የአባይ ግድብ አሞላልና የውሃ አጠቃቀም አንድምታው

Wednesday, 23 April 2014 11:49

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ ከፈለገች የተፈጥሮ ሀብቶቿን መጠቀም የግድ ይላታል። ከሀብቶቿ መካከልም የገፅና የከርሰ ምድር ውሃዎች የሚጠቀሱ ናቸው። ይህን እውን ለማድረግ በቂ የገንዘብ የቴክኖሎጂ የሰው ሃይልና የኢንተርፕረነረሺፕ ክህሎት ይጠይቃል። የእነኚ ሁኔታዎች አለመሟላት ሀገሪቱ ሀብቶችዋን እንዳትጠቀም አድርጎ ቆይቷል። ካለፉት 10 ዓመታት ወዲህ ግን በተለይ የገ ምድር ውሃን ለሃይል ማመንጫነት ለመጠቀም ብዙ ጥረት ተደርጓል። ከዚህ የሚገኘው ታዳሽ የሆነው ሃይል አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት እያደገ የሚሄደው ኢኮኖሚን ለመደገፍ ወደጎረቤት ሀገሮች በመላክ የውጭ ምንዛሪን ለማግኘትና የንግድ ትስስርን ለማጎልበት ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል።

ከዚህ አኳያ ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ 640 ኪሎ ሜትር ላይ የሚያገኘውና እየተገነባ ያለው የህዳሴ ግድብ በሀገር ውስጥ ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ ያገኘ ሊሆን ከጎረቤት በተለይም ከታችኛው ተፋሰስ ሀገር ከግብፅ በኩል እየተነሳ ያለው ቅሬታና ንትርክ ገና በአግባቡ አልተፈታም። ሁኔታው ነገ ምን ይዞ ይመጣል የሚለውም እንቆቅልሽ ገና አልታወቀም።

እ.ኤ.አ በታህሳስ 2011 ሳሊኒ ከሚባለው የኢጣሊያ ተቋራጭ ኩባንያ ጋር በተደረገው ውል መሰረት ግንባታው እስካሁን 1/3ኛው እንደተጠናቀቀ ተገልጿል። ከ5 ዓመታት በኋላም በ2018 ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። እንደ ውጥኑ ግድቡ ከተጠናቀቀ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ትልቁ የሃይድሮ ኤሌትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ይሆናል። ከ60 እስከ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንደሚይዝ የተነገረለት ግድብ 6ሺህ ሜጋዋት አቅም ያለው የኤሌትሪክ ሃይል እንደሚያመነጭ ይገመታል። የሚፈጀው ወጭም በመንግስት ስሌት 44 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን እንደ አንዳንድ ባለሙያዎች ግምት ደግሞ የኤሌትሪክ መስመር ግንባታውን ጨምሮ የፕሮጀክቱን ወጭ ከ6 እስከ 7 ቢሊዮን ዶላር ያደርሱታል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት በአሜሪካ የዮስኮን ዩኒቨርስቲ የስነ ውሃ ተመራማሪው ፕሬፌሰር ፓውል ጄብሌክ እንደሚገልጹት የውሃ ማከማቻው ግድብ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሚይዝ ቢሆንም ውሃው የሚያርፍበትን ሪዘርቪየር እንዴት ይሞላዋል የሚለው ጉዳይ መታየት ያለበት ዋና አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። በአካባቢው ያለው የአየር ፀባይ ከአመት አመት ተለዋዋጭ መሆኑ በውሃው ላይ አሉታዊም ሆነ አወንታዊ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ ይችላል። ይህም ኢትዮጵያ በምታመነጨው የኤሌትሪክ ሃይል ላይ እንዲሁም ወደ ታችኞቹ ተፋሰስ ሀገሮች በሚደርሰው የውሃ መጠን ላይ የራሱ ተፅዕኖ ይኖዋል። የግድቦች ስጋት ተደጋግሞ እንደሚሰማው የግድቡ ግንባታ የውሃውን ፍሳሽ መጠን ይቀንሰብናል የሚል ሲሆን የኢትዮጵያ ባለስልጣኖች ደግሞ በበኩላቸው የግድቡ ዓላማ የኤሌትሪክ ሃይል ለማመንጨት ብቻ በመሆኑና የግድቡ ውሃ የሃይል ማመንጫውን ካንቀሳቀሰ በኋላ ተመልሶ ወደ ውሃው ተፈጥሮአዊው መውረጃ ስለሚለቀቅ በፍሰቱ መጠን ላይ ይህ ነው የሚባል ተፅዕኖ አያሳርፍም በሚል ይከራከራሉ። ይሁን እንጂ ግብፆች ይህን የመሰለ ግዙፍ ግድብ እስኪሞላ ድረስ ባሉት አመታቶች ውስጥ ሊፈጠር ስለሚችለው የውሃ መጠን ማነስ ስጋት አላቸው።

ሆኖም በኢትዮጵያ መንግስት መግለጫዎች መሰረት የሪዘርቭየሩ አሞላል በየአመቱ አነስተኛ የውሃ መጠን ብቻ ወደ ግድቡ በማስገባት የሚከናወን ነው። ነገር ግን ጠቀም ያለ ውሃ በመያዝ በአጭር ጊዜ ለመሙላት ቢያስፈልግ እንኳን የግብፅ የአስዋን ግድብ የሀገሪቱን አጠቃላይ የውሃ ፍጆታ ለ3 ዓመታት መሸፈን የሚቻል የመጠባበቂያ ውሃ ስላለው ይኸንኑ እስከዚያው በአማራጭ መጠቀም እንደሚችሉ የኢትዮጵያ ባለስልጣኖች ይገልፃሉ።

በሌላም በኩል የውሃ ባለሙያው ፕሮፌሰር ፓውል ጀብሊክ በዚህ ጉዳይ ላይ ሌላ አስታራቂ ሀሳብ አላቸው። ይህውም አለም አቀፍ የሆነው የሙሌት ፖሊሲ ነው ሲሉ ይገልፃሉ። በዋናነትም ሁኔታው በተለመደው የሙሌት ደንብና በሚቀጥሉት ጥቂት አመታት በሚኖረው ግዙፍ ፍሰት ላይ የተመረኮዘ ይሆናል። እናም በመጀመሪያ ደረጃ የሙሌት ደንቡን በተመለከተ በመሰረተ ሀሳቡ ላይ ኢትዮጵያ ሱዳንና ግብፅ ከአንድ ስምምነት መድረስ አለባቸው። ሊተገበር የሚችል የሙሌት ደንብ መንደፍ ይኖርባቸዋል። ፕሮፌሰር ፓውል እንደሚሉት የሙሌት ደንቡ ሁለት መልክ አለው። አንደኛው በየወሩ ወይም በየአመቱ በጣም አነስተኛ የውሃ መጠን ወደ ግድቡ እንዲገባ በማድረግ በረጅም ጊዜ ግድቡ እስኪሞላ መጠበቅ ሲሆን፤ ይህ ግን ባለ በሌለ አቅሟ ግድቡን እያስገነባች ላለቸው ኢትዮጵያ አዋጭ አይመስልም። ከፍተኛ የውሃ መጠን የሚይዘውን ግድብ በአጭር ጊዜ ለመሙላት ቢሞከር ደግሞ የታችኛዎቹን የተፋሰስ ሀገሮች ስለሚጎዳ የሙሌት ደንቡ ላያስማማ ስለሚችል ሊያቀራርቡ የሚችሉ አማራጮችን በመፈለግ ግድ እንደሚሆን ፕሮፌሰር ፓውል ጀብሉ ይገልፃሉ። በሌላም በኩል ኢትዮጵያ በየዓመቱ የውሃውን 5 በመቶ ብቻ የሚሆን መጠን ወደ ግድቡ ብታስገባ (መቸም የሚሆን አይደለም) በዚህ መልኩ ግድቡ በጭራሽ ሊሞላ አይችልም። የትነት መጠኑም ስለሚኖር የሙሌት ሂደት የኤሊ ጉዞ ይሆናል። በዚህ አካሄድ ምናልባት የተወሰነ ኤሌትሪክ ኃይል ሊመነጭ ይችላል። ሆኖም ፈፅሞ የተለመደውንና የተጠበቀውን ያህል አይሆንም። ነገር ግን ወደሱዳንና ግብፅ የሚፈሰው የውሃ መጠን ትርጉም ባለው ሁኔታ አይጎዳም።

በዚህ ጉዳይ ሌላም አማራጭ ይኖራል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውሃውን 20 በመቶ ብታስቀር ግድቡ በጥቂት አመታት ውስጥ በተቻለ ፍጥነት ሊሞላ ይችላል የሚፈልገውን የኤሌትሪክ ሃይልና ከሽያጭ የምትጠብቀውን ጥቅም ልታገኝ ትችላለች። ነገር ግን በታችኛዎቹ የተፋሰሱ ሀገሮች ላይ ከባድ ተፅዕኖ እንደሚያስከትል ግልፅ ነው። ስለሆነም ይላሉ ፕሮፌሰር ፓውል ሌሎች የሙሌት አማራጮችን መመልከት አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ከአማካይ የውሃ ፍሰት በላይ የሚሆነውን ውሃ ብቻ ብታስቀር ይህም የሚሆነው የወንዙን ታሪካዊ የፍሳሸ መውረድ መጠንን በማወቅ ሲሆን የወንዙ የወር የፍሰት አማካኝ መጠን ግን አይታወቅም። ይሁንና የወሩን አማካይ መጠን በማስላት አውጥቶ ከዚያ በላይ የሚሆነውን ወደ ግድቡ ማስገባት ይቻላል። የውሃው መጠን ከዚህ አማካይ መጠን በታች ሆኖ በተገኘ ጊዜ ደግሞ ሁሉም ለታችኛዎቹ የተፋሰሱ ሀገራት ይለቀቃል ማለት ነው። በዚህ ስሌት መሰረትና በውሃው ሙሌት ደንብ መሰረት የታችኛዎቹ የተፋሰሱ ሀገሮች ከወትሮው በተለየ መልኩ አይጎዱም።

ምክንያቱም በደረቅ ወቅቶች ሁሉንም ውሃ ስለሚያገኙ ነው። በዝናባማ ወራት ቢሆንም አማካኝ የውሃ መጠን ይገኛሉ። የዚህ ዓይነቱ የሙሌት ደንብም ቢሆን ኢትዮጵያን ሊጎዳ የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖረው እንደሚችል የጠቆሙት ፕሮፎሰሩ ምክንያቱ ደግሞ የአየር ፀባይ በአመታት ውስጥ ተለዋዋጭ መሆኑ ኢትዮጵያ በዝናብ አጥር ወቅት አጠቃላይ ውሃውን እንዳለ ወደታችኛው ተፋሰስ ሀገራት እንድትለቅ ሊያስገድዳት ይችላል ይላሉ። የሆነው ሆኖ የሙሌት ፎርሙላን በተመለከተ የተለያዩ አማራጮች እንዳሉ የጠቀሱት ፕሮፌሰር ፓውል ወሳኙ ጉዳይ ሶስቱ ሀገሮች በዚህ ጉዳይ ላይ መነጋገርና መስማማት መቻላቸው መሆኑን ይመክራሉ።

ባለፈው ወር የኢትዮጵያ የግብፅና የሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች ካርቱም ላይ ተገናኝተው የአንድ የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ ለማቋቋም መስማማታቸው የሚታወስ ነው። በኮሚቴው አሰራር ላይ ግን ግብፅና ኢትዮጵያ መለያየታቸው አይዘነጋም። ሌላው ተዛማጅ ጥያቄ ከላይ እንደተጠቀሰው የግድቡን ወጭ በኢትዮጵያ አቅም ብቻ መሸፈን ይቻላል ወይ የሚለው ሲሆን እስካሁን ባለው ሁኔታ ለዚህ ፕሮጀክት ብድር ገንዘብ የማግኘት እድሉ የመነመነ ቢሆንም ባለፈው ጥቅምት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መንግስታቸው ታላቁን የህዳሴ ግድብ ከግብፅና ከሱዳን ጋር በሽርክና ለመገንባት ፍላጎት እንዳለው ገልፀው እንደነበር ይታወሳል። ይህንኑ መግለጫ ተከትሎም የግብፅ ባለስልጣኖች እየተለሳለሱ መምጣታቸው ይሰማል።

እናም ይህ ከሆነ ተንታኞች እንደሚሉት ለኢትዮጵያ ይህን ከፍተኛ የግንባታ ወጭ ለመሸፈን ከማገዝም በላይ ሀገሪቱ ከምታመነጨው የኤሌትሪክ ሃይል በቅናሽ ዋጋ እንዲገዙ ያስችላቸዋል። ከሁሉም በላይ የወንዙን ውሃ በጋራ እያለሙ በጋራ እንዲጠቀሙ እድል ይፈጥርላቸዋል ተብሎ ይታመናል። በተለይም ኢትዮጵያና ግብፅ ይህን ካደረጉ ፕሮፌሰር ፓውል ጀብሎክ እንደሚሉት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትም ፕሮጀክቱን ሊደግፉ ይችላሉ።

“በመሰረቱ ዝርዝሩን አላውቅም የሆነው ሆኖ በእኔ ትንተና ግብፅ ለግድቡ ወጭ ብትጋራና ኢትዮጵያም በዚህ ብትስማማ መቀናቀኑ ቀርቶ የሽርክና ማህበርተኞች ይሆናሉ። በእኔ እምነት ይህ ቀና አካሄድ ነው ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ፕሮፌሰር ፓውል ይገልፃሉ። እንደ እርሳቸው ግንዛቤ ግብፅ ጠቀም ያለ የአክስዮን ድርሻ ገዝታ ሁለገብ ተጠቃሚ ስትሆን ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ስኬታማ ትሆናለች የግድቡን ግንባታም ሆነ ስለሙሌቱ የታችኛዎቹ ተፋሰስ ሀገሮች እጣ ፈንታም እንዲሁ በጋራ ስለሚወሰኑ ሀገሮቹ ልዩነታቸው ከማስወገድ አልፈው የጋራ ተጠቃሚ ይሆናሉ ማለት ነው። እንዲያውም ይላሉ ፕሮፌሰር ፓውል የግብፅና የሱዳን የሃይል ማመንጫ ግድብ በየዓመቱ ከፍተኛ የውሃ መጠን በትነት መልክ ስለሚያባክኑ የህዳሴ ግድብ ደግሞ የትነት መጠኑ ካለው የጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ የተነሳ በጣም አነስተኛ ስለሚሆን ሁኔታው የታችኛዎቹን ተፋሰስ ሀገሮች ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ አያደርጋቸውም።

ስለሆነም ሶስቱ ሀገሮች ከተስማሙ በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ በኢትዮጵያ ሰሜን ምዕራብ በሚገኙ ከፍተኛ ቦታዎች ተጨማሪ ግድቦችን በጋራ እያስገነቡና እያስተዳደሩ ይበልጥ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ። ይህም በክረምት ከፍተኛ የውሃ መጠን ኢትዮጵያ ውስጥ በመያዝ በበጋ በታችኛዎቹ ተፋሰስ ሀገራት የናይል ወንዝ ሃይሉ በሚመናመንበትና በሚቀንስበት ቀውት ተጨማሪ ውሃ ወደ ግብፅና ሱዳን በርሃዎች እንዲዘልቅ ማድረግ እንደሚቻል የዊንስኮን ዩኒቨርስቲው የውሃ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ፓውል ዲቭሎክ ይገልፃሉ።

    ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ የዘለቄታዊ ጥቅሟን ከግምት በማስገባት የተለያዩ ሙያተኞች በተለይ ውሃ እንዴትና በምን መጠን ወደ ማጠራቀሚያው ገብቶ የሃይል ማመንጫውን ያንቀሳቅሳል በሚለው ጉዳይ የሚሰጡትን አስተያየት ዋጋ ልትሰጠው ግድ ይላል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1316 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 913 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us