በከተማችን የታዳሽና ቆጣቢ ኢነርጂ አጠቃቀም ዕድገት

Wednesday, 30 April 2014 13:27

በሀገራችን ከ94 በመቶ በላይ የሚሆን የኃይል ፍላጎት በባዮማስ ወይም ከደንና እፅዋት ቅጠላ ቅጠሎች እንደሚሸፈን ሙያተኞች ይገልፃሉ። ይህም ለደን መጨፍጨፍ ለአካባቢ መራቆትና ለአፈር መሸርሸር የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል። የኢነርጂው አጠቃቀምም ባላዊና አባካኝ መሆኑ የተጠቃሚዎች ፍላጎት ፈጣን እንዲሆን በማድረግ የደን ጭፍጨፋው የዚያኑ ያህል እንዲፋጠን ምክንያት ነው። ከዚህ ባሻገር ማገዶውን ለመልቀም የሚወስደው ጊዜ በጣም ረጅም በመሆኑ በተለይ በገጠር ሴት ልጆች ከትምህርታቸው ተፈናቅለው ከማጀት ህይወት አዙሪት እንዳይወጡ ያደርጋቸዋል። ሳይማሩና ሳይሰለጥኑ ወደትዳር ህይወት ሲገቡም የባል ጥገኛ በመሆን አስቸጋሪ ህይወት ለመኖር የሚገደዱ ሲሆን የሚወልዷቸውም ልጆችም ወደ ተሻለ ህይወት የማምራት ዕድላቸው እጅግ በጣም የጠበበ ይሆናል። የማገዶ እንጨት ጢስም በጤና ላይ የሚያስከትለው ጫና ከፍተኛ ሲሆን ለሕፃናት በለጋ ዕድሜ መቀጨትም የራሱ የሆነ ድርሻ አለው።

ከዚህ አንፃር የደን ውድመትን በመከላከልና የአካባቢ ብክነትን በመቀነስ ጤናው የተጠበቀ ህብረተሰብ ለመፍጠር የሀገር ሀብትም በቁጠባ ለመጠቀም የተሻሻሉ ቆጣቢ ምድጃዎችን ስራ ላይ ማዋል እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የታዳሽ ኢነርጂ ቨርዥን አስተባባሪ አቶ መስከረም አበበ ይገልፃሉ።

ዛፎችና እፅዋቶች በተፈጥሮአቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ይሰጣሉ። የተፈጥሮ ሚዛን እንዳይዛነፍ የዝናብ ውሃ በስራቸው አማካኝነት ወደ መሬት እንዲሰርግ ያደርጋሉ በዚህም ምክንያት የከርሰ ምድር ውሃ እንዲጠራቀም ምንጮችና ወንዞች በቂ ውሃ እንዲኖራቸው ያደርጋል። በመሬት ላይ እፅዋቶች በተለያዩ ምክንያት ሲጎዱና ሲወድሙ የዝናብ ውሃ ወደ መሬት መስረጉ ቀርቶ ወደ ጎርፍነት ይለወጣል። ይህም በሰው በእንስሳት በንብረትና በምርት ላይ ከፍተኛ አደጋ እንዲደርስ ያደርጋል። የእፅዋትና የእንስሳት ተመጋቢነት እንዲሁም የፀሐይ አስፈላጊነት እዚህ ላይ ሊጠቀስ ግድ ይላል እፅዋቶች በፀሐይ ብርሃን አማካኝነት በፎቶሲንተሲስ ስርዓት ምግባቸውን ሲያዘጋጁ ከውስጣቸው የሚያስወግዱት ንጥረ ነገር ኦክስጅን ነው። ይህ ንጥረ ነገርም የሰውም ሆነ የእንስሳት እስትንፋስ እንዳይቋረጥ የሚያደርግ ብርቅዬ ሀብት ነው። በአንፃሩ ሰዎች እና እንስሳት ኦክስጅንን ለህልውናቸው ማቆያ ተጠቅመው ወደ ውጭ የሚያስወግዱት ካርቦንዳይኦክሳይድ የተባለው ንጥረ ነገር ሲሆን ይህም ለእፅዋት ህልውና እጅግ አስፈላጊ ነው። ከዚህ አኳያ እፅዋቶችና ዛፎች ሲቆረጡና ሲወድሙ በተፈጥሮ እና በሰው ልጆች መካከል ያለው ጤናማ ግንኙነት እየተጎዳ ይሄዳል። በከባቢ አየር ውስጥ የኦክስጅን መጠን ሲቀንስና የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን ሲጨምር የአየር መዛባትና የሙቀት መጨመር ይከሰታል። ይህ ደግሞ በተቃራኒው በሰው በእንስሳትና በእፅዋት ላይ ጭምር አሉታዊ ተፅእኖ ያሳርፋል። የሚገርመው ግን ለዚህ ሁሉ ጥፋት ቁጥር አንድ ተጠያቂ የሰውልጅ መሆኑ ነው። ምክንያቱም ማናቸውም የተፈጥሮ ውድመቶች የሚከሰቱት በርሱ ነውና።

እንደ አቶ መስከረም ገለፃ አንድ ያደገ ዛፍ በአማካይ በአመት 48 ፓውንድ ካርበን ዳይኦክሳይድ መጥጦ የሚያስቀር ሲሆን በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥም ለሁለት ሰው የሚያስፈልግ ኦክስጅን ወደ ከባቢ አየር ይለቃል። ከዚህ አንፃር ባልተገባ መንገድ ዛፍ መቁረጥ ማለት ለአካባቢ ብክለት እንዲስፋፋ ማድረግ ነው። በሀገራችን የህዝብ ቁጥር አመታዊ እድገት 3 በመቶ ነው። የህዝብ መጨመርም የማገዶ ፍላጎት መጨመርን እንደሚጠቁም መረዳት አያዳግትም። አሁን ባለው ሁኔታ የኢነርጂ አጠቃቀሙ በቀድሞው መልኩ ማለትም በባዮማስ መሆኑ ከቀጠለ ከድህነትም ሆነ ከረሀብ አዙሪት የመላቀቃችን ጉዳይ የሩቅ ጊዜ ህልም መሆኑ ይቀጥላል። የደኑ መመንጠርም የአፈር መከላትን ስለሚያስከትል የእርሻ ምርታማነትም እየቀነሰ ይሄዳል። ይህም የችግሩ አንዱ ገፅታ ይሆናል። ስለሆነም ይህን በብዙ መልኩ ተያያዥ ሆነን ተጽኖ ለመግታት በተለይም በከተማችን የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂን በማምረትና በማሰራጨት በማለማመድ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።

በሀገራችን ካለፉት መንግስታት ጀምሮ በማገዶ ምክንያት የሚቆረጠውን ደን ለማስቀረት ጥረት ይደረግ እንደነበር አንዳንድ ጥናቶች ያመለክታሉ። በዚህ ረገድ በ1970ዎቹ የቤት ውስጥ የማገዶ ፍላጎትን ለማሟላትና ደን ምንጠራን ለማስቀረት በሚል በከተሞች ኬሮሲን በቤት ውስጥ ምግብ ማብሰያነት ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል። ይሁን እንጂ ይህ መፍትሄ አልሸሹም ዞር አሉ ዓይነት ነገር ነበር። ምክንያቱም ዛፍ መቁረጥን በተወሰነ መልኩ ቢቀርፍም ከውጭ ስለሚገዛ የውጭ ምንዛሪን መጠየቁ እንዲሁም አካባቢን በመበከልና ለጤና ጠንቅ መሆኑ አሉታዊ ጎኑ እንዲያመዝን አድርጎል። ከዚህ ጎን ለጎን ድንጋይ ከሰልና ናፍጣን የሚጠቀሙ ፋብሪካዎችና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት የኃይል ምንጫቸውን ወደ ኤሌትሪክ እንዲቀይሩ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል። በሌላም በኩል በዛን ወቅት የማገዶ ፍላጎትን ለማርካት በሚል በኢደስ አበባና በሌሎች ትላልቅ ከተሞች ዳርቻ የማገዶ ዛፍን የመትከል መርሀግብር ተዘርግቶ የተተገበረ ሲሆን ይህን ፕሮጀክትም የዓለም ባንክና የአፍሪካ ልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፍ ይደረግለት እንደነበር የፎረም ፎር ኢንቫይሮንሜንት ጥናታዊ ፅሁፍ ያመለክታል። ከላይ እንደተጠቀሰው የኬሮሲንንም ሆነ ለማገዶ የተተከሉ ዛፎችን ቆርጦ ለገበያ ማቅረብ ጊዜያዊ የችግር ማስታገሻነት ካልሆነ በስተቀር በአካባቢ ጥበቃ ላይ ያስከትል የነበረውን አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያስቀር አልነበረም። በሂደትም አዳዲስ አስተሳሰቦችን የተሻሻሉ አሰራሮች እየተስፋፋ ሲመጡ ኃይል ቆጣቢ ምድጃዎችን ታዳሽ ኢነርጂ እንደ አማራጭ እየታዩ መጥተዋል።

በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በሚገኙ ከተሞች 20 በመቶ የሚሆነው ሰው ለቤት ውስጥ ምግብ ማብሰያነት የሚጠቀመው የኃይል ምንጭ የማገዶ እንጨትና ከሰልን ሲሆን አጠቃቀሙም ባህላዊና አባካኝ ነው። ከእንጨት የሚወጣው ጭስም ከፍተኛ በመሆኑ በታፈነ ማዕድ ቤት ውስጥ ስራው መከናወኑ በጤና ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት እያስከተለ ይገኛል። ከጭሱ የሚለቀቁት በካይ ንጥረ ነገሮች በዋንኛነት ካርበንሞኖክሳይድ ናይትሮጂን፣ ኦክሳይድ ሃይድሮካርቦን ሲሆኑ እንደ አለም የጤና ድርጅት ገለፃም ንጥረ ነገሮቹ የመተንፈሻ አካላት በሽታን በማስፋፋት ትልቅ ድርሻ አላቸው።

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ በካይ ካልሆኑትና በአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የኢነርጂ ቨርዥን አማካኝነት ለህዝብ እየተዋወቀና ምርቱ እየተስፋፋ የሚገኘው የባዮጋዝ ኢነርጂ ነው። አዘገጃጀቱም ከበሰበሰ ከሰውና ከእንስሳት እዳሪ የሚገኙ ባክቴሪያዎች በማብላላት ሲሆን የሚገኘው ጋዝም እንዲጠራቀም ተደርጎ በማስተላለፊያ ቱቦ አማካኝነት ለተጠቀሚው እንዲደርስ ይደረጋል። ስራውም የተወሳሰበ ስላልሆነ በገጠርም ሆነ በከተማ በቀላሉ ሊስፋፋ የሚችል ነው። ይህን መሰሉ የኢነርጂ አመራረት በአንድ ጠጠር ሁለት ወፍ እንዲሉ የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ችግርን ከማቃለል ባለፈ በካይ ያልሆነ ኢነርጂ ጥቅም ላይ ለመዋል የሚያስችል ነው።

በከተማችን እየተገነቡ የሚገኙትን ነባር የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሆቴሎች ማረሚያ ቤቶች ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ያሏቸው የመፀዳጃ ቤቶች አሰራራቸው ለባዮጋዝ የተመቹ ቢሆንም እየሰጡ ያሉት ጥቅም ግን እጅግ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አሁኑ ወቅት ይህ ሁኔታ እንዲቀየር የከተማው የአካባቢ ባለስልጣን በየዓመቱ ለሶስት ትምህርት ቤቶች የባዮጋዝ ማምረቻን በማቋቋም ለመምህራን ክበቦች የኃይል ምንጭ ለማቅረብ አስችሏል። ከዚህ ጎን ለጎን ቴክኖሎጂውን ወደ ህብረተሰቡ ለማድረስ በአነስተኛና ጥቃቅን ለተደራጁ አንቀሳቃሾች የተግባር ስልጠና ለመስጠት መታቀዱን አቶ መስከረም አበበ ይገልጻሉ።

በብስባሽ ቆሻሻዎች የሚመረተው ባዮጋዝ ለቤት ውስጥ ምግብ ማብሰያ እንዲሁም ለመብራት አገልግሎት ከፍተኛ ጠቀሜታን ያስገኛል። ጋዙ ጥቅም ላይ ሲውል የሚፈጠረው የእሳት ነበልባል በእቃዎች ላይ ምንም አይነት ጥላሸት ወይም የመልክ መቀየር አይፈጥርም። ማዕድ ቤቱንም ከሽታና ከመሰል ብክለቶች ነፃ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎችም ባዮጋዝን ከጀኔረተር በማገናኘት ለወፍጮ ኃይል ምንጭነትና ለመብራት አመንጪነት ያገለግላል። የባዮጋዝ ጥቅም በዚህ ብቻ አያበቃም ከምድጃው የሚወጣው ዝቃጭ ለተፈጥሮ ማዳበሪያነት ያገለግላል። ዝቃጩን አድርቆ በማሸግ ለማዳበሪያነት ገበያ ላይ በማቅረብ የገቢ ምንጭ ማስገኘት ይቻላል። ይህ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በፋብሪካ እንደሚመረተው ማዳበሪያ በአፈር ላይ አሉታዊ ተፅእኖ አያስከትልም።

የባለስልጣን መስሪያቤቱ በከተማችን ታዳሽ ኃይልን የሚያስፋፋው ከባዮጋዝ በተጨማሪ ከፀሐይ ኃይል ኢነርጂን ለመጠቀም የሚያስችል ኢነርጂን ጥቅም ላይ በማዋል ነው። ይህ ቴክኖሎጂ ለምግብ ማብሰያና ለውሃ ማሞቂያ ከማገልገሉ በተጨማሪ የኤሌትሪክ ኃይል ሲቋረጥ ኃይል ተክቶ ማገልገል የሚችል ነው። ብርኮት ተብሎ የሚጠራው በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የምግብ ማብሰያ አስፈላጊው ለምግብ ማዘጋጃ የሚሆን ግብዓት መሳሪያ ውስጥ በመክተት በፀሐይ ኃይል አማካኝነት በውስን ደቂቃዎች ውስጥ ምግቡን ያበስላል። ሙቀቱ ብዙ የማያስቸግርና የማይከብድ ሲሆን ምግቡም ለጭስ የተጋለጠ አይደለም።

ምግብ ማብሰያው ከወዳደቁ ብረቶች የሚሰራ በመሆኑ ማንም ሰው በቀላሉና ምንም ወጭ ሳያወጣ በቀላሉ ሊያመርተው የሚችል ነው። ይሁን እንጂ ሀገራችን ካላት እምቅና ተትረፈረፈ የፀሐይ ኃይል ምንጭ አኳያ ከታየ ምንጩ ገና ምንም ጥቅም ላይ አልዋለም ማለት ይቻላል።

በአሁኑ ወቅት አንዳንድ የግል ድርጅቶ የተለያዩ መሳሪያዎችን ከውጭ ሀገር በማስመጣት በገጠር በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የመብራት አገልግሎትና የምግብ ማዘጋጃ መሳሪያ እያቀረቡ የሚገኙ ሲሆን ይህም አካባቢን ከውድመት እየታደገ ሲሆን በተጨማሪም ሰዎች በጪስ ተጨናብሰው ለበሽታ እንዳይጋለጡ በማድረግ ላይ ይገኛል። ይሁን እንጂ ከ85 በመቶ የሚሆነው የገጠር ሕዝብ ላላት ሀገራችን አቅርቦቱ በጣም ኢምንት በመሆኑ ወደፊት ይበልጥ ሊሰራበት ግድ ይላል። ነገር ግን አንዳንድ የውጭ ኩባንያዎች መሳሪያውን ወደሀገር የማስገባቱ ሂደት ካለው ቢሮክራሲያዊ ተቀላልፎና አዙሪት እንዲሁም ከፍተኛ ቀረጥ በስራው እንዲበረታቱ እንዳላደረጋቸው ባገኙት አጋጣሚ እሮሮአቸውን ሲያሰሙ ይስተዋላል። በመሆኑም መንግስት አካባቢን እጠብቃለሁ የውሃ ሃብቱንም በስፋት እጠቀማለሁ ካለ በገጠር ባዮማስ ኢነርጂ እንዲቀንስ ባለሀብቱን ሊያበረታታ ግድ ይላል። ይህ ሁኔታ በትኩረት ሊሰራበት ግድ ይላል።

     በከተማችን የአሌትሪክ ኃይል በበቂ ሁኔታ መኖሩ የፀሐይ ኃይል እንደ አንገብጋቢ ላይታይ ይችላል። ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የከተማችን አካባቢዎች የሚገኙ የመንገድ መብራቶች በፀሐይ ኃይል እንዲሰሩ በመብራት ኃይል ኮርፖሬሽን እየተደረገ ያለው ጥረት ሊበረታታ ይገባዋል። ምክንያቱም ፀሐይም እንደልብ ስላለ የኤሌትሪክ ኃይልን መቆጠብ ስለሚያስችል ነው። ከዚህ በተጨማሪ በሆነው ባልሆነው የሚፈጠረውን የከተማ የኤሌትሪክ መቆራረጥ ይህን ተከትሎ የሚፈጠረውን የህዝብ ብሶትን ለመቅረፍ መልካም አጋጣሚ ስለሚፈጥር ቢታሰብበት መልካም ነው።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
1234 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1017 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us