በኢትዮጵያ የኢታኖል ምርት አተገባበርና የደረሰበት ደረጃ

Wednesday, 14 May 2014 13:33

በአይቸው ደስአለኝ

 

በአሁኑ ወቅት በዓለም ለአየር መበከልና ለሙቀት መጨመር ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያደርገው የካርቦን ውጤት የሆነው የኢነርጂ ምንጭ እንደሆነ ይታወቃል። ይህን ለመግታት እንዲቻል ለፋብሪካ፣ ለትራንስፖርትና ለቤት ውስጥ አገልግሎት ታዳሽ ኢነርጂን መጠቀም እንደ አይነተኛ አማራጭ ተወስዷል። ከዚሁ ጋር በገጠሩ ኢትዮጵያ በደን ምንጣሮ የሚተማመነውን የማገዶ ምርትን በመግታት ህብረተሰቡ ታዳሽ በሆነው በባዮ ኢነርጂ እንዲጠቀም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የተሰራጩ ሲሆን ኃይል ቆጣቢ ምድጃዎችም የተጠቃሚውን ጤንነት በማረጋገጥ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ ከሀገራችን የህዝብ ብዛት አንፃርና በአካባቢ ላይ ከሚደርሰው ውድመት አኳያ የተሰራው ስራ ገና እዚህ ግባ የማይባል በመሆኑ ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

ከሰሞኑም በኢትዮጵያ የኢታኖል ምርት በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አማካኝነት እንዴት እየተከናወነ እንደሚገኝና የገጠመውን ፈተና በተመለከተ ከውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዲሁም ስኳር ኮርፖሬሽን፣ ከሆርን አፍሪካ ሪጅናል ኢንቫይሮንሜንት ማዕከል፣ ከጋያ መንግሥታዊ ያልሆነ ማህበር በተጨማሪም ከተለያዩ ክልሎች ኢነርጂ ቢሮ የተውጣጡ ባለሙያዎች በተገኙበት የምክክር ጉባኤ የተካሄደ ሲሆን ምርቱን በቀጣይነት ለማስፋፋት እንዲቻልም ስልቶች ተቀይሰዋል።

በዕለቱ የውሃ የመስኖ እና የኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት የሆኑት አቶ ተስፋዬ ሪቻላ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ከእፅዋት የሚገኝ የኢነርጂ ምንጭን በስፋት በማምረት ከውጭ ሀገር በግዢ የሚገባውን የፔትሮሊየም ነዳጅ ውጤትን መተካትና የባዮፊውል ምርቶችን ከሀገር ውጭ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህ ተግባራዊነትም ኢታኖልን በነባር ፋብሪካዎችና አዳዲስ ተቋቁመው በቅርቡ ወደ ምርት ስራ የሚገቡት የስኳር ፋብሪካዎች በስፋት በማምረት ጥቅም ላይ እንደሚውል ተናግረዋል። ከዚህ ጎን ለጎንም መስሪያ ቤታቸው የተሻሻሉ ምድጃዎችን ስርጭት መርሃ ግብርን በመቅረፅ የደን ጭፍጨፋን ለመታደግና የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ጥቅምንና ጤናን በማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተው ከዚህ ጋር በተያያዘም መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ኢታኖልን ለቤት ውስጥ ምግብ ማብሰያነት የማስተዋወቅና የማስፋፋት ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። አክለውም የውሃ፣ የመስኖና የኢነርጂ ሚኒስቴር ለወደፊት እድገት ማሳያ ይሆን ዘንድ ከአካባቢና ደን ሚኒስቴር ከአለም ባንክና ከኖርደክ ከላይማቲክ ፋስሊቲ ጋር በመተባበር አራት አነስተኛ የሙከራ የኢታኖል ማምረቻዎች ተከላ በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራና በጋምቤላ እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በእለቱ የቀረበው የጋያ ማህበርና የሆርን አፍሪካ ኢንቫይሮሜንት ጥናት እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ የባዮ ኢታኖል ንዑስ ዘርፍ እድገት በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ የተጠበቀውን እድገት አላስመዘገበም በተለይም ጠንካራ ተቋማት አለመኖርና አጠቃላይ ምርቱ ለምግብ ማብሰያነትና ለኃይል ማንቀሳቀሻነት ጥቅም ላይ ውሎ የሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በውል አለመታወቁ ዋንኛው እንቅፋት መሆኑን አመልክቷል። ይህን ችግር ለመቅረፍም ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ምርቱን ለማሳደግና ለመጠቀም ፕሮጀክት ተቀርጾ እየተተገበረ እንደሚገኝ ተጠቅሷል። በዚህም የድርጊት መርሃ ግብር ተዘርግቶ ተደራሽነቱን በማስፋት ለበርካቶች የስራ እድልና ገቢን በመፍጠር አሳታፊ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ሀገሪቱ እየተከተለች ያለቸውን አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለማገዝ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ፕሮጀክቱ በኢታኖል ዘርፍ ሀገሪቱ የምትከተላቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተፈትሸው ለኢንቨስትሜንት ምቹ እንዲሆን ይደረጋሉ። በሌላም በኩል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው እንዲጎላ ምርቱን በግብአትነት የማያገለግሉ የፍራፍሬና የቅጠላቅጠል ተረፈ ምርቶች በአስተማማኝ መልኩ የሚገኙበትን ዘዴ ይቀምራል። የገበያ ጥናትም ይካሄዳል። ከዚህም የአዋጭነት ጥናት ቀርቦ ለገበያ የሚሆን የድርጊት መርሃ ግብር ይዘጋጃል።

የጋያ ማህበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ጌታነህ ደስአለኝ በበኩላቸው እንደተናገሩት ለኢታኖል ምርት ግብአት የሚሆኑ አማራጮችን ለመመልከት በየክልሎች የምልከታ ስራዎችን አከናውነዋል። በተለይ ሸንኮራ በሚበቅልባቸው በቤንሻንጉል ክልል አካባቢዎች በቀን መቶ ሃምሳ ሊትር ሊያመርት የሚችል የኢታኖል ማብላያ ማሽን ተክለው ለሙከራ አምርተዋል። በጋምቤላ፣ በአማራና በኦሮሚያ ከተሞችም ማምረት ጀምረዋል። በቅድሚያም ኢታኖል ከምን ሊመረት ይችላል የሚለውን ትኩረት ሰጥተው ጥናት አካሂደዋል። ከዚያም የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ ምን ይመስላል የሚለውን አጥንተዋል። ለዚህ እንዲያግዝ አለም አቀፍ አማካሪ ቀጥረው እየሰሩ ሲሆን ከሸንኮራ አገዳ ምን ያህል ኢታኖል ሊመረት ይችላል የሚለውን ካወቁ በኋላ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ እንደሚተገበር አመልክተዋል። እንደ እርሳቸው በአንዱ ክልል የሚገኝ ግብአት በሌላው ክልል ሊገኝ ስለማይችል ይህን ከግምት በማስገባት አመራረቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ጥንቃቄ አድርገዋል። ከዚያም ስራው በሙያ ይሰራ የሚለውን ማለትም በመንግስት ወይም በግል ወይም ደግሞ መንግስስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ይሁን የሚለውን አለም አቀፍና የሀገር ውስጥ አማካሪዎች እንደሚወስኑ አስታውቀዋል።

እንደሚታወቀው በሀገራችን ኢታኖልን በማምረት ቀዳሚውን ስፍራ በመያዝ መጀመሪያ የሆነው የፊንጫ ስኳር ፋብርካ ነው። ከ15 ዓመታት በፊት ምርቱን ኬ 50 በሚል ለቤት ውስጥ ምግብ ማብሰያ እንዲሆን ገበያ አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል። ነገር ግን ኢታኖሉ ለኬሮሲን በተሰራ ቡታጋዝ ጥቅም ላይ በመዋሉ አደጋ አስከትሎ ከገበያ ሊወጣ እንደቻለ የሚታወስ ሲሆን ከዚህ ጊዜ በኋላ ኢታኖል ለቤት ውስጥ ምግብ ማብሰያ መሆኑ ቀርቶ ከመቶ እጅ ቤንዚን ውስጥ 5 በመቶ የሚሆነውን ኢታኖልን በመደባለቅ ለትራንስፖርት አገልግሎት እንዲውል መደረጉ ይታወሳል። የምርቱ መጠንም በየአመቱ እያደገና እየተስፋፋ ይገኛል። ከዚህ አንፃር ከፊንጫ ፋብሪካ ምን ዓይነት ልምድ እንደቀሰሙ የተጠየቁት አቶ ደስአለኝ ጌታነህ ሲመልሱ ልምድ እንደወሰዱ ጠቁመው የኢታኖል ምርትንም ከፋብሪካው በዓመት 500 ሺህ ሊትር ገዝተው ለሀገር ውስጥ ተጠቃሚዎች እንደሚያከፋፍሉ ገልፀዋል። አያይዘውም በውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር እንዲሁም በስኳር ኮርፖሬሽን በሚደረግላቸው ድጋፍ በሶማሌ ክልል በሚገኙ ማለትም በሀርቲሼክ ሁለት ጣቢያዎች ለሚገኙ ስደተኞች ከ3ሺህ 728 በላይ በኢታኖል የሚሰሩ ምድጃዎችን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ጋር በመሆን በማከፋፈል በመጠለያ ጣቢያዎች አካባቢ ሊከሰት ይችል የነበረውን የአከባቢ ደን መራቆትን ለመታደግ ችለዋል።

ይሁን እንጂ ከፊንጫ ስኳር ፋብሪካ የሚገኘው የኢታኖል ምርት አስተማማኝ ካለመሆኑም በተጨማሪ የሚፈለገውን ያህል መጠን አያቀርብም። ምክንያቱም የሚሰጠው በኮታ ነው። በዚህም የተነሳ ህብረተሰቡ በየአካባቢው ኢታኖልን እንዲያመርት ጥረት እንደሚደረግ አቶ ደስአለኝ ተናግረዋል። የምርቱን ግብአት መሰረት ለማስፋትም በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከቢራና ከወይን ፋብሪካዎች የሚገኙ ተረፈ ምርቶች እንዲሁም አትክልትን ጨምቀው ከሚያሽጉ ፋበሪካዎች ለመውሰድ እቅድ ይዘው እንደሚንቀሳቀሱ አስረድተዋል።

ኢታኖል በሀገር ውስጥ እንዲመረት የሚደረገው አንዱ አላማ ከውጭ የሚገባውን የፔትሮልየም ምርት ለማስቀረት እንደሆነ ይታወቃል። ይህም የውጭ ምንዛሪን ያስቀራል። ነገር ግን ኢታኖልን በኬሮሲን ምድጃ መጠቀም ስለማይቻል ለኢታኖል የሚሆን ምድጃ ከውጭ ማስመጣቱ እንደገና የውጭ ምንዛሪን ስለሚያስወጣ ነገሩን ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ አያደርገውምን ተብለው የተጠየቁት አቶ ደሳለኝ ሲመልሱ ያለውን የሀገር ውስጥ አቅም በመጠቀም ኢታኖልን ከማምረት በተጨማሪ ምድጃውንም በሂደት ለማምረት እቅድ ይዘው እንደሚንቀሳቀሱ በአሁኑ ወቅትም የምድጃውን 80 በመቶ የሚሆነውን አካል በሀገር ውስጥ ማምረት እንደተቻለ ገልፀዋል። እንዲያውም ሜቲክ የተባለውን ኩባንያ አነጋግረው ምድጃውን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ለማምረት እንደሚቻል እንደገለፀላቸው ጠቅሰዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የምድጃው መመረትም አይቀሬ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል። የኢታኖል ምርትና ምድጃው በሀገር ውስጥ ገበያ አዋጭ መሆኑን የሸማቹን የመግዛት አቅም ያገናዘበ እንደሆነ ምን ያህል ተጠንቷል ተብለው የተጠየቁት አቶ ደሳለኝ ሲገልፁ እስካሁንባለው ሁኔታ የኢታኖል ዋጋ ከኬሮሲን ያነሰ እንደሆነ ሽታና ጭስ ስለሌላውም ተፈላጊነቱ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረው የህብረተሰቡን ፍላጎት በተመለከተም ለ18 ወራት ጥናት መደረጉን አስረድተዋል። ይሁን እንጂ የዋጋ ተመኑ በንግድ ሚኒስቴር የሚወጣ መሆኑን አያይዘው ገልፀዋል።

በእለቱ ስብሰባ ታዳሽ የሆነውን ኢታኖልን መጠቀም ከላይ ከተጠቀሱት ጥቅሞች በተጨማሪ የካርቦን ልቀትን መቀነስ ስለሚያስችል የካርቦን ፋይናንስን ማግኘት የሚያስችል ነው። ይሀን በተመለከተ አቶ ደሳለኝ ሲገልፁ የቅድመ ስራውን በአዲስ አበባ በቀን 1ሺህ ሊትር ኢታኖል ለማምረት በሚያስችል መልኩ ለማዘጋጀት ጥረት እየተደረገ ሲሆን በዚህም ጠቋሚ የካርቦን ፋይናንስ ምልክቶች አሉ ብለው ካርቦን ክሬድት የማስመዝገቡ ስራም በሂደት ላይ የሚገኝ ሲሆን በስሌቱም ከእያንዳንዱ የኢታኖል ስቶቭ ፋይናንስ ለማግኘት የሚያስችል እንደሆነ ጠቅሰዋል። በዚህ ረገድ ከአለም አቀፍ አማካሪዎች ጋር የሚሰሩ ሲሆን ነገር ግን ስራው ጊዜን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ በቀን 1ሺህ ሊትር አትክልትና ፍራፍሬ ተረፈ ምርትን በመጠቀም የሚያመርት ማሽን የገባ ሲሆን ከዚሁ ጋርም 1ሺህ የኢታኖል ስቶቮች ከውጭ ሀገር ገብተዋል። ለስቶሹ ማስቀመጫ የሚሆን ሳጥን መሰል ነገርም እየተሰራ ይገኛል። በሁለት ዓመት ውስጥም ስራ ላይ ይውላል። ስራ ሲጀምርም በቅድሚያ ተጠቃሚ የሚሆኑት የቀድሞው እንጨት ተሸካሚ ሴቶች ማህር አባላት ናቸው። ኢታኖሉንና ስቶቩን በመሸጥና በማከፋፈል ስራ ይሰማራሉ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ ኤጀንሲና የሴቶች እና የወጣቶች ማህበራት አጋር ናቸው። ፋብሪካው በአቃቂ ክፍለ ከተማ የሚተከል ሲሆን የሚያስተዳድረውም የአካባቢው ህብረተሰብ ነው።

በአጠቃላይ እነኚህና ሌሎች የባዮኢነርጂ አማራጮች የውጭ ምንዛሪን በማዳን የአካባቢ መራቆትንና ውድመትን በማስቀረት ተጠቃሚዎችንም ከመተንፈሻ አካላት በሽታ ያድናሉ። ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታውም መሰረት የሚጥሉ በመሆናቸው የባለ ድርሻ አካላት ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1217 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1110 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us