የከተማችን የፅዳት ፍላጎትንና አቅርቦትን እንዴት ማጣጣም ይቻላል?

Wednesday, 02 April 2014 12:34

ከ3 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ይኖርበታል በምትባለው በአዲስ አበባ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች የመኖሪያ ቤቶችና የሪል ስቴት ግንባታዎች እንዲሁም የትራንስፖርት ዘርፍ እየተስፋፋ ይገኛሉ። በዚህም የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ይበልጥ እየጎለበተ በመሄድ ላይ ይገኛል። የህብረተሰቡ አኗኗር ዘይቤም በዓይነትና በጥራት እየተለወጠ ነው። ከዚሁ ጋር የከተማዋ ዓለም አቀፍ ተፈላጊነት እየጨመረ ይገኛል። ይሁን እንጂ ያለው የፅዳት አወጋገድ ስርዓት ከተማውን በሚመጥን መልኩ ገና አልዳበረም ብዙ ስራንም ይጠይቃል። ይህን የፅዳት ፍላጎትና አቅርቦን በተመለከተ ከሰሞኑም ፎረም ፎር ሶሻል ስዲስ የተባለው መንግስታዊ ያልሆነው የቲንክታንክ ቡድን ከከተማዋ ባለሥልጣኖችን ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር የምክክልር መድረክ አካሂዷል።

በመክፈቻው ስነሥርዓት ላይ የፎረሙ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ምህረት አየነው እንደተናገሩት ፎረሙ ላለፉት ሁለት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ዘርፎች ስለሚሰጡ አገልግሎቶችና እጥረታቸውን በተመለከተ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት በማድረግ የተሻለ አገልግሎት አሰጣጥ እንዲዳብር የሚያስችል ረቂቅ የማሻሻያ ሃሳቦችን አዘጋጅቶ ለከተማው አስተዳደር አካላት ማቅረቡን ጠቁመው የሚካሄደው ውይይትም የተለያዩ ቢሮዎች በቀረበው ረቂቅ ላይ አስተያየት ሰጥተው እንዲዳብር ለማድረግ እንደሆነ አመልክተዋል። ረቂቅ ሀሳቦቹም የተቀረፁት በደረቅና ፍሳሽ አወጋገድ በህዝብ መናፈሻዎችና በመኖሪያ ቤቶች አቅርቦት ላይ ነው። ውይይቱን በገንዘብ የደገፈው በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ ረዳት አምባሳደር ሚስተር ክሪስ አለን በበኩላቸው በውይይቱ ላይ የሀገሪቱ ታዋቂ የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች መገኘታቸው ጠቃሚ ሀሳቦች ተነስተው እንደሚንሸራሸሩና የቀረቡት የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ሃሳቦችም እንደሚዳብሩ እምነታቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በስብሰባው ላይ እንዲገኙ የተጋበዙት የቢሮ ሃላፊዎች ውስጥ ከከተማዋ የህዝብ መናፈሻ አረንጓዴ ቦታዎች ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ በስተቀር ባለመገኘታቸው ውይይቱ በወኪሎች አማካኝነት ሊካሄድ የቻለ ሲሆን በዚህ ጉዳይ ላይም ከተሰብሳቢዎች ቅሬታ ተንፀባርቋል። በዚህ ፅሁፍም ትኩረታቸው በከተማዋ ፅዳት ፍላጎትና አቅርቦት ላይ ይሆናል።

በእለቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፅዳት ኤጀንሲ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ታደለ ደመኩ እንደተናገሩት ኤጀንሲው በ1996 በአዋጅ ደንብ ቁጥር 13 መሰረት ተቋቁም አስፈላጊው የሰው ሃይልና በጀት ተመድቦለት ስራውን እያከናወነ ይገኛል። ኤጀንሲው በደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ ስራ እንደተሰማራ ጠቅሰው የፍሳሽ ማስወገድ ሃላፊነት ደግሞ ለከተማዋ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ኤጀንሲ እንደተሰጠ ተናግረዋል እንዲያም ሆኖ ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ የተከማችን ትልቅ የቅሬታ ምንጭ ሆኗል ለየአካባቢው መፀዳጃ ቤቶች ሞልተው መጠጥ በማጣት ወደውጭ በመፍሰስ በጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን በማሳረፍ ላይ ይገኛሉ። እንዲያም ሆኖ ኤጀንሲው ችግሩን ለመፍታት የበኩሉን ጥረት እያደረገ ቢሆንም ህብረተሰቡ መፀዳጃ ቤት ለማስመጠጥ አገልግሎት ለማግኘት እስከ 6 ወራት ወረፋ እንጠብቃለን በማለት ቅሬታ ያሰማል። ባለስልጣን መስሪያቤቱም ችግሩን ለመፍታት 45 የፍሳሽ መምጠጫ ቦት መኪናዎች ከውጭ ሀገር ለማስገባት የግዥ ውል ፈፅሟል። አምስት መኪናዎችንም አስገብቷል። ተቀሩት 40ዎቹ ሲመጡ ደግሞ የፍሳሸ ማስወገድ ስርዓት የተሳለጠ ይሆናል ብለው የወረፋ መጠበቂያ ጊዜውም ከ6 ወር ወደ 3 ወር ዝቅ ሊል እንደሚችል አመልክተዋል።

በርግጥ በአሁኑ ወቅት በከተማችን የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓቱ ከአካባቢ አካባቢ በጣም የተለያየ ነው። በተሻለ ደረጃ የለማ አካባቢ ፍሳሽ ከከተማው ፍሳሽቆሻሻ ማስወገጃ ሲስተም ጋር የተገናኘ በመሆኑ ያለምንም ችግር መምጠጥ ሳያስፈልግ በተዘረጋለት ቦይ ስለሚለቀቅ የጤና እንከን አያስከትልም። ነገር ግን በአረጀ በተጨናነቀና በአብዛኛው በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደር ህዝብ ባለበት አካባቢ ግን ሁኔታው አሳሳቢ ነው። መፀዳጃ ቤት ሲሞላ ለማስመጠጥ የሚሆን ግንዘብ እጦት ባሻገር ለማህበራዊ ጤና የማሰቢያ ጊዜም የለም በመሆኑም ፍሳሹ ሳይመጠጥ አካባቢ እየበከለ ለረጅም ጊዜ ይቆያል። በአካባቢው የሚኖሩ ህፃናትም ለጤና ጠንቅ ተጋላጭና ሰለባ ይሆናሉ። በሌላም በኩል አንዳንድ አካባቢ ያሉ መፀዳጃ ቤቶች ፍሳሽ መውረጃቸው በቀጥታ ወደ ወንዝና ጅረት መውረጃዎች የተገናኙ በመሆኑ አካባቢውን በስፋት ሲበክሉ ይስተዋላል። በተለይም ዝናብ ለተወሰነ ሰዓት በዘነበ ቁጥር መፀዳጃ ቤቶችን ለማስተንፈስ በሚደረገው እንቅስቃሴ ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ አስፋልት ጭምር እየወጣ አካባቢን በመጥፎ ጠረን ሲያውድ ይስተዋላል። እነኚህ ችግሮች እንደ አጠቃላይ ከታዩ መፍትሄ ሊመጣ የሚችለው የተጎሳቆሉት መንደሮች እንደገና መልሰው እንዲለሙ ሲደረግ ብቻ ነው።

የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን በተመለከተም አቶ ታደለ ደመኮ ሲገልፁ አወጋገዱ የሚያተኩረው ከመኖሪያ ቤቶች ከድርጅቶች፣ ከመንገድ ላይና ከተለያዩ ተቋማት ደረቅ ቆሻሻን በመሰብሰብ በማጓጓዝና ወደ ተመደበው ቦታ ወስዶ መዘርገፍ ነው። ቆሻሻውን የማሰባሰቡ ስራም ስድስት ደረጃዎች አሉት። የመጀመሪያው በፅዳት ማህበራት አማካኝነት የሚከናወን ነው። በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከ6 ሺህ በላይ የፅዳት ማህበራት አባላት ይገኛሉ 560 የሚሆኑ አባላትም ከኤጀንሲው ጋር በመተጋገዝ ስራቸውን ያከናውናሉ። በሳምንት ሁለት ቀን ከእየመኖሪ ቤቱ ደረቅው ቆሻሻን በማሰባሰብ ወደ ገንዳዎች ይወስዳሉ። ህብረተሰቡም ገንዘብ ለእነርሱ ስለሚከፍል አገልግሎቱ ከተስተጓጎለት አቤቱታ ስለሚያቀርብ በስርዓት ቁጥጥር ይካሄዳል። በዚህ መሰረትም 78 በመቶ የሚሆነው የከተማው ነዋሪ በሳምንት ሁለት ጊዜ የፅዳት ማጓጓዝ አገልግሎት ያገኛል። እዚህ ላይ ግን ሊታወቅ የሚገባው ጉዳይ ኤጀንሲው በፕሮግራም አገልግሎቱን ይሰጥ እንጂ አገልግሎት ፈላጊው ከአካባቢ አካባቢ በጣም ይለያያል።

ደረቅ እና ፍሳሽ ቆሻሻ በስፋት የሚለቁ የንግድ አካባቢዎች በየቀኑ ቆሻሻ ስለሚያስወግዱ አገልግሎት ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነው። ለምሳሌ እንደ አትክልት ተራ የእንጨት ቤቶች ይጠቀሳሉ። በሌላ በኩል የዚህ መሰሉ እንቅስቃሴ እምብዛም የማይስተዋልባቸው በሳምንት አንድ ጊዜም አገልግሎት የማይጠይቁ አሉ በተለይ በጣም የለሙ አካባቢዎች ሁለተኛው ዓይነት የአሰባሰብ ደረጃ ወይም ስታንዳርድ የገንዳ አጠቃቀም ነው። በአሁኑ ወቅት እንደ አቶ ታደለ ገለፃ የቆሻሻ ገንዳ ከመንገድ እንዲነሳ ተደርጎ አካባቢን ሊበክል በማይችልበት ቦታ እንዲቀመጥ ተደርጓል። አካባቢውም በትርፍራፊና በደንታቢስነት በሚጣል ቆሻሻ እንዳይበላሽ እንዲፀዳ ይደረጋል። ገንዳው በቆሻሻ ሲሞላም ክፍት ሆኖ አካባቢን እንዳይበክል ተሸፍኖ እንዲቀመጥ ይደረጋል። የሞሉ ገንዳዎችም በ24 ሰዓት ውስጥ እንዲነሱ ይደረጋል። እንዲያም ሆኖ ገንዳ ስለተቀመጠ የአካባቢ ፅዳት ሙሉ በሙሉ ይጠበቃል ማለት አይደለም። የህብረተሰቡ የቆሻሻ አወጋገድ ባህልም ይበልጥ የሰለጠነና ኃላፊነት የተሞላው መሆን ይኖርበታል። አንዳንድ በለሊት ሰው አየኝ አላየኝ በሚል በዘፈቀደ ቆሻሻ መጣል በማይገባው በተለይ የሚጥሉ ሲሆን ይህ ሁኔታም በተለይ በአመት በዓል ወቅት የከብቶችና በጎችን ሆድእቃና አላስፈላጊ ቆሻሻ በየቱቦው በመጣል የፍሳሽ ቦይ እስከመዘጋት እንዲደርስ የሚያደርጉ አሉ። ይህ እኩይ ተግባር የሚወገደው በአስተሳሰብ ለውጥ እንጂ በቁጥጥርና በቅጣት አይደለም። በሌላም በኩል በተለይ በገንዳዎች ዙሪ ቆሻሻዎች አላግባብ ተጥለው ከሆነ ህብረተሰቡ በሚሰጠው ጥቆማ ኤጀንሲው ችግሩ እንዲቃለል እንደሚያደርግ አቶ ታደለ አመልክተዋል። እንደ እርሳቸው ገለፃ የገንዳ ስርዓት ዘለቄታዊ መፍትሄ የሚያስገኝ አይደለም። ከከተማዋ እድገት ጋርም አብሮ የሚሄድ አይደለም። ቆሻሻው በኮምፓክት ማሽን እየተሰበሰበ የሚወገድበት ስርዓት መፈጠር ያለበት ሲሆን በተወሰነ መልኩም ጅምሩ አለ። ሶስተኛው የአወጋገድ ሰታንዳርድ የመንገድ ፅዳት ነው።

ለዚህ ስርዓት ከሶስት ሺህ በላይ ቅጥር ሰራተኞች አሉ። በየክፍለ ከተማው በተዋቀረው አካሄድ ለሁለት ኪሎ ሜትር መንገድ ፅዳት ሶስት ፈፃሚ አለ። እነኚህ ፈፃሚዎች በጠዋት ተነስተው የተሰጣቸውን ርቀት በየእለቱ በሚከናወን ስራ ይፈፅማሉ። እንዲያም ሆኖ ግን ከከተማው ህዝብ አኗኗር ዘይቤ መለወጥና ከፅዳት ፍላጎት መስፋት አንፃር በጠረጋው ሂደት አቧራ ማስነሳቱ ቅሬታን እያስነሳ ይገኛል። እንደ አቶ ታደለ ገለፃ ይህን ቅሬታ ለማስወገድ እንዲቻል በ2005 እና በ2006 አቧራ ሳያቦኑ አስፋልትን ማፅዳት የሚችሉ 10 ማሽኖች ከውጭ ሀገር እንዲገቡ ተደርገው ወደ ስራ እንዲሰማሩ ተደርገዋል። ማሽኖቹ ስራ ላይ የዋሉትም በደቡብ አፍሪካ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሲሆን የፅዳቱ ስራ በማሽን የሚከናወነውም ከለሊቱ 10 ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት ድረስ ብቻ ነው። ይህም የሆነው መንገደኞችን ሊነሳ ከሚችል አቧራ ለመታደግ ነው ሌላኛው ስታንደርድ ደግሞ የግል ድርጅቶች የአወጋገድ ስርዓት ነው። በዚህ ዘርፍ ላይ የፅዳት ድርጅቶች ተሠማርተው እየሰሩ ይገኛሉ። ደረቅ ቆሻሻን ከትላልቅ ድርጅቶች በማሰበሰብ ወደ መጣያ ስፍራ ይወስዳሉ። ቆሻሻው ከተነሳበት እስከሚወገድበት ድረስ በስርዓት እንዲጓጓዝ በኤጀንሲው በተሰጠ መመሪያ ይከናወናል። የተቋማቱ ቆሻሻን ገንዳ ላይ ሸፍነው እንዲያስቀምጡ ይደረጋል፡

     ሌላው ስታዳርድ የተሸከርካሪ ምልልስ ተብሎ ይታወቃል። የምልልሱ አሰራር ከክፍለ ከተማ ክፍለ ከተማ እንደየ አገልግሎት ፍላጎት መጠን ይለያያል። የቀን ምልልሱ ዝቅተኛው 3 ሲሆን ከፍተኛው 6 ነው። የሌሊት ምልልስም እንደየአስፈላጊነቱ የሚከናወን ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከፍተኛውን ምልልስ ወደ 15 ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። በሌላም በኩል አሁን ባለው የከተማችን ከፍተኛ የመንገድ ግንባታና የትራፊክ መጨናነቅ የተነሳ የቀን ምልልሱ የሚቀንስበት አጋጣሚ ያለ ሲሆን በአንዳንድ ቦታ5 የነበረው ወደ 3 ቀን ቀንሷል። በአሁኑ ወቅት የመኪኖች ምልልስን ይበልጥ ለማሳለጥ 30 ተጨማሪ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ መኪኖች ተገዝተው ወደሀገር እንዲገቡ ተደርገዋል። መጨረሻ ስታንዳርድ ደስትቢን ስታንዳርድ ወይም ቆሻሻ መጠን አነስተኛ ማጠራቀሚያ ሳጥኖችን በየመንገዱ ዳር በማስቀመጥ መንገደኛው ቆሻሻን በውስጣቸው እንዲጥል የማድረግ አካሄድ ነው። በተለይ በአንደኛ ደረጃ በሚጠሩ ዋናዋና መንገዶች ላይ የዚህ መሰሉ ስራ ይሰራል። በከተማችን ባለው የፍላጎት መጨመር ሳቢያም 2000 ማጠራቂሚያ ሳጥኖች በየቦታው እንዲቀመጡ ለማድረግ ግዥ ተፈፅሟል። እንደ አቶ ታደለ ገለፃ እነኚህ ቆሻሻ መጣያዎች አብዛኛ ህብረተሰብ ካለው ግንዛቤ ማነስና ባለው ቆሻሻን የማስወገድ ዝቅተኛ ባህል የተነሳ አይጠቀምባቸውም። ስለሆነም ህብረተሰቡ እንደልምድ ስራው ለሌሎች አካላት እንዲከናወን ጥረት እየተደረገ ይገኛል። የቆሻሻ መድፊያ ቦታን በተመለከተም ባለፉት 40 ዓመታት ከተማውን ሲያገለግል የነበረው ያረጀ መድፊያ ቦታ ስለሞላና መሀል ከተማ ስሆነ የከተማው አስተዳደር ከፍተኛ ወጭ በመመደብ ዘመናዊ /Land fill/ መጣያ ቦታ በሰንዳፋ እያስገነባ ይገኛል። ለዚህ እንዲያግዙ አራት የቅብብሎሽ ጣቢዎች በአቃቂ በቦሌ፣ በካራ በቡራዩ እና በራሱ በቆሼ እየተዘጋጀ ይገኛል። በአጠቃላይ ለከተማዋ እድገት የሚመጥን የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት እንዲጎለበት በከፍተኛ ደረጃ የመንግስት ከዚህ ሌላ በግል ተቋማትን በማህበራት እየተከናወነ ይገኛል። ይሁን እንጂ አካባቢን ማፅዳት ከህብረተሰቡ ባህል ጋር የሚገናኝ እንደመሆኑ በተወሰኑ ተቋማት ብቻ የሚከናወን ድርጊት ውጤቱ እምብዛም ነው። ህብረተሰቡ ለራሱና ለአካባቢው ጤና መጠበቅ የሚሰጠው ዋጋ ሊጎለበት ግድ ይላል። በአሁኑ ወቅት የተጎሳቆሉ አካባቢዎች መልሰው እንዲለሙ መደረጋቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግን ቦታው የፍሳሽና የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን የሚያግዝ መሆኑ የዚያኑ ያህል የፅዳት ባህሉን ያገለብታል ተብሎ ይጠበቃል። በመሆኑም ቆሻሻውን በጥንቃቄ ማስወገድ ለፅዳት ፍላጎት ምላሽ እንዲሆን ነዋሪዎች ሊገነዘቡት ግድ ይላል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1175 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 809 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us