የእርሻውን ዘርፍ ከመሠረቱ ይቀይረዋል የሚባለው የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት

Wednesday, 08 October 2014 13:09

የአፍሪካ ህዝብ ብዛት ባለፉት 40 ዓመታት ከ270 ሚሊዮን ወደ 850 ሚሊዮን አሻቅቧል። የእንስሳት ቁጥሩም የዚያኑ ያህል በብዙ እጥፍ እንዳደገ እ.ኤ.አ. በ2014 በአፍሪካ ግሪን ሪቮሉሽን ፎረም የወጣው የእርሻ ሪፖርት ያመለክታል። የህዝቡ ቁጥር እድገት አሁን ባለው አካሄድ ከቀጠለም በ2050 ወደ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን እንደሚደርስ በሪፖርቱ ተጠቅሷል። ከዚህ አኳያ ይህን በቁጥር እየጨመረ የሚሄደውን ሰውና የቤት እንስሳት በህይወት እንዲቆይ ለማድረግና በተገቢው ለመመገብ የእርሻ ምርታማነት በብዙ እጥፍ ማደግ እንዳለበት ሪፖርቱ አመልክቷል።

በቅርቡ በመዲናችን በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንና በአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ፎረም ትብብር ተዘጋጅቶ በነበረው ስብሰባ ላይ ከአራት ሺህ በላይ የሚሆኑ ሳይንቲስቶች የመንግስታት መሪዎችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኃላፊዎችና ኤክስፐርቶች በተገኙበት አፍሪካን የእርሻ ዘርፍ ለማዘመን እንዲሁም በየጊዜው እየተቀያየረ ከሚመጣው የአየር ንብረትና የሙቀት መጨመር ለመታደግ እንዴት እንደሚቻል የተለያዩ ሃሳቦች ተንሸራሽረው የጋራ አቋም በመንግሥታት ደረጃ እንዲወሰድ እንዲሁም በዘርፉ መንግስታት ቃል ገብተው የነበረውን የበጀታቸውን 10 በመቶ ለዘርፉ የማዋል ጉዳይ ከምር እንዲተገበር ማሳሰቢያ ቀርቧል። ስብሰባው ከስምንት ዓመታት በፊት የአረንጓዴ ፎረሙ በሞዛምቢክ ዋና ከተማ በማፑቶ ስብሰባውን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያካሂድ መንግስታት በአሁኑ ወቅት አፍሪካ በምግብ እጥረት በድህነትና በኋላ ቀር አስተራረስ ዘዴ ተቀፍድዳ የምግብ ተመፅዋች ብትሆንም እስካሁን ድረስ በተገቢው ጥቅም ላይ ያልዋለው የእርሻ መሬትዋ እንዲሁም የውሃ ሀብትዋ በቴክኖሎጂ ታግዛ እንዲለማ ከተደረገ ከራስዋ አልፋ ለዓለም ገበያ የእርሻ ምርትን በማቅረብ ከሌሎቹ አህጉራት ጋር ተፎካካሪ መሆን እንደምትችል ጥናቱን አቅርቦ ከዚያን ወቅት ጀምሮ በተመረጡ ሀገሮች የተካሄደው እርሻን የማዘመን ስራ ፍሬያማ እየሆነ መምጣቱ በአፍሪካ ህብረት በተደረገው ስብሰባ ተገልጿል።

በእለቱ የኢትዮጵያው ግብርና ሚኒስትር አቶ ተፈራ ደርበው የኢትዮጵያን የእርሻ ልማት እንቅስቃሴን አስመልክተው እንደተናገሩት ባለፉት 10 ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለ ሁለት አሀዝ እድገት እንዲያስመዘግብ ካስቻሉት ዘርፎች አንዱ የእርሻ ክፍለ ኢኮኖሚ ምርታማነት መጨመሩ እንደሆነ ጠቅሰው ይህ እንዲሆንም አርሶ አደሩ በቂ ግብአቶችን ማለትም ማዳበሪያ ፀረ ተባይ መድሃኒት እንዲሁም የተሻሻሉ አዝዕርቶችን መጠቀምና ክህሎቱን ማሳደጉ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረጉን አመልክተዋል። አክለውም ገበሬው ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴዎችን እንዲጠቀም በሺህዎች የሚቆጠሩ የእርሻ ኤክስቴንሽን ሰራተኞች እገዛ ማድረጋቸው ገበሬው በራሱ ተነሳሽነት የአካባቢ ጥበቃ ስራና የተፋሰስ ልማት ስራዎችን ማከናወኑ ዝናብ በበቂ ሁኔታ እንዲመጣ እንዲሁም የዝናብና የጅረት ወንዞችን በአነስተኛ መስኖ ስራ ግብአትነት መጠቀም እንዳስቻለው ይህም አዎንታዊ ውጤት እንዳስገኘ አመልክተዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ ኢትዮጵያ በማፑቶው ስብሰባ ሀገሮች 10 በመቶ የሚሆነውን በጀታቸውን ለእርሻው ዘርፍ እንዲመደቡ የተወሰነውን ውሳኔ መተግበሯን አረጋግጠው በአነስተኛ መሬት ይዞታ የእርሻ ስራ የሚያከናውኑ ገበሬዎች ምርታማነታቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱና በዚህም ተጠቃሚ በመሆናቸው ገንዘባቸውን መልሰው በእርሻ ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንዳስቻላቸው አስረድተዋል። ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት በተለይም ገበሬው የልፋቱ ውጤት የሆነውን የእርሻ ምርት በደላሎች ሳይዘረፍ መንግስት ባቋቋመው የምርት ገበያ ድርጅት አማካኝነት ለሸማች ማቅረብ መቻሉ ለሌሎች ሀገሮች በአርአያነት ሊጠቀስ እንደሚችል አስታውቀዋል።

የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ፎረምን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሲመሩ የነበሩት የቀድሞው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ጋናዊው ኮፊ አናን በበኩላቸው እንደተናገሩት አፍሪካ ያልተጠቀመችበት የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ሀብት ክምችት አላት። ነገር ግን ይህን ሀብት በድህነት በገንዘብና በቴክኖሎጂ እጥረት የተነሳ ልትጠቀምበት አልቻለችም። በዚህ የተነሳም ከምግብ ተመፅዋችነት ለመላቀቅ አልቻለችም። ይባስ ተብሎም የህዝብ ቁጥርዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ በመሄዱ በአሁኑ ወቅት አህጉሪቱ በየ ዓመቱ 35 ቢሊዮን ዶላር በማውጣት ከውጭው ዓለም እህል እንደምትሸምት አስረድተዋል። ይሁን እንጂ እንደ ሚስተር ኮፊ አናን ገለፃ የአፍሪካ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው የአነስተኛ ገበሬዎች እርሻ በተገቢው እንክብካቤና ድጋፍ ተደርጎለት ምርታማነት በብዙ እጥፍ እንዲጨምር ቢደረግ የአፍሪካን የምግብ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ በመሸፈን ለእህል መሸመት የሚወጣው 35 ቢሊዮን ዶላር የአፍሪካ ደሃ ገበሬዎች ይበልጥ ባለፀጋና ዘመናዊ አምራች ሊያደርጋቸው እንደሚችል ጠቅሰው ይህንንም የመንግስታት ቁርጠኝነት ካለ መቶ በመቶ እውን ማድረግ እንደሚቻል አስታውቀዋል።

ኮፊ አናን በራስ መተማመን መንፈስ በተሞላበት በዚያ ንግግራቸው የአፍሪካ ምርታማነት እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው። በአምስት አመታት ጊዜ ውስጥም በእጥፍ ማደግ ይቻላል። የአፍሪካ አነስተኛ ገበሬዎች በተለይም አብዛኛዎቹ በሴቶች የሚታረሱት እርሻዎች አፍሪካውያን ምን ያህል የእርሻ ፈጠራ ስራ ሙያ እንዳላቸው በዚህ ዘዴያቸውም ለአየር ንብረት ተጋላጭነትን መቋቋም እንደሚቻል ማሳየት ችለዋል ብለዋል። ይሁን እንጂ በመሬት ላይ ያለውን እውነታ መመልከት አስፈላጊ ነው። በአሁኑ ወቅት ከጥቂት ዘመናዊ እርሻን ከሚጠቀሙ ሀገሮች ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካና ናይጄሪያን ከመሳሰሉት በስተቀር በአነስተኛ የመሬት ይዞታ ላይ የሚጠቀሙ ገበሬዎች የአስተራረስ ዘዴያቸው ከብዙ ሺህ ዓመታት ጀምሮ ስራ ላይ ከዋለው እምብዛም የተለየ አይደለም። የእርሻው ስራ የሚከናወነው ዝናብን ታሳቢ አድርጎ ነው። ዝናብ ከመጣ የተሻለ ምርት ይገኛል። ከቀረም እህሉ ጭራሹንም ሊቀር ይችላል። የከብት ርባታው ዘርፍም ቢሆን የግጦሽ መሬትን በማሰስ ከቦታ ወደ ቦታ በሚደረግ ፍልሰት ላይ የተመሰረተ ነው። በዝናብ እጦት የእርሻ ምርት እንደሚቃወሰው ሁሉ የከብት እልቂትም የዚያኑ ያህል ይከሰታል። የከብት ርባታ ምርታማነት ዝቅተኛ በመሆኑ የህዝቡ የስጋ መመገብም ሆነ የወተት ፍጆታው በጣም አናሳ ነው። በአፍሪካ ባህር ዳርቻዎች የተትረፈረፈ የአሳ ሀብት ክምችት ቢኖርም አህጉሪቱ አልተጠቀመችበትም። ጭራሹንም በህንድና አትላንቲክ ውቅያኖስ የአፍሪካ የባህር ጠረፎች ተገቢው ጥበቃ ስለማይደረግላቸው የአሳ ሀብቱ በውጭ የአውሮፓ የሩሲያ፣ የደቡብ ኮሪያና በምስራቅ እስያ ሀገሮች ኩባንያዎች እየተዘረፈ እንደሚገኝ የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት የ2014 ሪፖርት ያመለክታል።

የአፍሪካ ገበሬዎች ኑሮአቸው ከእጅ ወደ አፍ በመሆኑ ለእርሻቸው የሚጠቀሙት የማዳበሪያና የተባይ ማጥፊያ፣ የመስኖ ውሃና የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮች በጣም አናሳ ነው። በዚህ ሳቢያም የሚገኘው ምርት በጣም ዝቅተኛ ነው። ምርቱ ከተገኘ በኋላም ምቹ በሆነ የእህል ማከማቻ ጎተራ ውስጥ ባለመቀመጡ እንዲሁም ከዋናው የትራንስፖርት መንገድ ከ5 ሰዓታት በላይ በእግር ተጉዞ በሚገኝ አካባቢ መሆኑ በማከማቸቱና በማጓጓዙ ውድነት የሚባክነው ጊዜና የሚበላሸው ምርት በጣም ከፍተኛ መሆኑ ገበሬዎችን ይበልጥ ተጎጂ ያደርጋቸዋል። እነኚህና መሰል ችግሮች ካልተቀረፉ የእርሻ ውጤታማነትን ማምጣቱ እጅግ ከባድ ነው።

በሪፖርቱ እንደተመለከተው በአፍሪካ ካለው የእርሻ ምርታማነት ዝቅተኝነት የተነሳ በአንድ ሄክታር 10 ኩንታል እህል ብቻ ይመረታል። ይህ ምርት የአንድ የህንድ ገበሬ አንድ ሶስተኛ የአንድ ቻይና ገበሬ አንድ አራተኛ እንዲሁም የአንድ አሜሪካዊ ገበሬ አንድ አምስተኛ ምርት ነው። ይህም የአፍሪካን የምግብ እጥረትና የውጭ ጥገኝነት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። በሌላም በኩል ሲታይ የአፍሪካ ጠቅላላ የእርሻ ምርት ከታይላንድ ጠቅላላ የእርሻ ምርት ያነሰ መሆኑ በዘርፉ እጅግ በጣም ሰፊ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ያመለክታል።

የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ፎረም በዚህ ረገድ እንደሚመክረው መንግስታት የእርሻው ዘርፍ እንዲዘምን መሰረተ ልማቶች በሰፊው መዘርጋት አለባቸው። ይህም የእርሻ የሚሆን የግብአት አቅርቦትን ለማሳለጥ ይረዳል። ቴክኖሎጂ የአሰራር ዘዴዎችን ለማድረስ እንዲሁም ምርታቸውን ወደ ገበያ ለማቅረብ ያስችላቸዋል። ምርታማነት እንዲጨምር የመስኖ የእርሻ ከማስፋፋት በተጨማሪ የአፈሩ ጤንነት የተጠበቀ እንዲሆን የናይትሮጂን መጠኑ እንዲጨምር ኦርጋኒክና ኦርጋኒክ ያልሆነ ማዳበሪያን በስፋት ስራ ላይ ማዋል ይገባል።

ይሁን እንጂ የአፍሪካ እርሻ እንዲዘምንና ምርታማነት እንዲጨምር የእርሻ ግብአትን ማስፋፋትና ማጠናከሩ እንዳለ ሆኖ የእርሻ ይዘትና የባለቤትነት መብት በትክክል መረጋገጥ እንዳለበት ከሙያተኞች አስተያየት ቀርቧል። ገበሬዎች በእርሻቸው ላይ ለዘለቄታው ኢንቨስት ማድረግ እንዲችሉ ከተፈለገ የእኔ ነው የሚሉት ሰፋ ያለ መሬት ሊኖራቸው ይገባል። መሬቱን ከእርሻነት በተጨማሪ በኮላተራል መልክ መሬቱን በማስያዝ ከባንክ ገንዘብ መበደር የሚችሉበት ሁኔታ መፍጠር ወሳኝ ነው። ይህ ሲሆን በገንዘቡ የሚፈልጉትን የእርሻ ግብዓት ተጠቅመው የመሬት ምርታማትን ማሻሻል ይችላሉ። ከዚያ አልፈው በማከራየትም ሆነ ለሌላ ሰው በማስተላለፍ በተለያየ የሙያ ዘርፍ የመሰማራት መብታቸው ቢጠበቅ የእርሻ ትራንስፎርሜሽን ሊረጋገጥ እንደሚችል ሙያተኞች አመልክተዋል። ይህን በተመለከተ በወቅቱ የአፍሪካ የአረንጓዴ አብዮት ፎረም ፕሬዝዳት ሚስስ ጃኒ እንደተናገሩት የእርሻ ምርታነትን ለማረጋገጥ የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ ነገርግን ፎረሙ ስለ ዝርዝር አካሄዶች ለመንግስታት እንደማይገልፅ ጠቅሰው በተለይ የመሬት ስሪትን በተመለከተ መንግስታት የየራሳቸው አቅጣጫና ፖሊሲ እንዳላቸው አስረድተዋል።

የመሬት ስሪትና ሥርዓተ ለእርሻ ምርታማነት መጨመር ወሳኝ እንደሆነ በሀገራችን የተለያዩ ሙያተኞች ሲገልጹት ቆይተዋል። የባለቤትነት ስሜት አለመኖር በእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው በተደጋጋሚ ቢገለፅም በሀገራችን ያለው ገዢው ፓርቲ ግን የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ በህገ መንግስት የመንግስት ይዞታ መሆኑ የተረጋገጠ በመሆኑ ጉዳዩ ለምንም አይነት ድርድር አይቀርብም ብሎ ከድምዳሜ እንደደረሰ አይዘነጋም።

በሌላም በኩል የአፍሪካ እርሻ ወደ ዘመናዊነት እንዲቀየር የውጭ ኢንቨስትሜንት ወደአህጉሪቱ መግባት እንዳለበት በስፋት ተገለጿል። እንደሪፖርቱ ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ የውጭ ኢንቨስትሜንት ከጊዜ ወደ ጊዜ ጨምሯል። በርግጥ ከውጭ ኢንቨስትንቱ ተጠቃሚ የሆነው የሰርቪስና የማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ ቢሆንም በሂደት ወደ እርሻው ይበልጥ እንዲመጣ ይበልጥ መንግስታት መትጋት ይኖርባቸዋል። መንግስታት በኢኮኖሚ እድገታቸው ያገኙትን ገንዘብ ወደ እርሻው እንዲዞር የሚያደርጉት ጥረት በአዎንታዊ የታየ ሲሆን እርሻውን ከማሳደግ በተጨማሪ አራሹ ህዝብ ከእርሻ ስራ ተነስቶ ወደ አገልግሎቱ ዘርፍና ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲጎርፍ በማድረግ እርሻው በውስን የሰው ሃይልና በቴክኖሎጂ ድጋፍ እንዲከናወን ማድረግ እንደሚገባ በእለቱ ተገልጿል።

    ከዚህ አንጻር የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሚስስ ደሊሚኒ ዙማ የገለፁት ተጠቃሽነት አለው። ከ50 ዓመታት በፊት የደቡብ ኮሪያ፣ የጃፓን፣ የማሌዥያና የታይዋን እርሻ አሁን አፍሪካ ካለው እርሻ ተመሳሳይነት ነበረው። ብዙው ህዝብ በተበጣጠሰ የእርሻ መሬት ላይ ህይወቱን ይገፋ ነበር። ነገር ግን ባለፉት 50 አመታት ውስጥ ባመጡት ፈጣን እድገት የተነሳ አብዛኛው አራሽ እርሻ ወዳልሆነው አገልግሎቱና ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተሰማርቷል። እርሻውም በዘመናዊ ቴክኖሎጂና ሜካናይዝድ ዘዴ ተቀይሮ የእርሻ ምርታቸው ለውጭ ገበያ እየቀረበ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ ይገኛል። የእርሻ ትራንስፎርሜሽን ሲባልም እርሻውን ዘመናዊ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በእርሻ ስራ የተሰማራውን ወደ ሌላ የኢኮኖሚ ዘርፍ እንዲዛወር ማድረግ ነው። በአሁኑ ወቅት ለአፍሪካ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥነት በሆነው እርሻ ላይ 70 በመቶ የሚሆነው ሠራተኛ ህዝብ መሰማራቱ ለአህጉሪቱ አዋጭ አይደለም። በሂደት ወደሌላ ዘርፍ መሰማራት አለበት። ይህ ሲሆንም የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርቱ ይበልጥ ከአገልግሎቱና ከኢንዱስትሪው የሚገኝ ሲሆን የእርሻው አስተዋፅኦም አነስተኛ ይሆናል። ይህም ለአካባቢ ጥበቃም አዋጭ እንደሆነ ሙያተኞች በእለቱ ተናግረዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1217 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 987 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us