You are here:መነሻ ገፅ»ህይወት
ህይወት

ህይወት (55)

በአስናቀ ፀጋዬ

       

በሀገራችን መደበኛ ካልሆኑ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ውስጥ አንዱ እድር ነው። እድሮች ብዙ ጊዜ በአንድ አካባቢ በጉርብትና የሚኖሩ ሰዎች የጋራ ችግሮቻቸውን በተለይም በሃዘን ጊዜ ለመረዳዳት በመሰባሰብ የሚያቋቁሙት መኀበራዊ ተቋም ነው። እድሮች በመኅበራቸው አማካኝነት በየወሩ ገንዘብ በማዋጣት ከማኅበርተኛው አባል አንዱ በሞ ሲለይ ወይም ከቤተሰቡ ውስጥ አንድ ሰው አደጋ ሲያጋጥመው ለዚሁ አላማ ከሚሰበሰበው ገንዘብ ወጪ በማድረግ እንዲጠቀሙበት ይደረጋል።

የሰው ልጅ ወደዚህች አለም መጥቶ በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ ሀዘንና መካራ፣ ተድላና ደስታ፣ ማግኘትና ማጣት ይፈራረቅበታል። እነዚህን ሁሉ ከስተቶች እየታገለ በሚኖርበት ወቅት ሁሉ ችግሩ እያሸነፈው ይመጣል። ይህንንም በመገንዘብ መልካም ኑሮውን የሚቃረኑ ችግሮች ሲያጋጥሙት በጋራ መቋቋም አማራጭ የማይገኝለት መሻገሪያ መሳሪያ በህብረት መቋቋም ነው። በኢትዮጵያም የእድር ማህበራት ዋንኛ ዓላማ በጋራ በመሆን በሀዘን ጊዜ ከመረዳዳት ባለፈ ቤተሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ጠቃሚ አንቅስቃሴዎችን ማድረግ ነው።

እድሮች ልክ እንደእቁብ ሁሉ ባህላዊ የገንዘብ ተቋማትና የረጅም ጊዜ መኀበራት ናቸው። በዚህም ምክንያት የኛ ኢትዮጵያውያን ማህበራዊ እሴቶችን ለምሳሌ በሀዘን ጊዜ መረዳዳትና ችግሮችን በጋራ የመካፈል ባህል የሚንፀባረቅባቸው ተቋማትም ጭምር ናቸው።

ይህ ብቻ ሳይሆን በተለይ አሁን ማህበራዊ እድገታችንን ተከትሎ እድሮች በልማቱም በኩል የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ቀላል የሚባል አይደለም። ለምሳሌ እድሮች በተለያዩ የልማት ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ ያደርጋሉ። በማህበራቱ አማካኝነት በአካባቢያቸው ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ገንዘብ ወጪ በማድረግ በውሃ አቅርቦት፤ መንገድ ስራ፣ የጋራ መፀዳጃ ቤቶችንና የመሳሰሉትን ስራዎች ያከናውናሉ።

እድሮች የኢኮኖሚ አቅማቸውን ከፍ ለማድረግ የተለያዩ የገቢ መፍጠሪያ አማራጮችን ቀይሰው ይንቀሳቀሳሉ። በመዲናችን አዲስ አበባም አንዳንድ እድሮች ገቢያቸውን ለማስፋት አክሲዮኖችን ይገዛሉ፣ አዳራሾችን ያከራያሉ፣ ወፍጮ ቤት በመስራት ተጨማሪ ገቢ ይፈጥራሉ።

ዛሬ በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ የአኗኗራችንን ዘመናዊነትና ከጊዜው ጋር መሻሻልን ተከትሎ እነዚህ ማህበራዊ ተቋማት በይዘት፣ በአይነት፣ በቅርጽና፣ በአደረጃጀት እንዲሁም በአገልግሎት እየተሻሻሉና እየተለወጡ መጥተዋል። ለምሳሌ ቀብር አስፈፃሚ ድርጅቶች በሀገራችን እምብዛም ያልታወቁና ያልተለመዱ ነበሩ። ነገር ግን አሁን በየቦታው የቀብር አስፈፃሚ ድርጅቶች እየበዙ መጥተዋል። ታዲያ የነዚህ ቀብር አስፈፃሚ ድርጅቶች እየበዙ መምጣት አንድም በተለይ እድር የሌላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች መጥቀም አልያም በእድር ማህበር ሰበብ ሊቃጠል የሚችለውን ጊዜ ማዳን ነው። ምክንያቱም በእድር ማህበራት ከሄድን አንድ የእድሩ አባል በሞት ሲለይ ወይም ከቤተሰቡ ውስጥ አንዱ አደጋ ሲደርስበት የአስክሬን ሳጥን መግዥያ ገንዘብ ከማህበሩ ወጪ ሆኖ፣ ድንኳን ተተክሎ፣ ሰው ተጠራርቶ፣ ዘመድ አዝማድ ተሰባስቦ ነው እንግዲህ ስርዓተ ቀብሩ የሚፈፀመው።

በተቃራኒው ግን በቀብር አስፈፃሚ ድርጅቶች የሚሰራው ስራ ግን ከዚህ በተለየ መልኩ ነው። ምናልባት ጎረቤት መጥራት ላያስፈልግ ይችላል። ነገር ግን ጥቂት የሀዘንተኞች ቤተሰብ ከተሰበሰበ ሌላው ስራ በነዚሁ የቀብር አስፈፃሚዎች ስለሚከናወን ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች አይኖሩም። በርግጥ በቀብር አስፈፃሚ ድርጅቶች የቀብር ስነ-ሥርዓትን ማካሄድ ለማህበራዊ ህይወት የሚሰጠው ዋጋ ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ያሳድራል። ለምሳሌ አብሮ ከጎረቤት ጋር ሀዘንን መካፈል፣ እርስበእርስ መፅናናት፣ መረዳዳትና የመሳሰሉት ማህበራዊ እሴቶች እዚህ ጋር ላይኖሩ ይችላሉ።

ነገር ግን እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት በእድር ማህበራት ውስጥ በሀዘን ጊዜ የሚንፀባረቁ ባህላዊ እሴቶቻችን ለምሳሌ መረዳዳት፣ አንዱ ሌላውን ማፅናናት፣ ማበረታታትና የመሳሰሉት ሳይነኩ በተለይ በሴቶ በኩል የሚከናወኑ ስራዎችን እንሰራለን ከሚሉ ድርጅቶች ውስጥ አንዱ እናት የሴቶች እድር አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ነው።

“ይህ ድርጅት ከስምንት አመት በፊት በጥቂት ወጣቶች ተሞክሮ በጊዜው ስራው በህብረተሰቡ ብዙም ያልተለመደ መሆኑና እምብዛም ተቀባይነት ማግኘት ባለመቻሉ ምክንያት ውጤታማ ሳይሆን ቢቀርም ነገር ግን አሁን በያዝነው 2007 ዓ.ም ስራውን እንደገና በመጀመር ውጤታማ እየሆነ እንደመጣ” ከድርጅቱ መስራቾች ውስጥ አንዱ የሆኑት አቶ ዘነበ በለጠ ይናገራሉ።

በዚህም መሰረት ድርጀቱ ስራው መልካምና አዋጭ መሆኑን በመገንዘብ እንዲሁም በተለይ እድር የሌላቸውን ሰዎች ለማገልገልና፣ የጊዜን ጉዳይ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዲህ አይነቱን ስራ ለሰዎች ለማስለመድ አላማ በማድረግ በ50,000 ብር ከፒታልና በ17 ሰራተኞች ስራውን እያከናወነ ይገኛል።

ከሌሎች የእድር ማህበራትም ልዩ የሚያደርገው በውስጡ የሚሰሩት ሰራተኞች ከዚህ በፊት ስራ ያልነበራቸውና ነገር ግን ይህን ሃሳብ በማፍለቅና በመሰባሰብ ሰዎች ሀዘን ሲደርስባቸው በስልክ በመደወል አገልግሎቱን ሲፈልጉ እቤታቸው በመገኘት የሴት እድር የሚሰጠውን አገልግሎት ሁሉ ማድረግ መሆኑ ነው።

የአገልግሎቱን አይነትና አሰጣጥ በተመለከተ የእናት ሴቶች እድር አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ወ/ሮ መንበረ ታምራት ሲገልፁ “ሰዎች ሀዘን ሲደርስባቸው ለኛ ይደውሉልናል፣ በሚሰጡንም አድራሻ እቤታቸው ድረስ በመገኘት እንደፍላጎታቸው፣ እንደአቅማቸውና እንደትዕዛዛቸው እኛ የእቃና የጉልበት አገልግሎት እንሰጣለን። የአገልግሎት አይነታችንም በሴቶች በኩል በሀዘን ጊዜ የሚከናወኑ ስራዎችን ሁሉ መስራት ነው” ይላሉ፡፡

በአሁኑ ሰዓት ጥሩ ተቀባይነትንና ምላሽን ከህብረተቡ እያገኘሁ ነው የሚለው እናት የሴቶች እድር አገልግሎት ድርጅት ክፍያን በተመለከተ እንደአገልግሎቱ አይነትና እንደተጠቃሚው ፍላጎት የሚለያ ቢሆንም በትንሹ ለአንድ አገልግሎት 7000 ብር እንደሚያስከፍሉ ይገልፃሉ። ይህን በተመለከተ ዋና ስራ አስኪያጇ ሲናገሩ “አንድ አንድ ቦታ ሰልስት ሁለት ቀን ሌላ ቦታ ደግሞ ሶስት ቀን ሊሆን ይችላል። ስለሆነም በዚሁ መሰረት ቀኑ ከፍ ባለ ቁጥር የአገልግሎት ክፍያውም የዚያኑ ያህል እንደሚጨምር” ያስረዳሉ። አክለውም “ለኛ የሴት እድራቸውን ወደ ድርጅታችን ያዞሩ ደምበኞች አሉን። ያ ማለት እህትማማችነታቸው በሀዘን ጊዜ መረዳዳታቸው እንዳለ ሆኖ ነገር ግን ሀዘን ሲያጋጥማቸው በሴቶች የሚሰሩ ስራዎችን ለኛ ይሰጡናል። ይህም የሚሆነው በየወሩ ከሚያዋጡት ብር ላይ ለኛ በመክፈል ነው”

አንድ የሴት እድር ሊኖረው የሚችለውን እቃ ሁሉ አጠቃሎ የያዘው ድርጅቱ፤ በአንዳንድ እድሮች ውስጥ አቅመ ደካማ ሴቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዲሁም ከኑሮ ውጣ ውረድ፣ ልፋትና ጊዜ አኳያ በሀዘን ጊዜ የማጀቱን ስራ በመስራት የሰውን የስራ ጫና ማቃለል ተቀዳሚ አላማቸው እንደሆን የድርጀቱ መስራቾች ይናገራሉ፡፤ ከዚህም ጋር በተያያዘ የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ መንበረ ታምራት እንደሚሉት “ይሄ የኛ ስራ አብሮ መተዛዘኑንና መረዳዳቱን በምንም መንገድ አይቀንሰውም። ምክንያቱም ሰው ሀዘን ሲደርስበት ስራውን ትቶ የማጀት ስራ ላይ ጊዜውን እንዳያጠፋ እኛ ክፍተቱን ስለምንሞላ ነው” እንደሳቸው አባባል “በሀዘን ጊዜ በተለይ ሴቶች ላይ የስራ ጫና ስለሚበዛ ይህንን ስራ መሸፈን ቀላል አይደለም” ይላሉ።

አኗኗራችን ዘመናዊነትን እየተላበሰ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ እድሮችም ከዘመኑ ጋር አብረው እየዘመኑ መጥተዋል። የእድር ድርጅቶች በእንዲህ አይነት መልኩ መቋቋምና አገልግሎት መስጠት ይበል የሚያሰኝ ተግባር ቢሆንም ቅሉ በጊዜ ሂደት ግን ማህበራዊ እሰቶቻችንና ባህሎቻችን ተፅዕኖ እንዳይደርስባቸውና ከእነካቴውም እንዳይጠፋ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ምንስ ይጠበቅብናል? ይህ ሁሉም ሊመልሰው የሚገባ ጥያቄ ነው። 

በአስናቀ ፀጋዬ

ያለሁት አውቶብስ ውስጥ ነው። አውቶብሷ ጢም ብላለች። ወደ መርካቶ ነው የምትጓዘው። ከአውቶብሱ ኋላ ሁለት ተማሪ ወጣቶች ቆመዋል። የግል ጨዋታ የያዙ ይመስላሉ። አንደኛው የዘመኑን ቃሪያ ሱሪ ወይም ስኪኒ (ከላይ ወደታች እየጠበበ የሚሄድ ሱሪ) አይነት ለብሷል። ቀበቶ የታጠቀ ቢሆንም፤ ሱሪው ግን ከወገቡ ወደ መቀመጫው ለመውረድ እየታገለ ነው። ይህን የተመለከቱ አንድ በእድሜ ገፋ ያሉ አሮጊት “አዬ የዘንድሮ ወጣት ሱሪውንም በደምብ መታጠቅ አቃተው?” አሉና የጀመሩትን ንግግር አቋረጡ። ይህን የሰሙት ሁለቱ ወጣቶች በሴትየዋ ንግግር በመገረም ትንሽ አልጎመጎሙ። አሮጊቷ ቀጠለ አደረጉና “ምን አለ እስኪ ሱሪውን መታጠቅ ካቃተህ አንደኛህን ባዶህን ብትሄድ እኮ ይሻላል” ሲሉ በአውቶብሱ ውስጥ የተሳፈረው ሰው ሁሉ አተኩሮ ይመለከታቸው ጀመር። ሴትየዋ እንደዚህ በድፍረት መናገራቸው ሳይገርማቸው አልቀረም። ተማሪዎቹ ግን እሳቸው ዘንድ ያልደረሰ ነገር ግን የታፈነ ስድብ ተሳደቡ። በርግጥ ሌላው ይህን ነገር ተመልክቶ ዝም ይላል ወይም በሆዱ ይሳደባል። እሳቸው ግን ስላላስቻላቸው አወጡት፣ ተናገሩት፣ ተነፈሱት፣ አዎ ይህን አይነቱን ከወግና ባህል ያፈነገጠ አለባበስ እንዲሁ በዝምታና በቸልታ ማለፍ አልፈቀዱም።

አሁን የምዕራባውያን ተፅዕኖ ባህላችንን እየገረፈው በመምጣቱ ዛሬ በተለይ በከተማችን በወጣቱ ተዘውትረው የሚለበሱ ልብሶች ያሳቅቃሉ። ወጣት ሴቶቻችን እምብርታቸውንና ጡታቸውን የሚያጋልጥ ልብስ፤ ወንዶች ደግሞ ከበስተኋላ መቀመጫቸው እስኪታይ ድረስ ሱሪ ዝቅ አድርጎ መልበስ እየተለመደ የመጣ ባህል ሆኗል።

ልጃገረድ ሴቶቻችን በይበልጥም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሴቶች ፀጉራቸውን ሳይፈሽኑ፣ ቅንድብ ሳይቀነደቡ፣ ከንፈራቸውን ሳያቀልሙ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ዘበት እየሆነ መጥቷል።

ወጣት ተማሪ ወንዶቻችንም እንደዚሁ ፀጉርን አንጨብርሮ፣ አንገት ላይ ሰንሰለት አንጠልጥሎ፣ ጆሮ ላይ ሎቲ አድርጎ ወደ ትምህርት ቤት መምጣት ልማድ ሆኗል።

በርግጥ ይህ ጉዳይ ለወጣት ተማሪዎቻችን የዘመናዊነት መገለጫ ቢመስላቸውም፤ ከእኛ ኢትዮጵያውያን ባህልና ወግ ያፈነገጠ ተግባር እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ሲባል ግን እንደው ነጮቹ ያደረጉት ነገር ሁሉ ይቅርብን ማለት ሳይሆን ቢያንስ ከእኛ ባህል ጋር የሚቀራረበውን ወስደን ብንጠቀም የተሻለ ስለሚሆን ነው።

ምዕራባውያን ስለአለባበሳቸውና ድርጊታቸው የራሳቸው የሆነ ምክንያት ይኖራቸዋል። በርግጥ ይህን የባህል ወረርሺኝ እኛን በመሳሰሉ አዳጊ ሀገራት በመልቀቅ እነሱ የራሳቸውን የፖለቲካና፣ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያደርጉት ጥረት ቀላል የሚባል አይደለም።

በነገራችን ላይ ይህ የአለባበስ ጉዳይ በከተማችን ወጣት ወንዶችና ሴቶች ላይ የሚንፀባረቅ ቢሆንም፤ በተለይ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎችን በእጅጉ እየተፈታተነ ይገኛል።

ትምህርት ቤቶቻችን ለነገይቱ ኢትዮጵያ እድገት አስተዋፅኦ ያደርጋሉ ተብለው የሚጠበቁ የተማሩ ኃይሎች የሚፈሩበት ተቋም ነው። ትምህርት ቤቶቹ በስነ-ምግባር የታነፁና ማኅበረሰብን በቀጣይ ሊጠቅሙ የሚችሉ ሰዎች መፍለቂያ ቦታም ጭምር ነው። ተማሪዎች በእውቀትና በስነምግባር ታንፀው ሲወጡ ማኅበረሰቡን በቅንነትና በታማኝነት ያገለግላሉ። ከተማሪዎች መልካም የስነ-ምግባር ደምቦች መካከል ደግሞ አንዱ የደንብ ልብስን በአግባቡና በስርዓቱ መልበስ ነው።

የትምህርት ቤቶች የደንብ ልብስ ተማሪዎች የሚማሩበትን ትምህርት ቤት መለያና መኩሪያም ጭምር ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን የደንብ ልብስ ሁሉንም ተማሪ በአለባበስ እኩል የሚያደርግና በመካከላቸውም አንድነትን የሚፈጥር ነው። ታዲያ ይህ መሆኑ እየታወቀ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የሚታየው ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው።

ወደ አንድ ትምህርት ቤት እያመራሁ ነው። የአራት ኪሎን የድል ሐውልት አደባባይ አልፌ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ፋኩልቲ በኩል ሚኒሊክ መሰናዶ ትምህርት ቤት ደጃፍ ላይ ደርሻለሁ። ከደጅ የተወሰኑ አርፋጅ ተማሪዎችን ተመለከትኩ። ወደ አንዱ ጠጋ አልኩ፤ ተማሪ ቢንያም ይባላል። (በዚህ ጽሁፍ ስሙ የተቀየረ) የሚኒሊክ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነው። የለበሰው ሱሪ የትምህርት ቤቱ ደምብ ልብስ ቢሆንም፤ እንደ ዘመኑ ነው (ሲኪኒ)። ከላይ ነጭ ሸሚዝ አድርጓል። ከሸሚዙ ላይ የሚደረበውን ሰደርያ በእጁ አጣጥፎ ይዞታል። ለምን እንዳለበሰው ጠየኩት። የሰጠኝ መልስ፤ “ባክህ ይሞቃል፤ ሸሚዙንም አለማውለቄ እኔ ሆኜ ነው” የሚል ነበር። እና ወደ ትምህርት ቤት እንድትገባ ይፈቅዱልሃል? ስል በድጋሚ ጠየኩት። “ያው ወደ ውስጥ ስገባማ እለብሰዋለሁ፤ እስክገባ ነው” አለኝ። እንደ ተማሪ ቢኒያም የደንብ ልብሳቸውን በስርዓቱ የማይለብሱ ብዙ ተማሪዎች ይኖራሉ ብዬ ገመትኩ።

አሁን ወደ ትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ እየገባሁ ነው። በቀጥታ ያመራሁት ወደ ርዕሰ መምህሩ ቢሮ ነበር። አቶ ተገኔ መንግስቱ ይባላሉ፤ የምኒሊክ መሰናዶ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ናቸው። እኔም በትምህርት ቤቱ ውስጥ የታዘብኩትን መነሻ በማድረግ ተማሪዎች የደንብ ልብሶቻቸውን በተለይ (ከላይ የሚለበሰውን) በመተው ለምን ቲሸርት እንደሚለብሱ እንዲሁም የደንብ ልብሱ የትምህርት ቤቱ መለያ እንደመሆኑ መጠን ቲ-ሸርቱ በተማሪዎች ተዘውትሮ መለበሱ የትምህርት ቤቱን ምስል አያጠፋም ወይ? ስል ያቀረብኩላቸው የመጀመሪያ ጥያቄ ነበር። ይህን አስመልክቶ ርዕሰ መምህሩ ሲመልሱ፤ “ትምህርት ቤቱ የራሱ የሆነ ቋሚ የደንብ ልብስ አለው። ነገር ግን ቲ-ሸርት የሚያደርጉት ተማሪዎች ሁሉም ሳይሆኑ የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆኑና ቲ-ሸርቱን ለማሳተም ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች የሆኑ ብቻ መሆናቸውን የሚናገሩት ርዕሰ መምህሩ፤ እነዚህ ቲ-ሸርቶች ሲታተሙ በተማሪዎች ፓርላማ በኩል እውቅና ያላቸውና ትምህርት ቤቱም የተስማማበት ጉዳይ ነው” ይላሉ።

“ይህ ብቻ ሳይሆን ቲ-ሸርቶቹ ሲታተሙ በትምህርት ቤቱ እውቅና ስለሚያገኙና ተማሪዎቹ ለመታሰቢያነት ብቻ የሚጠቀሙት ስለሆነ በትምህርት ቤቱ ላይ ምንም አይነት ተፅዕኖ እንደማያሳድርና የተለመደ አሰራር እንደሆነ” ገልፀዋል።

“ነገር ግን በቂ ክትትል ካልተደረገበት የትምህርት ቤቱን ገፅታ ሊያበላሽ የሚችል ነገር ሊፈጠር እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልፀዋል።”

በደምብ ልብስ አለባበስ ስርዓት ላይስ በተማሪዎች በኩል ያሉ ችግሮች ምንድን ናቸው? እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችስ አሉ ወይ? ለአቶ ተገኔ ያነሳሁት ሁለተኛ ጥያቄ ነበር። እንደሳቸው ገለፃ “በትምህርት ቤታቸው ውስጥ በአለባበስ ዙሪያ ችግሮች አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ቢሆንም፤ በር ላይ በቂ ክትትልና ቁጥጥር ስለምናደርግ፣ ለተማሪዎች በስነ-ዜጋና ስነ-ምግባር ክበብ አማካኝነት የደንብ ልብሶቻቸውን በአግባቡ እንዲለብሱ ግንዛቤ ስለምንሰጥ ችግሩ ያን ያህል የጎላ አይደለም” ይላሉ። አክለውም “በአለባበሳቸው ወጣ ያሉ ተማሪዎች ቢያጋጥሙን እንኳን ጠበቅ ያለ እርምጃ እንደሚወስዱ ይገልፃሉ።”

ምንም እንኳን በሚኒሊክ ትምህርት ቤት በተማሪዎች የደንብ ልብስ አለባበስ ዙሪያ ያን ያህል የጎላ ችግር ባይኖርም፤ ከዚህ በተቃራኒ ግን በሌሎች ትምህርት ቤቶች የግል ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ብዙ ችግሮችን ማንሳት ይቻላል። ለምሳሌ አንዳንድ ተማሪዎች በደምብ ልብሶቻቸው ላይ በእስክርቢቶ ወይም በቀለም የተለያዩ ጽሁፎችንና ስዕሎችን መሳል፣ በደምብ ልብሳቸው ላይ ሌላ ተጨማሪ ይዘት ያላቸውን ነገሮች መጣፍ፣ ማሰፋትና የደንብ ልብሱን ሌላ የቅርፅ ይዘት በማላበስ ማስፋት ከችግሮቹ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ለእነዚህ ሁሉ ችግሮች ደግሞ ትምህርት ቤቶች፣ ወላጆች እንዲሁም መምህራን የድርሻቸውን ይወስዳሉ።

    ማኅበረሰብን በእውቀት የመለወጥና ሀገርን የመገንባት ኃላፊነት የተጣለበት የተማረ የሰው ኃይል የሚገኘው ከትምህርት ቤቶች እንደመሆኑ መጠን፤ ተማሪዎች በስነ-ምግባር የታነፀና በእውቀት የተገነቡ ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ የትምህርት ቤቶቻቸውን ሕግና ደምብ ሊተገብሩ ግድ ይላል። በተለይም እነዚህ ተማሪዎች የትምህርት ቤታቸውን የደንብ ልብስ በአግባቡ መልበሳቸው እንደቀላል ጉዳይ የሚታይ ባለመሆኑ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ጨርሰው በቀጣይ ወደመሃበረሰቡ በመቀላቀል የተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ ሲሰማሩ ሕግን አክብረው ስራቸውን እንዲሰሩ፣ ስርዓትን እንዲላበሱ እንዲሁም መልካም ስነምግባር እንዲኖራቸው የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ላቅ ያለ ነው።

በአስናቀ ፀጋዬ 

ይኸውላችሁ በቀደምለት ወደ ሥራ ለማቅናት ታክሲ ተሳፈርኩ። የተሳፈርኩበት ታክሲ ገና ባለመሙላቱ አውታንቲው በታክሲው መስኮት አንገቱን አስግጎ “ሃሎ! ትሄዳላችሁ? ሁለት ሰው የሞላ” ይላል። ታክሲው በየመንገዱ በመቆሙ የተማረረ አንድ ተሳፋሪ “ሾፌር ቶሎ ቶሎ እንሂድ እንጂ? እነሱ’ኮ ፒያሳ ናቸው አይሄዱም” አለ አውታንቲው ሁለት ሰዎችን ወደታክሲው ለማስገባት የሚያደርገውን ትግል ተመልክቶ። የዚህን ተሳፋሪ ንግግር ስሰማ አዕምሮዬ ውስጥ አንድ ነገር ብልጭ አለ። አዎ በሰው ማንነት ውስጥ ግለኝነት እንደሚንፀባረቅ። ስለሆነም ከዚህ ሰው ንግግር በመነሳት ከግለኝነት ጋር በተያያዘ የሚሰማኝንና የሚታየውን ገሃድ እነሆ ለመፃፍ ብዕሬን አወጣሁ።

ከከተሞች መስፋፋት እንዲሁም ከኑሮአችን እድገትና ኢኮኖሚያዊ መሻሻል ጋር በተያያዘ ሰዎች ለገንዘብ የሚሰጡት ዋጋ እየጨመረ መጥቷል። ግዜያቸውን ስራ ላይ እንዲያውሉ አስገዳጅ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መጥተዋል። ስራቸውን ለመስራት እራሳቸውን ከቴክኖሎጂ ጋር ማዛመድ ግድ ሆኖባቸዋል። በዚህም ምክንያት ግለኝነት በተለይም በእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ በሰዎች የማኅበራዊ ህይወታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል። ለዚህም ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል።

እስቲ አስቡት ዛሬ መንገድ ላይ በግለሰቦች መካከል የሆነ ፀብ ቢፈጠረና ወደ ግጭት ቢያመሩ ማነው ግለሰቦቹ ሳይጎዳዱ የሚያስታርቀው? ማነውስ ኧረ በገላጋይ! የሚለው? ከዚህ ይልቅ እኔ ምን አግብቶኝ በሰው ፀብ፣ በኋላ ልገላግል ገብቼ አጉል ብሆንስ፣ አርፌ ልጆቼን ላሳድግ፤ ከመሞት መሰንበት ይላል እንጂ።

ምን ይሄ ብቻ አይበለውና የጤና ችግር ገጥሞህ መሬት ላይ ወድቀህ ብትንፈራፈር ከንፈሩን መጦ የሚያልፍ እንጂ አይዞህ እኔን ብሎ አቅፎና ደግፎ ተገቢውን እርዳታ የሚያደርግልኝ ሰው አገኛለሁ ብለህ እንዳታስብ።

እንደው ምንአልባት የኮንደሚኒየም ቤት ዕጣ ደርሶህ ከገባህ ቡና ይጠሩኛል ብለህ ካሰብክ ከንቱ ድካም ነው ቢቀርብህ ይሻላል። ምክንያቱም ሰው በቤቱ የራሱን ደስታ መፍጠርና ማጣጣም እንጂ አንተ ቡና ጠጣህ አልጠጣህ ግድ የለውም።

አንተ ዛሬ በጠዋት ማልደህ ወደ ሥራህ ለመሄድ አውቶብስ ላይ ስትጋፋ አልያም ረጅም ሰዓት ሰልፍ ላይ ቆመህ ትራንስፖርት ስትጠብቅ፤ ወይ ያለው ማማሩ! አንዱ ምን የመሰለች አውቶሞቢል ይዞ ሚስቱን ከጎኑ አድርጎ በአጠገብህ ቢፈስ እንዳይገርምህ እሱ የመኪናው ባለጌታ ነው። ከአንተ ጋር ቢያንስ ሁለት ሰው መጫን ይችላል። ምን ታደርገዋለህ አይሰማህም፣ አይመለከትህም፣ አያሳፍርህማ ስለዚህ አትጓጓ።

ዛሬማ ቀብር አስፈፃሚ ድርጅቶች እንደ አሸን በፈሉበት በአሁኑ ጊዜ ስንቱ ነው በእድር ማኅበር ስርዓተ-ቀብር የሚፈፅመው? እንዲያውም ኧረ የዘመናዊነት መገለጫ እየሆነ መጥቷል። ይህ ብቻ ሳይሆን በእድር ሰበብ ሰው ከማንጋጋት በቀብር አስፈፃሚ ድርጅቶች ቀብርን ማስፈፀም ቀበሩ ቀልጣፋም ያማረም ይሆናል ብለው ሽንጣቸውን ይዘው የሚከራከሩም አይጠፉም።

የሚደንቅ እኮ ነው! ለምሳሌ አንድ በኑሮ ደህና የሚባል ቤተሰብ ውስጥ በተለይ ማታ ማታ የግለኝነት ድራማዎችን መታዘብ ይቻላል። አባት ሶፋ ላይ በኩራት ተቀምጦ ቡናውን እየጠጣ ከላፕቶፑ ጋር ይፋጠጣል። መኝታ ቤት እናት ቅንጡ ስልኳን ይዛ ፌስቡክ ወይም ሌላ ዓይነት ማኅበራዊ ድረገፅ ታፍተለትላለች። ልጆችም እንዲሁ በሞባይል ስልክ ወይም በኮምፒዩተር ጌሞች ላይ ራሳቸውን ይጠምዳሉ። ታዲያ በዚህ መሀል እናት ከልጆቿ ጋር፣ አባት ከሚስት ጋር ወይም እናትና አባት ከልጆቻቸው ጋር ውይይት፣ ንግግር፣ ጨዋታ፣ ስለውሎ ምናምን ቅብጥርሶ አያደርጉም ምክንያቱም ከዚህ ይልቅ የኛው ይበልጣል።

ድሮ ድሮማ ልጆች በአንድ መአድ ቀርበው እየተሻሙ ይበሉ ነበር። እናትና አባትም እንደዚሁ። አዎ ድሮማ ሞባይልም የለ ኮምፒዩተርም የለ ስለዚህ እናትም፣ አባትም ልጆችም ስለውሏቸው ይጨዋወቱ ነበር ወይ ግለኝነት!

የእኛ የኢትዮጵያውያን የጋራ እሴቶቻችን ለምሳሌ አብሮ መብላት፣ መጠጣት፣ ችግሮቻችንን በጋራ የመፍታትና የመረዳዳት ባህላችን እውነት በሰዎች የግለኝነት ባህሪይ ምክንያት ተፅዕኖ እየተደረገበት ነው?፣ ግለኝነት እውነት መጥፎ ገፅታ ብቻ ነው ያለው ወይስ በጎ ነገሮችም አሉት? ግለኝነት በራሱ አሁን ያለንበትን ማኅበረሰብ ይገልፀዋል? ለእነዚህና እነዚህን ለመሳሰሉት ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ጥልቅ እውቀት ይኖራቸዋል ብዬ ከገመትኳቸው ሰዎች መካከል ወደ አንዱ ስልክ ደወልኩ። ያለማንገራገር ፍቃድ አገኘሁና ለመነጋገር ቀጠሮ ያዝኩ።

አቶ ነቢል አብዱልቃድር ይባላሉ በICS (International Community School) የስነ-ልቦና ባለሙያና በዘርፉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ድህረ-ምረቃ ተማሪ ናቸው። ከላይ ላነሳኋቸው ጥያቄዎች መልስ ለመሻት ወደእሳቸው በቀጠሮዬ መሰረት አመራሁ። በፈገግታ ተቀበሉኝ ጨዋታችንን ጀመርን። እንደመንደርደሪያ ለአቶ ነቢል ያነሳሁት የመጀመሪያ ጥያቄ ስለግለኝነት ምንነት ነበር።

“ግለኝነት ከተለያዩ አቅጣጫዎችና ሁኔታዎች አንፃር ሊተረጎም ይችላል። ነገር ግን በአጠቃላይ ግለኝነት ማለት የማኅበረሰብን ጥቅም ከማስቀደም ይልቅ ለራስ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት ወይም ማስቀደም ማለት ነው። የግለኝነት አንዱ ምንጭም ራስ ወዳድነት ነው። ነገር ግን ደረጃው ይለያይ እንጂ ሁሉም ሰው ራስ ወዳድ ነው። ምክንያቱም የሰው ልጅ ራስ ወዳድ መሆኑ ተፈጥሮአዊ ሐቅ ነውና።

“ይህ ሲባል ግን ግለኝነት በራሱ መጥፎ ጎን ብቻ አለው ማለት አይደለም። ለምሳሌ የራስን ጥቅም ማስቀደም ከኢኮኖሚ አንፃር በጎ ነገር አለው። ምክንያቱም ግለሰባዊ ጥቅምን እያስከበርን በሄድን ቁጥር በኢኮኖሚ አካባቢ፣ ማኅበረሰብ፣ ኅብረተሰብ ብሎም ሀገር ጠንካራ እየሆነ ይሄዳል። የግለሰብ ስኬት የማኅበረተሰብ ስኬት ነው። ምክንያቱም ማኅበረሰብ የግለሰብ ጥርቅም በመሆኑ ሀገርም በኢኮኖሚ ያድጋል።”

“የሰውን ጥቅም ነጥቆ የራስ ማድረግ ስግብግብነት ነው” የሚሉት የስነ ልቦና ባለሙያው፤ “በሰዎች ውስጥ የሚታየው የግለኝነት ባህሪ ወደ ስግብግብነት የሚያመራ ከሆነ ግን የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ስለሆነም ሰው ግለኛ እየሆነ በሄደ ቁጥር ማንም ለማንም አያስብም። የእርስ በርስ ግንኙነትም ሊኖር አይችልም። በዚህም ምክንያት ሰው ማኅበራዊ እንሰሳ እንደመሆኑ መጠን ግለኝነቱ እያመዘነ በሄደ ቁጥር ከማኅበረሰቡ የሚፈለገውን ጥቅም እያጣ ይሄዳል።”

“ግለኝነት በሃገራችን ነባራዊ ሁኔታ በተለይም በምንኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ እየተንፀባረቀ ስለመምጣቱ ብዙ ማሳያዎችንና መገለጫዎችን ማንሳት ይቻላል። ሰው ግላዊ ባህሪይ እንዲኖረው ተፅዕኖ እያሳደሩ ከመጡ ሁነቶች አንዱና ዋነኛው Globalization (ልዑላዊነት) ነው። ለምሳሌ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ኅብረተሰቡ የተለያዩ ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን የማግኘትና የመጎብኘት እድሉ የሰፋ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ የውጪውን ባህል እንደወረደ ሳይመርጥ፤ ይጠቅመኛል ይጎዳኛል ሳይል ይቀበላል። የእነሱን አኗኗር፣ አመጋገብ፣ ዘመናዊ ባህል ይላበሳል። በዚህም ምክንያት የእኛ ማኅበረተሰብ የጋራ ባህል (Collective Culture) ያለው መሆኑ ቢታወቅም በግለኝነት ተፅዕኖ ውስጥ ይወድቃል።”

የስነ-ልቦና ባለሙያው ከሰጡኝ መረጃ በመነሳት፣ ከግለኝነት ጋር በተያያዘ በእኛ ማኅበረተሰብ አኗኗር፣ አመጋገብ እንዲሁም ባህል ላይ ይህ ነው የማይባል ለውጦች እየታዩ መጥተዋል። በተለይ በአሁኑ ጊዜ ሰዎች ከቴክኖሎጂ፣ ከእቃ ጋር ያላቸው ግንኙነት እየጨመረ መጥቷል። በዚህም ምክንያት ሰዎች ከማኅበራዊ ህይወት ይልቅ ግለኝነትን እየመረጡ መጥተዋል። 

በአስናቀ ፀጋዬ         

 


መዲናችን አዲስ አበባ እነሆ ከተቆረቆረች 127 ዓመታትን አስቆጥራለች። ይህች በእድሜ አንጋፋ የሆነችው ከተማችን የአፍሪካ ህብረት ድርጅት ዋና መቀመጫ እንዲሁም የበርካታ ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶችና የብዙ ሀገራት ኢምባሲ መገኛም ጭምር ናት። ይህ ብቻ ሳይሆን በተለይ አሁን ኢኮኖሚያዊ እድገቷን ተከትሎ ብዛት ያላቸውን የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ ላይ ትገኛለች።

ከተማዋ ከምስረታዋ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ የተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁነቶችን አሳልፋች። በተለይ ዛሬ ከተማዋ ከአራቱም አቅጣጫዎች እየሰፋችና መሠረተ ልማቷም በእጅጉ እየተስፋፋ ይገኛል።

በዚህ ሂደት ታዲያ ከከተማዋ እድገትና ስፋት ጋር ተያይዞ የነዋሪ ብዛት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ይገኛል።

ከዚህ በተጨማሪም የቆሻሻ ይዘት የሚወሰነው እንደህብረተሰቡ አኗኗር ሁኔታ፣ ባህል፣ የአየር ፀባይ፣ የኑሮ ደረጃና የስራ ስምሪት ዘርፍ እንደመሆኑ መጠን በከተማዋም ያለው ቆሻሻ በየጊዜው በአይነትና በበዛት እየጨመረ መጥቷል። ይህን ተከትሎም የህብረተሰቡ የቆሻሻ አያያዝ፣ አሰባሰቡና አወጋገድ ሁኔታም ብቃት ያለው መሻሻል አላሳየም።

ስለሆነም የችግሩን አሳሳቢነትና በተለይ በህብረተሰቡ ጤና ላይ እየደረሰ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲሁም በከተማዋ ውበት ላይ የሚፈጥረውን መጥፎ ገፅታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ የመልሶ መጠቀምና ማስወገድ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የፅዳት አስተዳደር ምክትል ስራ አስኪያጅ የሆኑትን አቶ ታደለ ዱመኮን አነጋግረን ስለቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ችግሮች መንስኤና ችግሮችን ለመቅረፍ ስለተወሰዱ የመፍትሔ አቅጣጫዎች የሰጡንን ምላሽ ለአንባቢ በሚመች መልኩ እንደሚከተለው አቅርበናል

የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ዋና ዋና ችግሮች ምንድን ናቸው?

አቶ ታደለ ዱመኮ እንደተናገሩት ለዚህ ችግር እንደዋነኛ መንስኤ የሚታየው በተለይ በከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የሰው ብዛት ሲሆን ለህዝብ ብዛቱ መጨመር ደግሞ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በንግድና በተለያየ ምክንያት ወደ ከተማዋ የሚፈልሰው ህዝብ ራሱ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው። በዚህም ምክንያት የህዝቡ ብዛትና የከተማዋ የመጸዳጃ ቤት አለመመጣጠን ሰው በየመንገዱ እንዲፀዳዳ እድል ይፈጥራል።

ሌላው እንደ ሁለተኛ መንስኤ የሚወሰደው በህብረተሰቡ ዘንድ የግንዛቤ እጥረት መኖሩ ነው። ይህም የሚመነጨው ህብረተሰቡ በራሱ ጽዳቱና ጤናው የኔ ነው ብሎ አለማሰቡ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም በከተማዋ በቂ የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች በበቂ ሁኔታ አለመስራት እንዲሁም በህብረተሰቡ ዘንድ ግዴለሽነትና ማንአለብኝነት በራሱ ሌላኛው መንስኤ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ከሕግ አንጻር የተወሰዱ እርምጃዎች ምንድን ናቸው?

በዚህ ረገድ የጽ/ቤቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ እንደገለፁት ቅጣትን በተመለከተ በ1996/13 የወጣ ሕግ ቢኖርም ከቅጣት አኳያ የተወሰደ ርምጃ እንደሌለና ነገር ግን መጀመሪያ በህብረተሰቡ ዘንድ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል።ከዚህ በተጨማሪም ደንቡን ተፈፃሚ የሚያደርገው የደንብ ማስከበር ጽ/ቤት እንደመሆኑ መጠን ከጽህፈት ቤቱ ጋር የሁለትዮሽ እቅድ አዘጋጅተው መፈራረማቸውንና ወደተግባርም ለመግባት እንዳቀዱ ጠቁመዋል።

ለችግሩ የተቀመጡ የመፍትሔ አማራጮች?

ይህን ሰፊና አንገብጋቢ የከተማዋን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ የፅዳት ኤጀንሲው አማራጭ መፍትሔዎችን እንዳስቀመጠ ጠቁመው በተለይ የችግሩን መንስኤ ማጥናትና መመርመር ቀዳሚው ተግባር እንደሆነ ገልፀዋል። በመሆኑም ከውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ጋር በመተባበር በከተማዋ ከ1000 በላይ የመንገድ ዳር ሽንት ቤቶችን ለማስገንባት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

ለውጦች ይኖራን?

ህብረተሰቡ በቆሻሻ አወጋገድ ዙሪያ ግንዛቤውን እንዲያሰፋ በኤፍ ኤም 98.1 የሬዲዮ ጣቢያ ላይ በየሳምንቱ ፕሮግራሞች እየተዘጋጁ ይቀርባሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በ36 ቱም ወረዳና በ10ሩም ክፍለ ከተማ የቤት ለቤት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተከናውነዋል። ከዚህ በተጨማሪም በኤጀንሲው ደረጃ ፕሮጀክት ተቀርፃ ዘጋቢ ፊልሞች፣ ፎቶዎችና ብሮሸሮች ተዘጋጅተው ለህብረተሰቡ የሚቀርቡበት መንገድ መመቻቸቱን ምክትል ሥራ አስኪያጁ ያስረዳሉ።

ከላይ ከተጠቀሱት ነጥቦች አንጻር ካለፈው ዓመት ይልቅ በዘንድሮ የተሻለ ለውጥ እየታየ መምጣቱንና ለውጡም በብዙ መንገድ ሊገለፅ እንደሚችል ጠቅሰው።

    ይህን መሰረት በማድረግም ከተማችን አዲስ አበባ በ2012 ዓ.ም ጽዱና የአፍሪካ ሞዴል ከተማ እንደትሆን ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትና በተለይ ደግሞ ህብረተሰቡ የቆሻሻ አወጋገድ ዙሪያ ግንዛቤውን እንዲያሰፋ እንደሚደረግ ጨምረው ገልጸዋል።

ወጣት ባህሩ ሰለሞን      

መፅሐፍት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ልክ እንደሌሎች መሠረታዊ ነገሮች በአውደ ርዕይ መልክ መቅረብ ጀምረዋል። ባለፈው የገና በዓለም ኤግዚቪሽን ማዕከል የመፅሐፍ አውደ ርዕይ እንደ አማራጭ ቀርቦ ነበር። ይህን አዲስ ነገር ይዞ የመጣው ደግሞ በመፅሐፍ አቅርቦትና አሳታሚነት ዘርፍ የተሰማራው ወጣት ባህሩ ሰለሞን ይሰኛል። ይህ ወጣት በያዝነው ዓመት ብቻ ከ10 ያላነሱ ደራሲያንን መፅሐፍት ለአንባቢያን እንዲቀርቡ ከማስቻሉም በተጨማሪ በመሰል አውደ- ርዕይዎች ላይ በቀጣይ የመሳተፍ ሃሳብ እንዳለው ነግሮናል። ወጣቱ ስለመጣበት የህይወት መንገድና በሥራዎቹ ዙሪያ ጥቂት ቆይታ አድርገናል።

ሰንደቅ፡- ከቤተሰቦችህ ጋር ከነበረህ የሆቴል ቢዝነስ ወደመፅሐፍት ሥራው እንዴት ልትመጣ ቻልክ?

ባህሩ፡- እንደሚታወቀው ሆቴል በምግብ አቅርቦቱ የሰዎችን የምግብ ፍላጎት የምትሞላበት ነው። መፅሐፍት ደግሞ ልክ እንደሆዳችን ሁሉ ለአእምሯችን ብልፅግና በእጅጉ የሚያስፈልጉ ነገሮች በመሆናቸው ወደዚህ ፊቴን አዙሬያለሁ ማለት ነው። በልጅነቴ መፅሀፍትን ማንበብ ፈልጌ የተቸገርኩ በመሆኑ ወደዚህ ስራ ስመጣ አንዱ አላማዬ መፅሐፍትን ማድረስ ነው።

ሰንደቅ፡- ከሆቴል ንግድ ወደመፅሐፍት ስራ ለመምጣት የግል ህይወትህ ተፅዕኖ ያለበት ይመስለኛል። ለመሆኑ ስለመፅሐፍት ያለህ ልምድ እንዴት ነበር?

ባህሩ፡- በልጅነቴ ምናልባት እኔ የአርሶ አደር ልጅ ስለሆንኩኝ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ መፅሐፍትን ማግኘት አልችልም ነበር። ምክንያቱም ተወልጄ ያደኩት ከዳንግላ ከተማ 5 ኪ.ሜ ወጣ ብላ የምትገኝ አካባቢ ነበር። ከ8ኛ ክፍል በኋላ ወደከተማ ገብቼ ስለነበር የምማረው በዛው አካባቢ ከአንዳንድ መምህራንና ልጆች መፅሐፍ እየተዋስኩ ነበር። በተለይ ግን የማልረሳው 10ኛ ክፍል ስደርስ የአማርኛ መምህራችን አንድ ልቦለድ አንብበን ስናበቃ አሳጥረን ታሪኩን እንድንተርክ የሚደረግበት አጋጣሚ ነበር። ያ ሁኔታ ደግሞ መፅሐፍን በደንብ የማንበቡን አጋጣሚ የፈጠረልኝ ነበር ማለት እችላለሁ። የሚገርምህ ልጅ እያለሁ ማንበብ ብፈልግም የማነበው ነገር የለም። ከአዲስ አበባ ተነስተህ ማርቆስ እስክትደርስ አንድ መፅሐፍት ቤት ነው ያለው። ያ ነገር አሁንም እንደዚያው ነው። በ1993 ዓ.ም ባህርዳር ገባሁ፤ ከዚህ ጊዜ በኋላ ግን አብዛኛው ህይወቴ ከመፅሐፍት ንባብ ጋር የተያያዘ ነው።

ሰንደቅ፡- ምን አይነት መፅሐፎችን መርጠህ ታነባለህ?

ባህሩ፡- የታሪክ መፅሐፍት ደስ ይሉኛል። ወጥ ልቦለዶችና ወጎችንም ማንበብ አልጠላም። ምናልባት እኔ ብዙም የማልመርጣቸው የስነ-ልቦና መፅሐፍትን ነው። በተለይ ስኬትን እና ገንዘብን ወዲያው ማግኘት የምትችልባቸውን መንገዶች እንጠቁማለን የሚሉ መፅሐፍት አይመቹኝም። እንደኔ እምነት ስኬት ራሱን ችሎ፤ ጥረት አድርገህ በረጅም ጊዜ የሚመጣ ነገር ነው ብዬ ነው የማስበው። ከዚህ ውጪ ያሉ መፅሐፍትን አነባለሁ።

ሰንደቅ፡- ካነበብካቸው መፅሐፍት ውስጥ በተለይ የምታስታውሰው ይኖራል?

ባህሩ፡- መፅሐፍቶች ሁሉ የየራሳቸው ታሪክ አላቸው። ግን ለእኔ አሁን ድረስ ሳስበው የሚያሳዝነኝና የማልረሳው መፅሐፍ “አይ ምፅዋ” የሚለው መፅሐፍ ነው፡ ይህ መፅሐፍ 17ሺህ የደርግ ሰራዊት በተወሰኑ ቀናት ስለማለቃቸው የሚተርክ ነው። ይህ ነገር በሁለት ወንድማማቾች ጦርነት ውስጥ ይህን ያህል ሰው ስለመፈጀቱ ሳስብ በጣም ነው የሚደንቀኝ። ስለዚህም ጦርነቱ አላስፈላጊ ነበር ሁሉ ብዬ አስባለሁ። ለዛም ይሆናል ይህንን መፅሐፍ በተለይ የማስታውሰው እንጂ ያነበብኳቸውን መፅሐፍት ታሪክ በፍፁም አልረሳም።

ሰንደቅ፡- ምን ያህል መፅሐፍትን አንብበሃል?

ባህሩ፡- መገመት ያስቸግረኛል። በተለይ ከ1996 እስከ 1999 ዓ.ም ድረስ ብቻዬን እኖር ስለነበር ቢያንስ በሳምንት ውስጥ ሁለት ሶስት መፅሐፍትን አነብ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ትዳር መጣ፤ ልጆች መጡ የንባብ ሂደቴ በነበረበት ሊቀጥል አልቻለም። ያም ሆኖ ሳላነበ ውዬ አላድርም።

ሰንደቅ፡- ብዙዎች ስለንባብ ጥቅም ይናገራሉ፤ አንተ ከማንበብህ ምን አገኘህ?

ባህሩ፡- ህይወት አግኝቻለሁ። ነገሮችን በተለያዩ መንገዶች እንዳይ ረድቶኛል። ማንበብ ማለት ከመማርም በላይ ማወቅ ነው። አንዳንዴ መማር ትርጉም አይኖረውም። እያነበብክ ራስህን ከማህበረሰብና ከዓለም ጋር የማታገናኝ ከሆነ መማር ትርጉም አይኖረውም። ቅድም እንዳልኩት አባቴ ገበሬ ነው። በእጅ አሸራው ነው የሚፈርመው። ግን መቼ አርሶ፣ መቼ እንደሚዘራ፣ መቼ እንደሚኮተኩት፣ መቼ እንደሚያርም፣ መቼ እንደሚሰበሰብና እንደሚወቃ በደንብ ያውቃል። አንድ ሰውም ተምሮ በአንድ “ፕሮፌሽን” ስራ ብቻ ተከልሎ ከተቀመጠ ከእኔ አባት በምንም አይለይም። ጎን ለጎን መፅሐፍትን ማንበብ የሚችል ከሆነ ግን ከኔ አባት በላይ ይችላል ብዬ ነው የማስበው።

ሰንደቅ፡- ወደመፅሐፍት ቢዝነሱ ስትገባ እንዳሰብከው ሆኖልሃል?

ባህሩ፡- አሁን ባለበት ሁኔታ እውነቱን ለመናገር ዘርፉ አትራፊ አይደለም። ይሄን ነገር ደግሞ ገና ሳልገባበትም አውቄዋለሁ። ነገር ግን ተስፋ አለኝ እየተሻሻለ ይመጣል። ዘርፉ ለምን አላደገም? የፀሐፊያኑ ችግር ምንድነው? የሚሉትን ነገሮች ለማየት እየሞከርኩ ነበር። የመፅሐፍት ነጋዴዎች ውስን ናቸው። ውስን ከመሆናቸው የተነሳ መፅሐፍት አንባቢያን ወዳሉበትና ወደሚፈልጉበት አካባቢ አልሄደም። እኔ ወደ ዘርፉ ስገባ ያሳስበኝ የነበረው ደራሲያኑን እንዴት አገኛለሁ የሚለው ነበር። እድሜ ለሚዲያው አግኝቻቸዋለሁ። አሁን ጥያቄው በብቃት የማከፋፈሉ ላይ ነው። እኔ ለምሳሌ ወደ ክፍለ ሀገር ለመላክ እጠቀምበት የነበረው አሰራር ትንሽ ኋላ ቀር ነው። እንዲሻሻል በህብረት እየሰራን ነው።

ሰንደቅ፡- መፅሐፍትን በመደብርና በአዟሪዎች እጅ ከመሸጥ በተጨማሪ በአውደ-ርዕይ ላይ ማምጣት ተጀምሯል። በተለይም በዚህ በገና ኤከስፖ አንተ ፈር ቀዳጅ ሆነህ ታይተሃል እንዴት ደፈርክ?

ባህሩ፡- አውደ-ርዕይዎች በየወቅቱ ይዘጋጃሉ። በተለይ በኤግዚቢሽን ማዕከል ብዙ ይካሄዳል። በዚህ ፕሮግራም ላይ ከትናንሽ ቁሳቁሶች እስከቤት እቃዎችና እስከ መኪና ድረስ የሚቀርቡበት ነው። ታዲያ እኛስ መፅሐፍትን ይዘን ለምን አንገባም ስል አሰብኩ። እናተርፋለን፣ አናተርፍም እርሱ ሌላ ጥያቄ ነው። ሰው እዛ ሲመጣ ሊበላ ነው፣ ሊጠጣ ነው ወይም ዕቃ ሊገዛ ነው። ድንገት ግን መፅሐፍትን ቢያገኝ ምን ስሜት ሊሰማው ይችላል? የሚለውን ለማየት ነበር ቦታ የጠየቅነው። ከጠበቅነው በላይ ተመልካች አግኝተናል። ብዙዎቹ መፅሐፍቶቹን እዛ በማየታቸው ተገርመው ገዝተውናል። ለምሳሌ ጫማ ሊገዛ የመጣ ወጣት የ490 ብር መፅሐፍትን ገዝቶ ሲወጣ ተመልክቻለሁ። በዚህም በሁለት ነገር ግባችንን መተናል። አንደኛው የሰውን ስሜት ማየት ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ማነው በብዛት መፅሐፍ የሚያነበው ወይም የሚገዛው የሚለውን ለማጥናት ነበር።

ሰንደቅ፡- በሁለት ሳምንታት የኤግዚቢሽን ማዕከል ቆይታ ምን ታዘብክ፤ እነማን በብዛት መፅሐፍ ይገዛሉ ወይም ያነባሉ ብለህ አሰብክ?

ባህሩ፡- ወደአውደ ርእዩ የሚመጣው የዕድሜ ገደብ የሌለው ህዝብ ነው። መፅሐፍት መደብር ቢሆን ግን መፅሐፍትን ለመግዛት ብለው ነው። ባይገርምህ በአውደ ርዕዩ ለመካፈል 20ሺህ ብር ነው ለቦታ ኪራይ ብንከፍልም አልከሰርንም። የተወሰነ ትርፍም አግኝተን ወጥተናል። የታዘብኩት ነገር ህጻናት መፅሐፍትን ሲያዩ ወደመፅሐፍት ይመጣሉ። ይሄ ጥሩ ነገር ነበር። ሌላው ግን በጣም የገረመኝ በርካታ ሴቶች መፅሐፍትን ሲገዙ ተመልክቻለሁ። ይህን አልጠብቅም ነበር። ወንዶች በተለይም ጎልማሶች ናቸው ብዙ የሚገዙ የሚመስለኝ። ነገር ግን በጣም የሚደንቀው ነገር የሴቶቹ ተሳትፎ ነው። በዚህም መፅሐፍት መደብር ድረስ የሚመጡት ወንዶች ግምቴን የተሳሳተ እንዳደረጉት ተረድቻለሁ። ምናልባትም መፅሐፍትን በየመንደሩ ማድረስ ብንችል ብዙ አንባቢ ሴቶች መኖራቸውን ማወቅ እንችላለን ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል። በተረፈ አብዛኞቹ ሴቶች ስነ-ልቦና ላይ፣ የፍቅር ታሪኮች ላይ፣ ልቦለዶች ላይና የስነ-ምግብና ውበት ላይ ያተረኮሩ መፅሐፍትን ሲመርጡ ፖለቲካ ግን የእነርሱ ምርጫ አለመሆኑን ታዝቤያለሁ። ሌላው ጎልማሳዎቹ ታሪክ ላይ ያተኩራሉ። ያው የዋጋቸው ነገር ግን ያዝ ሲያደርጋቸው ታያለህ።

ሰንደቅ፡- መፅሐፍትን ለአንባቢያን ቅርብ ከማድረግ አንጻር ምን ቢሰራ መልካም ነው ትላለህ?

ባህሩ፡- ከዚህ ቀደም ባልሳተፍም መፅሐፍት ላይ ብቻ ትኩረቱ ያደረገ አውደርዕይ ተካሄዶ ነበር። ይህ ነገር ቢቀጥል መልካም ይመስለኛል። በዚህ አጋጣሚ ግን ማስተላለፍ የምፈልገው ነገር መፅሐፍ ነጋዴዎች በጎ አመለካከት ኖሯቸው፤ ማህበር መስርተን በየቦታው፤ በየአካባቢው ለምሳሌ በአንድ ወቅት ጀሞ አካባቢ፣ በአንድ ወቅት ሰሚት አካባቢ፣ በአንድ ወቅት ሜክሲኮ አካባቢ ብቻ የሆነ ቦታ ላይ ለአምስት -ለአምስት ቀን የመፅሐፍት አውደ-ርዕይ እንዲዘጋጅ ብናደርግ ጥሩ ነው። በዚህም ለሰዎችም እንደርሳለን እኛም የምንፈልገውን ዓላማ ግብ እንመታለን የሚል እምነት አለኝ።

ሰንደቅ፡- አሁን የቤተሰብ ህይወት እየመራህ ነው። ልጆች እንዲያነቡ የተለየ የምታደርገው ነገር አለ?

ባህሩ፡- ባለቤቴ አሁን-አሁን ጥሩ አንባቢ ነች ማለት እችላለሁ። ድሮ ትዕግስቱ ኖሯት አንድ መፅሐፍ መጨረስ አትወድም ነበር። አሁን ጎበዝ ሆናለች። በተረፈ ግን ለልጆቼ እኔ አነብላቸዋለሁ። የመፅሕፍን ፍቅርም እየዘራሁባቸው እንደሆነ ይሰማኛል።

ሰንደቅ፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ?

    ባህሩ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ። በዚህ አጋጣሚ ግን ለላቪስን የንግድ ትርዒት አዘጋጆች ያለኝን ምስጋና መግለፅ እፈልጋለሁ። በቀጣይም ፋሲካን ጨምሮ በሚኖሩ የንግድ ትርኢቶች ላይ የመሳተፍ ሃሳቡ አለን፤ ሌሎቹም አዘጋጆች ይተባበሩን ዘንድ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ ማቅረብ እወዳለሁ፤ አመሰግናለሁ።

 


በኦቲዝምና ተዛማጅ የአእመሮ እድገት እክል ያለባቸው ልጆችን ትኩረት አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ኒያ ፋውንዴሽን ከትናንት በስቲያ በብሔራዊ ቴአትር የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። በመድረኩ ላይ በኢትዮጵያ ስላለው የኦቲዝም ሁኔታ ገለፃ ተደርጎ ነበር። ኒያ ፋውንዴሽን በአሁኑ ወቅት የኦቲዝም እና የአእምሮ እድገት ችግር ያለባቸውን ህፃናት በተለያዩ መንገዶች እያስተማረ ወደ ማህበረሰቡ በመቀላቀል ላይ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ 530 ሺህ ገደማ ህፃናት ከኦቲዝም እና ከዘገምተኛ እድገት ችግር ጋር ይኖራሉ። እነዚህ በሺዎች የሚቆጠሩ የኦቲዝም በሽታ ተጠቂዎች በማህበረሰቡ ውስጥ የሚኖሩ ቢሆኑም ከቤተሰቦቻቸው እና ከማህበረሰቡ ጭምር የሚደርስባቸው መገለል ከፍተኛ ነው። እነዚህ ህጻናት በየደረጃው ጭቆና የሚደረግባቸው ሲሆን፣ ከማህበረሰቡ እይታ እንዲሰወሩ እና የተገለለ ቦታ እንዲቀመጡ ይደረጋል። ይህም የሚሆነው የኦቲዝም ችግር ያለበት ልጅ ያላቸው ቤተሰቦች እንደ እርግማን ስለሚቆጥሩት እና ከማህበረሰቡ የሚመጣባቸውን ትችት መቋቋም ባለመቻላቸው ነው። እነዚህ ህጻናት በቤት ውስጥ በተዘጋጀላቸው ቦታ ተቆልፎባቸው እንዲቆዩ በመደረጉም ህፃናቱ ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ እና እንደ እህት ወንድሞቻቸው እና እኩዮቻቸው ከቤት ወጥተው እንዳይጫወቱ ያደርጋቸዋል።

በማህበረሰቡ ዘንድ ስለ ኦቲዝም በሽታ ያለው አመለካከት አነስተኛ በመሆኑ ከዚህ በሽታ ጋር የሚኖሩ ህፃናትም ሆኑ አዋቂ ሰዎች ለተለያዩ ትችቶች ተጋላጭ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ለሚሳሳቷቸው ስህተቶችም ምክንያቱን ከማጥናት ይልቅ መልሶ እነሱን ተጠያቂ የማድረግ አካሄድ ይታያል። በዚህም ሳቢያ መሠረታዊ የሆኑ የትምህርት፣ ስለጤንነታቸው ምርመራ እና ክትትል የማግኘት መብቶቻቸውን ያጣሉ። እነዚህ ህፃናት ጠቃሚ እንዳልሆኑ እና እንደማይፈለጉ ተደርገው ይቆጠራሉ። የፀሃይ ብርሃን እንዳያገኙ፤ ከተዘጋባቸው ጨለማ ቤት ወጥተው ብርሃን እንዳያዩ ይደረጋሉ። ወጥተው ከማህበረሰቡ ጋር እንዳይቀላቀሉ እና ህይወታቸውን በብቸኝነት እንዲያሳልፉ የሚገደዱበት ሁኔታም ከፍተኛ መሆኑን ያገኘናቸው መረጃዎች ያስረዳሉ።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ይህ የኦቲዝም ተጠቂዎች በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት አለማግኘት ታዲያ ችግሩ በበሽታው ተጠቂዎች ብቻ የሚያቆም አይደለም። ወላጆቻቸው በተለይ ደግሞ እናቶቻቸው በከፍተኛ ደረጃ የችግሩ ተጠቂዎች ናቸው። የኦቲዝም ተጠቂ ልጅ ያላት (ያሏት) አንዲት እናት ልጇን በመደበኛ ትምህርት ቤት ለማስተማር ያለበት ሁኔታ አይፈቅድም። ለእንደዚህ አይነቶቹ ልጆች የተዘጋጀ ትምህርት ቤት ባለመኖሩም ልጇን ለማስተማር አትችልም። ልጇን በቤተሰብ ውስጥ አሊያም በጎረቤት ዘንድ አስቀምጣ መንቀሳቀስ ደግሞ ህፃኑ ከሚኖረው የተለየ ባህሪይ የተነሳ የሚቀበላት አታገኝም። በዚህ አይነቱ ውስብስብ ችግር ታዲያ ሰርተው የራሳቸውን ገቢ ማግኘት ባለመቻላቸው ዝቅተኛ ገቢ ይኖራቸዋል በዛ ሲልም ምንም ገቢ አይኖራቸውም። በዚህም ሣቢያ ለራሳቸው እና ለልጆቻቸው አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ማድረግ አይችሉም። እነዚህ ልጆች ከሌሎች ልጆች የተለየ ፍላጎት ስለሚኖራቸውም ይሄንን ፍላጎታቸውን ለማሟላት ባለመቻላቸው ራሳቸውን እንደሚወቅሱ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በሀገራችን የሚገኙ በርካታ ኦቲዝም ተጠቂ ህጻናት በአይን ሲታዩ ጤነኛ የሚመስሉ መሆናቸውን የጠቆመው የአካል ጉዳተኞች መልሶ ማቋቋምን በተመለከተ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ፣ ማህበረሰቡ የግንዛቤ እጥረት ስላለበት በእነዚህ ህጻናት ለሚፈጠሩ ችግሮች የተለያዩ ምክንያቶች ያስቀምጣል ይላል። ብዙዎች ህጻናቱ በአግባቡ ተይዘው እና ግብረገብ ሆነው ባለማደጋቸው እንዲህ አይነት ባህሪይ እንድኖራቸው የሚያስቡ ስለሆነ ለዚህ ባህሪይም ተጠያቂ የሚያደርጉት ወላጆቻቸውን ነው። ከዚህ በተጨማሪም እንዲህ አይነቱ የተዛባ ባህሪይ በህፃናቱ ላይ ሊከሰት የሚችለው ወላጆች ላጠፉት ጥፋት ከፈጣሪ የተጣለባቸው ቅጣት እንደሆነ አድርገው ያምናሉ።

እነዚህን የማህበረሰብ ትችት የሚፈሩት የኦቲዝም ተጠቂ ህፃናት ወላጆችም የእነዚህን ህፃናት እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር፣ በማህበረሰቡ ዘንድም መኖራቸው እንዳይታወቅ እና ስለእነርሱ እንዳይነገር የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። ነገር ግን እነዚህ ህፃናት ባህሪያቸው ለመቆጣጠር አስቸጋሪ በመሆኑ ወላጆች እጅና እግራቸውን በማሰር በጭለማ ቤት ውስጥ ይቆልፉባቸዋል።

ኦቲዝም በእድገት ዘገምተኛነት ጋር የተያያዘ በሽታ ነው። ይህ ችግር ህጻናትን በተለያየ መልኩ የሚያጠቃ ሲሆን፣ በአብዛኛው መሠረታዊ የሆነ ችሎታዎች ዘገምተኛ እንዲሆኑ ማድረግ መገለጫው ነው። ከእነዚህ ችሎታዎች መካከልም ማህበራዊ ግንኙነት ማድረግ አለመቻል እና ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳይኖራቸው ማድረግ ይገኝበታል። ከዚህ ጎን ለጎንም የአእምሮ ብቃት አለመዳበር፣ የተለመደ ባህሪይ አለመያዝ መገለጫዎቹ ናቸው።

የኦቲዝም ምክንያቶች በህፃናቱ ላይ መታየት የሚጀምሩት ህፃኑ ሶስት ዓመት ከመሙላቱ በፊት ነው። እነዚህ ምልክቶች የተለያዩ እና ስፋት ያለቸው ሲሆኑ፣ እስከ እድሜ መጨረሻ ድረስ ይዘልቃሉ። በአብዛኛው በኦቲዝም የተጠቁ ህፃናት የሚያሳዩዋቸው ባህሪያት በቃላት መግባባት አለመቻል (ቋንቋን መጠቀም እና መረዳት አለመቻል)፣ መናገር እየቻሉ በውይይት ውስጥ መሳተፍ አለመቻል፣ አካላዊ ቋንቋዎችን መረዳት አለመቻል የሚሉት ይገኙበታል። በተጨማሪም ከሰዎች እና ከአካባቢያቸው ጋር መላመድ እና ጓደኛ ማፍራት አለመቻል፣ መጫወቻዎቻቸውን እና ሌሎች እቃዎችን በአንድ አይነት መንገድ ብቻ መደርደር እንዲሁም ተደጋጋሚ የሆነ ጭንቅላትን መወዝወዝ፣ እጅን ማወነጨፍ፣ እጅን እና አግርን መቆላለፍ እንዲሁም ባልተለመዱ እንቅስቃሴዎች ራሳቸውን መጥመድ አብዛኞቹ የኦቲዝም ተጠቂ ህፃናት የሚያሳዩዋቸው ባህሪያት ናቸው።

ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መልኩ ደግሞ እነዚህ ኦቲዝም ተጠቂዎች በተወሰኑ የሞያ መስኮች ከሌሎች የተለየ እና የላቀ ክህሎት አላቸው። በሙዚቃ፣ በኪነ-ጥበብ እና ከቁጥር ጋር በተያያዙ ክህሎቶች የተለየ ተሰጥኦ ይኖራቸዋል። እነዚህን ተሰጥኦዎች የሚተገብሩት ታዲያ ተምረው ወይም ተለማምደው ሳይሆን በራሳቸው ጊዜ በሚያደርጉት ጥረት መሆኑን የህክምና ባለሞያዎች ይገልፃሉ።

የኦቲዝም ችግር ያለባቸው ህፃናት በተወለዱ በጥቂት ቀናት ውስጥ የተወሰኑ ምልክቶቸን ማሳየት ይጀምራሉ። በሌሎች ህጻናት ላይ እንደሚታየው የሚያዩትን ነገር በአይን መከተል ያቅታቸዋል፣ ከነገሮች ጋርም መግባባት አይችሉም። በተጨማሪም የተወሰኑት በጣም ዝምተኛ እና ብዙም የማያለቅሱ ሊሆኑ ይችላሉ።

ከአለማችን ህዝብ አንድ በመቶው የኦቲዝም ተጠቂ እንደሆነ አሜሪካ የኦቲዝም ማህበር በ2014 ያወጣው መረጃ ያመለክታል። ይህ ችግር በአሜሪካ ያለውን ስርጭት ስንመለከት ከሚወለዱ 68 ህፃናት አንዱ የኦቲዝም ተጠቂ ነው። በዚህም ሲሰላ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን አሜሪካውያን ከኦቲዝም ችግር ጋር ይኖራሉ።

የኦቲዝም ችግር ከሴቶች ይልቅ በወንዶች ላይ አምስት እጥፍ የመከሰት እድል አለው። ይህ ማለት ከ189 ሴቶች አንዷ የዚህ ችግር ተጠቂ የምትሆን ሲሆን ከ42 ወንዶች ግን አንዱ ለዚህ ችግር ተጋላጭ ነው።

በኦቲዝም ከሚያጋልጡ ነገሮች አንዱ እድሜያቸው ከገፋ ወላጆ መወለድ ነው። እድሜያቸው ከገፉ ወላጆች የሚወለዱ ህጻናት ለዚህ ችግር የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታል። በተጨማሪም የመውለጃ ጊዜያቸው ሳይደርስ የሚወለዱ ህፃናት በከፍተኛ ደረጃ ለዚህ ችግር ተጋላጮች ናቸው።

የኦቲዝም ችግር በህፃናቱ ላይ ብቻም ሳይሆን በወላጆች ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራል። የኦቲዝም ችግር ያለበት ልጅ ያላቸው ወላጆች ተጨማሪ ልጆን የመውለድ እድላቸው ከ2 በመቶ እስከ 18 በመቶ ብቻ እንደሆነ ነው ጥናቶች የሚያመለክቱት። ለዚህ ደግሞ ምክንያቶቹ በቀጣይ የሚወለዱት ልጆች ተመሳሳይ ችግር ሊኖርባቸው ይችላል የሚል ስጋት፤ እነዚህን ህፃናት ለማሳደግ የሚጠይቀው ጊዜ፣ ወጪ እና የመሳሰሉት ነገሮች ሌላ ነገር ለማሰብ ፋታ የማይሰጥ መሆኑ ነው።

ወላጆች ልጃቸው የኦቲዝም ተጠቂ በሚሆነበት ወቅት ሙሉ ትኩረታቸውን ወደርሱ በማድረጋቸው በአካባቢቸው ምን እየተከናወነ እንደሆነ አይረዱም። በዚህም ሳቢያ ለተለያዩ አለመረጋጋት እና ለጭንቀት ይደረጋሉ። ለልጃቸው ሲሉ በማህበራዊ ጉዳዮች ውስጥ መሳተፍ ባለመቻላቸውም የተገለሉ ይሆናሉ። በተጨማሪም ትምህርት፣ ስራ እና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ውስጥ መሳተፍ ባለመቻላቸው በራሳቸው መተማመን የማይችሉ እና ለራሳቸው ዝቅተኛ ግምት ያላቸው ናቸው። በዚህም ሳቢያ ለተለያዩ ጥቃቶች የተጋለጡ ናቸው። በቤታቸው ውስጥ የሚኖራቸው የአኗኗር ሁኔታም የተዛባ እና በዘፈቀደ የሚከናወን ይሆናል።

ብዙውን ጊዜ የኦቲዝም ተጠቂዎች ተክለ ሰውነታቸው ግዙፍ ስለሚሆን እነዚህ ህጻናት እያደጉ ሲሄዱ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ይሆናሉ። በዚህም ሳቢያ በወላጆቻቸው ላይ የተለያዩ አካላዊና ስነ-ልቦነዊ ጥቃቶች የሚያደርሱ ሲሆን፣ ለራሳቸውም ሌላው ሊረዳቸው ባለመቻሉ ወንጀል ውስጥ ይገባሉ። በዚህም የተነሳ ወላጆች ለጭንቀት፣ ግራ መጋባት እና አንዳንዴም ትዳራቸውን እስከመፍታት እና ቤተሰባቸውን እስከመበተን ይደርሳሉ። በርካቶች ስለልጆቻቸው የኦቲዝም ተጠቂነት ተናግረው መፍትሄ ከማግኘት ይልቅ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማቸዋል።

እነዚህ የኦቲዝም ተጠቂ ህጻናት ታዲያ በየሀገራቱ ትኩረት ሳይሰጣቸው እንደቀረ ይገልጻል። ወላጆች በቂ መረጃ ከማጣታቸው የተነሳ መፍትሄ አለማፈላለጋቸው ብቻም ሳይሆን መንግስታትም ትኩረት አይሰጡትም። ይህን ችግር በህክምናም ሆነ በሌላ መንገድ ማዳን ባይቻልም ህፃናቱን በማለማመድ እና ትምህርት በመስጠት ከማህበረሰቡ ጋር መኖር እንዲችሉ ማድረግ ይቻላል። በተለያዩ ሀገራት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንዲህ ላሉ ህፃናት የሚውሉ ትምህርት ቤቶች እና ማዕከላት አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸው ችግሩን በጥቂቱም ቢሆን መቅረፍ እየተቻለ ነው።

    በሀገራችን ያለውን ሁኔታ ስንመለከት እስከ አሁን ድረስ ኒያ ፋውንዴሽን እና ነህምያ የኦቲዝም መንደር ብቻ ናቸው በእነዚህ ህፃናት ላይ እየሰሩ ያሉት። እነዚህ ማዕከላት በጣም ጥቂት ህፃናትን እያስተማሩ ወደ ማህበረሰቡ በመቀላቀል ላይ ይገኛሉ። ነገር ግን እጅግ በርካታ ህፃናት በየቤታቸው ከዚህ ችግር ጋር እየኖሩ ነው።

“መክፈል አልቻልንም” - ሕሙማን

በመላኩ ብርሃኑ

የሕክምና ወጪ ለመሸፈን ለልመና ከተሰማሩት አንዷ

 

ከቀዝቃዛው የህዳር ወር ምሽቶች በአንዱ። ወደየጉዳያቸው ከሚጣደፉት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል ስቃይ በሚነበብበት አይኗ አላፊ አግዳሚውን የምትማጸን አንዲት ታዳጊ መኪና ተደግፋ ቆማለች። ሰዎች አጠገቧ ሲደርሱ በእጇ የያዘችውን በአዳፋ ላስቲክ የተሸፈነ ወረቀት ወጣ አድርጋ ለማሳየት ትሞክራለች። ወረቀቱ ባህርዳር ከሚገኘው ፈገለገህይወት ሆስፒታል የተጻፈ የከፍተኛ ህክምና ማዘዣ (Referal slip) ነው።

የ16 ዓመቷ እናና ቢሻው የምትኖረው ጎጃም ዞን አዴት ከተማ ይልማዴንሳ በተባለ ወረዳ ውስጥ ነው። ይህንን ወረቀት ይዛ አዲስ አበባ የገባችው ለብዙ ዓመታት ሲያሰቃያት ከኖረው ህመም የመዳን ተስፋ ሰንቃ ነበር ። ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንደደረሰች ማዘዣውን የተቀበላት ሃኪም ከመረመራት በኋላ በሽታዋን አውቆ ተገቢውን ህክምና ለማድረግ በኤም.አር.አይ እንድትታይና ውጤቱን ይዛ እንድትመጣ አዘዛት። መሳሪያው የሚገኝበት የግል ሆስፒታል የጠየቃት 3ሺህ 500 ብር ክፍያ ግን ከአቅሟ በላይ መሆኑን ነው የምትገልጸው።

“አባቴ እስካሁን ያሳከመኝ የእርሻ በሬዎቹን ሸጦ ነበር። የያዝኩትን ጥቂት ብር ለመድሃኒት መግዣ፣ ለትራንስፖርት፣ ለምግብና ለማደሪያ አውዬው አልቋል። ከነበሽታዬ ወደሃገሬ ከመመለስ ውጪ የመዳን ተስፋ የለኝም። አሁን የትራንስፖርት ገንዘብ ለማግኘት ብዬ እየለመንኩ ነው” ትላለች-በዚያ ቀዝቃዛ ምሽት መንገድ ላይ ያቆማትን ምክንያት ስትናገር።

ከሁለት ወራት በፊት በኩላሊት ህመም የሚሰቃዩ ባለቤታቸውን ይዘው ከ500 ኪሎሜትር በላይ ከሚርቀው ሰሜን ወሎ ዞን ወደ አዲስ አበባ የመጡት ወይዘሮ የንጉስ በላይነው ደግሞ ከደሴ ሪፈራል ሆስፒታል የተሰጣቸውን የኤክስሬይ ውጤት እያሳዩ እርዳታ መለመን ከጀመሩ አንድ ወር አልፏቸዋል።

“ባለቤቴ ህመሙ ከጀመረውና በየሃኪም ቤቱ መንከራተት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። በመጨረሻ ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ስንሄድ ከባድ የኩላሊት በሽታ እንዳለበት ነገሩትና አዲስ አበባ ሄዶ እንዲታከም ጻፉለት። አዲስ አበባ መጥተን ሶስት የግል ሆስፒታሎችን ጠየቅን። በሃኪም የታዘዘለትን ህክምና [ጊዜያዊ የኩላሊት እጥበት] ለማግኘት በሳምንት ከስድስት ሺህ ብር ያላነሰ መክፈል እንዳለብን ነገሩን ። እኛ ጥሪታችንን አሟጠን ጨርሰናል። አምስት ልጆቻችንን ትተን ወደመጣንበት ቀዬ ለመመለስ የትራንስፖርት ገንዘብ ስላጣን እሱን በረንዳ ላይ አስተኝቼ እኔ እየለመንኩ ነው።” ብለዋል።

“እንግዲህ ቢሞትም ዘመድ መሃል ይሙት ብዬ ነው ወደመጣንበት ይዤው የምመለሰው” ይላሉ ወይዘሮ የንጉስ- አይናቸው እንባ እያቀረረ።

በጤንነት ላይ የተጋረጠ ሥጋት

ጥናቶች በኢትዮጵያ አንድን ዜጋ ከሚያሳስቡት መሰረታዊ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ውስጥ ከምግብና መጠለያ እንዲሁም መተዳደሪያ ስራ ከማግኘት ቀጥሎ የህክምና ወጪን በሶስተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጡታል። የህክምና አገልግሎት ክፍያ በየጊዜው እየጨመረ መሄድ ባደጉም ይሁን በማደግ ላይ በሚገኙ ብዙ የዓለማችን ሃገራት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊም ይዘት ያለው አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል። በተለይ እንደኢትዮጵያ ባሉ ሲሶ ህዝባቸው በድህነት ወለል ስር በሚገኝባቸው ሃገራት ይህ ችግር የጎላ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሃገሪቱ የግል ሆስፒታሎች እየጨመረ የመጣው የህክምና ዋጋ “ኢትዮጵያ ውስጥ በከባድ ህመም ከመያዝ ይልቅ መሞት ይሻላል” የሚል አስተያየት ያላቸውን ዜጎች ቁጥር አበራክቶታል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የበርካታ የግል ሆስፒታሎች የአገልግሎት ዋጋ ከብዙሃኑ የሃገሪቱ ህዝብ የመክፈል አቅም ጋር ሲነጻጸር የማይሞከር ሆኖ መገኘቱ ነው።

“የሆስፒታሎች ቁጥር በቂ አይደለም”

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የፖሊሲ ጥናት ዳይሬክቶሬት የተሰበሰቡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ሃገሪቱ ላላት 85 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ መንግስት መገንባት የቻለው 125 ሆስፒታሎችን ብቻ ነው። በአምስት ክልሎች በመሰራት ላይ ያሉ 129 ሆስፒታሎች ግንባታ ሲጠናቀቅ ይህ የሆስፒታሎች ቁጥር ወደ 254 ከፍ ይላል ተብሎ ይጠበቃል። በአንጻሩ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የጤናና ጤና ነክ መረጃዎች አመላካች ጥናት እንደሚያሳየው በሃገሪቱ የሚገኙት የግል ሆስፒታሎች ቁጥር 56 ብቻ ነው።ከነዚህም መካከል 34 ቱ የሚገኙት በአዲስ አበባ ውስጥ ሲሆን የቀሩትም በጥቂት የክልል ከተሞች ውስጥ የተወሰኑ ናቸው። እንደቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሶማሊ እና ጋምቤላ ባሉ የሃገሪቱ ክልሎች ደግሞ ምንም አይነት የግል ሆስፒታል የለም።

እስከ 2004 ዓ.ም ድረስ የተሰበሰቡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አንድ የመንግስት ሆስፒታል ከ680 ሺህ በላይ ለሆነ ህዝብ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በአንጻሩ በግል ሆስፒታል ተገልጋይ ምጣኔ መሰረት አንድ የግል ሆስፒታል ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎች አገልግሎት እንደሚሰጥ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

አንድ ዶክተር ለ28ሺህ 847 ዜጎች በሚዳረስባትና ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ እጥረት ባለባት ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግስት የሚደጎሙ ሆስፒታሎች ቁጥር አነስተኝነት ሲታከልበት በሃገሪቱ ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከባድ የጥራት ችግር እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል። ይህም በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ከህመማቸው ለመዳን ወደግል ሆስፒታሎች የሚያደርጉትን ምልልስ እንዲጨምሩ አስገድዷቸዋል። በዚህም ሳቢያ ሆስፒታሎቹ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ታካሚ ያስተናግዳሉ። ያም ሆኖ የአገልግሎት ዋጋቸው ከአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የኢኮኖሚ አቅም ጋር ሲተያይ የማይሞከር ሆኗል።

ከጊዜ ወደጊዜ የጤና አገልግሎት ፍላጎት እየጨመረ በመጣባት ኢትዮጵያ የህክምና ዋጋ እየናረ መሄድ በጤና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳረፈ ስለመሆኑ ባለሙያዎች ይስማሙበታል።

የኢትዮጵያ የጤና ዋስትና ኤጀንሲ ዳይሬክተር ዶክተር መንግስቱ በቀለ እንደሚናገሩት የኢትዮጵያ ህዝብ ለህክምና የመክፈል አቅምን በተመለከተ የተካሄዱ ጥናቶች እንዳረጋገጡት አንድ ዜጋ ከሚያገኘው ገቢ ለጤና አገልግሎት የመክፈል አቅሙ በሬሽዮ 0.33 በመቶ ብቻ መሆኑን አረጋግጠዋል። በርካታ የሃገሪቱ ዜጎች ዝቅተኛ ክፍያ በሚጠይቀው የመንግስት ሆስፒታል እንኳን ለመታከም የሚያስችል አቅም የላቸውም ያሉት ዳይሬክተሩ ይህም እውነታ ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁትን የግል ሆስፒታሎች ለመጎብኘት እንደማይችል አመላካች ነው ይላሉ። ለህክምና የመክፈል አቅም ደካማ መሆን በጤና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ ማነቆ ከፈጠሩት ችግሮች አንዱ መሆኑንም ዶክተር መንግስቱ ይናገራሉ።

የጤና መድህን ኤጀንሲ በቅርቡ ባካሄደው ጥናት እንዳረጋገጠው ለተመሳሳይ የህክምና አገልግሎት በግል ሆስፒታሎች የሚጠየቀው ዋጋ ከመንግስት ሆስፒታሎች ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ከ20 እጥፍ በላይ ይደርሳል። በተጨባጭ ምሳሌ ሲታይም አንድ የመንግስት ሆስፒታል ቀላል የሚባለውን የትርፍ አንጀት ቀዶ ህክምና ለመስራት 120 ብር ሲያስከፍል የግል ሆስፒታሎች ግን ከ3 እስከ 5 ሺህ ብር ድረስ ይጠይቃሉ። ይህ አሃዝም የአገልግሎት ክፍያውን ልዩነት ከ41 እጥፍ በላይ ያደርሰዋል።

ይህ ዘጋቢ መረጃ ለማሰባሰብ በተዘዋወረባቸው አዲስ አበባ፣ ባህርዳር፣ ደሴ፣ሃዋሳና አዳማ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ የግል ሆስፒታሎች የሚያስከፍሉት ዋጋ ከህብረተሰቡ የመክፈል አቅም ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሆኑን ለመገንዘብ ችሏል። ለህክምና ወደሆስፒታሎቹ መጥተው ያገኛቸው አንዳንድ ሰዎችም “መክፈል አልቻልንም፣ ህክምና ማግኘትም አንችልም፣ሌላ ምርጫ የለንም” ብለውታል። አንዳንድ አስተየየት ሰጪዎች ደግሞ የከፈሉት ዋጋ ውድ መሆኑን ነገር ግን የተጠየቁትን ከፍለው ከህመማቸው ከመፈወስ ውጪ አማራጭ እንደሌላቸው ነው የተናገሩት።

“ሕይወቴን ለማትረፍ ቤቴን ሸጫለሁ”

የ64 ዓመቱ ጡረተኛ የአዲስ አበባ ነዋሪ አቶ ዘመነ መንግስቱ በልብ የደም ስር መጥበብ ሳቢያ ህይወታቸው አደጋ ላይ መውደቁ የተነገራቸው ለአንድ ዓመት በፊት ነበር። በመንግስት ሆስፒታል ውስጥ ያክማቸው የነበረው ዶክተርም ይህ ህክምና በሆስፒታሉ እንደማይሰጥ በማስረዳት ህይወታቸውን ለማትረፍ ገንዘብ ከየትም ፈልገው እሱ በትርፍ ጊዜው ወደሚሰራበት የግል ሆስፒታል መምጣት ከቻሉ መፍትሄ እንደሚሰጣቸው ይነግራቸዋል።

“ልቤ በማንኛውም ጊዜ ስራውን እንደሚያቆም ነግሮ ተስፋ አስቆርጦኛል። ለሕክምናውን የተጠየቅኩትን 280 ሺህ ብር ለመሸፈን ያለኝ አንድ አማራጭ መኖሪያ ቤቴን መሸጥ ነበር።ነገር ግን ልጆቼ ማደሪያ እንዳያጡ ብዬ ሞትን መረጥኩ። ሆኖም ልጆቼ እያለቀሱ ስለለመኑኝ ቤቴን ሸጬ ታከምኩ። ህክምናው ከአንድ ቀን በላይ ባይፈጅም እኔና ልጆቼን ግን ሙሉ እድሜያችንን የሰው ቤት ተከራይተን እንድንኖር አስገድዶናል” ብለዋል።

ከ288ሺህ በላይ ነዋሪ ባላት ባህርዳር ከተማ ውስጥ ከሚገኙት ሁለት ሆስፒታሎች አንዱ ጋምቢ አጠቃላይ ቲቺንግ ሆስፒታል ነው። ይህ የግል ሆስፒታል በመንግስት ባለቤትነት ከሚተዳደረው ፈለገ ህይወት ሆስፒታል ጋር በድምሩ ከ5 ሚሊዮን በላይ ለሚገመቱ የአማራ ክልል እና አጎራባች ክልሎች ነዋሪዎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

ጋምቢ ሆስፒታል እንደ ኩላሊት እጥበት ህክምና፣ ሲቲ ስካን፣ ኢኮ ካርዲዮግራፊ፣ ታይሮይድ እና የካንሰር ምርመራዎች ያሉ በፈለገ ህይወት ሆስፒታል የሌሉ አገልግሎቶችን ይሰጣል። እነዚህ ምርመራዎች የታዘዙላቸው ብዙ የገጠርና የከተማ ሰዎች ወደዚህ ሆስፒታል ይሄዳሉ።

ይህ ዘጋቢ ሊቦ ከምከም ከተባለች የገጠር ወረዳ መጥተው በሆስፒታሉ ሲታከሙ ያገኛቸው ወይዘሮ አዘንጌ ዋልተንጉስ የታዘዘላቸው የልብ ምርመራ መሳሪያ ጋምቢ ሆስፒታል ብቻ የሚገኝ በመሆኑ ክፍያው ቢበዛባቸውም ከወዳጅ ዘመድ ተበዳድረው በመክፈል በአገልግሎቱን እየተጠቀሙ መሆኑን ይናገራሉ። “አሁን አሁን ግን ብሩ እያለቀ መድሃኒት መግዣም እያጣሁ ነው።ህክምናው ከቀጠለ በአቅም ማነስ ማቋረጤ አይቀርም ” ብለዋል።

ከአዊ ዞን የመጡት ወይዘሮ በርነሽ አባኔ በበኩላቸው የታይፎይድ እና የታይፈስ ምርመራ ለማድረግ ጋምቢ ሆስፒታል 120 ብር መክፈላቸውን ይናገራሉ። “በርግጥ ክፍያው ከፈለገ ህይወት ጋር ሲነጻጸር በ90 ብር እንደሚበልጥ ባውቅም እዚህ መጠቀም የፈለግኩት ግን ወረፋ ሳልጠብቅ ህክምናዬን አግኝቼ ቶሎ ወደመጣሁበት ለመመለስ በመፈለጌ ነው” ብለዋል።

የእብናት ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሙላት ፈንቴ በበኩላቸው “የአይን ሞራ ቀዶ ህክምና ለማካሄድ ወደጋምቤ ሆስፒታል ስመጣ 1 ሺህ 500 ብር ክፈል ተባልኩ።ወረፋውን ፈርቼ የተውኩት ፈለገ ህይወት የመንግስት ሆስፒታል 100 ብር ብቻ ነው የሚያስከፍለው። ይህን ያህል የተጋነነ ልዩነት መኖር አልነበረበትም” ነው ያሉት።

የነዋሪዋ ቁጥር ከ200 ሺህ የሚበልጠው ደሴ ከተማ ከባህርዳር ጋር ሲነጻጸር የተሻለ የህክምና ተቋማት አሏት። ሁለት የመንግስትና ሶስት የግል ሆስፒታሎች ይዛለች። ያም ሆኖ የደሴ ሪፈራል እና የቦሩ የመንግስት ሆስፒታሎች ግቢ ሁልጊዜም በታካሚዎች እንደተጨናነቀ ነው። ይህ ዘጋቢ በደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ወለል ላይ ተኝተው ካገኛቸው ህመምተኞች መካከል ሸህ ሰዒድ አሊን አናግሯቸው ነበር። ሃርቡ ከተባለ አካባቢ መምጣታቸውን የሚናገሩት እኚህ ታማሚ ላለፉት አራት ቀናት ህክምና ለማግኘት ወረፋ እየጠበቁ መሆኑን ነበር የተናገሩት። የግል ሆስፒታል ሄደው እንደሁ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልሳቸው ምሬት የተሞላበት ነበር። “ከዚህ ቀደም ደሴ ውስጥ በሚገኙት ሶስቱም ሆስፒታሎች ተመላልሼ በተለያዩ ዶክተሮች ታይቻለሁ። 12 ሺህ ብር ከፍዬ ገንዘቤን ጨረስኩ እንጂ አንዳቸውም በሽታዬን አላወቁልኝም። አሁን ባዶዬን ስቀር ነው ወደዚህ የመጣሁት።” ነበር ያሉት።

በደሴ ከተማ የሚገኙት የግል ሆስፒታሎች በመሳሪያ ዓይነትም ይሁን በባለሙያ ስብጥር ከመንግስት ሆስፒታሎች የተሻለ አቅም ባይኖራቸውም የሚያስከፍሉት ዋጋ ከፍተኛነት ግን 80 በመቶ የሚሆነው ነዋሪዋ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኘው ደሴ የማይሞከር መሆኑን ነው የተሰበሰቡ የህዝብ አስተያየቶች የሚጠቁሙት።

በመንግስት ሆስፒታሎች በነጻ የሚሰጠው የወሊድ አገልግሎት በነዚህ ሆስፒታሎች ከ 3ሺህ እስከ 7 ሺህ ብር ያስከፍላል። በተመሳሳይ በ8 ብር የሚሰጠውን የደም፣ የሽንትና የሰገራ ምርመራ በ45 ብር፣ 82 ብር የሚከፈልበትን የጉበትና ኩላሊት ምርመራ በ700 ብር ይሰራል።

ከአዲስ አበባ በ100 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው አዳማ ከተማ ደግሞ በሃገሪቱ ግዙፍ ተብለው ከሚጠሩ ሆስፒታሎች ውስጥ አዳማ ጄኔራል ሆስፒታልና የከተመባት ናት። የሆስፒታሉ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ከቢር ሁሴን ለግንባታና ለህክምና መሳሪያዎች ግዢ አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ ያወጡት የሃገሪቱን ዘመናዊ የህክምና ደረጃ ከፍ በማድረግ የውጭ ሃገር ህክምና ጉዞን ለማስቀረት መሆኑን ይናገራሉ።

በከተማዋ የሚገኘው አዳማ አጠቃላይ ሆስፒታል (በቀድሞ ስሙ ሃይለማርያም ማሞ) በከፍተኛ ሁኔታ በታካሚ ከመጨናነቁ የተነሳ በየበረንዳው ተኝተው ህክምና የሚጠብቁ ነዋሪዎች ቁጥር በርካታ ነው። በአንጻሩ በ86 ሺህ ስኩዌር ካሬ ላይ ያረፈውና ባለ250 አልጋ የሆነው አዳማ ጄኔራል ሆስፒታል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በተደራጀ የህክምናና ምርመራ አቅሙ ማስተድናገድ ከሚችለው ታካሚ በታች እያስተናገደ መሆኑን ነው ይህ ዘጋቢ የታዘበው። ዘጋቢው ለዚህ ምላሽ ለማግኘት ለ20 የአዳማ ነዋሪዎች “ቢታመሙ ወደአዳማ ጀኔራል ሆስፒታል ይሄዳሉ ወይ?” የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር። ሁሉም የሰጡት ምላሽ “ብንፈልግም የመክፈል አቅማችን አይፈቅድም” የሚል ነበር ።

የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት አቶ ህሩይ ሰንበቶ የስኳርና የደም ግፊት ህመማቸውን ለመከታተል ሁልጊዜም ሆስፒታል እንደሚመላለሱ ይናገራሉ። “እዚህ ሆስፒታል ብቅ ብዬ በሃኪም መታየት የቻልኩት ለአንድ ቀን ብቻ ነው” የሚሉት አቶ ህሩይ “አዳማ ጄኔራል የሚያስደስት ህንጻ ያለውና አዳዲስ መሳሪያዎች የተገጠሙለት ሆስፒታል ቢሆንም ዋጋው ግን አቅም የሚጠይቅ ነው” ይላሉ።

የሆስፒታሉ ማርኬቲንግ ሃላፊና ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶከማል ከቢር ግን “አገልግሎታችን የህብረተሰቡን አቅም ያገናዘበ እንዲሆን ለማድረግ ብዙ ቅናሽ አድርገናል” ነው የሚሉት። “በኛ ግምት ሆስፒታላችን በኢትዮጵያ ከሚገኙት ሆስፒታሎች ሁሉ ግዙፉና ዘመናዊው ነው። በዚያው መጠን ደሃው ህብረተሰብ እንዳይጎዳ ክፍያችንም ፍትሃዊ እንዲሆን ጥረናል። ኤም. አር. አይ እንደደረጃው ከ 1 ሺህ 500 ብር ጀምሮ፣ ሲቲ ስካን ከ900 ብር ጀምሮ፣ ኢንዶስኮፒ 700 ብር፣ኢኮካርዲዮግራፊ 240 ብር ነው የምናስከፍለው። የካርድ ክፍያችን 59 ብር ብቻ ነው።ለአንድ ሃኪም እስከ70 ሺህ ብር ደሞዝ እየከፈልን በዚህ ዋጋ አገልግሎት መስጠታችን አገልግሎታችን ትርፍን ሳይሆን ህብረተሰብን ያማከለ መሆኑን ያረጋግጣል” የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ።

ከ350ሺህ በላይ ነዋሪ ያላት ውቧ ሃዋሳ ደግሞ አሴር፣ ቤተ አብረሃም እና ክብሩ የተባሉ ሶስት የግል ሆስፒታሎች ሲኖሯት ሃዋሳ ሪፈራል እና አዳሬ የተባሉ ሁለት የመንግስት ሆስፒታሎችንም ይዛለች። የከተማዋ ጤና ሽፋን 97 በመቶ መድረሱን የሚናገሩት የከተማዋ ጤና መምሪያ ጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶች የጥራት ቁጥጥር አስተባባሪ አቶ ዘመን ለገሰ የሆስፒታሉ ቁጥር ለነዋሪው በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ መንግስት አንድ ተጨማሪ ሆስፒታልም እየገነባ መሆኑን ተናግረዋል።

በመንግስት ሆስፒታሎች ውስጥ አገልግሎት በማግኘት ላይ ሳሉ ይህ ዘጋቢ ያነጋገራቸው የነገሌ ቦረና ነዋሪው አቶ ድሪባ በዳዳ እና ከባሌ ሮቤ የመጡት አቶ በርከሌ ጉዲና “በመንግስት ሆስፒታሎች የሚሰጠው አገልግሎት ከታካሚው ብዛትና ፍላጎት ጋር የተጣጣመ አይደለም” የሚል ቅሬታ ያቀርባሉ።

“የሆስፒታሎቹ ዋጋ ዝቅተኛ ቢሆንም ታመን ስንሄድ ግን በተገቢው መንገድ የሚያስተናግደን የለም። መሳሪያዎች ቢኖሩም ወረፋው አይዳረስም። በዚህ መሃል ታማሚ እርዳታ ሳያገኝ ይንገላታል። ሃኪሞቹም ‘ወረፋ ስለማይደርሳችሁ ወደሌላ ሆስፒታል ብትሄዱ ይሻላል’ እያሉ ህመምተኞችን ወደግል ሆስፒታል ይልካሉ። የግል ሆስፒታል መታከም ደግሞ ከፍተኛ ዋጋ ይጠይቃል። ብዙው ታማሚ ምርጫ በማጣት ግራ የተጋባ ነው” ብለዋል።

በተቃራኒው የሶስቱም የግል ሆስፒታሎች ሃላፊዎች ውድ ነው ለሚባለው የአገልግሎት ክፍያቸው ምክንያት ካደረጉት ችግር መካከል ዋናው የህክምና ባለሙያዎች የሚጠይቁት ደመወዝ መጠን ከፍተኛነት ነው። “የህክምና ባለሙያዎች መንግስት ጋር ከሚከፈላቸው ደሞዝ 400 እጥፍ ይጠይቃሉ። አማራጭ ስለሌለን እንቀጥራቸዋለን። ይህ ከመድሃኒትና ከመሳሪያ ግዢ ወጪ ጋር ተዳምሮ በአገልግሎት ዋጋችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል” ነው ያሉት።

“የግል ሆስፒታል አትራፊ ንግድ አይደለም”

የግል ሆስፒታሎች በታማሚዎች ላይ ከፍተኛ የአገልግሎት ክፍያ በመጫን ትርፍ ያጋብሳሉ የሚለውን የህብረተሰቡን ወቀሳ የሆስፒታሎቹ ባለቤቶችና ስራ አስኪያጆች አይቀበሉትም። ‘የአገልግሎት ክፍያው ውድነት ሆስፒታሉ ካለበት ወጪ ጋር ሲተያይ የተጋነነ አይደለም’ የሚሉት ሆስፒታሎቹ “መንግስት ለሆቴል የሚሰጠውን ማበረታቻ ያህል እንኳን ለግል ሆስፒታሎች አያደርግም” በማለት ቅሬታቸውን ያቀርባሉ።

የኢትዮጵያ የግል ሆስፒታሎች ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሙላቱ ሲሳይ እንደሚናገሩት የግል ሆስፒታሎች ካለባቸው ከፍተኛ ወጪ አንጻር አትራፊ ናቸው ብሎ ማሰብ ስህተት ነው። “ባለሃብቶች በሆስፒታል ኢንቨስትመንት ላይ ሲሰማሩ በመንግስት የሚደረግላቸው ማበረታቻ አርኪ አይደለም። የህክምና መሳሪያዎች ከቀረጥ ነጻ ከማስገባታቸው በቀር ሆስፒታል ሲገነቡ እንኳን ከሊዝ ነጻ መሬት አይሰጣቸውም። ለህንጻ ኪራይ በወር እስከግማሽ ሚሊዮን ብር የሚከፍሉ አሉ። አንድ አልትራ ሳውንድ ማሽን መግዛት እስከ450ሺህ ብር ድረስ ያስወጣል። ከፍተኛ የትርፍ ግብር እና የአስተዳደራዊ ወጪዎች አሉባቸው። ከሁሉም በላይ ሆስፒታሎቹ በሃገሪቱ ባለው የባለሙያ እጥረት ሳቢያ ስፔሻሊስት ዶክተሮችን ለመቅጠር ከፍተኛ ደሞዝ መክፈል ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ አንድ የማህጸንና ጽንስ ስፔሻሊስት እስከ45 ሺህ ብር ደሞዝ ይጠይቃል። አንድ የቀዶ ህክምና ባለሙያ በኦፕሬሽን ወቅት ከሚገኘው ገቢ ከ65 በመቶ በላይ ይወስዳል። የመድሃኒት ቀረጥ ከፍተኛ ነው። ይህን ሁሉ ወጪ አካትቶ የሚሰራው የአገልግሎት ክፍያ ተመን በታካሚ ላይ ይወድቃል። በአዲስ አበባ ብቻ ወጪና ገቢያቸው አልመጣጠን ብሎ በኪሳራ የተዘጉ ሁለት ሆስፒታሎች አሉ። የግል ሆስፒታል ስራ ከውጪ እንደሚታሰበው ከልክ በላይ አትራፊ ተቋም አይደለም፣እንደውም መንግስት የባለሙያዎችን ችግር ተረድቶ ጣልቃ በመግባት ማስተካከል ይጠበቅበታል” በማለት ይሞግታሉ።

የጤና መድህን ኤጀንሲ ዳይሬክተር ዶክተር መንግስቱ በቀለ መንግስት የሆስፒታሎቹ ወጪ በዝቶ በአገልግሎት ላይ ተጽዕኖ እንዳይፈጥር የሚያስገቡትን መሳሪያ ከቀረጥ ነጻ ከማድረግ ባሻገር በመድሃኒቶች ላይም የተወሰነ ፐርሰንት የቀረጥ ቅናሽ ያደርግላቸዋል። ያም ሆኖ የህክምና ስነምግባርን በመጣስና ታማሚውን የመደራደሪያ ምርጫ በማሳጣት ትርፍ ለማጋበስ የሚሰሩና በዚያው መጠን ለህክምናው ከሚያስፈልገው በላይ ዋጋ የሚቆልሉ የግል ሆስፒታሎች መኖራቸው ግን አይካድም። ይህም ችግሩን አስከፊ አድርጎታል” ብለዋል።

“መንግስት ጣልቃ አይገባም”

የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ አንተነህ ምትኩ እንደሚናገሩት ህዝቡ በግል ህክምና ዋጋ መወደድ ላይ የሚያቀርበው ጥያቄ ትክክል ቢሆንም የሃገሪቱ ኢኮኖሚ በነጻ ገበያ ስርዓት የሚመራ በመሆኑ መንግስት የህክምና አገልግሎት ጥራትን መቆጣጠር እንጂ በግል ጤና ተቋማት አሰራር ውስጥ ጣልቃ ገብቶ ዋጋ መወሰን አይችልም። “ለዚህ መፍትሄው የመንግስትን የጤና ተቋማት በብዛት በማደራጀት የህክምና አገልግሎትን በጥራት ማዳረስ ብቻ ነው” ይላሉ።

መፍትሄው ምንድነው?

የኢትዮጵያ መንግስት የጤና አገልግሎት ማዳረስን ቀዳሚ የትኩረት መስክ አድርጎ እየሰራ ነው የሚሉት የኢትዮጵያ ጤና መድህን ኤጀንሲ ዳይሬክተር ዶክተር መንግስቱ በቀለ በሃገሪቱ የግል ሆስፒታሎች ውስጥ ያለውን የህክምና ዋጋ መናር ለመቆጣጠርና ህብረተሰቡ በተገቢው መንገድ አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ መንግስት የጤና ተቋማትን የማስፋፋት፣ የህክምና ባለሙያዎችን ቁጥር የመጨመር እና የዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎችን ወደሃገር ውስጥ የማስገባት ስራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።

     “ችግሩን ለመፍታት በዋናነት መፍትሄ የሚሆነው ግን ማንኛውም ዜጋ ሲታመም ኪሱ ውስጥ ገንዘብ የመኖርና ያለመኖሩን ጉዳይ ሳይጠብቅ አፋጣኝ የህክምና እርዳታ ማግኘት የሚችልበት የጤና መድህን ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረግ ነው። ይህንን ለማስፈጸም የተቋቋመው የጤና መድህን ኤጀንሲም ወደስራ ገብቷል። ወደፊት ማንኛውም ሰው ከገቢው ላይ በሚያዋጣው ጥቂት ገንዘብ የትኛውም ደረጃ ያለው ህመም ቢገጥመው ያለምንም ቅድመሁኔታ ወደህክምና ተቋማት መጥቶ ጥራት ያለው አገልግሎት ማግኘት የሚችልበት አሰራር እየተዘረጋ ነው። ምናልባት አሁን የሚነሱት የጤና አገልግሎት ዋጋ መናር ችግሮች ያኔ መፍትሄ ያገኙ ይሆናል” ነው ያሉት። ይህ ዘገባ በአፍሪካ ሚዲያ ኢኒሺየቲቭ ድጋፍ የአፍሪካ ስቶሪ ቻሌንጅ ለተባለ አህጉራዊ ውድድር የተዘጋጀ ነው፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት አርብ የበርካታ አረጋውያን እና አዕምሮ ህሙማን መጠለያ የሆነው የመቄዶኒያ የአረጋውያን እና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል በበርካታ ሰዎች ተጥለቅልቋል። የማዕከሉ ተረጂዎችም በቅጥር ግቢው ውስጥ በተዘጋጀላቸው መጠለያ ድንኳን ውስጥ ተቀምጠው ይጨዋወታሉ። ምርኩዞቻቸውን አገጫቸው ላይ ያስደገፉ አዛውንቶች ዝግ ባለ ድምጽ ከጐናቸው ካሉት ጋር ሲነጋገሩ፤ ሌሎች ደግሞ ካርታ ይጫወታሉ። ቀሪዎቹም ከፊት ለፊታቸው የተሰቀለው ቴሌቪዥን ላይ ዓይናቸውን ሰክተው ይመለከታሉ።

ይህንን ከላይ የተገለፀ ትዕይንት የተገነዘብነው በተጠቀሰው ዕለት ኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደር ኢትዮጵያ የምስረታውን አርባኛ ዓመት እና የሰራተኞች የምስጋና በዓልን ከእነዚህ አረጋውያን አና የአዕምሮ ህሙማን ጋር በማዕከሉ ግቢ ውስጥ ለማክበር አቅዶ ወደዚያው ባመራበት ወቅት ነበር። የህፃናት መንደሮቹ ሠራተኞች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ወደ ማዕከሉ መግባታቸውን ተከትሎ በአረጋውያን እና አዕምሮ ህሙማን ማዕከሉ ያሉ ሰዎችን የኋላ ታሪክ (ወድቀው የተገኙበትን፣ ወደ ማዕከሉ ሲመጡ የነበራቸውን ገፅታ፣ ወደ ማዕከሉ ለማምጣት የነበረውን ተግዳሮት ወዘተ) የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም እንዲከታተሉ ተደረገ። በርካቶች እንባና ድምጽ አውጥተው እስከማልቀስ በደረሰ ስሜት ውስጥ ሆነው ይሄንን ዘጋቢ ፊልም ከተመለከቱ በኋላ፣ እንግዶቹ በማዕከሉ የሚረዱ አረጋውያን እና አዕምሮ ህሙማንን እንዲጐበኙ ተደረገ። በዚህ ጊዜም ቀድሞ ካዩት በበለጠ በርካቶች እንባ አውጥተው ሲያለቅሱ ተስተውለዋል።

ኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደር ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት መጠናቀቅ ተከትሎ (እ.ኤ.አ በ1949) በአውስትራሊያዊው ሄርማን ጂሜነር እዚያው አውስትራሊያ ውስጥ ነበር የተቋቋመው። ሲቋቋምም ዓላማውን ያደረገው በጦርነቱ ምክንያት ከቤተሰቦቻቸው የተለያዩ ህፃናት ከቤተሰባቸው ጋር መቀላቀል እና የተበታተኑ ህፃናትን ደግሞ ሰብስቦ ከለላ መስጠትን ነበር። በዚህ መልኩ የተጀመረው ህፃናትን በመንደር የማሰባሰብ ተግባር በቀጣይ በተለያዩ አካባቢዎች በመስፋፋት በ133 ሀገራት ቅርንጫፍ መንደሮችን በመክፈት ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት መሆን የቻለ መንደር ነው። ይህ መንደር በቆይታውም 82ሺ 100 ወላጆቻቸውን በተለያዩ ምክንያቶች ያጡ ችግረኛ ህፃናትን መርዳት ችሏል።

ኤስ ኦ ኤስ በአሁኑ ወቅት ለችግረኛ ህፃናት መንደር በማቋቋም ህፃናቱ በቤተሰብ ስር እንዲጠለሉ ያደርጋል። በአሁኑ ጊዜው እያንዳንዱ የህፃናት መንደር ከሀምሳ በላይ ቤተሰቦች ያሏቸው ሲሆን፤ ህፃናቱም በእነዚህ ቤተሰቦች ስር በመሰባሰብ አንድ ልጅ ከቤተሰብ ማግኘት የሚገባውን ፍቅር፣ እንክብካቤ እና ከለላ ሁሉ እንዲያገኙ ይደረጋል። በእያንዳንዱ ቤተሰብ ስር እስከ 10 የሚደርሱ ሴትና ወንድ ልጆች ይኖራሉ። እነዚህን ህፃናት የሚያሳድጉ እና ቤተሰቡን የሚያስተዳድሩ እናቶች ያሉ ሲሆን፤ እነዚህ እናቶችም የየሀገራቸውን ባህል ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ ቤተሰቡን አስመልክቶ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በቁርጠኝነት የሚወጡ እናቶች መሆን አለባቸው። በተጨማሪም እነዚህ እናቶች ከእነዚህ የህፃናት መንደር ውጪ ቤተሰብ የሌላቸው እና ሙሉ ጊዜያቸውን እና ትኩረታቸውን ለእነዚህ ልጆች የሚሰጡ መሆን አለባቸው።

በኢትዮጵያ የኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደር አገልግሎት የተጀመረው በ1967 ዓ.ም ነበር። በወቅቱ በትግራይ አካባቢ ተከስቶ በነበረው የረሃብ አደጋ በርካታ ህፃናት ከወላጆቻቸው ተለይተው መቅረታቸውን እና ወላጆች በረሃቡ ምክንያት ሲሞቱ ህፃናት ያለ ወላጅ እና አሳዳጊ መቅረታቸውን ተከትሎ ነበር የመጀመሪያው የህፃናት መንደር በመቀሌ የተቋቋመው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም የኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደሮች በተለያዩ ስድስት የሀገራችን ከተሞች የተቋቋሙ ሲሆን፤ በዚህ የአርባ ዓመት ቆይታም በርካታ ህፃናትን መታደግ ችለዋል።

ወደዚህ የህፃናት መንደር የሚገቡ ህፃናት እድሜያቸው ከስድስት ዓመት በታች የሆነ ሲሆኑ፤ እነዚህ ህፃናት ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ቴክኒክና ሙያ አሊያም ወደ ዩኒቨርሲቲ እስከሚገቡ ድረስ በመንደሩ ውስጥ እንዲቆዩ እና ማንኛውም የሚያስፈልጋቸው ነገር እንዲሟላላቸው ይደረጋል። በተለይ ሴት ተማሪዎች ደግሞ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ጭምር እገዛ ይደረግላቸዋል።

በህፃናት መንደሮቹ ውስጥ የቅድመ ትምህርት ቤት ህፃናት ማቆያ እና መዋዕለ ህፃናት የሚገኙ ሲሆን፤ ከእነዚህ ደረጃ በላይ ያሉ ተማሪዎች ደግሞ በየአካባቢው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ይደረጋል። በህፃናት መንደሮቹ ውስጥ ለሚገኙ ህፃናት እና ለሌሎቹ አገልግሎት የሚሰጡ ነርሶችም በየመንደሩ ውስጥ ይገኛሉ።

የኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደር ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ሳህለማርያም አበበ በማዕከሉ በዚያው የመንደሮቹ 40ኛ ዓመት እና የሰራተኞቹ የምስጋና ቀን በሚከበርበት ተገኝተው በዚህ የህፃናት መንደር የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ገልፀውልናል። እንደ አቶ ሳህለማርያም ገለፃ ይህ የህፃናት መንደር በዋናነት ህፃናት በቤተሰብ መንፈስ እንዲኖሩ ማድረግ ነው። “እኛ የምናሳድጋቸው ህፃናት በተለያዩ ምክንያቶች የወላጅ ጥበቃና እንክብካቤ ያጡ ናቸው። ለእነዚህ ህፃናት እኛ እየሰጠናቸው ያለነው ቤተሰብ፣ የሚኖሩበት ምቹ የሆነ ቤት ነው። በተጨማሪም ያጡትን እናት ሰጥተናቸዋል። እንዲሁም እህትና ወንድም ሰጥተናቸዋል። ስለዚህ ህፃናቱ በቤተሰብ ውስጥ ሙሉ ጥበቃ ባለበት ነው የሚኖሩት” ይላሉ አቶ ሳህለማርያም።

የህፃናት መንደሩ ይህን የሰራተኞች የምስጋና ቀን በዓል በዚህ የአረጋውያን እና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ሲያከብር የዘንድሮው የመጀመሪያ ነው። ከዚህ ቀደም በራሱ ጊቢ እና በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ያከበረ ቢሆንም፤ ይህ ለ4ኛ ጊዜ የሚከበር በዓል ግን ከመንደሮቹ ጋር ተመሳሳይ ተግባራትን ከሚፈጽሙ ድርጅቶች ጋር ለማክበር በመወሰኑ እዚህ ማዕከል ውስጥ እንደተከበረ አቶ ሣህለማርያም ገልፀውልናል። በመሆኑም በመንደራቸው ውስጥ የሚገኙ ህፃናት መንደሩ ከሰጣቸው ቤተሰብ እና ወላጅ በተጨማሪ እነዚህ የመቄዶኒያ አረጋውያን ለህፃናቱ አያቶች ይሆናሉ የሚል ሃሳብ አለ።

“እነዚህ ህፃናት መንደራቸው በሚፈጥረው ግንኙነት አያት ያገኛሉ። ይህ ሲሆን ደግሞ፤ ህይወታቸው የበለጠ ይሳካል ማለት ነው። ይሄ ግንኙነት እየተጠናከረ ሲመጣ እኛም ልጆቻችንን እየያዝን እንመጣለን። ልጆቹ በፕሮግራም ወደ ማዕከሉ እየመጡ ጊዜ የሚያሳልፉበት እና ከአረጋውያኑ ልምድ እና ተሞክሮ የሚቀስሙበትን ሁኔታ እናመቻቻለን። አረጋውያኑም አልፎ አልፎ ወደ መንደሮቻችን እየመጡ ዘመድ ብለው የሚጐበኟቸው ቤተሰብ እንዲፈጠር እናደርጋለን” ይላሉ ሥራ አስኪያጁ።

አረጋውያንን መርዳት ማለት ከመመገብ እና ከማልበስም ያለፈ ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዘው የሚመጡ በርካታ ተግዳሮቶችን ማለፍ እንደሚያስፈልግ የገለፁት አቶ ሣህለማርያም፤ በማዕከሉ እየተከናወኑ ያሉት አረጋውያንን የመንከባከብ ተግባራትም እነዚህን ተግዳሮቶች በፅናት በማለፉ ሊደነቅ እንደሚገባው ገልፀዋል።

ኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደር ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከዚህ ማዕከል ጋር በሚያከናውናቸው ተግባራት ትውልዶችን የማገናኘት ስራ እየሰራ እንደሆነም ተገልጿል። እነዚህ አረጋውያን ያለፈው ታሪክ ባለቤት እና ሙሉ መረጃው በእጃቸው ላይ ያለ ሲሆን፤ በመንደሩ ውስጥ የሚያድጉት ህፃናት ደግሞ ቀጣይ ትውልድ በመሆናቸው የአሁኑ ትውልድ እነዚህን ትውልዶች የማገናኘት ሥራ የመስራት ዓላማ እንዳለው ነው አቶ ሣህለማርያም የገለፁልን። በመሆኑም ያለፉት እሴቶች በቀጣዩ ትውልድ ውስጥ እንዲቀጥሉ የማድረግ ስራ ይሰራል። አቶ ሣህለማርያም እንዲህ ይገልፁታል። “የማእከሉ መረጀ እንደሚያመለክተው ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አረጋውያን ናቸው። እነዚህ ሰዎች ሰፊ የታሪክ እውቀት ያላቸው ናቸው። በእኛ እድሜ ያለው ትውልድ የአሁን ትውልድ ሲሆን፤ የምናሳድጋቸው ህፃናት ደግሞ ቀጣይ ትውልድ ናቸው። ስለዚህ እኛ መካከል ላይ ሆነን እነዚህን ሦስት ትውልዶች ለማገናኘት እንሰራለን። ስለዚህ ያለፈው ታሪካችን አይጠፋም። ህፃናቱም እና ወጣቶቹ የአባቶቻቸው ታሪክና እሴት ይዘው ያድጋሉ ማለት ነው” ይላሉ።

ኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ ባዘጋጀው በዚህ በዓል ላይ የመንደሩ ሰራተኞች የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱት የመንደሩ ሰራተኞች ሽልማትን በማበርከት እንዲሁም ቀሪዎቹ ሰራተኞች ላበረከቱት አስተዋፅኦ በማመስገን የተከበረ ሲሆን፤ ለመቄዶኒያ የአረጋውያን እና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከልም፤ የ30 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ፣ የተለያዩ አልባሳት እንዲሁም በህፃናት መንደሩ ቴክኒክ ኮሌጅ የተሰሩ ቁሳቁሶች እና የገንዘብ መሰብሰቢያ ሳጥኖችን በስጦታ አበርክቷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካቶች የሚያዘጋጇቸውን ዝግጅቶች ወደ ማዕከሉ ይዘው በመምጣት ከአረጋውያን እና አዕምሮ ህሙማን ጋር ማክበራቸው እየተለመደ መምጣቱ እንደ ጥሩ ጐን ሊወሰድ ይገባል የሚል ሀሳብ ያላቸው የማዕከሉ አማካሪ ዶክተር ጌታቸው ተድላ፣ ጥቅሙንም አስረድተውናል። እዚህ የሚኖሩ አረጋውያን እና አዕምሮ ህሙማን መታየታቸው በሌሎች ሰዎች ውስጥ “ለካ እንዲህም ሊረዳ ይችላል” የሚል መነሳሳትን እንደሚፈጥርም አማካሪው ገልፀውልናል። “እዚህ ማዕከለ ውስጥ ያሉ ሰዎች ለሀገራችን ትልቅ ነገር የሰሩ መጨረሻ ላይ ግን በየቦዩ ወድቀው የተገኙ ናቸው። ሁሉንም ብናናግራቸው እያንዳንዳቸው አንድ መጽሐፍ ሊወጣቸው የሚችሉ ናቸው። ስለዚህ በህይወት ዘመናቸው ብዙ ያሳለፉ በመሆናቸው በሰው ሲጐበኙ እና ከሰው ጋር ሲነጋገሩ ደስተኞች ናቸው” ይላሉ።

    በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ በማዕከሉ የሚረዱ አረጋውያን እና የአእምሮ ህሙማን በየጊዜው በበርካታ ሰዎች መጐብኘታቸው በሰዎቹ ላይ ሊያመጣ የሚችለው ነፃነትን የመነፈግ ስሜት ሊኖር እንደሚችል ዶክተር ጌታቸው ይገልፃሉ። እንደ እርሳቸው ገለፃ የግለሰቦች ነፃነት አጠያያቂ ቢሆንም ነገር ግን አስገዳጅ ሁኔታም ይኖራል። “ነፃነት ቢኖር ያለ ምንም ጥርጥር ይመረጣል። ነገር ግን እነዚህ በማዕከሉ የሚኖሩ ሰዎች የሚበሉትም የሚጠጡትም ከሚጐበኟቸው ሰዎች በሚገኘው እርዳታ ነው። ስለዚህ እነርሱ ወደዱም ጠሉም ሰዎች ሊጐበኟቸው ይገባል። ነገር ግን ብዙዎቹ ሰው ሲጠይቃቸው እና ሲጐበኛቸው ደስ ሲላቸው ነው የማየው”

በኢትዮጵያ ከሚከናወኑ ውልደቶች መካከል ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆኑት የሚከናወኑት በቤት ውስጥ ነው ይላል በቅርቡ በኢትዮጵያ በእናቶች እና አዲስ የሚወለዱ ህጻናት ላይ ጥናት ያደረገው ኤሞሪ ዩኒቨርስቲ። በቤት ውስጥ በሚወልዱ ሴቶች ላይም በተለያዩ ምክንያቶች የከባድ ጉዳት እና የሞት አደጋዎች ሲያጋጥሙ ይታያሉ። በመሆኑም በሀገሪቱ በየዓመቱ 25ሺህ ያህል እናቶች በቤት ውስጥ ለመውለድ በሚያደርጉት ጥረት ህይወታቸውን ያጣሉ።

ባለፈው ሐሙስ ታህሳስ 2 ቀን 2007 ዓ.ም የጨቅላ ህፃናት ጤናን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ በራዲሰን ብሉ ሆቴል ተካሂዶ ነበር። በዚህ ኮንፈረንስ ላይ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የጤና ባለሞያዎች እና የጨቅላ ህፃናት ጤና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተው ነበር። በፕሮግራሙ ላይ የጨቅላ ህፃናት ጤና በኢትዮጵያ ምን ይመስላል የሚለውን አስመልክቶ መረጃዎች የቀረቡ ሲሆን እኛም የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።

አንዲት ሴት በቤት ውስጥ በምትወልድበት ወቅት ንጽህናውን ያልጠበቀ መሣሪያ፣ ንፁህ ያልሆነ የመውለጃ ቦታ እና የመሳሰሉት ለባክቴሪያ ስለሚያጋልጧት የተወለደው ህፃኑንም ሆነ እናትየዋ ለኢንፌክሽን የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው። በዚህም ሣቢያ በሀገራችን ልክ እንደ እናቶች ሁሉ ህፃናቱም በህይወት የመኖር እድላቸው አነስተኛ ነው። በዚህም መሠረት በቤት ውስጥ ከሚወለዱ 27 ህጻናት መካከል አንዱ ይሞታል። በተያያዘም ከአንድ ሺህ ህፃናት መካከል 77ቱ ከዚህ ንጽህናው ካልጠበቀ ውልደት ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን ያጣሉ።

በየትኛውም ስፍራ ወሊድ ቢከናወንም ከወሊድ ቀን አንስቶ እስከ 48ኛው ቀን ድረስ እናትየዋም ሆነች የተወለደው ህፃን በአስጊ ጊዜ ውስጥ እንደሚገኙ ይገመታል። ያለ ህክምና ባለሞያ እርዳታ በቤት ውስጥ የሚከናወን ውልጃ ደግሞ የበለጠ እናትየዋን እና ህፃኑን ተጋላጭ ያደርጋቸዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ለእናቶች ሞት ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት የደም ግፊት፣ የተራዘመ ምጥ እና የመሳሰሉት ሲሆኑ፣ በተለይ እንደኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ደግሞ የመጀመሪያዎቹ ምክንያቶች ያለ ህክም እና ባለሞያ በቤት ውስጥ በመውለድ ናቸው።

ከእናቶች ሞት በተጨማሪም በቤት ውስጥ የሚወለዱ ህፃናትን ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉ በርካታ ነገሮች አሉ። እነዚህ ምክንያቶችም በምጥ ወቅት ለአየር እጥረት መጋለጥ፣ በእርግዝና ወቅት በማህፀን ውስጥ እያሉ ከጥንቃቄ ማጣት የተነሳ በቂ እድገት ይዞ አለመወለድ፤ ዝቅተኛ ክብደት ይዞ መወለድ እና ለተለያዩ ባክቴሪያ እና ከንፅህና ጉድለት ጋር ለሚመጡ ችግሮች መጋለጥ ይገኙበታል። እነዚህ ምክንያቶች በቀላሉ በጤና ባለሞያዎች ሊቀረፉ እና ህፃናቱም ህይወታቸው እንዲተርፍ ማድረግ ቢቻልም በቤት ውስጥ ወሊድ በመፈፀሙ ብቻ የህፃናቱ ህይወት ያልፋል።

በኢትዮጵያ እድሜያቸው አምስት ዓመት ሳይሞላ ህይወታቸው የሚያልፍ ህጻናት ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም ከእነዚህ 42 በመቶ የሚሆነውን የሚይዘው የጨቅላ ህፃናት ሞት ነው። አንድ ህጻን ጨቅላ ህፃን የሚባለው ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 28ኛ ቀን ያለው ጊዜ ነው። በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ ታዲያ ይህ ህጻን የአተነፋፈስ ፣ የደም ዝውውር እና የመሳሰሉት ሂደቶች በትክክል መስራት አለመስራታቸውን ክትትል እና ጥንቃቄ ማድረግን ይጠይቃል። የ2011ዱ የኢትዮጵያ የስነ - ህዝብ ጤና ቆጠራ ይፋ እንዳደረገው በኢትዮጵያ ከአንድ ሺህ አዲስ የሚወለዱ ጨቅላ ህፃናት መካከል 37ቱ በዚህ የጨቅላ ህፃናት እድሜያቸው ይሞታሉ። በአፍሪካ ደረጃ አዲስ ከሚወለዱ አንድ ሺህ ጨቅላ ህፃናት መካከል በአማካይ 35 ነጥብ 9ኙ በጨቅላነት እድሜያቸው ይሞታሉ። ይህ ቁጥር የሚያሳየው ታዲያ የኢትዮጵያ የጨቅላ ህፃናት ሞት ከአፍሪካ ጋር ሲነፃፀር እንኳን ከፍተኛ መሆኑን ነው።

በዓለማችን ላይ በየዓመቱ 4 ሚሊዮን የሚገመቱ ህፃናቱ በጨቅላነት እድሜያቸው ይህችን ዓለም ይሰናበታሉ። ይህ ማለት ደግሞ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ሆነው ከሚሞቱ ህፃናት 40 በመቶውን ይይዛል። ይህ የጨቅላ ህፃናት ሞት በተጨማሪም 57 በመቶ የሚሆነውን የህፃናት ሞትን የሚይዝ ነው። ከእነዚህ የጨቅላ ህፃናት ሞት ደግሞ 99 በመቶው በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ነው የሚከሰተው። ለጨቅላ ህፃናት ሞት የተለያዩ ምክንያቶች የሚቀርቡ ቢሆንም፤ ዋናው እና አሳሳቢው ግን በቤት ውስጥ መወለዳቸው ነው። ለዚህ ማሳያ የሚሆነውም ከግማሽ በላይ የሚሆነው የጨቅላ ህፃናት ሞት የሚከሰተው በቤት ውስጥ መሆኑ ነው።

ይህን የጨቅላ ህፃናት ሞት ለመቀነስ እያንዳንዱ ሀገር የየራሱን እቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በተለይ መገባደጃውን እ.ኤ.አ. 2015 ያደረገው የምዕተ ዓመቱ የልማት ግብ ደግሞ በሁሉም ሀገራት ላይ ከፍተኛ ኃላፊነት ጥሎባቸዋል። ይኸውም የጨቅላ ህጻናትን ሞት ቀጣይነት ባለው መልኩ መቀነስ ሳይቻል ህፃናት በዚህ ዓለም ላይ እንዲኖሩ ማድረግ አይቻልም በሚለው መርህ ሁሉም ሀገራት የምእተ አመቱ አጀንዳ እንዲያደርጉት ተገደዋል። ሁሉም ሀገራት እስከ 2015 እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን ሞት በአንድ ሶስተኛ እንዲሁም የጨቅላ ህፃናት ሞትን ቢያንስ 50 በመቶ መቀነስ እንዳለባቸው የጋራ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ኢትዮጵያም ልክ እንደሌሎቹ ሀገራት ይህን ከፍተኛ የሆነ የጨቅላ ህፃናት ሞት ለመቀነስ የሚያግዟትን ስራዎች እየሰራች መሆኗን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። በህፃናት ሞት ላይ በተሰሩ የተለያዩ ስራዎች መቀነስ እየተሰተዋለ የመጣ ሲሆን፤ በጨቅላ ህፃናት ሞት ላይ ግን አሁንም ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግ እየተገለፀ ይገኛል። የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ ከምንም በላይ ህፃናቱ እንደተወለዱ በቂ የሆነ እንክብካቤ እንዲያገኙ የሚያግዟቸውን ጥንቃቄዎች ማድረግ እንደሚያስፈልግ ባለሞያዎች ይናገራሉ። ከእነዚህ ጥንቃቄዎቸ መካከል ደግሞ አንዱ የጨቅላ ህፃናት ማቆያ ዩኒት (Neonatal Incentive Care unit) ነው።

ይህ የጨቅላ ህፃናት ማቆያ ዩኒት ልዩ የጤና ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ጨቅላ ህፃናት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና በሰለጠኑ የጤና ባለሞያዎች በቅንጅት ክትትል የሚደረግበት ዩኒት ነው። በዚህ ዩኒት ህፃኑ አስፈላጊው ክትትል የሚደረግለት ሲሆን፤ ስለህጻኑ የጤንነት ሁኔታም ሆነ ሌላ መረጃዎች በዚህ ዩኒት ይከናወናሉ። ህፃኑ ባለበት የጤና ችግር መሠረትም አስፈላጊው ነገር ሁሉ ይደረግለታል።

ይህ የጨቅላ ህፃናት ማቆያ ዩኒት በሀገራችን ከተተገበራቸው ሆስፒታሎች መካከል ይርጋዓለም ሆስፒታል፣ አዲግራት ሆስፒታል እና አርባ ምንጭ ሆስፒታልም በጥሩ ተሞክሮዎቻቸው ተመርጠው ይህን የጨቅላ ህጻናት ማቆያ ዩኒት በመጠቀማቸው በጨቅላ ህፃናት ሞት ላይ ያመጡትን ለውጥ ይፋ አድርገዋል። ይህ በጨቅላ ህፃናት ማቆያ ዩኒት ቪ ኤስ ኦ በተባለው የበጎ አድራጎት ድርጅት አማካይነት እንደተቋቋመ እና በጎ ፈቃደኞችም የራሳቸውን አስተዋፅኦ እንዳደረጉ ተገልጿል።

የአዲግራት ሆስፒታል ይህን የጨቅላ ህፃናት መቆያ ዩኒት ለመጠቀም የሚችሉ ነርሶችን በማሰልጠን፣ የህፃናት፣ የእናቶች እና የነርሶችን መቆያ ክፍሎች በመለያየት እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ መሣሪያዎችን በማዘጋጀት ወደዚህ ሥራ እንደተገባ ተገልጿል። ይህን መስፈርት አሟልቶ ሥራውን በመጀመሩም ይህ ዩኒት ከመጠቀሙ በፊት የነበረውን 29 በመቶ የጨቅላ ህፃናት ሞት በሁለት ወራት ውስጥ በ14 በመቶ ቀንሷል። ከዚህ በተጨማሪም በመጀመሪያዎቹ 24 ሰዓታት ውስጥ የሚሞቱ ጨቅላ ህፃናት ቁጥር ከ1 ነጥብ 1 በመቶ ወደ ዜሮ ነጥብ 1 በመቶ ሊቀንስ ችሏል።

ይህ ሆስፒታል ይህን ዩኒት በመጠቀሙ ካገኘው የቁጥር ለውጥ በተጨማሪም የጨቅላ ህፃናት ምዝገባ እና መረጃ አያያዝ መሻሻል አሳይቷል። የጤና ሰራተኞቹ ብቃት፣ ተወዳዳሪነት እና ተነሳሽነት በአበረታች መልኩ ለውጥ ማሳየቱ የተነገረ ሲሆን፤ የታካሚዎቹ እርካታም መገኘቱ ተገልጿል።

ከጨቅላ ህፃናት ሞት 40 በመቶ የሚሆነው የሚከሰተው ገና እናትየዋ በምጥ ላይ እያለች እና ከተወለዱም በዚያው በተወለዱበት ቀን ነው የሚለው የተባበሩት መንግሥታት ህፃናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ)፣ ለእነዚህ ጨቅላ ህፃናት ሞትም ከ80 በመቶ በላይ ምክንያት የሚሆኑት ሶስት ችግሮች መሆናቸውን ይገልጻል። እነዚህ ችግሮችም ህፃኑ የመወለጃ ጊዜው ሳይደርስ በመወለዱ የሚፈጠሩ ውስብስብ ችግሮች፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ምጥ በተራዘመ ቁጥር ህፃኑን የሚገጥመው የመተንፈስ ችግር እንዲሁም ከንፅህና ጉድለት እና ከተለያዩ ችግሮች ጋር በተያያዘ የሚከሰት የኢንፌክሽን ችግር ናቸው።

    ኢትዮጵያ የተቀመጠውን የምእተ አመቱን የልማት ግብ ቀድማ ከአምስት ዓመት በታች ህፃናትን ሞት በአንድ ሶስተኛ መቀነስ በመቻሏ አበረታች ውጤት እያሳየች መሆኗን ያወደሱት የዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ጤና ተጠሪ ዶክተር ማኩራ ኦላሬ፤ በጨቅላ ህፃናት ሞት ላይ ግን ብዙ መስራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የጨቅላ ህፃናት ሞት ከሚታይባቸው አስር ሀገራት አንዷ ናት ያሉት ተጠሪዋ፣ በየዓመቱ በኢትዮጵያ 84ሺህ አዲስ የተወለዱ ህፃናት እንደሚሞቱ ተናግረዋል። ከእነዚህ ጨቅላ ህፃናት መካከል ደግሞ 29ሺህዎቹ በተወለዱበት ቀን ይሞታሉ። ይህ ሲሰላ ደግሞ በየቀኑ 80 አዲስ የሚወለዱ ህፃናት ይሞታሉ ማለት ነው።

     ዓለማችን በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የወጣቶቿ ቁጥር በ2014 ዓ.ም 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ደርሷል። ይህ ማለት ከዓለም ህዝብ 18 በመቶው እድሜው ከ15  እስከ 24 ዓመት ክልል ውስጥ የሚገኝ ወጣት ነው። በማደግ ላይ ካሉ ሀገራት ህዝብ መካከልም 88 በመቶዎቹ በዚህ የወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው” ሲል ስቴት ኮቭ ወርልድ ፖፑሌሽን በ2014 ሪፖርቱ አመልክቷል።

ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው የአለማችን ወጣቶች ታዲያ በአሁኑ ወቅት ትኩረት ከማግኘት ይልቅ በሌሎች ተሸፍነው እንደሚገኙ ነው የተገለፀው። በመሆኑም እነዚህ ወጣቶች ይልቁንም ለተፈጠረው የሀብት እጥረት እንደ ምክንያት እየተቆጠረ ይገኛሉ። በርካታ ሀገራት ወጣቶችን በፖሊሲያቸው፣ በህግ አወቃቀራቸው እና በውሳኔ ሰጪነት ውስጥ እያሳተፏቸው አይደለም። እስከ 60 በመቶ የሚሆኑት በታዳጊ ሀገራት ያሉ ወጣቶች ትምህርት ቤት የማይሄዱ፣ በመደበኛ ሥራ ላይ ያልተሰማሩ ነገር ግን መደበኛ ባልሆኑ ስራዎች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። ከ500 ሚሊዮን በላይ ወጣቶችም የቀን ገቢያቸው ከሁለት ዶላር በታች የሆነ እና ኑሮን ለመቋቋም ብርቱ ጥረት እያደረጉ የሚገኙ ናቸው። ለእነዚህ ወጣቶች ትኩረት ካለመስጠት የተነሳም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣቶች ያሉባቸው ታዳጊ ሀገራት ከዓለማችን ደሃ ሀገራት መካከል ቀዳሚ ተጠቃሾች ናቸው።

በዚህ የወጣትነት የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ዜጎች በየሀገራቸው ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማድረግ ባለመቻላቸው ከሁሉም ነገር የተገለሉ በመሆናቸው ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል እኩል ያሉትን ነገሮች መጠቀም አልቻሉም። በተለይ ይህ የወጣትነት የእድሜ ክልል አንድ ሰው ወደ ስነ-ተዋልዶ የሚገባበት፣ የወሲባዊ ግንኙነት ስሜት የበለጠ የሚዳብርበት እድሜ እንደመሆኑ በስነ-ተዋልዶ ጤና ዙሪያ ያላቸው እውቀት አነስተኛ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት የስነ-ህዝብ ልማት አስቀምጧል። በተለይ ግሎባላይዜሽን፣ ስልጣኔ እና እየተቀየረ የመጣው የሰዎች የአኗኗር ዘይቤ ወጣቶች በስነ-ተዋልዶ ጤና ላይ ሰፊ እውቀት ከማጣታቸው ጋር ተደማምሮ ወጣቶች ከፍተኛ ስጋት ከፊት ለፊታቸው እንዲደቀን አድርጓቸዋል ተብሏል።

በወጣቶች ላይ ካንዣበቡት የስነ-ተዋልዶ ጤና ችግሮችም ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ ያልተፈለገ እርግዝና፣ ጥንቃቄ የጎደለው ውርጃ፣ ኤች አይ ቪ ኤድስ እና የአባላዘር በሽታ የሚጠቀሱ ናቸው። የአባላዘር በሽታን በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት እንደገለፀው በየዓመቱ 340 ሚሊዮን አዲስ የአባላዘር በሽታ ተጠቂዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥም አንድ ሶስተኛው እድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች ናቸው። በየዓመቱ በኤች አይ ቪ ኤድስ አዲስ ከሚያዙት ዜጎች መካከልም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ15 እስከ 24 ዓመት ያሉ ወጣቶች ናቸው።

በሚገርም ሁኔታ ደግሞ ተመርምረው ራሳቸውን ያወቁት 10 በመቶ ወንዶች እና 15 በመቶዎቹ ሴቶች ብቻ ናቸው። የዓለማችን ከአንድ ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ወጣቶች ወደ መራቢያ እድሜ እየደረሱ መሆኑን የገለፀው ሪፖርቱ፤ ከእነዚህ ወጣቶች መካከል ታዲያ ያለእድሜያቸው የልጅ እናት እንዲሆኑ የሚደረጉ በርካቶች መሆናቸውን ይፋ አድርጓል። በዓለማችን ላይ ስምንት ሚሊዮን 50ሺ የሚሆኑ ሴቶች እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች ሆኖ አርግዘው ይወልዳሉ። እንደ ሪፖርቱ በታዳጊ ሀገራት በሚገኙ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ከሆኑ ሴቶች 19 በመቶዎቹ በዚህ እድሜያቸው ያረግዛሉ።

 

 

እነዚህ ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት በሚሄዱበት እድሜያቸው አርግዘው በመውለዳቸው ያለ እድሜያቸው ኃላፊነት ይጣልባቸዋል። ባልጠነከረ ሰውነታቸው ፀንሰው ከመውለድ በተጨማሪም ከትምህርት ገበታቸው ላይ መቅረት፣ በቤት ውስጥ በተለያዩ የጉልበት ሥራዎች ላይ መሰማራት እንዲሁም ከእድሜያቸው ለጋነት እና ተስፋ ከመቁረጥ የተነሳ በሌሎች ተፅዕኖ ስር መዋል እና ስለራሳቸው መወሰን አለመቻል ያጋጥሟቸዋል። የዓለማችን ዘጠና አምስት በመቶ ውልደት የሚከናወነው በታዳጊ ሀገራት እንደመሆኑ ይህን ያህል ወጣት ሴቶች በዚህ አይነቱ ሂደት ውስጥ አልፈው ተስፋቸው እንደሟሸሸ መገመት ይቻላል።

በሀገራችን ኢትዮጵያ ከሚከናወኑ በርካታ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አንዱ የሆነው ያለ እድሜ ጋብቻም የአለም ወጣቶች የሚጋሩት ችግር እንደሆነ ተገልጿል። ልክ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገራት ወጣቶች ታዲያ ይህ ያለ እድሜ ጋብቻ እጅጉን እንደሚያሰጋቸው ተገልጿል። በታዳጊ ሀገራት ከሚገኙ ዘጠኝ ወጣት ሴቶች መካከል አንዷ እድሜዋ 15 አመት ከመሙላቱ በፊት ትዳር ትመሰርታለች። በአሁኑ ወቅት 50 ሚሊዮን የሚሆኑ ወጣት ሴቶች ያለ እድሜያቸው ሊዳሩ ይችላሉ ተብለው በስጋት ቀጠና ውስጥ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በለጋ እድሜያቸው ወደ ልጅ እናትነት የመሸጋገር አደጋ እንደተጋረጠባቸው የገለፀው የተባበሩት መንግሥታት፤ በዚህም የወጣቶቹ የወጣትነት እና የጎልማሳነት እድሜ መለያ እንደሌለው ያትታል። ከእነዚህ የወጣትነት እርግዝና ጋር በተያያዘ የሚነሳው ደግሞ ጥንቃቄ የጎደለው ውርጃ ነው። በዓለም ላይ ከሚከሰቱት ጥንቃቄ የጎደላቸው ውርጃዎች መካከል 44 በመቶዎቹ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የሚከናወኑ ናቸው። በዓለማችን ላይ በየዓመቱ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚሆኑ ጥንቃቄ የጎደላቸው ውርጃዎች በወጣት ሴቶች ይፈፀማሉ።

ጥንቃቄ የጎደለው ውርጃን ለመፈፀም የሚወስኑትም ወጣት ሴቶች ስለስነ-ተዋልዶ ጤና በአስፈላጊው ቦታ አስፈላጊ ውርጃ ማግኘት ባለመቻላቸው አንዱ ምክንያት ነው። በተጨማሪም ጥንቃቄ የተሞላበት መረጃ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሞያዎች እና የጤና ተቋማት አለመሟላት፣ በጥንቃቄ ውርጃ ለመፈፀም የሚያስፈልጉ የገንዘብ እና የመሳሰሉት ድጋፎች እጥረት እንዲሁም እርግዝናው እንዳይከሰት አስቀድሞ ለመከራከል የሚረዳ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ለማህበረሰቡ አለመለመድ እንደ ምክንያት የተቀመጡ ናቸው።

በየዓመቱ ከዓለማችን ህዝብ መካከል 340 ሚሊዮን ሰዎች አዲስ በአባላዘር በሽታ ይያዛሉ። እነዚህ ሰዎች ደግሞ እድሜያቸው ከ15 ዓመት እስከ 24 ዓመት በሆናቸው ወጣቶች ላይ ነው። በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ላይ 2 ሚሊዮን እድሜያቸው ከ15 እስከ 19 ዓመት የሆናቸው ወጣቶች ከኤች አይቪ ጋር የሚኖሩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 780 ሺዎቹ ሴት ወጣቶች ናቸው።

እነዚህ ሴት ወጣቶች ከባህል፣ በፆታዊ እናበተለያዩ ማህበራዊ ምክንያቶች የተነሳ ከወንዶች ይልቅ በከፍተኛ ደረጃ ለአባላዘር በሽታ የተጋለጡ ናቸው። ነገር ግን ይህን የአባላዘር በሽታ ወሲብን በማዘግየት፣ ህክምና በማድረግ እና በሌሎችም መንገዶች መከላከል እንደሚቻል ግንዛቤው ያላቸው በጣም ጥቂት ሴቶች ብቻ ናቸው።

ያለ እድሜ ጋብቻም ሆነ ጥንቃቄ የጎደለው ውርጃ ዞሮ ዞሮ የእናቶች ሞትን በከፍተኛ ደረጃ እንዲከሰት ማድረጉ አይቀርም። አንዲት ሴት በለጋነት እድሜዋ ጋብቻ ፈፅማ ልጅ ስትወልድ በሚፈጠረው የሰውነት አለመጠንከር፣ አነስተኛ ክብደት ያለው ልጅ መውለድ እንዲሁም ረጅም ጊዜ የሚወስድ ምጥ ምክንያት ሴቷ ለሞት የምትዳረግበት አጋጣሚ ከፍተኛ ነው። በዓለማችን ላይ በየዓመቱ 70ሺ ወጣት ሴቶች በወሊድ ወቅት በሚፈጠር ውስብስብ ችግር ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ። እነዚህ ወጣት ሴቶች ታዲያ ወደ ትምህርት ቤት በመሄጃ፣ ወደ ሥራ አለም በመግቢያ እድሜያቸው ህይወታቸው ይቀጠፋል።

ይህ ሴቷ ያለ እድሜዋ የልጅ እናት ለመሆን በምትጥርበት ወቅት በአንዲት ወጣት ሴት ላይ የሚደርሰው ችግር ጉዳቱ በእርሷ ብቻ አያበቃም። ጉዳቱ ለሚወለደው ህጻን፣ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ እና ሀገርም ጭምር ነው። ከእነዚህ ወጣት ሴቶች ከሚወለዱ ህጻናት መካከል 1 ቢሊዮን የሚሆኑት አንድ ዓመት ሳይሞላቸው ህይወታቸው ያልፋል።

ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ የሚገኙት መረጃዎች ውስን ቢሆኑም ልክ እንደ ሌሎች ታዳጊ ሀገራት ሁሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በችግሮች የተተበተቡ ናቸው። ኤች አይ ቪን የተመለከትን እንደሆነ ከአራት ኢትዮጵያውያን ወጣት ሴቶች አንዷ እንዲሁም ከአስር ወጣት ወንድ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ስለ ኤች አይ ቪ ምንነት በቂ የሆነ ግንዛቤም ሆነ ኤች አይ ቪን መከላከል እንደሚቻል አያወቅም። ያለ እድሜ ጋብቻ ከፍተኛ እንደሆነ በሚነገርባት ሀገራችን ካሉ ወጣት ሴቶች መካከል 41 በመቶዎቹ እድሜያቸው 18 ዓመት ከመሙላቱ በፊት ትዳር የመሰረቱ ሆነው ተገኝተዋል።

በኢትዮጵያም ሆነ በአንዳንድ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት በተለይ ሴት ወጣቶችን በለጋነት እድሜያቸው ትዳር እንዲመሰርቱ ለማድረጋቸው ወላጆችም ሆኑ ማህበረሰቡ የሚያቀርቧቸው ምክንያቶች አሉ። ከእነዚህ ምክንያቶች መካከልም ወላጆች በህይወት እያሉ እና በጠንካራ እድሜያቸው የልጆቻቸውን ወግ ማዕረግ ማየት መፈለጋቸው፤ ከጥሎሽ በሚገኘው ገንዘብ ኑሯቸውን ለማሻሻል፣ በሁለቱ ቤተሰብ መካከል ግንኑነት ለመፍጠር፣ ሴቷ ጨዋነቷን እንደጠበቀች ትዳር በመመስረቷ ከጨዋ ቤተሰብ መገኘቷን ለማስመስከር እንዲሁም ሴቷ በማህበረሰቡ በተደነገገው የትዳር እድሜ ማግባት ስላለባት የሚሉት ይገኙበታል።   

Page 1 of 4

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us