ክትትል የተነፈገው ችግኝ ተከላና የአካባቢ ጥበቃ ሥራ

Wednesday, 17 September 2014 14:33

በአይቼው ደስአለኝ 

በሀገራችን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ቀደም ባሉት ዘመናት ሲከናወን የቆየ ነው። በተለይም በክረምት ወቅት በአዲስ አበባና በክልሎች በስፋት ይከናወናል። ነገር ግን በመርሃ ግብሩ ያስገኘው ውጤት በተጨባጭ ይፋ አይደረግም። ችግኝ የተተከለባቸው አካባቢዎችም አልፎ አልፎ ችግኞቹ ደራርቀው በከብቶች ተረጋግጠውና ተበልተው ቦታው ባዶ ሆነው ይስተዋላሉ። ይህ ሁኔታ ክትትል የሚያሻው ጉዳይ ነው። ነገር ግን አብዛኛዎቹ መርሃ ግብሮች ከመትከል ባለፈ ተጨማሪ ስራን አለማካተታቸው ቱሩፋቱን አናሳ እያደረገው ይገኛል።

የፌዴራል የአካባቢ ጥበቃና ደን ሚኒስቴር መንግሥታዊ ካልሆኑና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት አካባቢን ከመራቆትና ከመጥፋት እንዲሁም አፈርና የውሃ ምንጮችን ከመጠበቅ አንፃር የተለያዩ ሥራዎችን በመላው ሀገሪቱ እንዲከናወን እያስተባበረ ይገኛል። ለዚህ እንዲያግዝም የችግኝ ተከላው ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ብርሃኑ አያሌው ይገልፃሉ። እንደ እርሳቸው ገለፃ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ቁርጠኝነት በተሞላው ፖለቲካዊ አመራር በመታገዝ የልማት አጀንዳ ሆኖ በሁሉም ክልሎች እየተተገበረ ይገኛል። ለዚህ እንዲያግዝም የህዝብ ንቅናቄ ስራ ተሰርቶ በግለሰብ በማህበረሰብ እንዲሁም በዚህ አላማ በተደራጀ ተቋማት አማካኝነት ክንዋኔው ቀጥሏል።

በርግጥ የሀገራችን የደን ሽፋን ከ450 ዓመታት በፊት የነበረው የ40 በመቶ ሽፋን በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮ ምክንያት የተነሳ እጅግ ተመናምኖ ወደ 2ነጥብ 5 በመቶ ደርሶ ባለፈው 10 ዓመታት በተደረገው ደንን መልሶ የማልማት ሥራ በአሁኑ ወቅት ወደ 10 በመቶ ከፍ እንዳለ የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ መረጃ ያመለክታል። ይሁን እንጂ አሁንም ያለው ደን ቢሆን ለጥፋት ተጋላጭነቱ ከፍተኛ እንደሆነ መረዳት አያስቸግርም። በሀገራችን የህዝብ ቁጥር እድገቱ ከአለም በትልቅነቱ የሚጠቀስ ነው። በአመት እስከ 3 በመቶ ይጨምራል። ይህ ማለት ተጨማሪ የሚታረስ መሬት በየዓመቱ ያስፈልጋል ማለት ነው። መሬት ፈላጊዎች መሬት ሲያስፈልጋቸው ወደ ደን መሬቶች መስፋፋታቸው አይቀሬ ነው። የማገዶ ፍላጎትም የደን መጨፍጨፍን ያስከትላል። ከዚህ በተጨማሪ ከእንጨት ሥራዎች ለቤት ግንባታዎች ተብሎ ከፍተኛ ደን ይጨፈጨፋል። ስለሆነም የሚቆረጠውና የሚተከለው ችግኝ የተመጣጠነ እንኳ ቢሆን የተተከሉ ችግኞች ምን ያህል ፐርሰንቱ እንደሚፀድቅ አለመታወቁ የፀደቁትም ደን ለመሆን አመታትን ስለሚያስቆጥሩ የተራቆተ አካባቢን በደን አልምቶ አካበቢን ከመራቆትና የአፈርና ውሃን ከመመናመን ለመታደግ ከባድ ስራ መስራትን እንደሚጠይቅ መረዳት ግድ ይላል።

በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ይመለከተናል የሚሉ ባለድርሻ አካላት በተከላው መርሃ ግብር በመሳተፍ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ ተቋማት መካከል የኢየሩሳሌም የህጻናትና የማህበረሰብ ልማት ድርጅት የሚጠቀስ ነው። የድርጅቱ ኃላፊ አቶ ግርማ ከበደ እንደሚገልጹት ድርጅታቸው በሀዋሳና በድሬዳዋ በአካባቢ ጥበቃ ሥራ አበረታች ሥራ አከናውኗል።

ድርጅቱ በሀዋሳ ሀይቅ ዳርቻዎች ያከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው። ይህ ሥራ የሚሰራውም ክረምትን በመጠበቅ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ወቅቶችም መሆኑ ከሌላው ለየት እንዲል አድርጎታል። እንደሚታወቀው የደን መጨፍጨፍና የአካባቢ መራቆት መዘዝ ለመሬት ብቻ የሚተርፍ አይደለም። ረግረጋማና የውሃ አካባቢዎችንም ይበልጥ ይጎዳል። ደኖች ሲራቆቱ በክረምት የሚመጣ ዝናብ ወደ መሬት መስረግ ሲገባው አፈርንና ቁጥቋጦዎችን በመጠራረግ ወደ ውሃ ያስገባል። ይህም የመሬት ታችኛው ክፍል በደለል እንዲሞላ በማድረግ በሂደት የውሃ መጠኑ እንዲቀንስና እንዲመናመን ያደርጋል። ወደ ውሃው የሚገባው ጎርፍም በተለያዩ ቆሻሻዎች የተበከለ ከሆነ በውሃ ውስጥ የሚገኙትን ዕፅዋትንና እንስሳትን በመመረዝ እንዲወድሙ ያደርጋል። ይህም እንደገና በውሃ ውስጥ ጤናማ ስነህይወታዊ ተራክቦ እንዳይኖርና ውሃው ጭራሹኑ የተበከለ እንዲሆን ያደርጋል። በሀገራችን አሁን ባለው የቱሪዝምና የሆቴል ኢንዱስትሪ መስፋፋት የባህር ዳርቻዎችን ተመራጭ አድርጓቸዋል። በርካታ ህዝብ ወደ ሃይቅ ዳርቻዎች በመጓዝ የዕረፍት ጊዜውን በመዝናናት ያሳልፋል። ይህ በመልካምነቱና ለሀገር ገቢ በማስገኘት ተጠቃሽ ቢሆንም ከሆቴል ማስፋፋት ስራ ጎን ለጎን የአካባቢ ጥበቃ ስራ ካልተከናወኑ በሂደት አካባቢ ተራቁቶ የውሃው መጠን እስከመመናመን ከዚያም አልፎ ጭራሽኑ ሊደርቅ ይችላል። ይህ ደግሞ በራሱ በባህር ዳርቻዎች ያሉት መዝናኛ አካባቢዎች ህልውናንም ጥያቄ ውስጥ ሊከት ይችላል። በአሁኑ ወቅት ህዝብን በማዝናናት ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ የሚባሉት የሀዋሳም ሆነ የባህርዳር ሀይቆች ለዚህ መሰሉ አደጋ ተጋላጭነታቸው ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ ይገኛል። በእነኚያ በውሃ ዳርዳቻዎች ለመዝናኛ ቦታዎች መስፋፋት ትኩረት የተሰጠውን ያህል ለአካባቢ እንክብካቤ ትኩረት አልተሰጠውም። በዚያ የሚገኙ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላትም ሆነ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ችግሩ መኖሩን ቢያውቁም ተገቢውን ክትትል አድርገው ርምጃ ለመውሰድ ተነሳሽነቱን አጥተዋል። ስለሆነም ችግሩ ስር ከመስደዱ በፊት እልባት ሊሰጡት ይገባል። ሁኔታው በትኩረት ከተሰራበት ግን ሊቀረፍ የሚችል ነው። የኢየሩሳለም የህፃናትና የማህበረሰብ ድርጅት ከአዋሳ በተጨማሪም በድሬዳዋ ዙሪም የዚህን መሰል የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል። ተቋሙ ባለፉት 10 ዓመታት ባከናወነው ስራም አካባቢው በደን እንዲለብስና የተራቆቱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያንሰራሩ አድርጓል። ስራውም በአካባቢው ህብረተሰብ ተሳትፎ መከናወኑ የአካባቢ ጉዳይ በጋራ ስሜት ትኩረት ማግኘት እንዲችል የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል። አካባቢን በደን የማልበሱ ሥራ በአዎንታዊ ጎኑ የሚታዩ ቢሆንም ለዘላቂ ልማትና እድገት እንዲሁም አካባቢ ጥበቃ ስራ የህብረተሰብ የቤት ውስጥ ኢነርጂ አጠቃቀም ባህሉ በሂደት ወደ ታዳሽ ኢነርጂ መጠቀም እንዲያመራ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው። የድሬዳዋ አካባቢ ደረቃማ አየር የሚስተዋልበትና በአካባቢው ኦራይ ውድ ላንድ /ory wood land/ የሚበዛበት ነው። ይህ ሁኔታም በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች በከሰል አክሳይነት ሥራ እንዲሰማሩ አድርጓቸዋል። ይህ እንቅስቃሴም ለደን መጨፍጨፍና ለአካባቢ መራቆት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደርጋል። ደን መጨፍጨፍ ሳያንስ ከሰል ለማክሰል በሚካሄደው እንቅስቃሴም አካባቢ በጭስ ይበከላል። ወደ ከባቢ አየር የሚገባው በካይ ጋዝም ይጨምራል። አክሳዮቹም ለመተንፈሻ አካላት ህመም የተጋለጡ እንዲሆኑ ያደርጋል።

ከዚህ አኳያ ህብረተሰቡ መንግስት እየተከሰተለ ያለውን ሀይል ቆጣቢ ምድጃዎችን ታዳሽ ኃይል የሆኑ ባዮጋዝና ባዮፊውልን የመሳሰሉትን የመጠቀም ባህሉን ሊያዳብር ግድ ይላል። ይህ ሲሆን የደን ውጤቶችን ለማገዶነት የመጠቀሙ እድል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ይሄዳል። ይህም የደን መንከባከቡን እንዲሁም የችግኝ ተከላ ሥራውን ትርጉም ያለው እንዲሆን ያደርጋል። እንደ ድሬዳዋና ደሴን የመሳሰሉ ከተሞች ከተራራ ስር መቆርቆራቸው ለጎርፍና ለተፈጥሮ አደን ተጋላጭነታቸውን ከፍ ያደርገዋል። ተራሮቹ በደን ካልተሸፈኑና አካባቢ እንክብካቤ ካልተደረገለት የሚያስከትለውን መዘዝ መገመት አያስቸግርም። በ1999 ዓ.ም በድሬዳዋ የተከሰተውና ለበርካቶች ህይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት ምክንያት የሆነው ጎርፍ በቀጥታ ከአካባቢ መራቆት ጋር የተገናኘ ነው። ለአካባቢው መራቆት ምክንያትም በተራሮች ላይ ያለው የግራር ደን ለማገዶና ለከሰል እየተጨፈጨፈ ከአካባቢው በመወገዱ ነው። በመሆኑም አካባቢን በደን የማልበሱን ስራ በየትኛውም የሀገራችን አካባቢ አጠናክሮ መቀጠሉ አዋጭነት ያለው ሲሆን ለዘለቄታዊ አካባቢ ጥበቃ ስራ ግን ደንን ለማገዶነት የመጠቀሙ ፍላጎት እንዲቀንስ ማድረግና የታዳሽ ኢነርጂ ምንጮችን የመጠቀም ባህሉን ማጎልበት ተገቢ ነው።

የችግኝ ተከላ ሥራ የተራቆቱ መሬቶችን በደን ከማልበስ በተጨማሪ በከተሞችም አካባቢን በማስዋብ የሚገለፅ መሆኑን የሚገልጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የውበትና መናፈሻ ዘላቂ ልማት ኤጀንሲ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ እጀታ ናቸው። እንደ እርሳቸው ገለፃ የችግኝ ተከላ መርሃግብሩ በየጊዜው ሲከናወን የቆየ ቢሆንም ወጥና ቅንጅት የሚጎድለው ነበር። በከተማዋ በተለያዩ ፓርኮችና አካባቢዎች የሚተከሉት ችግኞችም ከ100ሺህ የሚበልጡ አልነበሩም።

በአሁኑ ወቅት የመንገድ አካፋዮች፣ መናፈሻዎች የጋራ መኖሪያ ቤቶች አረንጓዴ ቦታዎችና ክፍት ቦታዎች እየተስፋፉ በመምጣታቸው የዚያኑ ያህል ከተማዋን በማስዋብ የሚተከሉ ችግኞች ተበራክተዋል። ለዚህ እንዲያግዝም ስድስት የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ተቋቁመው ችግኞችን በተለያየ አይነታቸው በማፍላት በአስሩም ክፍለ ከተሞች እንዲከፋፈሉ እየተደረጉ በተዘጋጀላቸው የመትከያ አካባቢዎች ማለትም በመንገድ አካፋዮች በመናፈሻዎች በአደባባዮችና በክፍት ቦታዎች እንዲተከሉ በመደረግ ላይ ናቸው። በመጭው በጀት አመትም 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአበባ፣ ሀገር በቀል የዛፍ ችግኞችና የተለያዩ የሳር ዝርያዎችን ለመትከል ዝግጅት መጠናቀቁን ለመረዳት ተችሏል።

ሀገራችን እየተከተለች ባለችው አካባቢን የማይበክል አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ከሚያካትታቸው በርካታ ዘርፎች ወስጥ አረንጓዴ አካባቢዎችንና ደኖችን ማስፋፋትና መንከባከብ አንዱ ነው። የደኖች መኖር የአካባቢን አፈርና ውሃን ከመጠበቅ ባሻገር ከመሬት በኢንዱስትሪዎችና በትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች አማካኝነት የሚለቀቀውን በካይ ጋዝ ከባቢ አየር ውስጥ ሳይገባ በደን ዕፅዋቶች አማካኝነት መጥጦ በማስቀረት አካባቢን ከብክለት መታደግ ነው። ይህም አካባቢን በነፋሻ አየር እንዲሞላ ከማድረግ በዘለለ በካርቦን ንግድ አማካኝነት ከበለፀጉ ሀገሮች ጠቀም ያለ ገንዘብ ማግኘት የሚያስችል ነው። የዚህ ገንዘብ መገኘት ደግሞ ለበርካታ ወገኖች የስራ እድል እንዲፈጠር ደን መንከባከብ፣ ደን እንዳይቆረጥ ከማድረግ በዘለለ በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ እያገኘ እንዲሄድ ያደርጋል። ከዚህ አኳያ በወላይታ ሀምቦ አካባቢ ያሉ ገበሬዎች በካርበን ንግድና በንፁህ ልማት ስትራቴጂ አማካኝነት እየተንከባከቡ ባሉት ደን አማካኝነት ተጠቃሚ መሆናቸው በምሳሌነት የሚነሳ ነው።

     ችግኝ ተከላ አካባቢን ከመራቆት ከመታደግ ባለፈ ተዘርዝረው የማያልቁ ጠቀሜታዎችን ያስገኛል። ነገር ግን ችግኝ ከመትከሉ በይበልጥ እንክብካቤ ማድረጉም ሊሰመርበት የሚገባ ነው።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
1565 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1113 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us