ለእርሻ ምርታማነት የባዮቴክኖሎጂ ሚና አሻሚ ጉዳዮች

Wednesday, 30 July 2014 12:33

በአሁኑ ወቅት ሳይንቲስቶች በምግብ ራስን በመቻል ጉዳይና የእርሻ ምርታማነት ከመጨመር እንዲሁም ምርቱን ለተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ለግብአትነት መጠቀም ስለሚቻልባቸው ጉዳዮች የተለያዩ አስተያየቶች እየሰጠ ይገኛሉ። በተጨባጭ እንደሚስተዋለው በኢንዱስትሪ የገፉ ሀገሮች የእርሻ ማለትም የእፅዋትም ሆነ የእንስሳት ዘርፍ ምርታማነት አድጎ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ ገንዘብ ለማግኘት ከቻሉበት ዘዴዎች ውስጥ አንደኛው የባዮ ቴክኖሎጂን በመጠቀማቸው ነው። በአጠቃቀሙ ላይ የተለያየ አመለካከት መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ በምግብ ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ለደሃ ሀገሮች በሽያጭም ሆነ በምፅዋት በማቅረብ ተፅዕኖአቸውንና ቅቡልነታቸውን እያሰፉበት ይገኛሉ።

በሌላው ጠርዝ ደሃ ሀገሮች የእርሻ አስተራረስ ዘይቤያቸው ገና ከባህላዊ ዘዴ ያልተላቀቀ በተፈጥሮ ላይ ጥገኛ መሆኑ በሳይንስ ምርምር ባለመደገፉ በምግብ ራሳቸውን መቻል ተስኖአቸው ለተመፅዋጭነት ተዳርገዋል። እነኚህ ሀገሮች የእርሻ ምርታማነታቸውን በሳይንሳዊ ዘዴ ለመደገፍ ሃሳቡ ቢኖራቸውም በቂ የሰለጠነ የሰው ኃይል ካለመኖር ገንዘብና ቴክኖሎጂን ከማጣትና ከፈጠራ መብት ጋር በተያያዘ ባለው አወዛጋቢ ሁኔታ በዘርፉ እርምጃ ለማሳየት ተስኗቸዋል። አሁን አሁን ግን ባዮቴክኖሎጂን እንደ አንድ አይነተኛ አማራጭ በመውሰድ ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ጥረታቸውን ቀጥለዋል።

ዶ/ር አዳነ አብርሃም በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ተመራማሪ ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት ባዮቴክኖሎጂ በተለይም ለመተግበር የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎችም በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዳሉ ይጠቅሱና በተለይ የባዮቴክኖሎጂ ደህንነት ህይወትና ዘረመል ምህንድስና ጥቅሙና ጉዳቱ ይበልጥ እየታወቀና ጥቅሙ ተቀባይነትን እያገኘ እንደመጣ ይገልጻሉ። ከዚሁ ጋር ህጉን የማስፈፀም መርሆዎችና ተቆጣጣሪ ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች እንዳሉ ይናገራሉ። በኢትዮጵያ ከረጅም ጊዜያት ጀምሮ የእርሻ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የተለያዩ ርምጃዎች ተወስደዋል። ከእነርሱም ውስጥ አንደኛው የባዮቴክኖሎጂ ውጤት የሆነውን ከውጭ ሀገር የሚገባውን ማዳበሪያ መጠቀም ሲሆን ምርጥ ዘርን መጠቀም የመስኖ ልማትን ማስፋፋት የኤክስቴንሽን አገልግሎት ማቅረብ እንዲሁም ፀረ ተባይ መድሃኒትን መጠቀም እስካሁን ስራ ላይ እየዋሉ የሚገኙ ናቸው። እነኚህ ለእርሻ በግብአትነት ጥቅም ላይ የዋሉትም በአነስተኛ መሬት በሚታረሱ የእርሻ መሬቶችና በሰፋፊ እርሻዎች ነው። በሁለቱም እርሻዎች ምርታማነትን ማሳደግ እንደተቻለ በተጨባጭ የሚታይ ሆኖ በሌላ በኩል በተለይ ሰፋፊ እርሻዎችን ማስፋፋትና በእርሻዎቹ ፀረ ተባይ ኬሚካሎችን መጠቀም አሉታዊ ተፅዕኖ እያስከተለ ስለመሆኑ ከአንዳንድ ሙያተኞች ነቀፌታ ይሰማል። እንደ ዶ/ር አዳነ ገለፃ ባዮቴክኖሎጂን በተመለከተ በሀገራችን የተደነገጉት ህጎች አፅንኦት ከሚሰጧቸው መካከል ቴክኖሎጂው በሰው በእንስሳትና በአካባቢ ጤንነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያስከትል ጥንቃቄ ማድረግን ነው።

እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የእርሻ ምርታማነትን ለማሳደግ መንግሥት በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን ለዚህ እንዲያግዝም ለእርሻ የሚያግዙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትንና የምርምር ማዕከላትን በማቋቋም ጥናትና ሙከራዎችን በማድረግ በላቦራቶሪ የተዳቀሉ ዘሮችን እፅዋቶችን ለገበሬው በማደል ሰፊ ሥራ እየሰራ ይገኛል።

ዶ/ር በላይ አድማሱ በሆለታ የእርሻ ምርምር ጣቢያ ከፍተኛ ተመራማሪና ዳይሬክተር ናቸው። እንደ እርሳቸው ገለፃ በኢትዮጵያ ወደ 13 የሚጠጉ የእርሻ ምርምር ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን ለተቋማቱም ከመንግሥት ከፍተኛ በጀትና የሰው ኃይል ተመድቦ ስራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ። እርሳቸው የሚመሩት ተቋምም ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በሞሊኪዩራል ቴክኖሎጂ አማካኝነት እፅዋቶችን በማዳቀል ለገበሬዎች የሚያድል ሲሆን ይህም ገበሬዎችን ውጤታማ እንዲደረግ አመልክተዋል። በምርምራቸው አማካኝነት ዘሮች በቶሎ እንዲደርሱ በሽታንና ድርቅን መቋቋም የሚችሉ እፅዋቶችን በማዳቀልና በማጎልበት ለገበሬዎች በነፃ ያከፋፍላሉ። በአሁኑ ወቅት ለእርሻ ምርታማነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከሚያደርጉት መካከል ከአፈር በቂ ንጥረ ነገር ከማጣት በተጨማሪ የእፅዋትም ሆነ የእንስሳት ለበሽታ ተጋላጭነት በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው። ከዚህ አኳያ ባዮቴክኖሎጂ በሀገራችን ዛሬም ሆነ ወደፊት የላቀ ሚና እንደሚጫወት ሙያተኛው ይገልጻሉ።

የአርብቶ አደሩንና የአርሶ አደሩን ከብቶች ፍየሎች በጎችና ግመሎች ከበሽታ ለመጠበቅና የወሊድ አቅማቸውና ወተት የመስጠት ኃይላቸው እንዲጎለብት በደብረዘይት በጅጅጋ፣ በመልከሰዲ ያሉ የግብርና ምርምር ተቋማት ባዮቴክኖሎጂን በመጠቀም ከፍተኛ እገዛ እያደረጉ ይገኛሉ። ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በሀገራችን እስካሁን ድረስ ባዮቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ቢውልም የዘር መል ምህንድስና ወይም /Gonotic engineering/ ገና ወደ ሥራ አልገባም። ይሁን የዘር መል ምህንድስናንም በርካታ ሙያተኞች አጥብቀው ይቃወሙታል። በኢትዮጵያ ሕግም ተቀባይነት አላገኘም። ታዋቂው ኢትዮጵያዊው ሳይነቲስት ዶ/ር ተወልደ ገብረ እግዚያብሔር ከነቃፊዎቹ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው። እንደ እርሳቸው ምህንድስናው ነባር ዘሮችን ያጠፋል ስነምህዳርን ይጎዳል በምህንድስናው የፈጠራ ባለቤት የሆኑ የምዕራብ ሳይንቲስቶች የአለምን እርሻ በቀላሉ ተቆጣጥረው የሀገሮች ሉአላዊነት ጥያቄ ላይ ይወድቃል። ገበሬዎችም የውጭ ጥገኛ እንዲሆን ያደርጋል በማለት ይከራከራሉ።

ዶ/ር አዳነ አብርሃ በበኩላቸው በዘረመል ምህንድስና አሉታዊና አዎንታዊ ጎን እንዲሁም የዘርመል አፈጣጠር አካሄድን ሲገልጹ በመጀመሪያ ጠቃሚ ዘረመል ይመረጣል፣ ከዚያም እፁ በህብረህዋስ ካልቸር (አይነቴ) ተመርጦ ይመጣል። በመቀጠል ልውጠ እፁ ሰብል ይዘጋጃል። እንደገና ጠቃሚ ባዕድ ዘረመል ተለይቶና ተቆርጦ ይዘጋጃል። ከዚያም ወደ እፅዋት ዘረመል ይከተታል። ከዚያም ተዳቅሎ ወደ ተፈለገው ሰብል ዝርያ ተላልፎ ጥቅም ላይ ይውላል። በመጨረሻም የተዘጋጀው ዘረመል በላቦራቶሪ ውስጥ በተስማሚ ባክቴሪያ ተተክቶ ይባዛል።

እዚህ ላይ ለአንባቢ ግልፅ መሆን ያለበት በባዮቴክኖሎጂ አማካኝነት አንድ የስንዴ ዘር በበሽታ እየተጠቃ ለመጥፋት ሲደርስ ወይም ድርቅን መቋቋም ሲያቅተው ከሌላ በሽታን መቋቋም ከሚችል ወይም ድርቅን መቋቋም ከሚችል ዘረመል ተወስዶና ተዳቅሎ አዲስ በሽታንና ድርቅን መቋቋም የሚችል ስንዴ ቢፈጠር ዘረመል ምህንድስና ተካሄደ ማለት አይደለም። ዘረመል ምህንድስና ተካሄደ ማለት የሚቻለው ከሁለት የተለያዩ እፅዋቶች የዘረመል ውህደት ተፈጥሮ አዲስ ሌላ ተክል ሲፈጠር ነው። ለምሳሌ ከዓመታት በፊት በኡጋንዳ ከፍተኛ የሙዝ በሽታ ገብቶ በሀገሩ ያለው የሙዝ ዘር በበሽታ ተመቶ ሊጠፋ ደርሶ ነበር። በወቅቱ ሳይንቲስቶች ብዙ ምርምር ካካሄዱ በኋላ በሽታውን ሊቋቋም የሚችል ጠንካራ ዘረመል ከድንች ውስጥ አውጥተው በላቦራቶሪ ውስጥ ከሙዝ ዘረመል ጋር አዳቀሉት። የተዳቀለው ተክልም በሽታውን መቋቋም መቻሉ ተረጋግጦ ለገበሬዎች ታድሎ እንዲተከል ተደርጎ አዲስ የቀድሞውን በሽታ የሚቋቋም የሙዝ ተክል በሀገሪቱ ተስፋፍቶ የሙዝ ዝርያ ከኡጋንዳ እንዳይጠፋ ተደረገ። በሌላ በኩል ዘረመል ምህንድስናን በእንስሳት ላይ የሚያደርጉ ሳይንቲስቶች በኢሞራላዊነታቸው በሃይማኖቶች ጭምር እየተወገዘ እንደሚገኙ ልብ ይሏል። በነገራችን ላይ የክሎን ሳይንስም ከዚሁ ጋር የሚመደብ ነው።

እንደ ዶ/ር አዳነ አገላለፅ አዲስ ቴክኖለጂ ሲነሳ ሁለት ነገሮች ይነሳሉ። አንደኛው ቴክኖሎጂም ምን ጥቅም አለው ሲሆን ሌላው ምን ጉዳት ያስከትላል የሚለው ነው። የሚሰጠው ጥቅም ሊያስከትለው ከሚችለው ጉዳት ትርጉም ባለው ሁኔታ ልቆ ሲገኝ ለመጠቀም ይወስናል። በቴክኖሎጂው የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት የቁጥጥር ስርዓት ይዘረጋል። በአሁኑ ወቅት የዘረመል ምህንድስና ቴክኖሎጂ ከማንኛውም የግብርና ቴክኖሎጂ በተሻለ ፍጥነት እየተሰራጨ የሚገኝ ሲሆን 100 በመቶ እድገት እያሳየ ይገኛል። በተቃራኒው ሌሎች ወገኖች ቴክኖሎጂው በሰው ላይና በአካባቢ ላይ ጉዳት ስለሚያስከትል መቅረት አለበት የሚል ተቃውሞ ያሰማሉ። ደጋፊዎች ደግሞ አሉታዊ ተፅዕኖ እንኳን ቢኖረው ችግሩን በቁጥጥር አሰራር መግታት ይቻላል ይላሉ። ደጋፊዎች የቴክኖሎጂውን ጠቀሜታ በተመለከተ ሲገልፁ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ያሳድጋል። በዓለም ገበያ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ ይረዳል። የምርቶችን ጥራትና ንጥረ ምግብ ይዘትን ለማሻሻል ይረዳል፣ የፀረ ተባይ ኬሚካሎች አጠቃቀምን በመቀነስ ወጭን ለመቀነስ ከማስቻሉም በላይ ለአካባቢ ጥበቃ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፣ ሰብሎችን በአስቸጋሪ አካባቢዎች ለምሳሌ ጨዋማ፣ አሲዳማ ወይም ውሃ አጠር አካባቢዎች ላይ ለማምረት ያስችላል በማለት ይከራከራሉ።

ተቃዋሚዎች በበኩላቸው የአካባቢ ብክለትን ያስከትላል፣ የባዕድ ዘረመል ፍሰት ብዘሃ ህይወትን ሊበክልና ሊያጠፋ ይችላል፣ የላቀ አረምነት ወይም ፀረ አረምን የመቋቋም ባህሪ ሊከሰት ይችላል። በሌሎች እፅዋቶች ላይ በአጠቃላይ ህያዋን ላይ ተፅዕኖ ሊያስከትል ይችላል። አዳዲስና ያልተጠበቁ በሽታዎች ወይም ተባዮች ሊከሰቱ ይችላሉ በማለት የሚከራከሩ ሲሆን በሰውና በእንስሳት ጤና ላይም አለርጂ የመቀስቀስ ባህርይ የንጥረ ምግብ ይዘት መዛባትንና አንቲባዮቲክን የመቋቋም ባህሪይን ሊያመጡ እንደሚችሉ ይገልፃሉ።

ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስጋቶችን በተመለከተም የትላልቅ ኢንዱስትሪያዊ ሀገሮች በፓተንት መብቶቻቸው አማካኝነት የእርሻ ገበያውን በሞኖፖል መቆጣጠር እንደሚችሉ፣ በተቃራኒው የደሃ ሀገር ገበሬዎች በዘረመል ምህንድስና የተገኙ ዘሮችን ከአንድ በላይ መዝራት ስለማይችሉ ለጥገኝነት መዳረጉ የሀገር በቀል ዝርያዎች ቀስ በቀስ የመጥፋት አደጋ ሊገጥማቸው ይችላል። አንድን ሰብል በሰፊ ቦታዎች ላይ በመዝራት ለበሽታ ያጋልጣል፣ በስነምግባርና በሃይማኖታዊ ምክንያቶች የተነሳ ምህንድስናው ከተፈጥሮ ጋር መጫወት ነው በሚል የበኩላቸው ነቀፌታ ያቀርባሉ። ታዋቂ የዓለም ሳይንቲስቶች በበኩላቸው ከእነኚህ ከተጠቀሱት የቴክኖሎጂው ህፀፆች ተቃራኒ በሆነ መልኩ የአሜሪካ የሳይንስ እድገት ማህበር በ2001፣ የአውሮፓ የምርምር ዳይሬክተር በ2001፣ የዓለም ምግብና ግብርና ድርጅት በ2004፣ የዓለም የሳይንስ ምክር ቤት በ2003፣ የዓለም የጤና ድርጅት በ2002 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በገበያ ላይ የዋሉ ልውጠ ህየዋን ሰብሎች በሰው ጤና ሆነ በአካባቢ ላይ ከሌሎች ከተለምዶአዊ ዘዴ ከተዳቀሉት ሰብሎች በተለየ ሁኔታ የመጡት ጉዳት የለም ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

    በሀገራችን የእርሻ ምርታማነት እንዲጨምር የማድረጉ ጉዳይ ለጥያቄ የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው የእርሻው ክፍሉ ማለትም የሰብልም ሆነ የእንስሳት ምርቱ በዘመናዊ ዘዴ ተራብቶና ተስፋፍቶ ለውጭ ገበያ መቅረብ አለበት። የውጭ ገበያ ደግሞ ተወዳዳሪነትን ይጠይቃል። መወዳደር አለመቻል ተፈላጊነት ያሳጣል አለመፈለግ ደግሞ የውጭ ምንዛሪን ማጣት ነው። ስለሆነም ባዮቴክኖሎጂን መጠቀም አስፈላጊ ነው። አሁን በስፋት እየተስፋፉ ያሉት ትልልቅ የሸንኮራና የጥጥ እርሻዎችም ቴክኖሎጂውን እየተጠቀሙ ነው። አወዛጋቢውን የዘረመል ምህንድስናን በሀገር ውስጥ መጠቀም እንዲሁም ምርቱን ከውጭ የመጠቀሙ ጉዳይ ግን አከራካሪነቱ ይቀጥላል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1256 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 844 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us