የአዲስ አበባን የጐርፍ ተጠቂነትን ለመግታት ይቻላል

Wednesday, 12 February 2014 12:14

የአየር ንብረት ለውጥ መዘዞች በርካታ ናቸው። የዝናብ እጦት ድርቅ የአፈር መሸርሸርና የመሬት መጐሳቆል አንደኛው ፅንፍ ነው። በሌላኛው ፅንፍ ደግሞ ከባድ አውሎንፋስ ከባድ ዝናብ የበረዶዎች መቅለጥና የጐርፍ መጥለቅለቅ ይጠቀሳሉ። ጐርፍ በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ሲከሰት በሰው በእንስሳ በእህልና በንብረት ላይ ውድመት ያደርሳል። በቅርብ ጊዜ የተከሰቱትን ስናስተውል በደቡብ ኦሞ እኛንጋቶም ወረዳ በኦሞ ወንዝ መሙላት የተነሳ የተከሰተው በድሬዳዋ ከደጋማው ምስራቅ ሐረርጌ የጣለው ዝናብ በጐርፍ መልክ ያስከተለው ጣጣና በየጊዜው በአዋሽ ወንዝ ሙላት በሚከሰት አደጋ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ከባድ ጥፋት ማድረሱ ይታወቃል። የአየር ንብርት ለውጥ እስካለ ድረስም ይህ ችግር ቀጣይነት ይኖረዋል። ችግሩን ለመቅረፍም የመላመጃ ስራዎች መስራት እንደሚያስፈልግ ሙያተኞች ይመክራሉ።

ከሰሞኑም በተደጋጋሚ ጊዜ በጐርፍ እየተጠቃች ያለችውን አዲስ አበባን ለመተደግ የሚያስችል ለአራት ዓመታት የሚቆይ ጥናት አድረጐ ወደ ተግባር ለመሸጋገር የሚያስችል ስምምነት በአዲስ አበባና በኮፐን ሀገን ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ስምምነት ተፈርሟል። 14.2 ሚሊዮን ዶላር በተመደበለት በዚህ ፕሮጀክት ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ይሳተፋሉ። ከእነርሱም ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የእሴትና ድንገተኛ አደጋ ክፍል፣ የከተማ ልማት ኢንስቲትዩት፣ የአካባቢ ባለስልጣን የውበት የመናፈሻና የዘላቂ ማረፊያ ኤጀንሲ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የደረቅ ቆሻሻ ማኔጅመንት ኤጀንሲና የከተማ ግብርና ቢሮ በዋንኛነት የሚጠቀሱ ናቸው። ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት ሲስተም ዳይሬክተር ዶ/ር ከተማ አበበ እንደገለፁት በከተማችን የሚከሰተውን የጐርፍ አደጋ ለመግታት ሰፋ ያለ ጥናት ማድረግን እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ የተቀረፀው ፕሮጀክትም በ90 ሀገሮች ከተቀረፁ ፕሮጀክት ጋር ተወዳድሮ መስከረም 12 ቀን 2006 ዓ.ም ተቀባይነት እንዳገኘ አመልክተዋል። ለጐርፍ አደጋ ተጋልጦ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ከዓለም ታዋቂ የሆነችው ዴንማርክም ለዚሁ ጉዳይ ድጋፍ ለማድረግ ሦስት ኢትዮጵያውያንን በጐርፍ መከላከል ረገድ በዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ እያስተማረች እንደምትገኝ ጠቅሰዋል።

እንደሚታወቀው አዲስ አበባ ከተማ ከባህር ወለል ከ2500 ሜትር በላይ የተቆረቆረች ከተማ ነች። የክረምቱንና የበልግ ዝናብን በበቂ ሁኔታ ታገኛለች። ከከተማዋ በስተሰሜንና በስተምስራቅ ከሚገኙ ተራሮች በክረምት ወቅት የሚመጣው ጐርፍ ለበርካታ ጊዜያት በሰውና በንብረት ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት ያደርሳል።

በክረምት ወቅት በከተማዋ የሚያቋርጡ ጅረቶች ከመጠን በላይ ሲሞሉ ከጅረቶቹ ዳርቻ የሚገኙ የተጐሳቆሉ ቤቶችን ደርምሰው በመግባት ንብረትና ሰውን ጠራርገው ይወስዳሉ። ከመሄጃ ቦታቸው በመውጣት አካባቢን ያጥለቀልቃሉ። ቱቦዎች ፈንድተው ስለሚሰባበሩ ፍሳሽ ቆሻሻ በአውራ ጐዳና በመፍሰስ አካባቢን በመጥፎ ጠረን ይበክላል። መንገዶችም ለትራፊክ ዝግ ይሆናሉ። ከዚያ ሲያልፍ ከከተማዋ በስተደቡብ ያሉ የገጠር መንደሮችን አጥለቅልቀው በእንስሳትና በእርሻ ላይ ጉዳት ያስከትላሉ። በሰለጠኑት ሀገሮች የጐርፍ ውሃ አደጋ እንዳያደርስ በስርዓት እንዲወርድ ከማድረግ በተጨማሪ ውሃው ተጠራቅሞ ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋሉ። ስለሆነም ጎርፉ የሚያደርሰው ጉዳት ሳይኖር ልማት ያመጣል። ከዚህ አኳያ በሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የተደረሰው ስምምነት ጐርፍን መከላከል ብቻ ሳይሆን ጥቅም እንዲሰጥ የሚያደርግ በመሆኑ ሊበረታታ የሚገባ እንደሆነ የዴንማርክ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ዳይሬክተር ዶ/ር ጆንዳይተር ገልፀዋል።

የፕሮጀክቱ ሙሉ ወጪ የሚሸፈነው በዴንማርክ ሲሆን፤ የሚፈጀውም 4.2 ሚሊዮን ዶላር ነው። ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ ከተማ በተጨማሪ የታንዛንያን ዋና ከተማ ዳሬሰላምን ያካትታል። አዲስ አበባ ተራራ ላይ ስትገኝ ዳሬሰላም ደግሞ ለጥ ያለ ሜዳ ላይ ነው የምትገኘው። ከዚህ አንፃር ፕሮጀክቱ በተለያየ መልከዓምድር ላይ በመገኘታቸው የጐርፍን ተፅዕኖ በተለያየ የመሬት አቀማመጥ ለመግታት የሚያስችል በመሆኑ ተሞክሮው ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚሰጥ ነው። እንደሚታወቀው በከተሞች ፍሳሽ ቆሻሻዎችና የክረምት ውሃና ጐርፍ የሚያልፉት ለእነርሱ ተብለው በተሰሩ ቦዮችና ቱቦዎች ውስጥ ነው፤ እነኚህ መውረጃዎች ጐርፍን ታሳቢ አድርገው አለመሰራታቸው ከተሞችን ለጐርፍ ተጋላጭ ያደርጓቸዋል። ይህ ሁኔታም በከተሞቹ ዕድገትና ደረጃ የሚወሰን ነው። አዲስ አበባ ከመቶ ዓመታት በፊት የተቆረቆረችው ባህላዊ በሆነ አሰራር ነው። ከዚያ በኋላም በሀገሪቱ በተፈራረቁ የአገዛዝ ሰርዓቶች ማስተር ፕላንዋ ተቀያይሯል። አሁን አሁን ደግሞ ያልለሙ አካባቢዎች ፈርሰው በፕላኑ መሠረት እንዲለሙ ቢደረግም፤ የፍሳሽ ማስወገጃው ጉደይ ግን ገና እልባት ባለማግኘቱ ነው። ይህ ፕሮጀክት ተቀርጾ ጥናቱን ለማድረግ ከስምምነት የተደረሰው በአሁኑ ወቀት በከተማችን የተዘረጉት የፍሳሽ መውረጃ ቱቦዎችና ቦዮች በከተማዋ የሚከሰተውን ጐርፍ ማስተናገድ የሚችሉት 10 ከመቶ ብቻ ነው። ከዚህ አኳያ የጥናቱ አንዱ አላማ የቱቦና የውሃ መውረጃዎችን አቅም ከፍ ማድረግ እንደሆነ በዕለቱ ተገልጿል።

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በአሁኑ ወቅት ወቅቱን ጠብቆ ዝናብ አለመጣልና ሲመጣም እጅግ በከባድ ሁኔታ የሚከሰተው ጐርፍ የሚያስከትለው አደጋ በቀጥታ የሚገናኘው ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ነው። ስለሆነም በፕሮጀክቱ አማካኝነት ጥፋት የሚያደርስን ጐርፍ በመከላከልና በመጠቀም ከተማዋን አረንጓዴ ማድረግ “በአንድ ጠጠር ሁለት ወፍ” መሆኑን ዶ/ር ከተማ አበበ አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው በበኩላቸው የታቀደው ጥናትና ምርምር በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ስለሚሆን በጐርፍ አደጋ እየተማረረ ያለውን ኅብረተሰብ መታደግ እንደሚያስችል ጠቁመዋል። እንደ እርሳቸው ገለፃ በተለይ የስሜኑ የከተማዋ አካባቢ በጐርፍ ስለሚጠቃ ችግሩን ከመቅረፍ በተጨማሪ የጐርፍን ውሃ በመያዝ ለተለያዩ አገልግሎት በማዋል የውበትና የመናፈሻ ስፍራ መፍጠር ስለሚያስችል ጠቀሜታው የጐላ ነው። ከጠቂት ዓመታት በፊት የወጡት ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ 4ሺህ የሚሆኑ ሰዎች የጐርፍ ሰለባ የሆኑ ሲሆን፤ ጉዳቱም በህይወትና ንብረት መውደም የታጀበ ነው። ከዚህ አንፃር ከአራት ዓመታት በኋላ ፕሮጀክቱ ወደ ተግባር ሲተረጐም ችግሮቹ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ፕሮጀክት ሌላም የሚፈጥረው ዕድል አለ። ከተማዋ በጣም ሰፊ በመሆኗ በበርካታ አካባቢዎች የጐርፍ መውረጃ ቦዮች ተሻሽለው እንዲገነቡ እንዲሁም አዳዲስ እንዲቋቋሙ ስለሚደረግ ለበርካቶች የጉልበት ስራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ነው። በአሁኑ ወቅት አንድን ከተማ ከተማ ከሚያሰኙ በርካታ ጉዳዮች መካከል ከተማዋ ለተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭነትዋ ዝቅተኛ መሆን አንደኛው ነው። አዲስ አበባ ከዋነኛው የሀገራችን ከስምጥ ሸለቆ ከመቶ ኪሎ ሜትር በላይ ርቃ ትገኛለች። አንዳንዴ በሬክተር ስኬል ሲለካ በጣም አነስተኛ የሚባል የመሬት መንቀጥቀጥን ታስተናግዳለች። አንዳንድ ጂኦሎጂስቶች በበኩላቸው በመዲናችን ያለው ፍል ውሃ ምልክቱ ለመሬት መንቀጥቀጥ መነሻ የሆነው የእሣተገሞራ እንደሆነ ይገልፁና፤ በጣም ረጃጅም ፎቆች ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ስለሆነ ባይገነቡ ይመረጣል በማለት ይመክራሉ። በሌላ በኩል ከተማዋ ከውቅያኖስ እጅግ የራቀችና ተራራማ ላይ የተቆረቆረች በመሆንዋ በሌሎች ሀገሮች በባሕርዳርቻ እንደሚገኙ ከተሞች ለሀሪኬንና ቶርኔዶ ለተባሉ አውሎ ንፋስ የቀላቀሉ ዝናቦች ተጋላጭ ባለመሆንዋ ለመኖሪያ ተመራጭ ያደርጋታል ሲሉ ይገልፃሉ። ከዚህ ውጭ ከተማዋን ሊያሰጋት የሚችለው ከላይ የተጠቀሰው የጐርፍ አደጋ ነው። ስለሆነም የጐርፍ አደጋን በመከላከልም ሆነ ውሃን ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ፕሮጀክቱ ከተማችንን ከሌሎች ከተሞች ጋር በንፅፅር የተሻለች እንድትሆን ያርጋል። በከተማዋ በተለይ የኮንስትራክሽን ዘርፉ በፍጥነት እያደገ ነው። ይህ ደግሞ በቀጥታ የሀገሪቱ ቋሚ ካፒታል እንደመሆኑ እንክብካቤ የሚያስፈልገውና ለመጭው ትውልድም የሚቆይ ስለሆነ የከተማችንን የአደጋ ተጋላጭነት መቀነስ ፋይዳው የላቀ ነው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚታየው በከተማችን እየተባባሰ የሚገኘው የውሃ አቅርቦት መጓደል ለብዙዎች አሳሳቢ እየሆነ ነው። ውሃ በሳምንት ሁለቴና ሦስቴ ማግኘት የተለመደ ሆኗል። የሰው የውሃ ፍጆታ ደግሞ እየጨመረ ነው። ለቤት ውስጥ አገልግሎት፣ ለፅዳት፣ ለባኞ ቤት ወዘተ ብዙ ውሃ እያስፈለገ ነው። ኮንስትራክሽን ዘርፉም እንደዛው ይፈልጋል። ከዚህ አኳያ ክረምት በመጣ ቁጠር አንዳች ጥቅም ሳይሰጥ ነገር ግን ጥፋት እያስከተለ የሚገኘውን የጐርፍ ውሃ በተገለፀው ፕሮጀክት አማካይኝነት በመያዝና በማከማቸት መጠቀሙ በጣም ወሳኝ ነው።

በስምምነቱ ወቅት የፕሮጀክቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቁምላቸው የሺጥላ እንደተናገሩት የመሬት ገፅታን በመግራት ጐርፍን የመከላከል ስራ የ150 ዓመታት ታሪክ እንዳለው ጠቅሰው በየጊዜውም ጥናቶች እየተደረጉና ተሞክሮዎች እንዲዳብሩ ተደርገው ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት በመደረግ ላይ እንደሆነ አመልክተዋል። ይሁን እንጂ የአየር ንብረት መለዋወጥ የዝናቡንና የጐርፉን መጠን በጣም ተለዋዋጭ ስለሚያደርገው የገነቡ ቱቦዎችና የፍሳሽ መውረጃ ቦዮች ብዙ ፈተና እየገጠማቸው እንደሚገኝ አልሸሸጉም። በአሁኑ ወቅት በበለፀጉ ሀገሮች ባሉ ከተሞች የተዘረጉ ፍሳሽ ማውረጃዎች ጐርፍን መቋቋም ባለመቻላቸው ለተጨማሪ ወጭ እየዳረጋቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል። እንደ ዶ/ር ቁምላቸው ገለፃ ጐርፍን መከላከልና መያዝ የከርሰ ምድርን ውሃ ለማበልፀግና የከተማዋን የአየር ሙቀት ለመቀነስ ከማስቻሉ በተጨማሪ ብዝሃ ህይወትን ለማጐልበትና ሰላማዊና ማራኪ ህይወትን ለመምራት ያስችላል።

     የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ኃላፊ አቶ አዱኛ ሽመልስ በዕለቱ ከተገኙ ኃላፊዎች አንደኛው ሲሆኑ፤ መስሪያቤታቸውም ከፍተኛው ባለድርሻ አካል ነው። እርሳቸውም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በየጊዜው መከሰቱ ችግር እየፈጠረ በመሆኑ ኩሬዎችን በመገንባት ጐርፍን መከላከል እንደሚቻል ጠቁመዋል። አያይዘውም በተለይ ጐርፍን ለመከላከል የተቋቋመ መስሪያ ቤት ባለመኖሩ ችግሩ ሊገታ እንዳልተቻለ ጠቅሰው ከዚህ አኳያ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል። በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ ጐርፍን በመከላከልና ጥቅም ላይ ከማዋል በተጨማሪ ጥናቱና ትግበራው በኢትዮጵያውያን ሙያተኞች መካሄዱ ለሀገራችን ተጨማሪ የዕውቀት እሴት ያስገኛል። ሀገራችን የአየር ንብረት ለውጥን ተቋቁማ ከበክለት ነፃ የሆነ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት እያደረገች ያለውንም ጥረት የሚያግዝ እንደመሆኑ ተፈጥሮ ጥቅም የሚሰጥ እንጂ ጉዳት የማያደርስ እንዲሆን የሚያደርግ ነው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1165 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1027 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us