የወዳደቁ ዕቃዎችን መልሶ መጠቀም

Wednesday, 06 August 2014 14:16

በሀገራችን በተለምዶ አሮጌ ዕቃዎችን ከየመንደሩ ሰብስቦ ማደስ ወይም ወደሌላ ምርት የመቀየር ስራ የቆየ ልማድ ነው። ከዚህ አንፃር የቆራሌው ስራ ሰሪዎች በአብነት ይጠቀሳሉ። ከየመኖሪያ ቤቱ አላስፈላጊ የሆኑ የብረታ ብረት፣ ጠርሙስ፣ ቆርቆሮና የፕላስቲክ ዕቃዎችን በመሰብሰብና መርካቶ በመውሰድ ለልዩ ልዩ አገልግሎት እንዲውሉ ይደረጋሉ። ይህን መሰሉ አሠራር አካባቢ በቆሻሻ እንዳይበከል ከማድረግ በዘለለ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም አለው። ዕቃውን በመሰብሰብና በመሸጥ እንዲሁም ገበያ ውስጥ እቃዎቹ ተሻሽለውና ታድሰው እንደገና ለአገልግሎት መዋላቸው የወጪን ድግግሞሽ ከማስቀረት በተጨማሪ አላቂ ዕቃዎች ፋይዳ እንዳላቸው የሚያስገነዝብ ነው።

የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንና የአስተዳደሩ የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ ባለስልጣን አሮጌ ዕቃዎች መልሰው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ለአካባቢ ጥበቃ የበኩላቸውን እገዛ እንደሚያደርጉ በየጊዜው ትምህርት የሚሰጡ ሲሆን፤ በአንድ ቤተሰብ የሚወጣ ደረቅ ቆሻሻም የሚበሰብሰው እንዲበሰብስ ተደርጐ ሊቀልዝነት (ማዳበሪያ) እንዲውል የማይበሰብሱት ማለትም እንደ ጣሣ፣ ብረታ ብረት፣ ጠርሙስና የፕላስቲክ ውሃ መያዣዎች በአንድ ላይ ተጠራቅመው መልሰው ጥቅም ላይ በሚውልበት መልኩ እንዲወገዱ ይመክራል። ይህ መሰሉ አሰራርም ለበርካቶች የስራ ዕድልን ፈጥሯል። መልሰው ጥቅም እንዲሰጡ ሲደረግም አዲስ ዕቃ በመግዛት ሊወጣ ይችል የነበረውን ወጪ ይቀንሳል።

ከዚህ አኳያ በተለይ መበስበስ የማይችሉት የፕላስቲክ ጠርሙሶች በየቦታው ሲጣሉ በአካባቢ ላይ የሚያደርሱት ብክለትና ተዕዕኖ ቀላል አይደለም። አፈር የፀሐይ ብርሃን እንዳያገኝ በማድረግ ተፈጥሮአዊ መስተጋብርን እንዳያደርግ ከማድረግ በዘለለ በከብቶች ከተበላም እስከ ህልፈት ለሚደርግ በሽታ ያጋልጣል።

አሮጌ ፕላስቲኮች ተሰብስበው ለተለያየ ጥቅም ሊውሉ እንደሚችሉ የተረዱ በርካታ ወጣቶች በፕላስቲኮቹን በማከማቸት የተለያዩ ጌጣ ጌጦችን በመስራት ለገበያ በማቅረብ የተሻለ ገቢ በማግኘት ላይ ይገኛሉ። ፕላስቲኮቹ ተጥለው ቢቀሩ ኖሮ በአካባቢ ላይ ሊያደርሱት ይችል የነበረው ጥፋትም በዚህ አጋጣሚ ሊወገድ ችሏል።

አቶ ይስሃቅ አብርሃ በሃያዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢንጂነሪንግ ዲፓርትመንት የዘንድሮ ተመራቂ ሲሆን፤ የተለያዩ ጥናቶችን ለማካሄድ ፕሮጀክት ቀርጾ ወደ ስራ ለመግባት እየተዘጋጀ ነው። ስራውም አሮጌ ፕላስቲክ ጠርሙሶችን በመሰብሰብና በማከማቸት ፈጭቶ ለፋብሪካዎች በግብአትነት ማገልገል የሚችልን ፓሊስተር ፋይበር (ቀጫጭን የፕላስቲክ ክሮችን) በማምረት ለገበያ ማቅረብ ነው። በዚህ ስራው ለተወሰኑ ሰዎች የስራ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን፤ አካባቢ በብክለት እንዳይጐዳም የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል።

እንደ አቶ ይስሃቅ ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅት ፕላስቲክ ጠርሙሶች በጣም እየተበራከቱ ነው። ቀደም ሲል ሃይላንድ ተብሎ ለሚታወቀው የተፈጥሮ ውሃ ማሸጊያነት ያገለግል የነበረው ፕላስቲክ ለበርካታ ለስላሳ መጠጦች ማለትም ለአንቦ ውሃ፣ ለኮካ፣ ለፋንታ፣ ስፕራይት፣ ቶኒክ ወዘተ ጥቅም ላይ ውሏል። እነኚህ ምርቶች በፕላስቲክ መታሸጋቸውን በርካታ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ቢቃወሙም ምርቶቹ ግን ተስፋፍተው ከከተማ እስከ ገጠር ዘልቀዋል። በከተማ የውሃ ቱቦዎችን በመድፈን በየሜዳው በመበተን አካባቢን ይጐዳሉ። በገጠርም ከውሃ መያዣነት አልፈው በየቦታው ወዳድቀው ይታያሉ። ስለዚህ ፕላስቲኮቹ ተጥለው አካባቢን ከሚጐዱ በሚል እንደገና በመፍጨት ለፋብሪካ ምርት ግብአት ማዋል እንደሚቻል ተገንዝቦ ስራውን ለመጀመር አቅዷል፤ ለ10 ሺዎችም የስራ ዕድል ፈጥሯል።

የወዳደቁ ፕላስቲኮችን ከተለያዩ ደንበኞች ማለትም ከየመኖሪያ ቤቱ ከሚሰበሰቡ እንዲሁም ከቆሼና ከገንዳ ከሚሰበሰቡ ያገኛል። ፕላስቲኮቹም ተሰብስበው ወደ መፍጫ ማሽን ውስጥ ይገባሉ። ከተፈጩ በኋላም እንደገና ወደ ማፅጃ ማሽን ውስጥ እንዲገቡ ተደርገው በተገቢው ሁኔታ ከፀዱ በኋላ በዚያው ማሽን አማካኝነት ወደ ፓሊስተር ፋይበር (ክርነት) ተቀይረው ለፋብሪካዎች በግብአትነት እንዲላኩ ይደረጋሉ። በርግጥ በአሁኑ ወቅት ፕላስቲኮችን ከተለያዩ ደንበኞች ማሰባሰቡ ጊዜ መውሰዱ እንዲሁም በተበታተነ መልኩ መምጣታቸው ስራውን በተቀላጠፈ መልኩ ላለማከናወን እንቅፋት ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አለ። ፕላስቲኮቹ የሚፈጩትም ሆነ ፀድተው ወደ ክርነት እንዲቀየሩ የሚደረጉት በሀገር ውስጥ ማሽን አምራቾች በተመረቱ ማሽኖች ሲሆን፤ ለማሽን መግዣ የሚወጣ የውጭ ምንዛሬ አይኖርም። ከዚህ ጎን ክሮችን ለማጽዳት የሚያገለግለው የሶዳ ኬሚካል ከሀገር ውስጥ ገበያ መገኘቱ ስራውን ያለ ብዙ ውጣ ውረድ ለማከናወን ያስችላል።

ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ ራዕዩን ለማሳካት እንዲሁም ወደፊት ምርቱን ደረጃ በደረጃ ለማስፋት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፤ የስራ ዕድሉንም ለማስፋት ይተጋል። አሁን ላለው የስራ እንቅስቃሴም የመፍጫና የማፅጃ ማሽኖችን ከሀገር ውስጥ ገበያ ለመግዛት 240 ሺህ፣ ለቢሮ ቁሳቁሶች 40 ሺህ፣ ለሰራተኞች ደመወዝና ሌሎች ወጪዎች 25 ሺህ፣ ለሠራተኞች ጫማና ጓንት 25 ሺህ፣ በጠቅላላው 330 ሺህ ብር ወጭ አድርጓል። የፕላስቲክ ጠርሙሶቹ በሚፈጩበት ወቅት እንደሌሎች ሀገሮች ከታች ከወገባቸው ከላይ ጫፍ ተከፋፍለው አይቆራረጡም። እንዳለ ይፈጫሉ። ከተፈጩ በኋላ ወደ ዱቄትነት ከተቀየሩ በኋላ እንደገና ወደ ክርነት ይቀየራሉ። ይህ ፓሊስተር ፋይበር የተባለው ምርት ፋብሪካ ውስጥ በግብአትነት ከገባ በኋላ ለፕላስቲክ ወንበሮች፣ ጠረጴዛዎች፣ ትራስና ጫማዎችን ለማምረት ያስችላል።

ፕላስቲኮቹን የሚፈጩትና የሚያፀዱት ማሽኖች የሚሰሩት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ በመሆኑ ምንም የሚያቃጥሉት ነዳጅም ሆነ ወደ ከባቢ አየር የሚለቁት ጢስ የላቸውም። የሚያሰሙት ድምጽም አካባቢን የሚያውክ አይደለም። በርግጥ የዚህ መሰሉን ስራ ሌሎች ድርጅቶችም እንደሚሰሩት በእለቱ ከተነገረው ገለፃ ለመረዳት ችያለሁ። ነገር ግን ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በአሁኑ ወቅት በርካታ የለስላሳ ፋብሪካ መጠጦች ምርቶቻቸውን በፕላስቲክ ጠርሙሰ በማሸጋቸው አገልግሎት የሰጡ ፕላስቲኮች በስርዓት የሚሰበሰቡ ከሆነ በዚህ መሰሉ ስራ ለበርካታ ወገኖች የስራ ዕድል ለመፍጠር ይቻላል። ከዚሁ ጐን ለጐን በአዎንታዊነት መታየት የሚገባው የመፍጫና የማጽጃ ማሽኖች እንዲሁም ኬሚካሉ በሀገር ውስጥ መመረቱ በሀገራችን አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ሊያብቡ እንደሚችሉ ምልክት የሚሰጥ ሲሆን፤ የውጭ ምንዛሪ ከማዳን አንፃር ያለው ፋይዳም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በአሁኑ ወቅት ለአለማችን አካባቢ መበከል ምክንያት እንዲሁም ለተፈጥሮ ሀበት መመናመንና መውደም ምክንያቱ ሰዎች የፍጆታ መጠናቸው ከፍተኛ ከመሆን ባሻገር ጥቅም ላይ የዋሉ አላቂ ዕቃዎች ብዙ ሳያገለግሉ መጣላቸውና ተመልሰው ጥቅም ላይ እንዳይውሉ መደረጋቸው ነው። በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በየመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ለቢሮ መገልገያ የሆኑ ቁሳቁሶች ኮምፒውተሮች፣ ላፕቶፖችና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጥቶባቸው ወደ ሀገር ይገባሉ። ሌሎች የግል መጠቀሚያ ሞባይል ስልኮች፣ ቴሌቭዥኖችና መሰል ዕቃዎችም ከሀገራችን አቅም አንፃር ውድ በሆነ ዋጋ ተገዝተው ነው የሚመጡት። ጥቂት አገልግለው ያለ ጥቅም ሲቀመጡ ይበላሻሉ። ከዚያም እንደአልባሌ ነገር መጣላቸው ከከባቢ አየር እና ከአፈር ጋር ኬሚካላዊ ውህደት በማድረግ ለአካባቢ ብክለት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። በተለይ የዚህ መሰሉ ዝርክርክ አሰራር በመንግስት መስሪያ ቤቶች በስፋት ይስተዋላል። አሮጌ ዕቃዎች ከወጣባቸው ገንዘብ በላይ ሲጣሉ በአካባቢ ላይ የሚያደርሱት ጥፋት በአብዛኛው ሰው ዘንድ ግንዛቤ አላገኘም። ከዚህ በተጨማሪ ዕቃዎችን ለመተካት እንደገና የሚወጣው የሀገር ሀብት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ስለሆነም ማናቸውንም አላቂ ዕቃዎች በአግባቡ እስከመጨረሻው መጠቀም ከዚያ በኋላ ደግሞ መልሶ መጠቀም (Recycle) የማድረጉ ባህል እንዲዳብር ቢደረግ ወጭን ከመቀነስ ባለፈ የአካባቢን ብክለት መታደግ ያስችላል። ከዚህ አኳያ እንደ ወጣት ይስሃቅ የመሰሉ የፈጠራ ባለሙያዎችን ማበረታታት ግድ ይላል።

ወጣት ይስሃቅ የሚያመርታቸውን የፓሊስተር ክሮች ገበያ ትስስርን በተመለከተ ሲገልፅ የመጀመሪያው የምርቱ ደንበኛ ኦርል ኢንተርናሽናል የተባለ የፕላስቲክ ማምረቻ ፋብሪካ ነው። ፋብሪካው አንድ ኪሎ የፕላስቲክ ክርን በስልሳ ብር ይገዛል። ሌላው የምርቱ ደንበኛ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ሲሆን፤ ጽህፈት ቤቱ ምርቶቹን ለተለያዩ ሸማቾች የሚያቀርቡለትን ደላሎች ያቀርቡለታል። በዚህ አማካኝነት ሲያቀርብ ምርቱን በቅናሽ ያቀርባል። ከዚህ ውጭ ባሉት ትላልቅ ድርጅቶች ግን አንዱን ኪሎ በስልሳ ብር ያቀርባል። የወጣት ይስሃቅ የማምረቻ ድርጅት ከሌሎች ፕላስቲኩን መልሰው ጥቅም ላይ ከሚያውሉ በምን እንደሚለዩ ተጠይቆ ሲመልስ ሌሎቹ ምርቶቻቸውን በወቅቱ ከፈላጊዎች እንደማያደርሱ የርሱ ግን ቶሎ እንደሚያደርስ ከዚህ በተጨማሪም እርሱ በተለይ ክሮቹን በሶዳ ኬሜካል አጥቦ ለደንበኞቹ ማቅረቡ የምርቱ ጥራት የተጠበቀና ተመራጭ እንዲሆን ማስቻሉን አመልክቷል።

ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተም የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አስፈላጊውን የማምረቻ ቦታ አዘጋጅቶ የሰጠው ሲሆን፤ የውሃና ኢነርጂ ቢሮም የምክር ድጋፍ አድርጐለታል። መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ተሞክሮአቸውን እንዲሁም የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎችን አበርክተውለት የዕውቀት አድማሱን አስፍተውለታል። ከዚህ በተጨማሪ በትምህርት ገበታው ላይ ያደረገው ጥናትና ምርምር ከፍተኛ እገዛ አድርጐለታል። ይህ ወጣት በያዝነው ዓመት ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ስራ ፍለጋ የትምህርት ማስረጃዎቹን ወደ ቀጣሪ መስሪያ ቤቶች አልበተነም። በሙሉ ልብና በራስ መተማመን የራሱን ኢንተርፕራይዝ ነው ያቋቋመው። ይህም ለሌሎች ወጣቶች አርአያ የሚሆን ነው። ስራውን ከ350 ሺህ ብር ባነሰ ገንዘብ መጀመሩም ተነሳሽነቱ ካለ በሀገራችን ብዙ ስራዎች ሊሰሩ እንደሚችሉ የሚጠቁም ሲሆን፤ የስራ ዕድል ፈጠራውም በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ አካባቢን ከጥፋት በመታደግ ለፋብሪካዎች ግብአት በማቅረብ ገቢን መፍጠር የሚያስችል ነው። ስለሆነም መበረታታት የሚገባው ነው።

መንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ከእነ ይስሃቅ ተሞክሮ ሌሎችም በመስኩ እንዲሰማሩ ዕውቅና መስጠትና የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ሊያደርጉ ግድ ይላል።  

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1334 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 997 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us