የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችል፤ ነገር ግን ትኩረት የተነፈገው የፈጠራ ስራ

Thursday, 03 July 2014 12:41

በአሁኑ ወቅት በአየር ንብረት ለውጥና በሙቀት መጨመር ሳቢያ በሰው ልጅ ህይወት ላይ እያደረሰ ያለው ጫና ከሙያተኞች አልፎ ተራ ሰዎችን ጭምር እያሳሰበ ይገኛል። ሀገሮች በተባበሩት መንግሥታት አማካኝነት ከእ.ኤ.አ ከ1472 ጀምሮ እየተሰበሰቡ ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት ቢያደርጉም የጋራ ስምምነት ላይ ለመድረስ አልቻሉም። ለዚህም በምክንያትነት የሚጠቀሰው የሀገራቱ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ፍላጎቶች እጅግ የተራራቁ በመሆናቸው በተለይም ባለኢንዱስትሪዎቹ ወደ ከባቢ አየር የሚለቁትን በካይ ጋዝን በተገቢው ለመቀነስ ቁርጠኝነት ባለማሳየታቸው ነው። የኢነርጂ ምንጫቸው በካዩና የፔትሮኬሚካል ውጤት በመሆኑ ችግሩ ተባብሶ ቀጥሏል። ይህን የሃይል ምንጭ በታዳሽ ሃይል ለመቀየር አጠቃላይ ስምምነት ቢኖርም ወደ ተግባር የማሸጋገሩ ጉዳይ ገና ረጅም ጊዜን የሚጠይቅ ይመስላል። በሌላም በኩል አሁን ወደ እድገት ማማ እየወጡ ያሉትና በህዝብ ብዛታቸው ከዓለም ቀዳሚውን ስፍራ የያዙት እንደ ቻይና እና ህንድ የመሳሰሉት ወደ ከባቢ አየር የሚለቁት በካይ ጋዝ ከህዝባቸው የነፍስ ወከፍ የብክለት አስተዋፅኦ ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ስለሆነ “ልማታችንን ለማፋጠንና ከድህነት ለመውጣት የጀመርነውን ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን” በሚል የብክለት ቅነሳ ዓለም አቀፍ ድርድሮች እንዲጨናገፉ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። እንዲያም ሆኖ “አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ” እንዲሉ ደሃ ሀገሮች ምንም ለብክለት አስተዋፅኦ ሳያደርጉ በዓለም በተከሰተው የሙቀት መጨመር ሳቢያ የእርሻ ምርታቸው እየተሸመደመደ በርሃማነት እየተስፋፋ ወንዞቻቸውና ምንጮቸቸው እየደረቁ ከድጡ ወደ ማጡ እየገቡ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ አንዱዋ የዚህ ክስተት ሰለባ ናት።

የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ዕቀድ አውጥቶ እየተገበረ ይገኛል። በዚህም የታዳሽ ሃይል ምንጮች እንዲጎለብቱ የሃይድሮ ኤሌትሪክ ማመንጫዎችን የንፋስና የባዮ ፊውል ሀይሎችን እያስፋፋ ይገኛል። ይህ ሁኔታም ወደፊት እንደሚቀጥል አመልክቷል። የአየር ንብረት ለውጥ በህይወት ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ የተረዱ አንዳንድ ዜጎችም የፈጠራ ችሎታቸውን በመጠቀም አንዳንድ መሳሪያዎችን በመስራት ላይ ሲሆን በርካቶችም በኢትዮጵያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ እንዲሁም በፈጠራ ባለቤትነት መብት ማረጋገጫ ተቋም ዕውቅና አግኝተዋል። የፀሐይ ኃይልን ወደ ኢነርጂ ምንጭነት ባዮማስን በተለያዩ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ወደ ውጤታማ ኃይል ምንጭነት የመቀየር ስራዎች በምሳሌነት የሚጠቀሱ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ስራዎች እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ የእውቅና ሰርተፊኬታቸውን ከመያዝ በዘለለ ወደ ስራ ተሰማርተው ራሳቸውንም ሆነ ሀገራቸውን ሲጠቅሙ የሚታይበት አጋጣሚ እጅግ በጣም አነስተኛ ነው። ለዚህም በርካታ ምክንያቶች የሚጠቀሱ ሲሆኑ በዋነኝነት ደጋፊና አስታዋሽ ማጣት ነው።

አቶ መስፍን ስለሺ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ እንደማንኛውም ዜጋ የአየር ንብረት ለውጥን የሙቀት መጨመር ያሳሰባቸዋል። በአሁኑ ወቅት በድሬዳዋ አካባቢ የውሃ እጥረት ነዋሪውን እጅግ እያሰቃየው የሚገኝ ሲሆን የዚህ ምክንያትም በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ከመሬት ስር ያለው የውሃ መጠን መቀነሱ ነው። በ1999 ዓ.ም ከተማዋ በጎርፍ ለመመታት የበቃችው ከደጋው አጎራባች አካባቢ የጣለው ዝናብ ወደ መሬት መስረግ ሲገባው ደን በመጨፍጨፉ ምክንያት ጎርፍ ሆኖ ከተማዋን በማጥለቅለቅ እንደሆነ ሁሉም ያውቀዋል።

በዚህና ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች አቶ መስፍን ስለሺ የአየር ብክለት በአብዛኛው ሰው ሰራሽ በመሆኑ ከፋብሪካና ከኢንዱስትሪ የሚለቀቀውን ጭስ ወደ ከባቢ አየር ሳይሄድ እዚሁ ወደ ሌላ ንጥረ ነገር መቀየር የሚቻልበትን ዘዴ ማሰላሰል፣ ከዚያም ስራቸውን በመጀመሪያ በጋራዥ ውስጥ መሞከር ጀመሩ። ገራዥ ውስጥ ለጥገና የሚገቡ መኪኖች የሚለቁትን በካይ ጋዝ ወደ ሌላ ቦታ ሳይሄድ እዚያው ጋራዥ ውስጥ ወደ ሌላ ንጥረ ነገር መቀየር እንደሚቻል በጥረታቸው ለማሳየት ችለዋል። የመኪናውን ጭስ ወደ ሌላ ንጥረ ነገር ለመቀየር የተጠቀሙበት ዘዴ አስገራሚ ነው። ከውጭ በተኮረጀ ቴክኖሎጂ አይደለም። እናታቸው ጋን ለማጠብ የሚጠቀሙበትን ጋንን የማጠን ዘዴን ነው ለስራቸው የተጠቀሙት በዚያ መሰረት ጋዙን እዚሁ ማስቀረት እችላሁ ብለው ወደ ሙከራው ለመግባት ችለዋል።

እንደ እርሳቸው ገለፃ በመጀመሪያ እንጨት በማንደድ የሚወጣውን ጭስ በቱቦ አማካኝነት ወደ ተለያዩ ጋኖች እንዲገቡ አደረጉ። በጋኑ ውስጥም ጭሱን የሚይዝ የፕላስቲክ ከረጢት አስቀመጡ በአጠቃላይ አምስት ጋኖች በአንድ አቅጣጫ ሌላ አምስት ጋኖች በሌላ በኩል ደርድረው የመጀመሪያዎቹ አምስት ጋኖች በአንድ ሰዓሰት ውስጥ ይሞላሉ። ጭሱም ወደ ጋዝነት (የአየር) እና ወደ ዱቄትነት ይቀየራል። በሚቀጥለው ሰዓት ደግሞ አምስቱ ጋኖች በጭስ ይሞሉና ጭሱ ወደጋዝነትና ወደ ዱቄት ይቀየራል። እንዲህ እያለ የሚነደው እንጨት ሳይቋረጥ ጭሱ ወደ ከባቢ አየር ሳይወጣ እዚሁ ይቀራል ማለት ነው። አቶ መስፍን ከእንጨት ቃጠሎ የሚገኘውን ጭስ በዚህ መልኩ ከሞከሩ በኋላ ስራቸውን ከመኪና ናፍጣና ቤንዚን የሚወጣውን ጭስ በተመሳሳይ ሞክረው ውጤቱን በተጨባጭ ተመልክተዋል። ከበካዩ ጋዝ የተገኘው የአየር ጋዝና ዱቄትም ለተለያዩ ጥቅሞች አውለውታል። የአየሩን ጋዝ ለለስላሳ መጠጦችና ለድራፍት ማሸጊያነት ስራ ላይ የዋሉት ሲሆን ዱቄቱን ደግሞ ለቀለም መስሪያና ለማዳበሪያነት ተጠቅመውበታል። በፋብሪካ ደረጃ የሚለቀቀውን በካይ ጋዝንም በዚህ መልኩ በምድር በማስቀረት አካባቢን ከብክለት ለመታደግ በተጨማሪ ጠቀም ያለ ገንዘብ በመመደብ ሌላ ራሱን የቻለ የማሸጊያ ጋዝና የቀለም ማምረቻ ፋብሪካ በመገንባት ለበርካቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚቻል የፈጠራ ባለሙያው ይገልፃሉ።

አቶ መስፍን ስለሺ የፈጠራ ስራቸውን በ2003 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን አቅርበው ዕውቅና ተሰጥቷቸው የፓተንቱ መብት አግኝተዋል። እርሳቸው በራሳቸው ተነሳሽነት ይህን ከሰሩ ተመራማሪዎች ደግሞ ይበልጥ ሁኔታውን በማስፋት የተሻለ ስራ መስራት እንደሚችሉ የስራው ፈጣሪ አመልክተዋል።

አቶ መስፍን በ2003 ዓ.ም ከበርካታ ሙያተኞችና ከህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ለመወያየት ዕድል ገጥሟቸው ነበር። መሳሪያው በአንድ ፋብሪካ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በበርካታ ፋብሪካዎች ተተክሎ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል ገልጸዋል። የሌሎች ሰዎች እውቀት ከተጨመረበት ደግሞ የበለጠ ጠቃሚ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ መስፍን መሳሪያውን ለመስራትም ብዙ ወጭ እንደማይጠይቅ ይገልፃሉ። ችግሩ የጋራ በመሆኑ ሁሉም ርብርብ ቢያደርግ ከፍተኛ ውጤት ሊገኝ ይችላል። ፋብሪካዎቹም ዱቄትንን ጋዝን በማምረትም የበለጠ ገቢያቸውን ሊያዳብሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ እንደ አቶ መስፍን ጥረታቸው በርሳቸው ብቻ ውጤት ሊያመጣ እንደማይችል ይልቁንም ስራቸው ለህዝብ ይፋ አለመደረጉ እርስ በርሳችን አለመከባበራችንን እንደሚያመላክት ይህም በተነሳሽነታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደፈጠረባቸው ሳይጠቅሱ አላለፉም።

አቶ መስፍን በሀገር ውስጥ በጉዳዩ ዙሪያ ከተለያዩ ሹማምንቶች አልፈው እስከ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ድረስ ተነጋግረዋል። ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝም ወትውተዋል። ነገር ግን ሁኔታው በግለሰብ ደረጃ እንደማይቻል በርካታ ገንዘብም እንደሚያስፈልግ ተነግሮአቸው ጉዳዩ ወደ ተዘጋ ፋይል እንዲገባ ተደርጓል። ያቀረቧቸውም ሰነዶች እንደዋዛ ውሃ በልቷቸዋል። እርሳቸው ግን በዚህ ተስፋ አልቆረጡም ለዚህ ጉዳይ ትኩረት የሚሰጡ አለም አቀፍ ተቋማት ሊኖሩ እንደሚችል ከጓደኞቻቸው መረጃ በማግኘት ኢንተርኔት መበርበራቸውን ቀጠሉ ከዚያም ከአንድ የካናዳ ድርጅት ጋር ተፃፅፈው የፈጠራ ስራዎቻቸውን በተመለከተ መረጃቸውን ልከው ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

እንደ እርሳቸው ገለፃ የፈጠራ ስራቸው በገንዘብና በተጨማሪ ምርምር ተደግፎ ለዓለም ገበያ ቢቀርብ ከእርሳቸው አልፎ ለኢትዮጵያ እውቅናና የባለቤትነት መብት እንዲሁም ከፍተኛ ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችል ነው። ፈጠራው የብቻዬ ይሁን አላሉም እውቀት ያላቸው በዚህ ጉዳይ ይግቡበት ሁላችንም እንረባረብ ነው የሚሉት። እስካሁን ግን ከሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ድጋፍ አላገኙም። በርግጥ በሀገራችን ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የፈጠራ ስራዎች እምብዛም አይበረታቱም። ይህም በመንግስታዊ ተቋማት ድክመት ብቻ ሳይሆን እርስ በእርስ እውቅና የመሰጣጣት ባህላችንም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ስሚገኝ ነው። አንሞጋገስም አንወዳደስም ይህ ደግሞ እምቅ ችሎታ ያላቸው የፈጠራ ሰዎች ማለትም ደራሲዎች፣ አርቲስቶች ፣ ስፖርተኞች፣ ተመራማሪዎች እውቀትና ችሎታቸውን ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ላይ ሳያውሉት የጋን ውስጥ መብራት ሆነው ተኮማትረው እንዲቀሩ አድርጓቸዋል። ስለሆነም የፈጠራ ባለሙያዎች እንዲበረታቱ ማድረግ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው።

እንደሚታወቀውና ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከረው የአየር ንብረት ለውጥና የሙቀት መጠን መጨመር በእጅጉ እየተጎዳን ነው። ሁኔታው ካልተገታ ድህነትን ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት መጨናገፉ አይቀርም። በተለይ በዝናብ ጥገኛ የሆነው እርሻችን የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት መሆኑ የዝናብ መጥፋትና ድርቅ በቀጥታ የሚያሳርፈው ተፅዕኖ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። የእውቀትና የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ የመሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት፣ መንገዶች ክሊኒኮችና የትምህርት ተቋማትን ማበራከቱ የአየር ንብረት ለውጥ ቢከሰት እንዲት ችግሩን ከወዲሁ መግታት እንዲቻል የሚያደርጉት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። አደጋ በተከሰተ ቁጥርም ለምሳሌ ድርቅ ፣ ረሀብና የጎርፍ መጥለቅለቅ ሲያጋጥም ለተጎጂው ማህበረሰብ በአፋጣኝ የምግብና የመድሃኒት እርዳታ ለማድረግ የመሰረተ ልማት መስፋፋት ከፍተኛ እገዛ አድርጓል። አርሶ አደሩ ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚ እንዲኖረው ምርቱን በአስተማማኝ ዋጋ ለማቅረብ አስችሎታል። ከከተማ የሚያስፈልገውን የፍጆታ እቃዎችን በዚህ አማካኝነት ያገኛል። የምርጥ ዘር አቅርቦት፣ ማዳበሪያና ፀረ ተባይ መድሃኒቶችን በቀጥታና በዱቤ ማግኘት መቻሉ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል።

በሌላም በኩል ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችሉ ስልቶችም ተዘርግተው እየተተገበሩ ነው። ከነዚህም ውስጥ የኢነርጂ ምንጭን ከበካይነት ወደ ታዳሽነት መቀየር አንደኛው ነው። በርካታ የሃይድሮ ኤሌትሪክ ማመንጫዎች ተገንብተው ለኢንዱስትሪዎችን ለቤት ውስጥ የሚያስፈልጉ የሃይል ምንጮች ኤሌክትሪክ እንዲጠቀሙ ማድረጉ ደንን ከመጨፍጨፍና አካባቢን ከመራቆት ይታደጋሉ። በየዓመቱ በ20 በመቶ የሚጨምረውን የኢነርጂ ፍላጎትን ከማሳካት በተጨማሪ ለውጭ ገበያ ኤክስፖርት በማድረግ የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኝ ይደረጋል። በአሁኑ ወቅት እየተገነቡ የሚገኙት 10 የስኳር ፋብሪካዎችም በሚሊዮን ሊትር የሚቆጠር ባዩፊውል እንዲያመርቱ የሚደረገው ጥረት በካይ ያልሆነ ነዳጅን ለትራንስፖርቱ ዘርፍ ለመጠቀም ሲሆን ለቤንዚንና ለናፍጣ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማዳን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። በካይንና ለቤት ውስጥ ምግብ ማብሰያነት ጥቅም ላይ የዋለውን ኬሮሲንንም ለማስቀረት ይረዳል። ቆጣቢ ምድጃዎችን ጭስ አልባ ከሰሎችንና ባዮጋዝ በስፋት መጠቀምም መንግስት መርሃ ግብር ቀርፆለት እየተገበረው ይገኛል። ይህም አካባቢን በመራቆት ለመታደግ የሚያስችል ነው።

በሌላም በኩል ደንን በመንከባከብና አከባቢን ከመራቆት በመጠበቅ በካርቦን ንግድ አማካኝነት የውጭ ምንዛሪ የማግኘቱ ስልትም አንዱ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ገፅታ ነው። ደኖች ዕፅዋቶች እንደመሆናቸው በፎቶሲንተሲል አማካኝነት ምግባቸውን ሲያዘጋጁ ካርበንዳይኦክሳይድን በግብአትነት ይጠቀማሉ። በዚህ ሳቢያ ደኖች ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን ካርበን በመምጠጥ አካባቢን ከመበከል ከመታደግ አልፈው ኦክስጅንን በመልቀቅ አካባቢ ነፋሻ አየር እንዲያገኝና ደረቅ እንዳይስፋፋ አስተዋፆኦ ያደርጋሉ። ከዚህ አኳያ በወላይታ ሀምቦ አካባቢ ያለው ደን እንቅከብካቤ ተደርጎለት በካይ ጋዝን መምጠጥ በመቻሉ በአለም ባንክ ከፍተኛ ገንዘብ ለማግኘት አስችሏል። ስለሆነም ደንን መንከባከብ አንዱ የአየር ንብር ለውጥን መቋቋሚያ ዘዴ እንደሆነ ግንዛቤ የሚያሻው ነው። ከዚህ አኳያ አቶ መስፍን ስለሺ ከፋብሪካ የሚለቀቀውን በካይ ጋዝ ወደ ከባቢ አየር ሳይደርስ እዚሁ እንዲቀር በማድረግ ከጭሱም ለማሸጊያ የሚያገለግል ጋዝንና ለቀለም መስሪያ የሚያገለግል ዱቄትን ማምረት የሚያስችለው የፈጠራ ስራ ለዓለም ቢተዋወቅ ሀገራችን ከራስዋ አልፋ ለሌሎችም መድህን መሆን እንደምትችል የሚያሳይ ጠቋሚ ምልክት ነው።

    በአሁኑ ወቅት ወደ ከባቢ አየር በተለይ ከፔትሮሊየምና ከድንጋይ ከሰል የሚለቀቀውን ጭስ ለመግታት የሀገሮች ርምጃ በዘገየ ቁጥር ዓለምን ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍላት በተባበሩት መንግስታት የተካሄደውን ጥናት በርሊን ላይ ይፋ ሲደረግ ችግሩን ለመግታት በታዳሽ ሃይል የመጠቀምን አካሄድ ማሳደግ እንደሚገባ የጥናት ቡድኑ መሪ ሩጀን ኩማ ናትሪዋ አመልክተዋል። ስለሆነም የእነ አቶ መስፍን አይነት የፈጠራ ስራ ትኩረት የሚሻ ነው።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
1248 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 913 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us