የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ችግኝ መትከል ብቻ አይደለም

Thursday, 03 October 2013 19:46

በአይቼው ደስአለኝ

የአካባቢ መራቆት መዘዝ ተቆጥሮ አያልቅም። አፈር በዝናብ እንዲታጠብ፣ እፅዋቶች በቂ ማዕድን ከአፈር እንዳያገኙ፣ የጐርፍ መጥለቅለቅ እንዲከሰት ግድቦች በአፈር እንዲሞሉ፣ የዝናብ መጠን እንዲቀንስ፣ ድርቅና በረሃማነት እንዲስፋፋ አካባቢ እንዲበከል፣ የእርሻ ምርታማነት እንዲቀንስ፣ አላስፈላጊ ገደሎች እንዲፈጠሩ ወዘተ ያደርጋል። በዚህ የተነሳም በቅድሚያ እፅዋትን ለምግብነት የሚጠቀሙ ሰውና እንስሳት ለአደጋ ይጋለጣሉ። በርሃብና በእልቂትም ይዳረጋሉ። እንደ ሳይንቲስቶች አገላለፅ ተፈጥሮ የሰው ልጅን እንክብካቤ ትፈልጋለች። በተቃራኒው የሰው ልጅ ለተፈጥሮ የሚሰጣትን እንክብካቤ ከነፈገ ተፈጥሮ የሰው ልጅን ትበቀላለች። ከአካባቢው ተፈናቅሎ እንዲሰደድና እግሬ አውጭኝ እንዲል ታደርገዋለች። በሀገራችን የዚህ መሰሉ የተፈጥሮ አደጋ በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈፀሙ የሰው ልጅ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል። ከዚህ አኳያ ተፈጥሮንና አካባቢን መንከባከብ ህይወት ቀጣይነት እንድታገኝ የሚያደርግ ዋስትና መሆኑን ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባል።

ዶ/ር ሀብተማርያም አባተ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ተመራማሪ ሲሆኑ ከሰላሳ ዓመታት በላይ በተፈጥሮ እንክብካቤና በግብርና ተመራማሪነት ሰርተዋል። እንደ እርሳቸው ገለፃ የተፈጥሮ ጥበቃ ችግኝ በመትከል ብቻ የሚወሰን ስራ አይደለም። ተያያዥና ዘርፈ ብዙ ስራዎችን የሚጠይቅ ነው። ክረምት በገባና ዝናብ መጣ በሚል ብቻ በይድረስ ይድረስ የሚሰራ አይደለም። ቅድመ ዝግጅት ያስፈልገዋል። በበጋ ወቅቶች ማለትም በጥር፣ በየካቲትና በመጋቢት ወራቶች መትከያ ቦታዎች ሊዘጋጁ ግድ ይላል። በተራራዎች ላይም የእርከን ስራዎች በበጋ ተከናውነው መጠናቀቀ ይኖርባቸዋል። ከዚህ በኋላም ክረምት ሲገባ በባለሙያ በመታገዝ ስነ ህይወታዊ ያልሆነው ስራ በስነህይወታዊ ማለትም በችግኝ ተከላ በመደገፍ መከናወን ይገባዋል። እንደ ሙያተኛው ገለፃ ቀደም ባለው ዘመን ስራው በግብርና ሚኒስቴር በአፈር ጥበቃ ክፍል አማካኝነት ይሰራ ነበር። ነገር ግን የዚህ መሰሉ በተወሰነ ተቋም የሚሰራ ስራ የተፈለገውን ፋይዳ አላስገኘም። ስለሆነም ካለፉት 15 ዓመታት ወዲህ በህብረተሰቡ ተሳትፎ እየተከናወነ የተሻለ ውጤት ሊገኝ ችሏል። እንዲያም ሆኖ ግን የችግኝ ተከላ ስራ ከአካባቢ ጥበቃ ስራ ከ5 እስከ 10 በመቶ የሚሆነው ብቻ እንደሆነ ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባል። ከተተከለ በኋላም እንደ ልጅ ተንከባክቦ ማፅደቅና ማሳደግን ይጠይቃል። ከዚህ አኳያ ቅርብ ጊዜ ተሞክሮዎች ይህንን እውነት ያመላክታሉ። በሚሊንየም መባቻ ወቅት የችግኝ ተከላ ስራ በዘመቻ መልክ ተከናውኖ እንደነበር አይዘነጋም። በአሁኑ ወቅት ይህ ሁኔታ በሙያተኞች ሲገመገም ሙሉ በሙሉ ተሳክቷል ማለት አይቻልም። በከፊል ሲፀድቅ ከፊሉ ለውጤት አልበቃም። ይህ ሊሆን የቻለውም ችግኝ ተካዩ ሙሉ ጊዜን በዚያ ስራ ማሳለፍ ባለመቻሉ እንዲሁም ተከላው በተከለለ ቦታ ባለመከናውኑ በከብቶች ሊረጋገጥና ሊጋጥም በመቻሉ ነው። ከዚህ አኳያ ለችግሩ ምን ዓይነት መፍትሄ ማምጣት ይቻላል ተብለው የተጠየቁት ዶ/ር ሀብተማርያም ሲመልሱ በሀገራችን ያለውን የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ከባድ እንዲሆን የሚያደርገው የህብረተሰቡ የእንስሳት አያያዝ ሁኔታ ነው። ከብቶች ለግጦሽ የሚሰማሩት በዘፈቀደና በልቅ ሁኔታ ነው። በተገኘው ቦታ መሰማራታቸው በተፈጥሮ እንክብካቤ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ አለው በሀገራችን የመሬት ባለቤትነት የሚታወቀው ከክረምት እስከ መኸር ማለትም እስከታህሳስ ነው። ሰብሉ ከታጨደ በኋላ መሬቱ ባለቤት ስለማይኖረው ማንም ከብቱን ያሰማራበታል። ይህ ደግሞ በማሳው ያለው እፅዋት በእንስሳት ተግጦ አፈሩ በንፋስ ጭምር እንዲወሰድ ያደርጋል። እንደ ሙያተኛው ገለፃ በውጭ ሀገር ለእርሻም ሆነ ለሌላ ስራ የሚውል መሬት ባለቤት አለው ይከለላል። ጥበቃም ይደረግለታል። ከብቶች በአካባቢያቸው ብቻ እንጂ በሌላ ቦታ ተለቀው መሬት እንዲያራቁቱ አይደረግም። ስለሆነም በሀገራችን ያለው የልቅ ግጦሽ ስርዓት እንደገና መፈተሽ ይኖርበታል። ባለፉት ረጅም ዘመናት የተካሄደው የችግኝ ተከላ ስራ በልቅ ከብቶች ስምሪት ሳቢያም ብዙ ተፅእኖ ሊያርፍበት ችሏል። በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩ ከማሳ ውጭ የሚገኙትን በተራራ ወገብና ግርጌ ላይ የእርከን ስራ መስራቱ አፈር እንዳይሸረሸር ትልቅ ሚና በመጫወቱ ውሃ በጐርፍ መልክ ወደታች ሳይወርድ ወደ መሬት እንዲሰርግ ያደርጋል። ይህም የአፈር እርጥበት ሚዛናዊ በሆነ መልኩ እንዲጠበቅ አድርጓል። ተራሮችም ቢሆኑ ከብት እንዳይለቀቅባቸው እየተደረገ ያለው ሙከራ ሊበረታታ ይገባል።

በአሁኑ ወቅት በተለይ በገጠር ለአካባቢ ጥበቃ ስራ የሚያግዝ ሁኔታ እየተፈጠረ ይገኛል። ይኸውም መሬት አልባ ወጣቶች በማህበር እየተደራጁ መሬት እየተሰጣቸው አካባቢን መንከባከብ ጀምረዋል። ለዚህ እንዲያግዝም የብድር አቅርቦት ማግኘታቸው ለስራቸው መቃና የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል። ለዚህ ሁኔታ በምሳሌነት የሚጠቀስ አካባቢም አለ። እርሱም በወላይታ ዞን በሁምቦ ወረዳ የተከናወነው የአካባቢ ጥበቃ ስራ ነው። ቀደም ሲል ቦታው እጅግ የተራቆተ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን በተደራጁ ወጣቶች ለሞት በርካታ ጥቅሞችን እያስገኘ ነው። መሬቱ ውሃ የማዘል አቅሙ ጐልብቷል። ከተራራው ላይ የለመለመው ሳር እየታጨደ ለከብቶች መኖ ይውላል። ከዚህ አልፎ አካባቢው በCDM ተመዝግቦ የካርቦን ክሬዲት ገንዘብ በማስገኘት ከአካባቢው አልፎ ለሀገርም ጥቅም መስጠት ችሏል። ይህም የተራቆተ አካባቢን እንድያገግምና እንደገና ተስፋ እንዲሰጥ ማድረግ እንደሚል አመላካች ነው።

የአካባቢ መራቆትና የአፈር መሸርሸር ጥንታዊ ስልጣኔዎች ጭምር እንዲወድቁ ያደረገ ነው። ጥንታዊ ከተሞች በአብዛኛው ከተራራ ስር እንዲሁም ውሃ በአቅራቢያቸው የሚገኝባቸው ናቸው ተፈጥሮ ስትዛነፍም ለተደራረበ መከራ ሲጋለጡ ቆይተዋል። ታሪክ እንደሚያስተምረን የሰው ልጅ በእርሻ ስራ ተሰማርቶ የነበረው ከ11ሺህ ዓመታት በፊት በጥንታዊቷ ሜሶፓታሚያ ወይም በዛሬዋ ኢራቅ አካባቢ ነበር። እነኚህ እርሻዎች ሊጠፉ የቻሉት በአፈር መሸርሸርና በአካባቢ መራቆት ነው። በደቡብ አውሮፓ የሚገኘው የአናቶሊያ ሀይላንድ ስልጣኔም ሊጠፋ የቻለው ከመራቆት የተነሳ ነው። ቦታው የሜድትራሊያን ክላይሜት የነበረው ነው። አሁን ግን የለም በግሪክ የአቴንስና ለፖርት ስልጣኔ ሊወድቅ የቻለውም አካባቢው በተገቢው ስላልተጠበቀ ነው። በደቡብ አሜካ የኤክስኬስ ስልጣኔ ሊወድቅ የቻለው በዚሁ ሳቢያ ነው። በቻይና ያየለው ወንዝ አካባቢ እንዲሁም በሂማሊያ ተራራ ትይዩ የሆኑ አካባቢዎች የቀድሞ ገናናነታቸውን ያጡት በአፈር መሸርሸር ሳቢያ ነው። በአሁኑ ወቅት እንደገና የመልሶ ማገገሚያ ስራ በመሰራቱ አካባቢው ተፈጥሮአዊ ውበቱን መመለስ መቻሉን ዶ/ር ሀብተማርያም ይገልፃሉ።

ይህ ሁኔታም በሀገራችን በተመሳሳይ የተከሰተ ጉዳይ ነው እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በዓለም በቀደምትነት የመንግስትነት ታሪክ ካላቸው ጥቂት ሀገሮች ውስጥ አንዷ ናት። ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረውን የገናናው የአክሱም ስልጣኔም ለዚህ አብነት የሚሆን ነው የአክሱም ስልጣኔ ከአካባቢው አልፎ ቀይባህርን የህንድ ውቅያኖስንና የዐረቢያን ፔንሱላ ይዞ የንግድ መረቡ እስከ ህንድ የተዘረጋ ነበር። ለስልጣኔው ውድቀት ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ ምክንያቶች ነበሩት ውጫዊው ምክንያት በአካባቢው ከተነሱት ማለት ከፋርስ ስልጣኔ ጋር ወታደራዊ ፍጥጫ ውስጥ መግባቱ ሲሆን ከውስጣዊ ምክንያቶች ውስጥ የአካባቢ መራቆት በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው በአክሱም የተከሰተው የአካባቢ መራቆት የእርሻ ስራው እንዲከናወንና ምርት እጥረት እንዲፈጠር አድርጓል። ይህም ለወታደሮች የሚሆን ቀለብ እንዲቀንስ አድርጓል። ይህ ሲሆንም ባህር ተሻግሮ የሚጓዘው የንግድ ስርዓት ሊስተጓጐል ቻለ። በዚህም ሳቢያ ፖለቲካዊ ስርዓቱ ተዳክሞ በዮዲት ጉዲት ውድመት ደርሶበት ስልጣኔው ወደ ደቡብ ማለትም ወደላስታ እንዲያፈገፍግ ተገዷል። ስለሆነም የአካባቢ መራቆት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ህብረተሰቡ ጠበቅ ያለ ግንዛቤ እንዲያገኝ መደረግ ይኖርበታል። ተጽዕኖው በቅፅበት የሚከሰት አይደለም በሂደትና በአዝጋሚ ሂደት ነው። መሬት ራሱ ለተከታታይ አመታት ሲዘራበት እንደመጀመሪያው ወቅት ፍሬያማ አይሆንም። ምርታማነቱ ይቀንሳል። ይህ እንዲስተካከልም ገበሬው በባህላዊው ዘዴ ተጠቅሞ ማረሱን በመቀነስ መሬቱ እንዲያገግም ያደርጋል። የስሜን ኢትዮጵያ መሬት አሁን አሁን በአካባቢ እንክብካቤ ማገገም ቢስተዋልበትም ምርታማነቱ ገና የሚቀረው ነው። ይህም ለዘመናት በነበሩት መንግስታዊ ስርዓቶች ውስጥ እርሻ ዋነኛ የገቢ ማስገኛ ምንጭ ሆኖ በማገልገሉና አላግባብ በመታረሱ እንደሆነ የሚዘነጋ አይደለም።

እንደ ዶ/ር ሀብተማርያም ገለጻ አካባቢ እንዳይራቆት ለደን ለእርሻና ለግጦሽ የሚሆነው ተለይቶ እንክብካቤ ሊደረግለት ግድ ይላል። በተለይ ተራራማው አካባቢ ለደን ተለይቶ መያዝ ሲኖርበት ወገቡ ለከብቶች ግጦሽ መተው አለበት። ታችኛው ለእርሻ ሲሆን የሚጐዳ መሬት አይኖርም የማገዶ እንጨት ቢያስፈልግ ወደ ተራራ ይወጣል ሳር ከተፈለገም ወደ ወገቡ ይኬዳል። ደኖቹ የዝናብ ውሃ ጐርፍ ሆኖ ታችኛውን መሬት እንዳያጥለቀልቅና አፈሩን እንዳያጥብ ያደርጋሉ። ይህ ሁኔታም በግጦሽ መሬቱም ይሁን በእርሻ መሬት ላይ የሚገኘው አፈር እርጥበት ስለሚያገኝ በበጋም ሆነ በክረምት አዝርዕት ዘርቶ ማፍራት ያስችላል ይሁን እንጂ አንዳንድ ሙያተኞች በበኩላቸው ከዶ/ሩ ለየት ያለ ዕይታ አላቸው። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ተራራማ ሀገር ናት። አንዳንዱ በተለይ ምንም ለእርሻ የማያመቸው አካባቢ የዳገት መጠን /Slope/ በጣም ቀጥ ያለ ነው ይህ ሁኔታ በራሱ ለአፈር መሸርሸር አስተዋፅኦ ስለሚያደርግ በየዓመቱ በቢሊዮን ቶን የሚገመት ለም አፈር በጐርፍና በጅረቶች ታጥቦ ከሀገር ይወጣል። የዚህ መሰሉን ተፈጥሮአዊ ክስተት እንዴት መመከት ይቻላል ተብለው የተጠየቁት ዶ/ር ሀብተማርያም ሲመልሱ በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚገኙትን ተራሮች በምሳሌነት በመጥቀስ ተራሮች እንዳይራቆቱ ማድረግ እንደተቻለ ይገልፃሉ። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ከፍተኛ አካባቢዎች በታላቁ የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ለሁለት የተከፈሉ ናቸው። አንደኛው በስተምስራቅ ሲሆን ሌላኛው በስተምዕራብ የሚገኘው የሰሜን ኢትዮጵያ ተራሮች ነው እንደ ዶ/ር ገለፃ ጨርጨር ከፍተኛ መሬት በደን የተሸፈነ ነው። አርሶ አደሩም የአካባቢ መራቆት የሚያስከትለውን ተፅእኖ ከተሞክሮው በመረዳት ከብቶቹን ወደ ተራሮች አያሰማራም። በመኖሪያው አካባቢ ጥጆችንም ሆነ ላሞችን አስሮ ያረባል። በውስን ቦታ ላይ ከብት እያረባ ለማዕከላዊው ገበያም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ከብት ያቀርባል። ይህን ሲያደርግም አካባቢ አይራቆትም ከብቶቹ ከቦታ ወደ ቦታ ስለማይንቀሳቀሱ በአካባቢ ላይ ጉዳት አያደርሱም። ባሉበት ቦታ ሆነው ይደልባሉ። ከቦታ ወደ ቦታ ስለማይንቀሳቀሱም ሀይላቸውን አይጨርሱም በዚህም የተነሳ ይሰባሉ። ስጋቸውም ከፍተኛ ተፈላጊነት አለው ይህ ሁኔታ አካባቢ እንዳይራቆትም ሆነ አፈር እንዳይሸረሸር ያደርጋል። በተቃራኒው በሰሜን ተራሮች ያለው አርሶ አድር ከብቶችን ከቦታ ቦታ በማዘዋወር በተራሮችም ጭምር ለግጦሽ ስለሚያሰማራ በተፈጥሮ ላይ መራቆትን ያስከትላል። ከብቶችም ቢሆኑ የሚመገቡት ምግብ በጉዞ ለሚጨርሱት ሀይል መተኪያ ስለሚያውሉት ድካማቸው ሁሉ ለፍቶ መና ነው። ስለሆነም በተራራው አካባቢ ተፈጥሮ አጠባበቅን በተመለከተ በሌላ የኢትዮጵያ የአካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች የጨርጨር ገበሬዎችን ተሞክሮ ሊወስዱ ይገባል።

Last modified on Thursday, 03 October 2013 19:58
ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
2363 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 926 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us