ኃይል ቆጣቢ የባዮማስ ምንጮች እንዲጎለብቱ

Wednesday, 25 June 2014 13:28

በሀገራችን እ.ኤ.አ. በ2025 ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል ዕቅድ በመንግሥት ተዘጋጅቶ እየተተገበረ ይገኛል። የአካባቢ ጥበቃ ስራን ከማከናወን ጎን ለጎን በፔትሮኬሚካል የሚሰሩ በካይ የኃይል ምንጮችን በታዳሽ ባዮማስ ምንጭ መተካቱ አንደኛው ነው። ለባዩማስ ሃይል ምንጭ መገንቢያ የእርሻ ተረፈ ምርቶች በሀገራችን ቢገኙም እምብዛም ጥቅም ላይ አልዋሉም። ከእነርሱ ውስጥ የቡና ገለባ፣ የጥጥ ድማጭ ተረፈ ምርት፣ የስንዴ የጤፍና የሌሎች የጥራጥሬ ገለባዎች የሚጠቀሱ ሲሆን በተለምዶ ኤሌፋንት ግራስ ወይም የብስና ተክል (የውስጥ ሸንኮራ) ለዚህ የኃይል ምንጭነት ሊያገለግል እንደሚችል በጥናት ተረጋግጦ አንዳንድ ኩባንያዎችም የተክሉን ግንድ በመከታተፍ ወደ ድንጋይ ከሰል መሰል ምርት በመቀየር በካዩን የድንጋይ ከሰልን ለሚጠቀሙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በኃይል ምንጭ አጋዥነት እንዲያገለግል ለማምራት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።

ከሰሞኑ “በኢነርጂ ዙሪያ እንነጋገር” ተብሎ በሚታወቀውና በፎረም ፎር ኢንቫይሮንሜንትና በአጋር ድርጅቶች በሚዘጋጀው ውይይት ላይ በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ክላይሜት ኢኖቬሽን ማዕከል በዘርፉ ለተሰማሩ ኩባንያዎች ዕውቅና የመስጠትና የማበረታቻ ሽልማት ባዘጋጀው ውድድር ከተመረጡት ውስጥ አልፋሶል ሞደላር ኢነርጂ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የፕሮጀክቱን አተገባበርና የምርቱን አቅርቦት በተመለከተ ጥናታዊ ፅሁፉን ለተሰብሳቢዎች አቅርቧል።

የኩባንያው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ነብዩ አሰፋ በዕለቱ እንደተናገሩት የብሳና ተክል በምዕራብ ኢትዮጵያ በተፈጥሮአዊና በተትረፈረፈ ሁኔታ በተለይ በጋምቤላ ክልል ይበቅላል። ይህ በ2 ሚሊዮን ካሬ ስኩዌር ሜትር ላይ በቅሎ የሚገኘው ሳር በጥቅም ላይ አልዋለም። በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ከፊል አርብቶ አደሮች እንደመሆናቸው ለተክሉ እምብዛም ትኩረት ስለማይሰጡት በየዓመቱ በተፈጥሮአዊ ሰደድ እሳት እየተቃጠለ ይወድማል። በዚህም ሳቢያ ከፍተኛ መጠን ያለው በካይ የካርበን ዳይኦክሳይድ ጋዝን ወደ ከባቢ አየር ይለቃል። በዚህም በአካባቢው ያሉ እፅዋት እንስሳና ሰዎች ለጉዳት ይጋለጣሉ። ስለሆነም ይህን የተፈጥሮ የሳር ምርት በጥንቃቄ እየተንከባከቡ ለኃይል ምንጭነት በከሰል መልክ ለፋብሪካዎች ማቅረብ በመጀመሪያ የአካባቢው ስነምህዳር ሳይዛነፍ የተጠበቀ እንዲሆን የሚያደርግ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃም በካይጋዝን የሚያመነጩ የኢነርጂ ምንጮችን በመተካት ያገለግላል። ይህ ምንም ያልተነካና በገፍ የሚገኝ ሀብት በአካባቢው ያለ አንዳች ወጭ በቀላሉ ይገኛል። በዚያው ቦታ ወፍጮ መሰል ማሽን ተተክሎ ምርቱን ማምረት ይቻላል። ተቀጣጣይነቱ በጣም ውጤታማና ኃይል ቆጣቢ ሲሆን ለትራንስፖርት ለሚያገለግሉ ሞተሮች የአውቶማቲክ ማሞቂያ ስርዓት ለሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ለኃይል ሰጭነት አስተማማኝ ነው። በተፈጥሮ ከሚገኘው የብሰና ተክል ጥቅም ጋር ሲወዳደርም ለአያያዝና ከቦታ ቦታ ለመውሰድ እጅግ የቀለለ ሲሆን የድንጋይ ከሰልን ለሚጠቀሙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ደግሞ ተቀጣጣይነቱ ከድንጋይ ከሰሉ በጣም የላቀ ነው።

የኢነርጂ የይዘት መጠኑ 19GJ/ton ሲሆን ዲንሲቲው 600 ኩዩቢክ ኪሎ ግራም ነው። የኩባንያው ስራ አስኪያጅ አቶ ነብዩ አክለው እንደሚገልጹት በተጨባጭ እንደሚታየው የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከውጭ ሀገር ገዝተው የሚያስገቡት የድንጋይ ከሰል የካሎሪው መጠን ከፍተኛ ቢሆንም በሀገር ውስጥ ሊመረት ስለማይችል የውጭ ምንዛሪ እያስወጣ ይገኛል። ስለሆነም በኩባንያው የሚመረተው አቀጣጣይ ምርት ከውጭ ከሚገባው ድንጋይ ከሰል ጋር በመሆን ለኃይል ማንቀሳቀስ ተግባር በመዋል የውጭ ምንዛሪን ከማዳን ጎን ለጎን ብክለትን ከመቀነስ አንጻር የበኩሉን ሚና ይጫወታል።

እንደሚታወቀው የሀገራችን አረንጓዴ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ከካርበን የፀዳ ታዳሽ ኢነርጂ የመጠቀም መርህን የሚከተል ነው። ታዳሽ ኃይሉም ከወጪ አንፃር ሲታይ በሀገር ውስጥ ስለሚመረት ዋጋው አዋጭና ቀላል ከመሆኑም በላይ የውጭ ምንዛሪን ያድናል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በርካቶች ቀላልና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ በመገኘታቸውና የኃይል ምንጫቸው ታዳሽ አለመሆን እቅዱን ለማሳካት ፈታኝ የሚሆን ነው። በተለይ ለኮንስትራክሽን ዘርፉም ሆነ ለኢንዱስትሪዎች መስፋፋት እንደ ጀርባ አጥንት እያገለገለ የሚገኘው የሲሚንቶ ፋብሪካ የሚጠቀመው እጅግ በካይ የሆነውንና የአውሮፓ ኢንዱስትሪዎች የሚጠቀሙትን ድንጋይ ከሰል መሆኑ ከወዲሁ በአማራጭ ኢነርጂ እንዲተካ ማድረግ የመጭውን ጊዜ ፈተና ከወዲሀ ማቃለል የሚያስችል ነው።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት መረጃ እንደሚያመለክተው የሀገራችን የኢንዱስትሪ አማካይ አመታዊ እድገት 20 በመቶ ይሆናል። ከፍተኛው የሙቀት አማቂ ጋዞች ለቃቂ ከሆነው ከሲሚንቶ ፋብሪካ የሚወጣው ልቀት በ2002 ከነበረው የ2.7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን መጠን በ2007 ወደ 27 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በ2022 ደግሞ ወደ 65 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እንደሚያድግ ይጠበቃል። ከኢኮኖሚ ዘርፎች ሁሉ ከፍተኛ የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት የእድገት መጠን እያሳየ ያለው ይኸው የሲሚንቶ ፋብሪካ ነው። በአሁኑ ወቅት በየዓመቱ በአማካይ የልቀት መጠኑ 18 በመቶ ሲሆን ወደፊት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ሲያድግ የዚያኑ ያህል ችግሩ እየተወሳሰበ ስለሚሄድ ከወዲሁ የታዳሽ ኃይል ምንጮችን በሀገር ውስጥ ተረፈ ምርቶችና የተፈጥሮ ሀብቶች እንዲገኝ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

የአልፋ ሶል ሞደለር ኢነርጂ ኩባንያ አንዱ ዓላማ ይህንን ክፍተት ለመድፈንና የውጭ ምንዛሪን ማዳን ነው። ከዚህ አኳያ የኩባንያው ዋንኛ አላማ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከብሳና ሳር የሚገኘውን ምርት ማቅረብ እንደመሆኑ በሀገር ውስጥ ያለው የገበያ ሁኔታ ምን እንደሚመስል የተጠየቁት አቶ ነብዩ አሰፋ ሲመልሱ የምርቱን ተፈላጊነት አጥንተው ከፋብሪካዎችም ጋር ተዋውለው ወደ ምርት ስራ እንደሚገቡ ጠቅሰው ከዚሁ ጋር አንዳንድ ቴክኒካዊ ስራዎች የሚሰሩ ሲሆን ምርቶችን ወስደው በፋብሪካው ይሞከራሉ። በምን ያህል ጊዜ ጥቅም ላይ ውሎ አዲስ ምርት መቼ እንደሚያስፈልግ የሚለውን ይፈትሻሉ። በርግጥ የሚመረተው ብሪቲክ (የድንጋይ ከሰል መሳዩ ምርት) ሙሉ በሙሉ የድንጋይ ከሰሉን አይተካም። የማሞቅ ኃይሉ ከፍተኛ ሲሆን ውጤታማና ጢስ አልባ ነው። እስከ 20 በመቶ የሚሆነውን የፋብሪካውን ፍላጎት የሚያስችል ነው። ይህም በራሱ እንደ ትልቅ እርምጃ የሚታይ ነው። እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ ሌሎች በቀጣይ የሚሰሩ ስራዎች ያሉ ሲሆን ከጀርመን ኩባንያዎች ጋር የቴክኖሎጂ ልውውጥና የልምድ መቅሰም መርሃ ግብሮች አሉ። ከጃፓኖች ጋርም ተመሳሳይ የሆኑ ትብብር ይደረጋል ምርቱ ሃይለኛ ተቀጣጣይ እንደመሆኑ ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች በተጨማሪ ለብረት ማቅለጫ ኢንዱስትሪዎች ጥቅም ላይ መዋል ይቻላል። በአሁኑ ወቅት በበርካታ የአለም አካባቢዎች በተለይ በህንድና በቻይና የዚህ መሰሉ የባዮማስ ኢነርጂ በስፋት ስራ ላይ የዋለ ሲሆን ከብስና ሳር በሀገራችን የሚመረተው ምርትም በቀጥታ የአሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንደሚያስችል አቶ ነብዩ አስረድተዋል።

አክለውም በመጀመሪያ ይህን ያልተነካ የሀገር ውስጥ ሀብት ጥቅም ላይ ማዋል ባህል ካዳበረ የሀገር ውስጥ ቴክኖሎጂ በሒደት እንደሚዳብር ጠቅሰዋል። በአሁኑ ወቅት ኩባንያው ምርቱን ለመጀመር የተዘጋጀ ሲሆን የማምረቻው ማሽን ግን ከውጭ ሀገር የሚገባ ነው። ከዚህ አንጻር የውጭ ምንዛሪ በማዳኑ አላማ ላይ ይህ ሁኔታ አሉታዊ ተፅዕኖ አይኖረውምን ተብለው የተጠየቁት አቶ ነብዩ ሲገልፁ ከውጭ የሚገባው ማሽነሪ እምብዛም የተወሳሰበ እንዳልሆነ ጠቅሰው ለጊዜው ከውጭ ቢገቡም በሂደት እዚሁ ማምረት እንደሚቻል አሁንም አንዳንድ የማሽኑ አካላት በሀገር ውስጥ ሊመረቱ እንደሚችሉ ከውጭ የሚመጣውንም አስመስሎ በመስራት መተካት እንደሚቻል ገልፀዋል።

ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከረው የብሳና ሳር በጋምቤላ ክልል በተትረፈረፈ ሁኔታ ይገኛል። የሚቋቋመው የኃይል ምንጨ ፋብሪካ ሳሩን በራሱ በማምረት ወይንምስ ከአካባቢው አርብቶ አደሮች በመግዛት ይጠቀም እንደሆነ የተጠየቁት ስራአስኪያጁ ሲመልሱ ሳሩ በተለያዩ መልኩ እንደሚገኝ ጠቅሰው አንዳንድ ቦታ እጅብ ብሎ ሲገኝ ሌላ ቦታ ደግሞ ዘርዘር ብሎ የሚገኝ ነው። ስለሆነም የማምረቻው መሳሪያ ሲተከል ግብአቱ በቀጣይነትና በአስተማማኝ መልኩ እንዲያገኙ በተወሰነ ቦታ ኩባንያው የሚያለማው የእርሻ መሬት እንደሚኖር ጠቅሰው ከዚሁ ጎን ለጎንም የአካባቢው ነዋሪዎች ራሳቸው አምርተውም ሆነ በተፈጥሮ በአረም መልክ የሚበቅለውን ሰብስበው እንዲመጡ በማድረግና ለዚያም ክፍያ በመፈፀም ተጠቃሚ እንደሚያደርጓቸው አስረድተዋል። እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ በአሁኑ ወቅት የብሳና ሳሩን እንደ ልብ ማግኘት እንዲችሉ የክልሉ መንግስት ለ16 ወረዳ ጽህፈት ቤቶች የትብብር ደብዳቤ ፅፎላቸዋል። የኩባንያው አንዱ አላማም ለአካባቢው ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠር ነው። ልማቱም ህዝቡን ያማከለ ሲሆን ህዝቡም ልማቱን ይፈልገዋል። በሌላም በኩል የጋምቤላ መሬት ለጥ ያለ በመሆኑ አንዳንዴ ምርቱን የመሰብሰቡ ሂደት ሜካናይዝድ ሊሆን ይችላል። የአካባቢው ነዋሪ ህዝብ ቁጥር አነስተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ ከቦታ ቦታ ተዘዋዋሪ እንደመሆኑ ስራው ሲስፋፋ ለአካባቢው ነዋሪ የሚሰጠው የስራ እድልም የዚያኑ ያህል ይጨምራል።

እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት በጋምቤላ አካባቢ በርካታ የውጭና የሀገር ውስጥ የአግሮቢዝነስ ኩባንያዎች ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ተሰጥቷቸው ወደስራ የገቡ ሲሆን በዚህ ሳቢያም ከቀያቸው መፈናቀል የገጠማቸው ወገኖች አሉ። ይህን ድርጊት በመቃወም በአለም አቀፍ መድረክ ትችት እየቀረበ ሲሆን በአንዳንድ ኩባንያ ሰራተኞች ላይም በተጠቃሚዎች የኃይል ጥቃት እንደተፈፀመ የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ከዚህ አንፃር ለኩባንያው የስጋት ምንጮች ይሆናሉ ተብለው የሚገመቱ ጉዳዮች እንዳሉ የተጠየቁት ስራ አስኪያጁ ሲመልሱ ኩባንያው ስራውን የሚሰራው በአካባቢ በሚገኝ ከዚህ ቀደም ጥቅም ላይ ውሎ በማያውቅ ይልቁንም በመቃጠሉ ምክንያት ለአካባቢው ሰው እንሰሳና እፅዋት ጠንቅ በሚሆን የብሳና ሳር በመሆኑ ለአካባቢው ህብረተሰብ ጥቅም እንዲውል ብዙም ስጋት እንደማይኖር ጠቅሰው፤ ይህን ሁኔታም ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር እንደመከሩበት አመልክተዋል። አያይዘውም ህብረተሰቡ የሚፈጠረው የስራ እድል ህይወቱን ሊቀይር እንደሚችል ስለተረዳ አስጊ ሁኔታ እንደሌለ ተናግረዋል።

     በሌላም በኩል በየትኛውም አካባቢ የሚገኝ የደንም ሆነ የዕፅዋት ሽፋን አፈርን ከመሸርሸር በመጠበቅ ንፁህ አየርን ከመለገስና ካርቦን በመምጠጥ በኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከማድረግ በተጨማሪ የመሬት ስር (Understound) ውሃን በመቋጠር የአካባቢ ርጥበት እንዲጠበቅም ሆነ በውሃ ምንጭነት በመሆን ያገለግላል። የብሳና ሳርም የዚህ መሰሉን ጥቅም እንደሚሰጥ ይታወቃል። ስለሆነም በሚቆረጥበት ወቅት አካባቢው ለመራቆትና ለስነ ምህዳር መዛባት ሊጋለጥ አይችልምን ተብለው የተጠየቁት ስራ አስኪያጅ ይህ በተመለከተ ሲገልፁ ሳሩ ሙሉ በሙሉ ከስሩ ከመሬት እንደማይነቀል ጠቅሰው ከወገቡ ላይ ተቆርጦ ከታች ከነስሩ መሬት ውስጥ ስለሚቀር የመሬት ስር ውሃ እንደማይጎዳና የአፈር መሸርሸር ችግርም እንደማያስከትል ተናግረዋል። አክለውም ሳሩ ብዙም ሳይቆይ ስለሚያቆጠቁጥና ስለሚያድግ ችግር አይፈጥርም። እንደ እርሳቸው ገለፃ ሳሩ ቀድሞ በነረበረበት ሁኔታ በአካባቢው ህብረተሰብና በሰደድ እሳት ሲቃጠል የአካባቢ መራቆት ሊከተልና የመሬት ስር ውሃም ሊደርቅ ይችል ነበር። ሆኖም ግን ኩባንያው በዚህ ስራ ላይ ሲሰማራ ቃጠሎው ሙሉ በሙሉ ስለሚገታ ስነምህዳርም አይዛባም። ፋብሪካው ሰራ ሲጀምር ለ16 ቋሚና ለ100 ሰዎች ጊዜያዊ የስራ እድል እንደሚፈጥር ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1410 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 924 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us