የሃይድሮጂን ኢነርጂን በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ለማዋል

Wednesday, 09 July 2014 13:35

ኢነርጂ ወይም የሃይል አቅርቦት ከግለሰብ ቤት ህይወት ጀምሮ ትራንስፖርት ቢዝነስን የኢንዱስትሪ ግንባታን ወዘተ ዘርፎች የሚነካ ነው። በባህላዊ ዘዴ የሚመረተውና በተለይም በደሃ ሀገሮች በስፋት ጥቅም ላይ የዋለው የደንና የዕዕዋት ውጤትና እንዲሁም የከብቶችን እዳሪ መጠቀም ለአካባቢ መራቆት ለደን መመናመን ለውሃ ምንጮች መድረቅና በበረሃማነት መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስለሚያደርግ በሌላ ታዳሽ ኃይል ማለት ከውሃ ከፀሐይ ከጀኦተርማልና ከንፋስ እንዲሁም ከባዮፊልና ከባዮጋዝ በሚገኝ ኃይል መተካት እንዳለበት ሀገሮችተስማምተው እየተገበሩ ይገኛል።

በተመሳሳይ በታዳጊም ሆነ በበለፀጉ ሀገሮች ለትራንስፖርት ለኢንዱስትሪና ለመሰል ዘርፎች ጥቅም ላይ የዋለው የፔትሮ ኬሚካል ውጤት የሆነው ነዳጅ ዘይት፣ ናፍጣ፣ ድንጋይ ከሰል ወዘተ ፋብሪካን ካንቀሳቀሰ በኋላ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀው በካይ ጋዝ የኦዞን ሽፋንን ከመሸንቆር የአየር ንብረት ለውጥና የሙቀት መጨመር ምክንያት እየሆነ ምህዳሩም ይበልጥ የደሃ ሀገሮች ኢኮኖሚ እየተመታ ምድር ለመኖር የማትመች እንዲሆን እያደረገ ይገኛል። ይህም በካይ የሃይል ምንጭ ከላይ በተጠቀሱት ታዳሽ የሃይል ምንጮች እንዲተካ ሀገሮች ርብርብ በማድረግ ላይ ናቸው። በኢትዮጵያ እየተተገበረ የሚገኘው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ታዳሽ ሃይልን የመጠቀምና የማስፋፋት መርህን መሰረት ያደረገ ነው።

ከሰሞኑ “ስለ ኢነርጂ እንነጋገር” ተብሎ በሚታወቀውና በፎረም ፎር ኢንቫይሮንሜንትና በጀርመኑ GIZ በሚዘጋጀው ስብሰባ ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሳይንስ ፋካልቲ ማስተማርና በምርምር ላይ የሚገኙት አቶ ጥበቡ አሰፋ ከውሃ የሚገኝ አዲስ የሃይድሮ ኢነርጂ የምርምር ጽሁፋቸውን አቅርበዋል። አቶ ጥበቡ በኢነርጂ ዕጩ ዶክተር ናቸው።

እንደ እርሳቸው ገለፃ ዓለም ከፔትሮ ኬሚካል የሚገኘው የኃይል ምንጭ አካባቢን በካይ ብቻ ሳይሆን ከጥቂት አስርታት በኋላ ስለሚያልቅ ሌላ አማራጭ ምንጭ መፈለጉ አስገዳጅ እንደሆነ ተገንዘብዋል። እንደ ሳዑዲ አረቢያ የመሳሰሉ የሀብት ምንጫቸው ከ96 በመቶ በላይ በነዳጅ ዘይት የሆኑ ሀገሮች ጭምር ሁኔታው እያሳሰባቸው መጥቷል። በዚህም ሳቢያ ከአመታት በፊት ኢኮሎጂስቶች የሃይድሮጂን ኢነርጂን ማምረት የሚቻልበትን ዘዴ ቀይሰው ወደ ተግባር አሸጋግረውታል። የሃይድሮጅን ኢነርጂ በራሱ ለብቻው የሚገኝ ምርት አይደለም። ይልቁንም ከሌሎች ታዳሽ ሃይሎች ማለትም ከውሃ፣ ከጸሐይና ከንፋስ የሚገኝ ምርት ነው። ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተትረፈረፈ ታዳሽ ሃይል ያላቸው ሀገሮች ሃይድሮጅንን በማምረት የሃይል አቅርቦታቸውን በማሳደግና ለገበያ በማቅረብ ድህነትን ለመቅረፍ ይችላሉ።

እንደ አቶ ጥበቡ ገለፃ ኢትዮጵያ ለሃይድሮ ኢነርጂ ሊያገለግል የሚችል የተትረፈረፈ የሃይል ክምችት እንደላት ምርምር ባደረጉበት በስዊድንና በደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች ለማረጋገጥ የቻሉ ሲሆን ይህም በአማካሪዎቻቸው ጭምር ተረጋግጧል። በአሁኑ ወቅት በሀገራችንም ሆነ በአለም የኢነርጂ ፍላጎት እየጨመረ ነው። በተለይ ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ የሃይል ፍላጎቱ በየአመቱ 20 በመቶ ስለሚያድግ ለኢነርጂው ዘርፍ መስፋፋት ትኩረት መስጠት የግድ ይላል። ስለሆነም ሃይድሮጅን ኢነርጂ በውጤታማነቱና በዋጋው መጠነኛነት እንዲሁም በቀላሉ መመረት መቻሉ ተመራጭነቱን ያጎላዋል። ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ሃይድሮጂን ከተለያዩ የሃይል ምንጮች የሚገኝ መሆኑ ፍላጎትን በማርካት ረገድ ጠቀሜታው የጎላ ነው። በአሁኑ ወቅት የበለፀጉ ሀገሮች ብቻ ሳይሆን ታዳጊ ሀገሮች ጭምር ሃይድሮ ኢነርጂን በማምረት ጥቅም ላይ በማዋል ላይ እደሚገኙ አቶ ጥበቡ ይገልፃሉ።

ለምሳሌ ግብፅ ከአስዋን ግድብ በትነት መልክ የሚወጣውን ውሃ ወደ ሃይድሮጅን በመቀየር እየተጠቀመች ሲሆን ሞሮኮና የአውሮፓ ህብረትም በሰሜን አፍሪካ ያለውን የፀሐይ ሃይል ወደ ሃይድሮጂን እየቀየሩ በስፋት እየተጠቀሙ ይገኛሉ። ደቡብ አፍሪካም ከአለም አንደኛ በሆነችበት የፕላቲንያም ንጥረ ነገር ሃይድሮጅን የማምረት አቅምዋ ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል። በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ በጥቅም ላይ የዋለው የኢነርጂ ምንጭ 96 በመቶው የሚገኘው ከፔትሮኬሚካል ሲሆን 4 በመቶ የሚሆነው ብቻ ከታዳሽ የሃይል ምንጭ ነው። ይህም ዓለም ምን ያህል ለብክለት የተጋለጠች መሆኑን የሚያመላክት ነው። እንዲያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት ለአለም ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የጀርባ አጥንት ሆነው የሚያገለግሉት የሃይል ምንጮች የተፈጥሮ ጋዝ፣ ድንጋይ ከሰልና ነዳጅ ዘይት ናቸው።

በአሁኑ ወቅት የኢነርጂ ጉዳይ ሲነሳ በዋንኛነት ትኩረት የሚሰጥባቸው ሁለት ነጥቦች አሉ። አንደኛው የአመራረቱ ዋጋ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በኢንቫይሮሜንት ላይ ሊያሳርፍ የሚችለው አሉታዊ ተፅእኖ ነው፡ በዚህ ረገድ ከፀሐይ ሃይል የሚገኘው ኢነርጂ ተመራጭ ሲሆን ወደፊትም አሁን ያለውን የፔትሮኬሚካል ሃይል ለመተካት እንደሚያስችል ይታመናል። ሃይድሮጂንም ከዚሁ የፀሐይ ሃይል የሚገኝ በመሆኑ አለም ወደዚያው አቅጣጫ ማምራቱ አይቀሬ ነው። ሀይድሮጂን በካይ ጋዞች ማለትም ካርቦንዳይኦክሳይድ፣ ሜቴንና መሰል ጋዞችን ወደ ከባቢ አየር አይለቅም። በዚህም አካባቢን አይበክልም ለሃይል ማመንጫነት የሚቃጠለው እሳትም በአካባቢው ምንም አይነት ጉዳት አያደርስም። ከዚያ በተጨማሪ ከፀሐይ የተመረተ ሃይድሮጂን ወደ ሌላ ንጥረ ነገር ማለትም ወደ ናይትሬት ተቀይሮ ማዳበሪያ ለማምረት ያስችላል። ሃይድሮጂን ለማምረት ከላይ እንደተጠቀሰው ሌላ የሃይል ምንጭ ያስፈልጋል ያ ከሌለ ማምረት አይቻልም። በዚህም ሳቢያ በአሁኑ ወቅት 65 በመቶ የሚሆነው ሃይድሮጂን ከንፋስ የሚመረት፣ 33 በመቶ ደግሞ ከፀሐይ ሃይል ሲሆን 67 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ከውሃ የሚመረት ነው። ይህ ኃይልም ፔትሮ ኬሚካልን ተክቶ ለትራንስፖትና ለኢንዱስትሪ ሊያገለግል የሚችል ነው። ከዚህ ጋር ስለ ሃይል አቅርቦት ሲነሳ ትኩረት ሊያገኝ የሚገባቸው ነገሮች አሉ። ከእነርሱም ውስጥ የሃይል ምንጩን ከቦታ ወደ ቦታ በቀላሉ ማጓጓዝ መቻሉ ኢነርጂው ከአንድ አይነት ይዘት ወደ ሌላ ይዘት መቀየር መቻሉ ለምሳሌ ከፀሐይ ወይም ከንፋስ ወደ ሃይድሮጂን፣ ውጤታማ መሆኑ፣ ለማናቸውም አጠቃቀም ማከማቸት የሚቻል መሆኑ፣ አካባቢን የማይበክል መሆኑ የትራንስፖት ዋጋው ርካሽ መሆንና ቀላል መሆኑ የሚጠቀስ ነው። ከዚህ አንፃር ሃይድሮጂን ከሁሉም የሃይል ምንጮች 100 በመቶ ተመራጭነት እንዳለው አቶ ጥበቡ አሰፋ ይገልጻሉ። ከዚህ ጋር መታሰብ ያለበት ለምርቱ ግብአትነት የሚያገለግሉ ሀብቶች በአስተማማኝ መልኩ ማግኘት መቻሉ ነው። በዚህ መሰረት ከካርቦን የሚገኘው በካዩ ድንጋይ ከሰልና ነዳጅ ዘይት፣ ኬሚካል፣ ባዮማስ፣ አልጌ፣ ባክቴሪያና ውሃ መኖር አለባቸው። እንደ አቶ ጥበቡ ኢትዮጵያ የሃይድሮጂን ኢነርጂን ለመጠቀም ከፈለጉት ኤሌክትሮ ሊሲል የተባለውንና ከውሃ የሚመነጨውን ዘዴ መጠቀም እንደሚኖርበት የእርሻቸውም ጥናት ከጣና ሃይቅ ሃይድሮጂንና ማምረት ስለሚቻልበት ዘዴ የሚያተኩር ነው።

እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት መንግስት ታዳሽ ሃይል የሆነውንና ከውሃ የሚመነጨውን የኤሌትሪክ ሃይል ለማምረት እንዲቻል በርካታ ግድቦችን አስገንብቶ ወደ ስራ ከመግባቱ በተጨማሪ ግንባታቸው ያላለቀ ግድቦችም ስራቸው በመፋጠን ላይ ይገኛል። የሚገኘውም ሃይል ለገጠር መብራት ማስፋፊያ ለትራንስፖርትና ለፋብሪካ ማንቀሳቀሻነት እንደሚውል ይታመናል። ከዚህ አንጻር የሃይድሮጂን ኢነርጂ ለምን ዘርፍ እንደሚውል የተጠየቁት አቶ ጥበቡ አሰፋ ሲመልሱ ኢትዮጵያ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ ላይ ነች። ኢንዱስትሪዎችንም በማስፋፋት ላይ ስለምትገኝ የሃይድሮጂን ኢነርጂ ለፋብሪካ ማንቀሳቀሻነት ይውላል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሀገሪትዋ የእርሻ ዘርፉን ዘመናዊ ለማድረግ እንዲቻል በርካታ የማዳበሪያ ፋብሪካዎችን ትገነባለች። ለዚህ ፋብሪካ ደግሞ የአሞኒየም ንጥረነገር ያስፈልጋል። ናይትሮጂን ከከባቢ አየር ሲወሰድ ከውሃ ውስጥ አንድ እጅ ከሆነው ሄድሮጂን ከውሃ ተነጥሎ እንዲወጣ ይደረጋል። ሃይድሮጂን ከውሃ ወይም ከናቹራል ጋዝ የሚገኝ ነው። ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ናቹራል ጋዝ በሀገሪቱ ስለማይመረት በቀጥታ ከውሃ እንዲወጣ ይደረጋል። በዚህ አማካኝነት የሃይድሮጂን ወደ አሞኒየም ተቀይሮ በማዳበሪያ ፋብሪካ ለግብአትነት ይውላል።

እንደሙያተኛው ገለፃ ውሃው ለዚህ ስራ እንዲውል ከተፈለገ ውሃው ከመጠጥነት አልፎ በጣም የፀዳ መሆን አለበት። በሌላም በኩል በሃይል አመራረት ዘዴ ሁለት ዓይነት የሃይል ተሸካሚዎች የሚገኙ ሲሆን አንደኛው ኤሌክትሪክ ሲቲ ሁለተኛው ደግሞ ሀይድሮጂን ነው ስለዚህ በአሁኑ ወቅት አለም እየተከተለው የሚገኝና ፔትሮልየምን ይተካል የሚባለው ሀይድሮጂን ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ባላት የውሃ ሀብት አማካኝነት ሀይድሮጂንን ማምረት ትችላለች። ይህን ኢነርጂም አጠራቅሞ መያዝም ይቻላል። በሁለተኛ ደረጃ ሃይድሮ ኢነርጂ ለበርካቶች የስራ እድልን መፍጠር የሚያስችል ነው። ለኢንዱስትሪ፣ ለኤሌክትሮላይት ለፊውል ሰርቪስና ለሌሎች ኢንዱስትሪዎች የስራ እድልን መፍጠር የሚያስችል ነው። ከዚሁ ጋር ሃይድሮጂን ምግብን ለማቆየት ለኤሌክትሮኒክስ ውስጥ አካላት ወደፊት ፔትሮሊየም ነዳጅ ቢገኝ ደግሞ እርሱን ለማቅጠኛነት ያገለግላል። እንደ አቶ ጥበቡ የማምረቻ ቴክኖሎጂው በቀላሉ ሊፈበረክ የሚችል ነው። ከዚህ በተጨማሪ ሃይድሮጂንን ከኦክስጅን ጋር በመቀላቀል ከሀይቅ ወይም ከወንዝ በትነት መልክ ወደ ከባቢ አየር በመውሰድ በዝናብ መልክ ተመልሶ መጥቶ ለእርሻ ስራ እንዲውል ማድረግ ይቻላል። አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ወንዞች በሸለቆ ውስጥ ስለሚጓዙ ለእርሻ ስራ የተመቹ አይደሉም። ስለሆነም ውሃ ውስጥ የለውን ሃይድሮጂን ወደ ላይ ወስዶ እንደገና እንዲዘንብ ማድረግ ይቻላል።

ይሁን እንጂ እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት በአየር ንብረት ለውጥና በሙቀት መጨመር እንዲሁም በውሃ ዳርቻዎች ፋብሪካዎች በመስፋፋታቸው የተነሳ የውሃ ሀብት ችግር ውስጥ እየገባ፣ መጠኑ እየቀነሰ፣ እየተበከለና አደጋ እያንዣበበት ነው። ስለዚህ ውሃውን ከአደጋ ጠብቆ ሃይድሮጂን የማምረቱ ስራ ዋጋውን ውድ አያደርገውምን ተብለው የተጠየቁት ሙያተኛው በዚህ ረገድ መልሳቸውን ሲያስቀምጡ ውሃው ከብክለት ነፃ እንዲሆን የአካባቢ ጥበቃ ስራ መሰራት እንደሚገባው ጠቅሰው ውሃ የሚበክሉ ፋብሪካዎች ከውሃ ዳር እንዲርቁ በማድረግ የውሃ ጥራት ቁጥጥር ስርዓትን ዘርግቶ መተግበር እንዳለበት ተናግረዋል።

አክለውም በአሁኑ ወቅት በውሃ ዳርቻዎች ኢኮቱሪዝም ማስፋፊያ ሆቴሎች እየተገነቡ እንደሆነ ኢንዱስትሪዎችም ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎችን ወደ ውሃው መልቀቃቸው ጥፋት እያደረሰ ስለሆነ መቀረፍ እንዳለበት ጠቅሰው ብክለት በውሃ ውስጥ ያሉትን ህይወት ያላቸውን ነገሮች በማጥፋት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ጭራሹኑ ውሃውን ሊያሳጣ እንደሚችል አመልክተዋል። ከተበከለ ውሃ ሃይድሮጂን ማምረት አካሄዱን እጅግ የተወሳሰበ ከማድረግ በዘለለ ዋጋው ውድ ያደርገዋል። ስለዚህ ኢኮሲስተሙንና ኢኮሎጂውን መንከባከብ ግድ ይላል ብለዋል።

ከውሃ ውጭ ያሉትን ታዳሽ ሃይሎች ለምሳሌ ንፋስንና የፀሐይ ሃይልን ወደ ሀይድሮጂን በመቀየር ረገድ በኢትዮጵያ ምን ሊከናወን እንደሚችል የጠቀሱት ሙያተኛው በአሁኑ ወቅት አንዳንድ የአፍሪካ ሀገሮች የፀሐይ ሀይልን ወደ ሃይድሮጂን እንዲቀየሩት በኢትዮጵያ ግን በፀሐይ ዙሪያ ብዙም እንዳልተሰራ ጠቅሰው በናዝሬትና በአሼጎዳ መቀሌ በተተከሉት በንፋስ ሃይል ኤሌትሪክ በሚያመነጩት ላይ ሌላ ተጨማሪ መሳሪያ ቢተከል ሃይድሮጂንን ማምረት እንደሚል ጠቅሰው ይህም ወደፊት ጊዜውን ጠብቆ ሊከናወን እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

እንደ አቶ ጥበቡ አሰፋ ገለፃ ከኢንዱስትሪ አብዮት በፊት አውሮፓ ለኢነርጂ ይጠቀም የነበረው ባዮማስን ነበር። አሁን እኛ የምንገኘው ገና በዚያ ደረጃ ነው። ስለዚህ ፀሐይን ለሃይድሮጂን ማምረቻነት ለመጠቀም የሚያስችል የሲልክን ንጥረነገርን በማምረት በቴክኖሎጂ ማምረት መቻል ግድ ይላል።

ኢትዮጵያ በጂኦግራፊ አቀማመጧ ከምድር ወገብ 35 ዲግሪ ላይ ስለምትገኝ ከፍተኛ የፀሐይ ሀብት አላት። ስለዚህ የፀሐይ ሀይልን ወደ ሌላ ኢነርጂ መቀየር ይቻላል። ከንፋስ የሚገኘውን የኤሌትሪክ ሃይልንም ወደ ሃይድሮጂን መቀየር ይቻላል። ስለዚህ ጊዜ ሳይጠፋና ሳይባክን ከባህላዊው የኢነርጂ አጠቃቀም በመላቀቅ ወደ ዘመናዊ አጠቃቀም መግባት ግድ ይላል።

ዓለም በአሁኑ ወቅት ትኩረቱን ወደታዳሽ ሃይል አድርጓል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሜሪካ የድንጋይ ከሰልን እስከ 2030 ዓ.ም በሰላሳ በመቶ ለመቀነስ እቅድ ነድፋ እየተገበረች መሆኗን ገልፃለች። ሌሎች ሀገሮችም እንደዚሁ የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ጥረት እያደረጉ ነው። ኢትዮጵያም በ2025 ከብክለት ነፃ የሆነች ሀገርን ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰች ነው። አሁን 2014 ላይ ነን የቀረን 11 ዓመት ነው። ስለዚህ አተገባበሩ በተፋጠነ መልኩ ካልተከናወነ እቅዱን እውን የማድረጉ ስራ አጠያያቂ ነው የሚሆነው። ከዚሁ ጋር መታየት የሚገባው በሃይድሮጂንና በመሰል ታዳሽ ሃይል መጠቀም የተፈጥሮ ሀብት የተጠበቀና ቀጣዩን ትውልድ ጭምር የሚያገለግል ይሆናል። የውሃ ጥራት ይጠበቃል። አካባቢም ከመንከባከብ አልፎ ለሌሎች የስራ እድል መፍጠር ይቻላል።

      ስለሆነም የኢነርጂ ልማት በአንድም ሆነ በሌላ የሀገርን ኢኮኖሚ ለመደገፍ የሚያስችልና ድህነትን ለመቀነስ ስለሚረዳ የሙያተኛው ጥናትና ምርምር ውጤት አስፈላጊውን ትኩረት በመንግስት አግኝቶ ሀይደሮጂን ኢነርጂን መጠቀም እንድንችል የባለድርሻ አካላት እገዛ አስፈላጊ ነው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1359 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 968 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us