ረሀብን በ2015 ከዓለም ለማጥፋት የመከረው ጉባኤ

Wednesday, 28 May 2014 13:30

ዓለም አቀፉ የምግብ ፖሊሲ ጥናት ተቋም እንደሚገልፀው በ2015 የሚሊኒየም የልማት ግብ የጊዜ ገደብ ካበቃ በኋላ የሚኖረው ዋንኛ አጀንዳ በ2025 ረሀብን ማጥፋት ነው። ለዚህ እንዲያግዝም ረሀብን ከወዲሁ መከላከል የሚያስችል ኢንቫይሮንሜንታዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን በማመቻቸት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

ከሰሞኑም በአዲስ አበባ ከተለያዩ የዓለም ሀገሮች የመጡ 800 ኤክስፐርቶች በዚህ ጉዳይ ላይ ለሶስት ቀናት ያህል የመከሩ ሲሆን በውይይቱም እቅዱን ለማሳካት የሚያስፈልገውን ኢንቨስትሜንት ለማግኘት የሚገጥመውን ፈተና በዋነኛው አጀንዳነት ተነስቷል። የምግብ እጥረትና የተመጣጣኝ ምግብ ዕጦት እንዳይከሰት በሚያስችል መልኩ የሚዘረጋው ስልትም ተጋላጭ የሆኑ ግለሰቦችን ቤተሰቦችን ማህበረሰቦችንና ሀገሮችን በማገዝ ሁኔታውን መቋቋም የሚቻለበትን አቅም እንዲገነቡ ይደረጋል። ከዚህ በተጨማሪም መቋቋም የማይችሉት ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት ከችግሩ መለስ መቋቋም የሚችሉበትን ሁኔታ ያመቻቻል ይህም በአጭርና በረጅም ጊዜ እንዲሁም በቀላልና በውስብስብ ተለይቶ የተቀመጠ ነው።

በስብሰባው መክፈቻ ስነስርዓት ላይ የተገኙት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ እንዳመለከቱት በአንድ ሀገር ረሀብን ለመግታት እንዲቻል ለረሀብ፣ ለድርቅ እንዲሁም ለኢኮኖሚያዊ መዋዠቅ የማይበገር የእርሻ ስርዓት መገንባት ያስፈልጋል። ከዚህ ጎን ለጎንም ተያያዥ ስራዎች መከናውን እንዳለባቸው ጠቅሰው የሚመሩት መንግስት የእርሻ ምርታማነትን በማጎልበት ለአነስተኛ አምራች ገበሬዎች ምርት አመቺ የገበያ ስርዓትን እንዳመቻቸ አስታውቀዋል። በሌላም በኩል ከአመት ዓመት በመስኖ የሚለማው የእርሻ መሬት መጠን እንዲጨምር መደረጉን እንዲሁም አፈር መከላትንና መሸርሸርን ለመከላከል የውሃና አፈር መጠበቂያ ዘዴ በባዮሎጂካዊ አሰራር ተተግብሮ ቀጣይነት ያለው አመራር መከናወኑን አስረድተዋል።

የዓለም አቀፉ የምግብ ፖሊሲ ጥናት ተቋም የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ሚ.ር ሸንገንፋን በበኩላቸው በአለማችን እጅግ ዘግናኝ፣ አስፈሪና አውዳሚ ክስቶች እየተፈጠሩ ባለበት በአሁኑ ወቅት ስብሰባው መካሄዱ እጅግ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰው ለወደፊቱ የሚጠብቁትንና ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎች የምግብ ዋጋ መናር የተፈጥሮ ቅስፈት ሲሆኑ ችግሮቹም የማንንም ድንበር ሳይለዩ በማናቸውም ሀገሮች እንደሚከሰቱ አስረድተዋል። አክለውም የምግብ እጥረት ረሀብ እንዳይከሰት የሚደረገው ጥረት ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ሀገሮች በሚያሳዩት ትብብር በመሆኑ አስቀድሞ ራስን ማዘጋጀት አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል። ይህን አገላለፅ እንደሚጋሩት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብና የእርሻ ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር ሚስስ ማሪያ ሄሊና ሲመድ አስታውቀዋል።

በዓለም ላይ የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት በአጅጉ የሚጎዱት ድሆችን የመሰረተ ልማት ባልተስፋፋበትና ከእጅ ወደአፍ በሆነ ሁኔታ ህይወታቸውን የሚገፉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ናቸው። እነኚህ ሰዎች ባለማቋረጥ እርሻዎቻቸው ምርት ከማምረት ይነጥፋሉ። በሽታና ሌሎች አደጋዎችም ያጋጥማቸዋል። እነኚህ አነስተኛና ከባድ ያልተጠበቁ አደጋዎች ስር ከሰደደ ድህነት ጋር ሲገናኙ የጤና ረሀብና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዲከሰት ያደርጋሉ። ይህን ችግር ለመቅረፍ ጥናት በማካሄድ ርምጃ መውሰድንና ኢንቨስትሜንትን ማስፋፋት ይጠይቃል። ከዚሁ ጋር በአነስተኛ መሬት ለሚያርሱ ገበሬዎች ቅድሚያ የሚሰጥ ፖሊሲ በመቅረጥ አጥጋቢ ውጤት ሊያስገኝ የሚችል ስራ ማከናወን ያስፈልጋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ፈፃሚ ዳይሬክተር ሚስስ ኤርታሪን ከስን በበኩላቸው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባት ዋንኛው አማራጭ እንደሆነ ጠቅሰው ለዚህ ማሳለጫ የሚያገለግል የሜትሮሎጂ መረጃ ልውውጥ ወሳኝ ነው ብለዋል። እንደ እርሳቸው ለማናቸውም አደጋ ተጋላጭ ያልሆነ የኢኮኖሚ የማህበራዊና ፖለቲካዊ ከባቢ ሁኔታዎችን መፍጠር ያሻል። ይህም በተለይ ሊጠፉና ሊበታተኑ ለተቃረቡ ሀገሮች ፍቱን መድሃኒት ነው። እነኚህ ሀገሮች በአሁኑ ወቅት በኢንቫይሮንሜንትና በኢኮኖሚ ቀውስ አዘቅት ውስጥ ወድቀዋል። በሀገሮቹ የሚገኙ ማህበረሰቦችም በድርቅ፣ በጎርፍና በሌላም አደጋዎች ስለሚጠቁ የምርታማነት አቅማቸውን ማጎልበት ያስፈልጋል። አንድን ቤተሰብ ከዚህ መሰሉ ተጋላጭነት መከላከል መላው ህብረተሰብን ከጥፋት መታደግ በመሆኑ አቅሙን እንዲያጎለብት ማገዝ ግድ ይላል።

በአለፉት አምስት ዓመታት ዓለም ከፍተኛ ውድመቶችንና የተፈጥሮ አደጋዎችን ተጋፍጧል። ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ በሃይቲ ተከስቷል። በአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ረሀብ ደርሷል። በመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ ሱናሚ በኢስያ ተከስቷል። በጃፓን በኒውክለር ራድያሽን መለቀቅ የተነሳ ከባድ ጥፋት ደርሷል። በ2005 የደረሰው የምግብ የዋጋ ንረት መዘዙ እስካሁን ድረስ ተፅዕኖ ማስከተሉን ቀጥሏል። ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ታይፎን ዘያን የተባለው አውሎ ነፋት በፊሊፒንስ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ህልፈተ ምክንያት ሆኗል ከባድ የጎርፍ መጥለቅለቅ በእንግሊዝ ሀገር ጉዳት አድርሷል። በማዕከላዊት አፍሪካ የተቀሰቀሰው የርስበርስ ጦርነት ደሃውን ህብረተሰብ ከድጡ ወደማጡ ከቶታል። በሶሪያና በደቡብ ሱዳን የተፈጠረው ግጭትም ለህፃናትና ሰዎች ህይወት መጥፋትና ከሀገር መሰደድ ምክንያት ሆኗል። የመሬት መንሸራተት በአፍጋኒስታን ከባድ አደጋ አስከትሏል። በአረቡ ውሃ ግብ መሬት አዲስ የመካከለኛው ምስራቅ ሪልፓሪቶሪ ሲንደሮም የሚባል በሽታ ተቀስቅሶ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት አድርሷል። በቅርቡ የወጣው የበይን መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ፓናል ሪፖርት እንዳመለከተው በሰው ሰራሽ እንቅስቃሴ ሳቢያ በሙቀት መጨመር ሰብዓዊ ቀውስ ተባብሶ ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ተፈራ ደርበው በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት ተገቢ ያልሆኑ የፖሊሲ ውስኔዎች በዓለም አቀፍና በሀገር ውስጥ ያለውን የምግብ ስርዓት እጅግ አዛብተውታል። እንዲያም ሆኖ ግን በንኡስ የምግብ ስርዓት ውስጥ ያሉት ግንኙነቶች ባለመበጣጠሳቸው ችግሩን ለመቋቋም ተችሏል። የአየር ንብረት ለውጥና የሙቀት መጨመር የእርሻ ምርት አመራረትና በምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ አድርሰዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ ሚናቸውን ጥረቶች በተቻለ መጠን ያልተጠበቁ ክስቶችን ለመግታት የሚያስችሉ መሆን አለባቸው። ለዚህም ለማናቸውም ጥፋት የማይበገር ፖለቲካዊና ማህበራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ስርዓት መገንባት ያስፈልጋል።

እንደ አቶ ተፈራ ደርበው ይህ እውነት በኢትዮጵያ ግንዛቤ አግኝቷል። ሀገሪትዋ በተደጋጋሚ ለተፈጥሮ ውድመት ተጋልጣ ችግሮችን ያየች እንደመሆንዋ በዘላቂነት ለማንኛውም ችግር የማይበገር ስርዓት መዘርጋት ታምኖበታል። ለዚህም ችግሮችን መላመድና በሂደት ከችግሮቹ ለማገገም ስራ ይሰራል። በኢትዮጵያ ለዚህ እንዲግዙ በርካታ ስልቶች ተዘርግተው እየተተገበሩ ይገኛሉ። በ2010 የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ወጥቶ ስራ ላይ ውሏል። ይህ በአምስት አመታት ውስጥ ተከናውኖ ካበቃ በኋላም ሀገሪትዋ በ2015 መካከለኛ ገቢ ካላቸው የዓለም ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ የሚያደርግ በርካታ ስራዎች ይሰራሉ። ለዚህ እንዲያግዝና የእርሻ ምርት ማንነት የሚያጎላበት ኢንቨስትሜንት በከፍተኛ ደረጃ ስራ ላይ ይውላል። የኢነርጂ የኮሙኒኬሽንና የኢንዱስትሪ እድገትን የሚያጎለብት መሰረተ ልማት ይዘረጋል። ኢኮኖሚውም ከአሀድነት ወደ ብዝሃነት ተቀይሮ የኤክስፖርቱ ዘርፍ እንዲጨምር ይደረጋል። ሚኒስትሩ አክለው እንደገለፁት በ2011 የተነደፈው የኢኮኖሚ እቅድ አረንጓዴና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ እንዲገነባ የሚያስችል ስልት በውስጡ አቅፏል። ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ ዘዴዎችም የተጎዱ መሬቶች መልሰው እንዲለመልሙ ማድረግ የተጎዱና የተመነጠሩ ደኖች እንደገና እንዲያገግሙና አዳዲስ ደኖች እንዲተከሉ ይደረጋል። የእህልና እንስሳ ርባታ ምርታማነት በእጥፍ እንዲጨምር ስለሚደረግ ለተፈጥሮ ቀውስ የማይበገር ኢኮኖሚ እንዲገነባ የበኩሉን ሚና ይጫወታል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተሰራው ስራ የውሃ ሀብትን የማጎልትና የመስኖ ልማት የኢነርጂ ዘርፍ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ችሏል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሁንም በእርሻ ላይ ጥገኛ ሲሆን ይህ ሁኔታም ለመጭዎቹ አስርታትም ይቀጥላል። ዘርፉ ለሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት GDP 50 በመቶ እንዲሁም 80 በመቶ የስራ እድል በመፍጠር የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል። ከዚህ በመነሳት ለአየር ንብረት ለውጥና ለተፈጥሮ ጥፋት የማይበረገር የእርሻ ስርዓት እንዲፈጠር ጥሪቱ ተጥናክሮ ይቀጥላል። ከዚሁ ጋር የአነስተኛ ገበሬዎች ምርታማነት እንዲጨምር የእርሻ ገበያ ስርዓት እንዲጎለብት ተደርጓል። በዚህ ሁሉ እንቅስቃሴም ህዝብ ከመንግስት ጎን በመቆም የበኩሉን እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ ግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው አስታውቀዋል።

በውይይቱ ወቅትም የመገናኛ ብዙሃን ሙያተኞች እድል አግኝተው የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል። ከሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች ከተጠየቁት ውስጥ በአሁኑ ወቅት በአነስተኛ መሬት ላይ የእርሻ ስራን በማከናወን ውጤታማ የሆኑት ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያና ቬትናም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን የተሻለ የመንግስት አመራርና ተነሳሽነት እንዲሁም ሌሎችም ግብአቶችን ተጠቅመው መሆኑ ይታወቃል። በአፍሪካ ግን የተለየ አከባቢያዊ ሁኔታ ስላለ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል። ተብለው የተጠየቁት የአለም አቀፍ ፈንድ ለእርሻ የተባለው ድርጅት ስራአስኪያጅ ሚኒስተር ካናንዋነዜ ሲመልሱ አፍሪካ በተትረፈረፈ የእርሻ መሬት ማለትም 60 በመቶ የሚሆን የዓለም ለእርሻ ተስማሚ የሆነ መሬት በአህጉሪትዋ እንደሚገኝ ለመስኖ የሚያገለግልም ውሃ በበቂ ደረጃ እንደሚገኝ ጠቅሰው እነኚህን የተፈጥሮ ሀብቶች በተጨማሪ ግብአቶች ማለትም በማዳበሪያና በምርጥ ዘር እንዲሁም በአነስተኛ ደረጃ መስኖ በመታገዝ ምርታማነትን በማሳደግ፣ በምግብ ራስን እንደሚቻል ጠቅሰው ለዚህ ደግሞ የመንግስት ፈቃደኝነት፣ መልካም አስተዳደር፣ ዲሞክራሲ፣ ሃሳብን በነፃነት መግለፅን፣ የተጠያቂነት አሰራር መኖር እንዳለበት አመልክተዋል። በተለይም የተጠያቂነት አሰራር ከሌላ እቅዱ ያለውጤት እንደሚጨናገፍ አስጠንቅቀዋል። በሌላም በኩል በኢትዮጵያ አብዛኛዎቹ ገበሬዎች ያላቸው መሬት ከአንድ ሄክታር ያነሰ ይህም በህዝብ ቁጥር እድገት ይበልጥ እየተበጣጠሰ እደሚገኝና በዚህ ሁኔታ ምርታማነትን እንዴት ማሳደግ እንደሚችል የተጠየቁት ስራአስኪያጇ ሲመልሱ ቀድሞ ጠቅሸዋለሁ በአፍሪካ የተትረፈረፈ የእርሻ መሬት አለ የመሬትን ጥቅም ባለማወቃችሁ ግን የውጭ ኢንቨስተሮች ሰፋፊ መሬቶችን በሊዝ ተቀራምተው የእርሻ ምርቶችን በመውሰድ እናንተ የእነርሱን ምፅዋት ትቀበላላችሁ ብለዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1017 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 950 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us