የገበያ ያለህ የሚሉት የኃይል ቆጣቢ ምድጃ አምራቾች

Wednesday, 23 July 2014 17:09

በአይቼው ደስአለኝ


 

በከተማችን ለቤት ውስጥ ምግብ ማብሰያ የተለያዩ የኢነርጂ ምንጮችን ጥቅም ላይ ውለዋል። ባዮማስ ማለትም እንጨትና ከሰልን የሚጠቀመው የህብረተሰብ ክፍል እስከ 80 በመቶ ይገመታል። አሁን አሁን ታዳሽ የኃይል ምንጮች የሆኑ የኤሌክትሪክ ባዮጋዝና ባዮፊውል እየተለመዱ ቢመጡም ገና አልተስፋፉም። በሌላም በኩል ከውጭ በሚገባው በኬሮሲን የሚጠቀም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቤተሰብ ይገኛል። ይህ የኃይል ምንጭ ግን በካይ እንደመሆኑ በጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያስከትላል። በተጨማሪም የውጭ ምንዛሪንም የሚያስወጣ እንደመሆኑ በውስን የውጭ ምንዛሪ ጥራት ላይ ጫና እያሳረፈ ይገኛል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በየጊዜው በህዝብ ቁጥር እድገት የተነሳ እያሻቀበ ያለውን የኃይል ምንጭ ፍላጎት በተለያዩ ዘዴዎች ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ የሚገኝ ሲሆን በተለይ በርካታ የህብረተሰብ ክፍል የሚጠቀምበትን የባዮማስ ኢነርጂን በቁጠባ መጠቀም እንዲቻል ኃይል ቆጣቢ ምድጃዎችን ማስተዋወቅን የማሰራጨት ስራ እየሰራ ሲሆን እየተለመደ ሲመጣም በገበያ ላይ እንዲውል ማድረግ እንደሆነ በባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የኢነርጂ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መስከረም አበበ ይገልፃሉ።

የእንጨት ማገዶ ከከተማችን ዙሪያ በእንስሳት በተሽከርካሪና በሰው ሸክም ተጭነው መጥተው ለገበያ ይውላል። በቀን እስከ 80 አይሱዙ መኪና ከሰል ከሩቅ አካባቢ በመምጣት ጥቅም ላይ ይውላል። ይህ በቀጥታ ከደን ጭፍጨፋ ጋር የሚገናኝ ሲሆን በአካባቢ ላይ ውድመት ያስከትላል። በጤናም ላይ እደዛው አብዛኛው ተጠቃሚ በድህነት ውስጥ የሚማቅቅ እንደመሆኑ በፍጥነት ወደ ዘመናዊ ኤሌትሪክና ሌላ ታዳሽ ኃይል ለመግባት አይችልም። አኗኗሩና ገቢው መቀየር አለበት። እስከዚያው ግን ባህላዊውን ኢነርጂ መጠቀሙን ይቀጥላል። ስለሆነም ቢያንስ የደን ጭፍጨፋውን ፍጥነት ለመገደብ ባህላዊ ምድጃዎችን በቆጣቢ ምድጃ መቀየር አዋጭ መሆኑ ስለተረጋገጠ የማስፋፋቱና የማስተዋወቁ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በአሁኑ ወቅት በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት፣ በባለሀብቶችና በግለሰቦች ያላሰለሰ ጥረትና ቅስቀሳ ነዋሪዎች የተሻሻሉ ኃይል ቆጣቢ ምድጃዎችን አማራጭ የኃይል ምንጭ የሆኑትን ባዮጋዝ፣ የፀሐይ ኃይልን ከተጣሉ ቆሻሻዎች የተሰሩ ከሰሎችን መጠቀም ጀምረዋል። ለዚህ እንዲያግዝም የኃይል ቆጣቢ ምድጃዎችና አማራጭ ኢነርጂ ማስተዋወቂያ ጣቢያዎች ተቋቁመው ህዝብ እንዲያያቸው እየተደረገ እንደሚገኝ አቶ መስከረም ጠቅሰው በክፍለ ከተሞችና በወረዳ ደረጃም ኤግዚቢሽኖች እየተከፈቱ የመላመዱ ዕድል እንደተፈጠረ ተናግረዋል። በዚህም በተለይ እናቶች ዋንኛው ተጠቃሚና የማጀት ገፈት ቀማሽ እንደመሆናቸው ምድጃዎችን በመውሰድ እየተጠቀሙ ይገኛሉ። ይህ ሁኔታም በዚህ ብቻ ሳይገታ ቆጣቢ ምድጃ የማምረት ጉዳይ ለበርካታ ሴቶች የስራ እድል ለመፍጠር በቅቷል። ይህ በጎ ጅምር ግን በርካታ ጋሬጣዎች ተጋርጠውበታል። በዚህ ማሳያ የሚሆነው በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለከተማ ወረዳ ስድስት ውስጥ በብድር ባገኙት 12ሺህ ብር ተደራጅተው በቆጣቢ ምድጃ ማምረት ተሰማርተው የሚገኙ አባላት ናቸው። የማህበሩ አባል የሆኑት ወ/ሮ ተስፉ አዱኛ እንደሚገልጹት በ2002 ዓ.ም ማህበራቸው ሲመሰረት 12 አባላቱ ስራውን እንሰራለን ለውጤትም እንበቃለን በሚል ተስፋና መነቃቃት ተሰማርተው ነበር። በወቅቱም በወረዳው ጽ/ቤት አማካኝነት ለስራቸው ማከናወኛና መሸጫ ቦታ ተሰጥቷቸው እየተንቀሳቀሱ በተለያዩ ወቅቶች ምርቶቻቸውን በተለያዩ አካባቢዎች ቢያስተዋውቁም የተፈለገውን ገበያ ለማግኘት አልቻሉም። ለዚህም በዋንኛነት የሚጠቀሰው ምክንያት በአካባቢያቸው ያለው ነዋሪ በአብዛኛው የኤሌትሪክ ምጣድ ተጠቃሚ በመሆኑ ነው።

በርግጥ የአካባቢው ሰው ከማገዶ እንጨትና ከከሰል ተላቆ ወደ ኤሌክትሪክ ምጣድ መሸጋገሩ እሰየው ነው። ምክንያቱም የደን መጨፍጨፍ መጠንን የካርበን ዳይኦክሳይድ ልቀትን እንዲሁም በቤት ውስጥ ጭስ ህጻናትና እናቶች ለመተንፈሻ አካላት በሽታ እንዳይጋለጡ ስለሚያደርግ ነው። ሊበረታቱም የሚገባው ነው። የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ መሰረትንም ያሰፋል። ነገር ግን አሁንም እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ነዋሪ የእንጨትና የከሰል ተጠቃሚ በመሆኑና ምድጃውም ኃይል ቆጣቢ ባለመሆኑ ለደን ውድመትና ለአካባቢ መራቆት አስተዋፅኦው ከፍተኛ ነው። ስለሆነም የኃይል ቆጣቢ ምድጃ ምርት ዘመናዊ በሆኑ የገበያና የማስተዋወቅ ስራዎች ተደግፎ ለተጠቃሚው እንዲደርስ በስፋት መሰራት ይኖርበታል።

ማህበሩ እንቅስቃሴውን ከጀመረ አራት ዓመታትን ማስቆጠሩን የሚጠቅሱት ወ/ሮ ተስፉ በእነኚህ አመታት ውስጥ ለምርታቸው የገበያ ትስስር የተፈጠረላቸው አንድ ወቅት ብቻ እንደሆነ ያስታውሳሉ። ይህ አጋጣሚም GTZ የተባለው የጀርመን መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በአካባቢው በዚሁ ስራ የተሰማሩ ወጣቶችን የስራ እንቅስቃሴ ለመጎብኘት በቦታው መጥቶ በነበረበት ወቅት ምርቶቻቸውን ተመልክቶ የተወሰኑትን በገዛቸው ወቅት ሲሆን በዚህ ሽያጭ አማካኝነትም የተበደሩትን 12ሺህ ብር ለመክፈል ችለዋል።

መንግሥት ሴቶች ራሳቸውን ችለው ገቢ እንዲፈጥሩ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ጥሩና የሚበረታታ ነው የሚሉት ወ/ሮ ተስፉ ከዚህ አንጻር የወረዳው ጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ጽህፈት ቤት በተለያዩ ባዛሮች ላይ ያለምንም ክፍያ በመሳተፍ ምርታቸውን እንዲያስተዋውቁ ረድቷቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ ሁሌ ተደርጎ ለአባላቱ የእለት ጉርስና ለቤተሰቦቻቸው ማስተዳደሪያ ገቢ ለመፍጠር አልቻሉም። ይህም የደከሙበትን ጊዜ የፈሰሱትን ጉልበትና መሰል ወጭ ከንቱ እያደረገው ይገኛል። ሌላዋ የማህበሩ አባል ወ/ሮ አለም በበኩላቸው እንደሚሉት የማህበሩ አባላት ከፍተኛ የስራ ተነሳሽነት አላቸው። ነገር ግን ምርታቸው ገበያ ማጣቱ በተነሳሽነታቸው ላይ ቀዝቃዛ ውሃ እየቸለሰ ነው። በተለይም ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ያመረቱት ምርት ሳይሸጥ መቀመጡ አባላቱን ተስፋ እያስቆረጠ ነው። ይህንን ችግር በመጠኑም ቢሆን ለመቅረፍና እስከ ጊዜው ለማዝገም እንዲቻል ከምድጃዎች ምርት ጎን ለጎን የስፌትና ሌሎች የእጅ ስራዎችን በመስራት የቤተሰቦቻቸውን ነፍስ ለማቆየት ችለዋል። ከላይ እንደተጠቀሰው በመንግስት በኩል አቅም በፈቀደ ትብብርና እገዛ ተደርጎላቸዋል። ይሁን እንጂ ችግሩ ስላልተቀረፈ አባላቱ የመንገስ ጥንካሬያቸውን በማጎልበት በቀጣይ ምርቱን ለሸማቹ ህብረሰብ ለማስተዋወቅ ምድጃዎችን ተሸክሞ በየመንደሩ ለመዞር ቢያስቡም በብሎኬት የተሰሩት ምድጃዎች ክብደታቸው የትየለሌ በመሆኑ ለመተግበር እንደተሳናቸው በመጥቀስ ተማፅኖአቸውን ለባለሀብቶችና ለተቋማት ያሰማሉ።

የማህበሩ አባላቱ ፈተናውን በመጋፈጥና አንዳንድ ተባራሪ ስራ በመስራት ይህም ሲጠሩ ከሰዎች በመበደር ኪራይ ይከፍላሉ። የቤተሰባቸውንም ህይወት በዚህ መልኩ ይደግፋሉ። ይህ ሁኔታም ዘለቄታነቱ አጠራጣሪ በመሆኑ አባላቱ እንደ መጨረሻ አማራጭ ክፍለ ከተማውም ሆነ የወረዳው አስተዳደር በሌላ የስራ ዘርፍ እንዲሰማሩ እንዲያደርግ የሚል አስተያየት ያቀርባሉ።

የኢኮኖሚ ህግጋትና የኢንተርፕረነር ሺፕ ክህሎት እንደሚያመለክቱት አንድን ምርት ለማምረት የሰው ኃይል ገንዘብ የማምረቻ ቦታ እና እውቀት ዋንኛ ግብአቶች ናቸው። እነኚህ ግብአቶች ተቀናጅተው ምርትን እንደሚያስገኙ ይታወቃል። ከዚሁ ጋር ግን ምርቱ ከፍጆታ አልፎ ለገበያ የሚቀርብ ከሆነ አስፈላጊው የገበያ ጥናት መደረግና ምርቱም በገበያው ተፈላጊ መሆኑ መረጋገጥ አለበት። ገበያው መኖሩ ሳይረጋገጥ ወደ ምርቱ ተገብቶ ምርቱም በሂደትና በጊዜ ብዛት ተዋውቆ ሸማች ካላገኘ ምርቱን ለማምረት የወጣው ጊዜ ጉልበት እውቀትና ገንዘብ ባከነ ማለት ነው። ይህም ኢኮኖሚን የማደግፍና የስራ ተነሳሽነትን የሚገድል በመሆኑ እንደገና ሊጤን ይገባል። በርግጥ የማህበሩ አባላት የሚያቀርቡትን ተማፅኖ በማዳመጥ ሙያዊና ዘመናዊ በሆነ መልኩ ምርቱ ተቀባይ አግኝቶ በጅምላና በማከፋፈሉ ስራ ሌሎች ወገኖች እንዲገቡበት ቢደረግ የተሻለ ውጤት ሊመጣበት ይችላል። እስከአሁን ግን በማህበሩ አባላት የተደረገው ጥረት ከማምረት በመለስ በገበያ በኩል ውጤት አልተገኘም በርግጥም ገበያ ማፈላለጉ የሌላ ሙያተኛ ጉዳይ ሊሆን ይችላል።

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የደን ውድመትና የአካባቢ መራቆት በደን መጨፍጨፍ የሚመጣ ነው። በዚህ ሳቢያም ድርቅና የዝናብ መጥፋት እንዲሁም የጎርፍ መጥለቅለቅ እየተከተለ የእርሻ ምርታማነት ይቀንሳል። ይህም መራብና መታረዝን ብሎም በድህነት አዙሪት ውስጥ መዳከርና ተመፅዋችነትን ያባብሳል። ስለሆነም የደን መጨፍጨፍ ምክንያት የሆነውን የኢነርጂ አጠቃቀም በሂደት መቀየር አንደኛው መፍትሄ ሲሆን ማገዶና ከሰል ተጠቃሚ የሆነው የህብረተሰብ ክፍል በተቻለ መጠን በኃይል ቆጣቢ ምድጃ እንዲጠቀም ማድረግ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ባለስልጣንም አማራጭ የኃይል ምንጮችን በማስተዋወቅና በማስፋፋት በዚህ ጋር ቆጣቢ ምድዎችን ማስተዋወቁ ይበል የሚያሰኝ ነው። ይሁን እንጂ በኮልፌ ቀራኒዮ ወረዳ ስድስት ውስጥ በተደራጅት ማገዶ ቆጣቢ አምራቾች ላይ ያጋጠመውን የገበያ ችግር መቅረፍ ስለሚቻልበት ሁኔታ ቢያንስ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመመካከር ጥረት ቢያደርግ የኃይል ቆጣቢ ምድጃዎችን የማስተዋወቁ ስራ ይበልጥ ለስኬት ይበቃል።

የማህበሩ አባላት የተሰጣቸው ሼድ ለስራ አመቺ ሲሆን በውስጡም በርካታ ምርት ተጠራቅሞ ይታያል። ይህን ምርት ለመጨረሻ ጊዜ ያመረቱት ባለፈው 2005 ሰኔ ወር ላይ ነው። እንደእነርሱ ገለፃ ምርቱን ለማምረት የሚያስፈልጋቸው ጥሬ እቃ እና ጉልበት የተትረፈረፈ ነው። ችግሩ ግን ገበያ ነው።

የአባላቱን የገበያ እጦት በተመለከተ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ የተጠየቁት የወረዳ 6 ምክትል ስራ አስፈፃሚና የጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዶ አወል በሰጡት ምላሽ በወረዳው 105 አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እንደሚገኙ ጠቅሰው ለእነርሱም የስልጠናና የገበያ ትስስር ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አመልክተዋል። አክለውም የገበያ ትስስሩ በሁለት መልኩ እንደሚከናወን አንደኛው የወረዳው ጽህፈት ቤት የሚያካሂደው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ አንቀሳቃሾች በራሳቸው የሚፈጥሩት ነው ብለዋል። በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩትን ከቤቶች ኤጀንሲ ጋር በመነጋገር የገበያ ትስስር የሚፈጠር ነው። ከዚህ አኳያ የኮንስራክሽን ዘርፍ የተሻለ ዘመናዊ አሰራርን ስለሚከተልና ምርቱን የሚፈልግ የመንግስት ተቋም ስላለ ገበያው አስተማማኝ ነው። በሌላ በኩል የማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎች የገበያ ትስስር ከዚህ ለየት ይላል። እንደምክትል ስራ አስፈፃሚው ገለፃ የምድጃው በማህበር አባላት አብዛኛው ምርታቸውን ተጠቃሚ ገጠሬ ነው። የከተማው ነዋሪ አማራ መጠቀሚያ አለው። ከዚህ አኳያ ምርቱን ገጠር ድረስ መውሰድ ከቦታው ርቀት አኳያ አዋጭ አይደለም። ይሁን እንጂ እንደ GTZ ካሉት ፈርጣማ አቅም ካላቸው መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር ክፍተቱን ለመሙላት መሞከር እንደአማራጭ ተይዟል።

በአጠቃላይ ቆጣቢ ምድጃዎችን ማምረትና መጠቀም ከላይ የተጠቀሱትን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ያስገኛል። በከተማም ሆነ በገጠር በርካታ ህዝብ ባዮማስን በኢነርጂ ምንጭነት የመጠቀሙ ፍላጎት ከፍተኛ እስከሆነ ድረስ ምድጃዎች ተፈላጊነታቸው ግልፅ ነው። ይሁን እንጂ ምርትን ማምረት አንድ ነገር ሆኖ ሳለ ምርትን ገዝቶ ለፈለገው ማቅረብና ገበያ ውስጥ መግባት ደግሞ ሌላ ሙያንና ችሎታን የሚጠይቅ ነው። ስለሆነም የገበያ ትስስርን የማጠናከሩ ስራ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነው። ይህ ካልሆነ ግን ምርት ያለገበያ በአንድ እጅ ማጨብጨብ ነው። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1833 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 887 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us