የደቡብ ኦሞ ዞን መንግስታዊ ልማትና አካባቢያዊ ተፅዕኖው

Wednesday, 12 March 2014 12:40

በአይቸው ደስአለኝ

የኢትዮጵያ መንግስት እስከ መጪው 2025 ዓ.ም ሀገሪቱን መካከለኛ ገቢ አላቸው ከሚባሉት ሀገሮች ተርታ አሰልፋለሁ፣ ድህነትን በመቅረፍ የተሻለ የልማት እመርታን አስገኘለሁ በሚል ከፍተኛ በጀት መድቦ ግዙፍ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። ለዚህ እንዲያግዝ በርካታ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን እንዲሁም የሸንኮራ እርሻዎችን በማስፋፋት የስኳር ምርትን በማሳደግ ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ጥረት እያደረገ ሲሆን ከዚሁ ጎን ለጎን ለጨርቃጨርቁ ዘርፍ ግብአት የሚሆን የጥጥ እርሻን በማስፋፋት ላይ ይገኛል። ይህ ግዙፍ ስራ በአዎንታዊ ጎኑ የሚታየውን ያህል ነቀፌታና ትችትንም ማስተናገዱ አልቀረም።

አንዳንድ ወገኖች ስራው በመንግስት ብቻ መከናወኑ የግሉን ዘርፍ ያገለለ ስለሚሆን ተወዳዳሪነት እንዳይጎለብት ያደርጋል። ከዚህ በተጨማሪ የሀገሪቱን ውስን ገንዘብ በትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ማፍሰሱ የዋጋ ግሽበቱን ያባብሰዋል በማለት በአሁኑ ወቅት እያሻቀበ የሚገኘውን የኑሮ ውድነት በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። በሌላ በኩል የሚካሄደው የልማት እንቅስቃሴ በአካባቢ ላይ ከባድ ውድመትን እያስከተለ ነው የሚል ወቀሳም በአለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች እያቀረበ የሚገኝ ሲሆን በተለይም በደቡብ ኦሞ በመንግስት በጋምቤላ ደግሞ በውጭ ባለሀብቶች የሚከናወነው ስራ በአካባቢ ላይ ጥፋት ከማድረስ አልፎ ተወላጆችን በማፈናቀል ህልውናቸው ጥያቄ ላይ እንዲወድቅ በማድረግ ላይ ይገኛሉ ሲሉ ቅሬታቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ።

ከሰሞኑም ዋና ጽህፈት ቤቱን ኒውዮርክ ያደረገው ሂማን ራይትስ ዎች መንግስታዊ ያልሆኑ የመብት ተሟጋች ቡድን ባወጣው ዘገባ የኢትዮጵያ መንግስት በደቡብ ኦሞ በኦሞ ወንዝ ተፋሰስ በሚያካሂደው ግዙፍ የስኳርና የጥጥ እርሻ ልማት ሳቢያ 500ሺህ የኢትዮጵያና የኬንያ አርብቶ አደሮች ለችግር ተጋልጠዋል። ተቋሙ በኢትዮጵያ የመሬትና ውሃ አቅርቦት አርብቶ አደሮችን እየጎዳ ነው በሚል ከሳተላይት የተገኙ ምስሎች እንደሚያሳዩት በታችኛው የኦሞ ሸለቆ ነበር። ማህበረሰቦች ይዘውት የነበረው መሬት ለስኳር ተክል ተመንጥሯል የሂዩማን ራየትስ ዎች የአፍሪካ ጉዳይ ምክትል ዳይሬክተር ሚስስ ሌሰሊ ሌፍቶ በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የደቡብ ኦሞ የታችኛው ተፋሰስን ተቋማቸው ለረጅም ጊዜ እየተከታተለው እንደሚገኝ የኢትዮጵያ መንግስት በኦሞ ተፋሰስ ላይ በርካታ ግድቦችን በመገንባት ላይ መሆኑን ጠቅሶ የወንዙ ውሃም ከግድቦች ወደ እርሻዎች በመስኖ ተቀይሷል። እነኚህ አጠቃላይ ስራዎች በአካባቢው ባሉ ነባር ህዝቦች ላይ ፈተና ደቅነዋል። ወደ 200 ሺህ አርብቶ አደሮች በአካባቢው ይኖራሉ አብዛኛዎቹም መሬቶቻቸው ያለ አንዳች ካሳ ሲነጠቁ ተመልክተዋል። አንዳንዶችም በግዴታ ወደ ሌላ መንደሮች ተወስደው እንዲሰፍሩ ተደርገዋል። እናም ኑሮአቸው በከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቋል።

እንደሚታወቀው የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የዓለም ሙቀት መጨመርና የአየር ንብረት ለውጥ በተፈጥሮ ላይ እያስከተለ የሚገኘውን ተፅዕኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይ ይበልጥ እየተጠቃች የምትገኘውን የአፍሪካን ድምፅ በማሰማት የበለፀጉ ሀገሮቹ ኢንዱስትሪዎቻቸው ለብክለት አስተዋፅኦ ስላላቸው ተጠቂ ለሆኑ ድሀ ሀገሮች የካሳ ክፍያ እንዲከፍሉ በማለት በኮፐን ሀገንና በሜክሲኮ ተደርገው በነበሩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ንግግር በማድረግ የላቀ ውጤት ማስመዝገባቸው አይዘነጋም። ይሁን እንጂ በርሳቸውም ሆነ ከእርሻቸው ቀጥሎ ያለው አስተዳደር በሀገር ውስጥ በሚካሄድ የልማት እንቅስቃሴ ሳቢያ በኢንቫይሮንሜንትና በነባር ህዝቦች ላይ እየደረሰ ስላለው መፈናቅል በተመለከተ የሚቀርበውን ወቀሳ በማጣጣል የልማት ስራው ለአካባቢው ህዝቦች የሚበጀን መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት ጠቀሜታን ያስገኛል በማለት ሁኔታውን በማስተባበል ላይ ይገኛል።

ከወራት በፊት ሚስስ ሮዛ ፍራንክሊን የተባሉ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የውሃ ፖለቲካ ተመራማሪ ከቢቢሲ ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት የኦሞ ወንዝ ገና በላይኛው ተፋሰስ ላይ በተራራማው አካባቢ በሚገነባው የግልገል ጊቤ ሶስት ግድብ የተነሳ ወንዙ መፍሰሻ መሬቱን ትቶ አዲስ በሚሰራለት ቦይ እንዲፈስ በመደረጉ የስነምህዳር ቀውስ አስከትሏል። ከዚያም አልፎ በኬንያና የኢትዮጵያ ድንበር ላይ በሚገኘው በቱርካናሃይቅ የመጠን መቀነስ ያስከትላል። ነዋሪዎቹም ይጎዳሉ ብለው ተናግረው ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ ሰምታ ወደ ጎን በመተው መንግስት በሃይድሮኤሌትሪክ ግንባታም ሆነ በእርሻ ልማቱ ቅድሚያ ሰጥቶ እየገፋበት ይገኛል። በልማት ሳቢያ በተፈጥሮ ሀብትና በኢንቫይሮሜንት ላይ የሚርስ ውድመትና የነዋሪዎች መፈናቀል በደቡብ ኦሞ ሸለቆ ብቻ የተከሰተ ክስተት አይደለም። በጋምቤላ አካባቢም ከ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ በደን የተሸፈነ መሬት ለእንደነካራቱሬ ለመሳሰሉ የውጭ የእርሻ ኩባንያዎች እየተሸጠ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል። ነዋሪዎችም ተፈናቅለዋል በቅርቡ የአልጀዚራ ቴሌቭዥን ታዋቂውን ኢትዮጵያዊ የማህበራዊ ሳይንስ ተማራማሪ አቶ ደሳለኝ ራህማቶን ጠቅሶ በሰራው ዘጋቢ ፊልም እንዳመለከተው በጋምቤላ አካባቢ ነባር ነዋሪ ከሚባሉት በርካቶች የኑዌርና የአኝዋክ ጎሳ አባላት አካባቢያቸው ለውጭ ባለሀብቶች እንዲሰጥ ተደርጎ በሰፈራ መንደሮች በግዴታ እንዲሰፍሩ መደረጉንና የሰብዓዊ መብት ረገጣም እንደተፈፀመ አመልክቷል።

በተለይ ብዙ የውጭ የመብት ተሟጋቾች በሚያቀርቡት ትችት ኢትዮጵያ በየዓመቱ የ804 ሚሊዮን ዶላር ምግብ በምፅዋት ከውጭ እየተቀበለች የውጭ ሀገር ኩባንያዎችን በሀገሯ መሬት ላይ እንደሩዝና ስንዴ የመሳሰሉ አዝርእቶችን አምርተው ወደሀገራቸው ወስደው የገዛ ህዝባቸውን መመገባቸው የነገሩን እንቆቅልሽን ከማመልከት ባሻገር ለህዝብ ተቆርቋሪነት ማጣትን ያረጋግጣል በማለት ትችት ይሰነዝራሉ። በቅርቡም የአሜሪካ ኮንግረስ ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን የልማትና የወታደራዊ አርዳታን በተመለከተ ከፍተኛ ቁጥጥር እንዲደረግባቸው አፅንኦት ሰጥቶ ከሳሰባቸው ድርጊቶች ውስጥ በልማት ስም ተወላጆችን መሬት መቀማት አንደኛው ሲሆን የዚህ መሰሉ ድርጊት ካልተገታም እርዳታው ሊገኝ እንደማይችል ህጉ በግልጽ አስቀምጧል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ህገ መንግስት በይፋ እንደሚገልፀውም ማናቸውም ሰው ከመኖሪያ አካባቢው እንደማይፈናቀል ይጠቅስና አካባቢው ለልማት የሚፈለግ ቢሆን እንኳን ለተነሺዎች አስፈላጊው ካሳ እንደሚከፈል ይደነግጋል። ከዚህ አኳያ በደቡብ ኦሞና በጋምቤላ በልማት ምክንያት የተከናወነው መፈናቀል በግልፅ የህግ ጥሰት የተስተዋለበት እንደሆነ እየተጠቀሰ ይገኛል።

እንደ ሂዩማን ራይት ዎች ምክትል ዳይሬክተር ሚስስ ሌስሊ ሌፍቶ ገለፃ በደቡብ ኦሞ የመሬት ምንጣሮው በአካባቢው የሚካሄደው ሰፊ የልማት ስራ አንዱ አካል ነው። የግድብ ግንባታው የስኳር ተከላ ማምረቻውም ሆነ ለገበያ የሚሆነው እርሻ የኦሞን ወንዝ ውሃ በስፋት ይጠቀማል የሚል ስጋት አለ። በአካባቢው በኢትዮጵያም ሆነ በኬንያ የሚኖሩና ውሃውን በኑሮአቸው ለከብቶቻቸው የሚጠቀሙ 500 ሺህ ወገኖችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንደሚጎዳ አመልክተዋል። ተቋሙ በዘገባው የኢትዮጵያ መንግስት ልማቱን የማካሄድ መብት እንዳለው ጠቅሰው ነገር ግን ልማቱ የአካባቢውን ማህበረሰብ መብት በጠበቀ መልኩ ማከናወን እንዳለበት አሳስበዋል። የዚህ መሰሉ ግዙፍ ልማት ሲከናወን የጎንዮሽ ጉዳት አይጠፋምና ሁኔታው እንዴት ይታያል ተብለው የተጠየቁት ምክትል ዳይሬክተርዋ ሲመልሱ በርግጥ የኢትዮጵያ መንግስት እንደማናቸውም መንግስታት ለኢኮኖሚው እድገት ውሃውንም ሆነ የተፈጥሮ ሀብቱን ማልማት ይቻላል። ነገር ግን ችግሩ ልማቱ የሚከናወንበት መንገድ ነው። የሚያሳዝነውም የልማቱ ስራ የነዋሪዎቹን መብት ከግምት አለማስገባቱ ነው። አብዛኛዎቹ ሰዎች ስለ ይዞታቸው ጉዳይ አልተጠየቁም ካሳም አልተከፈላቸውም። የአኗኗራቸውም ሁኔታ በፍጥነት ካለመዱት ወደ አለመዱት ማለትም ከአርብቶ አደርነት ወደ አርሶ አደርነት የተቀየረ ነው ብለው ተቋማቸውና ሌሎች የመብት ተሟጋቾች ይህንን ጉዳይ በማንሳት ለኢትዮጵያ የመንግስት ጥያቄ ቢያቀርቡም መንግስት በበኩሉ ዘገባዎቹ ከእውነት የራቁ ናቸው በማለት ሲያስተባብል ቆይቷል። የሚሰራው ስራም የማህበረሰቡን ህይወት በአወንታዊ መልኩ ይለውጣል ባይ ነው። ሚስስ ሌስሊ ሌፍቶ በበኩላቸው የዚህ መሰሉ ግዙፍ የልማት ስራ ሲከናወን ማህበረሰቡ ሃሳቡን የመስጠት መብቱ ሊከበርለት ይገባል ይላሉ። ሰዎች በድንገትና በግብታዊነት መሬታቸውን ሲነጠቁና አዲስ ቦታ ላይ እንዲሰፍሩ ሲደረጉ ህይወታቸውን እንዴት ማቆየት እንደሚችሉ ይቸገራሉ። ምክንያቱም ከአኗኗራቸው ከሚያውቁት ፍፁም የተለየ ስለሚሆን ነው። ለአዲስ ህይወትም አልተዘጋጁም አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚጠቅሱት ኢትዮጵያ አፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ የዓለማችን ደሀ ሀገሮች ውስጥ አንዷ መሆንዋንና መንግስት የሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች ሀገሪቱን ወደ መካከለኛ ገቢ ሀገርነት ያሸጋግራታል ይላሉ። ነገር ግን እደ ሂይውማን ራይትስ ዎች ያሉ ተቋማት ለኢትዮጵያ መንግስት የማያቀርባቸው አቤቱታዎችን ጆሮ ሰጥቶ ማን ያደምጣቸዋል ተብለው የተጠየቁት ምክትል ዳሬክተር ሲመልሱ መንግስት ያወጣነውን ሪፖርት በጥንቃቄ ተመልክቶና ተገንዘቦ አስተሳሰቡን በመቀየር የልማቱ ስራ ሁሉንም ወገን በሚጠቅም መልኩ እንዲከናወን ያደርጋል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1564 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 940 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us