በኦሮሚያ ክልል የአዶላ ወረዳ አነስተኛ ገበሬዎች የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ ስልቶች

Wednesday, 13 August 2014 13:40

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በእርሻ መመራቱ እንደቀጠለ ነው። ይህም በተጨባጭ የሚረጋገጠው ዘርፉ ለሀገር ጠቅላላ ምርት /GDP/ የሚያበረክተው 41 በመቶ መሆኑ ሲሆን ለውጭ ገበያ ምርቶችን በማቅረብ ረገድ 60 በመቶ ነው። የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ደግሞ 85 በመቶ እንደሆነ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በ2010 እ.ኤ.አ ያወጣው መረጃ ያመለክታል። በዚህም የተነሳ መንግሥት የእርሻው ዘርፍ ለማናቸው ኢኮኖሚ እድገት መሠረት መሆኑን ተቀብሎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን (G+P) ዕቅድም ለእርሻ ኢኮኖሚ በዚያው እንዲቀጥል በማድረግ ድህነትን ለመቀነስ እንደሚቻል ግንዛቤው ተወስዷል።

ከዚሁ ጋር በተመሳሳይ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ በእድገትና ትራንስፎርሜሽኑ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል። ለዚህም ምክንያቱ ጉዳዩ ከሀገራችን አልፎ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አጀንዳ በመሆኑ ነው። የሰው ልጅን ህይወትም በመፈታተን ላይ ይገኛል። ያልተጠበቀ የአየር ንብረት ለውጥና ሙቀት መጨመር በሀገራችን እርሻ ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደሆነ በተደጋጋሚ ተገልጿል። ይህም በራሱ በትራንስፎርሜሽኑ ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚያሳርፍ ይታመናል።

አቶ አስቻለው ሽፈራው በኢንቫይሮሜንታል ኢኮኖሚ የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን ከበርካታ ዓመታት በፊት ጀምሮ በአክሱም ዩኒቨርስቲ ውስጥ በማስተማርና በምርምር ሥራ ተሰማርተው ይገኛሉ። ከሰሞኑም በከተማችን ኢንቫይሮሜንትን በተመለከተ በተካሄደ ስብሰባ ላይ በኦሮሚያ ወረዳ የአዶላ ወረዳ አነስተኛ ገበሬዎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እየተከተሉት ያለውን ስልት በተመለከተ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል። እንደእርሳቸው ገለፃ የአየርንብረት ለውጥ በእርሻ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ በአንድ ወቅት ብቻ ተከስቶ የሚቆም አይደለም። በተከታታይ የሚያጋጥምና የእርሻ ምርትን የሚያሽመደምድ ነው። ይህ ሁኔታም ገጠሬውንና ይበልጥ ተጋላጭ የሆነውን ክፉኛ ይጎዳል። አንዳንድ ጥናቶች እንዳረጋገጡትም ሁኔታዎች መፍትሄ ካላገኙ በ2020 የደሃ ሀገሮች የእርሻ ምርት እስከ 50 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል አለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ፓናል በቅርቡ የወጣው መግለጫ ያመለክታል።

የአዶላ ወረዳ ከአዲስ አበባ በስተደቡብ 457 ኪ.ሜትር ላይ ትገኛለች። በስተምስራቅ ከገርጀ ወረዳ ከሰሜን ምስራቅ የአሰናሶራ ወረዳ ከሰሜን ምዕራብ ከኦዶሻሻኮ ከዋደራ ወረዳ በስተደቡብ ትዋሰናለች። በአጠቃላይ የቆዳ ስፋትዋ 140 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ነው። አብዛኛው የወረዳው የመሬት አቀማመጥ ገደላማና ኮረብታማ ነው። ከባህር ወለል ያላት ከፍታም ከ1500 እስከ 2000 ሜትር የሚደርስ ነው። እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ገበሬ የአካባቢው አስተራረስ ዘዴ ባህላዊውንና ሞፈር ቀንበርን የሚጠቀም ነው። የበሬ ጉልበት በእርሻ ዝግጅት በተከላና በመኸር ወቅት በብዛት ጥቅም ላይ ይውላል። በወረዳው ያለው እርሻ ሙሉ በሙሉ የዝናብ ጥገኛ ነው። ነገር ግን አንዳንዶች የእርሻ ገበያቸውን ለመደጎም በሚል ከቦታ ወደ ቦታ በመዘዋወር የአርብቶ አደርነት ስራ ያከናውናሉ። የወረዳው ገበሬዎች በመኸርና በበልግ ወራት የተለያዩ እህሎችን ያመርታሉ። ለምሳሌም ጤፍ፣ ገብስ፣ በቆሎ፣ ባቄላ እንዲሁም ከፍራፍሬ ውስጥ ብርቱካን፣ ሙዝ እንዲሁም የቅጠላ ቅጠል ምግቦችን ያመርታሉ። ከዚህ በተጨማሪም ለኑሮአቸው መደጎሚያ እንዲሆን ቡናን አምርተው ለገበያ ያቀርባሉ። ለወደፊቱ ወረዳው የከብት ርባታን በከፍተኛ ደረጃ ለማርባት የሚያስችል ነው።

አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የአየር ንብረት ለውጥ ብዙ ዘርፎችን በሚያጠቃልል መልኩ ጉዳትን ያስከትላል። ለምሳሌ የውሃ ሃብትንና እርሻን የምግብ ዋስትናን መሰረተ ልማቶችን፣ ስነምህዳርን ብዝሃ ህይወትንና ጤናን ያውካል። ከዚህ በተጨማሪ በዝናብ ጥገኛ የሆነ እርሻን ይበልጥ ይጎዳል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተለዋዋጭ እንደመሆኑ በሂደት ሲመዘን የአየር ርጥበት ለመሬት ገፅ ሽፋን በሚሰጡ እፅዋቶች እንዲሁም በአዝዕርት ስርጭት ላይ ጫና ከማሳደሩም በላይ እየቆየ ሲሄድ ዝናብ እስከመጥፋት በማድረስ በሽታዎች እንዲቀሰቀሱ ያደርጋል። ከዚያ ሲያልፍም በተፈጥሮ ሀብት መመናመን የተነሳ በማህበረሰብ መካከል የእርስ በርስ ግጭት እንዲቀሰቀስ በር ይከፍታል። ይህም በአጠቃላይ ኢኮኖሚውን ይጎዳል። ችግሩን ለመቋቋም አቅም ከሌለም ሁኔታው ይባባሳል።

በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ሲከሰት የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት የሆነው እርሻው ሲጎዳ የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርቱ እንደሚቀንስ የአለም ባንክ የ2011 ጥናት አመልክቷል።

የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋምና መላመድ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ የሆኑ ዘዴዎች ናቸው። ለመቋቋም አየርን ሊባክሉ የሚችሉ የኢነርጂ ግብአቶችን በታዳሽ ሃይል መቀየር ለምሳሌ ነዳጅና ቤኒዚንን በመተው ኤሌትሪክን፣ ንፋስን፣ ፀሐይን እንዲሁም በዩፊውልና ባዮጋዝን መጠቀም ሲሆን በዚሁ ደንን በማደንና በማስፋፋት በከባቢ አየር ውስጥ በካይ ጋዝ በደኑ አማካኝነት እንዲመጠጥ ማድረግ ነው። በሌላ በኩል ችግሩን ለመላመድ የሚቻለው መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት ለምሳሌ መንገዶችን፣ የውሃ አቅርቦትን ክሊኒክን ትምህርት ቤትን የመሳሰሉትን ማስፋፋት ችግሩ ቢከሰት አስፈላጊው ርዳታ በወቅቱ እንዲደርስ ማድረግ የመላመጃ ዘዴዎች ናቸው።

ጥናት አቅራቢው አቶ አስቻለው ሽፈራው በአካባቢው የአየር ንብረት ለውጥ መኖር አለመኖርን እንዲሁም እንዴት እንደሚረዱት ለገበሬዎቹ መጠይቅ አቅርበው ነበር። ከተጠየቁት 77 በመቶ የሚሆኑት በወረዳው የዝናብ መጠንና ወቅታዊ ሙቀት እንደጨመረ የገለፁ ሲሆን 23 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የዝናብ መጠኑ በከፍተኛ ደረጃ እንደቀነሰ ተናግረዋል። የገበሬዎቹ መልስ የተለያየ ሊሆን የቻለውም የገበሬዎቹ አካባቢ የተለያዩ ማለትም ቆላ፣ ወይናደጋ እና ደጋ በመሆኑ ነው። ስለሆነም የአየር መዛባቱና ስርጭቱ እንዲሁም የዝናብ መጠኑ ከቦታ ቦታ ሊለያዩ ችሏል። በአጠቃላይ አብዛኛዎቹ ገበሬዎች የአየር ንብረት ሙቀቱ እንዲጨመረ፣ የርጥበት አዘል አየር ደግሞ እጅግ እንደቀነሰ ተናግረዋል። በተለይ ባለፉት 10 ዓመታት ማለትም እ.ኤ.አ ከ2000 እስከ 2010 ድረስ የአየር መዛባቱ በስፋት ተከስቷል። የክረምት ወቅት ዝናብ ለዘመናት ለእርሻ ምርታቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረው። ነገር ግን ባለፉት አመታት አማካይ የዝናብ መጠኑ በእጅጉ ቀንሷል። ይህም የገበሬዎቹን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ክፉኛ ጎድቷል።

ከዚህ በተጨማሪ በወረዳው ቀን ቀን የሙቀት መጠኑ ከፍተኛ ደረጃ እንደጨመረ ማታ ማታ ደግሞ የዚያኑ ያህል ከባድ ቅዝቃዜ እንዳለ ጠቅሰው የንፋስ መጠኑም እንደዛው ከባድ እንደሆነ ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋምና መላመድ በመንግስት ተቀባይነት አግኝቶ የሚተገበር ድርጊት ነው። ይህም ከፌዴራል መንግስት ጀምሮ እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ በፈፃሚዎችና በባለ ድርሻ አካላት አማካኝነት የሚተገበር ነው። ለዚህ እንዲያግዝ የመረጃ ልውውጡና በኤክስቴንሽን ሠራተኞች የሚደረገው እገዛ የላቀ ሚና ይኖረዋል። በተለይ የሜትሮሎጂ አገልግሎት በዚህ ረገድ የሚጠቀስ ነው። ይህ ትንበያ ገበሬዎች ስለ አካባቢያቸው የአየር ፀባይ ከሶስት ወር ቀድመው እንዲገነዘቡና የበኩላቸውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው። እንዲያም ሆኖ የገበሬዎች ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው።

እንዲያም ሆኖ የገበሬው የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም አቅም በተለያዩ ሁኔታዎች ተፅዕኖ ስር የወደቀ ነው። በተለይ የገበሬዎች ከእርሻ ውጭ ገቢ የማፍራት አቅማቸው የምርታማነታቸው መጠን፣ የትምህርት ደረጃቸው የእርሻው መሬት ስፋት ከብት አርቢ ከሆኑ የከብታቸው መጠን ብድር የማግኘት አቅማቸው የገበሬዎች የርስ በርስ ትግግዝ ችግሩን ለመላመድ እጅግ ወሳኝ ነው። ከዚህ በተቃራኒ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ገበሬዎች ችግሩን ለመላመድና ለማንሰራራት ያላቸው እድል ጠባብ ነው። በሌላም በኩል የተሻሻሉ የእህል ዘር የሚጠቀሙ እንዲሁም የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን ከብት የሚያረቡ አግሮፎረስትሪን (እርሻና ደን ልማትን) የሚያካሂዱ የውሃ እና የአፈር ጥበቃ በተሻለ መልኩ የሚያካሂዱና አነስተኛ መስኖ የሚጠቀሙና ወደ ሌላ አካባቢ በመሄድ የተገኘውን ስራ የሚሰሩ ችግሩን የመላመድ አቅማቸው ከፍተኛ ነው። ይሁን እንጂ ይህ የመላመድ ዘዴም በህዝብ የእድሜ መጠን ስርጭት በማህበራዊ ኢኮኖሚ ጥንቅርና በተቋማዊ ሁኔታ የሚወሰን ነው። በመሆኑም መንግሥት ችግሩን ለመላመድ ዘዴዎችን ከመተግበሩ በፊት ከላይ የተጠቀሱትን ቅድመ ሁኔታዎች ማጤን ይኖርበታል። ለዚህ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ችግሮችን በመለየት መፍትሄ መስጠት ተገቢ ነው።

የጥናት አቅራቢው አቶ አስቻለው በአዶላ ወረዳ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ በተመለከተ ከገበሬዎች ባገኙት መረጃ መሠረት የአየር ንብረት ለውን ተገንዝበው ችግሩን ለማላመድ የሚያስችለውን ርምጃ ለመውሰድ ተነሳሽነቱና ፍላጎቱ ያላቸውንና እስካሁን ያላቸውን ተሞክሮ ጠይቀው እንደተረዱት አሁን እስካሉበት ድረስ የመላመድ ዘዴዎችን ተግብረዋል።

በዚህም መሠረት የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን ለእርሻቸው የተለያዩ የከብት ዝርያዎችን ለርባታ መጠቀምን ለአየር ንብረትን ለመላመድ ከፍተኛ ሁኔታ መተግበራቸውን ለመረዳት ተችሏል። የዕፅዋትና የእህል ዝርያዎችን በሌላ መተካትና የውሃ እና የአፈር ጥበቃም በሁለተኛና በሶስተኛ ደረጃ የተተገበሩ ስልቶች ናቸው። እንዲያም ሆኖ በወረዳው አንዳንድ ችግሩ ባስ ያለባቸው ገበሬዎች አካባቢያቸውን በመልቀቅና በሌላ ቦታ የተገኘውን ስራ መስራትና ራስን ማስተዳደር እንደ አማራጭ ወስደዋል።

በአጠቃላይ በወረዳው የተሻሻለ ምርጥ ዘሮችንና የእንስሳት ዝርያዎችን መጠቀም የሰብል የመትከል ወቅትን መቀየር ውሃ እና የአፈር ጥበቃ ማካሄድ እንዲሁም በማዳበሪያ አማካኝነት ሰብሎች በቶሎ እንዲደርሱ የማድረጉ ስራ በከፍተኛ ደረጃና በበርካታ ገበሬዎች ተከናውነዋል። ዛፎችን ለጥላ መትከልና አነስተኛ መስኖን መጠቀም እንዲሁም የከብቶችን ቁጥር መቀነስ በሁለተኛ ደረጃ ተከናውነዋል።

እንደ ጥናት አቅራቢው በወረዳው የአየር ንብረት ለውጥንና ሙቀት መጨመርን ለመቋቋም እንደ ችግር የሚስተዋሉት ስለሁኔታው በገበሬዎች ዘንድ በቂ እውቀት አለመኖር በቂ የእርሻ መሬት አለመኖር፣ በቂ ካፒታልና መረጃ አለማግኘት በዋንኛነት የታዩ ናቸው። ከዚሁ ጋር የመንግስት አካላት ለጉዳዩ ትኩረት መንፈግ ችግሩ እንዲባባስ አድርጓል።

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው እርሻው በተለይም ከእጅ ወደ አፍ የሆነ አመራረትን የሚጠቀመው ዘርፍ የኢኮኖሚው የጀርባአጥንትና 83 በመቶ ለሚሆነው ህዝብ መተዳደሪያ ቢሆንም የዝናብ ጥገኛና ለተለዋዋጭ አየር ንብረት የተጋለጠ መሆኑ እሙን ነው። እርሻው በብዙ ድካምና ጉልበት ታርሶ እህል ቢዘራም ዝናብ ከቀረ የተለፋው ሁሉ ለፍቶ መና ይሆናል። ይህም ገበሬውን ለተረጂነት ከመዳረግ ባሻገር ለመፈናቀል ይዳርጋል። ከዚህ ሲያልፍ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲሽመደመድ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ድህነት እንዲባባስና ኑሮ እንዲወደድ ያደርጋል። ስለሆነም ለገበሬው የእርሻ ግብአት ከማቅረብ ጎን ለጎን የአየር መዛባትን ለመቋቋምና ለመላመድ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ተገቢ ነው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1016 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 931 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us