በከተማችን ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና የሥራ ዕድል ፈጠራው

Wednesday, 01 October 2014 14:38

ደረቅ ቆሻሻ ከየዕለት ህይወታችን እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘና ከሰው ልጅ ፍላጐትን ከማሟላትና ከመጠቀም ጋር በቅርብ የተቆራኘና በዚህም ሳቢያ የሚፈጠር ነው። ሰዎች ከዕለት ፍጆታቸው የሚጠቀሙባቸው ምግቦች የእነርሱ ማሸጊያዎች፣ የዕቃ መጠቅለያዎች፣ ቁርጥራጭ ወረቀቶች፣ የውሃ ማሸጊያ ፕላስቲኮች፣ ተረፈ ምርቶች፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችና በአጠቃላይ አገልግሎት ሰጥተው ያበቁ አልባሳትን ጨምሮ ሌሎች ቁሳቁሶች በቆሻሻነት ውስጥ ይመደባሉ። እነኚህ ቁሳቁሶች በአግባቡ ካልተወገዱ አካባቢን በመበከል በሰውም ሆነ በእንስሳት ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራሉ። በአግባቡ ከተከማቹና ከተያዘ ደግሞ መልሰው ጥቅም ላይ ሊውሉ ከመቻላቸውም በላይ ሀብት ሆነው ለሌሎች ወገኖች የሥራ ዕድል መፍጠር ያስችላሉ።

የአዲስ አበባ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን በተመለከተ ስልጣን በተሰጠው የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ አማካኝነት የሚከናወን እንደሆነ የኤጀንሲው ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደለ ደመኮ ይገልፃሉ። እንደ እርሳቸው አነጋገር የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት የራሱ ፖሊሲ፣ ደንብና መመሪያ ያለው ሲሆን፤ በ1996 ዓ.ም የወጣው ደንብ ቁጥር 13 ለዚህ መሠረት ነው። ትኩረት የሚያደርገውም ከመኖሪያ ቤቶች፣ ከድርጅቶች፣ ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት ደረቅ ቆሻሻን በመሰብሰብ ያስወግዳል። የማጓጓዣ ስራን ከመስራት ባሻገር መልሶ መጠቀም የሚያስችለው ተቋም አማካኝነትም እንደገና ለአገልግሎት እንዲቀርብ ይደረጋል።

ከዚሁ ጐን ለጐን የመንግስትን የቆሻሻ አወጋገድ ጥረት ለማሳለጥ እንዲቻል ከ6ሺህ በላይ አባላት ያሏቸው ማኅበራት በከተማችን የተቋቋሙ ሲሆን፤ በ560 ማኅበራት ታቅፈው በመንግስት መርሃ ግብር አማካኝነት ስራቸውን ያከናውናሉ። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት የአካባቢንና የኅብረተሰብን ጤንነት ከመጠበቅ እንዲሁም ብክለት እንዳይከሰት ከማድረግ በተጨማሪ ለበርካታ ወገኖች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። የሥራ ባህልም እንዲዳብር አድርጓል። ከዚህ ጋር ተያይዞም፤ ሥራ ለመጀመር የግድ መነሻ ካፒታል ሳያስፈልግ ጤና ብቻ ካለ ሥራ መስራት እንደሚቻል አመልካች ነው።

ከዚህ አኳያ በመንግስት መርሃ ግብር በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሥራ የተሰማሩ በርካታ ወገኖች ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን በመጥቀም ላይ ይገኛሉ። በከተማችን በአስሩም ክፍለከተሞች የሚገኙ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አረጋውያን እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራጅተው ቆሻሻን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ በፅዳት ሥራው ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

በዚህ የሥራ ዘርፍ ተሰማርተው ለሌሎች መሰል ማኅበራት አርአያ መሆን ከቻሉት ውስጥ በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 2 የፅዳት አገልግሎት ኅብረት ሥራ ማኅበር እና የጐዳና ህይወት በእኛ ይብቃ የፅዳት ማኅበር አባላት ከዚህ አኳያ ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው። በማኅበራቱ ታቅፈው የሚገኙ አባላት ይህን ስራ ከመጀመራቸው በፊት ምንም ዓይነት ሥራም ሆነ ገቢ ያልነበራቸው አንዳንዶቹ ጭራሽ ለተለያዩ ወንጀል ሥራዎች የተጋለጡ ነበሩ። ከተደራጁ በኋላ ግን ተስፋቸው ለምልሞ ራሳቸውን በሥራ ጠምደውና ከተስፋቢስነት ተላቀው ወደተቃና ህይወት ለማምራት ያስቻላቸውን የደረቅ ቆሻሻ ሥራ በመስራት ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው መሆን ችለዋል። እንደማኅበሩ ሰብሳቢ ወጣት ሀጐስ አንተነህ ገለፃ አባላቱ በ1998 ዓ.ም የከተማ አስተዳደሩ የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲና የአነስተኛና ጥቃቅን ጽህፈት ቤት በጋራ በፈጠሩላቸው የሥራ ዕድል መሠረት ተደራጅተው ወደ ሥራው መግባት ችለዋል። ሥራውን ሲጀምሩም በአንዳንድ የማኅበር አባላት ዘንድ ሥራው እንደ አስቸጋሪ ተደርጐ ተወስዶ ነበር። ነገር ግን በቁርጠኝነትና በሙሉ ኃይል ሥራውን ሙያ አድርገው በመያዛቸው አሁን ላሉበት ስኬት በቅተዋል።

በከተማችን በርካታ ሊሰሩ ከሚችሉ ሥራዎች ውስጥ አንዱ ቆሻሻ የማስወገድ ሥራ ነው። በሌላ በኩል መሥራት እየቻሉ ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታ የሚያጠፉ ሌላው የለፋበትን ሀብት መዝረፍና እንደሙያ አድርገው የያዙ አላፊ አግዳሚውን የሚያንጓጥጡ መንደሮችን በፀብ የሚያምሱ በርካታ ወጣቶች ከመሠል ወጣቶች ተምረውና በጐ በማሰብ ወደ ሥራ በገቡ በወጣት ጥፋተኝነት ዘብጥያ ከመውረድ ድነው የራሳቸውን ህይወት በሰላም መምራት እንደሚችሉ ትምህርት ሊወስዱ ይገባል።

የአራዳ ክፍለ ከተማ የፅዳት ማኅበር አባላት እንደሚገልፁት፤ ሥራውን በጀመሩበት ዓመት የአንድ አባል የወር ደመወዝ ከ200 ብር ያልዘለለ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ሥራው ተስፋፍቶና ዋጋ እያገኘ መጥቶ የአንድ ሰው ደመወዝ ወደ 1ሺህ ብር ከፍ ብሏል። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው በትንሽ የተጀመረ ሥራ በሂደት ወደተሻለ ዕድገት የሚያደርስ መሆኑን ነው።

አባላቱ በአሁኑ ወቅት ከዕለት ህይወት ማሰብ አልፈው ስለነገው ህይወታቸው ማሰብና መጨነቅ ጀምረዋል። አባላቱ በመተዳደሪያ ደንባቸው መሠረት ከገቢያቸው በመቆጠብ የካፒታል አቅማቸውን በማጠናከር ላይ ይገኛሉ። የፅዳት ሥራውን ለማቀናጀት እንዲቻልም ከሌሎች ማኅበራት ጎን በወረዳው ጽ/ቤት አማካኝነት በመጣመር የተሳለጠ ሥራ በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ፅዳት አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ስዩም ለማ እንደሚገልፁት፤ በወረዳቸው በሁለት መልክ የፅዳት አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል። የመጀመሪያው በማኅበራት የሚሰጥ የፅዳት አገልግሎት ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ በኬዝ ቲም የተዋቀረና የተለያዩ መንገዶችን በማፅዳት የከተማዋን ውበት ማስጠበቅ ነው። በአካባቢው በፅዳት ሥራ ለተሰማሩ ማኅበራትም ወረዳው ጽ/ቤት ሥራ ቦታቸው ድረስ በመሄድ የማበረታቻ ድጋፍ ያደርግላቸዋል። በዚህም የተነሳ የሥራ አፈፃፀማቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ አጥጋቢ መሆን ችሏል። በወረዳው የቤት ለቤት ቆሻሻ የማሰባሰብ ሥራም ያለአንዳች መዛነፍ በመርሃ ግብሩ መሠረት መከናወን ችሏል።

በዚህም የተነሳ እንደ ማኅበሩ አባላት ገለፃ በአሁኑ ወቅት በወረዳው የነበረው የፅዳት ችግር በመቃለሉ የሚሰበሰብ ቆሻሻም እንደልብ እየቀነሰ መጥቷል። ይህ ሁኔታ ጥሩ ቢሆንም፤ ነገር ግን በአባላት ገቢ ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳረፈ ይገኛል። ይህ በመሆኑም አባላት ቆሻሻን እንደየገቢ ምንጫቸው ወስደው ቆሻሻን በተገኘው አጋጣሚ ተከታትለው በመሰብሰብ እንዲወገድ ያደርጋሉ። በአሁኑ ወቅት አባላት አሁን ከሚሰሩበት አቅም በላይ መስራት ችሎታው ቢኖራቸውም የተሰጣቸው የሥራ አካባቢ የመሬት ስፋት ውስን በመሆኑ በገቢያቸውም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው አንድን ሥራ፣ ሥራ ብለው ከያዙት የበለጠ እየወደዱትና እያከበሩት እንደሚመጡ ሲሆን፤ የወረዳው የፅዳት ሠራተኞችም ከገቢያቸው እየቆጠቡ በሚያስቀምጡት ገንዘብ ከፅዳት ሥራው በተጓደኝ ሌሎች ሥራዎችን ለመሥራት ሁኔታዎች እንደሚያስገድደቸውና በዚህ ረገድም ወረዳው ትብብር ሊያደርግላቸው እንደሚገባ ነው።

የወረዳው ጽ/ቤተ እንደሚገልፀው ቀደም ባለው ጊዜ በወረዳው ነዋሪዎች ዘንድ ደረቅ ቆሻሻን የማስወገዱ ሥራ የግንዛቤ ችግር ነበረበት ችግሩን ለመፍታትም በፅዳት ሰራተኞች አማካኝነት የቤት ለቤት የማስተማር ሥራ በመሠራቱ እንዲሁም መልዕክት የያዙ በራሪ ወረቀቶች ለኅበርተሰቡ እንዲደርሱ በመደረጋቸው በአሁኑ ወቅት ኅብረተሰቡ ለአካባቢው ጤና የሚሰጠው ዋጋ ከፍ ለማለት በቅቷል። የፅዳት ሥራ ሙሉዕ ሊሆን የሚችለው ሥራው በመንግሥት መመሪያና በሌሎች ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ብቻ አይደለም። መላው ኅብረተሰብ በባለቤትነት መንፈስ ሲነሳም ጭምር ነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያመለክተው በአሁኑ ወቅት በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ወረዳዎች ኅብረተሰቡ የፅዳት አገልግሎት ማግኘት የሚያስችለውን ክፍያ ይፈፅማል። በዚህም መሠረት ፅዳት ሠራተኞች ባወጡት መርሃ ግብር መሠረት በየቤቱ እየሄዱ ቆሻሻን ያወጣሉ። እንደ አቶ ታደለ ደመኮ ገለፃ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ነዋሪዎች መካከል 78 በመቶ የሚሆነው የጽዳት አገልግሎት ያገኛል። አብዛኛው ነዋሪ በሳምንት ሁለት ቀናት ደረቅ ቆሻሻን ከቤቱ በማስወገድ በተዘጋጀለት ስፍራ ያስቀምጣል። በሌላ በኩል በየቀኑ ከቤታቸው ቆሻሻን የሚያወጡ ሲኖሩ፤ ሻል ባለና የነዋሪው ቁጥር እምብዛም ባልተጨናነቀበት አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች በሳምንት አንድ ጊዜ እንከን ቆሻሻ የማያወጡ አሉ። ከዚህ አኳያ የሕዝብ አሰፋፈር በቆሻሻ ማመንጨት ረገድ የራሱን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት መረዳት አያዳግትም።

በከተማችን የሕዝቡ አሰፋፈር ከከተማዋ ማስተር ፕላን እንዲሁም ከኅብረተሰቡ የገቢና የኑሮ ደረጃ የሚወሰን ነው። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት 90 በመቶ የሚሆነው የከተማዋ ነዋሪ 15 በመቶ በማይሞላው የከተማዋ መሬት ላይ ተጨናንቆ ይኖራል። መጨናነቁም በአካባቢው በቂ የውሃ መውረጃ ቱቦ፣ ቆሻሻ መድፊያ፣ መፀዳጃ እንዲሁም ቆሻሻን ማስወገድ የሚያስችል የውስጥ ለውስጥ መንገዶች እንዳይኖሩ አድርጓል። ይህም ለአካባቢ ብክለት በተላላፊ በሽታዎች መስፋፋትና በፅዳት አለመጠበቅና ለመጥፎ ሽታ የመጋለጥ ሁኔታውን አባብሶታል። ከዚህ አንፃር በማስተር ፕላን በተሰሩና አነስተኛ ሰዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎችና በተጨናነቁ መንደሮች መካከል ያለው የፅዳት ልዩነትም እጅግ የተራራቀ ነው።

ከቅርብ ዓመታት በፊት የተደረገ አንድ የፎረም ፎር ኢንቫይሮሜንት ጥናት እንዳመለከተው ከከተማችን ነዋሪ መካከል 39 በመቶ የሚሆነው ደረጃውን የጠበቀ መፀዳጃ ቤት እንደሌለው አመልክቷል። ይህ ሁኔታም የሚስተዋለው በተጨናነቁ ቁጭራ መንደሮችና በርካታ ሕዝብ ተዳብሎ፣ ተጠጋግቶና ተፋፍጐ በሚኖርባቸው አካባቢዎች ነው። ከዚህ አንፃር የከተማ ማስተር ፕላንና የሚገነቡ መኖሪያ ቤቶች ለከተማዋ ፅዳት መጠበቅ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ መረዳት የሚቻል ሲሆን፤ ከማስተር ፕላን ውጭ የሚሰሩ መኖሪያ ቤቶችም ለአካባቢ መበከልና ለፅዳት መበላሸት አስተዋፅኦ አላቸው።

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የከተማ ፅዳት እንዲጠበቅ የከተማው የፅዳት አስተዳደር አጀንሲ በተለይ በማኅበር ከተደራጁ ፅዳት ሠራተኞች ጋር በመተባበር ፅዳት እንዲጠበቅና ቆሻሻ ከቦታ ቦታ እንዲጓጓዝ በማድረግ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል። ይሁን እንጂ ከየቤቱ የተሰበሰበው ቆሻሻ አልፎ አልፎ በገንዳ ውስጥ ተከማችቶ ለቀናትና ሳምንታት ተከማችቶ አካባቢን በመጥፎ ሽታ ማወዱ የፅዳት ስራውን እጀ ሰባራ እንደሚያደርገው የተለያዩ ነዋሪዎች ሲገልፁ ይስተዋላል። ይህን በተመለከተ የፅዳት ኤጀንሲው ምን ለማድረግ እንዳሰበ የተጠየቁት አቶ ታደለ ሲገልፁ፤ እንደተባለው አልፎ አልፎ ገንዳዎች በወቅቱ አለመነሳታቸው አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳመጣ ጠቅሰው ችግሩን ለመፍታት ኅብረሰቡ በሚሰጠው ጥቆማ መሠረት የቆሻሻ ገንዳዎች እንዲነሱ እንደሚደረግ አመልክተዋል። እንደዚያም ሆኖ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ ፍላጐት ካለው የቆሻሻ ማስወገጃ መኪና አቅርቦት ጋር እንደማይመጣጠን ጠቁመው መንግስት ችግሩን ለመፍታት አዳዲስ የቆሻሻ ማንሻ መኪናዎችን ከውጭ ሀገር ለማስወጣት ከሚመለከታቸው ኩባንያዎች ጋር ውል ፈፅሞ የተወሰኑት ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ቀሪዎቹን በቅርቡ ተጠቃለው ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡ ተናግረዋል።

     እንደ እርሳቸው ገለፃ አዲስ አበባ ከአለም አቀፍ ዝናዋ ጋር የሚመጣጠን የፅዳት ስርዓት ያስፈልጋታል። ይህ እንዲሆንም፤ ከገንዳ ስርዓት መላቀቅ ይኖርባታል። ለዚህም ቆሻሻ በአንድ ቦታ ተጠራቅሞ በኮምፓክት ማሽን የሚሰበሰብበት ሥርዓት እንዲፈጠር ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ እንቅስቃሴ ተገብቷል። የዚህ መሰሉ አሰራርም በበለፀጉ ሀገሮች እየተተገበረ የሚገኝ ሲሆን፤ ሙሉ በሙሉ በሀገራችን ከተተገበረው የከተማዋን የፅዳት ደረጃ በእጅጉ ይቀይረዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የመንገድ ፅዳትን ለማሳለጥ እንዲቻል ከ3ሺህ በላይ ሰራተኞች ተመድበው በየዕለቱ ጠዋት ንጋት ላይ ወደ ሥራ እንዲሰማሩ መደረጉን ተናግረዋል። በየሁለት ኪሎ ሜትሮችም ሦስት ፈፃሚዎች ተመድበው ሥራው በመሠራት ላይ እንደሚገኝ ምክትል ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል። በአጠቃላይ የከተማችን ጽዳት መጠበቅ ከሥራ ፈጠራ ጋር ከተቆራኘ ዘርፉ ለበርካታ ወገኖች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ሲሆን፤ ይህ ሁኔታም ወደ ዘመናዊ አሠራር ከተቀየረ ቆሻሻ ሳይወገድ ወደ ኃይል ምንጭነት ተቀይሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ሊሰጥ ይችላል።

ይምረጡ
(14 ሰዎች መርጠዋል)
3033 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 958 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us