የደቡብ ወሎ ዞን አነስተኛ ገበሬዎች የአፈርና ውሃ ጥበቃ አተገባበር

Wednesday, 10 September 2014 11:11

በሰሜን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች ሊታረስ የሚችል ለም መሬት በአፈር መከላትና መሸርሸር የተነሳ መጎዳት ከጀመረ ዘመናት አስቆጥሯል። ሁኔታውም በሰፊ አካባቢዎች የሚስተዋል ነው። በሀገራችን እየታረሰ ከሚገኘው መሬት 45 በመቶ የሚሆነው በከፍተኛና ተራራማ አካባቢዎች ሲሆን በአማራ ክልል ደግሞ 66 በመቶ የሚሆነውን መሬት የሚሸፍን ነው። በ1996 ዓ.ም በተደረገ ጥናት በአካባቢው ተዳፋት መሬቶች ላይ ዓመታዊ የአፈር መሸርሸር መጠኑ በዓመት ከ200 ቶን ሲሆን በዚህ ሳቢያ የእርሻ ምርታማነት በየጊዜው እየተሽመደመደ ከዚያ በተጨማሪ የአየር ንብረት ለውጥ ስከት ጭራሹኑ እርሻው ወደ አዘቅት እንዲገባ ያደርጋል።

አቶ ሀሰን በሽር በወሎ ዩኒቨርስቲ በእርሻ ኢኮኖሚ ትምህርት ክፍል መምህር ናቸው ለበርካታ ጊዜያትም በአፈርና ውሃ ጥበቃ ዙሪያ ምርምርና ጥናት ያደረጉ ሲሆን በቅርቡም በአዲስ አበባ በአንድ አውደ ጥናት ላይ በደቡብ ወሎ ደሴ ዙሪያ አነስተኛ ገበሬዎች የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል የሚያካሄዱትን የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራዎችን በተመለከተ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል።

እንደ እርሳቸው ገለፃ በሰው ልክ የዕለት ተዕለት የህይወት እንቅስቃሴ በሚከናወኑ ተግባሮች ማለትም የደን ምንጣሮ የከብቶች ከመጠን በላይ የሆነ የሳር ግጦሽ እንዲሁም በተዳፋት መሬቶች ላይ የእርሻ ስራ መስፋፋት ለአፈር መሸርሸር የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል። በውጤቱም የመሬት ማርጀት ድርቅ፣ ረሀብና ስር ሰደድ ድህነት እንዲባባስ ሆኗል። የህዝብ ቁጥር በፍጥነት መጨመርና በአካባቢው ያለው የተፈጥሮ ሀብት መመናመን ችግሩ የተወሳሰበ እንዲሆን አድርጓል። ይህ ደግሞ ለድሆች ይበልጥ ፈተናን እየደቀነ ይገኛል። በሌላም በኩል የአፈር መከላት ድህነትን አባብሶ በምግብ ራስን የመቻል የሚለውን መርህ ከህልም እንጀራነት እንዳያልፍ አድርጓል። የገበሬው ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ህይወትም ገበሬው ለክፉ ቀን የሚሆነውን ጥሪት እንዳይቋጥር አድርጓል።

አቶ ሀሰን በሽር ጥናታቸውን በተለይ በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ዙሪያንና ኩታበርን የጠቀለለ ነው። በደቡብ ወሎ ካለው የመሬት ስፋት 34 በመቶ በደሴ ዙሪያ 20 በመቶ እንዲሁም በኩታበር 35 በመቶ የሚሆነው መሬት ለእርሻ ስራ ውሏል። እንደ እርሳቸው ገለፃ በገበሬዎች በአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራ በቤተሰብ ውስጥ ያለው የዕድሜ ሁኔታ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። የተለያዩ የጥበቃ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም የሚስችል ውሳኔ ለመስጠት እድሜ ከፍ ያለ ድርሻ አለው። የአብዛኛው ጥናት የተደረገበት አካባቢ ቤተሰብ አማካይ ዕድሜ 53 ዓመት ነው። ይህ ደግሞ ዘመናዊውንም ሆነ ባህላዊውን አሰራር ለመተግበር ከፍተኛ ድርሻ አለው። የውሃና የአፈር ጥበቃ ስራ ለማከናወን የእድሜ ደረጃ እንደግብአት ነው። በወጣት እድሜ ክልል የሚገኙት ከበሳሎቹ ስለቴክኖሎጂው በቂ ግንዛቤ ስላላቸው ዘመናዊውን ዘዴ ይጠቀማሉ። ከኤክስቴንሽን ሠራተኞች መረጃ በማግኘት ረገድ ደግሞ የዳታ ሁኔታ የተለያዩ ገጽታ አለው። ወንዶች የኤክስቴንሽን ሠራተኞች መረጃውን በአብዛኛው ከሴቶች ይልቅ በወንዶች ይሰጣሉ። ይህም በህብረተሰቡ ባህል ለሴቶች የሚሰተው ግምት አናሳ ከመሆኑ የተነሳ ሲሆን በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው ላይም የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል።

የእርሻ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ለማከናወን የገበሬዎች የትምህርት ደረጃም የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል። ትምህርት ያላቸው መረጃዎችን ለመቀበልና ለመተግበር ፍላጎትና ተነሳሽነት ሲኖራቸው በትምህርታቸው ያልገፉት በተቃራኒው ለሥራው የሚሰጡት ትኩረት አናሳ ነው። በአካባቢው ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል የተማሩ ገበሬዎች 31 በመቶ ሲሆኑ ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የተማሩ ደግሞ 24 በመቶ ናቸው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የተከታተሉት ደግሞ 7 በመቶ ናቸው። ከእነኚህ ውጭ ያሉት ደግሞ ጭራሹኑ ማንበብና መፃፍ የማይችሉ ናቸው። ይህ ሁኔታም ዘመናዊ የአፈር ጥበቃ ስራን ለማከናወን እንደመሰናክል እንደሚቆጠር አጥኚው ጠቁመዋል። የመሬት ይዘት መኖር በምግብ ራስን የመቻሉን ስራ ከማቀላጠፉም በላይ በአካባቢው የኢኮኖሚያዊ እድገት ለማምጣትም የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል። ይሁን እንጂ በዚህ ቦታ ያለው የመሬት ዕጥረትና መበጣጠስ የአፈር መሸርሸርንና መሬት መራቆትን እያባሰው ይገኛል። ከላይ የተጠቀሱት የመሬት ተዳፋትነትና የህዝብ ቁጥር እድገትም አሉታዊ ተፅዕኖአቸው ለአካባቢ የሚሰጠው እንክብካቤ እንዲገታ አድርጓል።

ጥናቱ በተካሄደበት አካባቢ የአንድ የገበሬ ቤተሰብ አማካኝ የመሬት መጠን 0ነጥብ69 ሄክታር ሲሆን ይህም ለእርሻ ምርታማነት እጅግ ጉዳት እንደሚያስከትል ለመረዳት አያዳግትም። እንደዚያም ሆኖ የአፈርና የውሃ ጥበቃው ሥራም በተበጣጠሰና በማይደጋገፍ መልኩ እንዲከናወን አድርጓል። የመሬታቸው መበጣጠስ ገበሬዎችን የአፈር ጥበቃ ስራ ለመስራት ከውሳኔ ላይ ለመድረስም እንደፈተና ይወሰዳል። ከዚሁ ጋር ከመሬታቸው በራቁ አካባቢ ሄዶ አፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለመስራት የመሬቱ አቀማመጥ አስቸጋሪና የተዘረጋ መንገድ አለመኖር ሥራው እንዳይከናወን እንቅፋት ሆኗል። ለመስራት ቢሞከርም ከፍተኛ ጉልበትንና ጊዜን የሚያባክን ነው። ከዚሁ ጋር የገበሬዎች መኖሪያ ከእርሻቸው መራቁና ጥቂት ኪሎ ሜትሮችን በእግር ማስጓዙ የአፈርና ውሃ ጥበቃን ለመሥራት ከውሳኔ ላይ ለመድረስ እንዳይችሉ ተፅዕኖ አሳርፏል። በሶሰት የተለያዩ ወረዳዎች በተደረገው ጥናት ገበሬዎች ከመኖሪያቸው እስከ እርሻቸው ቦታ ለመሄድ የ30፣ የ20 እና የ18 ደቂቃ ይወስድባቸዋል። ከጉዞው ጋር የእርሻ ስራውንና የአፈርና ውሃ ጥበቃን ስራ ከእርሻቸው ርቆ ሄዶ ለማከናወን አስቸጋሪ ከመሆን ባለፈ ለስራው ሊሰጡት የሚችለው ትኩረት አናሳ እንዲሆን አድርጓል።

የመሬት የባለቤትነት ስሜትም የዚያኑ ያህል አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተፅዕኖ እንዳለው በጥናቱ ለመመልከት ተችሏል። በአካባቢው የመሬት ሽንሸና በክልሉ አስተዳደር በተለያየ ወቅት ተከናውኗል። ለዚህ አፈፃፀምም የገበሬ ማህበራት መዋቅር ግልጋሎት ሰጥቷል። እንደዚያም ሆኖ መሬት የሌላቸው ገበሬዎች ለአጭር ለመካከለኛና ለረጅም ጊዜ መሬት እየተከራዩ ያርሳሉ። እንዲያም ሆኖ በተለይ መሬቱን ለአጭር ጊዜ የሚከራዩ ገበሬዎች መሬቱን ሊለቁ ስለሚችሉ የሚሰጡት ትኩረትና እንክብዳቤ አናሳ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል። ይህ ሁኔታም በአፈርና በውሃ ጥበቃ ስራ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ አሳርፏል።

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የመሬት ተዳፋትነት ለእርሻ አስተራረስም ሆነ ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ አሉታዊ ተፅዕኖ የአፈሩ አይነትም እንደዚም ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችል ይሆናል። ዝቅተኛ ተዳፋትነት ያለው መሬት የአፈር መሸርሸር መጠኑ አነስተኛ ሲሆን መካከለኛ ደግሞ ከፍ ይላል። ተዳፋትነቱ ወደ ቀጥታ የሚያመዝን ከሆነ ለአፈር መሸርሸርና ለሰብል ውድመት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል። የዚህ መሰሉ የእርሻ አስተራረስ ዘዴ ከመሬት እጦት የተነሳ የሚከናወን ሲሆን የመሬት እጥረት ከህዝብ ቁጥር ጋር ባለመጣጣም የሚከሰት ነው። ችግሩም መፍትሄ ሊያገኝ የሚችለው በረጅም ጊዜ ጥናትና ህዝብን በመልሶ ማስፈር እንደሆነ ሙያተኞች ይገልጻሉ። ከከፍተኛ መሬቶች ላይ በጎርፍ የሚታጠበው ለም አፈርም መተኪያ የማይገኝለት በመሆኑ ገዳቱ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ጥናት ከተደረገባቸው 803 የአነስተኛ ገበሬዎች አነስተኛ ማሳዎች ውስጥ 25 በመቶ የሚሆነው በጠፍጣፋ መሬት ላይ የተቋቋሙ እርሻዎች ሲሆኑ 47 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በመጠኑ ተዳፋት ነው። 24 በመቶ የሚሆነው በጣም ተዳፋት ሲሆን 4 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በገደል ላይ የሚታረስ ነው። በዚህም ሳቢያ በጣም ተዳፋት መሬቶች ላይና ገደል ላይ ተመሰረተ እርሻዎች ላይ ያለውን መሬት አፈር መሸርሸርን ለመግታት የሚከናወነው ስራ እምብዛም ውጤታማ አይደለም። ይህም በገበሬዎች ግንዛቤ ያገኘ ነው። ከላይ ከተጠቀሱት 803 አነስተኛ እርሻዎች ውስጥም ዝቅተኛ ለምነት ያለው መሬት 15 በመቶ ሲሆን መካከለለኛ ለምነት ያው ደግሞ 67 በመቶ ነው 18 በመቶ የሚሆነው ደግሞ የተሻለ ለም መሬት ነው። ከአካባቢው መሬት 93 በመቶ የሚሆነው መሬት “ባለቤት አለው” የሚባል ሲሆን 7 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በአራሾች የሚታረስ ነው።

የአካባቢው ገበሬዎች ዘመናዊ አፈርና ውሃ ጥበቃ የሚያካሄዱና የማያካሂዱ ተብለው ለሁለት ተከፍለዋል። የሚያካሂዱትም አፈርን ቦይ በመስራት በመጠበቅና የድንጋይ ካብ በማድረግ የሚጠብቁ ናቸው። ሌሎች ደግሞ ይህን ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት በጭራሽ የማያካሂዱ ናቸው።

የእርሻ መሬት መጠን ከገቢና ከሀብት መጠን ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ሲሆን ሰፊና ለም መሬት ያላቸው ገበሬዎች የተሻለ አፈርና የውሃ ጥበቃ ስራ እንደሚያከናውኑ ለመረዳት ተችሏል። በሌላም በኩል በአነስተኛ መሬት ላይ የሚሠራው የእርከን ስራ ለእርሻ ስራ የሚውለውን መሬት ስለሚያጣብብ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አስከትሏል። ሰፊና ለም መሬት ያላቸው የተሻለ ገቢና ሀብት ስላላቸው፤ ካለቸው ገንዘብ ሌላ የጉልበት ሠራተኛ ቀጥረው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራን ያከናውናሉ።

በጥናቱ ማረጋገጥ እንደተቻለው ከእርሻ አክስቴንሽን ሠራተኞች ጋር ያልተቋረጠ ግንኙነት ያላቸው ገበሬዎች መሬቶቻቸውን በተሻለ መልኩ በመንከባከብ ይታወቃሉ። የአፈርና ውሃ ጥበቃም የሚያከናውኑት በድንጋይ ካብ በመስራት ነው። በአካባቢው የምግብ ለስራ አማካኝነት የሚሰራው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እንዲሁም ህዝብን በዘመቻ መልክ የተፋሰስ ልማት ማሰራቱ ገበሬዎች ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ያላቸውን ግንዛቤ ከማሻሻሉም በላይ በተነሳሽነታቸው ላይ አወንታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉን በጥናቱ ተረጋግጧል።

    በአጠቃላይ በደሴ ዙሪያና በኩታ በር አካባቢ ያሉ ወጣትና ትምህርት የቀመሱ ገበሬዎች ሻል ያለ ለምነት ያለውና ሰፋፊ መሬት ያለቸው ሲሆን ትምህርት ካልቀመሱት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ የአፈር ጥበቃ ስራ ይሰራሉ። ከዚሁ ጎን ለጎን የከብት ርባታ ማካሄዳቸውና ገቢያቸው መጨመሩ ይበልጥ ገንዘባቸውን ለእርሻ ስራ ለማዋል እድል ፈጥሮላቸዋል። ዘመናዊ የአፈር እንክብካቤ ስራ በገጠር እንዲጎለብት ከማድረግ አንፃር የኤክስቴንሽን ስራ እጅግ የላቀ አስተዋፅኦ እንዳለው በጥናቱ ተረጋግጧል። የመሬት አቀማመጥ ሁኔታም የራሱ የሆነ አሉታዊና አዎንታዊ ሚና ይጫወታል። ከገበሬዎች መኖሪያ መንደሮች እስከ እርሻ መሬታቸው ድረስ ያለው ርቀት የምርታቸው ገበያ ማግኘትና ተፈላጊነት መረጃ የማግኘት ሁኔታ የእርሻ ግብዓት በዱቤ ማግኘት ጊዜን በመቆጠብ ለጥበቃ ስራው ይበልጥ ትኩረት መስጠት እንደሚያስችል ተረጋግጧል። ከዚህ አንፃር የመሰረተ ልማቶች መስፋፋት ገንቢ ሚና ይጫወታሉ። በአጠቃላይ እንደ ሰሜን ኢትዮጵያ ተራራማ አካባቢ ባሉ እርሻዎች የአፈርና ጥበቃን ለማካሄድ የመሬቱ አቀማመጥና ለምነት እንዲሁም የገበሬዎች እውቀት ወሳኝ መሆኑን ግንዛቤ ማግኘት ያሻል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1229 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1066 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us