እርጥበት አዘል መሬቶች እየተጐዱ ነው

Wednesday, 26 March 2014 12:23

በአይቼው ደስአለኝ

በሀገራችን ረግረጋማና ርጥበት አዘል መሬቶች በተለያዩ አካባቢዎች ይገኛሉ። የአካባቢን ስነምህዳርን በመጠበቅ አካባቢያዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን በማስገኘት ይታወቃሉ። በደረቃማ በጋ ወቅት ቦታዎቹ በክረምት ወቅት በውስጣቸው እንደ እስፖንጅ መጥጠው የያዙትን ውሃ በማስቀረት አካባቢን በማርጠብ ይደግፋሉ። በክረምት ወቅት የጐርፍን ውሃ ይዘው ወደ መሬት እንዲሠርግ ያደርጋሉ። ውሃን የማጣራትም አቅም አላቸው። በዚህም የዓሣ አስጋሪዎችን የአርብቶ አደሮችንና የአርሶ አደሮችን ህይወት ይታደጋሉ። ከዚህም ባሻገር ሌሎች ሰፊ ጠቀሜታን ይሰጣሉ።

አቶ አፈወርቅ ኃይሉ በትምህርታቸው የናቹራል ሪሶርስ የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፤ የኢትዮ ዌትላንድ ናቹራል ሪሶርስ ማኅበር ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ናቸው። በዚሁ ሙያ ከሰላሳ ዓመታት በላይ አገልግለዋል። በአሁኑ ወቅት ዓለምም ሆነ ሀገራችን በአየርንብረት ለውጥና በሙቀት መጨመር የተነሳ ክፉኛ እየተጠቁ ባሉበት በሀገራችን የሚገኙ የእርጥበት አዘል መሬቶች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እየሰጡ ያለውን ጥቅም ሲገለፁ፤ አካባቢዎቹ ከአየር ንብረት ለውጥ አኳያ ተጠብቀው በእንክብካቤ ከተያዙ በካይ የሆኑ ጋዞችን ከመቀነስ በተጨማሪ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አላቸው። ውሃ አቁረው በመያዝ የውሃ ተጠቃሚ እንድንሆን ያደርግሉ። የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አኳያም የበኩላቸውን ሚና ይጫወታሉ። በውሃዎቹ ውስጥ የሚገኙት ብስባሽ ግንዶቭ ሙቀትን ወደ ውስጥ በማስቀረት በአካባቢ ነፋሻ አየር እንዲኖር ያደርጋሉ። በውሃ ዳር የሚበቅሉ እንደ ቄጤማ የመሳሰሉ ተክሎች እንዲፀድቁ የውሃ ውስጥ እንሰሳት ህልውናቸው አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። የእነርሱ መኖር አፈር በጐርፍ ታጥቦ ከሀገር እንዳይወጣ ያደርጋሉ። ከውሃው የሚተነው አየርም ተመልሶ በዝናብ መልክ በመምጣት ለእርሻ ውሃ እንዲገኝ ያመጣሉ በአርብቶ አደሮች አካባቢም የግጦሽ መሬቶች ተመልሰው እንዲያንሰራሩ በማድረግ ከብቶች በደረቅ ወቅት ከእልቂት እንዲድኑ ባለቤት የሆኑ አርብቶ አደሮችም የስጋና የወተት ተዋፅኦን ለራሳቸውም ሆነ ለገበያ በማቅረብ እንዲጠቀሙ አመቺ ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ። ይህ ተያያዥ የስነምህዳር ኡደትም በአጠቃላይ ተፈጥሮ ሚዛንዋን ጠብቃ እንድትቆይ ያደርጋል።

እንዲያም ሆኖ ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአፍሪካም ሆነ በሀገራችን የዌትላንድ ርጥበት አዘል መሬቶች በእርሻ መሬት ፍላጐት መጨመር ሳቢያ ለአደጋ እየተጋለጡ በመሄድ ላይ ናቸው። የአየር ንብረት በሚያመጣው ድርቅና ቸነፍር የተነሳም ቦታዎቹ የአርሶ አደሮችን ትኩረት እየሳቡ ይገኛሉ። የህዝብ ቁጥር እድገት የሚያስከትለው ጫናም ችግሩን በማባባስ ላይ ናቸው። በሀገራችን ለዘመናት ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነውን ህዘብ ተሸክሞ ያለው የእርሻው ክፍል ከባህላዊ አስተራረስና ከዝናብ ጥገኝነት አለመላቀቁ በእነኚህ አካባቢ ያለው አርሶ አደር ወደ ርጥበት አዘል መሬቶች ዓይኑን ቢያማትር ብዙም አስደናቂ ሊሆን አይችልም። በዘርፉ የተሰማራው ህዝብ በሌላ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለመዋጥ እድል ካላገኘ በተበጣጠሰ መሬት በሚታረስ እርሻ የእህል ምርታማነትም ሆነ ውጤታማ የአካባቢ ጥበቃ ስራ ማከናወን ይቻላል ማለት እጅግ አስቸጋሪ ነው። መንግሰትም በተለያዩ ጉዳዮች ተጠምደው ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ እንደመሆኑ የርጥበት አዘል መሬቶች በአካባቢ ነዋሪዎች አንዲጠበቁና እንዲተዳደሩ ማድረግ ግድ የሚል ነው።

ከዚህ አኳያ በሀገራችን ርጥበት አዘል መሬቶችን ለመንከባከብ በመንግስት የሚከናወኑ ተግባሮችና የሕግ ማዕቀፎች ምን እንደሚመስሉ የተጠየቁት አቶ አፈወርቅ ሽመልስ፤ በተለያየ መልኩ ውሃ አዘል መሬችን ለመጠበቅ የተለያዩ ስራዎች ይሰራሉ። ጠቀሜታቸው እንዲቀጥልና ስነምህዳሩ እንዲጠበቅ የሚደረግበት ሁኔታ አለ። ነገር ግን ድርጊቱ ሙሉ በሙሉ የሚከናወነው የቦታዎቹን ስነምህዳራዊ ጠቀሜታን በመገንዘብ አይደለም። በአሁኑ ወቅት በተፋሰስ ልማት ውሃ አዘል መሬቶች ተጠብቀው እንዲዘልቁ ድጋፍ ሊያደርግ ይችላል። በአጠቃላይ በውስጡ ያሉትን የተፈጥሮ ሀብቶች ከመንከባከብ አንፃር ጠቀሜታ ይሰጣል። ነገር ግን በተናጥል የውሃ መሬቶችን የብቃል ማለት አይቻልም። በሀገራችን ውሃ አዘል መሬቶች በእንክብካቤ እጦት የጠፉ አሉ። ለምሳሌ የአለም ማያ ሐይቅ የሚጠቀስ ነው። በደቡብ በያቤሎ፣ በሞያሌ፣ በሜጋና በመሳሰሉት ውሃ አዘል መሬቶች ለግጦሽና ለእርሻ በመዋላቸው ለመጥፋት እየተቃረቡ ነው። ለዚህም ዋና ችግሩ እንደ አቶ አፈወርቅ ገለፃ፤ ውሃ አዘል መሬቶችን ለመጠበቅ በግልፅ የተቀመጠ ፖሊሲ አለመኖር ነው። ስለዚህ ፖሊሲዎች ተቀርፀው ካልተተገበሩ በተፋሰስ ልማት ስራ ብቻ ችግሮቹን መቅረፍ አይቻልም።

ከህዝብ ቁጥር መጨመርና ከግጦሽ መሬት ፍለጋ በተጨማሪ በሀገራችን ርጥበት አዘል ሌሎች ችግሮችም ይስተዋልባቸዋል። በዝቅተኛው የመሬት አካባቢ በተለይም ለአርብቶ አደሮችና በከፊል አርብቶ አደሮች አካባቢ ከተፈጥሮ ሀብት ከመሬትና ከውሃ ቅርምት ጋር ተያይዞ በማኅበረሰቦች አካባቢም ግጭቶች ይስተዋላሉ። ይህ ሁኔታ በደቡብ፣ በታችኛው የአዋሽ ተፋሰስ በአፈርና በዓሣዎች እንዲሁም በድሬዳዋ አቅራቢያ ባሉ ማኅበረሰቦች የሚታይ ነው። ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በተጨባጭ የርጥበት አዘል መሬቶች ስጋት ምን እንደሆነ የተጠየቁት አቶ አፈወርቅ ሲመለሱ፤ በርካታ ስጋቶች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ከእነርሱም ውስጥ መሬቶችን በጥናት ላይ በተመሠረተ ስልት አለመጠቀም፤ አካባቢው ለጉዳት እንዲጋለጥ ያደርጋል። የትኛውን ውሃ አዘል መሬት በምን ጥቅም ላይ እናውለው የሚል ስልት ስለሌለ ጉዳት ይከሰታል። ከዚሁ ጋር ተገቢ ባልሆነ ቦታ ላይ ውሃውን በማጠንፈፈ የእርሻ መሬት ማድረግ ቦታውን ይጐዳል። ከረግረጋማ መሮቶች ላይ አሸዋ መውሰድና ውሃውን መጠቀም ችግሩን ያባብሳል። ከእርሻ መሬቶች በጐርፍ የሚታጠብ አፈር ውሃ አዘል መሬቶች ላይ ሲተኛ ከዚህ በፊት ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት በመተው ወደ ደረቅ መሬት ይቀየራል። በውሃ ዳርቻ ያሉ ሣሮች ከተገቢው በላይ በከብቶች ሲጋጡም በሂደት ቦታው አንዲደርቅ ያደርጋል።

ርጥበት አዘል መሬቶች ከዝቅተኛ አስከ ከፍተኛ የመሬት አቀማመጥ ባላቸው የሀገራችን አካባቢ ይገኛሉ። በደጋማ አካባቢ ከባህር ወለል ከ1000 እስከ 2000 ሜትር ላይ ያሉ ሲሆን፤ በተለይ ከፍተኛ የወንዝ ምንጮች በሚገኙበት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ኢሉባቡር አካባቢ የውሃ ምንጭና ርጥበት ፈጣሪ በመሆን ጥቅም ይሰጣሉ። በመሬት ውስጥ ውሃ እንዲከማች ማድረጋቸው ለወንዞቹ ህልውና ከፍተኛ ጠቀሜታ ከመስጠታቸው ባሻገር በደን የተሸፈኑ አካባቢዎች ልምላሜያቸው የተጠበቀ እንዲሆን ያደርጋሉ። የቆዳ ስፋታቸውም ከ10 እስከ 300 ሔክታር ይደርሳል። እንደ ሙያኞች ገለፃ የኢሉባቡር 4 በመቶ የሚሆነው መሬት በርጥበት አዘል መሬት የተሸፈነ ነው። በምዕራብ ወለጋም ተመሳሳይ መጠን ያለው መሬት ይገኛል። ለአካባቢው ዓመቱን ሙሉ የውሃ ምንጭ ሆነው ያገለግላሉ። ከፍተኛ የዝናብ መጠን ከሰኔ እስከ ነሃሴ የሚያገኙ ሲሆን፤ 5 በመቶ የሚሆነውን የውሃ መጠን ደግሞ በታህሳስ በጥርና በየካቲት ያገኛሉ።

በአካባቢው ርጥበት አዘል መሬቶች ለጀልባና ለደለል መስሪያ የሚያገለግሉ ቄጤማዎችን ከማብቀል በተጨማሪ ለመድሃኒትነት ሊያገለግሉ የሚችሉ ዕፅዋቶችንም ያበቅላሉ። ለምሳሌ በሳይንሳዊ አጠራሩ በባላሞራንቴ የተባለውንና ለቆዳ በሽታ ህክምና የሚያገለግል ተክል በዚያ አካባቢ ጥቅም ላይ ይውላል። ረግረጋማና ርጥበት አዘል መሬቶች ለአካባቢው ከ10 እስከ 20 በመቶ የሚሆነውን የምግብ ፍላጐት የሚሸፍኑ ሲሆን፤ የምግብ እጥረት በሚያጋጥምበት በድርቅ ወራት ደግሞ እስከ 100 በመቶ የሚሆነውን ፍላጐት ያሟላሉ። በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኙ ርጥበት አዘል መሬቶች ላይ እርሻ ይበልጥ መስፋፋት የጀመረው የደርግ አገዛዝ ወደ ስልጣን ከመጣበት ከ1967 ጀምሮ ሲሆን፤ በተለይም በ1970ዎቹ አጋማሽ ሰሜን ኢትዮጵያ ክፉኛ በደርግ በተጠቃበት ወቅት 100 ሺህ ሰዎች ወደ አካባቢው ተወስደው እንዲሰፍሩ በተደረገበት ጊዜ ነው በዛን ወቅት ያለ አንዳች ጥናት የቁጥቋጦ መሬቶች እየተጨፈጨፉ የሰፈራ መንደሮች ሲቋቋምና ሰፋሪዎቹ እርሻ በመጀመራቸው ነው እንዲያም ሆኖ አካባቢው ከፍተኛ የዝናብ መጠን ስለሚያገኝ ጉዳቱ ሊቀንስ ችሏል።

በደጋማው ረግረጋማ መሬቶች በአብዛኛው የበቆሎ ሰብል የሚበቅልባቸው ሲሆን፤ ስኳር ድንች ጤፍ፣ ጐመንና ድንች በመጠኑ ይበቅልባቸዋል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ በአየር መለዋወጥ ሳቢያ ያልተለመዱ ተባዮች ሲከሰቱ ሰብሉ በከፍተኛ መጠን ለውድመት ይጋለጣል። በሌላም በኩል የቡና የኮሜርሺያል እርሻ በአካባቢው መስፋፋት የመሬቶቹ ስፋት እንዲቀንስ ሆኗል።

      በአሁኑ ወቅት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ያለውን የውሃ ሀብት እንዳለ ለማቆየትና ደኖች የተጠበቁ እንዲሆን የመሬት አስተዳደር ስርዓቱ በአካባቢው ኅብረተሰብና በአንዳንድ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ዕገዛ መከናወኑ የተሻለ ውጤት እየተገኘበት ይገኛል። በተለይም አዝዕርቶችን በማፈራረቅ መዝራት ውሃ ወደ መሬት ሰርጐ እንዲገባ የሚያስችሉ የቬቲቫር ዝርያ ያላቸውን ስሮች መትከሉና መንከባከቡ ውጤት እያስገኘ ይገኛል። በአጠቃላይ የአየር ንብረት ለውጥና የሙቀት መጨመር የሀገራችንን የእርሻ ኢኮኖሚ እየጐላ ባለበትና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥን እየተፈታተነ ባለበት ረግረጋማና ርጥበት አዘል መሬቶችን በአግባቡ መያዝና መንከባከብ ወሳኝ ነው። በይበልጥ ግን ፖሊሲ ቀርጾ ወደተግባር መግባት አስፈላጊ በመሆኑ የመንግስትን ትኩረት ይሻል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1098 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 913 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us