የሜትሮሎጂ ትንበያው የበልጉ መደበኛ ዝናብን ቀጣይነት ያሳያል

Wednesday, 09 April 2014 12:07

በዝናብ ጥገኛ የሆነው የኋላቀር አስተራረስ ዘይቤ የሚጠቀመውና ለ85 በመቶው ህዝብ መተዳደሪያ የሆነው የእርሻው ዘርፍ እንዲሻሻልና ምርታማነት እንዲጨምር ለማድረግ ግብአትን ቴክኖሎጂንና አጋዥ መሣሪያዎችን ከመጠቀም በተጨማሪ የሜትሮሎጂ መረጃን መገልገል ወሳኝነት አለው። ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ የሜትሮሎጂ ትንበያዎችና መረጃዎች መሰራጨት የጀመሩ ቢሆንም አደጋዎችን ለመከላከልም ሆነ መልካም አጋጣሚዎችን ለእርሻው ከመጠቀም አንፃር የተገኘው ውጤት እዚህ ግባ የሚሰኝ አይደለም። ለተለዋዋጭ አየር ንብረት የተጋለጠው ግብርና ባለፉት 50 ዓመታት ከባባድ ፈተናዎችን እንዲሁም 3 ታላላቅ የረሀብና የዕልቂት ጊዜያትን አስተናግዷል። በእኛው አቆጣጠር በ1951 ዓ.ም በ1965 እንዲሁም በ1977 ዓ.ም የተከሰተው ድርቅ በተለይ በመጨረሻው የደረቅ ዘመን የ1 ሚሊዮን ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ የነፍስ አድን ዕርዳታ ባይለግስ ኖሮ ችግሩ ከዚህ የከፋ ሊሆን እንደሚችል የምናስታውሰው ነው። የእርሻው ዘርፍ ለድርቅ ተጋላጭነት በተለይ በዓለም የሙቀት መጨመር ታክሎበት ይበልጥ አሳሳቢ ነው። በምግብ ራስን የመቻሉ ጉዳይም ገና የረጅም ጊዜ ግብ እንደሆነ ነው ደርሽፒንል የተባለው ዋንኛው የጀርመን ጋዜጣ ከሰሞኑ እንደዘገበውም ኢትዮጵያ በዓለም እጅግ በረሃብ ከሚጠበሱ አራት ሀገሮች መካከል አንደኛዋ መሆንዋን አመልክቷል።

ከዚህ አንፃር በየትኛውም የዝናብ ወቅት የሚገኘውን ውሃ ለእርሻ ስራ መጠቀም ከተቻለም አቁሮ ለድርቅ ወቅት ማስቀመጥ ለአርሶ አደሩም ሆነ ለአርብቶ አደሩ አማራጭ የሌለው የአኗኗር ዘይቤ መሆን ይኖርበታል። ምክንያቱም ውሃን አስቀድሞ ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ አለማዋል የሚያስከፍለው ዋጋ ከባድ እንደሆነ የቅርብ ታሪኮችን ያመለከተው ጉዳይ ስለሆነ ነው። ስለዚህ የአየር ንብረት ፀባይንና ትንበያን የተመለከቱ መረጃዎችን መከታተልና በግብአትነት መጠቀም ራስን ከአደጋ ለመታደግ ይረዳል።

አቶ ዳዲሞስ ወንድይፍራው በብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ሜትሮሎጂስት ከሰሞኑም በመጭዎቹ ተከታታይ የበልግ ሳምንታት መደበኛው የዝናብ ስርጭት በመልካም ሁኔታ ተጠናክሮ የሚቀጥል በመሆኑ ለአርሶ አደሩ እንደመልካም አጋጣሚ ይሆናል ሲሉ አመልክተዋል። እንደ እርሳቸው ገለፃ ከየካቲት 1 ቀን ጀምሮ እስከ ግንቦት መጨረሻ ያለው ወቅት የበልግ ጊዜ ተብሎ ይታወቃል። በዚህ ወቅት ዝናብ የሚያገኙት የሀገራችን አካባቢዎች የደቡብ ምዕራብ የመካከለኛው ምስራቅ ሰሜን ምስራቅና ሌሎች ቦታዎች ናቸው። በተለይ ከየካቲት መጨረሻ መጋቢትንና ሚያዝያን የተሻለ የዝናብ ስርጭት ይኖራቸዋል። ቀስ በቀስም ወደ ሰሜን ምስራቅና ምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተስፋፋ ይሄዳል። ከዚህ በተጨማሪ ከመጋቢት አጋማሽ በህዋላ ወደ ደቡብ ምስራቅና ሶማሌ ክልል እየተስፋፋ ይሄዳል። ከመጋቢት መጨረሻ ጀምሮ የሀገሪቱ ቆላማ አካባቢዎች ዝናብ ማግኘት ይችላሉ። እንደሚታወቀው አብዛኛዎቹ ዝናብ የሚያገኙት የወይናደጋ አካባቢዎች ጥራጥሬ የሚያመርቱ እንደሆነ ይታወቃል። በተለይ በደቡብና በማዕከላዊ አካባቢዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ እንደመኖሩ በምግብ ራስን ለመቻልም ሆነ የከተሜውን ገበያ ለማረጋጋት አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል። ይሁን እንጂ ዝግጅቱ አስቀድሞ እንዲጠናቀቅ አርሶ አደርም ሆነ የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች መረጃውን በተገቢው ለመጠቀም ራሳቸውን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል።

በመጋቢት መጨረሻ ሳምንትና በሚያዝያ መጀመሪያ ሳምንታት የሜትሮሎጂ ክስተቶች በመጠንም ሆነ በስርጭት ረገድ ከመጠናከራቸው ጋር ተያይዞ በምስራቅ ትግራይ ምስራቅ አማራ፣ አብዛኛው ኦሮሚያና ደቡብ ብሔር ብሔረሰብና ህዝቦች ክልል ከመደበኛው ዝናብ ጋር የተቀራረበ ቢሆንም በጊዜ ስርጭት አኳያ ደረቅ ቀናት እንደሚኖሩ ይጠበቃል። በተጨማሪም ጋምቤላ ቤኒሻንጉል ግሙዝ ምዕራብ አማራ ምዕራብ ትግራይ አፋርና ምስራቅ ኢትዮጵያ ከመደበኛው ጋር የተቀራረበና በጥቂት ስፍራዎቻቸው ላይ እንዲሁም በሰሜን ምስራቅና በደቡብ ምስራቅ ዝቅተኛ አካባቢዎች ከመደበኛው ያነሰ ዝናብ ይኖራቸዋል። ይህም ለበልግ ማሳ ዝግጅት ለዘር ጊዜና ለእርሻ ስራ እንቅስቃሴ ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች ለሚገኙ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ለመጠጥ ውሃና ለግጦሽ ሣር አቅርቦት እንዲሁም ለቋሚ ሰብሎች የውሃ ፍላጐት መሟላት የጐላ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ሆኖም ግን በደረቅ ቀናት የሚያመዝንባቸውም ሆኑ ከመደበኛ ዝናብ በታች ዝናብ እንደሚያገኙ ከሚጠበቅባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮችና የሚመለከታቸው ክፍሎች የተገኘውን ርጥበት በአግባቡ በመያዝና በመጠቀም ሊደርስ ከሚችለው የርጥበት እጥረት ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የዕፅዋት መጠውለግና መድረቅ በጊዜው መቀነስ ይገባል።

የመጋቢት ወር የዝናብ መጠን ከየካቲት የተሻለና የበዛ ነው። የበልግ ዝናብ በቦታም ሆነ በመጠን በመደበኛው ሁኔታ እየተስፋፋና እየተጠናከረ የሚሄድበት ነው። በተለይም በበልግ አብቃይ አካባቢዎች እየጨመረ ይሄዳል። ለግብርና እንቅስቃሴውም ጠቀሜታው የላቀ ነው። ምስራቅ ትግራይ፣ አማራ፣ አብዛኛው ኦሮሚያ፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል፣ ጋምቤላ፣ ምዕራብ አማራ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ አብዛኛው አፋርና ሶማሌ ከ5 እስከ 40 ሚሊ ሜትር የዝናብ መጠን ያገኛሉ። የዝናብ መጠኑም እየጨመረ ይሄዳል።

የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ከሳተላይት ባገኘው መረጃ መሠረት አብዛኛዎቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች ዝናባማ መሆናቸውን ነው የሚያመለክተው። ትንበያው ምን እርግጠኛ ጊዜውን የጠበቀ ነው ተብለው የተጠየቁት ባለሙያው አቶ ዳዲሞስ ወንድይፍራም እንደተናገሩት፤ ትንበያው በመጀመሪያ የበልግ ወቅት ከመግባቱ በፊት የአራቱን ወራት ሜትሮሎጂያዊ መረጃ መስጠቱን ጠቅሰው በእነኚህ ወቅቶችም የደረቅ ጊዜያት እንደሚኖሩ በትንበያው መጠቀሱን አመልክተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ኤጀንሲው የ1 ቀን፣ የ3 ቀናት፣ የ10 ቀናት እንዲሁም የ30 ቀናት ትንበያ የሰጠ ሲሆን፤ ይህንንም በዌብ ሳይታቸው ላይ እንደጫኑት ጠቁመዋል። ከዚህ አንፃር ባለፉት ተከታታይ ቀናቶች የነበሩት ሁኔታዎች ሲገመገሙ በተለይ በደቡብ ደቡብ ምዕራብ የመካከለኛው ምስራቅና ደቡብ መስራቅ አካባቢዎች መጠኑ ይለያይ እንጂ ከፍተኛ የዝናብ ስርጭት አለ። ከዚህ ሌላ አጠቃላዩ ዝንባሌ እንደሚያሳየው ተለዋዋጭነትና የሚዋዥቅ ባህርይ ያለው ዝናብ የሚከሰትበት ነው። ከዚህ አንፃር በአንዳንድ አካባቢዎች ዝናብ ተከስቷል። ይህም ከትንበያው ጋር የተጣጣመ መሆኑን መረዳት እንደሚቻል ገልፀዋል።

በአንዳንድ ደረቅ አካባቢዎች ከተጠቀሰው በታች ዝናብ ማግኘታቸውንና መዝነብ ሲገባ ባልዘነበባቸው አካባቢዎችን በተመለከተ የተጠየቁት አቶ ዳዲሞስ ሲገልፁ፤ በደመናው መጠንና ይዘት እንደሆነ ጠቅሰው ለምሳሌም ባለፉት 10 ቀናቶች ውስጥ የነበረው የዝናብ ስርጭት ሲገመገም በአብዛኛው የበልግ ዝናብ በሚያገኙ አካባቢዎች መደበኛ ስርጭት አግኝተዋል። እ.ኤ.አ ከማርች 1 እስከ 10 የነበረው ሲታይም በደቡብ ደቡብ ምዕራብ የመካከለኛው የምስራቅና እንዲሁም ጥቂት የሰሜን ምስሪቅ አካባቢዎች ከመደበኛው ስርጭት ያነሰ ዝናብ እንደነበራቸው ለመረዳት ተችሏል። ይህ ሁኔታ በመጋቢት መጀመሪያ ሳምንታት የነበረው ስርጭት እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ዳዲሞስ ሲመለሱ፤ ትክክል እንደሆነ ጠቅሰው፤ ነገር ግን አማራ ክልል፣ ትግራይና ጋምቤላ፣ ኦሮሚያና ቤንሻንጉል መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በሌላም በኩል ደቡብና በሌሎች አካባቢዎች የድርቅ ሁኔታዎች እንደተስተዋሉ እንዲሁም የረሀብ አዝማሚያ እንዳለ የሚጠቁሙ መረጃዎች ስለሚሰሙ በዚህ ረገድ ምን አስተያየት እንዳላቸው የተጠየቁት ባለሙያው፤ ይህን በተመለከተ ስለድርቅና ረሃብ መኖር በርሳቸው በኩል የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ጠቅሰው፤ ነገር ግን ከዝናብ አንፃር በተጠቀሱት አካባቢዎች የበልግ ዝናብ ስርጭት አጀማመሩ መደበኛና መልካም እንደነበር ቆይቶም እንደተለዋወጠ ጠቅሰው፤ ነገር ግን እስከ ረሃብ የሚያደርስ እንዳልሆነ አመልክተዋል። ትንተናውን እንደማስጠንቀቂያ መውሰድ ይቻል እንደሆነም ተጠይቀው፤ ሲመለሱ በመጭዎቹ ቀናቶች ያለው ሁኔታ ሲታይ የበልግ ዝናብ አንፃሪዊ በሆነ መልኩ እንደሚቀንስ ይህም ማለት ከመደበኛው ስርጭት እንደሚቀንስ በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኙ አካባቢዎችም እንደሚቀንስ ይህ ግን ለተወሰነ ጊዜ ብቻ እሚቆይና ቀጥሎ መጠኑ እንደሚጨምር ገልፀው ለዚህም ምክንያቱ በደመናው ውስጥ ርጥበት አዘል አየር ስለሚኖር ዝናብ የሚከሰትበት ሁኔታ ይፈጠራል። የተሻለ የደመና መጠን የሚኖረውም በደቡብና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንደሆነ አቶ ዳዲሞስ ወንድይፍራው አስረድተዋል።

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው የአገራችን እርሻ በዝናብ ላይ ጥገኛ እንደመሆኑ የአየር ሁኔታ ተለዋውጦ የዝናብ ወቅት አስቀድሞ መጀመር ካለበት በፊት ሲመጣም ሆነ ወቅቱን አሳልፎ ሲመጣ ወይም ጭራሹን ሲቀር የተዘራው ሰብል በብዙ መልኩ ይጐዳል። አስቀድሞ ሲመጣ ለተባይን ለውርጭ መከሰት የበኩሉን አስተዋፅዎ ያደርጋል። ዘግይቶ ሲመጣም እንደዛው ነው። የዝናብ መጠኑም እጅግ ከበዛ በጐርፍ መጥለቅለቅ ውድመት ይከሰታል። በዚህ ወቅት በግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ የሚሆነው አርሶ ገደሩ እንዲሁም ከፊል አርብቶ አደሩ ነው። ከዚህ አንፃር የሜትሮሎጂ መረጃን መቀበልና ተቀብሎ ለእርሻው በግብአትነት ወሳኝነት አለው። ከዚህ ውጭ ድርቅ ተከስቶ እህል ከተቃጠለና ከወደመ ምርት አይኖርም። የእርሻ ምርታማነትም ይቀንሳል አርሶ አደሩና ሌላው የድርቅ ሰለባ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል የዕለት ደራሽ እርዳታ ካልደረሰለት ከቻለ ቀየውን ለቆ መሰደድ ካልሆነም ባለበት ለህይወት ቅጥፈት ይዳረጋል።

በአሁኑ ወቅት ዓለምንና ሀገራችንን እያስጨነቀና ለብዙ ኪሣራ እየዳረገን የሚገኘውን የአየር ሙቀት መጨመርንና የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት እንዲቻል ከእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ የመላመድ አካሄድን መተግበር አዋጭ ሆኖ መንግስት በፖሊሲው አካቶታል። ለዚህ እንዲረዳ በተለይ መሠረተ ልማቶች ማለትም መንገዶች፣ ሆስፒታሎችና ጤና ተቋማት እንዲሁም ትምህረት ቤቶች መስፋፋት በረሃብና በምግብ እጥረት ወቅት እርዳታን ወደተጐጂዎች ለማዳረስ በጣም አስፈላጊ ነው። እንደዚያም ሆኖ ግን 70 በመቶ የሚሆነው የሀገራችን ህዝብ ከዋና መንገዶች የ6 ሰዓት የእግር መንገድ ተጉዞ በሚገኝ ቦታ ላይ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር ጥናት ያመለክታል ይህም የእርዳታ አቅርቦቱን አስቸጋሪ ስለሚያደርገው የመሠረተ ልማት ዝርጋታው ሊጠናከር ግድ ይላል።

     አቶ ወዳዲሞስ በበልግ ወቅት እየተከሰተ ያለውን የዝናብ መዋቅ እንዴት እንደሚገመግሙት ተጠይቀው ሲናገሩ መዋዥቅ በበልግ ወቅት በአብዛኛው እንደሚከሰት ሆኖም ግን አሁን በዓለም ላይ ካለው የሜትሮሎጂ መረጃ ጋር ተካቶ ሲታይ የአሁኑ የበልግ ዝናብ ከበፊቶቹ ጋር የተቀራረበ በመሆኑ በመሀል ሊያጋጥሙ የሚቻሉ እጥረቶችን ኅብረተሰቡ በመገንዘብ የዝናቡን አጋጣሚ መጠቀም እነደሚኖርበት አሳስበዋል። አክለውም አካባቢዎቹ የበልግ ዝናብ አብቃይ እንደመሆናቸው ከመድረቃቸው በፊት የግብርና ስራ ማከናወን ይኖርባቸዋል። እንዲያም ሆኖ ግን ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ድርቅ አይጠበቅም። ነገር ግን ይህ ለበልግ ስራ እንዲያገለግል አርሶ አደሩና የግብርና ባለሙያዎች ውሃ በማቆር ለአርብቶ አደሩና ለከፊል አርብቶ አደሩ መረጃ በማስተላለፍ ሊታደጓቸው ግድ ይላል። ይህን መረጃም በአዲስ አበባም ሆነ ሌሎች ትላልቅ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ሊጠቀሙበት ይገባል። ሙቀት በሚሆንበት ጊዜ አለባበሳቸውን ማስተካከል ከዚያ በተጨማሪ ደረቅና ሞቃታማ አየር ጋር ተያይዘው ከሚመጡ በሽታዎች ማለትም ወባ መራባት ስለሚችል እንዲሁም ጉንፋንና የመሳሰሉት በሽታዎች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርበት አቶ ዳዲሞስ ወንድይፍራው አሳስበዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1167 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 907 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us