ትኩረት ለጂኦተርማል-ኢነርጂ

Friday, 04 October 2013 18:14

በአይቸው ደስአለኝ

በሀገራችን አብዛኛው ህዝብ ለቤት ውስጥ ምግብ ማብሰያ ለመሳሰሉት የሚጠቀመው ተፈጥሮንና አካባቢን በሚያወድመው በባዮማስ ወይም በደንና በእፅዋት ውጤቶች ከሚመነጭ ማገዶ ነው። ይህ በተለይ በገጠር ህብረተሰብ በስፋት ጥቅም ላይ ስለሚውል ዘርፈ ብዙ መዘዞችን ያስከትላል። ለአፈር ምርታመነት ከፍተኛ ሚና የሚጫወተው ናይትሮጂንና ፎስፈት መሰረቱ የዕፅዋት ቅጠላቅጠሎችና ብስባሾቹ ሲሆን ነገር ግን ይህ ለማገዶነት ስለሚውል አፈሩ ማግኘት የሚገባውን ንጥረ ነገር ስለማያገኝ የእርሻ ምርታማነት እንዲቀንስ አስተዋፅኦ ያበረከታል። የማገዶ ጭስም በቤተሰብ ጤና ላይ ጉዳት ከማስከተል አልፎ ለአካባቢ ብክለትም የራሱን ሚና ይጫወታል። ስለሆነም በተለይ ችግሩን ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ አማራጭ ኃይል ቆጣቢ ምድጃዎችን ከመጠቀም ባለፈ ታዳሽ የኢነርጂ ምንጭን መጠቀም ያስፈልጋል። ከዚህ አኳያ ታዳሽ የሆነውን የሃይድሮ ኤሌትሪክ ፓወር ለማበልፀግ በተለያዩ አካቢዎች የሚሰሩት ግድቦች እንደ አንድ ማሳያ የሚጠቀሱ ናቸው። ከዚህ ጎንለጎን በተለይ ከሰሜን እስከ ደቡብ ሀገራችን ለሁለት ሰንጥቆ በሚያልፈው የታላቁ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ በብዛት የሚገኘውን የከርሰ ምድር የእንፋሎት ኃይል (የጂኦተርማል ኢነርጂን) ለመጠቀም ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ ጥረት እየተደረገ የሚገኝ ሲሆን በተወሰነ መልኩም ጥቅም ላይ ውሏል። ለዚህ ዘርፍ ጥናትና ምርምር እንዲሁም የመሬት ቁፋሮ ስልጣን ለማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር በብቸኝነት የተሰጠ ሲሆን መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም የበኩላቸውን እገዛ ከተቋሙ ጋር በተዋዋሉት መሰረት ያከናውናሉ።

ዶ/ር ሊኒሀንስ መንግስታዊ ባልሆነ የGIZ መስሪያ ቤት የፐሮግራም ዳይሬክተር ናቸው። ከሰሞኑ “Talk energy” ተብሎ በሚታወቀውወርሃዊ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ለሙያተኞች ድርጅታቸው በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የጂኦተርማል ኢነርጂን ለማጎልበት እየተገበረ የሚገኘውን ስራ አብራርተዋል። እንደእርሳቸው ገለፃ በኢትዮጵያ የተትረፈረፈ የጂኦተርማል ሀብት ቢኖርም እስካሁን ግን በአብዛኛው ህዝብ በትክክል አይታወቅም። ስለሆነም ይህን ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል ድርጅታቸው በጥናትና ምርምር በቁፋሮ እንዲሁም መንግስትን በማማከር ታዳሽ ሃይልን በተመለከተ ሊያሰሩ የሚችሉ ህጎች እንዲወጡ የበኩሉን ግፊት እያደረገ ይገኛል።

የጂኦተርማል ኃይል በሰው ልጅ ታሪክ ከብዙ ዘመናት ጀምሮ ለተለያዩ ጉዳዮች ጥቅም ላይ ውሏል ዋናው የኃይል ምንጭም በመሬት ሆድ ዕቃ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በአብዛኛው ለመሬት መንቀጥቀጥ በተጋለጡ የቴክቶኒክ ከርሰ ምድር ባላቸው አካባቢ ይገኛል። በምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ከሚገኙት ቀይ ባህር ኤርትራ፣ ሰሜን ሶማልያና በኢትዮጵያ በሃይል ምንጬ የሚገኝ ሲሆን በሀገራችንም በአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ስፋት ከሰሜን እስከደቡብ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት በአስተማማኝ መልኩ ጥቅም ላይ የዋለውና እየተስፋፋ የሚገኘው ጂኦተርማል በኦሮምያ ክልል በላንጋኖ ሃይቅ አጠገብ የሚገኘው የአሉቶ ማዕከል ነው። ይህ አሉቶ ኃይል በአሁኑ ወቅት 7 ሜጋ ዋት የኤሌትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ሲሆን ወደፊት አቅሙን ወደ 73 ሜጋዋት ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ዶ.ር ሊኒ አስረድተዋል። የጂኦተርማል ኃይል በሁለት መልኩ ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን አንደኛው እንፋሎት በቀጥታ ወደ ጀነሬተር እንዲገባ በማድረግ የኤሌትሪክ ኃይል ያመነጫል ከዚያም ቢኬብሎች አማካኝነት ወደ አጠቃላይ የኃይል ክምችት እንዲገባ ተደርጎ ወደ ተጠቃሚው እንዲደርስ ይደረጋል። ሌላው የእንፋሎት ኃይል በቀጥታ በቱቦ አማካኝነት ወደተጠቃሚዎች በመዘርጋት ለቤት ውስጥ ማሞቂያ፣ ማቀዝቀዣ እና ለመሳሰሉት ጉዳዮች ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል። በአሁኑ ወቅት ኃይሉን ወደ ውጭ በተለይም ወደ አውሮፓ ገበያ በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያገኙ በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ያሉ ሲሆን ሰሜን አፍሪካ ሀገሮች ግብፅ፣ ሊቢያ ቱኒዝያና አልጀሪያ በቱቦ ሜደተራኒያን ባህር አሻግረው ለአውሮፓ ገበያ ያቀረባሉ።

እንደ ሙያተኛው ገለፃ በኢትዮጵያ በንጉሱ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ የጂኢተርማል አሰሳና ቁፋሮ የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1969 ዓ.ም ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከሰሜን እስከ ደቡብ በተዘረጋው የስምጥ ሸለቆ አካባቢ አስራ ስድስት አስተማማኝ የኃይል ማበልፀጊያ አካባቢዎች ስራው እየተከናወነ ይገኛል። በተለይ በበስተደቡብ የስምጥ ሸለቆው አካባቢ የሚካሄዱ ስራዎች የቦታው ሙቀት ከሰሜኑ የሚቀንስ እንዲሁም ለብሔራዊው የኢነርጂ ሙቀት ቅርበት ስላለው አዋጭነቱ ተመራጭ ነው። የዚህ ታዳሽ ኃይል ቁፋሮች 3 ሺህ ሜጋ ዋት ለማመንጨት የሚያስችል እምቅ ኃይል በከርሰ ምድር ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ይህም ከሌሎቹ ታዳሽ ኃይሎች ጋር ሲነፃፀር የማምረቻ ዋጋው ይቀንሳል። በርግጥ በመጀመሪያ ደረጃ ጥናቱ ሲካሄድ የአየር ቅኝት ሲካሄድና ተመሳሳይ ስራዎች ጠቀም ያለገንዘብን የሚጠይቁ ቢሆንም አንዱ ቦታው ታውቆ ጥልቅ ጉድጓድ ተቆፍሮ ወደምርት ከተገባ የሚጠይቀው ዋጋ አነስተኛ ነው።

ከላይ ከተጠቀሱት 16 ዋነኛ ቦታዎች ውስጥ ኢነርጂው ተረጋግጦ እስከግማሽ ድረስ ቁፋሮ የተካሄደባቸው ቦታዎች 6ናቸው ከወራት በኋላም ስራው ተጠናቆ ወደ ማምረት ይገባል። በሌሎች አስር ጣቢያዎችም የቅኝት ስራ እየተከናወነ ሲሆን በቀጣይም ወደ ቁፋሮ እንደሚገባ ዶ/ር ሊኒ ሀንስ ተናግረዋል። እንደርሳቸው ገለፃ ስራው ከመጀመሩ በፊት የጂኦፊዚካል፣ የጂኦተርማልና የጂኦኬሚካል ሙያተኞች በመጣመር በአካባቢውና በአፈሩ ላይ ጥናት ያካሄዳሉ ከዚያም ከአፈሩ ላይ የፊዚካልና የኬሚካል ጥናት ከተደረገ በኋላ መስክ ላይ በመሄድ አስተማማኝ ነው በሚባለው ቦታ ላይ የቁፋሮ ስራው ይጀመራል። በአሁኑ ወቅት በአለም ላይ የጂኦፊዚክስና ኬሚካል ጥናት ለማካሄድ የሚያስችሉ በኮምፒውተር የሚታገዙ በጣም ዘመናዊ መሳሪያዎች ያሉ ቢሆንም ዋጋቸው እጅግ ውድ ነው። ይህም ስራውን ለማከናወን በሚያስችለው ውጭ ላይ ከፍተኛ ጫናን እያሳረፈ ይገኛል። መንግስት በሚከተለው ፖሊሲም በማናቸውም የኢነርጂ ስራዎች ላይ ማለትም ለሃይድሮ ኤሌትሪክ ለንፋስ ለሶላርና ለጂኦትረማል የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚው የተሰጠው ኃላፊነት ምርቱን አምርቶ መሸጥን አያበረታታም። በዚህም የተነሳ አብዛኛዎቹ የውጭ ኢንቨስተሮች በዘርፉ ለመሰማራት ያላቸው ፍላጎት በጣም ዝቅተኛ ነው። በርግጥ ከላይ የተጠቀሱትን መሳሪዎችን የሚጠቀሙ በርካታ የውጭ ኩባንያዎች በሌሎች ሀገሮች ምርቱን አምርተው ራሳቸው ለገበያ ማቅረብ ይቻላሉ። ይህ ሁኔታ በሀገራችን አለመኖር የተሻሉ ቴክኖሎጂዎችም ወደ ሀገርእንዳይገቡ የራሱን ተፅእኖ አሳርፏል።

በኦሮምያ ክልል በአሉት አካባቢ የሚካሄደው የጂኦተርማል ልማት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቁፋሮ የተገባው እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ ሲሆን ስራው በታለመለት እቅዱ ሲከናወን ቆይቶ በ1990ዎቹ 7.2 ሜጋ ዋት የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጨት ተችሏል። በአሁኑ ወቅት በዚያው አካባቢ ምርቱን ለማሳደግ የሚያስችል ፕሮጀክት ተቀርፆ ስራው እየተከናወነ ሲሆን በዚህ አማካኝነትም በ2014 ምርቱን ወደ 75 ሜጋ ዋት ከፍ እንዲል ይደረጋል። ከዚህ ሜጋ ዋት ጎን ለጎንም ሞቃት ውሃ ማለትም ለህክምና እና ለማሳጅ የሚያገልገል፣ እንፋሎት እንዲሁም የኤሌትሪክ ኃይል በማመንጨት ለተጠቃሚው እንዲቀርብ ይደረጋል። እንደ ዶ/ር ሊኒ ገለፃ ይህ ስራ እንደተጀመረ ከሁለት ዓመታት በኋላ ለማጠናቀቅ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ቴክኒካዊና ቢሮክራሲያዊ ችግሮች የተነሳ ሊስተጓጎል ችሏል። በአሁኑ ወቅት የሚመረተው ኃይል ወደዋናው ቋት የሚገባበት የመስመር ዝርጋታ ስራውም አብሮ እየተከናወነ ይገኛል።

በሌላም በኩል በርካታ የአጂኦፊዚካል ጥናቶች እንደሚያረጋግጡ በርካታ የጂኦተርማልና የሌሎች ንጥረ ነገሮች መገኛ ነው ተብሎ የሚታወቀው በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በአፋር ክልል የሚገኘው ስምጥ ሸለቆ ነው። ይህ የዳለሎልን የሚቀልጥ ድንጋይን ጨምሮ ሌሎችንም በከርሰ ምድር የሚገኙ ሀብት የያዘው ሞቃታማውና በረሃማው አካባቢ የተለያዩ ቁፋሮዎች እየተካሄዱበት ሲሆን ከእርሱም ውስጥ በጥጥ እርሻ ቦታነቱ የሚታወቀው የተንዳሆ አካባቢ በዋነንነት ይጠቀሳል የGIZ መስሪያቤትም በቦታው ከ1990ዎቹ ጀምሮ 6 ጉድጓዶችን በመቆፈር ፍለጋውን በማጧጧፍ ላይ ይገኛል። እንደ ሙያተኛው ገለፃ የአካባቢው የሙቀት መጠን ከፍተኛ መሆን ስራውን አስቸጋሪ አድርጎታል። ይሁን እንጂ በሰራተኞቹ ትጋት ከመሬት በታች እስከ 500 ሜትር ድረስ ተቆፍሮ ስራው እየተከናወነ ይገኛል። ከዚሁ ጎንለጎንም በሌሎች ሶስት ቦታዎች የአፈርና የኬሚካል ምርመራ ተደርጎ አስተማማኝ መሆኑ ስለተረጋገጠ የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ ስራዎችን ለመጀመር ዝግጅቱ ተጠናቋል። ስራውን ይብጥ ስኬታማ ለማድረግም ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ተመርጠው ስራውን እንዲረከቡ ጨረታ ወጥቶ ለአሸናፊው ለማስረከብ ጊዜ እየተጠበቀ ነው።

ከላይ ከተጠቀሱት እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ በመንግስታት በዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ኤክስፐርቶች ስራዎቹ የሚሰሩ ሲሆን በኦሮምያ ክልል ከቢቲ በተባለው የስምጥ ሸለቆ አካባቢም ከሚገኙ 16 ጣቢያዎች ውስጥ ቱሉ ሞያ በሚባል አካባቢ ለግል ኩባንያዎች የሽርክና ድርሻ ተሰጥቶ ወደ ስራ መገባቱን ዶ/ር ሊኒ አስረድተዋል። ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የጂኦተርማል ኢነርጂ በአብዛኛው በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በስተደቡብ የሚገኘው በተለምዶ የሃይቆች አካባቢ ሲሆን የሰሜኑ ደግሞ በርሃማው አፋር ክልል ነው።

በዚህ በርሃማ ክልል በተለይ በሞቃትነቱ በዓለም የሚታወቀውና ከባህር ወለል በታች 100 ሜትር ዝቅ ብሎ በሚገኘው በዳሎል ሰባት የግል ኩባንያዎች የጂኦተርማል ኃይልን ለማጎልበት ወደ ስራው የተሰማሩ ሲሆን በአንፃራዊነትም የተሻለ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ችለዋል። በዕለቱ ጽሁፋቸውን ያቀረቡት ዶ/ር ሊኒ በዳሎል ከመሬት እየቀለጠ ወደ ምድረገፅ የሚወጣውን ማግማ በሌላ ኃይል ጥቅም ላይ ማዋል አይቻልምን ተብለው ተጠይቀው የዚህ ዓይነቱ ማግማ በአለም በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ እንደሚገኝ ተናግረው በአሜሪካ ወደ ሌላ አይነት አማራጭ ኃይል በመቀየር ምርምር እተካሄደበት እንደሆነ ጠቅሰው ስራው ግን ቴክኖሎጂንና የገንዘብን አቅም በእጅጉ እንደሚፈታተን አመልክተዋል።

በዳሎል አካባቢ ሰባት የግል ኩባንያዎች ወደ ስራ በተሰማሩበት አካባቢ ከ500 እስከ 600 የሚሆን ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ኤሌትሪክን ማምረት እንደሚቻል የተረጋገጠ ሲሆን እንደመንግስት እቅድም ስራው ተጠናቆ ወደ ማምረት የሚገባው በ2018 ነው። እዛው በአፋር ክልል ተንዳሆ አካባቢም አንድ አዲስ በተጀመረ ጉድጓድ 75 ሜጋዋት የሚያመነጭ ጂኦተርማል የሚመረተ ሲሆን ስራው በ2018 እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል። ከዚህ ሌላም በአባያ ሀይቅ 120 ሜጋዋት የሚያመነጭ ጣቢያ በ2018 እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቅ ሲሆን ስራውም በተያዘለት እቅድ እየተከናወነ ነው። በመጨረሻም ዶ/ር ሊኒ ወደፊት በኢትዮጵያ የተትረፈረፈውንየጂኦተርማል ሀብትለመጠቀም የሀገር ውስጥ አቅምን ማጎልበት እንደሚገባ፣ መንግስት ከፍተኛ በጀት መመደብ እንደሚገባውና ለግሉ ዘርፍ ሰፋ ያለ የመጫወቻ ሜዳ እንዲዘረጋለት አሳስበዋል።

Last modified on Friday, 04 October 2013 18:16
ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1269 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 912 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us