በኢትዮያ የደን ይዞታ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?

Wednesday, 21 May 2014 12:53

ደኖች የአየር ጠባይን ለማስተካከልም ሆነ ከብክለት ለማፅዳት ሚናቸው ከፍተኛ ነው። አፈር በአየርና በውሃ ተጠርጎ እንዳይወሰድ በየቦታው መኖር አለባቸው። በአዳጊ ሀገሮች ደግሞ የኃይል ምንጭ ሆነው በማገዶነት ያገለግላሉ። በርከት ብለው በሚገኙባቸው አካባቢዎች ለእንስሳት መጠለያ ሆነው ያገልግላሉ። በኢትዮጵያ ከአመታት በፊት የደን መመናመን ያሳሰባቸው ወገኖች በጉዳዩ ዙሪያ ድምፃቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል። አሁንም ቢሆን የደን ይዞታው ወደ ነበረበት ቦታ ተመልሷል ባይባልም በየክልሉ የተራቆቱ አካባቢዎች ደን እንዲለበሱና እንዲያገግሙ የሚደረገው ጥረት በየአካባቢው በሚገኙ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅቶች ግለሰቦችና የማህበረሰብ አባላት አበረታች ስራዎችን እያከናወኑ ናቸው።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የደን ሁኔታ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በሰሞኑ ምሁራን በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት አካሂደዋል። ዶ/ር ተፈሪ መንግስቱ በአካባቢና ደን ሚኒስቴር የደን ዘርፍ አማካሪ ዶ/ር ዕምሩ ብርሃኔ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የደንና የህግ ዲፓርትሜንት መምህር ዶ/ር ዘውዱ እሸቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የክላይሜት ሳይንስ ማዕከል ዳይሬክተርና የአፍሪካ ዲዛስተር ሪስክ ማኔጅመኔት እንዲሁም የደንና የአካባቢ አየር ለውጥ አማካሪ እንዲሁም አቶ አደፍርስ ወርቁ በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪና በዚሁ ዘርፍ የፒኤች ዲ ትምህርታቸውን በጀርመን ሀገር የሚከታተሉ ናቸው።

እንደሚታወቀው ከበርካታ አስርታት በፊት 40 በመቶ የሚሆነው የኢትዮያ የቆዳ ስፋት በደን ተሸፍኖ የነበረ ሲሆን ነገር ግን ለእርሻ ስራ ለማገዶ እንዲሁም የእንጨት ውጤቶችን ለማምረት በሚል ምንጠራ ተካሂዶበት በመመናመኑ ወደ 3 በመቶ ዝቅ ለማለት ተገዶ ነበር። ከዚህ አንጻር አሁን ያለው ሁኔታ ምን እንደሚመስል ዶ/ር ተፈራ መንግስቱ ሲገልፁ የኢትዮጵያ የደን ሁኔታ በጣም እያሽቆለቆለ ስለመሆኑ ምን ጥርጥር የለውም። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን በመንግስት መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በግለሰቦችና በሕብረተሰብ አማካኝነት በተደረገ ጥረት ሁኔታው እየተሻሻለ መጥቷል። ከ5 ዓመታት በፊት የተደረገው ጥናት እንዳመለከተው ከ3 በመቶ በታች የነበው የደን ሽፋን ወደ 10 በመቶ በላይ ደርሷል። በአሁኑ ወቅት አዲስ የተቋቋመው የአካባቢና የደን ሚኒስቴር ትክክለኛውን መረጃ ለማግኘት የደን ቆጠራ እያካሄደ እንደሆነ አመልክተዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሰጡት ዶ/ር ዕምሩ ብርሃኔ እንደሚሉት የደን ሽፋናችን እየተሻሻለ ነው። በተለይ የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ በማልማት የተሰራው ስራ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል። ከዚሁ ጋር ሰው ሰራሽ ደኖች (በአዳዲስ ቦታዎች ላይ መተከሉ) እየተስፋፋ ነው። በተለይ በመሀል በደቡብና በሰሜን ኢትዮጵያ የተሰራው ለዚህ ምሳሌ ነው። ገበሬው በእርሻ መሬቱ አካባቢ ዶኖችን እየተከለና እየተንከባከበ ነው። አቶ አደፍርስ ወርቁ በበኩላቸው በተለይ በአማራና በትግራይ ክልል አካባቢ ለደን የሚሆን ቦታ በመከለል ደን እንዲጠበቅና እንዲለማ መደረጉን መመልከት እንደቻሉ ጠቅሰው ነገርግን በመተማ፣ በቁራና በሶማሌ ክልል የተፈጥሮ ደን እየተመናመነ እንዲመጣ መረዳት መቻላቸውን ገልፀዋል። በሌላ በኩል የአግሮ ፎረስተሪ ስራ መስፋፋቱ ተስፋ ሰጭ ቢሆንም የሚቆጠረውን ደን ይህን ያህል ይሆናል ብሎ መናገር እንደሚያስቸግር ተናግረዋል።

ዶ/ር ዘውዱ እሸቱ በበኩላቸው ቀደም ሲል ከተጠቀሰው ሃሳብ ጋር እንደሚስማሙ ጠቅሰው ነገር ግን አፅንኦት በመስጠት ለመናገር የሚፈልጉት በአሁኑ ወቅት የመስኩን ምሁራን ግራ የሚያጋባ ነገር እንዳለ፣ እስካሁን በተደረገው ጥናት ቀደም ሲል 30 በመቶ የሚሆን የደን ሽፋን በኢትዮጵያ እንዳልነበረ ተናግረዋል። አክለውም እ.ኤ.አ በ2011 የተደረገው ጥናት እንደመለከተው የደን ሽፋኑ ከ10 እስከ 14 በመቶ እንደደረሰ ነገር ግን ይህ እንደሁኔታው ተቀባይነት ቢኖረው እንኳን በኢትዮጵያ በዓመት 140ሺህ ሄክታር የደን መሬት እየተቆረጠ እንደሚገኝ በአማካይ በሁለት ሜትር ርቀት ላይ ሁለት ዛፎች አሉ ተብሎ ቢታሰብ ወደ 3.5 ሚሊዮን የሚሆን ዛፎች ይቆረጣሉ ማለት ነው። ስለሆነም የሚቆረጠውና የሚተካከለው በፍፁም ሊጣጣም አይችልም። በዚህ የተነሳም በአሁኑ ወቅት ሀገሮችም ከወንበርና ጠረጴዛ ጀምሮ ማናቸውንምየእንጨት ቁሳቁሶችን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማውጣት ወደ ሀገር ውስጥ እንደምታስገባ አስታውቀዋል።

እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ በዝናባማነቱ፣ በለምነቱና በውሃ መሰረትነቱ የሚታወቀው ይኸው የደን አካባቢ ነው። በአሁኑ ወቅት ቦታው ከፍተኛ ፈተና ተጋርጦበታል። ለባለሀብቶች እየተቸበቸበ አግሮ ቢዝነስ እየተስፋፋበት ነው። ሰፍራዎች ይካሄዳሉ። ደኖቹም መተኪያ ሳይበጅላቸው ይጨፈጨፋሉ። ይህን በተመለከተ ምን መደረግ ይኖርበታል በዚህ ጉዳይ ላይ በቅድሚያ አስተያየታቸውን የሰጡት ዶ/ር እምሩ ናቸው። እንደእርሳቸው አንድ መሬት ጥቅም ላይ ከማዋሉ በፊት ለምን መዋል አለበት የሚለው መታየት አለበት። ይህ ተለይቶ ከታወቀ በኋላ ነው ስራ ላይ መዋል ያለበት ከዚህ ውጭ አሁን በሚካሄደው አሰራር የደን መሬቶች ለተለያዩ ጥቅም መዋላቸው እንደጉድለት የሚታይ ነው። ከዚህ ጋር ልቅ የግጦሸ መሬት መኖር ደኖችን ጠብቆ ለማቆየት የሚደረገውን ጥረት የሚያጨናግፍ ነው። በሌላም በኩል በቆላማ አካባቢ ባሉና ለኤክስፖት ምርት በሚሆኑ ደኖች ላይ የሚፈጠረው ጫና ቀላል አይደለም። በተለይም በአካባቢው የሰፈራ ፕሮግራሞች መካሄዳቸው እስካሁን ድረስ መቀጠሉ ችግሩን እንዲባባስ አድርጎታል ዶ/ር ዘውዴ በበኩላቸው በዚህ ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን ሲገልፁ ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች እንደሚታያቸው አንደኛው የአካባቢው ህብረተሰብ ያርሰው የነበረው መሬት ይበልጥ እየተራቆተ ሲሄድ በዚያ የሚገኘውን የደን መሬት ለእርሻነት መጠቀሙ ነው። በሌላ በኩል በመንግስት ይዞታ ስር የሚገኙ የደን መሬቶች በትክክል የሚጠብቃቸውና የሚንከባከባቸው ባለቤት ስለሌላቸው ለውድመት ተጋላጭ ናቸው። በደን የተሸፈኑ መሬቶች ከለምነታቸው የተነሳ አአርሶ አደሮቹ ከፍተኛ ምርት በአጭር ጊዜ ስለሚያስገኙላቸው እርሻ አድርገዋቸው ይቀጥላሉ። ሁለተኛው ምክንያቶች የደን መሬቶች ለውጭ ባለሀብቶች ተሰጥተው የአግሮ ቢዝነስ ስራ ለማከናወን በሚል መመንጠራቸው ነው። እርሻቸው ኤክስፖት መርናቸው። በዚህ በኩል መጤን ያለበት ጉዳይ አለ። በተለይ በደጋዎቹ አካባቢ ያሉት ጥብቅ ደኖች አረንጓዴ ጫካ ከመሆናቸው በተጨማሪ የሀገሪቱን የውሃ ሀብት መጠን በከፍተኛ ደረጃ በስራቸው አቅፈው የሚገኙ ናቸው።

ደኖቹ ተቆረጡ ማለት ከታች ያለው ውሃም ደረቀ ማለት ነው። በአሁኑ ወቅት ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በዓመት ወደ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ ዛፎች ይቆረጣሉ። እነኚህ ዛፎች ለአካባቢ መጠበቅ የሚሰጡትን ጠቀሜታ ወደ ገንዘብ ለመቀየር ስሌቱ የተወሳሰበ እንኳን ቢሆን ዛፎቹን እንኳን ብቻ ወደ ገንዘብ መቀየር አያዳግትም። ስለዚህ ደኖች ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው ማመን ያስፈልጋል። ይህን ከግምት ያላስገባ ዘመናዊ የእርሻ ኢንቨስትሜንት ከ10 ዓመተት በላይ ጥቅም ሊሰጥ አይችልም። በ1970ዎቹ በአሶሳ አካባቢ እንዲሰፍሩ የተደረጉ አርሶ አደሮች ከ10 እና 15 ዓመታት በላይ ውጤታማ የሆነ የበቀሎ ምርት ማምረት አልቻሉም። በአሁኑ ወቅትም ያ አካባቢ ወደ በርሃማነት እየተቀየረ እንደሚገኝ ዶ/ር ዘውዴ አስረድተዋል።

ዶ/ር ተፈራ መንግስቴ በበኩላቸው ከላይ ከተጠቀሰው ለየት ያለ አስተያየት ያቀርባሉ። እንደ እርሳቸው ገለፃ በቆላማ አካባቢዎች አልፎ አልፎ የግብርና ውጭ ኢንቨስትሜንት መኖር ይህን ያህል ክፋት የለውም። ምክንያቱም በኢትዮጵያ በከፍተኛ መሬቶች ላይ ያሉ እርሻዎች ለዘመናት በመታረሳቸው ለምነታቸው እጅግ አሽቆልቁሏል። አሁን በላያቸው ላይ ያለውን ህዝብ መሸከም የሚያስችላቸው የእርሻ ምርት የላቸውም። ስለዚህ በዝቅተኛና ቆላማ አካባቢዎች በአግባቡ እርሻ ስራ ቢካሄድ ህዝቡን ለመመገብ ያስችላል። አንዳንድ መጠበቅ ያለባቸውን ከዚህ ህይወትንና ደንን ከግምት በማስገባት ስራው ቢከናወን ጉዳት የለውም ይላሉ። በዚያ አካባቢ የሚስተዋለው የደን መራቆት በእርሻ ኢንቨስትሜንት ብቻ ተከሰተ አይደለም። ከዕፅዋቶቸ ባህርይም ጋር ይያያዘል። ለማንኛውም የአጠቃቀም ስሌት ሊዘረጋለት የሚገባ ሲሆን በዚህ ረገድ ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት በባለሙያቸው የሚሰራ እቅድ ታቅዶ ሊተገበር እየተዘጋጀ እንደሆነም ዶ/ር ተፈራ ገልፀዋል።

ዶ/ር ዕምሩ በበኩላቸው ሰፈራን እንደ ብቸኛ የደን መመናመን ምክንያት ተደርጎ መወሰን እንደሌለበት ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት መንደር ማሰባሰብ ያልተነኩ ወይም ያልተደረሰባቸው የደን መሬቶች እንዳሌሉ አመልክተዋል። እንደ እርሳቸው ዋናውና አስፈላጊው ጉዳይ የደን መሬቶችን እንደራስ ንብረት በመመልከት ነው። ይሁን እንጂ እርሳቸውም ሆነ ዶ/ር ተፈራ እንደሚስማሙት ሰፈራ ዘለቄታዊ መፍትሄ አይደለም። ህዝቡ ካለበት አካባቢ ሳይፈልስ እዛው ሆኖ አካባቢውን መንከባከብ አለበት። የሀገሪቱ መሬት የሚለጠጥ አይደለም። ስለዚህ አካባቢ በተራቆተ ቁጥር ህዝብን ከመተው በማንሳትና ሌላ ቦታ በማስፈር መዝለቅ አይቻልም። ህብረተሰቡን የትም አትሄድም እዚሁ አካባቢህን ተንከባከብ በማለት እገዛ ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህ እንዲያግዝም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከውጭም ቢሆን አምጥቶ መሞከር ያስፈልጋል።

በኢትዮጵያ በቆላ አካባቢ ደኖች ውስጥ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ እንደ ሙጫና እጣን የመሳሰሉ ምርቶች በብዛት ይገኛሉ። ሆኖም ግን ይህ አካባቢም ቢሆን ዕጣ ፈንታው ከሌሎች አካባቢ የተለየ አይደሉም። ውድመትና መራቆት እያጋጠማቸው ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ለብዙ ዓመታት ጥናት ያደረጉት አቶ አደፍርስ ሲገልፁ እጣንና የሙጫ ዛፎች ከሌሎች ደኖች ተለይተው አይታዩም ደኖቹ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ብቻ የሚታዩ ከሆነ ምናልባት እያደገ ከሚሄደው ኢኮኖሚ ጋር ያነሰ ወይም የማይመጣጠን ስለሆነ ጥቅሙ ዝቅ ተደርጎ እንዲታይ ሊያደርግ ይችላል። ስለዚህ ደኑ ምን አይነት ኢኮኖሚያዊ ኢኮሎጂያዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ አለው የሚለው መታየት ይኖርበታል ሲሉ ገልጸዋል። አክለውም ኢትዮጵያ ከደኑ ዘርፍ በርካታ የኤክስፖርት ምርት እንደሌለበት ጠቅሰው ትልቅም ይሁን ትንሽ የኤክስፖርት ፕሮጀክቶች የመንግስት የፖሊስ አቅጣጫ እንደሚያበረታታቸው አመልክተዋል። ይሁን እንጂ ማበረታታቱ በምን ሁኔታ ላይ ነው የሚለው ሲታይ የዶ/ር እምሩና ጓደኞቻቸው ጥናት እንደሚያመለክተው ከፍተኛ ቅርቃር ውስጥ እየተገባ እንደሆነ አስረድተዋል። ምክንያቱም የዕጣንና የከርቤ ዛፎች በተፈጥሮ የመብቀል ትግል ይስተዋልባቸዋል። ይህ እንዳለ ሆኖም ሌላም ሰው ሰራሽ ችግሮች አሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ እጣንና ሙጫን ወደ ውጭ ገበያ የሚልኩ 34 ኩባንያዎች አሉ። ከዚህ ሌላ በርካታ የህብረት ስራ ማህበራት አሉ። ማህበረሰቡን በማደራጀት ስራ በመፍጠርና ገቢ በማስገኘት የላቀ ሚና ይጫወታሉ። ስለዚህ ዕጣኑና ሙጫው ሲታሰብ ይህ ሁሉ ጉዳይ መታሰብ እንዳለበት አቶ አደፍርስ አስታውቀዋል።

     እንደ እርሳቸው ገለፃ ዕጣንና ሙጫ እየሱስ ክርስቶስ በቤተልሄም ሲወለድ የተሰጡ ስጦታዎች ናቸው። ነገር ግን አሳዛኙ ነገር ዛሬም ሀገራችን ምርቶቹን ወደ ውጭ የምትልከው ከዚያ ዘመን ባልተለየ ምንም እሴት ሳይጨመርበት ጥሬ ምርቱ ሆኖ ነው ኢትዮጵያ ካላት በርካታ ብሔራዊ ፓርኮች ውስጥ በከፍተኛ መሬቶች ላይ ደረቃማ ደኖች ባለበት አካባቢ ሁሉ ዕጣነና ሙጫዎች ይገኛሉ። ኢኮሎጂያዊ ጠቀሜታን በተመለከተ የሱዳን በርሃ የኢትዮጵያን ድንበር ሰርስሮ አልፎ ወደ ደጋማው ክልል እንዳይገባ ገትሮ የያዙት በታችኛው ቆላማ መሬት ላይ የሚገኙ የሙጫና ዕጣን ተክሎች ናቸው። ትላልቆቹ መሰረተልማቶችና የህዳሴው ግድብ ጭምር ያለበት ቦታ እነኚህ ምርቶች መኖራቸው ኢኮሎጂው እንዳይዛነፍ ያደርጋሉ። አያይዘውም የሙጫና የዕጣን ምርቶች በሶማሌ ክልል ላለው ህብረተሰብ ከከብት ርባታ ቀጥሎ በሁለተኛነት ገቢ የሚያስገኙ ናቸው። ስለዚህ ጥቅማቸው በቀላሉ ስለማይታይ በጋምቤላ እና በሁመራ በሚገኙ ሰፋፊ እርሻዎች ዳርዳር ቢተከሉ አካባቢን መጠበቅ እንደሚቻል ጠቅሰው የኢንቨስትሜንት ቢሮም ስለ ሰፋፊ እርሻ መልማት ሲያቅድ እነኚህ የበረሃ ደኖች አብረው እንዲለሙ ቢደረግ አካባቢን ከመራቆት አድኖ ተጨማሪ ገቢ ስለሚያገኙ የአካባቢው ህብረተሰብ ተጠቃሚሆኖ ለደን እንክብካቤው የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚችል አመልክተዋል። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የደን ተከላውም ሆነ የደን የመጠቀሙ ስራ በሙያተኛ ቢመራ ስራችን ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ እንዳይሆን ያደርጋል።

ይምረጡ
(6 ሰዎች መርጠዋል)
2391 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 924 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us