የመናገሻን አፈር ከጥፋት ለማዳን …

Wednesday, 29 October 2014 14:57

በመላኩ ብርሃኑ

 

የክረምት ዝናብ የጠገበው መሬት ሲረግጡት ስምጥ ስምጥ ይላል። አረንጓዴ ለብሶ ለጥ ባለው መስክ ላይ የፈሰሱት የቀንድና የጋማ ከብቶች በስብጥር ለስፍራው አይን የሚያፈዝዝ ውበት ቸረውታል። እረኝነት የወጡ ህጻናት የገመዱትን ጅራፍ እያጮሁ በደስታ ይቦርቃሉ። ማርቆስ እና ኮሎቦ የተባሉት ሁለቱ የመናገሻ ከተማ ቀበሌዎች የሚዋሰኑበት ይህ ለጥ ያለ ሜዳ በለመለሙ ዛፎች የተሸፈነውን የመናገሻ ተራራ ትራስ አድርጎ ተዘርግቷል። አብዛኛው የመሬቱ ክፍል ለእርሻ ስራ የዋለ ሲሆን በጥቂት ቦታዎች ላይ ተራርቀው የበቀሉ ባህርዛፎች ይታያሉ። ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡ ምዕመናን ከተራራው ስር ወደተቆረቆረችው መናገሻ ማርያም ቤተክርስቲያን የሚጓዙት ይህንን መሬት አቋርጠው ነው።

ይህንን የመሰለውን የተፈጥሮ ውበት አለንጋ እንዳረፈበት ገላ እዚህም እዚያም ሸነታትረው ያበላሹት ቦዮች አፈሩን ከሳሩ አላቅቀው ለጸኃይ አጋልጠውታል። ቦዮቹ አፈሩን እያጠበ ከተራራው የሚወርደውን ውሃ ያለከልካይ በሜዳው ላይ እንዲጋልብ ማለፊያ መንገድ ሰጥተውታል። ብዛት ያላቸውን አነስተኛ ማሳዎች ዳር ዳር ከብበውና መሃል ለመሃል ገምሰው የገበሬውን የእርሻ መሬት እያጠበቡበትም ነው። አሁን አሁን ይህ ችግር የአካባቢውን የግብርና ስራ ፈተና ውስጥ እየከተተው መምጣቱን ነው አርሶአደሮቹ የሚናገሩት።

አርሶአደር ሸለመ በዳኔ በከፊል የታረሰ ማሳቸው ዳር ቆመው መሬታቸውን ተስፋ በቆረጠ እይታ ይቃኙታል። ቀስ በቀስ እየሰፋ መጥቶ በሁለት ዓመታት ውስጥ ማሳቸውን ለሁለት የከፈለው ሰፊ ቦይ ቤተሰቦቻቸውን ሲመግቡበት የኖሩትን ግብርና አስቸጋሪ አድርጎባቸዋል። ይህ ቦይ በተለይ ጠንከር ያለ ዝናብ በሚጥልበት ወቅት ሁሉ አፈሩን እየሸረሸረ ስፋቱን መጨመሩ ለእኚህ አርሶአደር ራስ ምታት ሆኖባቸዋል።

“ውሃው በማሳዬ ውስጥ እንዳያልፍ ያደረግኩት ጥረት ሁሉ አልተሳካም። የሰራሁት መከላከያ ሁሉ ዝናብ ሲዘንብ እየተናደ የእርሻ መሬቴ አፈር በጎርፍ እየታጠበ ነው። ጭራሽ መሬቴን ለሁለት ከፍሎ በበሬዎቼ ላይ ታች እያልኩ ለማረስ የማልችልበት ደረጃ ላይ አድርሶኛል። መሬቱ በመጥበቡም የማገኘው ምርት እየቀነሰ መጥቷል። የሆነ አካል መፍትሄ ካላበጀልኝ በቀር ይህ የአፈር መሸርሸር ነገ መሬቴን ነጥቆኝ ልጆቼን በረሃብ እንዳይበትንብኝ እየሰጋሁ ነው” ይላሉ ፍርሃት በተጫነው ስሜት ሁኔታውን ሲገልጹ።

በንግድ ስራ ለሚተዳደሩት አቶ ከተማ ኢብሳ አሳሳቢ የሆነባቸው ደግሞ ወደመንደራቸው የሚያስገባው መንገድ በጎርፍ መበላሸቱ ነው። “በስንት ርብርብ የተሰራ አንድ ኮረኮንች መንገድ ቢኖረን ዝናብ በዘነበ ቁጥር ከመናገሻ ዳገት ላይ የሚመጣው ውሃ አፈሩን እየሸረሸረ ቦዮች ሰራበት። በበጋ የደለደልነው አፈር በክረምት እየተናደ መንገዱን ወጣ ገባ ስላደረገው አሁን መኪና ወደስፍራው መግባት እየተሳነው ነው። ከዚህ ሁሉ በላይ በክረምት ወቅት መንገዱ ሁሉ ውሃ መውረጃ እየሆነ ለመተላለፍ አስቸጋሪ ሆኖብናል። ችግሩ በዚሁ ከዘለቀ ነገ ከቤቱ የወጣ ሰው መመለሻ ስለማግኘቱ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቸግራል” ይላሉ ስጋት ባጠላበት ድምጸት።

እነዚህ ነዋሪዎች የሚያነሱት ዓመታትን የዘለቀ የአፈር መሸርሸርና መሸሽ ችግር የመናገሻ ከተማን እጅግ እያሳሰባት ነው። የከተማው ማዘጋጃ ቤት “በአፈሩ ላይ የሚደርሰው ጥፋት በጊዜ ካልተቋጨ ወደፊት ለከተማዋ ከፍተኛ ስጋት መሆኑ አይቀሬ ነው” ይላል።

እጇን በእጇ የቆረጠች ከተማ

ወይናደጋ የአየር ንብረት ያላት መናገሻ ከተማ ከአዲስ አበባ በ28 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን በደረጃ 3 ከተመዘገቡት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከተሞች አንዷ ናት። ከተቆረቆረች 79 ዓመት ቢሞላትም እንደከተማ እውቅና ያገኘችው ግን በ1998 ዓ.ም ነው። ከ26ሺህ በላይ የሆኑትና በወጣ ገባ መሬቷ ላይ የሰፈሩት ነዋሪዎቿ በአብዛኛው መተዳደሪያቸው ግብርና በመሆኑ ለመናገሻ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ጉዳይ ዋና አጀንዳዋ ነው።

ከመግቢያዋ ጀምሮ የሚያጥራት የመናገሻ ተራራን ጨምሮ በዙሪያዋ ያለው የወጨጫ ተራራ ከተማዋን መሃል አስገብተው አቅፈዋታል። በተለይ ከጥፋት ከተረፉትና ከፍተኛ እንክብካቤና ጥበቃ ከሚደረግላቸው የደን ክልሎች ውስጥ የሚመደበው የሱጳ ጥብቅ የተፈጥሮ ደን ክልል ስለሚያዋስናት የአየር ንብረት ሚዛኗ የተጠበቀ፣ አፈሯም ለምነቱን እንደያዘ ረጅም ዘመን የዘለቀ ነው። የመናገሻ ዙሪያ በደን የተሸፈነ በመሆኑ ዝናብ አያጣውም። ማርቆስ እና ኮሎቦ የተባሉትና በ2000 ዓ.ም በተከለሰው ማስተር ፕላን የመናገሻ ከተማ አካል የሆኑት የአርሶአደር ቀበሌዎች በለም መሬታቸው የሚታወቁ ናቸው። ይህ የተፈጥሮ ሃብት የሚገባውን ያህል እንክብካቤ ሳያገኝ በመቅረቱ ሳቢያ ዛሬ ፊቱን እያዞረ ነው።

ለዓመታት የተካሄደው የደን ምንጠራ ከግጦሽ መሬት ማስፋፋት እና ከአካባቢው ገበሬዎች ኋላ ቀር የአስተራረስ ዘይቤ ጋር ተዳምሮ መሬቱን ለጥፋት የተጋለጠ አድርጎታል። በዚህም ሳቢያ አፈሩ በተደጋጋሚ ጊዜ በጎርፍ የመታጠብና የመሸርሸር አደጋ ስለገጠመው ለምነቱን እያጣ ነው። መሬት ቆንጥጠው የሚይዙና አፈር አቃፊ ስር ያላቸው ሃገር በቀል ዛፎች ተመንጥረው በማለቃቸውም በተለይ በወጨጫና በመናገሻ ተራሮች ላይ ያለው አፈር በውሃ ታጥቦ እንዲንሸራተትና እንዲናድ ምክንያት ሆኗል።ይህ ብቻም ሳይሆን ከዳገታማ አካባቢዎች ተነስቶ ተዳፋት ስፍራዎች ላይ የሚያርፈው ውሃ ለእርሻ ስራ የዋለውን መሬት እያጠበና የአፈሩን ለምነት እያሳጣ በግብርና ምርት ውጤታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥሯል። የውሃው ሃይል አፈሩን በጥልቀት እየቦረቦረ የሚፈጥረው ትላልቅ ቦይ በአካባቢው የበቀሉ ባህርዛፎችን ስር ከአፈር እያላቀቀ እንዲወድቁ አድርጓቸዋል። ይህም በተለይ ኮረቦዳ፣ አሊያንስ እና መናገሻ ማርያም የተባሉት አካባቢዎች ላይ የከፋ ችግር እንዲከተል ምክንያት ሆኗል።

ተፈጥሮ ለምነት ያደላትና ከሌሎች የሃገራችን ከተሞች ጋር ሲነጸጸር አንጻራዊ የሆነ የደን ሽፋን ያላት መናገሻ ከተማ ላጋጠማት የአፈር መታጠብ፣ ሽሽት እና መሸርሸር ምክንያቱ የአካባቢ ጥበቃና እንከብካቤ መጓደል መሆኑን ሁሉም ይስማሙበታል። ይህ ሰው ሰራሽ ችግር ነው መናገሻን “እጇን በእጇ የቆረጠች ከተማ” ያስባላት።

ነዋሪው የቆየ ስህተቱ የፈጠረውን ችግር ለማስተካከል ዛሬ ላይ አንዳንድ ጥረቶችን ማድረጉ ግን እውነት ነው። የመናገሻ ነዋሪና የሆለታ ደን ምርምር ማዕከል ሰራተኛ የሆኑት አቶ እሸቱ ደስታ ከተማዋን ከጊዜ ወደጊዜ ስጋት ውስጥ እየከተተው ያለውን የአፈር መሸርሸር እና መንሸራተት ችግር ለማስወገድ ነዋሪው ያደረጋቸው ጥረቶች በሙሉ አልተሳኩም ነው የሚሉት።

“አብዛኛው ቦታ ተዳፋት ስለሆነ አፈሩ በዝናብ ውሃ ለመታጠብ የተጋለጠ ነው። ችግሩን ለመከላከል በበጋ የሚሰራው እርከን ገና ሰኔ ሲገባና ዝናብ መጣል ሲጀምር ይናዳል። እንደመናገሻ እና ወጨጫ ባሉ ተራሮች ላይ የተሰሩ ሰፋፊ የእርከን ስራዎች ጎርፍ እያዘሉ በተደጋጋሚ ጊዜ በመናዳቸው የተነሳ ገበሬው መሬቱን ባንነካካው ይሻላል እያለ ነው። እንደሚመስለኝ አፈሩን አቅፎ የያዘው ደን ከላዩ ላይ ተጨፍጭፎ ስላለቀ መሬቱ አሁን ሳስቷል። በቀላሉ የሚናደውም ለዚህ ይመስለኛል። ገበሬው ከዳገቱ ላይ በሃይል የሚመጣው ውሃ እህሉን እንዳያጥብበት ሲል የሚሰራው ቦይ ጎርፍ እያጠራቀመ የበለጠ ጥፋት እያደረሰ ነው። በተለይ ማርቆስ ቀበሌ ውስጥ ውሃው የእርሻ መሬትን አፈር ጠራርጎ እየወሰደው ነው።” ይላሉ።

አቅምን የፈተነ ጥፋት

“ችግሩ ከከተማችን የበጀትም ሆነ የሰው ሃይል አቅም በላይ ሆኗል” ይላሉ የመናገሻ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ከንቲባ አቶ ሶፊሳ ደጀኔ። አቶ ሶፊሳ እንደሚናገሩት የከተማው ማዘጋጃ ቤት የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ በአካበቢ ጥበቃ ላይ ትኩረት አድርጎ ተንቀሳቅሷል። በዚህም ጎርፍ በሚበዛባቸው አካባቢዎች የውሃ መውረጃ ዲሽ በመገንባት ወደእርሻ መሬት እና ወደመንገድ ገብቶ ጥፋት እንዳያስከትል አቅጣጫ የማስቀየስ ስራ ተሰርቷል። የአርሶአደር ቀበሌዎች የሆኑትን የማርቆስ እና የኮሎቦ ነዋሪዎች በማስተባበር የተፋሰስ ልማት ለማከናወን ጥረት ተደርጓል። በወልመራ ወረዳ እንደአጠቃላይ የተካሄደው የተፋሰስ ልማት እና የነዋሪው የ30ቀን በጎ ፍቃድ አገልግሎት በከተማችን ዙሪያ ቀበሌዎችም ተግባራዊ ሆኗል። አርሶ አደሩ ጎርፍ በሚበዛባቸውና በቦረቦር ስፍራዎች ላይ በልማት ቡድን ተደራጅቶ እርከን እንዲሰራ በማድረግ ጎርፉ የሚያደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት ተሞክሯል። የተራቆቱ አካባቢዎችን በከተማው የችግኝ ማፍያ ጣቢያ በተዘጋጁ ሃገርበቀል ዛፎች ለማልበስ ህብረተሰቡን በማስተባበር የችግኝ ተከላ ስራዎችም ተሰርተዋል። ያም ሆኖ ይላሉ ከንቲባው፣ “ከችግሩ ስፋት አንጻር የሰራናቸው ስራዎች ሁሉ የተፈለገውን ውጤት አላስገኙም። በበጀት እና በባለሙያ በኩል ባለብን የአቅም ውስንነት ምክንያት እየደረሰ ያለውን ችግር ለማስቆም አልቻልንም። ችግሩ አሁን ከአቅማችን በላይ ሆኗል።” ብለዋል።

በመናገሻ ከተማ ማዘጋጃ ቤት በኩል የስጋቱ መጠን ከፍተኛነት ላይ በቂ ግንዛቤ አለ የሚሉት አቶ ሶፊሳ አስተዳደራቸው ችግሩን ለመከላከል ካደረገው መጠነኛ ሙከራ ባሻገር በበጀት እጥረት እና በአቅም ውስንነት ምክንያቶች ሳቢያ የስጋቱን አጣዳፊነት የሚመጥን መፍትሄ ማምጣት አለመቻሉን ግን አልሸሸጉም።

ጋቢዮን ያላሰረው የአፈር ሽሽት

ጋቢዮን በጠንካራ ሽቦ ተጠላልፎ በተሰራ መረብ መሰል መያዣ ውስጥ ድንጋይ በመሙላት አፈር እንዳይንሸራተት ለማገድ የሚጠቅም ዘዴ ነው። ጋቢዮን በተለይ በመንገድ ግንባታ ወቅት የአፈር መንሸራተት ሊከሰትባቸው ይችላል ተብለው በሚገመቱ አካባቢዎች ላይ አፈሩን ለመገደብ እና መንገዱንም ከብልሽት ለማዳን እንደዋና መፍትሄ ይወሰዳል። የሚንሸራተተውን አፈር አጥብቆ በመገደብና አስሮ በማስቀመጥ ባለበት ቦታ እንዲቆይ ያደርገዋል።

የመናገሻ ከተማን ጨምሮ በአጠቃላይ የወልመራ ወረዳ ብዙ ቀበሌዎች ችግር የሆነውን የአፈር መሸርሸርና መሸሽ አደጋ ለመከላከል መሬቱን በእርከን መልክ አበጅቶ አፈሩን በጋቢዮን ማሰር አንድ መፍትሄ ተደርጎ ተወስዷል። በ2005/6 ዓ.ም የመናገሻ ከተማ ማዘጋጃ ቤት በጀት መድቦ ከወልመራ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ጉዳታቸው ከፍተኛ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ጋቢዮን ለማሰር እንቀስቃሴ ተጀምሮ እንደነበር ማዘጋጃ ቤቱ ይናገራል። ስራው ከተጀመረ በኋላ ግን በበጀት እጥረት ሳቢያ ጋቢዮን ማቅረብ ባለመቻሉ በተለይም ችግሩ ካካለለው አካባቢ ስፋት ጋር ሲነጸጸር ይህንን ለመሸፈን በቂ አቅም ስላልነበር የተያዘው እቅድ ተግባራዊ መሆን አልቻለም። ይህ ብቻም አይደለም፣ የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት በውስን አቅም ያሰባሰባቸውን ድጋፎች ተጠቅሞ የአፈር መሸርሸሩ በጠናባቸው ተዳፋት ስፍራዎች ላይ ያሰራቸው ጋቢዮኖች በጎርፍ ተንደው ከጥቅም ውጪ ሆነዋል። በዚህ ሳቢያም እንቅስቃሴው ውጤታማ መሆን አልቻለም።

ሶስቱ የመናገሻ ራስ ምታቶች

የመናገሻ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት በከተማዋ የሚገኙት ጋራ መናገሻ፣ አሊያንስ ፍላወር እንዲሁም ኮረቦዳ ተብለው የሚጠሩት አካባቢዎች የአፈር መሸርሸር ችግሩ የጠናባቸው ናቸው ተብለው በጥናት የተለዩ ናቸው። በነዚህ ስፍራዎች ላይ የተሞከሩት የእርከን ስራና የአፈር ጥበቃ መፍትሄዎች በሙሉ ውጤታማ መሆን አልቻሉም።

በጋራ መናገሻ አካባቢ የተሰሩት እርከኖች በውሃ ተጠራርገው በመወሰዳቸው አፈሩን ከመሸርሸርና ከመሸሽ ለማዳን የተደረገው ጥረት አልተሳካም። አካበቢው ደናማ በመሆኑና ዝናብ ስለማያጣው ከተራራው ላይ የሚመጣው ውሃ አፈሩን እየጠረገ ወደተዳፋት አካባቢዎች ይዘልቃል። አቶ ሶፊሳ እንደሚሉት ችግሩ በዚህ ከቀጠለ በተራቆተው መሬት ላይ አፈሩን ለመጠበቅ የተተከሉትን ችግኞች እየጠራረገ መውሰዱ የማይቀር ነው። ይህንን ለማስቀረት በወረዳው ትዕዛዝ አፈሩ በእርከን ተገድቦ በጋቢዮን እንዲታጠር እንቅስቃሴዎች ተጀምረው የነበረ ቢሆንም በከተማው አቅም ወጪውን መሸፈን አልተቻለም። በዚህ ሳቢያ እቅዱ ፈተና ገጥሞታል።

ከኮረቦዳ መንደር ዝቅ ብሎ ወደሚገኘው ኮረቦዳ ወንዝ የሚገባውን የታጠበ አፈር ለመከላከል 10 መኪና ሙሉ ድንጋይ ለአፈር ማገጃ ለማዋል ቢሞከርም ውጤት ማግኘት ግን እንዳልተቻለ ነው ከንቲባው የሚናገሩት። ይህ ቦታ የተፋሰስ ልማት ከሚካሄድባቸው የመናገሻ ከተማ አካባቢዎች አንዱ በመሆኑ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የአፈር ጥበቃ ስራውን ለማጠናከር ጥረት ተደርጓል። ነገር ግን ይህ ለውጥ ተመዘገበ ብሎ ለመናገር በሚያስችል ደረጃ የታየ ለውጥ የለም ይላሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ‘አሊያንስ ፍላወር’ ተብሎ የሚጠራው የአበባ እርሻ በእርሻው መሃል የሚያልፈውን ቦይ ለመዝጋትና የውሃውን መውረጃ አቅጣጫ ለማስቀየስ ብሎ በጎን በኩል በዘፈቀደ የቀደደው ተለዋጭ ቦይ ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት ጎርፉን ወደነዋሪዎች መንደርና እርሻ እንዲገባ በማድረግ ጥፋት እያስከተለ መሆኑን አቶ ሶፊሳ ይናገራሉ። ይባስ ብሎም ውሃው ወደዋናው አውራጎዳና በመግባት አስፓልቱን እያበላሸ በመሆኑ ማዘጋጃ ቤቱ ለድርጅቱ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ባሻገር ለመንገዶች ባለስልጣን እና ለሌሎች የሚመለከታቸው ክፍሎች ጉዳዩን በደብዳቤ ማሳወቁንም ገልጸዋል።

“ያም ሆኖ ድርጅቱ የውሃ መውረጃ ዲሽ ለመገንባት አቅም የለኝም በማለቱ እና የሚመለከታቸው አካላት እስካሁን የወሰዱት ምንም እርምጃ ባለመኖሩ ምክንያት ነዋሪው ከፍተኛ እሮሮ እያሰማ ነው። ግጭት የተፈጠረበት ወቅትም ነበር። በስፍራው ያለውን የአፈር መሸርሸር ጥፋት ለመከላከል ያላስቻለው አንዱ ሰው ሰራሽ ምክንያትም ይኸው ነው” ብለዋል አቶ ሶፊሳ።

እንደአቶ ሶፊሳ ገለጻ በመናገሻ ከተማ ውስጥ በዋናነት ለከባድ የአፈር መሸርሸር በመጋለጥ ለመዘጋጃ ቤቱ ራስ ምታት የሆኑት እነዚህ ሶስት አካባቢዎች ቢሆኑም ከዚህ በፊት ያልተጎዱ አካባቢዎች አሁን የችግሩ ገፈት ቀማሽ እየሆኑ መጥተዋል። ነገሩም ከከተማዋ አቅም በላይ ሆኗል።

“የችግሩ ተጠቂ መናገሻ ብቻ አይደለችም”

የወልመራ ወረዳ የግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግርማ ደሜ የአፈር መሸርሸር ችግር ሃገር አቀፍ ፈተና ነው ይላሉ። “ የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ሃገር አቀፍ የትኩረት መስክ ስለመሆኑ በአምስት ዓመቱ የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ እንደአንድ ተግባር መቀመጡ ምስክር ነው” ይላሉ። “በየአካባቢው የሚተገበሩት የተፋሰስ ልማት፣ የችግኝ ተከላ እና የእርከን ስራ እንቅስቃሴዎች ችግሩን ለመከላከል የተቀየሱ መፍትሄዎች ናቸው። በወልመራ ወረዳ ባሉት 23 ቀበሌዎች በሙሉ መናገሻን ጨምሮ የአፈር መሸርሸር ችግር በብዛት ይታያል። ይህንን ለመከላከል ጋቢዮን ማሰርና እርከን መስራት የመከላከሉ ተግባር አማራጭ መፍትሄዎች ናቸው።” ይላሉ።

“የመናገሻ ከተማ ድጋፍ የሚፈልግ በመሆኑ የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት የባለሙያ ድጋፍ በማድረግና ከአንዳንድ አካባቢዎችም ድጋፍ በማሰባሰብ በቅርቡ በስፋት ጋቢዮን ለማሰር እና የእርከን ስራዎች ተጠናክረው እንዲሄዱ ለማድረግ እንጥራለን። ያም ሆኖ ለአደጋ ከተጋለጠው አፈር አንጻር ችግሩ ሰፊ በመሆኑ የበላይ አካላትን ትኩረትም ይፈልጋል።” ነው የሚሉት አቶ ግርማ።

“ችግሩ ሰው ሰራሽ ነው”

የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግርማ እንደሚናገሩት የመናገሻ አካባቢ አብዛኛው ክፍል በደን የተሸፈነ ነበር። በረጅም ጊዜ ውስጥ ደኑ ተመንጥሮ በመሳሳቱ ምክንያት አፈሩ ለዝናብ ተጋልጧል። ይህም የሚወርደውን ውሃ መቋቋም እንዳይችል በማድረግ እንዲሸረሸር ምክንያት ሆኖበታል። በአካባቢው ያለው የአስተራረስ ዘይቤ እጅግ ኋላ ቀርና በሳይንሳዊ መንገድ ያልተደገፈ በመሆኑ ለአፈሩ መጎዳት እና ለጥፋት መጋለጥ ሌላው ምክንያት ሆኖ ይቀርባል። ለግጦሽ መሬት ተብሎ የሚጨፈጨፈው ደን ስፍራውን ለዝናብ እና ለጎርፍ አደጋዎች ስለሚያጋልጠው ጥፋቱ ይጨምራል።

“እነዚህ ምክንያቶች ህብረተሰቡ ስለአፈር ጥበቃ ካለው ግንዛቤ አናሳነት ጋር ሲደመሩ የሚደርሰውን ውድመት የከፋ ያደርጉታል። ስለሆነም ችግሩ ተፈጥሮ በአካባቢው ላይ ፈርዳ የጣለችው ቅጣት ሳይሆን ሰውሰራሽ ጥፋት ነው። ሰው የሰራውን ጥፋት ሰው ሊመልሰው ስለሚችልም የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮችን በማመቻቸት የአካባቢው አስተዳደር ከህዝቡ ጋር ተረባርቦ ቢያንስ የሚደርሰው ጉዳት ባለበት እንዲቆም ማድረግ ይችላል። ይህንን በተግባር ለመተርጎምም እቅድ ይዘን እየሰራን ነው” ብለዋል ሃላፊው።

አቶ ግርማ በመናገሻ አካባቢ ያለው አፈር ለአደጋ የተጋለጠበት ደረጃ ከፍ ያለ በመሆኑና አደጋው ያንዣበበባቸው አካባቢዎችም ሰፊ ስለሆኑ ለመከላከል ጠንካራ አቅም ይጠይቃል ነው የሚሉት። ከተማው ባለው በጀት፣ ወረዳው ግብርናም በሰው ሃይልና በሙያ ድጋፍ በማድረግ የተጀመሩትን ስራዎችም አጠናክሮ ለመቀጠል ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

ቀሪውን ሃብት ከጥፋት ለማዳን

የአፈር ለምነት መሟጠጥ ለመናገሻ ከተማ “ስጋት” በሚባል ደረጃ ላይ ከደረሰ ሰንብቷል። በዚህ ሳቢያ የሚከሰተው የአፈር ለምነት መቀነስ እና የምርታማነት ማሽቆልቆል ለከተማዋ ብቻ ሳይሆን ለሃገርም ችግር ነው። የከተማዋ ማዘጋጃ ቤትም ሆነ የወረዳው ግብርና ጸህፈት ቤት ከመፍትሄዎቹ አንዱና ዋናው ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር መሆኑ ላይ ይስማማሉ። አሁን ችግሩ እየሰፋ መምጣቱ በራሱ ቀደም ብለው የተሰሩ ስራዎች ጠንካራ አለመሆናቸውን አመላካች ቢሆንም ጊዜው ግን ገና አልረፈደም። የችግሩ ስፋት ከወረዳውም ይሁን ከከተማዋ የበጀት አቅም በላይ መሆኑ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ድጋፍ እንዲያደርግ ግድ ይለዋል። መጪው ጥፋት ለመናገሻ እና ወልመራ አስተዳደር መዋቅሮች ስጋት እንደሆነው ሁሉ ለክልሉም ሆነ ለፌዴራል መንግስትም የትኩረት አቅጣጫ መሆን ይገባዋል።

      የኦሮሚያ ደን ፕሮጀክት እያንዳንዱ ትልቅም ይሁን አነስተኛ እርሻ ከጠቅላላ ይዞታው 5 በመቶ የሚሆነው በተፈጥሮ ደን እንዲሸፈን የሚያስገድድ መመሪያ ማውጣቱ በሰዎች ጥፋት የተራቆተውን ደን መልሶ እንዲያገግምና አፈሩም ከጥፋት እንዲጠበቅ ለማድረግ መልካም እርምጃ ነው። የተተከሉት ዛፎች በቅለው ምግባቸውን ራሳቸው እስኪጠብቁት ድረስ ግን የአፈርን ለምነት ለመጠበቅ እና መሸርሸርን ለመከላከል የሚያግዙ ሌሎች ሳይንሳዊ ዘዴዎች በስራ ላይ መዋል አለባቸው። በተለይ በሌሎች ስፍራዎች እንደሚደረገው ህብረተሰቡን በማስተባበር በተፋሰስ ልማት፣ በእርከን ስራ እንዲሁም በችግኝ ተከላ እና የውሃ መውረጃ ዲሽ ግንባታ ላይ ፈጣን ስራዎችን መስራት ግድ ይላል። እነዚህ ስራዎች ውጤት እንዳያስገኙ ፈተና የሆኑትን ተደጋጋሚ እንቅፋቶች በማጥናትም ሳይንሳዊ መፍትሄዎችን መቀየስ ተገቢ ይሆናል። ይህ ችግር አፋጣኝ ትኩረት ካልተሰጠው በቀር ከጥፋት ተርፈው ዛሬ የአካባቢ ስነምህዳርን በመጠበቅ ላይ ከሚገኙት ደኖች ዋናው የከተመበት ይህ የመናገሻና አካበቢው መሬትበጊዜ ሂደት አፈሩ ታጥቦና ተራቁቶ ምድረበዳ እንዳይሆን ያሰጋል።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
1529 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 834 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us