የአዲስ አበባ ቆሻሻ አወጋገድ መልካም እድሎችና ተግዳሮቶች

Wednesday, 04 June 2014 12:24

ከተማችንን ፅዱ ውብና አረንጓዴ እንዲሁም ለነዋሪዎችና በየጊዜው ወደ ከተማዋ ለሚመጡ እንግዶች ምቹ የመኖሪያና የስራ ቦታ ለማድረግ በርካታ ስራዎችን ማከናወን ያስፈልጋል። ዘመናዊ የከተማ ማስተር ፕላን በቅድሚያ ማዘጋጀት መተኪያ የማይገኝለት ተግባር ነው። ከዚያም የኢንዱስትሪ፣ የንግድ፣ የቢዝነስ፣ የመንግስትና የግል መስሪያ ቤቶች የአገልግሎት መስጫ ተቋማትና የመኖሪያ አካባቢዎች ተለይተው መዘጋጀትና መገንባት አለባቸው። ከመንገድ ግንባታዎች ጋር የጎርፍና የፍሳሽ መውረጃ ቦዮች በስርዓት ተዘርግተው በበቂ ሁኔታ አገልግሎት መስጠት አለባቸው። ነገር ግን የከተማዋ አመሰራረት የኋላ ታሪክ ሲቃኝ የተቆረቆረችው ከዚህ ተቃራኒ በሆነ በባህላዊና በወቅቱ ከነበሩት መንግስታት ፍላጎት አንጻር በመሆኑ በዚያን ጊዜ መከናወን የነበረባቸው ስራዎች ባለመሰረታቸው ችግሮቹ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፉ አሁንም ድረስ ለከተማዋ እድገት ማነቆ መሆናቸው ቀጥሏል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ በአዋጅ ቁጥር 15/2001 የተቋቋመ ሲሆን በተለይ የደረቅ ቆሻሻን ስብሰባ በማስወገድ ረገድ ኃላፊነት ተሰጥቶቷል። ቆሻሻን ከመኖሪያ ቤቶችና ከመንገዶች ላይ የሚሰበስቡና የሚያስወግዱ ሠራተኞችን መድቦ ባለው አቅም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

የኤጀንሲው የኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ባለስልጣን አቶ ታደለ ደመኮ እንደሚገልፁት በከተማው ከየቤቱ የሚወጣውን የደረቅ ቆሻሻ በየዕለቱ ለማንሳት 568 የፅዳት ማህበራት ተደራጅተው ስራቸውን እያከናወኑ ሲሆን ከእነኚህ በተጨማሪ 14 የግል የፅዳት ድርጅቶች በስራው ተሰማርተው አገልግሎት በመስት ላይ ይገኛሉ። በአስተዳደሩም በኩል በየዓመቱ በጀት እየተመደበ በመንግስታዊ መዋቅር አማካኝነት እንቅስቃሴ ይካሄዳል። ስራውን የሚመሩ ኃላፊዎችና አስፈፃሚ የሆኑ 4 ሺህ ሠራተኞች እስከታችኛው አካል ተመድበዋል። በያዝነው ዓመት የደረቅ ቆሻሻ ገንዳ ማመላለሻ ተሸከርካሪ እጥረት ለመፍተት በመጀመሪያ HC 50 መኪናዎች በ140 ሚሊዮን 120ሺህ ብር የተገዙ ሲሆን ከዚህ ጋር 10 የመንገድ ማፅጃ ተሸክርካሪዎችና ማሽነሪዎች በ30 ሚሊዮን ብር ተገዝተው ወደ ስራ እንዲሰማሩ ተደርገዋል። የገንዳ አቅርቦትን ለሟሟላት 500 ገንዳዎች ከሀገር ውስጥ ኩባንያዎች በ20 ሚሊዮን ብር ተገዝተው አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል።

ይህ በመንግስትና በሌሎች ተቋማት እየተከናወነ የሚገኘው ስራ በአዎንታዊ መልኩ የሚታይ ቢሆንም ከከተማዋ አወቃቀር፣ ከህዝብ ቁጥር እድገት፣ ከገጠር ከተማ ፍልሰት አንፃር እንዲሁም በድህነት ሳቢያ የጎዳና ተዳዳሪው ቁጥር ከእለት ወደ እለት እያሻቀበ በመሄድና በየቦታው ከመፀዳዳት አኳያ ሲታይ የፅዳት ስራው ገና “አባይን በጭልፋ” በሚል ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው። የፎርም ፎር ኢንቫይሮንሜንት የቅርብ ጊዜ ጥናት እንደሚያመለክተው በከተማችን 30 በመቶ የሚሆነው ነዋሪ የራሱ መፀዳጃ ቤት የለውም። ይህም የከተማው ጥጋ ጥግና ወንዛወንዝ ለብክለት ተገላጭ መሆኑን የሚያመለክት ነው። በአሁኑ ወቅት ሰዎች በኑሮ ውድነትና በቤት ኪራይ ንረት ለጎዳና ተዳዳሪነት ይዳረጋሉ። በመልሶ ማልማት መፈናቀልም ለጎዳና ህይወት የሚዳረጉ አልጠፉም። በልማት ሰበብ የፈራረሱ አካባቢዎች ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያነት መቀየራቸው ከተማውን የማስዋቡን ስራ ውሃ ቅዳ ውሃመልስ እያደረገው ነው። የኤጀንሲው መረጃ እንደሚያመለክተው በአዲስ አበባ ከተማ ከ3 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚኖር ሲሆን በየቀኑም ከ152ሺህ ህዝብ በላይ ከሌሎች አካባቢ ለተለያዩ ስራዎች ወደ ከተማዋ በመግባት ጉዳዩን ፈፅሞ ተመልሶ ይወጣል። በየቀኑም ከ5ሺህ ሜትር ኩብ በላይ ደረቅ ቆሻሻ ከየመኖሪያ ቤቱና ከማምረቻ ቦታዎች ይለቀቃሉ። ይህም ቆሻሻ ማንሳቱ ስራ ምን ያህል ከባድና ከአቅም በላይመሆኑን ከማመልከት በተጨማሪ በአካባቢ ላይ የሚያደርሰው ብክለትም የሚታለመውን ከተማዋን ለኑሮ ምቹ የማድረግ ጉዳይ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳረፈ ይገኛል። የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቱም ላይ የሚስተዋሉ እንከኖች አልጠፉም።

ከተማዋን ለማፅዳት የሚደረገው ጥረት በሚፈለገው ደረጃ ስራው አልተከናወነም። ከከተማችን ነዋሪዎች በተደጋጋሚ እየቀረቡ ያሉ ቅሬታዎች ውስጥ የተወሰኑትን በማንሳት የችግሩን አሳሳቢነት መረዳት አያዳግትም። ነዋሪው ከየቤቱ ለሚሰበሰበው ቆሻሻ ለሚሰጠው አገልግሎት ከተጠቀመበት የውሃ አገልግሎት ክፍያ አብሮ እየፈፀመ ቢሆንም በከፈለው መጠን ግን አገልግሎት አያገኝም ቆሻሻውን የማንሳቱ ስራ የሚቆራረጥ ከመሆኑ ባሻገር ለረጅም ጊዜም ሳይነሳ የሚቆይበት አጋጣሚ አለ። የደረቅ ቆሻሻ ገንዳዎች በወቅቱ ባለመነሳታቸው ለቀናት ሞልተው ቆሻሻ በዙሪያቸው እየተዝረከረከ የከተማዋን ገፅታ ከማበላሸት የጤና ችግር እያስከተለ ይገኛል። ይህ ብቻ ሳይሆን ከቁጥጥር ማነስ የተነሳ ቆሻሻ መድፋት በማይገባው ቦታ እየተደፋ የአካባቢ ጠረን ሲታወክ ይስተዋላል። ከዚህ አንፃር ከተማውን ለማፅዳት ምንም ያህል በጀት፣ ቁሳቁስና የሰው ኃይል ቢመደብ ስራው በተጠያቂነትና በኃላፊነት የሚከናወን ካልሆነ ጥረቱ ከድካም ባለፈው በውጤት መብቃቱ አጠራጣሪ ነው። በርግጥ በሀገራችን የሚገኙ መንግስታዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በአብዛኛው ማለት ይቻላል የመፈፀም ውስንነት ይታይባቸዋል። ኃላፊዎችና ሠራተኞች በቅድሚያ ስራቸውን በኃላፊነት እንዲወጡ የተቀጠሩበት ግዴታ እንደሆነ ሊያውቁት የሚገባ ሲሆን አገልግሎት የሚፈልገው ህብረተሰብም ግብር እንደመክፈሉ መጠን አገልግሎት የማግኘት መብት ያለው እንደሆነ ሊያውቁት ግድ ይላል። አገልግሎት ፈላጊውም መብቱን የመጠየቅ ባህሉን በማዳበር ስራዎች የሚከናወኑት በሁሉም ዜጎች ኃላፊነትና ተጠያቂነት መሆኑን ሊረዳው ይገባል።

የከተማው የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ከላይ የተጠቀሱት ውስንነቶች እንዳሉ እንደሚገነዘብ አቶ ታደለ ይገልፃሉ። እንደዛም ሆኖ ስራውን ለማቀላጠፍና ለማሻሻል ጥረት እያደረገ ነው። የቤት ለቤት የተቋማትና የድርጅቶችን የመንገድ ላይ ቆሻሻ አወጋገድን ለማሳለጥ የጥናትና የምርምር ስራዎችንና የአካባቢ ግምገማን ያካሂዳል። ከላይ ከተጠቀሱት በሰው ኃይል የፅዳት ስራውን ከማከናወን ጎን ለጎን ከአውሮፓ ተገዝተው በመጡ 10 ዘመናዊ ማሽን ተሸከርካሪዎች የመንገድ ማፅዳት ስራው ይከናወናል። ይህም በአጭር ጊዜ ብዙ ስራ ማከናወን ከማስቻሉም በላይ ስራው ከለሊት 10 ሰዓት እስከ ጠዋት 12 ሰዓት መሆኑ መንገደኛን በአካባቢ ያለ ሰው በአቧራ እንዳይታፈን አመቺ ሁኔታን ፈጥሯል። ቆሻሻን ወደ ውስጥ ከመዋጥ በተጨማሪ ማሽኖቹ አስፓልትን የማጠብ ስራ ያከናውናሉ ይህም የከተማዋን የፅዳትደረጃ ከሌሎች ደረጃቸውን ከጠበቁ ዓለም አቀፍ ከተሞች ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ይታመናል።

ለሾፌሮችና ለረዳቶቻቸው ተገቢው ስልጠና የተሰጣቸው ሲሆን ተሸከርካሪዎችም ሙሉ ኢንሹራንስ ተገብቶላቸዋል። ማሽኖቹም ከወጣው የአስፓልት መንገዶች ደረጃ ማለትም ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ አራት በተመደቡ ጎዳናዎች ስራቸውን ያከናውናሉ። ለጎዳናዎች ደረጃ አሰጣጥ መስፈርትን በተመለከተም አቶ ታደለ ሲገልፁ አሰራሩ ከፅዳት አወጋገድና ከገፅታ ግንባታ ጋር ተያያዥነት ያለው ነው። አብዛኛዎቹ አስፋልቶች ሰፊውን የዲፕሎማሲና የቢዝነስ ስራዎች በስፋት የሚከናወንባቸው የመሰብሰቢያ አዳራሾች ሆቴሎችና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የሚገኙባቸው ከቦሌ አየር ማረፊያ እስከ መስቀል አደባባይ አድርጎ በሂልተን እስከ ቤተመንግስት በቀለበት መንገድ በአፍሪካ ህብረት፣ ሜክሲኮ፣ ብሔራዊ ቴአትር፣ በቸርቸል ጎዳና፣ ፒያሳና አዳዲስ የተገነቡ መኖሪያ አካባቢዎች በደረጃ ውስጥ ተካተዋል። ከዚሁ ጋር በተጨማሪ አካባቢዎቹ በ10 ዞኖች ተከፍለዋል። ኤርፖርት ዞን፣ ጎተራ፣ ሜክሲኮ፣ አፍሪካ ህብረት፣ ፓርላማ፣ ቀበና፣ ፍልውሃ፣ መገናኛ፣ ፒያሳና ብሔራዊ ዞን ተብለው ተለይተው በ10 ማሽን መኪናዎች ይፀዳሉ።

እነኚህ አበረታች ስራዎች እየተከናወኑ ቢገኙም አንዳንድ ችግሮች መስተዋላቸው አልቀረም ከእነርሱም ውስጥ በተለይ ፅዳት በሚከናወንባቸው እንደ ቦሌ አካባቢ ለመዝናናት በሌሊት በአካባቢው የሚዘዋወሩ መኪናቸውን አቁመው በመጥፋት በስራው ላይ እውከት ሲፈጥሩ ተስተውሏል፡፤ በየመንገዶች ላይ በተለይ የተሻለ ኑሮና መደብ ያላቸው የሃይላንድ ፕላስቲክና ጠርሙሶችን መንገዶች ላይ በዘፈቀደ መጣላቸው በማሽን ለማፅደዳት ችግር ፈጥረዋል። በኮንስትራክሽን ምክንያት አሸዋና አፈር በየመንገዱ በገልባጭ መኪናዎች መበቱነም እንደችግር ተስተውሏል። ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋርም የመተግበር እቅድ ዘርግቶ እንቅስቃሴውን ቀጥሏል። የንግድ ማዕከላት በሆኑት በመርካቶ ከሚገኙና በአትክልት ስራ ካሉ ነጋዴዎች ማህበራት እንዲሁም ከእሁድ ገበያ ነጋዴዎችና በአዳራሽ ከሚሰሩ ሰራተኞች ጋር በማቀናጀት የአካባቢ የማፅዳት ስራ እየተከናወነ ነው። ሆኖም ግን በእነኚህ አካባቢዎች ለፅዳት ስራ መሟላት ያለባቸው ቁሳቁሶች በበቂ ሁኔታ አለማሟላታቸው በስራው ላይ ውስንነት እንደተፈጠረ የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልፃሉ።

የቆሻሻን የማስወገድ ስራ አካባቢን ከብክለት ከመጠበቅ በተጨማሪ ቆሻሻን ወደ ቀልዝ (ብስባሽ አፈር) በመለወጥ አካባቢን በጓሮ አትክልትና በዛፎች ለማልማት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚሰጥ ይታወቃል። በዚህ ረገድ ከላይ የተተቀሱት 568 የፅዳት ማህበራት በዘርፉ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ከየቤቱ የሚወጣው ቆሻሻ አስቀድሞ በመለየት ተመልሰው ጥቅም ላይ የሚውሉትን ለተቀባይ ድርጅቶች በማቅረብ ታድሰው ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚደረግ ሲሆን ይህም ለማህበራት አባላት የገቢ ምንጭ እያስገኘ ይገኛል። በተለይ በየቦታው የሚጣሉ የፕላስቲክ እቃዎች ባለመነሳታቸው በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ ሲሆን በተለይ ፕላስቲኩ ባለመበስበሱ አፈር አስፈላጊውን ኦክሲጅን እንዳያገኝ በማድረግ ጥፋት ያስከትላሉ። ተሰብስስበው ጥቅም ላይ ሲውሉ ግን ተመልሰው ታድሰው ጥቅም ከመስጠታቸው በተጨማሪ ተቆራርጠውም በጌጣጌጥ ስራ ስለሚያገለግሉ ለቆሻሻ አስወጋጆች ገቢ ያስገኛሉ። የቆሻሻ ብስባሽን ወደ ማዳበሪያነት የመቀየሩ ስራም በተለያዩ ማህበራት አካባቢ በተለይ በ3 ቁጥር ማዞሪያ በቀበና እንዲሁም በቄራ አካባቢ የሚገኙ በከተማ ግብርና የተሰማሩ ማህበራት ማዳበሪያውን በመጠቀም የተሻለ ምርት እያገኙ እንደሚገኝ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ግብርና ቢሮ ያወጣው መረጃ ያመለክታል። ከየቤቱ የሚወጡ ደረቅ ቆሻሻ በተለይ ገቢ ላላቸው ሰዎች ደኖችን ለማልማት የሚያስችል ቢሆንም ጥቅሙን ካለመረዳትና የስራው ባህል ባለመኖሩ የተነሳ እስካሁን የሚጠበቀውን ያህል ወደ ስራ አልተተገበረም።

     ደረቅ ቆሻሻ በአግባቡ ከተወገደና ከተያዘ ጥቅም የሚሰጠውን ያህል በየቦታው ተዝረክርኮ ሲጣልም የዚያኑ ያህል ጉዳት ማስከተሉ አይቀርም። በአሁኑ ወቅት በከተማችን ያለው ወቅት የዝናብ ነው። ከቤት ጣሪያም ሆነ ከከተማዋ ዳርቻ የሚመጣ የዝናብ ውሃ በስርዓት እንዲፈስ ቱቦዎችና ቦዮች ከቆሻሻ የፀዱ መሆን አለባቸው። በግዴለሽነት አስተዋሽ ሲያጡም ውሃ ከመውረጃ ቦዩ ወጥቶ በመፍሰስ አካባቢን ይበክላል። ትራስፖርቱን ያስተጓጉላል፣ አንዳንዴም የተሸከርካሪ አደጋን ያስከትላል። ስለሆነም በግዴለሽነት ቸል የሚባለው የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ከባድ ዋጋ ያስከፍላል። ወደ ከተማችን በየዕለቱ ወደ ደረቅ ቆሻሻነት የሚቀየር የጫት ምርት ከተለያዩ አካባቢዎች ይገባል። የሚገዛውም በውድ ዋጋ ነው። የጫቱ ገራባ ግን በዘፈቀደ የትም ይጣላል። በዚህ የተነሳ አካባቢ ይበከላል። ለቦይ መደፈንም መንስኤ ይሆናል። ይህ የጫት ገራባ ግን በስርዓት ከተያዘ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ሊሆን የሚችል ግብአት ነው። በአሁኑ ወቅት በከተማችን ተደራጅተው ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ሊሆን የሚችል ግብአት ነው። በአሁኑ ወቅት በከተማችን ተደራጅተው የማገዶ ቆጣቢ ምድጃና ከሰል አምራች ማህበራት ለከሰል ምርትነት በግብአትነት ከሚጠቀሙበት ውስጥ በየሜዳው እንደዋዛ የሚጣለው የጫት ገራባ ነው። በዚህ ረገድ ጎግል የተባለው እንዲሁም በቀጨኔ አካባቢ የሚገኙ የጭስ አልባ ከሰል አምራች ማህበራት በምሳለኔት የሚጠቀሱ ሲሆን ለበርካታ ወገኖች የስራ እድል ከመፍጠር ባሻገር የደን ውድመትን በመከላከል ረገድ የበኩላቸውን ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ። ከዚህ አንፃር ቆሻሻን ወደ ሌላ ምርት መቀየር እንዲሁም ለማዳበሪያነት መጠቀም ቆሻሻ በራሱ ገንዘብ ሊሆን እንደሚችል አመልካች ሲሆን ለጤና እና ለውበትም አስተዋፅኦው ቀላል አይደለም።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1087 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 920 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us