የወንዶ ገነት ከተማ ትኩረት አስፈልጓታል

Wednesday, 20 August 2014 13:31
  • አረንጓዴው ውብ ገፅታዋ በረሃማነት አንዣቦበታል

በመድሃኒት ረዳ


በደቡብ ክልል የሲዳማ ዞን ውስጥ ከሚገኙ የገጠር ወረዳዎ አንዷ ናት። እጅግ ውብ በሆነው የተፈጥሮ ፀጋዋ የምትታወቀው የወንዶ ገነት ወረዳ ከሐዋሳ በ23 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ስትገኝ ወይናደጋማ የሆነ የአየር ንብረት ያላት፤ በቱሪስት መዳረሻነቷ አንዷ ብዙዎቻችን እናውቃታለን። በሀገሪቱ ካሉ የቱሪስት መዳረሻ ከተማዎች ወደሆነችው ወደ ሐዋሳ ከተማ ለሥራ፣ ለመዝናናትም ሆነ በአጋጣሚ የሚመጡ ሁሉ በወንዶ ገነት ተፈጥሯዊ ፍል ውሃ መንፈሳቸውን ዘና ሳያደርጉ እንደማይመለሱ ይናገራሉ።

የወንዶ ገነት ከተማ ስያሜዋን ያገኘችው ከቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ እንደሆነ ይነገራል። ከዚያ ቀደም “መልጊያ ወንዶ” የሚል መጠሪያ የነበሯት የወንዶ ገነት ከተማ በተፈጥሮ ውበት አድናቂነታቸው በሚነገርላቸው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በ1940ዎቹ “ወንዶ ገነት” የሚል መጠሪያ ማግኘቷንና አካባቢውም ለልጃቸው ተናኘወርቅ ባለቤት ራስ ደስታ ዳምጠው መታሰቢያ እንደነበረ የአካባቢው ቀደምት ነዋሪዎች ይናገራሉ። በዚህ ድንቅ የተፈጥሮ ገፀ በረከት በታደለው አካባቢ ጊዜያው የንጉሡ ቤተመንግስተ ተሰርቶ የነበረ ሲሆን እስከ አሁን ድረስ ይህ ታሪካዊ መስህብ ዋነኛ የአካባቢው የቱሪስት ገቢ ማስገኛ በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛል።

የወንዶ ገነት ከተማ ከሌሎች አካባቢዎች ለየት የሚያደርገው ድንቅ የተፈጥሮ ገፅታ አላት። እጅግ ጥቅጥቅ ያሉ ሀገር በቀል ዛፎች፣ የተለያዩ የአእዋፋትና የእንስሳት ዝርያዎች፣ ለመስኖ አገልግሎት የሚሰጡ ከመቶ በላይ ምንጮችና ወንዞች፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ጫት፣ ሸንኮራና መሰል የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ከመሆኗም በላይ ዙሪያዋን ከከበቧት ተራራዎች ላይ ቀዝቃዛና ፍል ውሃዎችን በአንድ ጊዜ የምታመነጭ ተፈጥሮ ሁሉን የቸራት ልክ እንደስሟ ምድራዊ ገነት ብትባል የማይበዛባት ከተማ ናት።

በረሃማነት ያንዣበበባት የወንዶ ገነት ከተማ

ከላይ በጥቂቱ ለመግለፅ የሞከርኳት የወንዶ ገነት ከተማን በቅርብ ጊዜ የተመለከታት አንባቢ በዚህ ፅሁፍ ተአማኒነት ላይ ጥርጣሬ እንደሚገባው አልጠራጠርም። ምክንያቱም ከላይ የዘረዘርኳቸው የወንዶ ገነት ገፅታዎች ከአምስት ዓመታት በፊት የነበሩ አሁን ግን ትዝታዎቻቸው ብቻ የቀሩ በመሆናቸው ከተመለከትኳት ከጥቂት ዓመታት ቆይታ በኋላ ነው በሥራ ወደ ሐዋሳ ከተማ በሄድኩበት አጋጣሚ በሥራ የዛለውን አእምሮዬን ድንቅ በሆነው የወንዶ ገነት ተፈጥሯዊ ገፅታ እና ፍልውሃ ዘና ለማድረግ በማሰብ በሥፍራው የተገኘሁት።

ከሐዋሳ ከተማ በስተምዕራብ በኩል 23 ኪሎ ሜትር ተጉዤ ወንዶ ገነት ከተማ ስደርስ ግን አይኔ ያየውን ነገር ለማየት ተቸግሯል። የአይን ማረፊያ የሆኑት ደኖቹ ተራቁተዋል። ዙሪያውን በአረንጓዴ ተውበው የከበቧት ተራሮች እርቃናቸውን ቀርተው አረንጓዴ መጎናፀፍያቸው ወደ አፈርነት ተለውጧል። በየሰፈሩ በየመንደሩ ሲግተለተሉ ይታዩ የነበሩት የሰው ህይወት የሚያድሱ ምንጮቿ ደርቀዋል። የአይን ማረፊያና የመንፈስ ምግብ የሆነው አትክልትና ፍራፍሬ ዛፎች ተመናምነዋል። ይህንን ስመለከት ውስጤ እጅጉን አዘነ። ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ በእጅጉ ጉጉት አደረብኝ በዚያ አካባቢ ያገኘኋቸውን አንዳንድ ነዋሪዎች ስለሁኔታው ጠየኳቸው። ካነጋገርኳቸው ሰዎች መካከል በፍል ውሃው ሲዝናና ያገኘሁት ወጣት ሰለሞን አብርሃም ይባላል። ስለሁኔታው እጅግ ሀዘንና ቁጭት በተሞላበት መንፈስ እንዲህ አለኝ። “ተወልጄ ያደኩት በዚህ አካባቢ ነው። አሁን ግን በሥራ ምክንያት ራቅ ብያለሁ። ለረዥም ጊዜ በሥራ ስላሳለፍኩኝ በልጅነት ስቦርቅበት ያደኩበት ከተማ ላይ መንፈሴን ለማዝናናት ነበር የተመለስኩት። ስመለስ ግን ምንም ነገር በነበረበት አልጠበቀኝም። ባየሁት ነገር ግን በቃላት መግለፅ ከምችለው በላይ አዝኛለሁ” አለኝ። እንባ ባቀረሩ አይኖቹ እሩቅ አሻግሮ እየተመለከተ። “ልጅ ሆነን” አለኝ ከቆመበት በመቀጠል “ልጅ ሆነን ይህ አካባቢ ጥቅጥቅ ያለ ደን ነበር። ፍራፍሬ በየመንገዱ የሚወድቅ እንጂ የሚሸጥ እንኳን አልነበረም። በየሰፈራችን ባሉ ወንዞች እየዋኘን ነው የልጅነት ጊዜያችንን ያሳለፍነው። አሁን ግን አካባቢውን ተዟዙሬ ብፈልግ እነዚያን ምንጮችና ወንዞች ከጥቂቶቹ በስተቀር የሉም፤ ምን እየተካሄደ እንዳለ ግራ ይገባል” አለኝ በትካዜ።

ሌሎቹም ነዋሪዎች የወጣት ሰለሞንን ሃሳብ የሚጋሩ ናቸው። በተፈጠረው ነገር ከፍተኛ ትኩረት ካልተሰጠ ገነት የነበረችው የወንዶ ገነት ከተማ ፍፁም በረሃማ ወደ መሆን እየተቀየረች ነው በማለት። ይህ ነገር እንዲህ እንደዋዛ አይቼ የማልፈው ጉዳይ አልሆንልሽ አለኝ። ዓለም ወደ አረንጓዴ አብዮት ፊቱን ባዞረበት ዘመን ያሉንን አረንጓዴ ሥፍራዎች ማጣታችን ውስጤን በእጅጉ ከነከነኝ። ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ብዬ ያሰብኳቸውን መሥሪያ ቤቶች ለማነጋገር በማሰብ ወደ ቢሮዋቸው እያጠያየኩ አመራሁ። ይሁንና የሄድኩበት በእለተ ቅዳሜ በመሆኑ በሥራ ላይ ላገኛቸው አልቻልኩም ሌላ አማራጭ የነበረኝ በስልክ ማነጋገር በመሆኑ የስልክ ቁጥራቸው ከጥቂት ጥረት በኋላ አግኝቼ ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ።

ወደ አዲስ አበባ ከተመለስኩኝ በኋላ በቀጥታ ስልኬን አንስቼ የወንዶ ገነት ከተማ የግብርና ምክትል ኃላፊ ነኝ ወዳሉት አቶ ሚልኪያስ ዳንኤል ነበር የደወልኩት። ስለታዘብኩት ጉዳይ አንስቼ ጠየኳቸው። አቶ ሚልኪያስ ያነሳዋቸውን ጥያቄዎች በሙሉ እንደሚጋሩት ገለፁልኝ። ምክንያት ነው ያሉትንም የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ ለእርሻ ማስፋፊያ መኖሪያ የደኖች መመንጠር፣ ከአጎራባች የኦሮሚያ ወረዳ የህዝብ ፍልሰት፣ የግንዛቤ ማነስ ለዛሬዋ ወንዶ ገፅታ ምክንያቶች ናቸው አሉኝ።

አቶ ሚልኪያስ የደረደሩልኝ ምክንያቶች ምንም እንኳን የሚታይ እውነታዎች ቢሆኑም በቂ ስላልመሰሉኝ ይህ ሁሉ ሲሆን ለዚህ ዓላማ የተቀመጡ መስሪያ ቤቶች ምን እየሰሩ እንደሆነ መጠየቄ አልቀረም። በምላሻቸውም “ይህንን ችግር ለመፍታት ህብረተሰቡን በማወያየት ግንዛቤ እየፈጠርን ነው። በደን ውስጥ የሰፈሩ ነዋሪዎች እንዲለቁ ጥረት ቢደረግም በውስጡ የሰፈሩት ግለሰቦች በርካታ ሀብት ያፈሩና መሣሪያ እስከመማዘዝ የሚደርሱ በመሆናቸው ችግሩን አወሳስበውታል። ያም ሆኖ በደኑ ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ የሰፈሩ ግለሰቦችን ለማስለቀቅ ጥረት እየተደረገ ሲሆን በአስተዳደራዊ እርምጃ መልቀቅ ያልቻሉትን በህጋዊ እርምጃ እንዲለቁ ለማድረግ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥተን እየተጠባበቅን ነው” ብለዋል።

ሌላው በየዓመቱ በአካባቢው አዳዲስ ችግኞችን መትከል ጀምረናል ያሉት ም/ኃላፊው የወንዶገነትን ከተማ ወደ ነበር ይዘቱ ለመመለስ ዞኑ ብቻውን የሚያደርገው ጥረት ግን በቂ ይሆናል ብለን አናምንም ነው ያሉት። በመሆኑም የክልሉ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ የሐዋሳ ከተማ፣ የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ደን ኮሌጅ የምርምር ተቋም በጋራ በመሆን ርብርብ ካልተደረገ የወንዶ ገነት ከተማ ብቻ ሳይሆን ገባር ወንዞቹን ከዚህች ከተማ ከፍተኛ ሥፍራዎች የሚያገኘው የሐዋሳ ሐይቅም አደጋ ተጋርጦበታል። አሁንም ከተራቆቱ አካባቢዎች የሚነሳው ደለል ወደ ሐይቁ በመግባት ለሃይቁ ስጋት ማሳደሩን በርካታ ጥናቶች እያመላከቱ እንደሆነ አቶ ሚልኪያስ መፍትሔ ያሉትን ሐሳብ ተናግረዋል።

በአካባቢው በአሁኑ ወቅት በብቸኛነት የሚገኘው የወንዶገነት ደን ኮሌጅ የምርምር ተቋም አካባቢ የሚገኘው ጥቅጥቅ ያለ ደን መሆኑን ያስታወሱት አቶ ሚልኪያስ በዚህ ምክንያት ወደ ከተማው የሚመጣው የቱሪስት ቁጥር በእጅጉ ማሽቆልቆሉንም አልሸሸጉም።

አስቸኳይ መፍትሄ የሚያሻው ጉዳይ

     የወንዶ ገነት ከተማን ወደቀድሞ ይዘቱ መመለስ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም። የከተማዋ ዋነኛ የገቢ ምንጯን በግብርና ላይ የመሰረተችውና 148 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ለያዘችው የወንዶገነት ከተማ ለመስኖ አገልግሎት የሚውሉ የቀድሞ ምንጮቿን፣ ለቱሪስት አይን ማረፊያ የሆኑትን አረንጓዴ አካባቢዎችን መልሶ ማልማት ከምንም በፊት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው እንላለን። ከከፍታማው የወንዶ ገነት ተራሮች በሚነሱ ወንዞች ዋስትና ያለው የሐዋሳ ሐይቅን ከተጋረጠበት በደለል የመሞላት ችግር ለማዳን፤ ለተለያዩ ጥናትና ምርምር የሚውሉ እፅዋቶችን ሙሉ በሙሉ ከማጥፋት ለመታደግ ለወንዶገነት ከተማ ትኩረት መስጠት ነገ የማይባል የቤት ሥራ መሆን ይኖርበታል። “የልጅነት ትዝታችን፣ የደከመ መንፈስና አካል ማንቂያችን፣ የአእምሮ ምግባችን የሆነውን የወንዶ ገነት የተፈጥሮ ገፅታ ወደ ቀድሞ ይዘቱ መልሱልን” የአካባቢው ነዋሪዎች ተማፅኖ ነው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1383 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1048 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us