የባዮቴክኖሎጂ አዎንታዊ ጠቀሜታና የአተገባበሩ አሻሚነት

Wednesday, 24 September 2014 12:20

ባዮቴክኖሎጂ በተለያዩ ዘርፎች ማለት በግብርና በኢንዱስትሪ በህክምና ወዘተ በአለም ከፍተኛ ጠቀሜታን እየሰጠ ይገኛል። በግብርናው በኩል የተዳቀሉ በሽታን መቋቋም የሚችሉ እንስሳትንና እፅዋትን በማራባትና በመዝራት ምርታማነት እንዲጨምር ከማድረጉም በላይ በተለይ የበለፀጉ ሀገሮች በዚህ ቴክኖሎጂ አማካኝነት የግብርና ውጤቶችን በዓለም ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ ትርፍን ለማጋበስ አስችሏቸዋል። በኢንዱስትሪው በተለይ በምግብ ዝግጅት ረገድና ምግብና መጠጦች ሳይበላሹ ለረጅም ጊዜ እንዲቆዩ በማድረግ ተጠቃሚው ለጉዳት እንዳይጋለጥ በማድረግ ጠቀሜታ መስጠት ችለዋል። በህክምናው ዘርፍም እፅዋቶች ለመድሃኒት ቅመማ እንዲውሉ በማድረግ ከመቼውም በላይ አመርቂ ውጤት አስገኝቷል።

በሀገራችን በተለይ የግብርና ሌሎች የምርምር ተቋማት ቴክኖሎጂው ለምርምር ግብአትነት መዋል ከጀመረ በርካታ አመታት አልፈዋል። በዚህ አማካኝነት የተሻሻሉ በሽታንና ድርቅን መቋቋም የሚችሉ አዝርዕቶች በላቦራቶሪ እየተመረቱ ለአርሶ አደሮች ቀርበው ምርታማነት እንዲጨምር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል። በእንስሳት ርባታ ረገድም ቴክኖሎጂው ጥቅም ላይ ውሏል። የስጋና የወተት ከብቶችም ተዋፅኦዋቸው እንዲሻሻልና እንዲጨምር እገዛ አድርጓል። እንዲያም ሆኖ የባዮቴክኖሎጂን አሉታዊ ገፅታን በማንሳት ነቀፌታን ከመሰንዘር ያልተቆጠቡ ሙያተኞች በሀገራችንም ሆነ በአለም ደረጃ እንደሚገኙ እሙን ነው። ብዝሃነትንና ሀገር በቀል እውቀትን በመገዳደር አሉታዊ ተጽዕኖ ያመጣል የሚሉ አሉ። ነገር ግን አዎንታዊው ገፅታው የመመልከቱ ጉዳይ እየተስፋፋ ነው።

ዘረፉ የተለያዩና በርካታ ቴክኒኮችን በውስጡ ይዟል። የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ምርታማነትን ለመጨመር በግብርናው ዘርፍ በስፋት እየተሰራበት ሲሆን አበረታች ውጤትም ተገኝቶበታል። በጤናው ዘርፍም የተሻለ ውጤት ስላሳየ በርካታ ሀገሮች እየተጠቀሙበት ነው።

ከሰሞኑም በሀገራችን ሳይንስና ቴክኖሎጂን በተመለከተ ኃላፊነት የተሰጠው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሀገራችን ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን ለማድረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። የውይይቱ ዓላማም በባዮቴክኖሎጂው አማካኝነት በግብርና በጤና እና ሥነምግብ ምርምር እስካሁን የተከናወኑ ሥራዎችን በመገምገም ያጋጠሙ ተግዳሮቶችንና መልካም አጋጣሚዎች ምን እንደሚመስሉ ለመመልከት ያስቻለ ነበር። በዕለቱም በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የባዮ ቴክኖሎጂ ምርምር ዳይሬክተር በሆኑት በዶ/ር እንዳለ ገብሬ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቧል። እንደ እሳቸው ገለፃ ዘርፉ የተለያዩ ቴክኒኮችን ያካተተ ለግብርናው ልማት ከፍ ያለ ጠቀሜታ ያለውና የወደፊቱ የሳይንስ እድገትም በሰፊው አጽንኦት ሊሰጠው እንደሚችል አመልክተዋል።

በቴክኖሎጂም የሚታገዘው የግብርናው ዘርፍ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ገቢ እያስገኘ በመምጣት ላይ ይገኛል። እንደዚያም ሆኖ በዘረመል ጥንቅር ላይ ሊያስደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ አስፈላጊ እንደሆነ የጠቆሙት የፅሁፍ አቅራቢ ለዚህ እንዲያግዝም የባዮ ሴፍቲ አጠቃቀም እጅግ ወሳኝ እንደሆነ አመልክተዋል።

አክለውም በአሁኑ ወቅት አሜሪካ፣ ካናዳና አውሮፓ 97 በመቶ የሚሆነውን የዓለም የባዮ ቴክኖሎጂ ገበያ በእጃቸው አስገብተዋል። ይህም የሳይንስ ምርምር ጠቀም ባለ ገንዘብ ከተደገፈ የተትረፈረፈ ሀብት ሊያስገኝ እንደሚችል መንግሥታቱ ተገንዝበው ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጡት አመላካች ነው ብለዋል። በበለፀጉት ሀገሮች ከመንግስት ተቋማት በተጨማሪ ታዋቂ የግል ኩባንያዎች በባዮቴክኖሎጂ ዙሪያ ከፍተኛ ምርምር በማካሄድ ለግብርና እድገት ብሎም የዓለም የግብርና ኢኮኖሚ በጥቂት ኩባንያዎች ሞኖፖሊ ሥር እንዲወድቅ ማድረግ ችለዋል።

ስለግብርና ቴክኖሎጂ ምርምርና የሰለጠነ የሰው ኃይል ረገድ በዓለም በታዳጊና በበለፀጉ ሀገሮች መካከል የሰማይና የመሬት ያህል መራራቅ አለ። የግብርና እውቀትና ሳይንስ ለሀገሮች ብልጽግና ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት በተጨባጭ የሚታይ ነው። የተትረፈረፈ ምርት የዓለም ገበያ በማጥለቅለቅ ለኩባንያዎች ጠቀሜታ ይሰጣል። እንዲያውም የምግብ አቅርቦት ከፍላጎት በላይ በሆነበት በአሜሪካና በአውሮፓ አንድ ሶስተኛ የሚሆነው ምግብ ከእህል አጨዳ እስከ ምግብ ዝግጅት ባለው ሂደት ውስጥ ይባክናል። ተዘጋጅቶ አልቆ ለገበያ ከቀረበው ምግብ ውስጥም አንድ አራተኛ የሚሆነው እንደሚደፋ የዓለም የምግብ ድርጅት የ2013 ዓመታዊ ሪፖርት ያመለክታል።

በተቃራኒው የአፍሪካን የምግብ ሁኔታን የግብርና ደረጃ ስንመለከት ከላይ ከተጠቀሰው ጋር እጅግ በጣም በዝቅተኛ ደረጃ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም። ከዓለም ሊታረስ ከሚለው መሬት ውስጥ ሰፊው ቦታ የሚገኘው በአፍሪካ ይገኛል። 60 ሚሊዮን ሄክታር የሚታረስ መሬት አፍሪካ አላት። ነገር ግን አህጉሪትዋ 40 በመቶ የሚሆነውን የምግብ ፍላጎትዋን የምትሸፍነው ከውጭ በግዢና በእርዳታ በሚገኝ እህል መሆኑን በሀዋርድ ዩኒቨርስቲ የአፍሪካ ተመራማሪው ዶ/ር አልም አንተ ታረቀኝ ይገልጻሉ። ሰፊ የብዝሃ ህይወት ባለቤት ለም አፈርና ውሃ ቢኖራትም አፍሪካ በአብዛኛው ባህላዊ ዘዴን በሚጠቀም እርሻ ላይ በመንጠልጠሏ ህዝቧ በምግብ እጥረት መከራውን ያይባታል። ከዚህ አኳያ በአሁኑ ወቅት አፍሪካ ባላት ውስን የገንዘብ አቅም አነስተኛ የሰለጠነ የሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ የተነሳ ባዮቴክኖሎጂን በስፋት መጠቀም ባትችልም ወደፊት በዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን ከወዲሁ መንግስታት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሊያሳዩ ግድ ይላል። ይህ ሲሆንም በምግብ ራስን የመቻል ጉዳይ ከእንቆቅልሽ ተላቆ ወደ እውነታ ሊቀየር ይችላል።

እንደ ዶ/ር እንዳለ ገብሬ ገለፃ የባዮቴክኖሎጂ የምግብ ምርትን በማሳደግ ሰብል በሽታንና አረምን መቋቋም የሚችል እጽዋትን ለማዘጋጀት ድርቅንና ተለዋዋጭ የአየር ንብረትን መቋቋም የሚችሉ ተክሎችን ለማብቃት እፅዋት የራሳቸውን የናይትሮጂን ማዳበሪያ በራሳቸው ውስጥ በተሻለ ብቃት እንዲያዘጋጅ ለማስቻል በእንስሳት ዘርፍም አዳዲስና የተሻሻሉ በሽታ የመመርመሪያ ዘዴዎችን መድሃኒቶችንና ክትባቶችን ለማምረትና የምግብ ይዘትን ለማሻሻል ጠቃሚ ነው።

እንደሚታወቀው የሀገራችን ግብርና ማለትም የእንስሳት ርባታውና የእህል ምርቱ ለሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት /GDP/ 49 በመቶ አስተዋፅኦ ያደርጋል። በርካታ ህዝብም (85 በመቶ) የሚሆነው በስራ የተሰማራው በዚሁ ዘርፍ ነው። ይህ ሁኔታም የሚያመለክተው የእርሻው ዘርፍ በቴክኖሎጂ ያልተደገፈና ኋላ ቀር መሆኑን ነው። ስለሆነም የባዮቴክኖሎጂ ጠቀሜታ አጠያያቂ አይደለም። ግብርናው እንደዘመን ያደርጋል። ምርትና ምርታማነትን ያሳደጋል፤ ጥራትን ለማሻሻል ያስችላል። የብዝሃ ህይወት በሀገራችን በስፋት መኖርም ለቴክኖሎጂው አመቺ ነው።

ከዚሁ ጋር አብሮ መታየት ያለበት የሀገራችን እርሻ የዝናብ ጥገኛ ከመሆኑ ባሻገር ለተለዋዋጭ አየር ንብረት ተጋልጧል። ወቅት ድርቅ በተደጋጋሚ የሚከሰት ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ነው እየታየ ያለው። ባለፈው ዘመናት ማለትም ከ20 ዓመታት በፊት ድርቅ በ10 እና በ15 ዓመታት ውስጥ የሚከሰት ነበር። ዛሬ በሁለት አንዳንዴም በአንድ ዓመት ውስጥ የሚመጣ አዙሪት ሆኗል። ይህ ሲከሰትም የእህል ምርት በመጥፋት ገበሬውን ከኑሮው ከማፈናቀል በዘለለ ሀገሪቱ ከግብርናው ዘርፍ የምታገኘውን ጥቅም አሳጥቶ ኢኮኖሚው እንዲዋዥቅ ያደርጋል። ይህ የመዋዠቅ ሁኔታም በድርቅ ወቅት ብቻ ሳይሆን በጤናማው ወቅትም የሚታይ ነው። በመኸር ወቅት ማለትም ከታህሳስ እስከ የካቲት ወር የተትረፈረፈ ምርት ወደ ገበያ ሲመጣ የእህል ዋጋ በገበያ ይረክሳል። መኸር ሲያልፍ ተመልሶ ይወደዳል። እህል ሲወደድም ተያያዥ የኢኮኖሚ አውታሮች ዋጋቸው ይንራል። ስለሆነም በድርቅ ሳቢያ እህል ምርት ሲያሽቆለቁል በሸማች ህብረተሰብ ላይ ዘርፈ ብዙ ጫና የማሳረፉ ጉዳይ በተጨባጭ የሚስተዋል ነው።

ስለሆነም የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን የሚያስችል ማናቸውንም ግብዓት ተመራጭነቱ የጎላ ነው። የባዮቴክኖሎጂ ጠቀሜታንም ከዚህ አንጻር መረዳት ተገቢ ነው። በሀገራችን የግብርና ምርምሮች መካሄድ ከጀመሩ ከ40 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። የምርምሩ ውጤት በተጨባጭ ሲመዘን ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ከዚህ ጋር በርካታ ጉዳዮች ተያያዥነት አላቸው። ስለሆነም ቴክኖሎጂው ተቀባይነት አለው። እንደዚያም ሆኖ የባዮቴክኖሎጂን በምን መልኩ ጥቅም ላይ ይዋል የሚለው ጉዳይ ማከራከሩን ቀጥሏል።

የመልካ ኢትዮጵያ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ስራ አስኪያጅ የሆኑት ዶ/ር ሚሊዮን በላይ እንደሚሉት ባዮቴክኖሎጂ ለእርሻ ምርታማነት አዎንታዊ ሚና መጫወቱ ምንም ጥርጥር የለውም። አሁን የበለፀጉት ሀገሮች የግብርና ምርትን ለራሳቸው ተጠቅመውና ለገበያ አቅርበው ከዚያም ባሻገር ለምፅዋት ጠያቂ ሀገሮች የእህል ርዳታ መስጠት የቻሉት በባዮቴክኖሎጂ በመታገዛቸው ነው። ነገር ግን በአሜሪካ በአውሮፓ እንዲሁም ባዮቴክኖሎጂን በስፋት በሚጠቀሙ ሀገሮች አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ህንድና ደቡብ አፍሪካ ያለው ሰፋፊ እርሻ አንደ አይነት ዘርን ብቻ፣ ከፍተኛ የውሃ ፍጆታን ኬሚካልንና መሰል የሳይንስ ውጤቶችን መጠቀሙ እጅግ በጣም ውድ ነው። በዚህ ላይ በብዝሃነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አምጥቷል።

በተቃራኒው በሀገራችን ለግብርናው ምርት እንደ የጀርባ አጥንት የሚያገለግለው በአነስተኛ መሬቶች ላይ የሚታረሰው የገበሬዎች ማሳ ላይ ነው። ገበሬው ግፋ ቢል የሚጠቀመው የባዮቴክኖሎጂ ውጤት የሆነውን ማዳበሪያ ብቻ ነው። አስተራረሱ ባህላዊ ሲሆን በዚህ አካባቢ ሰፋፊ እርሻ ለማቋቋም ቢሞከር የገበሬውን መፈናቀል ሊያስከትል ይችላል። ይህ ቢተገበር ባህላዊው የገበሬው የአዝዕርት የአስተራረስ እህልን የማከማቸት ድርቅንና በሽታን ሊቋቋሙ የሚችሉ የትኞቹ ዘሮች መሆናቸውን የመለየት እውቀት የምግብ አዘገጃጀት የጠላ፣ የንፍሮ፣ የዳቦ፣ የእንጀራ ጭምር ዝግጅት አብሮ ሊጠፋ ይችላል። ይህ ደግሞ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ስለሆነም በአነስተኛ መሬቶች ላይ እርሻን በሚጠቀሙ ገበሬዎች አካባቢ ባዮቴክኖሎጂን እንዴት መተግበር ይቻላል የሚለው በሳይንቲስቶች መልስ ማግኘት የሚገባው ጥያቄ ሲሆን የመንግስታት ፖሊሲዎችም ተደጋግመው ሊፈተሸ የሚችልበት አጋጣሚ መፈጠር አለበት። ምክንያቱም የምግብ ዋስትና ጉዳይ አሁንም ብዙ ትውልድን ተሻግሮ የመጣ ፈታኝ ጉዳይ ነው፡

     ዛሬም በሀገራችን ዝናብ ዘነበ አልዘነበ በየዓመቱ እስከ 6 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች ከውጭ በሚገኝ የምፅዋት እህል ህይወታቸውን ይገፋሉ። ይህ ሁኔታም በብሔራዊ ክብር ላይ ከባድ ጫና እያሰፈረ የሚገኝ ነው። አሁን ባለው አነስተኛና እጅግ በተበጣጠሰ መሬት ላይ በሚታረስ እርሻ የምግብ ዋስትና ይረጋገጣል ማለት ለብዙዎች ግራ አጋቢ ጉዳይ ነው። በዚህ ላይ ግማሽ የሚሆኑ የሀገራችን ገበሬዎች ከአንድ ሄክታር ያነሰ የመሬት ይዞታ ኖሮአቸው በምግብ ራስን የመቻሉ ጉዳይ በጣም ከባድ ነው። የእርሻ ግብአት ተጨምሮም ቢሆን የሚገኘው ምርት እስካሁን ራስን አላስቻለም። በዚህ ላይ የመሬት ስሪቱ ገበሬው ከሁለት ዓመት በላይ ከእርሻ ስራው ተነጥሎ በሌላ ስራ ቢሰማራ ይዞታውን እንዲያጣ ማድረጉ፣ ነገሩን ውስብስብ አድርጎታል። ስለሆነም የባዮቴክኖሎጂ ትሩፋትን በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ለእርሻው ዘርፍ የጀርባ አጥንት በሆነው በአነስተኛ ማሳ ላይ እንዴት ይተግበር የሚለው በጥልቅ ማሰብን የሚጠይቅ የትውልዱ የቤት ስራ ነው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1369 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 767 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us