ዓለማችን ከ50 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች መጠለያ ሆናለች

Wednesday, 25 June 2014 13:36

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ቀን ባለፈው አርብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከብሯል። እለቱ “አንድ ቤተሰብ በጦርነት ተበተነ ማለት ብዙ ነገር ማለት ነው” (One Family Torn Apart by War is Too Many) በሚል መሪ ቃል ነበር የተከበረው። በዕለቱ በርካታ ዜጎች ከቀያቸው ተነጥለው በስደት ሀገር መኖራቸው ብቻ ሳይሆን የስደተኞች ጉዳይ ምን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ተገልጿል። ኢትዮጵያ በተለይ ከጎረቤት ሀገራት የሚመጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደቡብ ሱዳናውያን፣ ሶማሊያውያን እና ኤርትራውያን ስደተኞችን በማስተናገድ ትታወቃለች።

በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ላይ 16ነጥብ7 ሚሊዮን ስደተኞች ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪ 33 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለው ይኖራሉ። በአጠቃላይ 51 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው እና በስደት ዓለም የሚኖሩ ሲሆን፣ ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ሲመዘገቡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ይህ የመጀመሪያ ነው ሲል የተባበሩት መንግስታት የስተደኞች ኤጀንሲ ገልጿል።

በ2012 ዓ.ም የነበረውን የስደተኞች እና ከቤታቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ቁጥር ስንመለከት ደግሞ 42 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎች ነበሩ። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 6ነጥብ3 ሚሊዮን የሚሆኑት ስደተኞች ከአምስት ዓመት በላይ ከሀገራቸው ውጭ ተሰደው የኖሩ ናቸው።

እስከ አሁን ባለው መረጃ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎቿ ተሰደዋል ተብላ የተቀመጠችው ሶሪያ ናት። በሶሪያ ግጭት ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ ዘጠኝ ሚሊዮን ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ይህም ሀገሪቱ በስደተኞች ቁጥር ከዓለም ቀዳሚውን ደረጃ እንድትይዝ አድርጓታል። ከእነዚህ ከቤት ንብረታቸው ከተፈናቀሉ ሶሪያውያን መካከልም 3 ሚሊዮን ያህሉ ሀገራቸውን ጥለው የወጡ ሲሆን፣ 2ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆኑት በቱርክ፣ ዮርዳኖስ፣ ሊባኖስ እና ኢራቅ በሚገኙ የስደተኛ ካምፕ ውስጥ ተጠልለዋል ይላል የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ።

ኢትዮጵያም በአቅሟ በአሁኑ ወቅት 565ሺ ስተደኞችን በማስተናገድ ላይ ትገኛለች። ከእነዚህ ስደተኞች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ደቡብ ሱዳናውያን ሲሆኑ፤ በደቡብ ሱዳን ግጭት ከተነሳበት እ.ኤ.አ. ህዳር 2013 ጀምሮ 150ሺ ደቡብ ሱዳናውያን ወደ ኢትዮጵያ ጎርፈው በተለያዩ ስደተኞች መጠለያ ካምፖች ተጠልለዋል። ኢትዮጵያ ካላት አቀማመጥ የተነሳ ከደቡብ ሱዳናውያን በተጨማሪም ለኤርትራ እና ለሶማሊያ ስደተኞች መጠለያ ሆናለች። ከኢትዮጵያ ስደተኞች እና ስደት ተመላሾች ጉዳይ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 95ሺ 616 ኤርትራውያን ስደተኞች በትግራይ እና በአፋር አካባቢ በሚገኙ የስደተኛ መጠለያ ካምፕ ውስጥ ይገኛሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለ242ሺ 422 ሶማሊያውያን እና ለ36ሺ 796 ሱዳናውያን ስደተኞች መጠጊያ ሆና ታገለግላለች።

የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ቁጥር በግልጽ የሚታወቀው ሀገራቸውን ለቀው የሚሰደዱት ብቻ ቢሆንም አሁንም ግን ከሀገሪቱ የሚወጡ መረጃዎች በርካታ ስደኞች እየተፈጠሩ መሆናቸውን ይገልፃሉ። በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግስታት ተልእኮን ጠቅሶ የተባበሩት መንግስታት እንደዘገበው ከሆነ በደቡብ ሱዳን 96ሺ ዜጎች መጠለያ ያስፈልጋቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 30ሺ የሚሆኑት በዋና ከተማዋ ጁባ የሚገኙ ናቸው። 38ሺ የሚሆኑት በቤንቲዩ፣ 18 ሺህ ሰዎቹ ደግሞ በማላካይ አካባቢ የሚገኙ እንደሆኑ እየተገለፀ ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ ዜጎቻቸው ለስደት ይዳረጋሉ ተብለው ከተቀመጡት ሀገራት መካከል አፍጋኒስታን አንዷ ስትሆን 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎቿ ተሰደዋል። ሶሪያ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳንም ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል ዜጎቻቸው ተሰደዋል። በተቃራኒው ዜጎች በከፍተኛ ደረጃ የሚሰደዱባቸው (ተቀባይ) ሀገራት የተባሉት ፓኪስታን 1ነጥብ 6 ሚሊዮን ስደተኞችን በማስተናገድ ቀዳሚዋ ስትሆን፣ ኢራን፣ ሊባኖስ እና የመሳሰሉት ሀገራት ይከተላሉ።

ዓለማችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየገጠሟት ባሉት የተለያ ግጭቶች ምክንያት የስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እያሻቀበ መምጣቱን ያመለክታል። ባለፈው ዓመት በዓለማችን ላይ 8 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ስደተኞች ብቻ ነበሩ። ይህ ቁጥር ታዲያ ዘንድሮ በእጥፍ አድጎ 16 ነጥብ 7 ሚሊዮን ደርሷል። ለዚህ ቁጥር ያለገደብ ማሻቀብ ደግሞ የተባበሩት መንግስታት የተለያዩ ምክንያቶችን አስቀምጧል።

እንደ ቀዳሚ ምክንያት የተቀመጠው ግጭቶች የሚፈጁት ጊዜ እንደዋና ምክንያት ተቀምጧል። በአሁኑ ወቅት 21 ያህል ሀገራት በግጭት ውስጥ መሆናቸውን የገለፀው መረጃው እነዚህ ግጭቶች ግልጽነት የጎደላቸው እና ጊዜያቸውን እያራዘሙ የበርካታ ዜጎች ህይወት እያበላሹ ይገኛሉ ብሏል። ጦርነቶቹ ለረጅም ጊዜ በመካሄዳቸውም ዜጎች ያላቸውን ነገር ትተው ተስፋ በመቁረጥ ስደትን እንደ አማራጭ መውሰዳቸው የስደተኞች ቁጥር እንዲያሻቅብ ምክንያት ሆኗል።

ሌላው እንደምክንያት የተቀመጠው ደግሞ ግጭቶች እየተከሰቱ ያሉት በተወሰኑ ቡድኖች፣ በሃይማኖት አክራሪዎችና በባንዳዎች መካከል በመሆኑ ሰዎች በሀገራቸው ውስጥ ስፍራ በማጣታቸው (Shrinking of Humanitarian Space) ነው። በዚህ ሳቢያ ግጭት የሚፈጥሩት አካላት የራሳቸው የሆነ ህግ ብቻ እንዲከበር በማድረግ በሰው ልጅ ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራሉ። ይህን ተከትሎም ሰዎች ሀገራቸውን ትተው ወደ ሌላ ሀገር ይሰደዳሉ። ከዚህ በተጨማሪም እነዚህ ግጭት ፈጣሪዎች በየሀገራቱ ባሉ የስደተኞች ካምፖችን ጭምር ዒላማ በማድረግ ዜጎች ወደ ሌላ ሀገር እንዲሰደዱ በማድረግ የስደተኞችን ቁጥር ከፍ ያደርገዋል እንደ ድርጅቱ ገለፃ።

እንደመጨረሻ ምክንያት የተቀመጠው ደግሞ የሀገራት የጥገኝነት አሰጣጥ ነው። ሀገራት ወደ ሌላ ሀገር ለሚገቡ ስደተኞች በተለያየ ደረጃ ፈቃድ መስጠታቸው የስደተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲያሻቅብ አድርጓል ይላል ዘገባው።

ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ዜጎች ከቀያቸው እና ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በጎረቤት ሀገራት ሲኖሩ ንብረታቸው ተበትኖ፣ ልጆቻቸው ከትምህርት ገበታ ርቀው እና ህይወታቸው ተመሰቃቅሎ ነው የሚኖሩት። እነዚህን ስደተኞች ለማስተናገድ ፈቃደኛ የሆኑ ሀገራት የመኖራቸውን ያህል ስደተኞቹ አስፈላጊው ነገር ሲሟላላቸው አይታይም። የስደተኞቹ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ የሚመለከታቸው አካላት በየጊዜው የሚያደርጉት ድጋፍ እና እርዳታ እንኳን አይዳረስም።

በኢትዮጵያ ለሚገኙ 550ሺህ የጎረቤት ሀገራት ስደተኞች እርዳታ እንደሚያደርግ የገለፀው የአለም ምግብ ፕሮግራምን ለአብነት ብንመለከት ለስደተኞች የተለያዩ አትክልቶች፣ ኃይል ሰጪ ብስኩቶች እና ስኳር እንዲሁም ዘይት እና ጨው እየተሰጠ ቢሆንም በቀላሉ ለማዳረስ ግን አልተቻለም። አብዛኛዎቹ ስተደኞች ወደ ኢትዮጵያ የሚሰደዱት በረሀብ ምክንያትም ጭምር እንደሆነ ነው ድርጅቱ የገለፀው። በየስደተኛ መጠለያው ያሉትን ስደተኞች መመገብ አቅቶ ባለበት በአሁኑ ወቅትም በርካታ ዜጎች ሀገራቸውን ለቀው ወደዚህ ስደተኛነት ጎራ እየተቀላቀሉ ይገኛሉ።

ስደተኞችን በማስተናገዱ ረገድ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የአፍሪካ ሀገራትን ጨምሮ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ ይላል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን። ይህ ማለት 86 በመቶው የአለም ስደተኞች በእነዚህ ታዳጊ ሀገራት ይገኛሉ። ከሰሀራ በታች ያሉ ሀገራት ደግሞ የአለምን ስተደኞች አንድ አራተኛ (ሩብ ያህሉን) ያስተናግዳሉ፤ እንደ ኮሚሽኑ ዘገባ። ይህ ሁኔታ ደግሞ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ተጨማሪ ሸክምን በመፍጠር ተያይዘው እንዲወድቁ እያደረጋቸው ነው።

     በስደተኛ መጠለያ ካምፕ ውስጥ ያሉ በተለይ ህፃናት ለምግብ እጥረት፣ ለተቅማጥ በሽታ፣ ለወባ እና ለመሳሰሉት አሰቃቂ በሽታዎች እየተዳረጉ እንደሆነም በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
2234 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 714 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us