ረጲን ከቆሻሻ ማከማቻነት ወደ ኃይል ማመንጫነት

Wednesday, 19 March 2014 14:01

በአሁኑ ወቅት ለአካባቢ ውድመትና ብክለት ለሰው ልጅ ጤና ጠንቅ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያደረገ የሚገኘው ታዳሽ ያልሆነውና በባህላዊ ዘዴ ጥቅም ላይ የሚውለው የባዮማስ ኢነርጂ እንደሆነ ሙያተኞች ይገልፃሉ። በኢትዮጵያ በተለይ ለቤት ውስጥ አገልግሎት የሚውለው 94 በመቶ የሚሆነው የኃይል ምንጭ ባዮማስ መሆኑ በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን ጥፋት ለመገመት አያደግትም። ከዚህ አንፃር ይህን ችግር ለመቋቋምና ለመቅረፍ እንዲቻል የኃይል ምንጩን በታዳሽና ቆጣቢ በሆነው መተካት በዋንኛነት መፍትሄ ሆኗል። ታዳሽ ኃይል ከከሰልን ከማገዶ የሚመነጨውንና ለጤና ጠንቅ የሆነውን ጭስን ለማስቀረት የላቀ ጠቀሜታ አለው።

ታዳሽ ኃይልን ከተለያዩ ምንጮች ማግኘት ይቻላል ፀሐይ፣ ንፋስ፣ ባዮፊውል፣ ጂኦ ተርማል ወዘተ ከዚህ ውስጥ ይጠቀሣሉ። ከዚህ በተጨማሪ በመሬት ውስጥ ታምቆ LPC የተባለውን ጋዝ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማውጣት ለቤት ውስጥ ምግብ ማብሰያነትም ሆነ ለኤሌክትሪክ ምንጭነት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል የሪጅን ኢነርጂ ልማት በማከናወን የሚገኘው የፊንላድ ኩባንያ ስራ አስኪያጅ የሆኑት ሚስተር ኢስሞ ጌፊርድ ይገልፃሉ። በአሁኑ ወቅትም በአካባቢው 100 ሺህ ኪዩቢክ ሜትር ሚቴን ጋዝ እንዳለ አመልክተው፤ ይህ ጋዝ ከመሬት ውስጥ በተፈጥሮአዊ ሁኔታ እያፈተለከ በመውጣቱም ከካርቦንዳይኦክሳይድ የበለጠ በአካባቢ ላይ ብክለት እንደሚያስከትል አስታውቀዋል። ከዚህ አኳያ ጥፋት የሚያስከትለውን ጋዝ አምቆ ጥቅም ላይ ማዋል አካባቢ እንዳይበከል በማድረግ ከንፁህ ልማት ኘሮጀክት CDM ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪም ያስገኛል።

እንደሚታወቀው የረጲ አካባቢ ላለፋት 40 ዓመታት ከአዲስ አበባ ከተማ የተሠበሰበ ቆሻሻ የሚደፋበት ሲሆን፤ ቆሻሻው በግልፅ ሜዳ ላይ በመጣሉ መጥፎ ጠረንን በማስከተል በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ በተለይ ገና በሚወለዱ ህፃናት አካላት ላይ የጤና ችግር ሲያስከትል ቆይቷል። በአካባቢው ጡንቻቸውን የሚተማመኑ የጐበዝ አለቆች ቆሻሻውን መልሶ ለመጠቀም በሚያደርጉት ግብግብ ወደ ቦታው በሚሄድ ሰው ላይ ከፍተኛ ወንጀልን በመፈፀም አካባቢውን የስጋት ምንጭ አድርገውት እንደነበር አይዘነጋም። ነገር ግን ለዕውቀትና ለቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባውና ያ የሚያስፈራ አካባቢ የኃይል ምንጭ በመሆን ለአካባቢው ነዋሪዎችም ትሩፋት እንደሚያስገኝ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ኘሮግራም የአካባቢ ቴክኒካዊ የአየር ንብረት ለውጥ አማካሪ ሚንስተር ጆን አቢሪን ይገልፃሉ።

የረጲ ታዳሽ ኃይል ምንጭ አካባቢ ለመጀመሪያ ጊዜ የመልክዐ-ምድራዊና ከርሰ-ምድራዊ የዳሠሣ ጥናት የተካሄደበት እ.ኤ.አ በ2009 ሲሆን፤ ስራውን በጋራ በመተጋገዝ ውል የተፈራረሙትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተባበሩት መንግስታት የልማት ኘሮግራምና ዋና ፅህፈት ቤቱ በአዲስ አበባ የሆነው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢያዊ የኢንቫይሮመንት ማዕከል ነው። ለስምምነቱ መሠረት የሆነውም ከኪዮት ኘሮቶኮል የሚመነጨው የንፁህ ልማት መካኒዝም ነው። ከዚህ ጎን ለጎንም እጀግ አደገኛ መርዛማ ንጥረ ነገሮችን በማስወገድ የኃይል አቅርቦቱን ዘለቄታዊ በሆነ መልኩ መጠቀም እንዲቻልና ከካርቦን ገበያ ገንዘብ በማመንጨት የአካባቢው ነዋሪን ተጠቃም ማድረግ ነው።

የረጲ አካባቢ በ36 ሔክተር መሬት ላይ ያረፈ የከተማ ክልል ነው። አካባቢው ላለፉት 40 ዓመታት በየዕለቱ 900 ቶን ደረቅ ቆሻሻን ሲቀበል ኖሯል። ይህ ቆሻሻም አንዳችም ጊዜ ታክሞም ሆነ ወደሌላ ዓይነት ግብአትነት እንዲቀየር ጥረት አልተደረገም። በአካባቢው ላይ ጥናት ያደረጉት ሚ/ር ኢስሞ እንደሚገልፁት፤ ቆሻሻው በውስጡ አደገኛ በካይ ንጥረ ነገር የሆነውን ኤል ኤር ጂን የያዘ ሲሆን፤ ከውስጡ የሚወጣው መጥፎ ጠረን ለሰው ጤና አደገኛ ነው። ከ40 ዓመታት በፊት አካባቢው ለቆሻሻ መድፊያነት ሲመረጥ ከከተማዋ ነዋሪዎች እጅግ የራቀ ስለሆነ ብዙም ጉዳት አያስከትልም በሚል ታሳቢ ነበር። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ከነዋሪው ህዝብ ቁጥር መጨመር ከገጠር ወደ ከተማ እየፈለሰ በሚመጣው ህዝብ የተነሳ አካባቢው በመኖሪያ መንደሮች ለመከበብ በቃ። ቦታውም የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕንቅስቄዎች መናኸሪያ ሆኖ ትምህርት ቤቶች ጭምር ሊስፋፉበት ችለዋል። በቦታው መበከል ሳቢያ የተለየዩ ከሠው ወደ ሠው የሚተላለፉ በሽታዎች ተከስተዋል። ተማሪዎች በሚቴን ጋዝ አማካኝነት በሚከሰት መዘዝ የመተንፈሻ አካላት ዕውክታ በየጊዜው ይገጥማቸዋል። ያልተወለዱ ህፃናት በወሊድ ወቅት መጨናገፍና መሞትም ዕጣፈንታቸው ሆኗል። አላፊ አግዳሚውም በሰንፋጭ ጠረን ይታወካል።

በርግጥ በዚያ ቦታ የሰው ልጅ ጤንነት የተጠበቀ እንዲሆን ስር-ነቀል በሆነ መልኩ መለወጥ ይኖርበታል። ከዚህ ባሻገር ከመሬት ውስጥ ታምቆ ያለውን ታዳሽ ኃይል ጥቅም ላይ አውሎ ነዋሪውም እንዲጠቀም ማድረግ አስፈላጊ ነው። በአካባቢው ያለው የታዳሽ ኃይል ኘሮጀክት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት መርሃ-ግብር ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ለሙከራ በተተከለ ማሽን ፓምኘ በማድረግ በመሬት ውስጥ ታምቆ ያለውን የጋዝ መጠንና ዓይነት ለማወቅ ጥረት ተደርጓል። ሙከራውም የሜታን ጋዝ ለኃይል አቅርቦት እንደሚውል ይህን በማደርግም አካባቢውን ከብክለት መታደግ እንደሚችል ተረጋግጦ በዚህ ሂደትም የካርቦን ገንዘብ ማስገኘት እንደሚያስችል ታውቋል። ይህ ገንዘብም ለአካባቢው ነዋሪ ጥቅም እንዲሠጥ ይደረጋል። ይህን አስመልክቶ ሚስተር ጆን አበሬን ሲናገሩ፤ በረጲ የሚካሄደው የታዳሽ ኃይል ልማት የካርቦን ፋይናስ ዘለቄታዊ ልማት ከማስገኘት በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ኢንቫይሮንመንታዊ ጠቀሜታን እንደሚያስገኝ አመልክተዋል። ኘሮጀክቱን በአሁኑ ወቅት እየመራ የሚገኘው የፊላንድ ኩባንያው ስራ አስኪያጅ ሚስተር አሲም በበኩላቸው፡ ኩባንያው በዋነኛነት LFG የተባለውንና የሚቴን ጋዝ ውጤት የሆነውን ከመሬት ውስጥ ማሰባሰብና ወደ አንድ ቋት ማስገባት ከዚያም ወደ መንደድ ደረጃ እንዲደርስ የሚያደርግ ማሽንን መትከል ስራውን ማከናወን፣ ጥገና ማካሄድ፣ ቁጥጥር ማድረግ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪ ለአካባቢው ነዋሪዎች በቦታው ላይ በጉልበት የጐበዝ አለቃ ሆነው ላሉት ስራ አጦች ዘለቄታዊ የስራ ዕድል መፍጠር ነው።

በአሁኑ ወቅት ጋዝ ይገኝበታል የተባለበት አካባቢ በጥንቃቄ ፅዱ ሆኖ የታጠረ ሲሆን፤ ጋዝን የሚያወጣው መሣሪያ ተከላና ሌሎች የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። የአፍሪካ ቀንድ የኢንቫይሮመንትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣንም ተቀናጅተው እጅግ በተራቀቀ መሣሪያ አማካኝነት ጋዙ ከባቢ አየርን እንዳይበክል ተደርጐ ለኃይል ምንጭነት ሲውል ምን ያህል ብክለት ማስቀረት እንደተቻለ በጥንቃቄ ይቆጣጠራሉ ቀሪዎቹ ከብስባሹ የሚመነጩ በካዮች በመቃጠል ሂደት እንዲወገዱ ይደረጋል። በዚህ ሂደት የከተማው አስተዳደር የአፍሪካ ቀንድ የኢንቫይሮመንት ማዕከልና የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት ከካርቦን ሸማች ሀገሮች ጋር ድርድር በማድረግ የሚገኘው ገንዘብ ለፕሮጀክቱ ማጠናከሪያ እንዲውል ያደርጋሉ።

በንፁህ ልማት ስርዓት የገንዘብ መጠየቂያ ፕሮፖዛልም የፕሮጀክት ዲዛይኑ ተዘጋጅቶ ለሚመለከተው አካል የቀረበ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም ለምዝገባ እየተጠባበቀ ይገኛል። አንዴ ፕሮጀክቱ ዕውቅና አግኝቶ ከተመዘገበም የከተማው አስተደደር በመጭዎቹ አስር ዓመታት ቀላል የማይባል ገንዘብ የሚያገኝ ሲሆን፤ የተረጋገጠ የካርቦን መሸጫ ካርድም ያገኛል። ከዚሁ በተጨማሪ ፕሮጀክቱ በጐልድ ስታንዳርድ ፋውንዴሽን በመመዝገብ ገንዘብ በአስተማማኝ እያገኘ ለዘለቄታው ፕሮጀክቱ የቀጥላል። ከዚህ አንፃር ፕሮጀክቱ ለወደፊቱ ከአካባቢው አልፎ በተዋረድ ለሌሎች አካላት ጠቀሜታ መስጠት ይችላል። እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት በከተማችን በየቀበሌውያ በየመንደሩ በቆሻሻ ማሰባሰብ ስራ ተደራጅተው የሚሰሩት ወደ 50 ሺህ አባላት አሉ። ይህ ከየቤቱ አያስፈልግም ተብሎ የሚጣልን ቆሻሻ በስርዓት ወደሚቀበርበት ወደ ረጲ ቆሼ እንዲሄድ ማድረግቸው የፅዳት ሠራተኞች ብቻ ሳይሆን የኃይል ምንጭ አጋር ይሆናሉ። ስለሆነም ትሩፋቱ በፕሮጀክቱ አማካይኝነት ወደኪሳቸው እንዲገባ ይደረጋል።

ከዚህ አኳያ ቆሻሻ ሀቭት ነው የሚለው ቃል ከመፈክር አልፎ በተግባር ዕውን መሆኑ ይረጋገጣል ማለት ነው። ይህ ጉልበትን ብቻ የሚጠይቀው የደረቅ ቆሻሻ ማሰባሰብ ስራም የተናቀ መሆኑ ቀርቶ በርካቶች በውስጡ ገብተው የሚሰሩት ስለሚሆን የስራ ዕድለ ፈጠራ አቅሙ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም። ደረቅ ቆሻሻን አሰባስበው ሪሳይክል በማድረግ መልሶ ጥቅም ላይ የሚያውሉ ወገኖችም ስራው ሲስፋፋ የበለጠ ግብአት ስለሚያገኙ ምርቶቻቸውን አስፋፍተው ለገበያ በማቅረብ ገበያቸውን ያሳድግሉ። ተጨማሪ የስራ ሀድልም ለሌሎች ይፈጥራሉ። ስለሆነም ቆሻሻ አካባቢን መበከሉ ቀርቶ ታዳሽ ኃይል ይሆናል። ይህም ደን እንዳይጨፈጨፍና አካባቢ እንዳይራቆት የበኩሉን ዕገዛ ስለሚሰጥ ጠቀሜታው ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም። ስለሆነም ቆሻሻን ሁሉም ነዋሪ በስርዓት ሰብስቦ በማዳበሪያ በማከማቸት በቀላሉ ከቦታ ቦታ ተጉዞ ወደተፈለገው ቦታ እንዲሄድ ማድረግ ይጠበቅበታል።

የረጲ ፕሮጀክት ከማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ሲቃኝ በንፁህ ልማት ስርዓትና በካርቦን ንግድ በሚገኝ ገንዘብ አካባቢው እንዲለማ ተደርጐ ከዚህ ቀደም ባልታየ መልኩ ሰፊ የመናፈሻ ስፍራ እንዲገነባ ይደረጋል። ይህም በጐብኚዎች ስለሚታይ ገንዘብ ያመጣል። ወደ 200 የሚጠጉ ስራ አጦችም በመናፈሻውና በተያያዥ ስራዎች እንዲሰማሩ እንደተደረጉ የአፍሪካ ቀንድ የኢንቫይሮመንት ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር አርአያ አስፋው ይገልፃሉ። በስራ ላይ የዋለው ቴክኖሎጂም ለንፁህ ልማት ወሳኝና በጣም ዘመናዊ መሆኑ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ነው። መሣሪያው አተካከሉ ጥንቃቄ የተደረገበት በመሆኑም አንዳችም የማፈትለክ ክስተት ሳይኖር በስርዓት ጋዝ ተሰብስቦ ወደሚፈለገው ገበያ እንዲሄድ የሚያደርግ ነው።

ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገባ በየዓመቱ 46 ሺህ 494 ቶን የካርቦንዳይኦክሳይድ መጠን የሚያህል ሜታን ጋዝ ወደ ከባቢ አየር እንዳይለቀቅ በማድረግ ምንም ጉዳት ሳያደርስ ወደ ኃይል ምንጭነት ይቀይረዋል። ከዚህ አኳያም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውንና የሙቀት መጨመርን ለመቀነስ የሚካሄደውን ጥረት ያግዛል። ጤናማና ነፋሻማ አየር እንዲኖር ያደርጋል። ለከተማዋ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን በማፋጠንም በኅብረተሰቡ ላይ እየተስተዋለ የሚታየውን የመተንፈሻ አካላት ህመምን ለመግታት ያስችላል። ለሌሎች አካባቢዎችም እንደ ሞዴል ይሆናል።

     ቆሻሻ የዚህን የመሰለ ጥቅም የሚሰጥ ከሆ፤ ስለቆሻሻ ያለንን አስተሳሰብ መቀየር ግድ ይላል። እንደሚታወቀው ቆሻሻን በስርዓት የማስወገድ ባህላችን እጅግ በጣም ደካማ ነው። ቤታችንን አፅድተን ያገኘነውን ደረቅ ቆሻሻ ከቤታችን ራቅ አድርጐ መጣል የተለመደ ነው። ቆሻሻው ወደ መሬት ውስጥ ከገባ በሂደት ከመሬት ስር በካዩን ሜታን ጋዝ በማመንጨት አካባቢን እንደሚበክል ብዙ ሰው አያውቅም። ዓይነምድርንና ሽንትን በየቦታው የመፀዳዳቱ ነገርም እየባሰ እንጂ እየተሻሻለ ሲመጣ አይስተዋልም። በአብዛኛው እኛ የምናውቀው መጥፎ ሽታ ማምጣቱን እንጂ ከላይ የተጠቀሰውን በካይ ጋዝ በሂደት እንደሚያመጣ አይደለም። ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎች በየወንዛ ወንዙም እየተለቀቁ በኢኮ ሲስተሙ ላይ ጥፋት እያደረሱ ስለመገኘቱ በተደጋጋሚ ሲገለፅ የቆየ ነው። መሻሻል ግን እምብዛም አይስተዋል። ሰለሆነም አካባቢ እየተራቆተና አየር እየተበከለ ይገኛል። ነገር ግን ይህን ጥፋት ወደ ልማት መቀየር እንዲቻል ከተፈለገ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓታችን ይበልጥ መጐልበት አለበት። ባህላችንም መሻሻል ይኖርበታል። በከተማችን በፍጥነት እየተስፋፋ የሚገኘው የኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ቆሻሻን በማመንጨት ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው። በመልሶ መልማት የሚፈራርሱ ያረጁ መኖሪያ ቤቶችና መንደሮችም ፍርስራሻቸው የቆሻሻ ምንጭ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። በመሆኑም ቆሻሻ በስርዓትና በአንድ ቦታ እንዲከማች በማድረግ ታዳሽ ኃይል እንዲሆን የማድረጉ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መረባረብ ግድ ይላል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1152 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 943 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us