውሮፓ ወይም ህንድ ውቅያኖስ የሚከሰት ችግር በሀገራችን ላይ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ ይችላል። ከሁለት ዓመታት በፊት ሞዛምቢክ ውስጥ ከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ ተከስቶ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ አድርሶ ነበር። በተቃራኒው በዛን ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ድርቅ ነበር። በኢትዮጵያ ከባቢ አየር ውስጥ የነበረ ርጥበት አዘል አየር ኢትዮጵያ ውስጥ ዝናብ ድርቅ ሳይወርድ ቆይቶ በንፋስ ወደ ደቡባዊ አፍሪካ በመገፋቱ ሞዛምቢክ ላይ ከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ ሊደርስ ችሏል። የበረዶ መቅለጥና የሚያስከትለው መዘዝም ከዚህ አኳያ ሊታይ የሚችል ነው።

እንደ አቶ ገብሩ ገለፃ በታሪካዊና በኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ሳቢያ አብዛኛዎቹ የአለም ዋና ከተሞች በባህር ዳርና በውቅያኖስ ዳርቻዎች የተቆረቆሩ ናቸው። በረዶ የሚቀልጠው ደግሞ በሰሜን ዋልታ አካባቢ ነው። ከበረዶ መቅለጥ በተወሰነ መልኩ ተጠቃሚ የሚሆኑ ሀገሮች አሉ። ለምሳሌ ካናዳና ሩሲያ በዚህ ምክንያት በረዶ ሲቀልጥ ተጨማሪ የእርሻ መሬት ሊያገኙ ይችላሉ። ለተወሰነ ወቅትም ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ነገር ግን የበረዶ መቅለጥና የባህር መጠን መጨመር አነስተኛ ደሴቶች በባህር ውሃ እንዲጥለቀለቁና እስከመጨረሻው አካባቢውን ለቀው እንዲሰደዱ የሚያደርግ ክስተት ሊፈጠር ይችላል። በዚህም ምክንያት በየትኛውም የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ላይ የደሴቶች መንግስታት ተወካዮች የበለፀጉ ሀገሮች የልቀት መጠናቸውን ከምር እንዲቀንሱ አምርረው ጥያቄያቸውን ያቀርባሉ። በባህር ውሃ መጠን መጨመር ሳቢያ በውቅያኖስ ዳርቻ የሚገኙ ከተሞችም በየጊዜው የመጥለቅለቅ አደጋ እያጋጠማቸው ሲሆን ከፍተኛ ዋጋም እየከፈሉበት ይገኛሉ። ስለሆነም እነርሱም በአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ላይ መንግስታት በቁርጠኝነት የልቀት መጠን ቅነሳውን ተግባራዊ እንዲያደርጉ በመጠየቅ ላይ እንደሚገኙ አቶ ገብሩ ያስረዳሉ።

      ችግሩን ለመላመድና ለመቋቋም እንደኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገሮች ምን አይነት ርምጃ መውሰድ እንደሚገባቸው የተጠየቁት አቶ ገብሩ ሲመልሱ የአየር ንብረት ለውጥ ክስተት ተወደደም ተጠላም የሚቀጥል እንደሆነ ጠቅሰው አሁን የአለም መሪዎች ብክለትን ለመቀነስ ቢስማሙ እንኳን ለውጡ ቀጣይነት እንዳለው አመልክተዋል። ምክንያቱም ሲገልፁ ግሪን ሀውስ ጋዞች በከባቢ አየር ውስጥ ከ60 እስከ 70 ዓመታት ያህል ስለሚቆዩ የአየር ንብረት ለውጡ ችግር በዚህ ወቅት እንደማይፈታ አመልካች ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ ሀገር እንደየኢኮኖሚ፣ የቴክኖሎጂና የገንዘብ እንዲሁም የእውቀት አቅሙ የአዳፕቴሽንና ሚቲጌሽን ስራ ለዘለቄታው መሥራት እንደሚገባው አቶ ገብሩ አሳስበዋል።

ከእ.ኤ.አ 1972 ዓ.ም ስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ በዓለም ሀገሮች ዘንድ ትኩረት አግኝቶ በተደራዳሪዎች መካከል የተጀመረው ውይይት 42 ዓመታትን አስቆጥሯል። ይሁን እንጂ ከዚያን ዘመን ጀምሮ ዓለም በኢንዱስትሪ እየበለፀገች ደሀ ሀገሮችም በኢኮኖሚ ለመዳበር በሚያደርጉት ጥረት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁት በካይ ጋዝ እየጨመረ ችግሩ ይበልጥ እየተወሳሰበ እንዲሄድ አድርጓል። በዚህም የተነሳ የደሀ ሀገሮች እርሻ ምርት ይበልጥ እየተሽመደመደ ወደ ውጭ ገበያ የሚልኩት ምርትም እየቀነሰ ሲሄድ በተቃራኒው በዓለም ገበያ ያለው የምግብ የእህል ዋጋ ይበልጥ እየናረ ሀገሮች ምግብ ለመሸመት የሚያወጡት ወጪ እጅግ ከፍ ብሏል። በዚህ ሳቢያም ከግብርናው አልፎ አጠቃላይ ኢኮኖሚያቸው እንዲጋሽብ ምክንያት ሆኗል። ስለሆነም ወደከባቢ አየር የሚለቀቀው በካይ ጋዝ እንዲቀንስ ተደራዳሪዎች ከምንጊዜውም በተሻለ መልኩ ልዩነቶቻቸውን በማጥበብ ዓለምን ከጥፋት ለመታደግ ቁርጠኝነታቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። ዶ/ር ኃብተማርያም አባተ በኢትዮጵያ የግብርና ትራንፎርሜሽን ኤጀንሲ ከፍተኛ ተመራማሪ ሲሆኑ ከ30 ዓመታት በላይ በሙያቸው አገልግለዋል። የአየር ንብረት ለውጥ በተመለከተ በተካሄደ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችም ተካፍለው ልምድ አካብተዋል። ድርድርን በተመለከተም እንደሚገልጹት የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለረጅም ዓመታት ተካሂደዋል። በተለይ እ.ኤ.አ በ2009 ኮፐን ሀገን ላይ በተደረገው ውይይት ላይ ጉዳይ እልባት ያገኛል የሚል ተስፋ ተጥሎ ነበር። ነገር ግን ለችግሩ እልባት ሳይሰጠው ቀርቷል።

ከዚያ በመቀጠል ላለፉት አምስት ዓመታት ከፍተኛ እንቅስቃሴ የተደረገ ሲሆን ባለፈው ዓመት በፓላንድ ዋና ከተማ ዋርሶ ላይ በተደረገው ስብሰባም ጉዳዩ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጠው ከፍተኛ ግፊት ተደርጓል። ጥረቱ በዚያው ቀጥሎ ከሰሞኑ ኒውዮርክ ውስጥ በተደረገው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ በተጠራው የአየር ጠባይ ለውጥ ስብሰባ መሪዎች ቃላቸውን እንደሚያድሱ መናገራቸውን ዶ/ር ኃብተማርያም አመልክተዋል። እንደ እርሳቸው ገለፃ የኒውዮርኩን ስብሰባ ከሌላው ጊዜ የሚለየው በ100ሺህ የሚቆጠሩ ትዕይንተ ህዝብ አድራጊዎች የዓለም መሪዎች በመጭው ዓመት ፓሪስ ላይ በሚካሄደው ስብሰባ ላይ የልቀት መጠናቸውን አሳሪ በሆነ ህግ ላይ ተመርኩዘው እንዲቀንሱ ከፍተኛ ግፊት ማድረጋቸው ነው። በተያያዘም ከኒውዮርክ ቀጥሎ ፔሩ ከዚያም ፓሪስ ላይ የሚደረጉት ስብሰባዎች ከበፊቱ ጊዜያት የበለጠ ፍሬያማ ይሆናሉ ተብለው ይጠበቃሉ። ይሁን እንጂ በድርድሩ ውስጥ ሥር የሰደደና እስካሁንም እልባት ያልተገኘላቸው ችግሮች እንዳሉ እሙን ነው።

በአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ዋናው ጉዳይ ወደ ከባቢ አየር በኢንዱስትሪዎች አማካኝይነት የሚለቀቀውን በካይ ጋዝ የመቀነስ ጉዳይ ነው። ይህን በተመለከተ የበለፀጉ ሀገሮች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች አሉ። ይኸውም የልቀት መጠን ሲቀንስ አብሮ በኢኮኖሚ ላይ ጫና የማሳረፍ ጉዳይ አለ። ይህም የፋብሪካዎችን እንቅስቃሴ መግታትና አልፎም የሠራተኞችን ቁጥርን መቀነስ ወደሚያስችል መዘዝ ሊያስከትል ይችላል። በሌላም በኩል በበለፀጉ ሀገሮች ድርድር የሚያካሄደው ፈፃሚው የመንግስት አካል የድርድር ውሳኔዎችን ከመተግበሩ በፊት ጉዳዩን ወደሕግ አውጪው አካል ስለሚወስደው ይህም ስምምነቱ ተግባራዊ እንዳይደረግ ጭምር የማድረግ አቅም ስላለው የሚካሄዱ ድርድሮች ለፍቶ መና እንዲሆኑ የሚያደርግበት አጋጣሚ አለ።

ታዳጊ ሀገሮችም በፊናቸው እኛ ከዚህ ቀደም ለልቀቱ ምንም አስተዋፅኦ ስላላደረግን የልቀት መቀነሱ ጉዳይ እኛን አይመለከተንም፤ የበለፀጉ ሀገሮች ጉዳይ ነው የሚል አቋም ሲያራምዱ ቆይተዋል። በተለይ ከአሜሪካና ከአውሮፓ የማይተናነስ የልቀት መጠን ያላቸው ታዳጊዎቹ ህንድና ቻይና በዚህ አቋማቸው ይታወቃሉ። ይህ የበለፀጉና የአዳጊ ሀገሮች አቋም ድርድሩ ይበልጥ እንዲወሳሰብና መፍትሄ የራቀው እንዲሆን አድርጎት ቆይቷል። ከዚህ አንፃር ይህ የሀሳብ ልዩነት እንዴት ሊቀራረብና ሊቀረፍ እንደሚችል የተጠየቁት ዶ/ር ኃብተማርያም ሲመልሱ ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች ከ1990 ጀምሮ ሲነሱ እንደነበር ታዳጊ ሀገሮች የብክለቱ ቀጥተኛ ተጎጂዎች ስለሆንን ካሳ ይከፈለን የሚል ጥያቄ ያነሱ እንደነበር ጠቅሰው ሙቀቱን ለመቋቋሚያ የሚያስፈልገን ቴክኖሎጂም ይቅረብ በሚል ሁኔታውን ያጦዙት ነበር። ይሁን እንጂ ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ግን ሁኔታው እየተቀየረ እንደመጣና የኢኮኖሚ እድገት አካባቢን በመበከል የሚመጣ ከሆነ ዘለቄታነት እንደማይኖረው ግንዛቤ ለማግኘት በቅቷል። ብክለት የመቀነስ ጉዳይም የበለፀጉ ሀገሮች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የታዳጊ ሀገሮች ጉዳይ ጭምር እንደሆነ በመረዳት እንደቻይና የመሳሰሉ ሀገሮች የልቀት መጠናቸውን በተናጥል ለመቀነስና የተራቆቱ አካባቢዎችን በደን የመሸፈን ስራ በከፍተኛ ደረጃ እያከናወኑ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ቻይና በኒውዮርኩ ስብሰባ ላይ ብክለት ለመቀነስ ዝግጁነትዋን የገለፀች ሲሆን አሜሪካ በበኩልዋ ከዚህ ቀደም ስታራምደው የነበረውን አቋም ማለትም ቻይና እና ህንድ የልቀት መጠናቸውን ካልቀነሱ እኔም አልቀንስም በሚል በድርድሩ ላይ ታስቀምጥ የነበረውን ቅድመ ሁኔታ በማለስለስና በማለዘብ የተሻለ አቋም በማራመድ ላይ ትገኛለች። ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማም በኒውዮርኩ ስብሰባ ላይ ከቻይናው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ቻይና እና አሜሪካ ከፍተኛ የልቀት መጠን ያላቸው ሀገሮች እንደመሆናቸው ሁለቱም ከባድ ኃላፊነት ስላለባቸው ወደ መስማማት መምራት አለባቸው በማለት ገልጸዋል። ከዚህ አኳያ ሁኔታዎቹ ይበልጥ እየለዘቡ መምጣታቸውን መረዳት የሚቻል ሲሆን በፓሪሱ ስብሰባ ላይ ወደ አሳሪ ስምምነት የመድረስ እድሉ ሰፊ እንደሆነ ዶ/ር ኃብተማርያም አመልክተዋል።

ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት በአሁኑ ወቅት በዓለም ሙቀት መጨመር ሳቢያ የሚከሰቱ ችግሮች በጣም አስከፊ እየሆኑ ነው። በአንድ አካባቢ የመጣ ችግር ወደ ሌላ አካባቢ በፍጥነት እየተዛመተ ይገኛል። በሰሜን ዋልታ አካባቢ በሙቀት ሳቢያ በረዶ እየቀለጠ የባህር ውሃ መጠን እየጨመረ በባህር ዳርቻ የሚገኙ ከተሞችን እንዲሁም በውቅያኖስ ውስጥ የሚገኙ ደሴቶችን ወደ መዋጥ እየተቃረበ ነው። ከባህር በሚነፍስ አየር ውሃ ወደ መሬት ገብ ከተሞች እየመጣ በማጥለቅለቅ ጉዳት እያደረሰ ነው። ከሰሞኑ የስዊድን ሳይንቲስቶች ይፋ ባደረጉት ጥናት በየዓመቱ 280 ቢሊዮን ኪዩቡክ ውሃ በበረዶ መቅለጥ ሳቢያ እየተከሰተ ወደባህር በመግባት የውሃ መጠን እንዲጨምር እያደረገ ነው።

በስካንዲኔቭያ የምትገኘው የኮፐንሀገን ከተማ ከዚህ አኳያ የባህር መዋጥ እያሰጋት የባህር ዳርቻዎችዋን በግንብ እያጠረች ስትሆን የሞዛምቢክ ዋና ከተማም በተከታታይ ከህንድ ውቅያኖስ በሚከሰት ንፋስና ጎርፍ እየተጠቃች ትገኛለች። ቻይና እና ፊሊፒንስም ከዓመት በፊት በሳይክሌን አውሎንፋስ ተመተው የሰውና የንብረት ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚዘነጋ አይደለም። ይህ ሁሉ የችግሩ አሳሳቢነትን የሚጠቁም በመሆኑ ሀገሮች ወደስምምነት የሚመጡበት ወቅት መቃረቡን ያመለክታል።

ከዚህ አኳያ ቻይና በተናጠል የልቀት መጠኗን በመቀነስ ለሌሎች አርአያ እየሆነች ትገኛለች። ፋብሪካዎችም በታዳሽ ሀይል እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ላይ ስትሆን በአሜሪካም የሎቢ ቡድኖች የኢኮኖሚ እድገትን ለመጠበቅ ሲባል ብቻ የድርድርን ሀሳብ ውድቅ ማድረግ አይገባም በሚል ከሌሎች ቡድኖች ጋር በመሆን በመንግስት ላይ ጫና በማሳረፍ ላይ ይገኛሉ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም በበኩሉ በየጊዜው ሳይንቲስቶች በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የሚያቀርቧቸውን እጅግ አስጊ መረጃዎችን ለመንግስታቱ በማቅረብ የልቀት መጠን እንዲቀንስ የበኩሉን ግፊት እያደረገ ይገኛል። ከዚህ ቀደም በአየር ጠባይ ለውጥ ድርድር ላይ የራስዋን ችግሮች በማንሳት ችግሮች እልባት እንዲያገኙ ከቻይና ቀጥሎ ምክንያት ሆና የቆየችውና በህዝብ ብዛትዋ ከአለም ሁለተኛ የሆነችው ህንድ ነበረች። የህንድ ድሆች ብዛታቸው ከአፍሪካ ህዝብ ይበልጥ ይህን ደሃ ህዝብ ከድህነት ለማላቀቅ ህንድ ኢኮኖሚዬን ማሳደግ አለብኝ በሚል እየሰራች በፍጥነት እድገት ለማምጣት የቻለች ሲሆን፤ የዚያኑ ያህልም የብክለት መጠኗም ጨምሯል። ነገር ግን የልቀት መጠኗ ከ1ነጥብ 2 ቢሊዮን በላይ ከሚሆነው ህዝቧ ጋር ሲሰላ በነፍስ ወከፍ የሚደርሰው ከአፍሪካዊትዋ ናሚቢያ ያነሰ ነው። በዚህም መሰረት ይህን ያህል ደሃ ህዝብ ይዤ የልቀት መጠኔን ብቀንስ ተመልሼ ህዝቤን ወደ ድህነት አረንቋ ስለምመልሰው በዚህ በኩል አትምጡብኝ በሚል ስትከራከር ቆይታለች። ይህ የህንድ አቋም በአሁኑ ወቅት ምን ያህል ለዝቧል ተብለው የተጠያቁት ዶ/ር ኃብተማሪያም ሲመልሱ ይህ አስተሳሰብ ላለፉት 20 ዓመታት ድርድሩ ወደፊት እንዳይራመድ አድርጎት መቆየቱን ጠቅሰው ነገር ግን የሙቀት መባባስ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ ያለኢኮኖሚ እድገት በድህነት መኖር እንደሚቻል ሙቀት ግን ኢኮኖሚንም ሆነ የሰው ልጅን ከነጭራሹ ሊያጠፋ ስለሚችል ቅድሚያ ለሰው ልጅ ህልውና መስጠት አስፈላጊ ነው ወደሚል አቋም እየተገፋ ራሳቸውን ለድርድርና ለመለሳለስ እያዘጋጁ መምጣታቸውን ተናግረዋል። አክለውም ሕንድም እንደቻይና በፊናዋ ታዳሽ የሆኑትን የንፋስና የፀሐይ ኃይልን በቴክኖሎጂዋ አማካኝነት ጥቅም ላይ በማዋል የልቀት መጠኗን እየቀነሰች እንደምትገኝ ጠቅሰዋል።

የበለፀጉ ሀገሮች ከኢንዱስትሪ አብዮት ከተጀመረ ከ1850 ጀምሮ የተጓዘበት የብልፅግና አካሄድ የአካባቢ ጥበቃንና የተፈጥሮ ሀብትን ከግምት ውስጥ ያስገባ አልነበረም። ብዙ ጥፋት በማድረስ ነው አሁን ላሉበት ደረጃ የደረሱት። የህዝባቸው ኑሮ በተደላደለ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን የፍጆታ መጠናቸውም እጅግ የተንዛዛ ነው። በአሜሪካ አንድ ሰው መኪናን መቀየር የሸሚዝ ያህል ነው። በግል እስከ ሶስት መኪና የሚያዝበት ሀገር ነው። ይህም የነዳጅ ፍጆታቸውና ወደ ከባቢ አየር የሚለቁት የብክለት መጠን ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል። በቀን ለስራና ለሌላ ጉዳይ እስከ 2ሺህ ኪሎ ሜትር ይጓጓዛሉ። የተመረቱ ምርቶችም ከተለያየ ቦታ ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው የሚመጡ ሲሆን በአጠቃላይ የአሜሪካ የኢነርጂ ፍጆታ የአለምን 40 በመቶ እንደሆነ በቅርብ የወጡ ጥናቶች ያመለክታሉ። ከዚህ አኳያ የህዝቧ ብልፅግና ምን ያህል በተፈጥሮ ውድመት ላይ የተመሰረተ መሆኑን መገመት አስቸጋሪ አይደለም። የአሜሪካ መንግስት በCOP ስብሰባ ወደ ድርድር ሲገባም ይህን በመሬት ላይ ያለውን የህዝቡን የቅንጦት ህይወት ጭምር የማስጠበቅን ጉዳይ ችላ ሳይል ነው። የኪዮቶ ፕሮቶኮልን አለመፈረም ጉዳይ ከዚህ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው።

     በሌላ በኩል ታዳጊ ሀገሮች ድሆች ናቸው። እርሻቸው የኢኮኖሚያቸው የጀርባ አጥንት ነው። እስከ 70 በመቶ የሚሆነው ህዝባቸውም ገጠሬና ህይወቱ በዝናብ ላይ ጥገኛ በሆነ እርሻ ስራ ላይ የተመሰረተ ነው። የአየር ንብረት ለውጥ ሲመጣም ህዝባቸው በቀጥታ ወደ ምግብ እጦትና ወደ ምፅዋት ጠያቂነት ከመቅፅበት ይሸጋገራል። ከአየር ንብረት ለውጥ ውጭ ለቤት ውስጥና ለሌላ ጉዳይ በኢነርጂ ምንጭነት የሚጠቀመው ደንን በመጨፍጨፍ ሲሆን ከሰል ማክሰልም ራሱ የገቢ ምንጭ ማግኛ ነው። ይህ ሁሉ በአከባቢ ላይ ተጽዕኖ በማምጣት የአፈር ለምነት እንዲጠፋና ምርታማነት እንዲቀንስ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል። የተፈጥሮ መራቆት ከዚህ አልፎ በረሃማነት እንዲስፋፋ በማድረግ ላይ ይገኛል። ስለሆነም የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ለደሀ ሀገሮች ትልቅ ተስፋን የሚፈነጥቅ ነው። ደሃ ሀገሮች አሁን ያላቸው የገንዘብ አቅም ቴክኖሎጂና እውቀት ችግሩን ለመቋቋምና ለመላመድ የሚያስችላቸው አይደለም። ስለሆነ አሁንም የለጋስ ሀገሮች የገንዘብና የቴክኖሎጂ እገዛ ያስፈልጋቸዋል። ከዚህ ቀደም በኮፐን ሀገኑ ስብሰባ አፍሪካ ሀገሮች በቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አማካኝነት በተደረገው ጠንካራ ክርክር አየር ንብረትን ለውጥን ለመቋቋሚያ የሚሆን 100 ቢሊዮን ዶላር ከበለፀጉ ሀገሮች እንደሚገኝ ቃል ተገብቶ ነበር። ነገር ግን ተግባራዊ አልሆነም። ችግሩ ምንድነው ተብለው የተጠየቁት ዶ/ር ኃብተማርያም እንደገለፁት ሀገሮች በራሳቸው የውስጥ ችግሮች የተጠመዱና በገጠማቸው የገንዘብ ቀውስ የተነሳ ነው። አሁን ያለው የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ በመባባሱ የተነሳም ሀገሮች ችግሩን በተናጥል ሳይሆን በጋራ መቋቋም ስላለባቸው ጉዳዩ በፓሪሱ ስብሰባ ማለትም በመጪው ዓመት እልባት ያገኛል የሚል ተስፋ መኖሩን ጠቁመዋል።

በመላኩ ብርሃኑ

 

የክረምት ዝናብ የጠገበው መሬት ሲረግጡት ስምጥ ስምጥ ይላል። አረንጓዴ ለብሶ ለጥ ባለው መስክ ላይ የፈሰሱት የቀንድና የጋማ ከብቶች በስብጥር ለስፍራው አይን የሚያፈዝዝ ውበት ቸረውታል። እረኝነት የወጡ ህጻናት የገመዱትን ጅራፍ እያጮሁ በደስታ ይቦርቃሉ። ማርቆስ እና ኮሎቦ የተባሉት ሁለቱ የመናገሻ ከተማ ቀበሌዎች የሚዋሰኑበት ይህ ለጥ ያለ ሜዳ በለመለሙ ዛፎች የተሸፈነውን የመናገሻ ተራራ ትራስ አድርጎ ተዘርግቷል። አብዛኛው የመሬቱ ክፍል ለእርሻ ስራ የዋለ ሲሆን በጥቂት ቦታዎች ላይ ተራርቀው የበቀሉ ባህርዛፎች ይታያሉ። ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡ ምዕመናን ከተራራው ስር ወደተቆረቆረችው መናገሻ ማርያም ቤተክርስቲያን የሚጓዙት ይህንን መሬት አቋርጠው ነው።

ይህንን የመሰለውን የተፈጥሮ ውበት አለንጋ እንዳረፈበት ገላ እዚህም እዚያም ሸነታትረው ያበላሹት ቦዮች አፈሩን ከሳሩ አላቅቀው ለጸኃይ አጋልጠውታል። ቦዮቹ አፈሩን እያጠበ ከተራራው የሚወርደውን ውሃ ያለከልካይ በሜዳው ላይ እንዲጋልብ ማለፊያ መንገድ ሰጥተውታል። ብዛት ያላቸውን አነስተኛ ማሳዎች ዳር ዳር ከብበውና መሃል ለመሃል ገምሰው የገበሬውን የእርሻ መሬት እያጠበቡበትም ነው። አሁን አሁን ይህ ችግር የአካባቢውን የግብርና ስራ ፈተና ውስጥ እየከተተው መምጣቱን ነው አርሶአደሮቹ የሚናገሩት።

አርሶአደር ሸለመ በዳኔ በከፊል የታረሰ ማሳቸው ዳር ቆመው መሬታቸውን ተስፋ በቆረጠ እይታ ይቃኙታል። ቀስ በቀስ እየሰፋ መጥቶ በሁለት ዓመታት ውስጥ ማሳቸውን ለሁለት የከፈለው ሰፊ ቦይ ቤተሰቦቻቸውን ሲመግቡበት የኖሩትን ግብርና አስቸጋሪ አድርጎባቸዋል። ይህ ቦይ በተለይ ጠንከር ያለ ዝናብ በሚጥልበት ወቅት ሁሉ አፈሩን እየሸረሸረ ስፋቱን መጨመሩ ለእኚህ አርሶአደር ራስ ምታት ሆኖባቸዋል።

“ውሃው በማሳዬ ውስጥ እንዳያልፍ ያደረግኩት ጥረት ሁሉ አልተሳካም። የሰራሁት መከላከያ ሁሉ ዝናብ ሲዘንብ እየተናደ የእርሻ መሬቴ አፈር በጎርፍ እየታጠበ ነው። ጭራሽ መሬቴን ለሁለት ከፍሎ በበሬዎቼ ላይ ታች እያልኩ ለማረስ የማልችልበት ደረጃ ላይ አድርሶኛል። መሬቱ በመጥበቡም የማገኘው ምርት እየቀነሰ መጥቷል። የሆነ አካል መፍትሄ ካላበጀልኝ በቀር ይህ የአፈር መሸርሸር ነገ መሬቴን ነጥቆኝ ልጆቼን በረሃብ እንዳይበትንብኝ እየሰጋሁ ነው” ይላሉ ፍርሃት በተጫነው ስሜት ሁኔታውን ሲገልጹ።

በንግድ ስራ ለሚተዳደሩት አቶ ከተማ ኢብሳ አሳሳቢ የሆነባቸው ደግሞ ወደመንደራቸው የሚያስገባው መንገድ በጎርፍ መበላሸቱ ነው። “በስንት ርብርብ የተሰራ አንድ ኮረኮንች መንገድ ቢኖረን ዝናብ በዘነበ ቁጥር ከመናገሻ ዳገት ላይ የሚመጣው ውሃ አፈሩን እየሸረሸረ ቦዮች ሰራበት። በበጋ የደለደልነው አፈር በክረምት እየተናደ መንገዱን ወጣ ገባ ስላደረገው አሁን መኪና ወደስፍራው መግባት እየተሳነው ነው። ከዚህ ሁሉ በላይ በክረምት ወቅት መንገዱ ሁሉ ውሃ መውረጃ እየሆነ ለመተላለፍ አስቸጋሪ ሆኖብናል። ችግሩ በዚሁ ከዘለቀ ነገ ከቤቱ የወጣ ሰው መመለሻ ስለማግኘቱ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቸግራል” ይላሉ ስጋት ባጠላበት ድምጸት።

እነዚህ ነዋሪዎች የሚያነሱት ዓመታትን የዘለቀ የአፈር መሸርሸርና መሸሽ ችግር የመናገሻ ከተማን እጅግ እያሳሰባት ነው። የከተማው ማዘጋጃ ቤት “በአፈሩ ላይ የሚደርሰው ጥፋት በጊዜ ካልተቋጨ ወደፊት ለከተማዋ ከፍተኛ ስጋት መሆኑ አይቀሬ ነው” ይላል።

እጇን በእጇ የቆረጠች ከተማ

ወይናደጋ የአየር ንብረት ያላት መናገሻ ከተማ ከአዲስ አበባ በ28 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን በደረጃ 3 ከተመዘገቡት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከተሞች አንዷ ናት። ከተቆረቆረች 79 ዓመት ቢሞላትም እንደከተማ እውቅና ያገኘችው ግን በ1998 ዓ.ም ነው። ከ26ሺህ በላይ የሆኑትና በወጣ ገባ መሬቷ ላይ የሰፈሩት ነዋሪዎቿ በአብዛኛው መተዳደሪያቸው ግብርና በመሆኑ ለመናገሻ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ጉዳይ ዋና አጀንዳዋ ነው።

ከመግቢያዋ ጀምሮ የሚያጥራት የመናገሻ ተራራን ጨምሮ በዙሪያዋ ያለው የወጨጫ ተራራ ከተማዋን መሃል አስገብተው አቅፈዋታል። በተለይ ከጥፋት ከተረፉትና ከፍተኛ እንክብካቤና ጥበቃ ከሚደረግላቸው የደን ክልሎች ውስጥ የሚመደበው የሱጳ ጥብቅ የተፈጥሮ ደን ክልል ስለሚያዋስናት የአየር ንብረት ሚዛኗ የተጠበቀ፣ አፈሯም ለምነቱን እንደያዘ ረጅም ዘመን የዘለቀ ነው። የመናገሻ ዙሪያ በደን የተሸፈነ በመሆኑ ዝናብ አያጣውም። ማርቆስ እና ኮሎቦ የተባሉትና በ2000 ዓ.ም በተከለሰው ማስተር ፕላን የመናገሻ ከተማ አካል የሆኑት የአርሶአደር ቀበሌዎች በለም መሬታቸው የሚታወቁ ናቸው። ይህ የተፈጥሮ ሃብት የሚገባውን ያህል እንክብካቤ ሳያገኝ በመቅረቱ ሳቢያ ዛሬ ፊቱን እያዞረ ነው።

ለዓመታት የተካሄደው የደን ምንጠራ ከግጦሽ መሬት ማስፋፋት እና ከአካባቢው ገበሬዎች ኋላ ቀር የአስተራረስ ዘይቤ ጋር ተዳምሮ መሬቱን ለጥፋት የተጋለጠ አድርጎታል። በዚህም ሳቢያ አፈሩ በተደጋጋሚ ጊዜ በጎርፍ የመታጠብና የመሸርሸር አደጋ ስለገጠመው ለምነቱን እያጣ ነው። መሬት ቆንጥጠው የሚይዙና አፈር አቃፊ ስር ያላቸው ሃገር በቀል ዛፎች ተመንጥረው በማለቃቸውም በተለይ በወጨጫና በመናገሻ ተራሮች ላይ ያለው አፈር በውሃ ታጥቦ እንዲንሸራተትና እንዲናድ ምክንያት ሆኗል።ይህ ብቻም ሳይሆን ከዳገታማ አካባቢዎች ተነስቶ ተዳፋት ስፍራዎች ላይ የሚያርፈው ውሃ ለእርሻ ስራ የዋለውን መሬት እያጠበና የአፈሩን ለምነት እያሳጣ በግብርና ምርት ውጤታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥሯል። የውሃው ሃይል አፈሩን በጥልቀት እየቦረቦረ የሚፈጥረው ትላልቅ ቦይ በአካባቢው የበቀሉ ባህርዛፎችን ስር ከአፈር እያላቀቀ እንዲወድቁ አድርጓቸዋል። ይህም በተለይ ኮረቦዳ፣ አሊያንስ እና መናገሻ ማርያም የተባሉት አካባቢዎች ላይ የከፋ ችግር እንዲከተል ምክንያት ሆኗል።

ተፈጥሮ ለምነት ያደላትና ከሌሎች የሃገራችን ከተሞች ጋር ሲነጸጸር አንጻራዊ የሆነ የደን ሽፋን ያላት መናገሻ ከተማ ላጋጠማት የአፈር መታጠብ፣ ሽሽት እና መሸርሸር ምክንያቱ የአካባቢ ጥበቃና እንከብካቤ መጓደል መሆኑን ሁሉም ይስማሙበታል። ይህ ሰው ሰራሽ ችግር ነው መናገሻን “እጇን በእጇ የቆረጠች ከተማ” ያስባላት።

ነዋሪው የቆየ ስህተቱ የፈጠረውን ችግር ለማስተካከል ዛሬ ላይ አንዳንድ ጥረቶችን ማድረጉ ግን እውነት ነው። የመናገሻ ነዋሪና የሆለታ ደን ምርምር ማዕከል ሰራተኛ የሆኑት አቶ እሸቱ ደስታ ከተማዋን ከጊዜ ወደጊዜ ስጋት ውስጥ እየከተተው ያለውን የአፈር መሸርሸር እና መንሸራተት ችግር ለማስወገድ ነዋሪው ያደረጋቸው ጥረቶች በሙሉ አልተሳኩም ነው የሚሉት።

“አብዛኛው ቦታ ተዳፋት ስለሆነ አፈሩ በዝናብ ውሃ ለመታጠብ የተጋለጠ ነው። ችግሩን ለመከላከል በበጋ የሚሰራው እርከን ገና ሰኔ ሲገባና ዝናብ መጣል ሲጀምር ይናዳል። እንደመናገሻ እና ወጨጫ ባሉ ተራሮች ላይ የተሰሩ ሰፋፊ የእርከን ስራዎች ጎርፍ እያዘሉ በተደጋጋሚ ጊዜ በመናዳቸው የተነሳ ገበሬው መሬቱን ባንነካካው ይሻላል እያለ ነው። እንደሚመስለኝ አፈሩን አቅፎ የያዘው ደን ከላዩ ላይ ተጨፍጭፎ ስላለቀ መሬቱ አሁን ሳስቷል። በቀላሉ የሚናደውም ለዚህ ይመስለኛል። ገበሬው ከዳገቱ ላይ በሃይል የሚመጣው ውሃ እህሉን እንዳያጥብበት ሲል የሚሰራው ቦይ ጎርፍ እያጠራቀመ የበለጠ ጥፋት እያደረሰ ነው። በተለይ ማርቆስ ቀበሌ ውስጥ ውሃው የእርሻ መሬትን አፈር ጠራርጎ እየወሰደው ነው።” ይላሉ።

አቅምን የፈተነ ጥፋት

“ችግሩ ከከተማችን የበጀትም ሆነ የሰው ሃይል አቅም በላይ ሆኗል” ይላሉ የመናገሻ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ከንቲባ አቶ ሶፊሳ ደጀኔ። አቶ ሶፊሳ እንደሚናገሩት የከተማው ማዘጋጃ ቤት የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ በአካበቢ ጥበቃ ላይ ትኩረት አድርጎ ተንቀሳቅሷል። በዚህም ጎርፍ በሚበዛባቸው አካባቢዎች የውሃ መውረጃ ዲሽ በመገንባት ወደእርሻ መሬት እና ወደመንገድ ገብቶ ጥፋት እንዳያስከትል አቅጣጫ የማስቀየስ ስራ ተሰርቷል። የአርሶአደር ቀበሌዎች የሆኑትን የማርቆስ እና የኮሎቦ ነዋሪዎች በማስተባበር የተፋሰስ ልማት ለማከናወን ጥረት ተደርጓል። በወልመራ ወረዳ እንደአጠቃላይ የተካሄደው የተፋሰስ ልማት እና የነዋሪው የ30ቀን በጎ ፍቃድ አገልግሎት በከተማችን ዙሪያ ቀበሌዎችም ተግባራዊ ሆኗል። አርሶ አደሩ ጎርፍ በሚበዛባቸውና በቦረቦር ስፍራዎች ላይ በልማት ቡድን ተደራጅቶ እርከን እንዲሰራ በማድረግ ጎርፉ የሚያደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት ተሞክሯል። የተራቆቱ አካባቢዎችን በከተማው የችግኝ ማፍያ ጣቢያ በተዘጋጁ ሃገርበቀል ዛፎች ለማልበስ ህብረተሰቡን በማስተባበር የችግኝ ተከላ ስራዎችም ተሰርተዋል። ያም ሆኖ ይላሉ ከንቲባው፣ “ከችግሩ ስፋት አንጻር የሰራናቸው ስራዎች ሁሉ የተፈለገውን ውጤት አላስገኙም። በበጀት እና በባለሙያ በኩል ባለብን የአቅም ውስንነት ምክንያት እየደረሰ ያለውን ችግር ለማስቆም አልቻልንም። ችግሩ አሁን ከአቅማችን በላይ ሆኗል።” ብለዋል።

በመናገሻ ከተማ ማዘጋጃ ቤት በኩል የስጋቱ መጠን ከፍተኛነት ላይ በቂ ግንዛቤ አለ የሚሉት አቶ ሶፊሳ አስተዳደራቸው ችግሩን ለመከላከል ካደረገው መጠነኛ ሙከራ ባሻገር በበጀት እጥረት እና በአቅም ውስንነት ምክንያቶች ሳቢያ የስጋቱን አጣዳፊነት የሚመጥን መፍትሄ ማምጣት አለመቻሉን ግን አልሸሸጉም።

ጋቢዮን ያላሰረው የአፈር ሽሽት

ጋቢዮን በጠንካራ ሽቦ ተጠላልፎ በተሰራ መረብ መሰል መያዣ ውስጥ ድንጋይ በመሙላት አፈር እንዳይንሸራተት ለማገድ የሚጠቅም ዘዴ ነው። ጋቢዮን በተለይ በመንገድ ግንባታ ወቅት የአፈር መንሸራተት ሊከሰትባቸው ይችላል ተብለው በሚገመቱ አካባቢዎች ላይ አፈሩን ለመገደብ እና መንገዱንም ከብልሽት ለማዳን እንደዋና መፍትሄ ይወሰዳል። የሚንሸራተተውን አፈር አጥብቆ በመገደብና አስሮ በማስቀመጥ ባለበት ቦታ እንዲቆይ ያደርገዋል።

የመናገሻ ከተማን ጨምሮ በአጠቃላይ የወልመራ ወረዳ ብዙ ቀበሌዎች ችግር የሆነውን የአፈር መሸርሸርና መሸሽ አደጋ ለመከላከል መሬቱን በእርከን መልክ አበጅቶ አፈሩን በጋቢዮን ማሰር አንድ መፍትሄ ተደርጎ ተወስዷል። በ2005/6 ዓ.ም የመናገሻ ከተማ ማዘጋጃ ቤት በጀት መድቦ ከወልመራ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ጉዳታቸው ከፍተኛ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ጋቢዮን ለማሰር እንቀስቃሴ ተጀምሮ እንደነበር ማዘጋጃ ቤቱ ይናገራል። ስራው ከተጀመረ በኋላ ግን በበጀት እጥረት ሳቢያ ጋቢዮን ማቅረብ ባለመቻሉ በተለይም ችግሩ ካካለለው አካባቢ ስፋት ጋር ሲነጸጸር ይህንን ለመሸፈን በቂ አቅም ስላልነበር የተያዘው እቅድ ተግባራዊ መሆን አልቻለም። ይህ ብቻም አይደለም፣ የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት በውስን አቅም ያሰባሰባቸውን ድጋፎች ተጠቅሞ የአፈር መሸርሸሩ በጠናባቸው ተዳፋት ስፍራዎች ላይ ያሰራቸው ጋቢዮኖች በጎርፍ ተንደው ከጥቅም ውጪ ሆነዋል። በዚህ ሳቢያም እንቅስቃሴው ውጤታማ መሆን አልቻለም።

ሶስቱ የመናገሻ ራስ ምታቶች

የመናገሻ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት በከተማዋ የሚገኙት ጋራ መናገሻ፣ አሊያንስ ፍላወር እንዲሁም ኮረቦዳ ተብለው የሚጠሩት አካባቢዎች የአፈር መሸርሸር ችግሩ የጠናባቸው ናቸው ተብለው በጥናት የተለዩ ናቸው። በነዚህ ስፍራዎች ላይ የተሞከሩት የእርከን ስራና የአፈር ጥበቃ መፍትሄዎች በሙሉ ውጤታማ መሆን አልቻሉም።

በጋራ መናገሻ አካባቢ የተሰሩት እርከኖች በውሃ ተጠራርገው በመወሰዳቸው አፈሩን ከመሸርሸርና ከመሸሽ ለማዳን የተደረገው ጥረት አልተሳካም። አካበቢው ደናማ በመሆኑና ዝናብ ስለማያጣው ከተራራው ላይ የሚመጣው ውሃ አፈሩን እየጠረገ ወደተዳፋት አካባቢዎች ይዘልቃል። አቶ ሶፊሳ እንደሚሉት ችግሩ በዚህ ከቀጠለ በተራቆተው መሬት ላይ አፈሩን ለመጠበቅ የተተከሉትን ችግኞች እየጠራረገ መውሰዱ የማይቀር ነው። ይህንን ለማስቀረት በወረዳው ትዕዛዝ አፈሩ በእርከን ተገድቦ በጋቢዮን እንዲታጠር እንቅስቃሴዎች ተጀምረው የነበረ ቢሆንም በከተማው አቅም ወጪውን መሸፈን አልተቻለም። በዚህ ሳቢያ እቅዱ ፈተና ገጥሞታል።

ከኮረቦዳ መንደር ዝቅ ብሎ ወደሚገኘው ኮረቦዳ ወንዝ የሚገባውን የታጠበ አፈር ለመከላከል 10 መኪና ሙሉ ድንጋይ ለአፈር ማገጃ ለማዋል ቢሞከርም ውጤት ማግኘት ግን እንዳልተቻለ ነው ከንቲባው የሚናገሩት። ይህ ቦታ የተፋሰስ ልማት ከሚካሄድባቸው የመናገሻ ከተማ አካባቢዎች አንዱ በመሆኑ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የአፈር ጥበቃ ስራውን ለማጠናከር ጥረት ተደርጓል። ነገር ግን ይህ ለውጥ ተመዘገበ ብሎ ለመናገር በሚያስችል ደረጃ የታየ ለውጥ የለም ይላሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ‘አሊያንስ ፍላወር’ ተብሎ የሚጠራው የአበባ እርሻ በእርሻው መሃል የሚያልፈውን ቦይ ለመዝጋትና የውሃውን መውረጃ አቅጣጫ ለማስቀየስ ብሎ በጎን በኩል በዘፈቀደ የቀደደው ተለዋጭ ቦይ ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት ጎርፉን ወደነዋሪዎች መንደርና እርሻ እንዲገባ በማድረግ ጥፋት እያስከተለ መሆኑን አቶ ሶፊሳ ይናገራሉ። ይባስ ብሎም ውሃው ወደዋናው አውራጎዳና በመግባት አስፓልቱን እያበላሸ በመሆኑ ማዘጋጃ ቤቱ ለድርጅቱ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ባሻገር ለመንገዶች ባለስልጣን እና ለሌሎች የሚመለከታቸው ክፍሎች ጉዳዩን በደብዳቤ ማሳወቁንም ገልጸዋል።

“ያም ሆኖ ድርጅቱ የውሃ መውረጃ ዲሽ ለመገንባት አቅም የለኝም በማለቱ እና የሚመለከታቸው አካላት እስካሁን የወሰዱት ምንም እርምጃ ባለመኖሩ ምክንያት ነዋሪው ከፍተኛ እሮሮ እያሰማ ነው። ግጭት የተፈጠረበት ወቅትም ነበር። በስፍራው ያለውን የአፈር መሸርሸር ጥፋት ለመከላከል ያላስቻለው አንዱ ሰው ሰራሽ ምክንያትም ይኸው ነው” ብለዋል አቶ ሶፊሳ።

እንደአቶ ሶፊሳ ገለጻ በመናገሻ ከተማ ውስጥ በዋናነት ለከባድ የአፈር መሸርሸር በመጋለጥ ለመዘጋጃ ቤቱ ራስ ምታት የሆኑት እነዚህ ሶስት አካባቢዎች ቢሆኑም ከዚህ በፊት ያልተጎዱ አካባቢዎች አሁን የችግሩ ገፈት ቀማሽ እየሆኑ መጥተዋል። ነገሩም ከከተማዋ አቅም በላይ ሆኗል።

“የችግሩ ተጠቂ መናገሻ ብቻ አይደለችም”

የወልመራ ወረዳ የግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግርማ ደሜ የአፈር መሸርሸር ችግር ሃገር አቀፍ ፈተና ነው ይላሉ። “ የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ሃገር አቀፍ የትኩረት መስክ ስለመሆኑ በአምስት ዓመቱ የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ እንደአንድ ተግባር መቀመጡ ምስክር ነው” ይላሉ። “በየአካባቢው የሚተገበሩት የተፋሰስ ልማት፣ የችግኝ ተከላ እና የእርከን ስራ እንቅስቃሴዎች ችግሩን ለመከላከል የተቀየሱ መፍትሄዎች ናቸው። በወልመራ ወረዳ ባሉት 23 ቀበሌዎች በሙሉ መናገሻን ጨምሮ የአፈር መሸርሸር ችግር በብዛት ይታያል። ይህንን ለመከላከል ጋቢዮን ማሰርና እርከን መስራት የመከላከሉ ተግባር አማራጭ መፍትሄዎች ናቸው።” ይላሉ።

“የመናገሻ ከተማ ድጋፍ የሚፈልግ በመሆኑ የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት የባለሙያ ድጋፍ በማድረግና ከአንዳንድ አካባቢዎችም ድጋፍ በማሰባሰብ በቅርቡ በስፋት ጋቢዮን ለማሰር እና የእርከን ስራዎች ተጠናክረው እንዲሄዱ ለማድረግ እንጥራለን። ያም ሆኖ ለአደጋ ከተጋለጠው አፈር አንጻር ችግሩ ሰፊ በመሆኑ የበላይ አካላትን ትኩረትም ይፈልጋል።” ነው የሚሉት አቶ ግርማ።

“ችግሩ ሰው ሰራሽ ነው”

የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግርማ እንደሚናገሩት የመናገሻ አካባቢ አብዛኛው ክፍል በደን የተሸፈነ ነበር። በረጅም ጊዜ ውስጥ ደኑ ተመንጥሮ በመሳሳቱ ምክንያት አፈሩ ለዝናብ ተጋልጧል። ይህም የሚወርደውን ውሃ መቋቋም እንዳይችል በማድረግ እንዲሸረሸር ምክንያት ሆኖበታል። በአካባቢው ያለው የአስተራረስ ዘይቤ እጅግ ኋላ ቀርና በሳይንሳዊ መንገድ ያልተደገፈ በመሆኑ ለአፈሩ መጎዳት እና ለጥፋት መጋለጥ ሌላው ምክንያት ሆኖ ይቀርባል። ለግጦሽ መሬት ተብሎ የሚጨፈጨፈው ደን ስፍራውን ለዝናብ እና ለጎርፍ አደጋዎች ስለሚያጋልጠው ጥፋቱ ይጨምራል።

“እነዚህ ምክንያቶች ህብረተሰቡ ስለአፈር ጥበቃ ካለው ግንዛቤ አናሳነት ጋር ሲደመሩ የሚደርሰውን ውድመት የከፋ ያደርጉታል። ስለሆነም ችግሩ ተፈጥሮ በአካባቢው ላይ ፈርዳ የጣለችው ቅጣት ሳይሆን ሰውሰራሽ ጥፋት ነው። ሰው የሰራውን ጥፋት ሰው ሊመልሰው ስለሚችልም የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮችን በማመቻቸት የአካባቢው አስተዳደር ከህዝቡ ጋር ተረባርቦ ቢያንስ የሚደርሰው ጉዳት ባለበት እንዲቆም ማድረግ ይችላል። ይህንን በተግባር ለመተርጎምም እቅድ ይዘን እየሰራን ነው” ብለዋል ሃላፊው።

አቶ ግርማ በመናገሻ አካባቢ ያለው አፈር ለአደጋ የተጋለጠበት ደረጃ ከፍ ያለ በመሆኑና አደጋው ያንዣበበባቸው አካባቢዎችም ሰፊ ስለሆኑ ለመከላከል ጠንካራ አቅም ይጠይቃል ነው የሚሉት። ከተማው ባለው በጀት፣ ወረዳው ግብርናም በሰው ሃይልና በሙያ ድጋፍ በማድረግ የተጀመሩትን ስራዎችም አጠናክሮ ለመቀጠል ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

ቀሪውን ሃብት ከጥፋት ለማዳን

የአፈር ለምነት መሟጠጥ ለመናገሻ ከተማ “ስጋት” በሚባል ደረጃ ላይ ከደረሰ ሰንብቷል። በዚህ ሳቢያ የሚከሰተው የአፈር ለምነት መቀነስ እና የምርታማነት ማሽቆልቆል ለከተማዋ ብቻ ሳይሆን ለሃገርም ችግር ነው። የከተማዋ ማዘጋጃ ቤትም ሆነ የወረዳው ግብርና ጸህፈት ቤት ከመፍትሄዎቹ አንዱና ዋናው ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር መሆኑ ላይ ይስማማሉ። አሁን ችግሩ እየሰፋ መምጣቱ በራሱ ቀደም ብለው የተሰሩ ስራዎች ጠንካራ አለመሆናቸውን አመላካች ቢሆንም ጊዜው ግን ገና አልረፈደም። የችግሩ ስፋት ከወረዳውም ይሁን ከከተማዋ የበጀት አቅም በላይ መሆኑ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ድጋፍ እንዲያደርግ ግድ ይለዋል። መጪው ጥፋት ለመናገሻ እና ወልመራ አስተዳደር መዋቅሮች ስጋት እንደሆነው ሁሉ ለክልሉም ሆነ ለፌዴራል መንግስትም የትኩረት አቅጣጫ መሆን ይገባዋል።

      የኦሮሚያ ደን ፕሮጀክት እያንዳንዱ ትልቅም ይሁን አነስተኛ እርሻ ከጠቅላላ ይዞታው 5 በመቶ የሚሆነው በተፈጥሮ ደን እንዲሸፈን የሚያስገድድ መመሪያ ማውጣቱ በሰዎች ጥፋት የተራቆተውን ደን መልሶ እንዲያገግምና አፈሩም ከጥፋት እንዲጠበቅ ለማድረግ መልካም እርምጃ ነው። የተተከሉት ዛፎች በቅለው ምግባቸውን ራሳቸው እስኪጠብቁት ድረስ ግን የአፈርን ለምነት ለመጠበቅ እና መሸርሸርን ለመከላከል የሚያግዙ ሌሎች ሳይንሳዊ ዘዴዎች በስራ ላይ መዋል አለባቸው። በተለይ በሌሎች ስፍራዎች እንደሚደረገው ህብረተሰቡን በማስተባበር በተፋሰስ ልማት፣ በእርከን ስራ እንዲሁም በችግኝ ተከላ እና የውሃ መውረጃ ዲሽ ግንባታ ላይ ፈጣን ስራዎችን መስራት ግድ ይላል። እነዚህ ስራዎች ውጤት እንዳያስገኙ ፈተና የሆኑትን ተደጋጋሚ እንቅፋቶች በማጥናትም ሳይንሳዊ መፍትሄዎችን መቀየስ ተገቢ ይሆናል። ይህ ችግር አፋጣኝ ትኩረት ካልተሰጠው በቀር ከጥፋት ተርፈው ዛሬ የአካባቢ ስነምህዳርን በመጠበቅ ላይ ከሚገኙት ደኖች ዋናው የከተመበት ይህ የመናገሻና አካበቢው መሬትበጊዜ ሂደት አፈሩ ታጥቦና ተራቁቶ ምድረበዳ እንዳይሆን ያሰጋል።

 

እዉነትም ተስፋ
    ቦታዉ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ዉስጥ ነዉ። ይህ ቦታ የአካባቢዉ ነዋሪወች የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻወችን የሚጥሉበት፤ ለእይታ አይደለም በተወሰኑ ሜትሮች ርቀት በአካባቢዉ ለመጓዝ የሚታሰብ አልነበረም። ቦታዉ የተለያዩ ወንጀሎች የሚፈፀሙበት እንደነበር ነዋሪወች ያስታዉሳሉ፡
     ዛሬ ላይ ግን እድሜ ለተስፋ እርሻ የጓሮ አትክልት የህብረት ስራ ማህበር አካባቢዉ ተለዉጦ ለእይታ የሚስቡ አረንጓዴ ምርቶች ያሉበትና ለአካባቢዉ ነዋሪዎች እፎይታን የፈጠረ አካባቢ መሆን ችሏል።
     ማህበሩ አካባቢዉን ወደ አረንጓዴነት በመቀየር ያለፉበት ሂደት በጣም ፈታኝ በመሆኑ ሲቋቋሙ ከነበሩት 70 አባላት ዛሬ ድረስ ፀንተዉ የሚገኙት 13ቱ ብቻ ናቸዉ። አባላቱ ስራዉን ሲጀምሩ ለስራቸዉ መነሻ የነበረዉ ካፒታል በነፍስ ወከፍ ያዋጡት 80 ብር ነበር። መነሻ ካፒታላቸዉም 5600 ብር ነበር ማለት ነዉ። በቦታዉ የነበረዉን ቆሻሻ ማስወገድ ደግሞ   ከመዋጮዉ የበለጠ ከባድና ፈታኝ እንደነበር አባላቱ ያስታዉሳሉ።
     በ2001 ዓ.ም ህጋዊ እዉቅና አግኝተዉ የተቋቋሙት ተስፋዎቹ ግን ፈተናዎች እያለፉ ከቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ የሚወጣዉን ፍሳሽ በመጠቀም የመጀመሪያ ምርታቸዉን ለማየት ቢችሉም ገዥ ማግኘት ግን በወቅቱ ሌላዉ አስቸጋሪ ጉዳይ ነበር። ምክንያቱ ደግሞበአካባቢዉ የነበረዉን ቆሻሻ የሚያዉቁ ሰዎች ከዛ ቦታ ላይ የተመረተን አትክልት መጠቀም የሚዋጥላቸዉ አልነበረም።
     ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ ለማለፍ የራሱን ጊዜ የጠየቀ እንደነበር የማህበሩ አባል ወ/ሮ እቴነሽ የማነ እንዲህ ያስታውሱታል። “እኛ እራሳችን አትክልቱን ስንመገብ ያዩ የአካባቢው ነዋሪዎች አመለካከት እየተቀየረ መጣ።” ዛሬ ላይ የአካባቢው ነዋሪወች በ1 ነጥብ 75 ሔክታር መሬት ላይ በተስፋ እርሻ የጓሮ አትክልት ልማት የህ/ስ/ማህበር የሚመረቱ የጎመን፤ የቆስጣ፤ ሰላጣ፤ ጥቅል ጎመን፤ ቀይስር፤ ሸንኮራ አገዳ፤ ካሮት፤ ቲማቲም የድንችና ሽንኩርት ምርቶችን በጥርጣሬ መመልከታቸውን ትተው የማህበሩን ትኩስ የአትክልት ምርቶች ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል። በቦታው አትክልት ሲገዙ ያገኘናቸው ወ/ሮ መቅደስ ተገኘም ይህንኑ ነዉ የሚያረጋግጠት። “አትክልት ለመግዛት ሩቅ ቦታ አንሄድም፤ በዛ ላይ ደግሞ ትኩስ ነዉ። አካባቢዉም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ወደ አረንጓዴነት ተቀይሯል።” አካባቢዉ ወደ አረንጓዴነት የተቀየረዉ በተስፋዎቹ ጥረት መሆኑን የሚናገሩት ወ/ሮ መቅደስ አካባቢዉከዚህም በላይ   ተቀይሮ እንደሚያዩት እምነታቸዉ ከፍተኛ ነዉ።
      የተስፋዎቹ ስራም በቆሻሻ ቦታነት የተፈረጁ ሌሎች አካባቢዎችንም አረንጓዴና የገቢ ምንጭ ማድረግ እንደሚቻል አንድ ማሳያ ነዉ። ካፒታላቸዉንም ወደ 60000.0 ብር ማሳደግ ችለዋል። የማህበሩ አባላት በማሳቸዉ ወደፊት ቋሚ አትክልቶችን በመትከል በጊዜ ሂደት ቦታዉ የመናፈሻ አገልግሎት የሚሰጥበትን ሁኔታ ማመቻቸት የአጭር ጊዜ እቅዳቸዉ ነዉ። ዛሬ ላይ የልፋታቸዉን ያክል እንደማያገኙ የሚገልፁት አባላቱ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸዉ በሂደት እንደሚረጋገጥ እንደ ስማቸዉ ተስፋ ያደርጋሉ። እስከዛዉ ግን የተገኙ ማህበራዊና አካባቢያዊ የጓሮ አትክልት ተጠቃሚጠቀሜታዎችን ይበልጥ እያሳደጉ በተለይም የአካባቢዉ ማህበረሰብ በአካባቢዉ መለወጥ ያገኘዉ ደስታ እነሱም የማህበረሰቡ አካል በመሆናቸዉ የደስታዉ ተጋሪ መሆናቸዉን በማመን ዛሬም የነገ እድገታቸዉን ተስፋ በማድረግ የፆታና የእድሜ ልዩነት ሳይገድባቸዉ በጋራ ይሰራሉ።
 
************************************************************************************************************

 


የዝናብ መምጣት ተከትሎ በማህበሩ አባላት የጉልበት ተሳትፎ የተሰሩ የውሃ መቀልበሻ ግድቦች በአንድ ቀን ዝናብ የሚፈርሱበት ሁኔታ በቀበናና ቡልቡላ አትክልት አምራቾች የህ/ስ/ማህበር ለአብነት መመልከት ችለናል


ተግዳሮቶች                 
     የከተማ ግብርና የስራ እድል በመፍጠር፤ የአካባቢን ገፅታ በመቀየርና ለአካባቢው ነዋሪዎች ትኩስ የአትክልት ምርቶችን በማቅረብ እያበረከተ ያለው አስተዋፅዖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። ዘርፉም ከተማውን ማእከል ያደረገ ፖሊሲና ስትራቴጅ ተቀርፆለት ወደ ስራ መገባቱ የሚበረታታ ነው።
      ይህ ዘርፍ ግን የሚፈለገውን ውጤት ለማስገኘት እንዲቻል ችግሮችን እየለዩ የመፍትሄ አቅጣጫ እያስቀመጡ መሄድን ይጠይቃል። በቦሌና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው በከተማ ግብርና ላይ ከተሰማሩት መካከል በ አምስቱ ቅኝት አድርገን ነበር። ማህበራቱም አሉ የሚሏቸውን ችግሮቻቸውን አንስተዋል።
1.    የግብዓት አቅርቦት
     ምርታማነትን ለማረጋገጥ አስፈላጊ ናቸው ከሚባሉት ግብአቶች መካከል ምርጥ ዘር አንዱ ነው። ምርጥ ዘር በተወሰነ ቦታ ላይ የምርት መጠንን ለማሳደግና የምርት ጊዜን ለማሳጥር ያለው ጠቀሜሚታ ከፍተኛ ነው። ይህ ሲባል ምርጥ ዘር ስለተዘራ በቀላሉ የምርት ጭማሪ ይገኛል ማለት አይደለም። ዘሩ ከመዘራቱ በፊትና ከተዘራ በኃላ ሌሎች አስፈላጊ ክትትሎች ካልተደረጉለት ውጤቱ እንደሚፈለገው አይሆንም። በቦሌና አቃቂ  ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ያነጋገርናቸው ማህበራት በምርጥ ዘር አቅርቦት በኩል ችግሮች እንዳሉ ያነሳሉ። የተሻሉ የዘር አይነቶች ለሁሉም የአትክልት አይነቶች እንደማያገኙ የገለፁት ማህበራቱ በተወሰኑ አትክልቶች የሚቀርቡ ዘሮችም ቢሆን የአቅርቦት ችግር እንዳለ ያነጋገርናቸው ማህበራት ጥያቄ ነው።
2.    ገበያ
      በጓሮ አትክልት ልማት የተሰማሩ ማህበራት የድካማቸውን ዋጋ ከነሱ ይልቅ ደላሎች እንደሚጠቀሙበት ያነሳሉ። ገበያውን የሚሰቅሉትም የሚያወርዱትም ደላሎች መሆናቸውን የገለፁት ማህበራቱ አሁን አሁን ደላላ ከሚበላው መሬት ይብላው እያሉ ምርቱን ከማሳው ላይ እያለ ለነጋዴ መሸጥ እንደጀመሩ እንደ መካነ ብሩህ ያሉ ማህበራት ያወሳሉ።
     የመሸጫ ቦታ በማእከል ደረጃ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም ማግኘት ስላልቻሉ አማራጭ የሌላቸው ማህበሮች በደላሎች አማካኝነት የድካማቸውን ዋጋ ሳይሆን እንጥፍጣፊ እየቀመሱ ይገኛሉ። አትክልት በባህሪው ቶሎ የሚበላሽ መሆኑ ደግሞ አንዳንዴ ባዶ እጃቸውን የሚመለሱበት አጋጣሚ እንዳለ ማህበራቱ ያነሳሉ።
3.    የባለሙያ ድጋፍ
     የግብርና ስራ - አይደለም በከተማ በገጠርም የባለሙያ ድጋፍ ያስፈልገዋል። ለዚህም ነው በእያንዳንዱ የገጠር ቀበሌ ሶስት የግብርና ባለሙያዎች የሚመደቡት። በከተማ የሚሰሩ የግብርና ስራዎች በመጠናቸው አነስተኛ ቢሆኑም የባለሙያ ድጋፍ ግን ይሻሉ። ድጋፉን ደግሞ ከገጠሩ ማህበረሰብ በተሻለ በቀላሉ ወደ ተግባር የመለወጥ እድሉ በከተማ ከፍተኛ ነው። በቦሌና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በከተማ ግብርና የተሰማሩ ማህበራት ከባለሙያዎች የሚያገኙት ድጋፍ ግን ጉራማይሌ ነው። አንዳንድ ቦታዎች ባለሙያ እንደተመደበ ቢያውቁም የባለሙያው ድጋፍ ግን በቀናት እንኳን ያልታየበት እንደ ተስፋ እርሻ የጓሮ አትክልት የህ/ስ/ማህበር አይነት አለ። በሌሎች ደግሞ ለግብረ ይውጣ በሳምንት አንዴ ሪፖርት ለመልቀም ብቻ የሚመጡ ባለሙያዎች እንዳሉ ማህበራቱ ያነሳሉ። ይህ ሲባል በአንፃሩ የተሻለ ድጋፍ የሚያደርጉ ባለሙያዎች የሉም ለማለት ሳይሆን በአብዛኛው ግን ድጋፉ አነስተኛና ለአንዳንድ ማህበራት ደግሞ ከናካቴው የሌለ በመሆኑ ክፍለ ከተማዎቹ አስፈላጊውን እርምጃ ሊወስዱ ይገባል።
4.    ጎርፍ
     የዝናብን መምጣት ተከትሎ በማህበሩ አባላት የጉልበት ተሳትፎ የተሰሩ የውሃ መቀልበሻ ግድቦች  በአንድ ቀን ዝናብ የሚፈርሱበት ሁኔታ እንዳለ በቀበናና ቡልቡላ አትክልት አምራቾች የህ/ስ/ማህበር ለአብነት መመልከት ችለናል። በሌላ መልኩ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በምርቶቻቸው ላይ የሚፈጠረው ጥፋት ከፍተኛ ነው። በአጠቃላይ እነዚህ ችግሮች ካልተፈቱ የማህበራትን ህልውና የሚፈታተኑና ወደዚህ ዘርፍ ለመግባት ፍላጎት ያሳዩ ግለሰቦችና የተደራጁ አካላትን የሚያርቅ በመሆኑ መፍትሄ ያሻዋል።

 

 

 

      ይህ ጽሑፍ ፎረም ፎር ኢንቫይሮመንት ከሌሎች ስድስት መያዶች እና ከአካባቢና ደን ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የቀረበ ነው፡፡     ጥቂት እፍታ - ስለ “አቃቂ የአረንጓዴ
ዳርቻ” ግንባታ!
    

 

      በአቃቂ ወንዝ ተፋሰስ የሚተገበረው “ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ዞን ግንባታ” ፕሮግራም በዘላቂ ልማት መካነ ጥናት አስተባባሪነት በሰባት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ ከአካባቢና ደን ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እየተተገበረ የሚገኝ ፕሮጀክት ነው።
     ፕሮጀክቱ በቦሌ፣ በአቃቂ ቃሊቲ፣ በኮልፌ ቀራኒዮ እና በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተሞች በከተማ ግብርና በተለይም በጓሮ አትክልት ማምረት በተሰማሩ ማህበራት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ዞን ግንባታን ለመፍጠር እንዲቻል በማለም የተጀመረ ሲሆን ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ በምታደርገው ጉዞ የአረንጓዴ ልማትን በማሳደግ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ ተግባር ለመፈፀም ግብ አስቀምጧል።
    ፕሮጀክቱ ልምዶችን ለመቀመርና ለማስፋፋት የተለያዩ ድጋችንና ስልጠናዎችን ለማህበራቱ አባላት ይሰጣል። የተጎዱ አካባቢዎች አገግመው የገቢ ምንጭ የሚሆኑበትን ብሎም ተሞክሮዎች እንዲስፋፉ ለማህበራቱ ድጋና ክትትል የሚያደርጉ ባለሙያዎችን ያሰልጥናል፤ አደረጃጀቶችንና አሰራሮችንም ያስተዋውቃል።
    ለዚህ ፕሮጀክት ስኬትም ISD, APAP, FfE, OSD, PAN-ETHIOPIA, TKM እና MEF በዘላቂ ልማት መካነ ጥናት አስተባባሪነት ድጋፍና ትብብር ያደርጋሉ።

 


 

 

******     *********      *********

 

 

 

     አቶ መንገሻ ዳኜ በዘላቂ ልማት መካነ ጥናት ባልደረባና “ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ዞን ግንባታ በአቃቂ ወንዝ ዳርቻ” ሲኒየር ኮሙዩኒቲ ፋሲሊቴተር ናቸው። በፕሮጀክቱ ጅማሮ፣ ዓላማ፣ አተገባበርና ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ አነጋረናቸዋል።

 

     ለፕሮጀክቱ በመነሻነት የተያዘው ዓላማ ምንድን ነው?
    ለአጀማመሩ መነሻው በኢትዮጵያ የተጀመረው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ነው። ኢትዮጵያ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ ስታቅድ ኢኮኖሚውን ከበካይ ጋዝ ልቀት በፀዳ መልኩ ለመተግበር ራዕይ አስቀምጣ እየተንቀሳቀሰች ነው። ከ2011 ጀምሮም ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል። በዚህ ዓላማ መሰረትም የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት በመቀነስ ያሰብንበት እንደርሳለን ተብሎ በተቀመጠው ግብ መሰረት ይህንን ፖሊሲ ተከትሎ ከ26 በላይ ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ ይገኛሉ። ይህ ‹‹ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ዞን ግንባታ በአቃቂ ወንዝ ዳርቻ›› ፕሮጀክትም አንዱ የሙከራ ፕሮጀክት ነው። ለ15 ወራት የሚቆይ ፕሮጀክት ነው።

 


     ከፕሮጀክቱ ምን ውጤት ይጠበቃል፤ እስካሁን የተሰሩ ስራዎችስ ምን ምን ናቸው?
     የሙቀት አማቂ ጋዞችን በመቀነስ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ዞን ግንባታ ፕሮጀክት አምስት ያህል ውጤቶች እንዲያመጣ ታስቦ እየተተገበረ ነው። የመጀመሪያው ወደ 20 ለሚጠጉና በስራ ላይ ላሉ በአቃቂ ወንዝ ዙሪያ የጓሮ አትክልት በማልማት ስራ ላይ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞችን አሰራር ማሻሻልና መቀየር ነው። ሁለተኛው ውጤት ይህ ፕሮጀክት በሚተገበርበት ወቅት ድጋፍና ክትትል የሚያደርጉ የህብረተሰብ ክፍሎችንና የመንግስት አካላት ተውጣጥተው የተቋቋሙ ሁለት ኮሚቴዎች አሉ። የማስተባበርና የማቀናጀት ስራ የሚሰሩና የእነዚህን ኮሚቴዎች አቅም አጎልብተን የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉ ማብቃት ነው። እነዚህ ኮሚቴዎች እያንዳንዳቸው 15 አባላት አሏቸው። በሶስተኛነት የተቀመጠው ግብ ላይ ሶስት ንዑሳን ግቦች አሉ። አንደኛው የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድና አያያዝ የተሸሻለ እንዲሆን ማስቻል፤ ሁለተኛው የፍሳሽ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ እንዲሻሻል ማስቻል እና ሶስተኛው ሀይል ቆጣቢ ምድጃዎችን ማዳረስ ናቸው። እስካሁን ከ80 በላይ ለሚሆኑ ገቢያቸው አነስተኛ ለሆኑ ቤተሰቦች ምርጥ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን አድለናል። ሌላውና በአራተኛነት የሚጠበቅ ውጤት በአቃቂ ወንዝ ዳርቻ የተጎዱ ቦታዎችን እንዲያገግሙ በማስቻል በእነዚህ ቦታዎች እየሰሩ ላሉ ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች እንዲጠቀሙባቸው ማድረግ ነው። የመጨረሻውና አምስተኛው ውጤት ልምዶችንና ተሞክሮዎችን ማስፋፋትና ማዳረስ ነው። ለዚህ ይረዳ ዘንድም ስትራቴጅ ተቀርፆ እየተሰራበት ይገኛል። በየሶስት ወሩ ዜና መፅሄት እየታተመ ነው። በየሶስት ወሩም የሬዲዮ ፕሮግራም እየተዘጋጀ ይገኛል። በጓሮ አትክልት አልሚዎች መካከል የልምድ ልውውጥ እንዲካሄድም ተደርጓል። ህብረሰተብ አሳታፊ ውይይቶችና ግምገማዎችም ተካሂደዋል።

 


     እስካሁን ያለው አፈፃፀም ምን ይመስላል?
     የአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚሰራ ስራ ውጤት በአንዴ ተጨባጭ ለውጥ የሚታይበት አይደለም። ጊዜ ይፈልጋል። ነገር ግን በአቃቂ ወንዝ ተፋሰስ ዙሪያ የሚሰሩት የጓሮ አትክልት አልሚ ማህበራትና ኢንተርፕራይዞች ምንም ግንዛቤ በጉዳዩ ላይ አልነበራቸውም። አሁን ግን በሰጠናቸው ስልጠና መሻሻል አሳይተዋል። እስካሁን ከእያንዳንዱ ማህበር ለተውጣጡ 10 አባላት በድምሩ ለ200 ሰዎች ስልጠና ሰጥተናል። በዚህም የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክቶ ግንዛቤ አግኝተዋል ብለን እናምናለን። ከልማዳዊ አመራረት ተላቀው ዘመናዊ አሰራር የተከተሉትም ብዙዎች ናቸው። ማዳበሪያ ገዝተው ይጠቀሙ የነበሩ አሁን ኮምፖስት ወይም የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅተው መጠቀም ጀምረዋል። ፀረ ተባይና ፀረ አረም ኬሚካሎችን መጠቀም አቁመዋል። በአቃቂ ወንዝ ዳርቻ ችግኞችን ተክለው ከጎርፍ መጥለቅለቅና ከአፈር መሸርሸር ለመታደግ ጥረት እያደረጉም ነው። ይሁንና ለውጡ የበለጠ የሚጎለብት ሊሆን ይገባል። በምናየው መሻሻል ግን አፈፃፀሙ ጥሩ ነው ማለት ይቻላል። 

 


     ተዟዙረን ያነጋገርናቸው ማህበራት የመሸጫ ቦታ፣ የግብዓት አቅርቦት፣ የባለሙያ ድጋፍና ክትትል እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ያነሳሉ። ይህ ስልጠናው ያመጣውን ለውጥ በዘላቂነት እንዳይተገበር እንቅፋት አይሆንም?
     በዚህ ፕሮጀክት የሚሰሩ ስራዎች ብዙ ናቸው። ከስልጠናዎች በተጓዳኝ የሚደረጉ ድጋፎች አሉ። ሰልጠናዎችም በአረንጓዴ አመራረት፣ በገንዘብ አያያዝ፣ በገበያ ትስስርና ስለ አስተዳደርም ያተኮረ ስልጠና ነው የተሰጣቸው። ሌሎች የሚደረጉ ድጋፎችን ስናይ ደግሞ ለኢንተርፕራይዞች ጊዜያዊ ግንባታ ለማከናወን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገርን ነው። በቅርቡ የቆርቆሮ ሱቆች ተሰርተውላቸው የመሸጫም የመሰብሰቢያ ቢሮም አድርገው ይገለገሉባቸዋል። የምርጥ ዘር አቅርቦትም እናከናውናለን። የመስሪያ መሳሪያዎች እና የስራ አልባሳት ድጋፍም ይደረግላቸዋል። የቢዝነስ ፕላን እንዲያቀርቡ በማድረግም ለእያንዳንዱ ኢንተርፕራይዝ የ30 ሺህ ብር ድጋፍ ይደረጋል። እነዚህ ድጋፎች ለሁሉም ተራ በተራ የሚደረጉ ይሆናል። በተለይ ከገበያ ትስስር ጋር ያለውን ችግር ትኩረት ሰጥተን እየሰራንበት ነው። ፕሮጀክቱ ባቀፋቸው የኮልፌ ቀራኒዮ፣ ቦሌ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማዎች ቢያንስ ለሁሉም ኢንተርፕራይዞች በአማካይ በሚገኝ ቦታ ሁለት የጓሮ አትክልት መሸጫ ሱቅ ለመገንባት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንሰራለን።

 

     እስካሁን ባለው አፈፃፀም ያጋጠሙ ችግሮች ምንድን ናቸው?
     እስካሁን ባለው አፈፃፀም ከተለያዩ ከሚመለከታው የመንግስት ቢሮዎች ጋር ተባብረን በመስራታችን የተጋነነ ችግር አላጋጠመንም። ጥሩ በሚባል አፈፃፀም ላይ ነው ያለው። ግን በችግር ደረጃ የምናነሳው በአቃቂ ተፋሰስ ካሉ ቦታዎች እንዲያገግሙ ሆነው ለጥቅም ይውሉ ዘንድ በአካባቢው ላሉ ኢንተርፕራይዞች ለማስረከብ ያስቀመጥነውን እቅድ ለማሳካት ከመሬት ጋር የተያያዘው አሰራር አልተቃለለንም። ይህም በቅርቡ ተፈትቶ በቀሪ የፕሮጀክቱ መፈፀሚያ ጊዜ እንደምናሳካው አምናለሁ።

 

     የአየር ንብረት ለውጥ የረጅም ጊዜ ውጤት በመሆኑ የፕሮጀክቱ ዘላቂነት እስከምን ድረስ ይሆናል?
     የዚህ ፕሮጀክት የአሁን ዕቅዱ የ15 ወር ነው። ይህ ማለት ግን ስራ ይቆማል ማለት አይደለም። ያቋቋምናቸው ሁለቱ የእስትሪንግ ኮሚቴዎች ድጋፍና ቁጥጥር እንዲያደርጉ አስፈላጊው ስልጠና ሁሉ እየተሰጣቸው ነው። አብዛኞቹ አባላት ከመንግሰት መዋቅር ጋር የተቆራኙ በመሆናቸው ዘላቂነቱ ላይ ስጋት አይኖረውም። ምክንያቱም እነዚህ ኮሚቴዎች ከስራዎቻቸው ጋር የተጣመረ ፕሮጀክት በመሆኑ የመንግስት ድጋፍና ክትትል በማይለየው መልኩ እንዲጠናቀቅ ታስቦ ነው የተጀመረው። ይህም ይሳካል ብለን እናምናለን።

 

ፎረም ፎር ኢንቫይሮመንት
ፖ.ሣ.ቁ 10386
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
ስልክ 251-115-521-662/115-521-015
Fax! - 251-115 521 034
www.ffe-ethiopia.org
Email - This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Page 1 of 4

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 177 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us