ባዮጋዝን በአማራጭ ኢነርጂ ምንጭነት

Wednesday, 19 February 2014 13:25

የአየር ንብረት ለውጥና የሙቀት መጨመር ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ኢንቫይሮሜንታዊ አሉታዊ ተፅዕኖ እያመጣ ይገኛል። አፍሪካ በተለይ ለዚህ ተጋላጭ የሆነችበት ምክንያት በዝናብ ላይ ጥገኛ የሆነ እርሻ መተማመን፣ ድህነት መንሰራፋቱና ይህን ለመቋቋም ያላት አቅምም ውስን ከመሆኑ የተነሳ ነው። በዚህም የተነሳ የአየር ንብረት ለውጥ ዘላቂ ልማት እንዳይመጣ ትልቅ እንቅፋት ይፈጥራል። የሚሊኒየም ግቡንም ለማሳካት እንዳይቻል ሳንካ ፈጥሮአል። የዝናብ መዋዠቅና ባህርይ መቀየር በእርሻ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማምጣት የምግብ እጥረት እንዲከሰት ያደርጋል። የውሃ አቅርቦትን በማመናመን አዳዲስ በሽታዎችን በመፍጠር የችግር አዙሪት እንዲባባስ ያደርጋል። ከዚህ አንፃር ለሙቀት መከሰት አንዱ ምክንያት የሆነውን የመሬት መራቆትና የደን ውድመትን ለማስቀረት አማራጭ የኃይል ምንጭን መጠቀም በጣም ወሳኝ እንደሆነ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የኢንቫይሮሜንታል ኢኮኖሚክስ ሙያተኛ የሆኑት አቶ ዘነበ ገብረእግዚያብሔር ይገልፃሉ።

እንደ እርሳቸው ገለፃ በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ የእርሻ ምርታማነቱ የሚቀንሰውና የሚቆረቁዘው አፈሩ የናይትሮጂንና የፎስፈረስ እጥረት ስላለበት ነው። ስለሆነም አፈሩ እንዲለማ ማድረግ አስፈላጊ ነው። በኢትዮጵያ የመሬት አፈር ለምነት መዳከምና መመናመን ለዝቅተኛ ምርታነትን ለገጠር ድህነት መስፋፋት የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል። የመሬት መከላት በተለያየ ሁኔታ ይከሰታል። አንደኛው ምክንያት አፈር መሸርሸር ነው። ይህም ተገቢ ንጥረ ነገር በአፈር ውስጥ እንዳይኖር ከማድረግ በተጨማሪ ምርታማነት እንዲቀንስ ያደርጋል። የተፈጥሮ ፍግ ውድቅዳቂ እንጨቶች ቅጠሎች ለኩበት መስሪያ ስለሚውሉ አፈሩ ማግኘት የሚገባውን ማዳበሪያ ያጣል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በደን ምንጣሮ ምክንያት ዛፎች ስለተመናመኑ ለማገዶ የሚሆን እንጨትና ከሰል እጥረት የተፈጠረ ሲሆን በዋጋም ደረጃ በየጊዜው እያሻቀበ በመሄድ ላይ ይገኛል። በገጠር ገበሬዎች ኩበትን ለማገዶነት በስፋት የሚጠቀሙት በዚህ ሳቢያ ሲሆን ይህም አፈር ለምነት እንዲቀንስ እያደረገ ነው። ስለዚህ የማገዶ አጠቃቀምን ይዘት ስርነቀል በሆነ መልኩ መለወጥ በጣም አስፈላጊ ነው።

አቶ ብሩክ ገብረእግዚያብሄር እንደሚናገሩት በኢትዮጵያ ገጠር በአንፃራዊነት የከብቶች ቁጥር ከሰው ብዛት ጋር ሲወዳደር እጅግ ከፍተኛ ነው። ከዚህ አኳያ በሀገራችን ባዮጋዝን ለማምረት የሚያስችል መልካም አጋጣሚ ያለ ሲሆን በዘርፉም ኢንቨስተሮች እንዲገቡ ሳቢ ሁኔታ አለ። ሚስተር ፓትሪክሀንስ የተባሉ የዚህ ባለሙያ በበኩላቸው ይህን ሀብት በመጠቀም ለገጠሩ ህዝብ ከባዮጋዝ የሚመነጭ የኢነርጂ አቅርቦትን በበቂ ሁኔታ ማቅረብ እንደሚያቻል ይገልፃሉ። በኢትዮጵያ 3/4ኛ የሚሆን ህዝብ ለምግብ አቅርቦት የሚያገለግለው የእርሻ መሬት ለምነቱ በተበላ አፈር ላይ የተመሰረተ ነው። አፈሩ መልሶ እንዲያገግም ከተፈለገ ማገዶን ከባዮማስ መጠቀም የግዴታ መቆም ይኖርበታል። ለዚህ መፍትሄውም ባየጋዝን ማጎልበትና ማስፋፋት አስፈላጊ ነው። እንደ አቶ ዘመነ ገለፃ የባዮጋዝ አመራረትና ስርጭት በኢትዮጵያ የተጀመረው በ1970ዎቹ ነው። ይህ እንቅስቃሴ ከ30 ዓመታት በፊት ቢጀመርም የእድሜውን ያህል ግን አልተስፋፋም። አብዛኛው የባዮጋዝ አመራረት በተቋማት ደረጃ ተዘጋጅቶ ከማሳያነት የዘለለ ጠቀሜታ ለህብረተሰቡ እየሰጠ አይገኝም። በአሁኑ ወቅት የቴክኖሎጂው ስርጭት በግብርና ሚኒስቴር የገጠር ልማት ዲፓርትሜንት በኩል ይካሄዳል። የባዮጋዝ ምድጃዎች የሚመጡት ከህንድና ከቻይና ሲሆን በአጠቃቀሙ ተመራጭና በዋጋውም ደህና የሚባለው ከቻይና የሚገባው ነው። ይህ የባዮጋዝ ምርትና ስርጭት ከላዩ የተጠቀሰውን የአየር መሸርሸርንና የመሬት መራቆትን ከማስቀረት አንፃር የላቀ ሚና ቢኖረውም የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ግን በዘርፉ እምብዛም አልተሳቡም። ወደ ስራው ያልተሰማሩትም የባዮጋዝ አመራረት በመጀመሪያው ዙር ከፍተኛ ኢንቨስትሜንት ስለሚጠይቅ ነው። በአሁኑ ወቅት የባዮጋዝ ጠቀሜታ የሚታየው የማገዶ እንጨቶችንና በበካይነቱ የሚታወቀውንና ከውጭ ተገዝቶ የሚመጣውን ኬሮሲንን ከመተካት አንፃር እንጂ የአፈር መከላትንና ደህንነትን ከመቀነስ አኳያ የሚጫወተውን ሚና ከግምት ከማስገባት አይደለም።

በኢትዮጵያ ገጠር የከብቶች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል። የከብቶች እዳሪ ወይም እበት በውስጡ ለአየር ንብረት መበከል በእጅጉ አስተዋፅኦ የሚያደርገው ሜቴን የተባለው ጋዝ ይገኛል። ሜቴን ጋዝ በየሜዳው ከብቶች ሲፀዳዱና ሳር በአፋቸው ሲያመነዥጉ ከአፋቸው በመውጣት ወደ ከባቢ አየር በመግባት ብክለት እንዲከሰት ያደርጋል። ይህ ንጥረ ነገር ከካርበን ዳይኦክሳይድ 22 እጥፍ አየርን ይበክላል። ከዚህ አንፃር በገጠር ቀበሌዎችና መንደሮች ከብቶችን በአንድ ውስን ስፍራ በማርባት በእዳሪያቸው ያለውን ሜቴን ከሰው አይነምድር ጋር በመቀላቀል ሜቴን ካርቦንዳይኦክሳይድን በመፍጠር ለመብራትና ለምግብ ማብሰያነት መጠቀም ይቻላል። የባዮጋዝ አመራረት የኃይል ምንጭን ከማጎልበት በተጨማሪ ከብቶችንከቦታ ወደ ቦታ ለግጦሽ በመውሰድ የማርባቱን ዘዴ ሊቀንስ የሚችል ነው። እንደሙያተኞች ገለፃ በቁጥር ውስን ከብቶችን በአንድ አካባቢ ማርባት ከብቶች በቀላሉ እንዲደልቡ ያደርጋል። ከቦታ ወደ ቦታ በመዘዋወር ሣርን ከመጠን በላይ ማስጋጥ የአፈር መሸርሸርና መከላትን ስለሚያስከትል ይህም መልሶ ድርቅንና የዝናብ እጥረትን ስለሚያመጣ ተመራጭ አይደለም። ከብቶች ከቦታ ወደ ቦታ ሲዘዋወሩም ከመደለብ ይልቅ ይከሳሉ ይህም በገበያ ላይ ተፈላጊነታቸውን ይቀንሳል። በአሁኑ ወቅት በተለይ በቦረና አካባቢ ከብቶችን በበረት ውስጥ ማሰባሰብ መጀመሩ ለርባታውም ሆነ ለባዮጋዝ ምርት ተመራጭ ስለሆነ እየተበረታታ ያለ ስራ ነው። በአጠቃላይ የባዮ ጋዝ አመራረት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን ሜታን ንጥረ ነገር እንዳይለቀቅ ስለሚያደርግ ከኢነርጂ ምርት በተጨማሪ የሚቲጌሽን ስራ መስራት እንደሚያስችል አቶ ዘመነ ገብረእዝጊያቤር ያስረዳሉ።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የባዮጋዝ ጣቢያዎች ለማቋቋምና ምርቱን ለማሰራጨት ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ ውድ ተግባር የመለወጡ ጉዳይ እዚህ ግባ የሚሰኝ አይደለም። የአመራረት ሂደት ለአካባቢ ጥበቃ ለስራ ፈጠራና እድል የሚያግዝ ቢሆንም ይህን ያህል የተነቃቃ አይደለም። የሰዎች የፈጠራ ክህሎትም መታየት የሚገባውን ያህል አልወጣም።

በኢትዮጵያ በገጠር ባዮጋዝን በኃይል ምንጭነት ለመጠቀም ሁለት አማራጮች አሉ። አንደኛው በግለሰቦች ቤት ማዘጋጀት የሚችል ሲሆን፤ በሁለተኛ በገጠር መንደሮች አምርቶ ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል። ይህም የባዮጋዝ መጠኑን መወሰን የሚያስችል ነው። ከዚህ በተጨማሪ ለአነስተኛና ጥቃቅን ኢንዱስትሪዎች ኃይል ማቅረብ ያስችላል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁኔታው ሲታይ ጠቀሜታው በእጅግ እየተስፋፋ እየሄደ እንደሚገኝ መረዳት አያዳግትም። ከፍተኛው የህዝባቸው ቁጥር ገጠሬ የሆነው ቻይና ህንድና ኔፓል ባዮጋዝን በስፋት እየተጠቀሙ ይገኛሉ። በቻይና አምስት ሚሊዮን የባዮጋዝ ማምረቻ ተቋማት የሚገኝ ሲሆን 15 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብም ከ8 እስከ 10 ወራት ያህል ጋዝን ለመብራትና ለምግብ ማብሰያነት ይጠቀምበታል። የገጠሩም ኃይሉን የሚጠቀምበት የባዮጋዝ ምድጃ አለው። ከዚህ በተጨማሪ የዶሮ እንቁላልን ለማስፈልፈል፣ ሻይ ለማፍላት እህልና ፍራፍሬን ሳይበላሽ ለማከማቸት ያገለግላል።

በሀገራችን ባዮጋዝ መስፋፋት ከቻለ በተለይ ለገጠሬው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ሊያስገኝ ይችላል። እንጨትን ከብት የእህል ገለባዎችን ተክቶ ለቤት ውስጥ ማብሰያነት ያገለግላል። እንደየሁኔታውም ቤንዚንና፣ ናፍጣንና ኤሌትሪክ ኃይልን ተክቶ መጠቀም ይቻላል። ወደፊትም ባዮጋዝ ሀገራችን እየተከተለችው ላለው አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ አጋዥ በመሆን ታዳሽ ኃይል እንዲስፋፋ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። እንደሚታወቀው ሀገራችን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በምትከተለው ስትራቴጂ በተለይ የደኑ ዘርፍ እንዲስፋፋ አዳዲስ ደኖችም እንዲከተሉ ጥረት እየተደረገ ነው። ይህም በመንግስት በአርሶ አደሮችና በአርብቶ አደሮች እየተከናወነ ይገኛል። ወደፊትም በ7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ደን ለመትከል እቅድ ተይዟል። ይህ ደን ለእርሻ መሬት ማስፋፊያነትና ለማገዶና ለመሳሰሉት አላግባብ እንዳይወድም ለማድረግ የባዮማስኢነርጂ አጠቃቀም ወደታዳሹ ባዮጋዝ መቀየር ይኖርበታል። ባዮጋዝንም አካባቢ እንዲጠበቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

በከብቶችና በሰው አይነምድር የሚመረት ባዮጋዝ በተመረተ በኋላ የሚቀረው ተረፈ ምርት በውስጡ አፈርን ማልማት የሚያስችል አሁን ጥቅም ላይ ከዋለው ማዳበሪያ ይበልጥ የተሻለ ንጥረ ነገር ስላለው አፈርን ማልማት የሚያስችል ነው። ይህ የከብትና የሰው ዓይነምድር በዚህ መልኩ ጥቀም ላይ ከዋለ ከኢነርጂ በተጨማሪ ከአካባቢ መበከል ሳቢያ ሊቀሰቀሱ የሚችሉ በሽታዎችንም ለማስቀረት ስለሚያስችል ጥቅማቸው ዘርፈ ብዙ ነው። ከዚያ አኳያ ከተማችን በተለይ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትዋ ብዙ ጉድለት እንዳለበት ይታወቃሉ። መፀዳጃ ቤት የሌለው ነዋሪ ቁጥሩ የትየለሌ ነው። ይህም በብክለትና ለበሽታ መስፋፋት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ምንም ጥርጥር የለውም። ከዚህ አኳያ በተለምዶ በየትምህርት ቤቶች አንዳንድ ተቋማት በጅምር ያሉ የባዮጋዝ ማምረቻዎች መስፋፋት ያለባቸው ሲሆን የህዝብ መፀዳጃዎችም ተስፋፍተው ፍሳሾች በመውረጃ ቱቦዎች አማካኝነት ወደ ባዮጋዝ ማምረቻ ገብተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ሙያተኞች ይመክራሉ።

     በአሁኑ ወቅት አብዛኛዎቹ የሀገራችን ገበሬዎች የእርሻ ምርታማነታቸውን ለማሳደግ በሚል የተለያዩ ዓይነት መጤ ማዳበሪያዎችን ይጠቀማሉ። ማዳበሪያው ከውጭ የሚገባ እንደመሆኑ ለዋጋ ተለዋዋጭነት የተጋለጠ ነው። ቀላል የማይባል የውጭ ምንዛሪ ይወጣበታል። ማዳበሪያውን የሚጠቀም ገበሬ አለቅጥ እየጨመረ የሚሄደውን የማዳበሪያ ዋጋም ካለማወላወል የመክፈል ግዴታ አለበት። የማዳበሪያ ክፍያውን ለማካካስም በእህል ዋጋ ላይ ጭማሪ ያደርጋል። እህሉ ከገጠር ተጓጉዞ ከተማ ሲደርስም ትራንስፖርቱ ዋጋ ሲጨምርበት የእህል ዋጋ ይንራል። ይህም አብዛኛውን ከተሜ ህይወት እየተፈታተነ ይገኛል። ስለሆነም አፈርን ከማዳበሪያ ይልቅ በተፈጥሮአዊ ዘዴ ማለትም ኦርጋኒክ በሆነ መልኩ ሊያዳብር በሚችለው መልኩ ማዳበር ተመራጭነት አለው። በተለይ በሀገራችን በሚገኙ ሞቃታማ አካባቢ እርሻዎች አፈሩ ለብዙ ጊዜ ታርሶ ያረጀ በመሆኑ ማዳበሪያ ቢጨመርበትም ብዙ ላይሰራ ይችላል። ስለሆነም በመሬት ላይ የሚገኙት የእርሻ ተረፈ ምርቶች የከብት እዳሪና ሌሎች እዚያው በስብሰው አፈሩን እንዲያለሙ ማድረግ እንዲቻል ባዮጋዝን መጠቀም ወሳኝ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ባዮጋዝ ተመርቶ የሚቀረው ስለሪ የተባለው በናይትሮጂን የበለፀገ ንጥረ ነገር አፈርን በማልማት ትልቅ ሚና ይጫወታል። በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ይህ ንጥረነገር በተለያዩ እህሎች በተተከሉበት እርሻ ሙከራ ተደርጎ የጤፍ የስንዴና የባቄላ ምርታማነት ሊያድግ እንደቻለ አቶ ዘነበ ገብረእዝጊያብሔር አመልክተዋል። ይህ ሁኔታ በአጠቃላይ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለአፈር ልማት፣ ለስራ እድል ፈጠራና ለኢነርጂ ልማት ትልቅ ድርሻ ያለው የባዮጋዝ ምርት ትኩረት ሊያገኝ ግድ ይላል።

ይምረጡ
(7 ሰዎች መርጠዋል)
2017 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1031 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us