የብሪኬትስ ከሰል

Wednesday, 27 August 2014 11:16

በኢትዮጵያ በገጠር መቶ በመቶ በከተማ ደግሞ 30 በመቶ ለቤት ውስጥ ምግብ ማብሰያነት ጥቅም ላይ የዋለው የማገዶ እንጨት ነው። ይህ እንጨት ሲነድ ጭሳማ ሲሆን እሳቱም እስከ 70 በመቶ ሊባክን የሚችል ባህላዊ ምድጃን የሚጠቀም ነው። ማገዶው ባለመቆጠቡም ለሶስት ጊዜ እንጀራ መጋገሪያ የሚሆነው ማገዶ ለአንዴ ብቻ ጥቅም ላይ ይውላል። ይህም ደን በፍጥነት እንዲጨፈጨፍ የሚያደርግ ገፊ ምክንያት ነው። ጭሱም በቤት ውስጥ ማገዶውን የሚጠቀመውን ጤና ከመጉዳት ባሻገር አካባቢን በበካይ ጋዝ ይጎዳል። እንደ አለም ባንክ ጥናት የቤት ውስጥ ጭስ ብክለት ለህፃናት ህልፈትና ለመተንፈሻ አካላት በሽታ ከፍተኛውን ድርሻ ያበረክታል።

ከዚህ አኳያ ብክለትና የደን ጭፍጨፋን ለመግታት መንግስት እየተከተላቸው ካሉ አማራጭ መፍትሄዎች ውስጥ ባህላዊውን ምድጃ በቆጣቢ ምድጃ መቀየር እንዲሁም ለቡናና ሻይ ማፊያና ለወጥ መስሪያ ከወዳደቁ ገለባዎች፣ እንጨቶች፣ የጫት ገራባዎች የእንጨት ፍቅፋቂ የሚሰሩትንና በርካሽ የሚሸጡትን የብሪኬትስ ከሰሎች በስፋት መጠቀም ይገኙበታል። ይህ አካሄድም ከከተማችን አዲስ አበባ አልፎ ወደ ገጠርም እየተስፋፋ ይገኛል። ይህም ለበርካቶች የስራ ዕድል ከመፍጠር በተጨማሪ የቴክኒክና የፈጠራ ሥራ እንዲዳብር እያስቻለ ይገኛል።

አቶ ንጉሴ ፈይሳ በጉለሌ አካባቢ የተደራጀ የማገዶ ቆጣቢ ምድጃና የብሪኬትስ ክፍል አምራቾች ማህበር ስራ አስኪያጅ ናቸው። በዚህ ስራ ከተደራጁ አራት ዓመታትን አሳልፈዋል። ሲደራጁ የአባላት ቁጥር 12 ነበር፤ አሁን ግን በተለያዩ ምክንያቶች ቁጥራቸው ቀንሶ ስምንት ናቸው። ስራቸው የሚያተኩረው በኢነርጂ ቴክኖሎጂ ሲሆን የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ቀደም ሲል ከከፍተኛ ትምህርት ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ውስጥ በኢነርጂ ቴክኒክ ዘርፍ ውስጥ በኤክስፐርትነት አገልግለዋል። ይህንን ልምድና እውቀት ይዘው ነው በግላቸውና ከማህበሩ አባላት ጋር ወደ ሥራው የተሰማሩት።

እንደ አቶ ንጉሴ ገለፃ ማህበራቸው ከማንኛውም ባዮማስ ተረፈ ምርት ከቁርጥራጭ እንጨት እስከ የወዳደቁ ካርቶኖችና ረጋፊ ባህላዊ ከሰሎች ባሉት ግብአቶች የብርኬት ከሰሎችን የሚያመርት ሲሆን የከሰል ማምረቻ ማሽኑንም ራሳቸው ናቸው የሚያመርቱት። ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ አካላቶችንና ቁሳቁሶችን በመጠቀም ቆጣቢ ምድጃዎችን ያመርታሉ። ምድጃዎቹንም ለሆቴሎች ለዩኒቨርስቲዎችና ለሌሎች ተቋማት ለምግብ ማብሰያነት ያቀርባሉ።

ምርቱን ከእነርሱ ተቀብለው ወደ ሸማችና ወደ አከፋፋዮች ከማቅረብ ረገድ የተፈጠረውን የሥራ እድል አስመልክቶም አቶ ንጉሴ ሲገልፁ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የፈጠሩት እድል እንዳለ ጠቅሰው በቀጥታ ማህበሩ ቀጥሮ የሚያሰራቸው የ14 ሠራተኞች አሉ። ጊዜያዊ ሠራተኞችም እንደዚያውም በተዘዋዋሪም ማሽኑን ማህበሩ ካመረተ በኋላ ከሰል እንዲያመርቱበት ለሌሎች ማህበራት በመስጠትም የስራ እድል ፈጥረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ለምድጃዎች መስሪያ የሚሆኑ ጡቦችንና ለራሳቸው ገቢ እንዲፈጥሩ ያደረጋቸው ማህበራት አሉ። ከዚህ አኳያ ከማህበራቸው ጋር በስራ የተሳሰሩ በለገጣፎ አካባቢ የተደራጁ አምስት አባወራዎች የሚገኙ ሲሆን በሳምንት 500 ሸክላዎችን አምርተው ለእነርሱ ያቀርባሉ። በዚህም በሳምንት 5ሺህ ብር ገቢ ያገኛሉ። ሌሎች ደግሞ የብረኬትስ ከሰል እንዲያመርቱ ተደርገው ከሰሉን ከማህበሩ ቆጣቢ ምድጃዎች ጋር በማቀናጀት ለገበያ እንዲቀርብ ያደርጋሉ። ይህም ስራው ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል መሆኑን አቶ ንጉሴ ይገልጻሉ።

በመግቢያችን ላይ እንደተጠቀሰው በርካታው የሀገራችን ህዝብ ለቤት ውስጥ ምግብ ማብሰያነት ባዮማስን መጠቀሙ ለአካባቢ መራቆት የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል። የእነ አቶ ንጉሴ ማህበር ደግሞ ቢያንስ የደን ጭፍጨፋውን መጠን ለመቀነስ ቆጣቢ ምድጃዎችንና የብረኬትስ ከሰሎችን በማምረት ለገበያ ያቀርባል። ሌሎች ማህበራትም እንደዚህ ይሰራሉ። ስለዚህ ቆጣቢ ምድጃውንም ሆነ ከሰሉን የመጠቀም ባህሉ ምን እንደሚመስል የተጠየቁት አቶ ንጉሴ ሲመልሱ ቀደም ሲል ነዋሪው ሲጠቀምበት ከነበረው መሳሪያና የአሰራር አካሄድ ተላቆ ወደ አዲስ ለመሸጋገርና ለመላመድ ችግሮች ይስተዋሉበት ነበር። ነገር ግን በሂደት ህብረተሰቡ የቆጣቢ ምድጃንና ብርኬትስ ከሰሉን ጠቀሜታን ተረድቶ በስፋት በመጠቀም ላይ ይገኛል። በተለይ ከሰሉ ከባህላዊው ከሰል ጋር ሲነፃፀር ግብአቱ በርካሽ መገኘቱና ከተመረተ ባህላዊም የገበያ ዋጋው ቀላል በመሆኑ ሸማቹ እየለመደው መጥቷል። ማገዶ ሰብስቦ እና ቅጠል ከጫካ ጠርገው የሚያመጡት ጭምር ከሰሉን እየለመዱት በመምጣታቸው ወደጫካ የመሄድ መጠኑን ቀንሰዋል።

እንደ ስራ አስኪያጅ ገለፃ ለከሰል መስሪያ የሚያገለግሉ ግብአቶች አላስፈላጊ ተብለው በቆሻሻ መልክ የሚጣሉ ናቸው። ተረፈ ምርቶቹ የመፍሰሻ ቱቦን ይዘጉ የነበሩ የጫት ገራባዎች ሰጋቱራዎች ከፋብሪካ የሚወገዱ ተረፈ ምርቶች ሲሆኑ ወደ ከሰልነት መቀየራቸው አካባቢ እንደቆሻሻና እንዳይበክል አድርጓል። በአሁኑ ወቅት የብርኬትስ ከሰሉ ፈላጊው ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ የገበያውን ፍላጎት በማህበሩ አቅም ብቻ ለማሟላት አይቻልም። ስለሆነም በርካታ ወጣቶች ይህን እድል ተገንዝበው ወደ ስራው መግባት ይኖርባቸዋል።

ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ ከሚኖረው አራት ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ በግምት አንድ ሚሊዮን አባወራና ቤተሰብ ቢኖር በቀን አንድ ሚሊዮን ብርኬትስ ከሰል ያስፈልጋል ማለት ነው። ይህ እንግዲህ ለምን ያህል ሰዎች የስራ እድል ሊፈጠር እንደሚችል መገመት አያስቸግርም። ሰፊ ገበያ መኖሩንም የሚያመለክት ነው።

ሌሎች ወገኖች እንደ እናንተ ማህበር አባላት ወደ ስራው ለመግባት ያላቸው ፍላጎት ምን ይመስላል? የተባሉት አቶ ንጉሴ ሲገልፁ ከአንድ ዓመት ወዲህ ጀምሮ እያሰለጠኑ ወደ ስራው እንዲገቡ ያደረጓቸው እንዳሉ ጠቅሰው ከሰሉ በተረፈ ምርት እንደሚሰራ፣ ሲገዛም ዋጋው እርካሽ እንደሆነ፣ ከከሰለ በኋላ ግን ዋጋው በብዙ እጥፍ እንደሚጨምር ተናግረዋል። ከጫካ በተለምዶአዊው መንገድ ከስሎ የመጣው ከሰል ከጆንያ ወጥቶ ለገበያ ሲቀርብ በጆንያ ውስጥ የሚቀር ረጋፊና ደቃቅ ከሰል አለ እርሱን ባለከሰሎች ወንዝ ነው የሚደፉት። የእነ አቶ ንጉሴ ማህበር ይህን ደቃቅ ከሰል ኩንታሉን 15 ብር ገዝተው ወደ ብርኬትስ ቀይረው እስከ 800 ብር ያጣሩታል። ይህ የሚያሳየው ቢኖር ስራው በጣም አዋጭ መሆኑን ነው።

ባህላዊና ከጫካ በደን ጭፍጨፋ የሚመረተው ከሰል በርካታ ዛፎችን በመቁረጥና በማቃጠል ከፍተኛ ብክለትን ወደ ከባቢ አየር በመልቀቅ የሚከናወን ከመሆኑም በላይ በአክሳዩ ጤናም ላይ ከፍተኛ ጉዳትን ያስከትላል። በተለይ በሀገራችን ደረቃማ የደን መሬቶች /Dry wood land forests/ ለከሰል ማክሰያነት እየዋለ አካባቢ በመራቆት ላይ ይገኛል። ከሰል ሆኖ ከመጣ በኋላም በቤት ውስጥ ምግብ ማብሰያነት ሲያገለግል ከውስጡ ያለው ጭስ ሙሉ በሙሉ ከውስጡ ካልወጣ በጭሰ አማካኝነት የሚለቀቀው የካርቦን ሞኖክሳይድ ንጥረ ነገር የብዙ ወገኖቻችንን ህይወት እየቀጠፈ ጉዳት ያደርሳል።

ከዚህ አንፃር የብሪኬትስ ከሰል አከሳሰል ከባህላዊው የጫካ ከሰል አከሳሰል ጋር ሲነፃፀር የብክለት መጠኑ ምን እንደሚመስል አቶ ንጉሴ ሲገልፁ፤ ብሪኬትስ ሲያከስሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ ጠቅሰው፤ አከሳሰሉም ሦስት አይነት ደረጃዎችን እንደሚያልፍ ተናግረዋል። የመጀመሪያው ስራ ጭሱን ከተረፈ ምርቱ ለመቀነስ ዲሃይድሬት ይደረጋል። ይህም ማለት በውስጡ ያለው ውሃ እንዲወጣ ይደረጋል። ከዚያም ወደ ፍምነት ተቀይሮ ወደ ማቀዝቀዝ (ማዳፈን) ይሸጋገራል። ውሃው ከተረፈ ምርቱ እንዲወጣ ሲደረግ ጭሱ ነጭ ከለር ይኖረዋል። ወደ ፍምነት ሲቀየር ከለሩ ወደ ሰማያዊ ይቀየራል። ሲዳፈን ደግሞ ጥቁር ይሆናል። ይህ እንግዲህ ከመክሰሉ በፊት በውስጡ ያለው በካይ ንጥረ ነገር በጥንቃቄ እንዲወገድ የሚደረግበት አካሄድ ነው። ይህም ከሰል ሆኖ ገበያ ላይ ሲቀርብ በተጠቃሚው ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ነው። ከዚያም ወደ ወፍጮ ገብቶ ከመፈጨቱ በፊት ሌላ አላስፈላጊ ቆሻሻ እንዳይኖረው ተገቢ ቁጥጥር ይደረጋል። ወፍጮው ውስጥ ገብቶ ያልደረቀ ጥሬ ከሰል ከተገኘም ወፍጮው ስለማይፈጨው ጭስ የመፍጠሩ ዕድል አይኖርም። በአጠቃላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ስለሚደረግ ጭስ አይኖርም።

እንደ አቶ ንጉሴ ገለፃ፤ ማንኛውም ተረፈ ምርት ለከሰል ማክሰያ ግብአት መሆን ይችላል። ነገር ግን የአከሳሰል ዘዴው ይለያያል። የቡና ገለባና ሰጋቱራ በቀጥታ ይከስላል። እንጨት ጭራሮና ቆሻሻዎች እየተለዩ ይከስላሉ። የአትክልት ተራ ተረፈ ምርቶችም ለብቻቸው ተለይተው ለግብአትነት ይውላሉ። እሾሃማ እንጨቶችም ተለይተው ይከስላሉ። ስለዚህ እንደየባህሪያቸው ይከስላሉ።

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ማኅበሩ ከከሰል ምርት ጋር ቆጣቢ ምድጃዎችንም ያመርታል። አሁን ያለው የአመራረት ደረጃም በጐጆ ኢንዱስትሪ ደረጃ ነው። ይህን ወደ ከፍተኛ የማምረት አቅም ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር ያለውን ዕድል በተመለከተም አቶ ንጉሴ ሲገልፁ፤ በአሁኑ ወቅት ማኅበራቸው ወደ መካከለኛ ደረጃ እየተሸጋገረ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ መንግስትም ከዚህ አንፃር ከፍተኛ እገዛ እያደረገላቸው እንደሆነ አመልክተዋል። የመስሪያ ቦታም እየተዘጋጀላቸው ይገኛል። እንደሚታወቀው በኦሮምያ ክልል በሻሸመኔ አካባቢ ከፍተኛ የጣውላ ምርት አለ። በዚህ የተነሳም ለብሪኬትስ መስሪያ የሚሆን ሠጋቱራ ከዚያ እንዲያገኙ መንግስት አመቻችቶላቸው የብሪኬትስ ከሰል አምርተው ለገበያ ያቀርባሉ። በሳምንት 5 ሺህ በወር 20 ሺህ የብሪኬትስ ከሰልን በማምረት ወደ አዲስ አበባ በማምጣት ለተጠቃሚው አቅርበዋል። ይሁን እንጂ እንደ ማኅበሩ ስራ አስኪያጅ ገለፃ ስራው ላለፉት 6 ወራት እየተቀዛቀዘ መጥቷል። ከዚህ ሌላ በዚያ አካባቢ ስራውን ለማጠናከር እንደ ስጋት የፈጠረባቸው በእነርሱ ስም ሌሎች ሕገወጥ ደን ጨፍጫፊዎች ደን በመመንጠር ሊጠቀሙ ይችላሉ የሚለው ጉዳይ ነው። ስለሆነም ስራውን ለጊዜው ለመግታት ተገደዋል።

ማኅበሩ ብሪኬቶችን ከተረፈ ምርቶች እንጂ በቀጥታ ከደን በሚገኝ ውጤት የማምረት ዓላማ የለውም። የብሪኬት ማምረት ዓላማውም ቢያንስ የደን ጭፍጨፋውን መጠን ለመቀነስ ኃይል ቆጣቢ ከሰሎችን በኃይል ቆጣቢ መድጃዎች መጠቀም ነው። በአጠቃላይ በሻሸመኔ አካባቢ ብርኬትስ ማምረቻም ወደ ሁለት ሚሊዮን ብር ኢንቨሰት እንዳደረጉ ስራ አስኪያጁ አስረድተዋል።

ኃይል ቆጣቢ ምድጃዎቹም ሆነ ከሰሎቹ ስርጭታቸው እየተስፋፋ ደረጃ በደረጃ ነባሩን ምድጃና ከሰል መተካት መቻል ነው። ይሁን እንጂ ተጠቃሚው ኅብረተሰብ በንፅፅር የተሻለውን ምድጃ ስለሚወስድ የቆጣቢ ምድጃዎች የቁጠባ መጠንን ማወቅ ግድ ይላል። ከዚህ አንፃር ማኅበሩ የሚያመርታቸው ምድጃዎች ከባህላዊው 3 ጉልቻ ምድጃ ጋር ሲነፃፀር እንደ አቶ ንጉሴ ቢያንስ 25 በመቶ መቆጠብ መቻል አለበት። ከፍ ሲልም እስከ 40፣ 60 እና 75 በመቶ መቆጠብ መቻል አለበት። ይህም በማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ላቦራቶሪ ተረጋግጧል። የማዕድንና ኢነርጂ ቢሮውም የሚያመጣው ቴክኖሎጂ ካለ ማኅበሩ ይቀበላል።

    በሀገራችን የምግብ አዘገጃጀትን የአመጋገብ ባህላችን ይወስነዋል። እንጀራና ዳቦ ተቆርሰው የሚበሉ ሲሆን ሻይ ቡናና ወጥ የመሳሰሉት ለማባያነት ያገለግላሉ። ከዚህ አንፃር ከሰሉ ለማባያ ለሚሆኑት ወጥና ቡናና ሻይ እንጂ ለእንጀራና ለዳቦ አያገለግሉም። ከዚህ አንፃር ቴክኖሎጂውን ለሚቆረሱ ምግቦች ለመጠቀም የሚቻልበት አማራጭ እንዳለ የተጠየቁት አቶ ንጉሴ ሲመልሱ፤ እስካሁን ድረስ ከሰልን ለዳቦ መጋገሪያነት እንዳልተጠቀሙ ጠቅሰው፤ ነገር ግን በጣም ቆጣቢ የሆኑ የእንጀራም ሆነ የዳቦ መጋገሪያ ምድጃዎችን እንደሚያመርቱ አመልክተዋል። የዳቦ ምድጃው እስከ 73 በመቶ ድረስ ይቆጥባል። አንዲት እንጨት ለቃሚ ከጫካ ለቅማ የምታመጣውንና ለአንድ ቀን ብቻ የምትጠቀምበትን እንጨት በመጣዱ አማካኝነት ለሦስት ቀናት መጠቀም ትችላለች። ይህም የሴትየዋን መከራና እንግልት ከመቀነሱም በላይ በጭስ ከመጨናበስና በእሳት ከመለብለብ ያድናታል። በቆጣቢው ምድጃ ጭስ በጭስ ማውጫው በኩል ስለሚሄድ ብክለት አይኖርም። ከዚህ መረዳት የሚቻለው ቆጣቢ ምድጃንና ከሰልን በማምረት የደን ጭፍጨፋን መግታት የሚቻል መሆኑን ነው። ስለዚህ ሊበረታታ ይገባል።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
1217 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 935 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us