የመሬት ቅርምት ዓለም አቀፍ መነጋገሪያ ነው

Wednesday, 07 May 2014 13:50

በአሁኑ ወቅት ዓለማችንን የሙቀት መጨመርና የአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ እየጎዳት ነው። ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ አይጥልም ከጣለም ውድመትን ያስከትላል። በዝናብ እጦት የተነሳ የከርሰምድር ውሃ እጥረት እየተከሰተ ኃይቆችና ወንዞች እየደረቁ ይገኛሉ። በዚህ ሳቢያ የእርሻ ምርት እያሽቆለቆለ በመሄዱ ሀገሮች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እጅግ እያዳገታቸው ይገኛሉ። በዚህም ሳቢያ የተሻለ ቴክኖሎጂና ገንዘብ ያላቸው እንደቻይና፣ ህንድና አንዳንድ የገልፍ ሀገሮች ኩባንያዎች ፊታቸውን ወደ አፍሪካ በማዞር ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን በመከራየት እንደ ሩዝ፣ ስንዴና መሰል ሰብሎችን አምርተው ወደ ሀገራቸው በመውሰድ የሀገራቸውን የምግብ ፍላጎት በማሟላት እየተጠቀሙበት ነው። ይህም መሬት ሰጭ ሀሮችን በአንድ በኩል በቀረጥ ገቢ በማስገኘት ሲጠቅም በሌላ በኩል ዜጎችን ከመሬት በማፈናቅል በኢንቫይሮሜንት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳረፍ አሉታዊ ተፅዕኖ በማድረሱ እያወዛገበ ይገኛል።

አንዳንድ ወገኖች በመሬት አከራይ አፍሪካ ሀገሮች የህግ የበላይነትና ዲሞክራሲ ካልሰፈነ አሰራሩ ግልፅነት ስለሚጎድለው በመሬት ኪራይ የሚገኘው ገቢ ጭራሹኑ የት እንደሚገባ ደብዛው እንደሚጠፋና መንግስታዊ ኤሊቶችን ኪስ ያዳብራል ይላሉ። ነገር ግን ተጠያቂነት አሰራር በሰፈነበት ሁኔታ የመሬት ኪራይ አወንታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ለልማትም ያግዛል ሲሉ ይደመጣሉ።

ከሰሞኑም በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ በዋደሮው ዊልሰን ማዕከል በምሁራን መሬት ቅርምትን የተመለከተ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል። ከጥናት አቅራቢዎቹ መካልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላምና የፀጥታ ማዕከል መምህር የሆኑት አቶ ፋና ገብረሰንበት፣ በዊደሮው ዊልሰን ማዕከል የደቡብና ደቡብ ምስራቅ ኢሲያ ፕሮግራም ከፍተኛ ባሙያ ሚስተር ማይክል ጉልደማን እንዲሁም በዊልሰን ማዕከል የአፍሪካ ጉዳይ ዳይሬክተር ሚስተር ሙንቲ መዋንጋይ ይገኙበታል።

እንደ ማይክል ጎልድማን ገለፃ በኢስያ የመሬት ቅርምቱን ወይም የመሬት ኪራይ አሰራርን በስፋት ከሚያካሂዱት ውስጥ ካምቦዲያ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ላኦስና ፊሊፒንስ ይገኙበታል። በእነኚህ ሀገሮች ውስጥ ለመሬት ተቀራማቾች በእያንዳንዱ ሀገር የአንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማከራየት ከስምምነት ተደርሶ ውል ተፈፅሞ ወደ ስራ ተገብቷል። በአፍሪካ ውስጥም ተመሳሳይ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ሚስተር ጎልድማን ይጠቅሳሉ። ይሁን እንጂ እንባለሙያው ገለፃ የመሬት ቅርምት የተባለለትን ውጤት ለአከራዮቹ አላስገኘም። በብዙ ሀገሮች የገበሬዎች የመፈናቀል አጋጣሚዎች በርካታ ሲሆኑ ብዙ መሬቶችም በኪራይ ተይዘው አካባቢዎች ከተመነጠሩ በኋላ ኩባንያዎቹ ወደ ምርት ሂደት አይገቡም። ለምሳሌ ያህልም ካምፒዲያ የጠቀሱት በላስተር ጎልቲማን ተቀራማቾቹ ገበሬዎች ለእርሻና ለግጦሽ ይጠቀሙባቸው የነበሩትን ወስደው በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን መሬት አልባ አደርገዋል። ይህም የተደረገው ያለ አንዳች ካሳ ክፍያ መሆኑም ድሆች ከድህነት ማጥ ውስጥ እንዳይወጡ እንደሚያደርግ ሙያተኛው አስረድተዋል። በተመሳሳይ የዚህ መሰሉ ችግር በአፍሪካ እንደሚስተዋል ሚስተር ጎልድማን ይጠቅሳሉ።

በአፍሪካ ውስጥ የመሬትና የውሃ ቅርምት ገበሬዎችን ከማፈናቀል አልፎ ወደ ጎሳና ፖለቲካ ግጭት ውስጥ ዘፍቋቸዋል። ለአብነትም የዳርፉር ግጭትን መጥቀስ ይቻላል። የአካባቢው ፖለቲካዊ ጡዘት በተቃዋሚዎችና በመንግስት መካከል የፖለቲካ አለመግባባት እንደመነሻ ቢሆንም ችግሩ መልኩን ቀይሮ አንዱ ጎሳ የሌላውን ጎሳ መሬት በኃይል ወደመንጠቅ ያመራል። አስቀድሞ የውሃና የሀብት እጥረት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በመፈጠሩ እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ ባንኪሙን ጭምር ማመልከታቸውን ሙያተኛው አስታውሰዋል።

በአፍሪካ በመሬት ቅርምቱ ሳቢያ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በተለይ እንደሳዑዲ አረቢያ ባሉ ሀገሮች መምጣቱ እንዲሁም ኤክስፐርትና ሰራተኞች መግባታቸው በአካባቢው ነዋሪዎች ቅሬታን እያሳደረ ይገኛል። የዚህ መሰሉ ቅሬታ በኢስያ የሚስተዋል ሲሆን በተለይ በኤንዶኔዥያ የሚስተዋለው የጎሳ ግጭትና የመገንጠል ንቅናቄ የቅርሞቱ መዘዝ እንደሆነ የዊደሮው ዊልሶን ተመራማሪው ይገልፃሉ።

እንደ ተመራማሪው ገለፃ የአፍሪካና የኢስያ የመሬት መዋዕለ ንዋይ ፍሰት በዓይነትና በመጠን ልዩነት አለው። በኢሲያ መዋዕለ ነዋይ አፍስሾቹ እዚያው የሚገኙ ኢሲያውያን ሲሆኑ ወደ አፍሪካ መዋዕለ ነዋይ የሚፈሱት ግን ከኢስያ ከአሜሪካ ከአውሮፓ፣ ከመካከለኛው ምስራቅና ከደቡብ ኢስያ የመጡ ባለሀብቶች ናቸው። በላቲን አሜሪካና በካሪቢያን ሀገሮች የመሬት ቅርምቱ እጅግ ከፍተኛ ሲሆን እስካሁንም ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጋ መሬት ለባለሀብቶች መሰጠቱን ሚስተር ጎልድማን ይገልፃሉ። በላቲን አሜሪካ ልክ እንደ አፍሪካ መሬት ነጠቃና ወረራ እንዲሁም ማፈናቀል የሚስተዋል ሲሆን በተለይ በኮሎምቢያ ችግሩ እንደሚከፋ ተናግረዋል። የመሬት ስሪትና አያይዝ እንዲሁም የኪራይ ሁኔታ በላቲን አሜሪካ ያለው ሁኔታ ከአፍሪካ ለየት ያለ ነው። በላቲን አሜሪካ በመጀመሪያ መሬቶቹ በትላልቅ ኩባንያዎች ይያዛሉ። ከዚያም ኩባንያዎቹ ለሌሎች ባለሀብቶች ከፍተኛ መጠን ባለው የኪራይ ውል ለሌሎች መሬት ገዥዎች ያከራያሉ። በሌላ በኩል የላቲን አሜሪካ ከኢስያ ጋር የሚመሳሰልበት ሁኔታ ቢኖር ኢንቨስተሮቹ የአካባቢው ሰዎች መሆናቸው ነው። እንደሚስተር ጎልድማንየላቲን አሜሪካ የመፈናቀል ሁኔታ ማህበራዊ ጫናን የማስከተሉ ጉዳይ እንደሌሎቹ ሀገሮች የከፋ አይደለም። በሌላም በኩል በቀድሞ የሶቭየት ህብረት አባል ሀገሮች የሚታየው የመሬት ሽሚያ እንዲሁም የቻይና ኩባንያዎች ወደ እነዚህ ሀገሮች መዋዕለ ነዋይ ለማፍሰስ እያሳዩት ያለው ፍላጎት በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ጠቅሰው ይሁን እንጂ የመሬት የማግኘትና የመያዝ ጉዳይ ድብቅ መሆኑ በሀገሬው ሰዎች ዘንድ ቅሬታን እየፈጠረ እንደሆነ አልሸሸጉም። ይህም ፖለቲካዊ ዋጋ እንደሚያስከፍል ተናግረዋል።

የመሬት ቅርምት መዘዝ ፖለቲካዊ ውጥረትን ከማባባስ አልፎ የመንግስታትን እድሜ ሲያሳጥር ተስተውሏል። ለዚህ አብነት የሚሆነውም በ2004 በማደጋስካር የተከሰተው ሁኔታ ነው። እንደሚስተር ጎልድማን በተጠቀሰው አመት የደቡብ ኮሪያው ግዙፉ ኩባንያ ዴኡ ከማዳጋስካር መንግስት ጋር ሰፊ ክልል የሚሸፍን መሬት በኪራይ ለመያዝ ውል በመግባቱ የተነሳ ፖለቲካዊ አምባጓሮን አስከትሎ፣ አመፅን ቀስቅሶ ለበርካቶች ህይወት መጥፋት ምክንያት ከሆነ በኋላ መንግስትን ከስልጣን ለማሰናበት አብቅቷል። ኩባንያው ከመንግስት ጋር የገባው ውል በአዲስ መንገድ የተሰረዘ ሲሆን ኩባንያውም በአሁኑ ወቅት በሀገሬው ህዝብ እንደጭራቅ ለመታየት በቅቷል። ከዚያን ወቅት በፓላሞ ዴኡ ከዚህ መሰሉ ቅሌት እጄን አላስገባም ብሎ ራሱን አግልሏል። የርሱንም ፈለግ በርካታ ኩባንያዎች እንደተከተሉት ሚስተረ ጎልድማን ተናግረዋል። እንደ እርሳቸው ገለፃ በቢዝነስ ውስጥ ዝናን የመሰለ ሀብት እንደሌለ ይህም የመርህና የተጠያቂነት ጉዳይ ነው። በመሆኑም የመሬት ቅርምት ጉዳይ ሊያስከትል የሚችልውን ዳፋ ከግምት ማስገባት ይበጃል ሲሉ መክረዋል።

የኢትዮጵያን ሁኔታ በተመለከተ ሙያተኛው ሲያብራሩ ለመሬት ቅርምት በርካታ ኩባንያዎች ወደዚህች ሀገር በመምጣት ከመንግስት ጋር እንደሚፈራረሙ ጠቅሰው አልፎ አልፎም መንግስታቱ ባለሀብቶችን አንፈልግም በማለት እስከ ማባረር ይደርሳሉ ብለው የዚህ መሰሉ አዝማሚያም በኢትዮጵያ መስተዋሉን አልሸሸጉም። በርግጥ መንግስታት እንዳለ መሬት ተቃራማቾችን አንፈልግም አይሉም። ነገር ግን የገባችሁትን ግዴታ ግን እንፈትሻለን፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ውሉን እናቋርጣን እያሉ ነው። ይህን መሰሉ ሁኔታም በኢትዮጵያ ጋንቤላ ተከስቷል። ካራቱሬ ከተባለው የህንድ ኩባንያ ጋር የተገባው እሰጥ አገባ ለዚህ ተጠቃሽ ነው። ካራቱሬ በገባው ውል መሰረት ለመንግስት ገቢ ማድረግ የነበረበት ገንዘብ ገቢ ባለማድረጉ እንዲሁም በተጠቀሰው የጊዜ ሰሌዳ ወደ ስራ አለመግባቱ ንትርክ ውስጥ የገባ ሲሆን እንደሚስተር ጎልድማን ገለፃም ካራቱሪ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የገባውን ውል ሳያቋርጥ እንዳልቀረ ጭምጭምታ ይሰማል። በተመሳሳይ በዚህ መሰሉ ሁኔታ እምብዛም ጥቅም የማያስገኙ ኩባንያዎች በተለያዩ ሀገሮች ውላቸው ተሰርዞ ከሀገር እንዲባረሩ ተደርገው በትርፋማነታቸው በሚታወቁ ኩባንያዎች መተካታቸውን ሚስተር ጎልድማን አስታውቀዋል። አትራፊ ኩባንያዎች ለግብርና ዘርፍ ማደግና ለማህበራዊ አገልግሎት መስፋፋት አስተዋፅኦቸው ከፍተኛ ነው ሲሉ ሙያተኛው አክለው ገልፀዋል።

የዊዶሮው ዊልሰን ጥናት ማዕከል ተመራማሪው ሚስተር ማይክል ጎልድማን የሰጡትን አስተያየት በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጡ የተጠየቁት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲውን መምህር አቶ ፋና ገብረሰንበት ሲናገሩም በኢትዮጵያ መንግስትና በካራቱሬ ኩባንያ መካከል እ.ኤ.አ በ2009 እና 2010 በይፋ ውል ከተደረገ በኋላ ለኩባንያው የ300 ሺህ ሄክታር መሬት ለመስጠት እቅድ ተይዞ ነበር። ነገር ግን ይህን የሰሙ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ወገኖች እንዲሁም የመብት ተሟጋቾች የተቃውሞ ድምፅ በማሰማታቸው የመሬቱ መጠን ከ2/3ኛ እንዲያንስ እንደተደረገ በአሁኑ ወቅትም በኩባንያው የተያዘው መሬት 100ሺህ ሄክታር ብቻ እንደሆነ አቶ ፋና አስረድተዋል።

     አያይዘውም ውሉ ሲፈፀም ከተሰጠው 100ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ግማሽ የሚያህለውን ሲያለማ ብቻ ቀሪው ሄክታር መሬት እንደሚለቀቅለት የሚል ሃሳብ በውሉ ውስጥ እንዲካተት መደረጉን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ካራቱሬ በአሁኑ ወቅት ከ5ሺህ እስከ 6ሺህ ሄክታር መሬት ብቻ እንደያዘ አቶ ፋና ጠቅሰው አሁን እንደሚሰማውም ኩባንያው በእርሻው የፈለገውን ያህል ውጤት ስላላገኙ ትራክተሮችንና ከሞባይነሮችን በሀገር ውስጥ ለሚገኙ አነስተኛ መዋዕለ ነዋይ አፍሳሾች እንዳከራየ ተናግረዋል። እንደአቶ ፋና ገለፃ ካራቱሬ በሚያደርገው አካሄድ መንግስት ደስተኛ አይደለም ብለው ካራቱሬና መንግስት ጋንቤላ ውስጥ ኩባንያው በሚያደርገው እንቅስቃሴ ግንኙነታቸው ክፉኛ ተበላሽቷል። በሌላ በኩል ኦሮሚያ ክልል ቦኮ እና ከአዲስ አበባ ወጣ ብለው በሚገኙ የአበባ እርሻዎች ላይ ካራቱሬ ጥሩ ውጤት እያሳየ መሆኑን አቶ ፋና ገብረሰንበት አስረድተዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1207 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 942 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us