ከተማችንን የማስዋቡ ሥራ እንዴት እየተከናወነ ነው?

Wednesday, 16 July 2014 12:08

አዲስ አበባ በውስጥዋ ከ3 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ይዛለች። ይህ ቁጥር ከገጠር ወደ ከተማ በሚደረግ ፍልሰትም የመጨመር ዕድሉ የሰፋ ነው። ለስራ እና ለንግድ በየዕለቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ከተማዋ ይገባሉ። ይወጣሉ፤ ከተማዋ ከመሰረተ ልማት አኳያ ብዙ የማስፋፋት ስራዎች እየተከናወኑላት ቢገኝም በማህበራዊ ህፀዶችን በድህነትና በስራ አጥነት የተነሳ በነዋሪው መካከል የኑሮ ልዩነቱ እጅግ በመስፋቱ የከተማዋ ገፅታ ዥንጉርጉር እንዲሆን አድርጓታል። ጥቂትና አዳዲስ የሚባሉት በከተማዋ በስተደቡብ የሚገኙ አካባቢዎች ከትላልቅ የአፍሪካ ከተሞች ጋር የሚወዳደሩ ሲሆን በተቃራኒው በመሐልና በስተሰሜን የተከማዋ አካባቢ ያሉ ቁጭራ መንደሮች ደግሞ ከተማ ይሁን ገጠር ጭራሹን ለመለየት ያስቸግራሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ዘርፍ የከተማዋን የፅዳት ውበትና አረንጓዴ ልማት ስራዎች አካሄድን በተመለከተ እንደገለፀው ከተማችን እያስመዘገበች ያለውን ፈጣን ዕድገት ተከትሎ እየተስፋፋ የመጣውን የመሠረተ ልማት የሪል ስቴት የጋራ መኖሪያ ቤቶች የንግድ ማዕከላትና ሌሎች ግንባታዎች በከተማዋ ገፅታ እንዲሁም ለነዋሪዎችና ለእንግዶችዋ ምቹና ተመራጭ እንድትሆን ለማስቻል የከተማን ፅዳት ውበትና አረንጓዴ ልማት ስራዎች በእኩል ትኩረት ተሰጥቶ ካልሄደ እየተመዘገበ ባለው እድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከማሳደሩም በላይ የተከማዋን ገፅታ በእጅጉ ጎድቶ ያሉትን እሴቶች ሊያሳጣ ይችላል ሲል አመለክቷል።

ከዚህ መረዳት የሚቻለው ልማትና እድገት ትርጉም ባለው መልኩ ሊመጣ የሚችለው የተመጣጠነ እድገትና ተመሳሳይነት ባለው መልኩ በሁሉም አካባቢ ልማት ሲመጣ ነው። አሁን ባለው አካሄድ መንግስት ያልለሙ አካባቢዎች እንዲለሙ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የተጎሳቆሉ መንደሮች ፈርሰው ነዋሪዎች በአዲስ አበባ እንደየአቅማቸው ተለዋጭ ቤት ተሰጥቷቸው እንዲሰፍሩ መደረጉ በመልካም ጎኑ የሚታይ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ግን በካሳ ክፍያና በመሰል ጉዳዮች የተነሳ ከተጎሳቆሉ አካባቢዎች የሚገኙ ተነሺዎች ባለመነሳታቸው የአካባቢው ገፅታ ከበፊቱ በባሰ መልኩ ተበላሽቶ ይታያል። በዚህ ረገድ በአራት ኪሎ አካባቢ ያለውን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።

የከተማ አስተዳደሩ ከተማዋን በ2012 በፅዳቷ፣ በውበቷና በአረንጓዴነቷ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መላውን የከተማ ባለሀብትና ህብረተሰብ በማነቃቃት በከተማዋ የውበትና የመናፈሻ ስራ ለማሳተፍ ያላሰለሰ ጥረት ቢያደርግም ባሉት ስር የሰደዱና የተከማቹ ችግሮችን ለመቅረፍ የህብረተሰቡን ድጋፍና ድርሻ በላቀ አቅም ተጠቅሞ የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ ባይቻልም ጥረቱ ግን ቀጥሏል። ልማቱ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ግን በይበልጥ በነዋሪው መካከል ያለው የገቢ ልዩነት እየተቀራረበ በመምጣት ከተቻለ ይልቁንም ድህነት በሂደት እንዲቀረፍ ከተደረገ ነው። ካልሆነ ነገሩ “ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ” እንደሚሆን ሙያተኞች ይገልጻሉ።

ከዚህ አኳያ በልደታ ክፍለ ከተማ በውበት መናፈሻና ዘላቂ ልማት እየተከናወነ ያለውን ስራ የጽህፈት ቤት የስራ ሂደት ኃላፊ አቶ ግዛቸው አያሌው እንደሚገልፁት ክፍለ ከተማው በያዝነው በጀት ዓመት 12ሺህ 8 መቶ 90 ሜትር ካሬ ቦታ በባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የለማ ሲሆን ሶስት ዝግ መናፈሻዎችን ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጓል። በወረዳ ደረጃ 7ሺህ 6 መቶ 24 ሜትር ካሬ ለማልማት ታቅዶ ከእቅድ በላይ ተከናውኗል። ከዚህ በተጨማሪ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች አማካኝነት የማስዋብ ስራ ተከናውኗል። ብሔራዊ ቴያትር አካባቢ በብሔራዊ ባንክና በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን በድምሩ 8ሺህ 9 መቶ 84 ሜትርካሬ ለምቶ እንክብካቤ እየተደረገለት ይገኛል።

መንግስታዊ ተቋማት ከዋንኛ ተግባራቸው በተጨማሪ ለከተማዋ መዋብ ብዙ ወጪ አውጥተው ለሌሎች አርአያ የሚሆን መነሳሳት ለመፍጠር ችለዋል። የንግድ ድርጅቶችና ባለሀብቶች በማስዋብ ስራው ላይ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ክፍለ ከተማው ጥረት አድርጓል። አንድ መቶ አስር የሚሆኑ ተቋማትና ባለሀብቶች በመንገድ ዳርቻዎችና አካፋዮች እንዲሁም አደባባዮች በአረንጓዴ ልማት እየተሳተፉ ይገኛሉ። በአጠቃላይም 2ሺ 5 መቶ ሜትርካሬ ለልማት ውሎ እንክብካቤ እየተደረገ ይገኛል።

ያለሙት አካባቢዎች በመጠኑም ቢሆን የከተማዋን ውበት ከመጠበቅና ገፅታዋን ከመቀየር አንጻር ትልቅ ጠቀሜታ እየሰጡ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ህብረተቡ እየተገለገለባቸው የገቢ ምንጭ ለመሆን ችለዋል። መልሶ ማልማት በሚከናወንባቸው ቦታዎች በመንግስት ከ9ሺህ ካሬ በላይ በሆነ ቦታ አፈር የመሙላትና የማስተካከል እንዲሁም የተመረጡ አገር በቀል የሆኑ 7 ዓይነት ችግሮች እንዲተከሉ ተደርጓል። በልማቱ ስራ አካባቢ የሚኖሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ነዋሪዎችም ቦታውን እንዲረከቡ እየተደረ የመንከባከቡ ስራ ይከናወናል። በተለይ በክፍለ ከተማው በልደታ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት ያለው ቦታ በመልሶ ማልማት ከተገነባ በኋላ ደረጃውን የጠበቀ የመዋኛ ስፍራ ከሌሎች ከተሞች ተሞክሮ የተወሰደ ዝግ በመናፈሻም እየተሰራ ይገኛል አራት ክፍት መናፈሻዎችና ሌላ አንድ ዝግ መናፈሻም ተቋቁሟል።

በክፍለ ከተማው በሚገኙ አስር ወረዳዎች በመንገድ ዳርቻና አካፋዮች ላይ የጥበቃና የመንከባከብ ተግባራት የሚያከናውኑ ከ50 በላይ ቋሚ ሠራተኞች አሉ በየቢሮዎች ከሚሰሩ አመራርና ፈፃሚ አካላት አንድ መቶ አስር ሠራተኞች ተያያዥ ስራዎችን ያከናውናሉ። እንዲያም ሆኖ አካባቢው ካለው ነዋሪና ለከተማው ከሚሰጠው ጠቀሜታ አንጻር ከዚህ የበለጠ ሊሰራ እንዲመገባ አቶ ግዛቸው አመልክተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ዘርፍ መረጃ እንደሚያመለክተው በልደታ ክፍለ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከናወኑ የማስዋብ ስራዎች ተጠቅሰዋል። በዚህም መሰረት በአደባባይ 7020፣ በመንገድ አካፋይ 9714፣ በመንገድ አካፋይ 5.062 በማህበራት አረጓዴ ቦታና በኮንዶሚኒየም መኖሪያ አካባቢዎች 5.119 ሜትር ካሬ በድምሩ 21016 ሜትር ካሬ በመልሶ ማልማት የውበት ስራ ይከናወናል።

ጽዳትን በመተመለከተም ከሱማሌ ተራ እስከ ተክለሃማኖት ከተክለሃይማኖት አብነት አደባባ በኮካ ኮላ ፋብሪካ እስከ ጦርሃይሎች ከበርበሬ በረንዳ እስከ ሆቴል ዲያፍሪክ ከዚያም በመቀጠል እስከ ፑሽኪን አዳባበይ ከተከለሃይማኖት ጥቁር አንበሳ እስከ ሜክሲኮ አደባባይ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እስከ ኢሜግሬሽን ከጤና ጥበቃ እስከ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል። ከዲአፍሪካ ሆቴል እስከ ፖሊስ ሆስፒታል ከኮካ ኮላ ፋብሪካ አደባባይ እስከ ወንድማማቾች ድልድይ፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እስከ 39/40 ኮንደሚኒየም ቤቶች ድረስ ከኢሜግሬሽን ብሔራዊ ሸበሌ፣ ልደታ እስከ ጦር ሃይሎች ሆስፒታል የሚገኙ ነጋዴዎች ከአካባቢያቸው እስከ 50 ሜትር ርቀት ያለውን ቦታ በፅዳት እንዲንከባከቡ ግዴታ የተጠላባቸው ሲሆን በተጠቀሰው ርቀትም የቆሻሻ ማጠራቀሚያ በማስቀመጥ አካባቢውን የሚያፀዱ ሠራተኞን በራሳቸው ወጭ እንዲቀጥሩ ተደርጓል። በአጠቃላይ እስከ 300 የሚደርሱ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ እቃዎችን በማስቀመጥ የውበት ማስዋብ ስራ ይሰራሉ።

ከዚህ ሁኔታ መረዳት እንደሚቻለው ጽዳት ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ስራ አለመሆኑ ሲሆን የክፍለ ከተማው አስተዳደር በስራው ባለሀብቶችንና ነጋዴዎችን ማሳተፉም በክንዋኔው ላይ የባቤትነት መንፈስ እንዲጎለብት ያደርጋል። ይህ ብቻ ሳይሆን በፅዳት ስራ ለሚሰማሩ ወገኖች የስራ እድል የፈጠረ መሆኑ ስራው በያዝለቀቅ ሳይሆን በቋሚነት በዘለቄታው እንዲከናወን የሚያደርግነው። ከላይ የተጠቀሰው የክፍለ ከተማው አካባቢ ሰፊ ነው በመንግስት በጀትና የሰው ሃይል ብቻ ለማከናወን አይቻልም። በቦታው በርካታ የማምረቻ የማከፋፈያ ተቋማት ሆስፒታሎች ሆቴሎች እንዲሁም የንግድ አካባቢዎች ሲኖሩ በተጨማሪም ያልለሙና የተጎሳቆሉ መፀዳጃ ቤቶች የሌላቸው መንደሮች ይገኛሉ። በአደባባዮች በአውራጎዳናዎች በአከፋይና በክፍት ቦታዎች የሚከናወነው ስራ እንደተጠበቀ ሆኖ በየጉራንጉሩ የሚገኙ ፅዳታቸው ያልተጠበቀ አካባቢዎች እንደሚገኙ ግንዛቤ ሊኖር ግድ ይላል። በዚህ ላይ የራስንናየአካባቢን ጽዳት የመንከባከብ ባህሉ በዝቅተኛ ደረጃ በሚገኝበት ሁኔታ የማስዋቡን ስራ በትክክል ተደራሽ በማድረግ ፈታኝ እንደሆነ መረዳት አያዳግትም።

ከዚህ አንጻር የልደታ ክፍለከተማን ተሞክሮ መመልከት ይቻላል። በአካባቢው በማስዋብ ስራው ውጤት እየተመዘገበ ቢሆንም የሚጠበቀውን ያህል እንዳሆን የተፈጠሩ ችግሮች መኖራቸውን የስራ ሂደት ሃላፊው ሳይጠቅሱ አላለፉም። በከተማችን በስፋት ተንሰራፍቶ የሚገኘውን የማህበራዊ ቀውስ አመልካች የሆነው ጎዳና ተዳዳሪነት ለዚህ አሉታዊ ተፅዕኖ ተጠቃሽ ነው። እነኚህ የማህበራዊ ቀውስ ሰለባዎች ቦታዎቹን በተለይም ያልተከለሉትን በመዋያ በማደሪያና በመፀዳጃነት እየተጠቀሙ እያበላሹዋቸው ሲሆኑ አንዳንድ ኃላፊነት የማይሰማቸው ሰዎችም የተተከሉ እፅዋቶችን መንቀላቸው ሰሩን መረጋገጣቸውና አጭሮችን መነቃቀላቸው በአረንጓዴ በማቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በማስከተል ላይ ይገኛል።

የህብረተሰቡን ተሳትፎ አለማጠናከር ለወረዳዎች አስፈላጊ ለስራ የሚያገለግሉ ግብአቶች አለመሟላት የሚለሙና የሚዋቡ ቦታዎችን ለይቶና መረጃዎችን አጠናቅሮ በመያዝ ለባለድርሻ አካላት አለማቅረብ በውሃ እጥረት ምክንያት ተተከሉ ሳሮች መጠውለግና መድረቅ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አለማዘጋጀት ለችግሩ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል።

ችግሮቹንም ለመቅረፍ በቀጣይ ትኩረት የሚደረግባቸውን ተግባራት አቅዶ ማከናወን አደረጃጀቱን ውጤታማ ማድረግ አዳዲስ ባለሀብቶች ወደ ልማቱ እንዲገቡ የማድረግ ስራን ማከናወን ተበላሹትንና የጠፉትን እንደገና መትከልና መንከባከብ ተጨማሪ የማስዋቢያ ችግኞችን በክፍት ቦታዎች ላይ መትከል እንዲቻል መግባባት ላይ መድረሱን የስራ ሂደት መሪው አመልክተዋል። በተለይ የታክሲ ማቆሚያ አካባቢዎች በሾፌሮችና ረዳቶች እንዝህላልነት አካባቢዎች ከመጎሳቆላቸው በተጨማሪ ያለሃፍረት ወደመፀዳጃ ቦታን መቀየራቸው ሁሉን ሊያሳስብ የሚገባ ነው። ቀድሞ ባለው ጊዜ ለጎዳና ተዳዳሪዎችና ታክሲ ሾፌሮችና ረዳቶችን በማሰባሰብ ከዚህ አኳያ የፅዳት ግንዛቤያቸውን ለማጎልበት ጥረት ተደርጎ ነበር። ይሁን እንጂ ስራው ዘላቂነት አላገኘም አካባቢን መጠበቅም የአስተሳሰብ ለውጥን የሚጠይቅ በመሆኑ ረጅም ጊዜን ይጠይቃል። ስለሆነም የማስተማሩን ስራ አጠናክሮ መቀጠሉ ብቸኛ አማራጭ ነው።

    ከአስር ዓመታት በፊት በታዋቂው አርቲስት ስለሺ ደምሴ ማነቃቃት የከተማችን የፅዳት አጠባበቅ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ትልቅ እመርታን አሳይቶ ነበር። በዛን ወቅት የተሰሩት አረንጓዴ ልማቶች በአሁኑ ወቅት ከጥቂት ቦታዎች በስተቀር ከሽፈዋል ማለት ይቻላል። ከዚህ አንፃር በማስዋብ ስራ ተሞክሮ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ተፈትሸው ጠንካሮቹ ሊጎለብቱና ደካሞቹ ሊቀረፉ ግድ ይላል። እንዲያም ሆኖ በተጨባጭ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የህዝብ ቁጥር እድገት የድህነትና የጎዳና ተዳዳሪ ጉዳይ ነው እነኚህ ችግሮች ካልተቀረፉ ስራዎች ከዘሌታነት ይልቅ ወደ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ሊሽከረከሩ ይችላሉ።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1595 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1092 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us